የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከመስከረም 28 - ጥቅምት 4

3ኛ ትምህርት

Oct 8–14




የሰው ልጅን ተፈጥሮ መረዳት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዘፍ. 1፡24-27፤ ዘፍ. 2፡7፣19፤ ማቴ. 10፡28፤ መክ. 12፡1-7፤ 1 ነገ. 2፡10፤ 1 ነገ. 22፡40።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አፈር ወስዶ ሰውን አበጀው፤ በአፍንጫውም የህይወት እስትንፋስ እፍ አለበት፤ ሰውም ህያው ነፍስ ሆነ፡፡” (ዘፍ. 2፡7)

የ እግዚአብሔር ቃል “በእርግጥ ትሞታለህ” (ዘፍ. 2፡16-17) በሚለው ሀሳብ እና በሰይጣን ማሳሳቻ የተስፋ ቃል “መሞት እንኳን አትሞቱም” (ዘፍ. 3፡14) በሚሉት ቃላቶች መካከል ያለው ውጥረት በኤደን ገነት የአትክልት ስፍራ ብቻ ተወስኖ የቀረ አይደለም። በዓለም ታሪክ ሁሉ ውስጥ ዘልቆ የተስተጋባ ጉዳይ ነው።

አያሌ ሰዎች የሰይጣንን ቃላት ከእግዚአብሔር ቃላት ጋር ለማጣጣም ጥረት ያደርጋሉ። በነዚህ ሰዎች አመለካከት “በእርግጥ ትሞታለህ” የሚያመለክተው ጠፊ የሆነውን አካል ብቻ ነው “መሞትን እንኳን አትሞቱም” የሚለው የተስፋ ቃል ደግሞ የማይሞተውን ነፍስ ወይም መንፈስ የሚገልጽ ነው። ነገር ግን ይህ አቀራረብ የሚሠራ አይደለም። ለምሳሌ ሁለት የሚጣረሱ የእግዚአብሔር ቃላት እና የሰይጣን ቃላት ሊጣጣሙ ይችላሉን? ከአካላዊው ሞት የሚድን ነፍስ ወይንም መንፈስ የሚባል ነገርስ አለን? ለእነዚሀ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት አያሌ የፍልስፍና ብሎም ሳይንሳዊ ጥረቶች ተደርገዋል። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት እንዳደረገ ክርስትያን እኛን ሙሉ በሙሉ የሚያውቀን (መዝ. 139) እኛን የፈጠረን ኃያሉ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለዚህ ለነዚህ ወሳኝ ጥያቄዎች ምላሽ ልናገኝ የምንችለው እርሱ ለኛ በሰጠው ቃል በኩል ብቻ ነው።

በዚህ ሳምንት ብሉይ ኪዳን የሰው ልጅ ተፈጥሮን እንዴት አድርጎ እንደገለጸው እና የሰው ልጅ ሲሞት ይሆናል ብሎ የገለፀውን እናያለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለጥቅምት 5 ሰንበት ይዘጋጁ።

መስከረም 29
Oct 09

“ህያው ፍጡር”


ዘፍ. 1፡24-27 እና ዘፍ. 2፡7፣19ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እንስሳትንና የሰው ልጅን ሲፈጥር የሚያመሳስላቸውና የሚያለያያቸውን ምን ነገር ተገነዘባችሁ? ዘፍጥረት 2፡7 ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ ምን ይነግረናል?



ዘፍጥረት እንደሚነግረን በፍጥረት ሳምንት በስድስተኛው ቀን ላይ አምላክ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱ እንስሳትንንና የሰው ልጆችን ወይንም ጥንዶቹን ፈጠሯል (ዘፍ. 1፡24-27)። “እግዚአብሔር አምላክ የዱር አራዊትንና የሰማይ ወፎችን ከምድር ሠርቶ ነበር” ይለናል (ዘፍ. 2፡19)። “እግዚአብሔር አምላክም ከምድር አፈር ወስዶ ሰውን አበጀው”(ዘፍ. 2፡7)።

ምንም እንኳን እንስሳት እና የሰው ልጆች ሁለቱም በተመሳሳይ መንገድ “ከምድር አፈር” ቢሰሩም የሰው ልጅ አፈጣጠር በሁለት ዋነኛ መንገዶች ለየት ይላል። የመጀመሪያው እግዚአብሔር የሰውን ልጅ አካል ቀርጾ አውጥቶ ያበጀው ራሱ ሲሆን “በአፍንጫውም የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት ሰውም ህያው ነፍስ ሆነ” (ዘፍ. 2፡7)። ሕያው ከመሆኑ አስቀድሞ አካል ያለው ፍጡር ነበር። ሁለተኛው እግዚአብሔር ሰብአዊ ዘርን ሲፈጥር በራሱ መልክ እና አምሳል ነው የፈጠራቸው(ዘፍ. 1፡26-27)።

ዘፍ. 2፡7 እንደሚያብራራልን “የህይወት እስትንፋስ” ወደ አዳም አካል ሲገባ እርሱን “ህያው ነፍስ” ወደ መሆን ቀየረው። ይህም ማለት ከእያንዳንዳችን ተለይታ የምትኖር ነፍስ የለችንም። ይህ “ነፍስ” የሚባል ራሱን የቻለ አካል ከሰው ልጅ አካል ለብቻው ተለይቶ ይገኛል የሚለው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃሳብ ሳይሆን የአረማውያን አስተምህሮ ነው። የሰው ልጅን እውነተኛ ተፈጥሮ በሚመለከት ያለን ትክክለኛ መረዳት ተጨባጭ ስላልሆነችው ነፍስ ታዋቂነትን ካተረፈው አስተሳሰብ እና በዚህ እምነት ላይ ከተመሰረተው አደገኛ የተሳሳተ ትምህርት እንድንጠበቅ ያደርገናል።

ከሰው ልጅ አካል ተለይቶ ለብቻው የሚኖር አካል ፈጽሞ የለም። እግዚአብሔር ግሩምና ድንቅ አድርጎ ስለፈጠረን በዚህ ጉዳይ ላይ መፅሐፍ ቅዱስ ከሚል ባለፈ ግምት ውስጥ ልንገባ አይገባንም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሚስጥራዊ የሆነው የህይወት አፈጣጠር ብቻ ሳይሆን (ሳይንቲስቶች ራሳቸው ህያው መሆን ምን ማለት እንደሆነ ለመግለፅ የተስማሙበት ትርጓሜ የለም) በህይወት መኖር ራሱ የበለጠ ሚስጥራዊ ነው። በአእምሯችን ውስጥ የሚገኙት ጥቂት ኪሎዎችን የሚመዝኑት ህዋሶች (ሴሎችና ኬሚካሎች) እንደ ሃሳብና ስሜት ያሉ የማይጨበጡ ነገሮችን በምን መልኩ ሊፈጥር ይችላል? ይህንን የሚያጠኑ ሰዎች የሚነግሩን ምንም እንደማያውቁ ነው።

ህይወት ምን አይነት አስደማሚ ነገር ነው! ከህይወት ስጦታ በላቀው ተአምራዊ በሆነው የዘላለም ህይወት ሀሴት ልናደርግ የሚገባን ለምንድነው?

መስከረም 30
Oct 10

“ኃጢያት የምትሰራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች”


ህዝ. 18፡4፣20ን እና ማቴ. 10፡28ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለሰው ልጅ ነፍስ አፈጣጠር እንድንረዳ የሚያግዙን እንዴት ነው?



በዚህ ኃጢአተኛ አለም ውስጥ የሰው ህይወት ተሰባሪ እና ጊዜያዊ ነው (ኢሳ. 40፡1-8)። በኃጢአት የተጠቃ ማንኛውም ነገር ዘላለማዊ ሊሆን አይችልም። “ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደገባ ሁሉ ሞትም በሀጢያት በኩል ገብቶአል በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋል” (ሮሜ 5፡12)። ሞት የኃጢያት ተፈጥሮአዊ ውጤት ነው፤ ይህም ህይወት ያላቸውን ፍጡራን ሁሉ የጎዳ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ ሁለት ወሳኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሳቤዎች አሉ። አንደኛው የሰው ልጆችም እንስሳትም ሁለቱም ይሞታሉ። በንጉስ ሰለሞን እንደ ተነገረው ነው “የሰው ዕድል ፈንታ እንደ እንስሳት ነው፤ ሁለቱም ዕጣ ፈንታቸው አንድ ነው አንዱ እንደሚሞት ሌላው እንዲሁ ይሞታል ሁለቱም አንድ እስትንፋስ አላቸው ሰውም ከእንስሳት ብልጫ የለውም ሁሉም ከንቱ ነው። ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳሉ ሁሉም ከአፈር እንደሆኑ ተመልሰው ወደ አፈር ይሄዳሉ” (መክ. 3፡19-20)።

ሁለተኛው ፅንሰ-ኃሳብ የግለሰቡ አካላዊ ሞት የሚያመላክተን ነገር ቢኖር እርሱ/እርሷ እንደህያው ነፍስ(በዕብራይስጡ ነፈሽ) መኖር ማቆሙን/ ሟን ነው። በዘፍ. 2፡16-17 ላይ እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ክፉውንና መልካሙን ከምታሳውቀው የእውቀት ዛፍ በበሉ ጊዜና ኃጢአት በሰሩ ሰዓት እንደሚሞቱ አስጠንቅቋቸዋል።

ይህንኑ ማስጠንቀቂያ በማስተጋባት ጌታ በህዝ. 18፡4 እና ቁጥር 20 ላይ ጉዳዩን በማጠንከር “ኃጢያት የምትሠራ ነፍስ እርሷ ትሞታለች” ብሎ ተናግሯል። ይህ አገላለፅ ሁለት ዋነኛ ነገሮችን ያመለክተናል። አንደኛው ሁሉም ሰብአዊ ዘር ሀጢያተኛ ስለሆነ ሁሉም ሰብአዊ ዘር ልናስወግደው በማንችለው ማርጀትና በመሞት ቀንበር ስር ወድቀናል (ሮሜ 3፡9-18፣23)። ሌላኛው ነጥብ ደግሞ ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እሳቤ ነፍስ አትሞትም የሚባለውን ዝነኛ አስተምህሮ ዋጋ ቢስ ያደርጋል። ነፍስ የማትሞት እና ከሞት በኋላ በሌላ ስፍራ ህያው ሆኖ የምትቆይ ከሆነ ታዲያ መጀመሪያውኑ አንሞትማ? አይደለም እንዴ? በተቃራኒው አወዛጋቢ ስለሆነው ስለሞት ኃሳብ መፅሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን መፍትሔ ወደ ገነት ወይንም ማቆያ ስፍራ(መንጽሔ) አልያም ወደ ገሃነም የምትገባ ነፍስን አይደለም። የዚህ መፍትሄ በክርስቶስ አምነው የሞቱ ሰዎች በመጨረሻው ትንሳኤ ከሞት መነሳታቸው ነው።

ኢየሱስ ስለ ህይወት እንጀራ ባስተማረበት ወቅት እንደገለፀው “የአባቴ ፈቃድ ወልድን አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው ነው፤ እኔም በመጨረሻው ቀን አስነሳዋለሁ።”(ዮሐ. 6፡40)። በክርስቶስ የመጀመሪያ ምፅዓት ምክንያት እርግጠኞች የሆንበት ዳግም ምፅዓቱ (ያለ ክርስቶስ የመጀመሪያ መገለጥ ሁለተኛው ምፅዓት ምን ጥቅም አለው?) በምናምነው ነገር ሁሉ ውስጥ ወሳኝ ሀሳብ የሆነው ለምንድነው? ከዳግም መምጣቱ የተስፋ ቃል ውጪ ሌላ ምን ተስፋ ይኖረን ነበር?

ጥቅምት 1
Oct 11

“መንፈስ ወደ እግዚአብሔር ይመለሳል”


ዘፍ. 2፡7ን እና መክ. 12፡1-7ን ያንብቡ። በነዚህ ጥቅሶች መካከል ምን አይነት ተፃራሪነት እናስተውላለን ስለ ሰው ልጅ የሞት ሁኔታ የበለጠ እንድንረዳ እነዚህ ጥቅሶች በምን መንገድ እገዛ ያደርጉልናል? በተጨማሪ ዘፍ 7፡22ንም ይመልከቱ።



ከዚህ ቀደም እንደተመለከትነው የሰው ልጅ ራሱ ነፍስ ነው (ዘፍ. 2፡7)፤ አካል ሲሞት ነፍስም መኖር ታቆማለች (ህዝ. 18፡4፣20)።

ነገር ግን “መንፈስስ” ምንድነው? አያሌ ክርስቲያኖች እንደሚያምኑት አካል ከሞተ በኋላ ንቁ ሆኖ መኖር ይቀጥላልን? እይታቸውን ለማረጋገጥም መክ. 12፡7ን ይጠቅሳሉ፤ ማለትም “አፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ መንፈስም ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ” የሚለውን ማለት ነው። ነገር ግን ይህ አገላለፅ የሞተው ሰው መንፈስ በእግዚአብሔር ዘንድ ህያው ሆና እንደምትቆይ አይነግረንም።

መክብብ 12፡1-7 አስደናቂ ተውኔታዊ ቃላትን በመጠቀም የእርጅና ሂደት እንዴት በሞት እንደሚደመደም ያብራራልናል። ቁጥር 7 ላይ ዘፍ. 2፡7 ላይ ከተጠቀሰው የፍጥረት ሂደት ተገላቢጦሽ የሆነውን ኃሳብ ይጠቅስልናል። ከዚህ ቀደም እንደተጠቀሰው በስድስተኛው የፍጥረት ቀን ላይ “እግዚአብሔር አምላክ ከምድር አፈር ወስዶ ሰውን አበጀው በአፍንጫውም የህይወት እስትንፋስ እፍ አለበት ሰውም ህያው ነፍስ ሆነ።” (ዘፍ 2፡7) ይላል። አሁን ግን መክብብ 12፡7 ላይ የሚነግረን “አፈር ወደ መጣበት መሬት፣ መንፈስ ደግሞ ወደሰጠው ወደ እግዚአብሔር እንደሚመለስ” ነው።

ስለዚህ የህይወት እስትንፋስ ያም በአዳም አፍንጫ ላይ እግዚአብሔር እፍ ያለበት በዚሁ መልክ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠው እስትንፋስ ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ይመለሳል፤ በሌላ አባባል እስትንፋሱ በውስጡ መዘዋወር ወይንም መተላለፉን ያቆማል። በልባችን ልናስቀምጠው የሚገባን ነገር ቢኖር መክብብ 12፡7 እያብራራልን ያለው ወደ ሞት እየሄደ ስላለው ሰብአዊ ዘር ሁኔታ ሲሆን ይህም ፃድቁን ከኃጢያተኛው ያልለየ መሆኑን ነው። የሞቱ ሰዎች ሁሉ መንፈሳቸው ህያው ሆኖ በእግዚአብሔር ሃልዎት ፊት ከተገኙ የሀጢያተኞችም መንፈስ በእሱ ፊት አለ ማለት ነው? ይህ አስተሳሰብ ከአጠቃላዩ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር የማይጣጣም ነው።

ምክንያቱም ለሰው ልጆችም ለእንስሳቱም ለሁለቱም ወደ ሞት የሚሄዱበት ሂደት ተመሳሳይ ስለሆነ (መክ. 3፡19-20) ሞት መኖርን ማቆም ከሚለው ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም። ባለመዝሙሩ እንደገለፀው “ፊትህን ስትሰውር በድንጋጤ ይሞላሉ፤ እስትንፋሳቸውንም ስትወስድባቸው ይሞታሉ፤ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ።” (መዝ. 104፡29) አብዛኛውን ጊዜ እንደምንለው ሞት የህይወት ክፍል ብቻ ነው። ይህ ስህተት የሆነው ለምንድነው? ሞት የህይወት ተቃራኒ ነው፤ የህይወት ጠላት ነው። “የሚደመሰሰውም የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው” (1 ቆሮ. 15፡26) በሚለው ጥቅስ ውስጥ የምናገኘው ምን አይነት ታላቅ ተስፋ አለ?

ጥቅምት 2
Oct 12

“ሙታን አንዳች አያውቁም”


ኢዮብ 3፡11-13ን፤ መዝ. 115፡17ን፤ መዝ. 146፡4ን እና መክብብ 9፡5 እና 10ን ያንብቡ። ስለ ሰው ልጅ የሞት ሁኔታ እነዚህ ጥቅሶች የሚያስተምሩን ምን ነገር አለ?



አንዳንድ የመፅሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚሞግቱት እነዚህ ጥቅሶች (ኢዮብ 3፡11-13፤ መዝ 115፡17፤ መዝ 146፡4፤ መክብብ 9፡ 5፣10) የተፃፉት በረቀቀ የግጥም ቅኔ ለዛ ስለሆነ ስለ ሰው ልጅ የሞት ሁኔታ ለመግለፅ ልንጠቀማቸው አይገባም ይላሉ። እውነት ነው አንዳንዴ የግጥም ቅኔዎች አሻሚና በቀላሉ ለመረዳት አዳጋች ናቸው፤ ነገር ግን ከነዚህ ጥቅሶች አንፃር ግን ጉዳዩ እንደዛ አይደለም። ቋንቋቸው ግልጽ እሳቤያቸው ደግሞ በዚህ ርዕስ ጉዳይ ላይ ከተፃፉ የብሉይ ኪዳን አስተምህሮች ጋር ሙሉ በሙሉ የተጣጣመ ነው። በመጀመሪያ ኢዮብ 3 ላይ ይህ የሃይማኖት አባት ካጋጠመው ስቃይ በመነሳት የተወለደበትን ቀን ረገመ። (በእንደዚህ ዓይነት አደገኛ ሁኔታ ላይ ሆኖ ባልተወለድኩ ብሎ ያልተመኘ ማን አለ?) በተወለደበት በዛኑ ቀን ከሞተ አሸልቦ ስለሚቀር ረፍት ያገኝ ነበር (ኢዮብ 3፡11፣13)።

መዝ. 115 ሙታን ፀጥ ረጭ ባለ ስፍራ እንደሚጠበቁ ይነግረናል “እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑት የሞቱት አይደለም” (መዝ. 115፡17)። ይህ አባባል ታማኝ የሆኑ (አመስጋኝ የሆኑ) ሙታን፣ እግዚአብሔርን በሰማይ እንደሚያመልኩ የሚናገር አይመስልም።

በመዝ. 146 መሠረት አንድ ሰው ሲሞት አዕምሮአዊ እንቅስቃሴውም አብሮ ያቆማል፤ “መንፈሳቸው ትወጣለች ወደ መሬታቸው ይመለሳሉ ያን ጊዜም ዕቅዳቸው እንዳልነበር ይሆናል” (መዝ. 146፡4)። በሞት ጊዜ ምን እንደሚሆን በትክክል የሚገልጽ መልካም መፅሐፍ ቅዱሳዊ ማሳያ ነው። መክ. 9ም ጨምሮ ሲናገር “ሙታን አንዳች አያውቁም” ይለናል በመቃብር ውስጥ “መስራትም ሆነ ማቀድ፤ ዕውቀትም ሆነ ጥበብ የለም” ይለናል (መክ. 9፡5፣10)። እነዚህ ጥቅሶች ሙታን ምንም ነገር እንደማያውቁ የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ያረጋግጣሉ።

ሙታን ምንም አያውቁም የሚለው መፅሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ በክርስቲያኖች ላይ ጭንቀትን ሊፈጥር አይገባም። ሲጀመር ዘላለማዊ የሆነ የገሃነም እሳት ወይንም ያልዳኑ ሰዎች የሚቆዩበት ጊዜያዊ ስፍራ(መንጽሔ) የሚባል ነገር የለም። ሁለተኛ በክርስቶስ አምነው የሞቱ ሰዎች አስደናቂ የሆነ ሽልማት ይጠብቃቸዋል። “ለአማኞች ሞት ትንሽ ነገር” መሆኑ እምብዛም አያስደንቅም። …ለክርስቲያኖች ሞት እንቅልፍ፤ የፀጥታ እና የጨለማ ጊዜ ነው። ህይወት ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ተሸሽጋለች፤ ህይወታችን የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እኛም ከርሱ ጋር አብረን በክብር እንገለጣለን፤ ዮሐ. 8፡51-52፣ ቆላ. 3፡4።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገፅ 787።

በክርስቶስ አምነው ስለሞቱ ሰዎች ያስቡ። ከ1500 አመታት ወይንም ከ5 ወራት በፊት ሞተው ቢሆን ልዩነት አያመጣም፤ በመቃብር ሲሞቱ በሞት አይኖቻቸው ተጨፍኗል። እነርሱ ቀጥሎ የሚያውቁት ነገር ቢኖር የክርስቶስ ዳግም መመለስን ነው። ታድያ በአንድ መልኩ ከእኛ በህይወት ካለነው ይልቅ የሞቱ ሰዎች የተሻሉ ናቸው ብሎ አንድ ሰው እንዴት ሊሞግት ይችላል?

ጥቅምት 3
Oct 13

ከቀደሙ አባቶች ጋር ማረፍ


ዘፍ. 25፡8ን፣ 2 ሳሙ. 7፡12ን፤ 1 ነገ. 2፡10ን እና 1 ነገ. 22፡40ን ያንብቡ። ስለሞት ባለዎት መረዳት ላይ እነዚህ ጥቅሶች የሚጨምሩልዎ ምን አይነት መረዳት አለ?



ብሉይ ኪዳን ስለሞት እና መቀበር በተለያየ መንገድ ይገልጽልናል። አንዱ ሀሳብ ወደ ወገኖቹ ተከማቸ የሚለው አገላለፅ ነው። ለምሳሌ ስለ አብርሃም ሲነግረን “ከዚያም አረፈ፤ ዕድሜ ጠግቦ በመልካም ሽምግልና ሞተ፤ ወደ ወገኖቹም ተሰበሰበ” (ዘፍ. 25፡8)። አሮንና ሙሴም ወደ ወገኖቻቸው ተሰብስበዋል(ዘዳ 32፡50)::

መልካምም የሆኑ ክፉ ነገስታት ሲሞቱ ወደ ተመሳሳይ ስፍራ መሄዳቸው ስለሞት ባህሪ ምን ይነግረናል? (2 ነገ. 24፡6፤ 2 ዜና 32፡33)



ሞትን የሚገልጽበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ የሚለው ነው። ስለ ንጉስ ዳዊት አሟሟት መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ከዚያም ዳዊት ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ (1 ነገ. 2፡10)። ይህ ተመሳሳይ የሆነ አገላለፅ ታማኝና ታማኝ ላልሆኑ ነገስታት አሟሟት ጥቅም ላይ ውሏል። ከአባቶች ጋር ማንቀላፋት ከሚለው ሃሳብ ላይ ሶስት ትርጉሞችን ልናወጣ እንችላለን። የመጀመሪያው በቅርቡ ይሁን ወይንም ቆይቶ አድካሚና ስቃይ ከተሞላበት ሥራችን የምናርፍበት ጊዜ ይመጣል። ሁለተኛው ሃሳብ ደግሞ ይህን ደስ የማይል መንገድ ለመሄድ እኛ የመጀመሪያዎቹ ወይንም ብቸኛዎቹ ሰዎች አይደለንም፤ ምክንያቱም ከኛ ቀድመው አባቶቻችን በዚህ መንገድ አልፈዋልና። ሶስተኛ ሀሳብ ደግሞ ከእነርሱ አጠገብ በመቀበራችን ምንም በማናውቅበት መንገድ ከእነርሱ ጋር እየተባበርን ነው፤ ይህ ለዘመናዊውና ብቸኝነት ላይ ለሚያተኩረው ሰው ትርጉም የማይሰጥ ቢሆንም በጥንት ጊዜ ግን ትልቅ ትርጉም የሚሰጥ ነገር ነበር።

በክርስቶስ አምነው የሞቱት ከወዳጆቻቸው አጠገብ ሊቀበሩ ቢችሉም ምንም አይነት ንግግር ተለዋውጠው አያውቁም። ያ የክብር ቀን እስኪመጣ ድረስ ምንም አያውቁም፤ ከዚህ ከባድ እንቅልፍ በሚነቁበት ጊዜ ግን በክርስቶስ አምነው ካንቀላፉ ወገኖቻቸው ጋር ይገናኛሉ።

ሙታን አስተውለው በተለይም የሚወዷቸው ሰዎች ከእነርሱ በኋላ የሚያዩትን ስቃይ ማየት ቢችሉ ብለው ያስቡ። ታድያ ህያው ለሆኑት በሞት የማንቀላፋት እውነታ ምቾት የሚሰጥ የሆነው ለምንድነው?

ጥቅምት 4
Oct 14


ተጨማሪ ሀሳብ


"ታላቁ ተጋድሎ” የሚል ርዕስ ካለው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ “የመጀመሪያው ታላቅ ማታለል” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

“ቀዶ ጥገና ለማድረግ ሲባል ማደንዘዣ ቢወስዱ መሞት ምን ሊመስል እንደሚችል ግንዛቤ ማግኘት ይችላሉ። ነገር ግን ማደንዘዣውን ብንወስድም አዕምሮአችን ግን መስራቱን ይቀጥላል። የአዕምሮአቸው እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ስለቆመባቸው ሙታን ነገሮች እንዴት ሊሆኑ እንደሚችሉ እስቲ ያስቡ። በሞት ውስጥ ያላቸው ተሞክሮ አይኖቻቸውን መጨፈን ሲሆን ቀጥሎ የሚያውቁት ነገር ቢኖር የክርስቶስ ዳግም ምፃት ወይንም ከሺኅ ዓመት በኋላ የርሱን ተመልሶ መምጣት ነው (ራእይ 20፡7-15ን ይመልከቱ)። እስከዚያ ድረስ ግን የሞቱ ኃጢአንም ይሁኑ ጻድቃን በሞላ እነርሱ ቅፅበት በሚመስል ጊዜ ውስጥ ያርፋሉ። በህይወት ለምንቆየው ሞት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ጊዜን እንደሚወስድ እናስባን። በህይወት ላሉቱ አዎን እንደዛ ይሰማቸዋል፤ ለሞቱ ሰዎች ግን የቅጽበት ያክል ብቻ ጊዜ ነው።

“የሰው ልጆች ሁሉ ነፍስ በጥፋት ሰዓት በቀጥታ ወደ ሰማይ አርጋ ከሆነ ከህይወት ይልቅ መሞትን የበለጠ በተመኘን። ብዙዎች በዚህ እምነት ተነድተው መኖራቸውን ወደ መደምደሚያ ያመጡ አሉ። በችግር፣ በመደነጋገር እና ተስፋ በመቁረጥ ስንደክም፣ የህይወትን ገመድ በቀላሉ በጥሰን ወደ ዘላማዊ ህይወት በረከት ተመንጭቀን መሄድ እንዳለብን እናስባለን።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ገጽ 539 “በመጽሐፍ ቅዱስ በየትም ስፍራ ላይ ሰዎች ሲሞቱ ወዲያውኑ ፃድቃን ወደ ሽልማታቸው ኃጢአን ደግሞ ወደ ቅጣታቸው እንደሚሄዱ አይነግረንም።

የሃይማኖት አባቶችና ነብያት ይህንን አይነት ማረጋገጫን ጥለውልን አላለፉም። ክርስቶስ እና ሐዋርያቱም ስለዚህ ነገር እንዲህ ያለ ፍንጭን አልሰጡንም። መፅሐፍ ቅዱስ በግልፅ እንደሚያስተምረን ሙታን ወዲያውኑ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ አይለንም። እስከ ትንሳኤ ድረስ ያንቀላፋሉ።” ገፅ. 549፣ 550




የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሳይከፋፈል ህያው ሆኖ ስለሚኖረው የሰው ልጅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠን ማብራሪያ ስለ ሞት ባህሪ የበለጠ እንድናስተውል የሚያግዘን እንዴት ነው?

2.ዓለም በሙሉ በተፈጥሮዋ ነፍስ አትሞትም በሚል ማረጋገጫ የሌለው ትምህርት ተወስዶአል። በሙታን ሁኔታ ያለን መልዕክት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ይህ አስደናቂ ትምህርት ቢሆንም ከክርስቲያኖች መካከል ጠንካራ ተቃውሞን የሚያቀርቡ ሰዎችን የምናገኘው ለምን ይሆን?

3.ስለ ሙታን ሁኔታ ያለን መረዳት በአይኖቻችን ከሚታዩ ነገሮች ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው? ይህም ማለት የምናየውን ነገር ሁሉ በተለይም ያየነው ወይንም እያየን የመሰለን ነገር አንዳንዶች አይተናል ብለው እንደተናገሩት የኛ የቅርብ ሰው ሙት መንፈስ ቢሆን ማመን የሌለብን ለምንድነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL