የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከህዳር 10-16

9ኛ ትምህርት

Nov 19–25




የሚጣረሱ ጥቅሶች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ሉቃስ 16፡19-31፤ ሉቃስ 23፡43፤ ዮሐ. 20፡17፤ ፊሊ. 1፡21-24፤ 1ጴጥ. 3፡13-20፤ ዮሐ. ራዕይ 6፡9-11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው፤” (ዮሐ. 5፡39)

ጴ ጥሮስ እንደሚመክረን “በእናንተ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቁአችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጃችሁ ሁኑ” (1ጴጥ. 3፡15)። ጳውሎስም ሲያክል “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።” (2 ጢሞ. 4፡2-3)። እንዲህ ከሆነ ከእምነታችን ጋር የሚጣጣሙ ጥቅሶችን ብቻ ሳይሆን እኛ ከምናምንበት ጉዳይ በተለየ ሌላ አስተምህሮ ያላቸው ጥቅሶችን ልንመረምርና ልናብራራ ይገባናል።

ይህንን ስናደርግ የኢየሱስን አነቃቄ ምሳሌዎች መከተል ይኖርብናል። “ክርስቶስ ራሱ አንድም የእውነት ቃል አልሸፈነም፤ ነገር ግን ሁልጊዜ በፍቅር ይናገረው ነበር… ጨካኝ አልነበረም፤ አላስፈላጊ የሆኑ አሰቃቂ ቃላትን አልተናገረም፤ በጣም ስስ ለሆነችም ነፍስ አላስፈላጊ ህመምን አልጫነም። የሰው ልጆችን ድካምም አልገሰፀም።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 353። በዚህ ሳምንት ሰዎች ነፍስ በተፈጥሮዋ እንደማትሞት ማረጋገጫ አድርገው ስለሚያቀርቧቸው ሳቢ የሆኑ ጥቅሶች እናጠናለን። እነዚህ ሀሳቦች የእኛን እምነት ሊያጠናክሩና ስለዚህ ወሳኝ አስተምህሮ ጥያቄ ላለባቸው ሰዎች በትህትና የተሞላ ምላሽ እንድንሰጣቸው ሊያግዙን ይገባል። የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለህዳር 17 ሰንበት ይዘጋጁ።

ህዳር 11
Nov 20

ሃብታሙ ሰው እና አልዓዛር


ሉቃስ 16፡19-31ን ያንብቡ። ይህ ታሪክ ከሞት በኋላ ስለምንሆንበት ሁኔታ ቃል በቃል የሚገልጽ ያልሆነው ለምንድነው?



አንዳንድ ሊቃውንት ሉቃስ 16፡19-31 ስለ ሙታን ሁኔታ ለመግለፅ ቃል በቃል ሊተረጎም ይገባል ይላሉ። ነገር ግን ይህ እይታ መፅሐፍ ቅዱሳዊ ወዳልሆኑ አያሌ መደምደሚያዎች የሚመራና ከዚህ ቀደም ካየናቸው ጥቅሶች ጋርም የሚጣረስ ነው። ይህንን ቃል በቃል ለመውሰድ በመጀመሪያ ሰማይና ገሃነም ነዋሪዎቻቸው እርስ በእርስ ንግግር እስኪለዋወጡ ድረስ ቅርብ ለቅርብ ናቸው ብለን ማመን አለብን (ሉቃስ 16፡23-31)። በተጨማሪም ከሞት ባሻገር አካላችን በመቃብር ውስጥ ቢያርፍም “አይን” “ጣት” “ምላስ” ያላት እና የጥም ስሜት ያላት ንቁና መንፈሳዊ የሆነች ነፍስ አለች ብለን ልንገምት ነው ማለት ነው (ሉቃስ 16፡ 23-24)።

ይህ ጥቅስ የሰው ልጅ ስላለበት የሞት ሁኔታ የሚገልጽ ከሆነ የዳኑ ሰዎች ከጠፉ ወዳጆቻቸው ጋር ስለማያቋርጥ ስቃያቸው የሚነጋገሩ ከሆነ በርግጥም ሰማይ የደስታና የሃሴት ስፍራ ሊሆን አይችልም (ሉቃስ 16፡23-31)። በገሃነም ውስጥ የምትወደው ልጇን የማያቋርጥ ስቃይ በሰማይ ሆና የምታይ እናት እንዴት ደስተኛ ልትሆን ትችላለች? በዚህ አውድ መሠረት ሃዘን፣ ለቅሶ እና ህመም የለም ተብሎ የተገባው የተስፋ ቃል ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም (ራዕይ 21፡4)።

በዚህ ተከታታይነቱን ባልጠበቀ አካሄድ የተነሳ አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠበብት የሃብታሙን ሰውና የአላዛርን ታሪክ የሚያዩት እንደምሳሌ ሲሆን እያንዳንዱ ዝርዝር ሃሳብም ቃል በቃል ሊተረጎም አይችልም። ጆርጅ ላድ የተባለ አድቬንቲስት ያልሆነም ቢሆን እዚህ ጋር እንደ አድቬንቲስት ይህ ታሪክ ስለምን እንደሚናገር ሲተርክ “ይህ ምሳሌያዊ ታሪክ በጊዜው የነበሩ የአይሁድ አስተሳሰብን የተጠቀመ እንጂ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ሊያስተምረን የታሰበ ታሪክ አይደለም” G. E. L[add], “Eschatology,” in The New Bible Dictionary, edited by J. D. Douglas (Grand Rapids, MI: Eerdmans, 1962), p. 388

የሃብታሙ እና አላዛር ምሳሌያዊ ታሪክ በጥሩ ሁኔታ በለበሰ “ሃብታም” እና “አካሉ በቁስል በተወረሰ አንድ የኔ ቢጤ” መካከል ስለሚታየው ንፅፅር የሚናገር ነው (ሉቃስ 16፡19-20)። ይህ ክፍል የሚያስተምረን (1) አሁን ያለን የኑሮ ደረጃ እና ማህበራዊ እውቅና ወደፊት ለምንቀበለው ሽልማት እንደ መስፈርት እንደማያገለግል (2) የእያንዳንዱ ግለሰብ ዘላለማዊ እጣ ፈንታ የሚወሰነው እዚህ ባለን ህይወት እንደሆነና ከሞት ባሻገር በሚኖረን ህይወት ሊቀለበስ እንደማይችል ነው (ሉቃስ 16፡25-26)።

“ሙሴንና ነቢያትንም የማይሰሙ ከሆነ፥ ከሙታንም እንኳ አንድ ቢነሣ አያምኑም አለው።” (ሉቃስ 16፡31) ከኢየሱስ ሃይለኛ ቃላት የመፅሐፍ ቅዱስን የገዥነት ስልጣንና እኛ እንዴት ምላሽ ልንሰጥ እንደሚገባን በተመለከተ ምን ይነግረናል?

ህዳር 12
Nov 21

“ዛሬ…ከኔ ጋር በገነት”


ነፍስ እንደማትሞት ማረጋገጫ ተብለው ከሚጠቀሱ ብዙ ጥቅሶች መካከል በስፋት የሚጠቀሰው ሉቃስ 23፡43 ነው “ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።” ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች (ከጥቂቶቹ በስተቀር) ይህንን ጥቅስ የተረጎሙበት መንገድ ተመሳሳይ ነው፤ ክርስቶስ በሞተበት በዛኑ ቀን ላይ ክርስቶስንና ያ ወንበዴ አብረው በገነት እንደሚሆኑ በሚመስል መልኩ ማለት ነው። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠበብት ነፍስ ተፈጥሮዋ እንደማትሞት የሚነገረውን አስተምህሮ አጥብቀው የሚያምኑ ስለሆኑ ይህ እኛን ሊያስደንቀን አይገባም። ይሄ ግን ጥቅሱን በደንብ ተርጉሟል ብለን ማለት እንችላለን?

ሉቃስ 23፡43ን ከዮሐ. 20፡17 እና ዮሐ. 14፡1-3 ጋር ያነፃፅሩ። በመስቀል ላይ ንስሃ ለገባው ወንበዴ የተገባለትን ቃል ኢየሱስ ለመቅደላዊት ማርያም ከተናገረው እና ለደቀ መዛሙርቱ ከገባላቸው ቃል ጋር በማነፃፀር ልናስተውለው የሚገባን እንዴት ነው?



ክርስቶስ እና ወንበዴው በዛኑ ቀን ወደ ገነት (ወይንም ሰማይ) ሄደዋል የሚለው እሳቤ ኢየሱስ ለመቅደላዊት ማርያም ወደ ሰማይ ወደ አባቱ ዘንድ ገና እንዳልሄደ ከተናገረው ቃል ጋር ይጣረሳል። በተጨማሪም በዛችው ቀን ኢየሱስና ንስሃ የገባው ወንበዴ ወደ ሰማይ ሄደዋል የሚለው የተሳሳተ ሀሳብ ኢየሱስ ዳግም በሚመጣ ጊዜ ደቀ መዛርቱን እንደሚወስዳቸው ከሰጣቸው የተስፋ ቃልም ጋር የሚጋጭ ነው (ዮሐ. 14፡1-3)። በሉቃስ 23፡43 ላይ ያለው ጥያቄ “ዛሬ” ተብሎ እንደ ተውሳከ ግስ የተቀመጠው ቃል አብሮ የሚሆነው “ትሆናለህ” ከሚለው ጋር ነው ወይስ ከግሱ በፊት ካለው “እልሃለሁ” ከሚለው ግስ ጋር ነው? የሚለው ነው።

ዊሊያም ፓሮሺ ይህን በመረዳት “ከሰዋሰው” አንጻር ትክክለኛው ሃሳብ ይህ ነው ብሎ መወሰን እንደማይቻል ተረድቷል። “ሆኖም ሉቃስ ይህንን ተውሳከ ግስ (ዛሬ) ከግሱ አስቀድሞ ካለው ሀረግ ጋር የመጠቀም አዝማሚያ ይታይበታል። ይህም በሉቃስና በሐዋሪያት ሥራ 20 ጊዜ “ዛሬ” የሚለውን ቃል ሲጠቀም በ14ቱ አድርጎታል። Wilson Paroschi, “The Significance of a Comma: An Analysis of Luke 23:43,” in Ministry, June 2013, p. 7

ስለዚህ ትክክለኛው የሉቃስ 23፡43 አነባበብ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ በገነት ከእኔ ጋር ትሆናለህ” የሚለው ነው። ከዚህ አንጻር “እውነት እልሃለሁ ዛሬ” የሚለው አገላለፅ “ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ለሚለው ሃሳብ ተገቢና ጠንከር ያለ አፅንኦትን ለመስጠት የተጠቀመበት ነው። በአጭሩ ኢየሱስ ቃል የገባለት ባለበት በዚያው ስፍራ እንደዳነ ነው።

ሉቃስ 23፡39-43 ላይ ያለውን ንስሃ የገባውን ወንበዴ ታሪክ ያንብቡ። ምንም ያክል ሀጢያተኛ ቢሆን ለእግዚአብሔር ሊያበረክተው የሚችለው ምንም ነገር ባይኖርም በክርስቶስ በኩል ግን የዘላለም ህይወት እንደሚኖረው ቃል ተገብቶለታል። ይህ ታሪክ መዳን በእምነት ብቻ የመሆኑን ታላቅ እውነታ በከፍተኛ ደረጃ አጉልቶ የሚያሳየው እንዴት ነው? እኛስ በምን አይነት መንገድ ነው እንደዚህ ወንበዴ የሆንነው? ከእርሱ የምንለየውስ በምንድነው?

ህዳር 13
Nov 22

መሄድና ከእርሱ ጋር መሆን


ፊል. 1፡21-24 እና 1ተሰ. 4፡13-18ን ያንብቡ። ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር” (ፊሊ 1፡23 እና “ከጌታ ጋር እንደሚሆን”(1 ተሰ. 4፡17) የጠበቀው መቼ ነው?



ጳውሎስ ከፍተኛ በሆነ የጋለ ስሜት አሁን “ከክርስቶስ ጋር”(2 ቆሮ. 5፡17) አብሮ ለመኖር ከዳግም ምጽአቱ በኋላም “ከክርስቶስ ጋር”(1 ተሰ. 4፡17) ለመሆን ተነሳስቷል። ለዚህ ሐዋርያ ሞት ራሱ የአዳኙ ንብረት ስለመሆኑ ከተሰጠው ማረጋገጫ ሊለየው አልቻለም። ለሮሜ ሰዎች በፃፈው ደብዳቤ ላይ እንዳለው “ሞት ቢሆን ህይወት፣ . . . በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።” (ሮሜ 8፡38-39) “በሕይወት ሆነን ብንኖር ለጌታ እንኖራለንና፥ ብንሞትም ለጌታ እንሞታለን። እንግዲህ በሕይወት ሆነን ብንኖር ወይም ብንሞት የጌታ ነን።” (ሮሜ 14፡8)።

ይህንን እርግጠኝነት በልቡ ይዞ ጳውሎስ “በክርስቶስ ስላንቀላፉት” አማኞች (1ተሰ. 4፡14) እና በክርስቶስ ዳግም ምጻት ወቅት የዘላለም ሕይወትን ለመቀበል ከሞት ስለሚነሱ አማኞች አስቀድሞ ተናግሯል (1 ቆሮ. 15፡16-18፤ 1 ተሰ. 4፡13-18)። ጳውሎስ “ልሄድ፤ ከክርስቶስም ጋር ልሆን እናፍቃለሁ” (ፊል. 1፡23) ብሎ ሲናገር ከሞት በኋላ ነፍሱ ሄዳ ከክርስቶስ ጋር እንደምትኖር እያመላከተ ነውን? በፍጹም። በዚህ ጥቅስ ላይ ጳውሎስ አሁን እየኖርንበት ካለበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተላቆ ከክርስቶስ ጋር ለመሆን መናፈቁን እየገለፀ ሲሆን በሁለቱ ክስተቶች መካከል ስላለው የጊዜ ርቀት እየጠቀሰ አይደለም። ይህ ጥቅስ ጳውሎስ ሲሞት ወደ ሰማይ ወዲያውኑ ለመሄድ እየጠበቀ እንዳለ አያስተምረንም። እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጻት ድረስ ሽልማቱን እንደማይቀበል ገብቶታል (2 ጢሞ. 4፡8)።

በአጭሩ ጳውሎስ እያለን ያለው “ከሞትን (በሞት ከተለየን) በኋላ ቀጥሎ የምናውቀው ነገር ቢኖር በሰማይ ደመና ተገልጾ ሙታንን የሚያስነሳውን የኢየሱስን ዳግም ምፅአት ሲሆን ከዚያም “ከጌታ ጋር” (1ተሰ. 4፡17) ይሆናል። በወቅቱ የነበሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዳንድ ጊዜ እነዚህን በረጅም ጊዜ ርቀት የሚለያዩ ሁለት ክስተቶች አንድ አድርገው መግለፃቸው ልብ ሊባል ይገባል” Andrews study Bible, p. 1555. ለምንድነው ግን ጳውሎስ ከመኖር ይልቅ መሞትን የመረጠው? ምክንያቱም ከዚያ በላይ በስቃይ ህመም መጎሳቆል ስላልፈለገና ከመከራው ሁሉ እንዲያርፍ ስለፈለገ ነው (1ቆሮ. 9፡27)። ይህንንም በዳግም ምፃቱ ጊዜ “የፅድቅን አክሊል” እንደሚቀበል (2ጢሞ. 4፡6-8) እርግጠኛ በመሆን ሊያደርገው ፈልጓል። ምንም እንኳን በርግጥም መሞትን እየፈለገ ባይሆንም ከሞተ በኋላ ምን ተከትሎ እንደሚመጣ ግን ያውቅ ነበር።

በተለይ በአስቸጋሪ ጊዜያት ቀጥሎ የሚያውቀው ነገር “ከክርስቶስ ጋር መሆኑን” በማወቅ አይኑ በሞት እንዲከደን ያልተመኘ ማን አለ? ይህ አስተሳሰብ ጳውሎስ ፊልጲስዮስ ላይ የተናገረውን ኃሳብ የበለጠ እንድንረዳ የሚያግዘን እንዴት ነው?

ህዳር 14
Nov 23

በመንፈስ ሄዶ በእስር ቤት ላሉት መስበክ


1ጴጥ. 3፡13-20ን ያንብቡ። ክርስቶስ “በመንፈስ ሄዶ . . . በኖህ ዘመን ለነበሩት በእስር ቤት ላሉ ነፍሳት የሰበከው እንዴት ነው” (ዘፍ 4፡10ንም ይመልከቱ)



ነፍስ በተፈጥሮዋ አትሞትም ብለው የሚያምኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ክርስቶስ በመቃብር ውስጥ አርፎ በነበረበት ጊዜ “በእስር ቤት ላሉ በመንፈስ ሄዶ” መስበኩን (1ጴጥ 3፡19) ይጠቅሳሉ። እንደነርሱ አባባል ስጋ ያልለበሰው መንፈስ ወደ ገሀነም ወርዶ ከስጋቸው ለተለዩት ነፍሶች ሰበከላቸው። ነገር ግን ይህ አብረቅራቂ የሚመስል ሀሳብ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንፃር ስናየው ተቀባይነት የለውም። ምክንያቱም ሙታን ለመዳን ሁለተኛ እድል የላቸውም (ዕብ. 9፡27-28)። ታድያ ኢየሱስ የመዳን እድል ለሌላቸው ሰዎች ለምን ይሰብካል? ከምንም በላይ በዚህ ጊዜ አስፈላጊው ነገር ይህ ፅንሰ ሀሳብ ሙታን እስከመጨረሻው ትንሳኤ ድረስ ምንም የማያውቁ ሆነው በመቃብር ይቆያሉ ከሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር ይጋጫል (ኢዮብ 14፡10-12፤ መዝ. 146፡4፤ መክ. 9፡5፤ 10፤ 1ቆሮ. 15፡16-18፤ 1ተሰ. 4፡13-15)።

ይህ ጥቅስ ኢየሱስ በመቃብር አካሉ ሳለ ወደ ገሀነም ሄዶ በኖህ ዘመን ለነበሩት የጥንት ክፉ ሰዎች ሰብኮ ከሆነ እነዚህ ህዝቦች ብቻ ተነጥለው ለምን ይሄን መልዕከት ሰሙ ከእነርሱ ጋር ሌሎች በገሃነም የሚቃጠሉ ህዝቦችስ የሉም በኖህ ጊዜ የነበሩ ሰዎች ብቻ ለምን ስብከቱን ሰሙ? ክርስቶስ በኖህ ጊዜ ለነበሩ የወደቁ መላዕክት ሄዶ ሰበከ ማለትም እኮ ትርጉም የለሽ ነው። “በእስር ቤት ያሉ ነፍሳት” ተብሎ የተጠሩት “ቀደም ብሎ” ታዛዥ እንዳልነበሩ ቢገለፅም (1 ጴጥ. 3፡19-20)

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ክፉ መላዕክት ሲናገር እስከ ዛሬም ድረስ የማይታዘዙ እንደሆኑ ነው (ኤፌ. 6፡12፣ 1ጴጥ. 5፡ 8)። ከዚህም በተጨማሪ የወደቁ መላዕክት ያለምንም የድነት እድል “በዘላለም እስራት እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ በጨለማ ጠብቆአቸዋል” (ይሁዳ ቁ. 6)። ልናስተውል የሚገባን ነገር ቢኖር 1 ጴጥ. 3 ላይ “በእስር ቤት ያሉት መናፍስት” ብሎ ቁጥር 19 ላይ የጠራቸውን በቁጥር 20 ላይ ሲገልጻቸው በኖህ ጊዜ የነበሩትን “የማይታዘዙትን” ነው። “መንፈስ” የሚለው ቃል በግሪኩ “ኔውማ” ሲሆን ከዚህ ጥቅስ ሌላ በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ላይ (1ቆሮ. 16፡18፣ ገላ. 6፡18) የድነትን ጥሪ መስማትና መቀበል የሚችሉ ህያዋን ሰዎችን ለመጥቀስ ጥቅም ላይ ውሏል። “በእስር ላሉ” የሚለው አገላለፅ ቃል በቃል የታሰሩ ሰዎችን ሳይሆን በአመፀኛው የሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ ስላለው የኃጢያት እስራት እየጠቀሰ ነው (ሮሜ 6፡1-23፣ ሮሜ 7፡7-25)።

ንስሐ ለማይገቡ የኖህ ጊዜ ሰዎች ክርስቶስ ስብከቱን ያስተላለፈው በመለኮት ምሪት በኩል በእግዚአብሔር በታዘዘውና በጊዜው ለነበሩ ሰዎች “የጽድቅ ሰባኪ” በሆነው (2ጴጥ. 2፡5) በኖህ በኩል ነበር(ዕብ. 11፡7)። እነዚህ በ1ኛ ጴጥሮስ ውስጥ የተጠቀሱት ጥቅሶች የተፃፉት ሙታን ስላሉበት ሁኔታ ለመተንተን ሳይሆን ታማኝ መሆን ማለት እንደሆነ ከሚገልጽ አውድ አንጻር ነው።

ህዳር 15
Nov 24

ከመሰዊያው በታች የነበሩት ነፍሶች


ዮሐ. ራዕይ 6፡9-11ን ያንብቡ። የሙታን ሰማዕታት ነፍሶች “በመሰዊያው ስር” ሆነው እየጮኹ ያሉት እንዴት ነው?



የየአምስተኛው ማህተም መከፈት ያልተለመደ ክስተትን ያሳየናል። ዘይቤያዊ በሆነ አነጋገር “ከመሰዊያው በታች” ያሉ የሰማዕታት ነፍሶች እግዚአብሔር እንዲቀበል እየጮሁ ተመለከታቸው (ራዕይ 6፡9-11)። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ይህ “መሰዊያ” በሰባተኛው ማህተም ጊዜ የተጠቀሰው የወርቅ ጥና (እጣን ማጨሻ) ነው ወደማለት ያዘነብላሉ (ራዕይ 8፡1-6)። ነገር ግን በራዕይ 6፡9-11 ላይ “ደም”(ከእጣኑ ይልቅ) የሚለው ሀሳብ የመስዋዕቱ ደም ወደሚፈስበት የሚቃጠል መስዋዕት መሰዊያ ይመራል(ዘሌ. 4፡18፣30፣34)። የመስዋዕት ደማቸው በመሰዊያው ዙሪያ እንደተረጨ ሁሉ ለእግዚአብሔር ቃልና ለየሱስ ምስክር ታማኝ ሆነው የቆዩ ሰማዕታት ደም ምሳሌያዊ በሆነ አገላለፅ መፍሰሱንና (ራእይ 6፡9፣ ራዕይ 12፡17፣ ራእይ 14፡12) ህይወታቸውን ማጣታቸውን ያመለክተናል።

ከመሰዊያው በታች ያሉ “ነፍሶች” የሚለው አገላለጽ ራሱ ምሳሌያዊ ነው። ይህንን ቃል በቃል ከወሰድነው ሰማዕታቱ እግዚአብሔር እንዲበቀል አሁንም በመጮህ ላይ ስለሆኑ ሙሉ ሙሉ ደስተኛ ሆነው ሰማይ አይደሉም ብለን ልንደመድም እንችላለን። በድነት ሽልማታቸው ሃሴት እያደረጉ ናቸው ለማለት ይከብዳል። በቀል እንዲመጣ መፈለግ በራሱ ህይወትን ምስቅልቅሏ እንዲወጣ የሚያደርግ ነገር ነው። ሞታችንንም ያመሰቃቅላል ማለት ነው?

በተጨማሪም ዮሐንስ የተመለከተው ሰማይ ትክክለኛውን ሰማይ እንዳልሆነ ማስታወስ አስፈላጊ ነው። “ነጭ፣ ቀይ፣ ጥቁር ወይንም ግራጫ ፈረሶች እና ተዋጊ ጋላቢዎች በዛ የሉም። ኢየሱስም የታረደ በግ ሆኖ በዛ ስፍራ ላይ አልነበረም፤ አራቱ አውሬዎችም በትክክል ባለክንፍ ባህሪን የተላበሱ ፍጥረታት አልነበሩም…። ልክ እንደዛው ሁሉ በሰማይም ከመሰዊያው በታች የምትገኝ ነፍስ የለችም። ሁሉም የትዕይንት ክፍል ስዕላዊ እና ምሳሌያዊ መግለጫዎች ናቸው” The SDA Bible Commentary, vol. 7, p. 778።

ጆርጅ ላድ አድቬንቲስት ያልሆነው ፀሐፊ (እንደገና አድቬንቲስት በሚመስል አነጋገር) “ዮሐንስ ራዕይ 6፡9-11 ላይ ባለው ክፍል ላይ መሰዊያው የመስዋዕት ደም የሚፈስበት የመሰዊያ ስፍራ መሆኑ ግልጽ ነው። ዮሐንስ ከመሰዊያው በታች ሰማዕታትን የማየቱ ጉዳይ ከሙታን ሁኔታ ወይንም በመቆያ ስፍራ ከሚኖራቸው ሁኔታ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፤ በእግዚአብሔር ስም ሰማዕታት ሆነው ስለመሰዋታቸው ጉልህ በሆነ መንገድ ለመግለፅ ነው” A Commentary on the Revelation of John (Grand Rapids, MI: Eerdmans, 1972), p. 103 ለፍትህ ያልጮኸ(በተለይ በፍትህ መጓደል ምክንያት የተበደለ) ፍትህ እስኪያገኝ ድረስ ድምጹን ጮክ አድርጎ ያልጮኸ ማን አለ እኛስ ፍትህ የጎደላት አለም ውስጥ ብንሆንም በስተመጨረሻ ፍትህ እንዳለ ልናምን የሚገባን ለምንድነው ከዚህ አስደናቂ የተስፋ ቃል ልናገኘው የሚገባን አበረታች ነገር ምንድነው?

ህዳር 16
Nov 25


ተጨማሪ ሀሳብ


የክርስቶስ ተምሳሌታዊ ትምህርቶች ከሚለው መጽሐፍ “ታላቅ ጉድጓድ ተደፈነ” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ፣ የዘመናት ምኞት ከሚለው መጽሐፍ ደግሞ “ቀራንዮ” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ፣ የክርስትያን ትምህርት መሠረቶች ከሚለው መጽሐፍ ደግሞ “አስተማሪዎች እንደ ክርስትያናዊ ቅንነት ተምሳሌቶች” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ። “ስለ ሀብታሙ ሰው እና ስለ አልዓዛር በተነገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ ሊያሳየን የፈለገው ነገር ቢኖር ሰው በህይወት እያለ የዘላለም እጣ ፈንታው ላይ መወሰን እንደሚችል ነው። በዚህ የምህረት ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ ለእያንዳንዱ ነፍስ ተሰጥቷል። ነገር ግን ሰዎች ራሳቸውን በማስደሰት ይህንን እድል ሳይጠቀሙ ካባከኑ ከዘላለም ህይወት ራሳቸውን ቆርጠው ይጥላሉ። ከምህረት ጊዜ በኋላ የሚሰጣቸው ሌላ ዕድል የለም።

በምርጫቸው አማካኝነት በነርሱ እና በአምላካቸው መካከል ሊያሳልፍ የማይችል መስመርን አስቀምጠዋል” Ellen G White, Christ’s object lessons, p. 260 “የቀደሙ ክርስቲያኖች ወደ ተራራና ምድረበዳ ሲሰደዱ፣ በጨለማ ክፍል ውስጥ በረሃብ በቅዝቃዜና በስቃይ እንዲሞቱ ሲደረጉ፣ ከስቃይ ለመዳን ብቸኛው መንገድ ሰማዕት መሆን ብቻ እንደሆነ ሲገነዘቡ ለነርሱ ሲል ለተሰቀለላቸው ክርስቶስ ሲሉ ስቃይ ለመቀበል የተገባቸው ስለሆኑ ሀሴት ያደርጉ ነበር። ይህ ዋጋ ከፍ ያለ ምሳሌነታቸው ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መከራ ውስጥ ለሚያልፉ ለእግዚአብሔር ሰዎች መጽናናትንና መበረታታትን ይሰጣል።” Ellen G. White, Testimonies for the church, vol. 9, p. 213.




የመወያያ ጥያቄዎች



: 1. ስለ ሰው ልጅ ተፈጥሮ መጽሐፍ ቅዱስ የሚገልጽልን አጠቃላይ እሳቤ በዚህ ሳምንት ያየናቸውን አንዳንድ ጥቅሶች ይበልጥ እንድንረዳ እገዛ የሚያደርግልን እንዴት ነው?

2. ለድርድር የማይቀርበውን የክርስቲያን ሰማዕታት ሀይማኖት እና በዚህ ትውልድ ውስጥ ያለውን ተለዋዋጭ ሃይማኖት ያነፃፅሩ። በሌላ አባባል ልንሞትላቸው የሚገቡን ነገሮች ምንድናቸው አንድ ሰው እውት አንጻራዊ ነው ወይንም ባህላዊ ነው ብሎ ካሰበ ለዚህ ነገር ለምን ሲል ይሞታል በተመሳሳይም እኛ ውሸት ነው ብለን ላልናቸው ነገሮች ለመሞት ፈቃደኛ ስለሆኑት ሰዎች የምንማረው ምን ነገር አለ?

3. ስለ ሃብታሙ እና ስለ አላዛር በተነገረው ምሳሌ ላይ የበለጠ ጊዜ ይውሰዱ። ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ ብዙዎች በእርሱ አመኑ። ነገር ግን ይኸው ተመሳሳይ ማስረጃ እያላቸው ብዙዎች ደግሞ አላመኑም። የሰው ልጅ ለእውነት ምን ያክል ልቡ ደንዳና እንደሆነ ይህ ጉዳይ ምን ያስተምረናል ከእንደዚህ ዓይነት ተመሳሳይ ደንዳናነት ራሳችንን ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለብን?

4. ኢየሱስ ሙታን ህያው ስለሚሆኑበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ አለ “መልካም የሰሩ ለህይወት ትንሣኤ፣ ክፉ የሰሩ ለፍርድ ትንሳኤ ይወጣሉ” (ዮሐ. 5፡29)። ምንም እንኳን ክስተቶቹ በተመሳሳይ ጊዜ የሆኑ ቢመስልም በሁለቱ ክስተቶች መካከል አንድ ሺህ አመታት ልዩነት አለ። ይህ አገላለፅ ጳውሎስ በፊል. 1፡23 ላይ የተናገረውን ሃሳብ እንድናስተውል እገዛ የሚያደርግልን እንዴት ነው




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL