የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


ጥቅምት 30 - ህዳር 6

7ኛ ትምህርት

Nov 9 - 15




የሚያምኑ ብፁአን ናቸው



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 8:54–58, ዘፍ. 12:3፣ ሮሜ. 4:1-5, ዮሐ. 12:1-8፣ ዮሐ. 19:4-22፣ ዮሐ 20:19-31፣ ዳን. 2፣ ዳን. 7።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “የሱስም ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው አለው” (ዮሐ. 20፡29)።



ሐንስ በወንጌሉ ውስጥ ስለተለያዩ ሰዎች ይናገራል፤ የተለያየ አስተዳደግ፣ እምነት እና ልምምዶች ያላቸው ቢሆኑም ሁሉም ኢየሱስ ማን እንደሆነ ይመሰክራሉ። “እነሆ የእግዚአብሔር በግ!” (ዮሐ. 1:36)። “መሢሕን አግኝተናል” (ዮሐ. 1:42)። “ሙሴ በሕግ ነቢያትም ስለ እርሱ የጻፉትን …አግኝተነዋል” (ዮሐ. 1:45)።

“መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ አለው!” (ዮሐ. 1:50)። “እንጃ እርሱ ክርስቶስ ይሆንን?” (ዮሐ. 4:29)። “እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን” (ዮሐ. 4:42)። “ጌታ ሆይ፥ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” (ዮሐ. 6:68)። “አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ” (ዮሐ. 11:27)። “ዕውር እንደ ነበርሁ አሁንም እንዳይ” (ዮሐ. 9:25)። “እነሆ ንጉሣችሁ” (ዮሐ. 19:14)። “እኔስ አንዲት በደል ስንኳ አላገኘሁበትም” (ዮሐ. 19:6)። “ጌታዬ አምላኬም” (ዮሐ. 20:28)።

ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እነማን ነበሩ፣ እናም ስለ ኢየሱስ ማንነት የመሰከሩት ለምን ነበር? *የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሕዳር 7 ሰንበት ይዘጋጁ።

ህዳር 1
Nov 10

ወደ አብርሃም ተመልሶ መስማት


ኢየሱስ ስለ ማንነቱ በመግለጽ ወይም አብርሃምን ጨምሮ ከብዙ ጊዜ በፊት የነበሩትንና ስለ ማንነቱ የመሰከሩትን እንኳ ለማንሳት አላፈረም ነበር። “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ፥ አየም ደስም አለው” (ዮሐ.8:56)። የአብርሃም ምስክርነት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እስኪካተት ድረስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ዘፍ. 12፡3፣ ዘፍ.18፡16–18፣ ዘፍ.26፡4፣ ማቴ. 1፡ 1፣ የሐዋርያት ሥራ 3፡25።



“እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ “ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ አስታወቀው” (ገላ. 3፡8)፡፡ የአብርሃም እምነት ደግሞ ወደፊት በሚመጣው አዳኝ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ክርስቶስ ለአይሁዶች እንዲህ ብሎአቸዋል “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ አየም፤ ሐሴትም አደረገ” (ዮሐ 8፡56)፡፡ በይስሐቅ ምትክ የቀረበው በግ ስለ እኛ መስዋዕት የሆነልንን የእግዚአብሔር ልጅ ይወክላል፡፡ የሰው ልጅ አምላካዊውን ሕግ በመተላለፉ ምክንያት ሞት ሲፈረድበት፤ እግዚአብሔር አብ ወደ ልጁ እየተመለከተ ኃጢአተኛውን እንዲህ አለው፡- “በአንተ ምትክ የሚሞትልህን ስላገኘሁ እነሆ በህይወት ትኖራለህ” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፣ ገጽ 169)

አብርሃም የአይሁድ ሕዝብ አባት ነበር። በእርሱ በኩል አሕዛብ ሁሉ እንደሚባረኩ የተገባውን ቃል ተቀበለ። ይህ በረከት የመጣው ከእርሱ ዘር በተወለደው በመሲሑ ነው።

አብርሃምም ለእግዚአብሔር በእምነት ምላሽ ለሚሰጡ ሰዎችም አባት ነበር (ዕብ. 11፡8፣ 17- 19)። የተስፋው ልጅ የሆነውን ልጁን ይስሐቅን (ዘፍ. 22) ለመሠዋት የነበረው ፈቃደኛነት የእምነት ማረጋገጫ ብቻ ሳይሆን የመዳን ዕቅድ መስኮት ነበር።

ኢየሱስ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ያይ ዘንድ ሐሤት አደረገ” ሲል (ዮሐ. 8:56) መሪዎቹም “ገና አምሳ ዓመት ያልሆነህ አብርሃምን አይተሃልን?” በማለት ምላሽ ሰጡ (ዮሐ. 8:57)።

የኢየሱስ መልስ አስደናቂ ነበር። “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብርሃም ሳይወለድ እኔ አለሁ” (ዮሐ. 8:58)። ኢየሱስ በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ውስጥ እግዚአብሔር ለሙሴ የተናገረውን የሚያስታውስ ቋንቋን ተጠቀመ። ይህን ሲል ራሱን የቻለ አምላክ ነኝ ማለቱ ነበር።

ምንም ጥያቄ የለውም፣ መሪዎቹ የተናገረውን አንድምታ ተረድተዋል ምክንያቱም ከዚያ በኋላ “ሊወግሩት ድንጋይ አነሡ” (ዮሐንስ 8፡59)። ሮሜ 4፡1-5ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ጳውሎስ ይህን የአብርሃምን ታሪክ ከሕግ ስራ ውጭ በእምነት ብቻ የሆነውን ታላቁን የመዳን እውነት ለመግለፅ እንዴት አድርጎ ተጠቀመ? እነዚህ ጥቅሶች አብርሃም በእምነት ለሚኖሩ ሰዎች አባት ነው የሚለውን ሐሳብ እንድንረዳ የሚረዱን እንዴት ነው?

ህዳር 2
Nov 11

የማርያም ምስክርነት


ከፋሲካ ስድስት ቀናት በፊት ኢየሱስ ማርያምን፣ ማርታንና ከሞት ያስነሳውን ወንድማቸውን አልዓዛርን ሊጠይቃቸው መጣ። ከለምጽ የተፈወሰው ስምዖን ኢየሱስ ላደረገለት ነገር የምስጋና ግብዣ አዘጋጀ። ማርታ ታገለግል ነበር፣ አልዓዛርም ከእንግዶቹ ጋር በማዕድ ተቀምጦ ነበር (ዮሐንስ 12፡1-8)። በዚህ ሥፍራ የማርያም ድርጊት አስፈላጊነት ምኑ ላይ ነበር? ይህ ኢየሱስ ማን እንደነበር የሚመሰክረው እንዴት ነው? ዮሐንስ 12፡1-3።



ሽቶው በጣም ውድ ነበር፣ ለአንድ ሠራተኛ የአንድ አመት ደሞዝ ዋጋ ያለው ነው።

ማርያም ምናልባት ይህን ስጦታ ያመጣችው አዳኙ ለኃጢአቷ ይቅርታ ስላደረገና እና ወንድሟን ከሞት ስላስነሳ የምስጋና መግለጫ እንዲሆን ሊሆን ይችላል። አንድ ቀን ደግሞ ይህ ለኢየሱስ መቃብር እንዲሆን አስባ ነበር። ነገር ግን በቅርቡ ንጉሥ ሆኖ እንደሚቀባ ሰማች። እንደዚያ ከሆነ ደግሞ ለእርሱ ክብር የሚሆነውን ለማምጣት የመጀመሪያዋ ትሆናለች ማለት ነው።

ማርያም የምታደርገው እንዲታወቅ አላሰበችም ይሆናል፣ ነገር ግን ዮሐንስ “ቤቱም ከናርዶስ ሽቱ ሞላ” በማለት ተናግሯል (ዮሐንስ 12፡3)። ይሁዳ ሽቶው ተሽጦ ትርፉ ለድሆች መሰጠት ነበረበት በማለት በፈጣን ተግሣጽ አፀፋውን ሰጠ። ኢየሱስ ወዲያውኑ “ተውአት ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፥ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም” በማለት ማርያምን አፅናናት (ዮሐ. 12፡7-8)።

ተደጋግሞ የሚመጣ አንድ ጭብጥ ሐሳብ በወንጌል ውስጥ ይታያል። ኢየሱስ በሰዎች ውስጥ ያለውን ያውቃል (ዮሐ. 2:24-25፤ ዮሐ. 6:70-71፤ ዮሐ. 13:11፤ ዮሐ. 16:19)።

በዚህ ሁኔታ በስምዖን ግብዣ ላይ፣ ኢየሱስ በይሁዳ ውስጥ የነበረውን ያውቅ ነበር። ዮሐንስ ይሁዳ ማን እንደሆነ ለመጠቆም ጥንቃቄ አድርጓል፤ ራሱን የሚያገለግል ሌባ ነው በማለት (ዮሐ. 12፡6)።

“ማርያም በጌታ አስክሬን ላይ ለመርጨት ያቀደችውን የጥሩ መዓዛ ስጦታ በሕያው አካሉ ላይ ቀባችው። ሽቶውን በአስክሬኑ ላይ አፍስሳው ቢሆን ኖሮ ያ ጣፋጭ ሽታ የሚያውደው መቃብሩን ነበር፤ አሁን ግን ሽቶው የሃይማኖትዋና የፍቅርዋ መግለጫ ሆኖ ስለቀረበ ጌታን እጅግ አስደሰተው። … ጌታ የሱስ ወደ ታላቁ የፈተና ጨለማ ሲገባ ማርያም ያደረገችለት የፍቅር መግለጫ ከኃጢአት ያዳናቸው ጻድቃን ለዘላለም የሚገልጹለት ፍቅር ማስታወሻ ሆነው” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 577)። ኢየሱስ በማርያም እና በይሁዳ ልብ ውስጥ ያለውን ያውቅ ነበር። እርሱ በእናንተ ልብ ውስጥም ያለውን ያውቃል። ይህ እውነት እኛን ለመለወጥና ለመሸፈን ክርስቶስ ጽድቃችን የመሆኑን አስፈላጊነት በተመለከተ ምን ሊነግረን ይገባል?

ህዳር 3
Nov 12

ጲላጦስ ሳያውቀው የሰጠው ምስክርነት


ዮሐንስ የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለመያዝ፣ ለፍርድ ለማቅረብ እና የሞት ፍርድ ሊያስፈርዱበት ያደረጉትን ሙከራ በተደጋጋሚ ዘግቧል። በኢየሱስ ብዙ ጊዜ የተነገረውና በዮሐንስ ወንጌል ውስጥም ያለው ጭብጥ፣ ኢየሱስ ጊዜው ወይም ሰዓቱ ገና አልደረሰም የሚለው ነበር፤ ይህም እርሱ የሚሰቀልበት ጊዜ መሆኑ ነው (ዮሐ. 2:4፤ ዮሐንስ 7:6፣ 8፣ 30፤ ዮሐ. 12:7፣ 23፣ 27፤ ዮሐ. 13:1፤ ዮሐ. 17:1)።

አሁን ሰዓቱ ደርሶ ነበር። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ስፍራ ተይዞ፣ ወደ ሐና፣ ከዚያም ወደ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ፣ ከዚያም ሁለት ጊዜ በጲላጦስ ፊት ቀረበ።

ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ስለመሆኑ የሚመሰክሩትን ብዙ ምስክሮች ዮሐንስ ከሁሉም የሕይወት አቅጣጫ በመውሰድ ጠቅሷል። አሁን ዮሐንስ ገዥ ወደሆነውና ኢየሱስን ወደሚመረምረው ጲላጦስ ያመላክታል። ይህ አስፈላጊ ምስክር ነበር፤ ምክንያቱም ጲላጦስ ሮማዊ፣ ገዥ እና ዳኛ ነበር፤ ሌሎቹ አብዛኛዎቹ ምስክሮች አይሁዶች እና ተራ ሰዎች ነበሩ። የጲላጦስ ፍርድ ከዮሐንስ ወንጌል ጭብጥ ጋር የተያያዘው እንዴት ነው? ዮሐ. 18:38፣ ዮሐ. 19:4-22።



ኢየሱስ አርብ በማለዳ ወደ ጲላጦስ ተወሰደ (ዮሐ. 18፡28)። ዕቅዱ የነበረው በፍጥነት እስረኛውን እጣ ፈንታው ወደሆነው መስደድ ነበር። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ውጫዊው ገፅታ የጲላጦስን ትኩረት ሳበው። ገዥው ኢየሱስን አቅርቦት ጠየቀው እና “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል” የሚለውን ከአንደበቱ ሰማ (ዮሐ. 18:37)።

ምንም እንኳን ገዥው በመጨረሻ በኢየሱስ ላይ የሞት ፍርድ ቢፈርድም፣ ኢየሱስን ንፁህ እንደሆነ አውጆ ነበር (ዮሐ. 18:38፤ ዮሐ. 19:4፣ 6)። በመስቀሉ ላይ ደግሞ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” (ዮሐ. 19:19) የሚለውን ቃል በመጻፍ ስለ ኢየሱስ ማንነት የሰጠውን ምስክርነት አጠናቋል። እናም ምንም እንኳን ስለ ክርስቶስ ንፁህነት ቢመሰክርም፣ ኢየሱስን በሞት እንዲቀጣ ፈርዶበታል።

ከጲላጦስ ፊት እውነት ራሱ ቆሞ ነበር እናም ህዝቡ እንዲዘብቱበት በመፍቀድ፣ ጲላጦስ በኢየሱስ ላይ ሞት ፈረደበት! ይህ ሕሊናችሁና ልባችሁ ትክክል መሆኑን የሚነግሯችሁን አለመከተልን በተመለከተ እንዴት ያለ አሳዛኝ ምሳሌ ነው! የሕዝብ ስሜት አልፎ ተርፎም ግፊት ትክክል ነው ብለን የምናምንበትን ነገር እንዳናደርግ ስለ መፍቀድ አደጋ ከጲላጦስ ምሳሌ ምን እንማራለን?

ህዳር 4
Nov 13

የቶማስ ምስክርነት


ዮሐ. 20:19-31ን ያንብቡ። ስለ እምነት እና ጥርጣሬ ከቶማስ ታሪክ ምን እንማራለን? ቶማስ የሠራው ትልቅ ስህተት ምንድን ነው?



ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በፍርሃት ምክንያት በአንድ ክፍል ውስጥ ተዘግተው በነበሩበት ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ ተገለጠላቸው። ቶማስ ግን ከእነርሱ ጋር አልነበረም። በኋላም የትንሣኤውን ዘገባ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ሰማ፣ ሆኖም እርሱ ግን ተስፋ ቆረጠ። እርሱ ስለ መንግሥቱ ከሳለው ምሥል ጋር አልገጠመለትም። ደግሞም ኢየሱስ እርሱ በሌለበት ሰዓት ለምን ራሱን ለሌሎች እንደገለጠ ሳያስብ አልቀረም።

ቶማስም “የችንካሩን ምልክት በእጆቹ ካላየሁ ጣቴንም በችንካሩ ምልክት ካላገባሁ እጄንም በጎኑ ካላገባሁ አላምንም አላቸው” (ዮሐ. 20:25)።

ቶማስ የእምነቱን ሁኔታ እየመራ ነበር። ይህ በኢየሱስ የማመን አቀራረብ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ተደጋግሞ ታይቷል። ኒቆዲሞስ ለኢየሱስ መልሶ፡- “ሰው ከሸመገለ በኋላ እንዴት ሊወለድ ይችላል?” አለ (ዮሐ. 3፡4)። በጕድጓዱ አጠገብ የነበረችው ሴት “ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” በማለት ጠየቀች (ዮሐ. 4፡11)። እንጀራውንና ዓሣውን የተመገቡት ሰዎችም “ምን ምልክት ታደርጋለህ?” ብለው ጠየቁ (ዮሐ. 6፡30)።

የዮሐንስ ወንጌል የሚቃወመው ይህንን “እዩ ከዚያም እመኑ” የሚለውን አተያይ ነው።

ኢየሱስ ከትንሣኤ በኋላ ቶማስን ባገኘው ጊዜ፣ ከሙታን የተነሳውን ሥጋውን መጥቶ እንዲያይ እና እንዲዳስሰው ጋበዘው። ከዚያ በኋላ ግን “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” አለ (ዮሐ. 20፡29)።

“እግዚአብሔር እምነታችንን ለመመስረት የሚያስችል በቂ ማስረጃ ሳይሰጠን እንድናምን ፈጽሞ አይጠይቀንም። ስለ ህልውናው፣ ስለ ባህሪይው እና ስለ ቃሉ እውነተኛነት የሚያረጋግጡልን ለአእምሮአችን አጥጋቢ የሆኑ ምስክሮች ከመጠን በላይ ሰጥቶናል። ሆኖም ግን እግዚአብሔር የጥርጣሬ በሮችን ሁሉ አልዘጋም። በዓይን የሚታይ ማረጋገጫ ባናገኝም እምነታችን በማስረጃዎች ላይ መመስረት አለበት” (ኤለን ጂ ዋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገጽ 101)።

በእግዚአብሔር ቃል፣ በፍጥረት፣ እና በግል ተሞክሮ፣ በኢየሱስ ላይ ለማመን በሚያስደንቅ ሁኔታ ማስረጃ ተሰጥቶናል። አንድ ሰው በኢየሱስ ለምን ታምናለህ? ብሎ ቢጠይቃችሁ ምን ትላላችሁ?

ህዳር 5
Nov 14

ስለ ኢየሱስ የምንሰጠው የእኛ ምስክርነት


ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ የመሰከሩትን ደጋግሞ ሲያቀርብ፣ ነጥቡ እኛን ወደ አንድ ትልቅ መደምደሚያ ለማድረስ ነው፡- “የሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ፤ ነገር ግን ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ ዘንድ ይህ ተጽፎአል” (ዮሐንስ 20:30፣ 31)።

በአካል፣ በሥጋ በዚያ መገኘትን አስቡና ኢየሱስ እነዚህን ብዙ ተአምራት ሲፈጽም ተመልከቱ። በእርግጠኝነት እናምናለን አይደል? እኛ እንደዚህ ማሰብ እንፈልጋለን፤ ነገር ግን በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ተአምራቱን ከተመለከቱት ሰዎች የበለጠ በኢየሱስ ለማመን የሚያነሳሱ ምክንያቶች አሉን። ለምን? በዛሬው ዘመን ላይ የምንገኝ ሰዎች፣ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ግን የሌላቸው አንዳንድ ለማመን ሊረዱን የሚገቡ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ለምሳሌ ማቴ. 24፡2፣ ማቴ. 24፡14፣ ማቴ. 24፡6-8 ተመልከቱ።



ይህ ደግሞ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሚገኙት ኃይለኛ ዘገባዎች ስላሉን ብቻ ሳይሆን፣ ኢየሱስና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የተነበዩት አብዛኛው ሲፈጸም የማየት ትልቅ አንጻራዊ ዕድል ስላለን ነው። ለምሳሌ እንደ ቤተ መቅደሱ ጥፋት (ማቴ. 24፡2)፣ ወንጌል በዓለም ዙሪያ መስፋፋቱ (ማቴ. 24፡14)፣ ታላቁ ክህደት (2ኛ ተሰ. 2፡3)፣ እና ዓለም የወደቀች እና ክፉ ቦታ ሆና መቀጠሏ ሊጠቀስ ይችላል (ማቴ. 24፡6-8)። በኢየሱስ ሕይወት እና አገልግሎት ጊዜ ሁሉ፣ የእርሱ ተከታዮች አናሳ እና ትንኮሳ የሚፈጸምባቸው እንዲሁም በሁሉም የሰው ልጅ ደረጃዎች ከረጅም ጊዜ በፊት ከታሪክ መጥፋት የነበረባቸው ወንዶች እና ሴቶች ነበሩ። እነርሱ እኛ ዛሬ እንደምናውቀው፣ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንደሚፈጸሙ እንዴት ሊያውቁ ቻሉ? እነርሱ ግን ያውቁ ነበር። በእርግጥ፣ የእኛ የራሳችን እምነት እንኳን ኢየሱስ ወንጌል ለዓለም ሁሉ እንደሚሄድ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ሆኖ ይገኛል።

እና ዛሬ ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በኋላ፣ እኛም የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን፣ ስለ ኢየሱስና ስላደረገልን ነገር የመመሥከር መብት አለን። ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለራሳችን ማወቅ የምንችለው በናትናኤል፣ በኒቆዲሞስ፣ በሰማርያ ሴት ወይም በፈሪሳውያን በኩል በተሰጠው ምክንያት አይደለም። ኢየሱስን የዓለም አዳኝ አድርገን የምንቀበለው በመንፈስ ቅዱስ የወቀሳ ኃይልና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነው።

ከዚያም እያንዳንዳችን፣ በራሳችን መንገድ እና ራሳችን ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት የተነሳ የምንናገረው ታሪክ ሊኖረን ይችላል። ታሪካችን ሙታን ሲነሱ ወይም ከመወለዱ ጀምሮ ዓይነ ስውር የነበረው ሲፈወስ የማየት ያህል አስደናቂ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ ምንም ችግር የለውም። ዋናው ነገር ኢየሱስን በግላችን ማወቃችን እና በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደተጠቀሱት በራሳችን መንገድ ስለ እርሱ መመስከራችን ነው።

ህዳር 6
Nov 15


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ዋይት፣ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት መፅሐፍ “የእምነት መፈተን” ከገጽ 145-155 እና የዘመናት ምኞት ከሚለው መፅሐፍ ደግሞ “የሱስ በጲላጦስ ፍርድ ቤት” ከሚለው ከገጽ 723-740 ያንብቡ።

ቶማስ “በየሱስ እግር ላይ ወድቆ “ጌታዬ አምላኬም” ሲል ጮኸ።” “የሱስ የቶማስን እምነት ተቀብሎ ስለ ጥርጣሬው አንተስ “ስለ አየኸኝ አምነሃል፤ ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ሲል በጥንቃቄ ገሰጸው። ቶማስ ከወንድሞቹ በሰማው ምስክርነት አምኖ ቢሆን ኖሮ እምነቱ የሱስን የበለጠ ያስደስተው ነበር። ዓለም የቶማስን አርአያነት ቢከተል ኖሮ ማንም ከኃጢአት ስለ መዳን አያምንም ነበር። ሰዎች በክርስቶስ የሚያምኑት የሌሎችን ምስክርነት በመቀበል ነው።

“እንደ ቶማስ ተጠራጣሪ የሆኑ ብዙ ሰዎች ቶማስ ከባልንጀሮቹ እንደተሰጠው ያለ ማስረጃ ቢያገኙ እንደሚያምኑ በመናገር ራሳቸውን ለመከላከል ይሞክራሉ። ያ ብቻ ሳይሆን ከዚያ የበለጠ ማስረጃ እንዳላቸው አይገነዘቡም። እንደ ቶማስ ለጥርጣሬ ምክንያት የሆነው ሁሉ እስኪወገድ የሚጠብቁ ብዙ ሰዎች ፍላጎታቸውን አይገነዘቡም። እንደዚህ ያሉ ሰዎች ቀስ በቀስ ጽኑ ኢ-አማኞች ይሆናሉ። መጥፎ ነገርን ብቻ ለማየት ራሳቸውን የሚያሰለጥኑና የሚያጉረመርሙ ሰዎች የሚሠሩትን አያውቁም። የጥርጣሬ ዘር ይዘራሉ፣ የጥርጣሬ መከርን ይሰበስባሉ። እምነትና መተማመን እጅግ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ብዙዎች ተስፋ ለማድረግና ለማመን አቅም ያንሳቸዋል” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 855)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በአብርሃም እና በቶማስ የእምነት መግለጫዎች ውስጥ ያለው አስፈላጊ ልዩነት ምንድን ነው? ከታሪካቸው ምን እንማራለን?

2. በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንዳየነው በጥናት ቡድናችሁ ውስጥ፣ ፈቃደኛ የሆኑት ስለ ኢየሱስ እንዲመሰክሩ አድርጉ። ዘገባዎቹ ሊለያዩ ቢችሉም የሚመሰክሩት ሰዎች ምን ይላሉ? ሁሉም ስለ አንድ ጌታ የሚመሰክሩት እንዴት ነው?

3. ጲላጦስ “እውነት ምንድን ነው?” የሚል በጣም ፍልስፍናዊ ጥያቄ ጠየቀ። ለዚህ ጥያቄ በዮሐንስ ወንጌል ሁሉ ላይ ካጠናነው አንጻር መልሳችሁን ስጡ።

4. በዳንኤል 2 እና 7 ላይ የሚገኙትን ትንቢቶች ተመልከቱ። ምንም እንኳን በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች እነዚህ ሁለት ምዕራፎች የነበሯቸው ቢሆንም፣ ትንቢቶቹ ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸውና ከዚህም የበለጠ ለማመን ብዙ ምክንያቶች ስለሚገኙ ዛሬ ላይ ለምንገኝ ምን ትልቅ ዕድል አለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL