የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026



ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ 2018 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Mar 28 - Jun 26




አዘጋጅ : ኒና አቼሰን

ትርጉም : በረከት ፈለቀ



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ-ክርስቲያን ዋና መሥሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፈረንስ ሥር መምሪያውን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያው የሚዘጋጀው በሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ሲሆን፣ ቦርዱ የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴና የመምሪያው አሳታሚ ነው። መምሪያው ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሐሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ፣ የአዘጋጁን ሐሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

በዚህ ሰንበት ትምህርት መምሪያ ውስጥ የሚገኙት ጥቅሶች የተወሰዱት በ1954 ዓ.ም በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ከታተመው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። The Bible in Amharic © United Bible Societies 1962. ISBN: 9966 843 63 9. ማሳሰቢያ፡- ሁሉም የትንቢት ድምፅ ጽሑፎች ከእንግሊዝኛው ቀጥታ የተተረጎሙ ስለሆነ፣ ገጻቸው ከአማርኛው ትርጉም ጋር አይመሳሰልም።

2ኛው ሩብ ዓመት ከመጋቢት 19/2018 ዓ.ም-- ሰኔ 19/2018 ዓ.ም መደበኛ እትም

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ

እርስዎ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ሆነው ያደጉ ቢሆኑ ወይም ለእምነቱ አዲስ ቢሆኑ፤ ብዙ ወይም ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያዎችን አንብበው ቢሆን እንዲሁም ዛሬ እራስዎን በመንፈሳዊ አቋም በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢያገኙም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ትርጉም ባለው ግንኙነት ውስጥ ማደግ የሚለው ርዕስ ወሳኝ ነው።

ይህ ርዕስ ሌሎችን ሁሉ ይነካል። ስለ እግዚአብሔር ያለዎት ምስል ተበላሽቶ ወይም ደብዝዞ ከሆነ፣ ሲያጠኑ የበለጠ እንዲገልፅልዎት በፀሎት ይጠይቁት። የግል አምልኮ ልምምድዎን (ጸሎት እና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት) እንዴት ማደስ እንደሚችሉ እያሰቡ ይሆናል፤ ወይም እንደ ኩራት እና ትህትና፣ እምነት እና እውቀት፣ ኃጢአት እና የእግዚአብሔር ሕግ፣ ንስሐ እና ይቅርታ፣ መሰናክሎችን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል እና ሌሎች ከእግዚአብሔር ጋር እንዲጓዙ እንዴት ማበረታታት እንደሚችሉ ያሉ ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎትን ግንኙነት የሚነኩ ሌሎች ርዕሶች ላይ እያሰቡ ሊሆን ይችላል።

ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎት ግንኙነት በጣም አስፈላጊው ግንኙነትዎ ነው። በተቻለ መጠን ጠንካራ አድርገው ለመገንባት አይዘግዩ። በዚህ ግንኙነት ላይ ለመስራት ጊዜው ወደፊት ሳይሆን አሁን ነው፣ ይህም በሌሎች ነገሮች ማለትም ባለትዳር ከሆኑ በትዳርዎ፣ ወላጅ ከሆኑ በልጆች አስተዳደግዎ፣ ከሌሎች ጋር በሚኖርዎት ወዳጅነት፣ በገንዘብ አወጣጥዎ፣ በትርፍ ጊዜ አጠቃቀምዎ እንዲሁም በዘላለማዊ መዳረሻዎ ሁሉ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

እግዚአብሔር ከሰው ልጅ ጋር አብሮ ለመሆን ስላለው ፍላጎት የሚያትተው ይህ ርዕስ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠቃልል ስለሆነ፣ ይህንን ወሳኝ ርዕስ ለማስተማር ሊመረጡ የሚችሉ ብዙ የተለያዩ ማዕዘኖች፣ ታሪኮች እና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያችንን ባህሪ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ የተወሰኑትን ብቻ እንነካለን።

ዛሬ ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎት ግንኙነት ምንም ይሁን ምን፣ እነዚህ ትምህርቶች የተጻፉት እርስዎን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። በዋናነትም፣ የእነዚህ አስራ ሶስት አጫጭር፣ ትኩረት የተደረገባቸው ትምህርቶች ግብ በዚህ ሩብ ዓመት እሱን እንደገና ስለመፈለግና ለኢየሱስ ክርስቶስ ያለንን ፍቅር እና ቁርጠኝነት እንደገና ማነቃቃት ነው።

ይህ ርዕስ ስለ ግንኙነቶች ስለሆነ፣ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያ ከቀደሙት በተለየ መልኩ ተጽፏል። ምክንያቱም ትምህርቶቹ የተጻፉት እኛን በግል ማወቅ ስለሚፈልገው ስለ ግል አምላክ ነው። ኤለን ጂ. ኋይት “በክርስቶስ ውስጥ ወጥ የሆነ ሕይወት” ታላቅ ተአምር ነው ትላለች።— የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 407። መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለ የሕይወት ጉዞ ለመግለጽ የሩጫ ምሳሌያዊ አገላለጽን ይጠቀማል። ሽልማታችን የማይጠፋ አክሊል (1ኛ ቆሮ. 9:24-25) እና ከአምላካችን ጋር የዘላለም ሕይወት ነው። መንፈሳዊ ሩጫችን ማራቶን እንጂ ፈጣን ሩጫ አይደለም። ሩጫችንን የምናቆምበት ወይም የምንዘረርበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። ይከሰታል፣ እና ሲከሰት፣ ከወደቅንበት ተነስተን መንቀሳቀሳችንን እንቀጥላለን። የማይቀሩ ፈተናዎችና መከራዎች ቢኖሩም መንገዱን መቀጠል አለብን (ዕብ. 12:4-11)። እናም ይህንን ውድድር ብቻችንን አንሮጥም፤ ኢየሱስንና ቃሉን የሚወዱ ሌሎች ሯጮች ከእኛ ጋር ይሮጣሉ። ከሁሉም በላይ አስፈላጊው ነገር፣ ኢየሱስ ረዳት እንደሚሰጠን ቃል ገብቷል። “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለ ሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው፤ ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውሥጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” (ዮሐንስ 14:16-17) የሕይወትን ሩጫ ብቻችንን አንሮጥም - አጽናኙ ከእኛ ጋር ብቻ ሳይሆን በውስጣችን ሆኖ ስንሮጥ እና ዓይኖቻችንን “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ በሆነው በኢየሱስ” ላይ ስናተኩር እኛን ለማጠናከርና ለመደገፍ በእኛ ውስጥ ይኖራል (ዕብ. 12:2)።

ይህንን ማጥኛ ሳዘጋጅ፣ መንፈስ ቅዱስ በተለየ ሁኔታ በግለሰብ ደረጃ እና እንደ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ እንዲያነሳሳን እጸልያለሁ።

ከእግዚአብሔር ጋር ጠንካራ ግንኙነት ከመፍጠር የበለጠ አስፈላጊ ነገር ሊኖር አይችልም።

ስለዚህ፣ እርሱን መውደድንና በእርሱ መኖርን ለመማር ኑ አብረን እናጥና።

ኒና አቼሰን በጀነራል ኮንፍረንስ የ”Alive in Jesus” የሰንበት ትምህርት የሥርዓተ ትምህርት አስተዳዳሪ እና ከፍተኛ አዘጋጅ ነች። ሌሎች እግዚአብሔርን በጥልቀት እና በግል በቅዱስ ቃሉ አማካኝነት እንዲያውቁ ለማነሳሳት እና ለማስታጠቅ ትኖራለች። አቼሰን ከባለቤትዋ ከማት ጋር የምትኖር ስትሆን አብረው ሶስት ልጆች አፍርተዋል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL