የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


ኅዳር 12 - 18

9ኛ ትምህርት

Nov 21 - 27




ነቢያትን መፈተን



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። ዳንኤል 10፥7-19፣ ዘዳ 13፥1-5፣ ኢሳ 8፥20፣ ዮሐ 11፥25፣ የሐዋ 15፥36-39፣ ኤር 28፥9፣15-17።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡”ወዳጆች ሆይ፥ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፥ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደ ሆነ መርምሩ፤ ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና” (1ኛ ዮሐንስ 4፥1)።

ትክክለኛ እንቁ በምድር ላይ ከሚገኙት ነገሮች ሁሉ እጅግ ዋጋ ያለው የከበረ ድንጋይ ነው። በርግጥ ብዙ ሌሎች ነገሮች እንቁ እንዲመስሉ ተደርገው ሊሰሩ ይችላሉ፣ ነገር ግን ዋጋ ቢስ ናቸው። ዕንቁ ትክክለኛ ወይም የውሸት መሆኑን እንዴት ማወቅ እንችላልን? የተሻለው መንገድ መፈተን ነው። አንዳንድ ፈተናዎች ቀላል መሳሪያዎችን በመጠቀም በቤት ውስጥ ሊደረጉ ይችላሉ። ሌሎች ሙያዊ ችሎታን ይፈልጋሉ። አብዛኞቹ መፈተኛዎች በራሳቸው የተረጋገጠ ውጤት ላያስገኙ ይችላሉ። ነገር ግን ዕንቁ በርካታ ፈተናዎችን ካለፈ ትክክለኛ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን ይቻላል።

ዕንቁ በምድር ላይ ካሉ እጅግ ጠንካራ ነገሮች አንዱ ነው። ከብርታቱ ምልክቶች አንዱ ከፍ ያለ የሙቀት ኃይል መቋቋም መቻሉ ነው። የተለያዩ የሙቀትና የእንቅስቃሴ ኃይሎችንም መቋቋም ይችላል። እንቁን ለመፈተን አግላችሁ በጣም በቀዘቀዘ ውሀ ውስጥ መክተት ነው። እውነተኛ እንቁ አይበላሽም የውሸት እንቁ ግን ይበታተናል።

የትንቢት ስጦታ ከእንቁ ይልቅ የከበረ ነው። ነገር ግን አንድ ሰው ስጦታው አለኝ ስላለ ብቻ እንዲያው በደፈናው ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። መፈተን አለበት። በዚህ ሳምንት የትንቢቶችን እውነተኛነት መፈተኛ ደንቦችን እናጠናለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለህዳር 19 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ህዳር 13
Nov 22

የመለኮት ሚና።


እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡበት ጊዜ ለህዝቡ ስለ ትንቢት ስጦታ ሲነግራቸው እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ቃሌን ስሙ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በህልም አነግረዋለሁ”(ዘሁ 12፥6)።

ትንቢታዊ መልዕክት መለኮትን (ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ኃይልን) ያካትታል። የሰው ተራ አስተያየት ወይም ስሜት አይደለም። ነቢይ በራዕይ ወይም በሕልም በቀጥታ ከእግዚአብሔር መልዕክት ይቀበላል (ዳንኤል 8፥1፣ኢሳያስ 1፥1፣ የሐዋ 9፥10...ይቀጥላል)። በተጨማሪም በግልጽ የሚታይ አካላዊ ለውጥን ያሳያል። ዳንኤል በራዕይ ላይ ሳለ የደረሰበትን አንዳንድ የአካል መለወጦች ይዘርዝሩ። ዳንኤል 10፥7-19ን ይመልከቱ።



ራዕይ በሚያይበት ጊዜ ዳንኤል ብርታቱን አጣ (ደከመ)። በዚያ በልምምዱ ጊዜ ፈጽሞ በእግዚአብሔር መደገፍ ነበረበት (በእግዚአብሔር ላይ ታመነ)። አብረውት የነበሩት ራዕይ ባያዩም የመለኮት መገኘት ብርቱ ከመሆኑ የተነሳ ፈርተው ሸሹ። እግዚአብሔር የአካል መለዋወጥን በመጠቀም ትንቢቱ ግንዛቤ እንዲኖረው ያደርጋል። ዘዳግም 13፥1-5 ስለ ትንቢታዊ ስጦታ ምን ያስተምረናል?



ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ኃይል ቢከሰትም ይህ አይነት ሁኔታ የሚደርስበት ሰው ሁል ጊዜ መለኮታዊ ምሪት ተቀበለ ማለት አይደለም። ሰይጣን ከተፈጥሯዊ ውጪ የሆነ ኃይል ሊያሳይ ይችላል። አንድ ምልክት በተናጠል (ብቻውን) ትንቢታዊ አገልግሎት ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ነቢያት ከአካል መለዋወጥ በተጨማሪ በሌሎች መፈተኛዎች መፈተን አለባቸው። ከተፈጥሮ ውጪ ክስተቶች ብቻ የትንቢታዊ ስጦታ እውነተኛነት መፈተኛ ሊሆኑ አይችሉም። የመጽሃፍ ቅዱሳዊ መፈተኛዎች ሁሉ መታየት አለባቸው። አሳዛኙ ነገር ታሪክ በሀሰተኛ ነቢያት የተሞላ ነው (ማቴ 7፥15ን ይመልከቱ)። በአንዳንድ ባህሎች ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ክስተቶች የተለመዱ ናቸው። ታዲያ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ ክስተት ሁሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ መሆኑን ለማወቅ እጅግ መጠንቀቅ ያለብን ለምንድነው?

ህዳር 14
Nov 23

ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መጣጣም


ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መጣጣም/መስማማት መስማማት

እኛ ሰዎች በቃላችን ባንቆምም እግዚአብሔር ግን አይዋሽም (ዘሁ 23፥19ን ይመልከቱ)። በነቢያት በኩል የሚሰጣቸው ትንቢታዊ መልዕክቶች ይህኑ የማይዛነፍ እውነተኛነቱን ያሳያሉ። ኢሳያስ 8፥20ን ያንብቡ። ምን ወሳኝ ነጥብ ይጠቁማል?



የትንቢታዊ ስጦታ መመዘኛ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ነቢያት የሚናገሩት ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር መስማማት አለመስማማቱ መፈተን አለበት። እውነተኛ ነቢይ መጽሐፍ ቅዱስን አይቃረንም፣ አያጣጥልም ወይም ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ሰዎችን አያወናብድም። በሀሰተኛ ነቢያት እንዳይታለሉ ወይም እነርሱን እንዳይከተሉ ነገር ግን እግዚአብሔርን እንዲከተሉ እንዲረዳቸው ሰዎች ቃሉን ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው።

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ነቢያት ትንቢታዊ መልእክታቸውን ለማጠናከር ከእነርሱ በፊት የነበሩትን ነቢያት ይጠቅሳሉ። እነዚህ ነቢያት ካለፉት ትንቢቶች አዲስ ማብራሪያዎችን ያክላሉ እንጂ በፍጹም ተቃራኒ መልዕክት አያስተላልፉም። ባለፉት ምዕተ-አመታት እግዚአብሔር ስለሰጠን ትንቢታዊ መልዕክቶች እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል? 2ኛ ጴጥ 1፥19-21፣ ሮሜ 15፥4፣ ያዕ 1፥17።



የድነት ዕቅድን ለመረዳት የብሉይ ኪዳን መሠረት ያለው እገዚአብሔር ራሱ በዘፍጥረት 3፥15 ላይ በሰጠው የመጀመሪያው ተስፋ ውስጥ ነው። የመስዋዕቱ ስነ- ስርአት የዚያ የማዳን ዕቅድ ምሳሌያዊ መግለጫ ነበር። ነገር ግን የእግዚአብሔር በግ ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ ከሰዎች መካከል በመኖሩ፣ በመሞቱና በመነሳቱ ተስፋ እንዴት እንደሚፈጽም በተከታታይ ለነቢያት ተብራርቷል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባ የሚያሳየው ደግሞ እግዚአብሔር እውነቱን የሚገልጠው ሰዎች ሊያስተውሉት በሚችሉት መንገድ መሆኑን ነው። በተከታታይ ትውልዶች ሰዎች ቃሉን የማስተዋል ችሎታቸው ጠለቅ እያለ ይሄዳል። “የእውነቱ መገለጥ” ወይም “የእውነት እድገት” የሚባለው ለዚህ ነው። ይህ ማለት አዲስ ትውልድ ካለፈው ትውልድ ይልቅ እውነቱን በበለጠ ለመረዳት ይችላል ማለት ነው። ነገር ግን አንድ መገንዘብ የሚገባን ወሳኝ ነገር አለ። አዲሱ እውቀት የቀድመውን እውቀት የሚቃረን መሆን የለበትም።

ህዳር 15
Nov 24

የክርስቶስ ስጋ መልበስ


1ኛ ዮሐንስ 4፥1-3 የሚነግረን ክርስቶስ ስጋ ለብሶ መምጣቱን የማመን ፈተና ከሌሎች ታላላቅ ሃይማኖቶች የመጡ ነቢያት እንደሆኑ የሚናገሩትን ወይም ከማንኛውም ሃይማኖት ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው ከመንፈሳዊው ዓለም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚናገሩ ሰዎች ክርስቶስ ሥጋ ለብሶ መምጣቱን ሳያምኑ ነቢያት ነን ቢሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው እናውቃለን። “ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም” (1ኛ ዮሐ 4፥3)።

ዮሐንስ ይህን ጥቅስ ሲጽፍ ክርስቶስ ሰው ነኝ ይላል እንጂ ሰው አይደለም እያሉ ስለሚያስተምሩ ሀሰተኛ መምህራን እያሰበ ነበር። ይህ ፈተና ከዚህም ያልፋል። መፈተኛው ነቢይ ነኝ የሚለው ሰው ክርስቶስ ስጋ ለብሶ በምድር ላይ የኖረ ትክክለኛ ሰው ነው ብሎ ማመኑ ብቻ እውነተኛ ነቢይ አያደርገውም። አብዛኞች ክርስቲያኖች ስለ ኢየሱስ ይህን ያምናሉ። የዮሐንስ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ፣ ለአንድ የተወሰነ ሁኔታ የተፈለገ ቢሆንም፣ ለኋለኞቹ ትውልዶች የሚያስፈልጉ አስፈላጊ (ወሳኝ) እውነቶችን የያዘ ነው። የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ምን ይነግሩናል? ዮሐ. 3:16፤ 2ኛ ቆሮ. 5:21፤ ዮሐ. 11:25፤ ዕብ. 4:14፣ 15፤ ዮሐ. 14:1-3።





እውነተኛ ነቢያት ክርስቶስ ስጋ የለበሰ መለኮትና በርግጥም ሰው መሆኑን ማመንና ማስተማር አለባቸው። ስለ ክርስቶስ ሙሉ እውነት--ስለ ተልዕኮው፣ ስለ ኃጢአት የለሽ ሕይወቱ፣ ስለ የስርየት ሞቱ፣ ስለ ትንሳኤው፣ በሰማይ ስለሚያከናውነው የሊቀ ክህነት አገልግሎቱና ስለ ዳግም ምጻአቱ የተሟላ እውነት ማቅፍ አለባቸው። ይህ ክርስቶስ በምድር ላይ ስለ መኖሩ በሀሳብ ተስማምቶ ብቻ የሚታለፍ ነገር አይደለም። የነቢይ መልእክት ዋናው ትኩረቱ ኢየሱስ ላይ ነው እንጂ እንዲሁ እግረ መንገዱን ነካ አድርጎ የሚያልፈው ርዕሰ አይደለም። መልእክቱ ወይም መልዕክቷ ሰዎችን ከክርስቶስ ጋር የሚያድን ግንኙነት ወደ መፍጠር መምራት አለበት።

በመንፈስ ቅዱስ የተመራ ትንቢታዊ የእግዚአብሔር ቃል የንጋት ኮክብ የሆነው ኢየሱስ በውስጣችን ያለውን ጨለማ እስኪያስወግድ ድረስ በልባችን ውስጥ እንዲነጋና ትንቢታዊው ስጦታው ከእርሱ ጋር አቆራኝቶን በቀጣይነት ወደ እርሱ እንዲያመለክተን ማድረግ ነው።

ክርስቶስን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ነቢያት የራሳቸውን ተከታዮች አይሰበስቡም፣ ወይም ራሳቸውን ከፍ ከፍ አያደርጉም (የሐዋ 4፥12)። መልእክቱን እንዲያደርሱ የተላኩባቸውን ሰዎች ያገለግላሉ እንጂ ሰዎቹ እንዲያገለግሏቸው አያደርጉም። ይህ እንዳለ ሆኖ በነገው ክፍል እንደምናየው፣ የእግዚአብሔር ነቢያት እንደ እኛ ሰዎች ነበሩ። እንደ ሁላችንም ወንጌሉ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኞች ነበሩ። ክርስቶስ፣ ሙሉ በሙሉ አምላክ፣ በእኛ ምትክ የሀጥያታችንን ሸክም ተሸክሞ መሞቱን ማስተዋል የእምነታችን ማዕከል የሆነው ለምንድን ነው? ይህን አስተምሮ ካላስተዋልነው ምን ይቀርብናል?

ህዳር 16
Nov 25

መልካም ፍሬዎች።


በተራራው ስብከት ላይ (ማቴ ምዕራፍ 5-7) ክርስቶስ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያንን መሰረት ጣለ። የዚያ መሠረት አንዱ ክፍል ትንቢታዊ አገልግሎት ነበር። ታድያ ስለ ሐተኛ ነቢያት አስጠነቀቀ። “በፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” አለ (ማቴ 7፥20)። የፍሬ ጥራቱን ለማወቅ ጊዜ ይወስዳል። ፀባዩን (ባህርዩን) ወይም ፀባይዋን በመመልከት መልዕክቱ ወይም መልእክቷ ምን ውጤት እንደሚያስገኝ በመመልከት ነብዩ ወይም ነቢይቱ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ እያቀረቡ ወይም ከእርሱ እያራቁ እንደሆነ ማየት ይቻላል። ዮሐ 1፥1-3፣ የሐዋ 15፥36-39 እና ገላትያ 2፥11-14ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ነቢያት ምን ያስተምሩናል?



ሆኖም ነቢይ መሆን አንድን ሰው ኃጢአት የለሽ ወይም የማይሳሳት አያደርገውም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ የሚሆኑትን እነ ዮሐንስን፣ እነ ጳውሎስንና እነ ጴጥሮስን እናያለን። እንከን የለሽ እግዚአብሔር ብቻ ነው። መልእክተኞቹ ግን ጉድለት አይታጣባቸውም። ነገር ግን አቅጣጫቸው ወደ እግዚአብሔር ነው። ነቢያት በአኗኗሯቸው መልዕክቱን የሚፃረር ፀባይ በማሳየት መልዕክቱን ማበላሸት የለባቸውም።

ማንኛውም ነቢይ ክርስቶስ የኖረውን አይነት ፍጹም ኑሮ መኖር አይችልም። ነገር ግን እውነተኛ ነቢያት የእግዚአብሔርን መንግስት ደንብና አኗኗር ይከተላል (ማቴ 7፥16-20)። የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነኝ እያለ አኗኗሩ ግን ሲያስተላልፈው የነበረውን መልዕክት በጭፍን ከተፃረረ ያ አይነት ሰው ሊታመን አይገባውም።

የነቢይነት ስራ ከባድ ቢሆንም,ብዙ ነቢያት “መልካም ፍሬ” አሳይተዋል። ለምሳሌ ሙሴ እስራኤላውያንን በምድረ በዳ በጥሩ ስኬት መራቸው (ዘዳ 34፥10-12)። ሀጌ 19 ዓመት ተቋርጦ የነበረውን ሁለተኛውን ቤተ መቅደስ እንዲሰሩ የይሁዳን ነዋሪዎች አደፋፍራቸው (ሐጌ 1፥12)። የኢሳይያስ የማያፈገፍግ መልዕክት አራት ነግስታትን በአስቸጋሪ ጊዜያት መራ። መልእክቱም ወደ መሲሁ ያመላክት ነበር (ኢሳ 39፥5ና ኢሳ 53፥4-6)። የዳንኤልን ከልብ የመነጨ ኑዛዜ (ዳንኤል 9፥15)፣ የኤርምያስንም ልባዊ ቆራጥነት ልንረሳ አንችልም (ኤርምያስ 9፥1)። የእግዚአብሔር ነቢያት ቢሰደዱና ቢበደሉም የእውነተኛ ነቢያት ዋና መስፈርት የሆነውን ለእግዚአብሔር እና ለህዝቡ ፍቅራቸውን ያሳዩ ነበር። የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮች በስራቸው እና በፀባያቸው ስንት ጊዜ አሳዝነዎታል? ከዚያ ልምምድ ምን አይነት ጠቃሚ ትምህርት ምማር ይችላሉ?

ህዳር 17
Nov 26

የተፈጸሙ ትንቢቶች።


ሰዎች ነቢይ የወደፊቱን የሚተነቢይ ነው ብለው ያስባሉ። ይህ የነቢይ አንዱ ሥራ ነው። የነቢይ ስራ ሌላም ብዙ ነገሮችን ያካትታል። ነቢያት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር እንዲመለሱ ይመራሉ፤ ምክርን፣ ማስጠንቀቂያንና ማደፋፈርንም ያበረክታሉ (ይሰጣሉ)። ሰዎች ወደፊት የሚሆኑ ክስተቶችን እንዲያውቁና እንዲዘጋጁ ከማድረግ አልፎ፣ ነቢያት የወደፊቱን ለምን ይተነብያሉ? ኤርምያስ 28፥9፣ 15- 27ን ይመልከቱ።



ነቢይ የሚፈተንበት አንዱ ሌላው መስፈርት ትንቢቱ መፈፀሙ ነው። የእውነተኛ ነቢይ ትንቢት ልክ እንደተናገረው መፈጸም አለበት። “ነቢይ በእግዚአብሔር ስም በተናገረ ጊዜ የተናገረው ነገር ባይሆን ባይመጣም ያ ነገር እግዚአብሔር ያልተናገረው ነው፣ ነብዩ በድፍረቱ ተናግሮታል እሱን አትፍራው (ዘዳ 18፥22)። ይህ ፈተና አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ትንቢቶች ቅድመ ሁኔታ ያዘሉ ናቸው። ቅድመ ሁኔታዎቹ ካልሆኑ ትንቢቶቹ ላይፈጸሙ ይችላሉ።

ይህን መርህ በዮናስና ለነነዌ በሰጠው ማስጠንቀቂያ ውስጥ እናያለን። የዮናስ መልዕክት እጥር ምጥን ያለችና ግልጽ ነበረች። “በአርባ ቀን ውስጥ ነነዌ ትገለበጣለች” (ዮናስ 3፥4)። ነገር ግን ትንቢቱ አልተፈጸመም። ለምን? ኤርምያስ 18፥7-10ን ያንብቡ። ይህ በሁኔታዎች ስላሚደገፈው ትንቢት ምን ያስተምረናል?



ቅድመ ሁኔታን ያዘሉ ትንቢቶች ህዝቡ ለእግዚአብሔር መልእክት በሚመልሱት መልስ ላይ ይተማመናል። ህዝቡ ሀሳባቸውንና ስራቸውን ከቀየሩ የተነገረው ትንቢት ላይፈፀም ይችላል። የነነዌ ሰዎች የዮናስን ትንቢት ሰሙና መንገዳቸውን ቀየሩ። ስለዚህ እግዚአብሔር አላጠፋቸውም። ቀጣዮቹ ትውልዶች ግን እንደገና ወደ ክፋታቸው ሲመለሱና ነነዌ እንደገና ክፉ እና ጨካኝ ስትሆን እግዚአብሔር አጠፋት። እግዚአብሔር ወደፊት የሚሆነውን ያውቃል። እኛ ግን አናውቅም። ምርጫዎቻችን ወደፊት ምን እንደሚደርስብን ወሳኝ ናቸው። ቅድመ ሁኔታዎችን ያዘለ የትንቢት ሀሳብ ማስተዋል ለምን ይጠቅማል? ይህ ግንዛቤ የመጽሀፍ ቅዱሳዊውን እውነት በበለጠ ለማስተዋል እንዴት ይረዳናል?

ህዳር 18
Nov 27

“ቅመሱና እዩ


ቅመሱና እዩ”

የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን የኤለን ጂ ዋይትን ትንቢታዊ ስጦታ መቀበልን በተመለከተ፣ ከመጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት የገጠማቸውን የሚመስል የአቀባበል ችግር ገጥሟታል። ኤለን ጂ ዋይት በታኅሳስ ወር 1844 የመጀመሪያ ራእይዋን ስትቀበል አንዳንድ ሰዎች ነቢይነቷን ሊቀበሉ አልፈለጉም። ይህ ሁኔታ ሰንበት ጠባቂዎች አድቬንቲስቶችን (በኋላ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የተባሉትን) የኤለን ጂ ዋይትን የነቢይነት ስጦታ የሚደግፍ መከራከሪያ (ማስረጃ) ወደ ማዘጋጀት መራቸው።

መጀመሪያ፣ ትንቢታዊ ስጦታ እስከ ዘመን መጨረሻ ድረስ እንደሚቀጥል የሚያሳይ ሥነ መለኮታዊ መረጃ አቀረቡ። መጽሐፍ ቅዱስ ዘመናዊ የትንቢት ስጦታ እንደሚኖር ይደግፋል እያሉ ተከራከሩ። ኢዩኤል 2ን፣ ራዕይ 12፥17ን እና ሌሎችን ጥቅሶች በመጥቀስ “በመጨረሻ ጊዜ” የትንቢት ስጦታ እንደሚኖር ማስረጃ አቀረቡ። እንዲያውም የቅሬታዋ ቤተ ክርስቲያን እንዱ መለየዋ የትንቢት መንፈስ ስጦታ መሆኑን ተከራከሩ። (Gerald ___, “The gift of prophecy and God’s Remenant church” The gift of prophecy chapter 4)።

ሁለተኛ፣ ቀደምት አድቬንቲስቶች የኤለን ጂ ዋይት ስጦታ በአማኞች ላይ መልካም ተጽኖ አስገኝቷል ብለው ዘገቡ። ለምሳሌ በ1840ዎቹ መጨረሻ ላይ የተደረገውን የሰንበት ጉባዔ (ኮንፍራንስ) ይከታተሉ የነበሩ አማኞች በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮዎች ላይ ባልተስማሙ ጊዜ አንድ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። በሚቀጥሉት አያሌ አስርት ዓመታትም ስጦታዋ “መልካም ፍሬ” ማፍራቱን ቀጥሏል። ጽሑፎቿም በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የእምነት ማህበረሰብ ውስጥ ተጽእኖ ማሳደሩን ቀጥለዋል።

ሦስተኛ፣ ኤለን ጂ ዋይትን ከጥቃት ለመከላከል ያቀረቡት መከራከሪያቸው (ማስረጃቸው) ደግሞ ራእይ በምታይበት ጊዜ ከተፈጥሯዊ ውጪ የሆኑ ሁኔታዎችን መለማመዷ ነው። ባለፈው እንደጠቀስነው በራዕይ ላይ ስትሆን ኤለን ጂ ዋይት ከተፈጥሮ ውጪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ሆና ከዚህ በፊት ያላወቀቻቸው የወደፊቱ ክስተቶች እንደተገለጡላት፣ ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የአካል ብርታት እንዳገኘች፣ ራእይ የምታይበትን ጊዜና ሁኔታ መቆጣጠር እንደማትችል መናገራቸው ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች ዛሬም የኤለን ጂ ዋይትን ነቢይነት ይቀበላሉ፣ ይደግፋሉም። እነዚህ መከራከሪያዎች (መረጃዎች) ሁሉ መልካም ሳሉ ለኤለን ጂ ዋይት ሰጦታ ዋናው ማስረጃ ግን በጽሑፎችዋ የተገለጠው የራሷ የህይወት ተሞክሮ ነው። ባለመዝሙሩ ዳዊት እንደሚለው “እግዚአብሔር መልካም እንደ ሆነ ቅመሱ እዩም” (መዝ 34፥8)። ነቢይነቷን መገምገም የምንችለው ጽሑፎቿን በጸሎት ስንመረምር ብቻ ነው።

ንባባችንን ወይም ምርመራችንን ለመጀመር አንዱ ቦታ ሀይለኛ የሆነችውን ትንሿን ወደ “ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ” የምትለውን መጽሐፍ ማንበብ ነው። ከዚያም 5 ጥራዝ ያለውን “Conflict of the Ages” የሚለውን መጽሐፍ በማንበብ ግምገማችንን ብንቀጥል ይመረጣል። ይህ መጽሐፍ ታላቁን ተጋድሎ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ዮሐንስ ይዘረዝራል። መጽሐፍቷ በወረቀትም ሆነ በኤሌክትሮኒክ መረጃ ማሰራጫዎች በቀላሉ ይገኛሉ (EG writings. Org ይመልከቱ)። መጽሐፍቷም ወደ ብዙ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL