በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመጋቢት 16–22

አንደኛ ትምህርት

March 25 - 31


የጴጥሮስ ስብዕና



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ. 5:1–11፣ ማቴ. 16:13–10 17፣ ማቴ. 14:22–33፣ ሉቃ. 22:31–33፣ 54–62፣ ገላ. 2:11–11 14፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ነገር ግን የነፋሱን ኃይል ባየ ጊዜ ፈራ፤ መስጠምም ሲጀምር ‘ጌታ ሆይ አድነኝ!’ ብሎ ጮኸ፡፡ ኢየሱስም ወዲያውኑ እጁን ዘርግቶ ያዘውና ለምን ተጠራጠርህ? ‘አንተ እምነት የጎደለህ ’ አለው” (ማቴ. 14:30-31)፡፡



ጴጥሮስ ስሙን የያዙ የሁለት መጻሕፍቶች (1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ) ደራሲ ነው፡፡ ከቀደሙት የየሱስ ተከታዮች መካከል አንዱ የነበረው ጴጥሮስ በጌታ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ከየሱስ ጎን የነበረ ሲሆን ባዶውን መቃብር ከተመለከቱት የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት መካከልም አንዱ ነበር፡፡ ከዚህ አኳያ የካበተ ተሞክሮ ባለቤት የነበረው ጴጥሮስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ እንዲህ ሲል ጽፎአል “ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ኃይልና ስለ መምጣቱ የነገርናችሁ እኮ የእርሱን ግርማ በዐይናችን አይተን እንጂ፤ በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት ተከትለን አይደለም” (2ጴጥ. 1:16)፡፡



ጴጥሮስ--አንድ ጊዜ በድሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ በሽንፈቱ በወንጌል መልእክቶች ተደጋግሞ ተወስቶአል፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ከየሱስ ጋር በነበራቸው ግንኙነት አፈ- ቃላጤአቸው እርሱ ነበር፡፡ ከየሱስ ትንሳኤና ዕርገት በኋላ ጴጥሮስ ስመ ጥር የቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነ፡፡ እንደ ገላትያ መልእክት ሁሉ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ስለ እርሱ ይናገራል፡፡

ከሁሉ በላይ ጴጥሮስ ስህተት ስለ መሥራት፣ ይቅር ስለ መባል እንዲሁም በእምነትና ራስን ዝቅ አድርጎ ወደ ፊት ስለ መራመድ ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ የእግዚአብሔርን ጸጋ በግሉ የተለማመደው ጴጥሮስ--ያንን ተመሳሳይ ጸጋ ለመለማመድ ለምንፈልግ ሁሉ ካጠገባችን የማይርቅ ብርቱ ድምጽ ሊሆነን ይችላል፡፡

መጋቢት 17
26-Mar

ከእኔ ተለይ!


ጴጥሮስን መጀመሪያ የምንተዋወቀው በገሊላ--በዓሣ አስጋሪነት ሙያ ተሰማርቶ በነበረበት ወቅት ነው (ማቴ. 4:18፣ ማር. 1:16፣ ሉቃ. 5:1–11)፡፡ ጴጥሮስ ዓሣ ለማጥመድ ሌሊቱን ሙሉ መረቡን ዘርግቶ ጥሎ ቢያድርም አንድም ጠብ ያለለት ነገር አልነበረም፡፡ ሆኖም እርሱና የሥራ ባልደረቦቹ የየሱስን ትእዛዝ ተቀብለው ዳግመኛ መረባቸውን በባህሩ ላይ ጣሉ፡፡ ጴጥሮስና ጓደኞቹ ጀልባዎቻቸው መስመጥ እስኪጀምሩ ያንን ሁሉ ዓሣ መያዛቸውን ሲመለከቱ ምን ያህል ተደንቀው እንደ ነበር ለመገመት አያዳግትም፡፡ ይህን ታምራት ከተመለከቱ በኋላ ወደ አእምሮአቸው የመጣው ምን ሊሆን ይችላል?

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ሉቃ. 5፡1-9፡፡ በሉቃ. 5፡8 ጴጥሮስ የሱስን የተናገራቸው ቃላቶች ምን ነበሩ? ማለትም--ይገኝበት ስለነበረው መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ዓይነት መረዳት ይሰጡናል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ጴጥሮስ ቀደም ሲል ስለ የሱስ የሚያውቃቸው ነገሮች አግራሞት ሳይፈጥሩበት እንዳልቀሩ ይታመናል፡፡ ይህ ታምራት ከመሆኑ አስቀድሞ የሱስ መረባቸውን ወደ ባሕሩ እንዲጥሉ ሲነግራቸው ሌሊቱን ምንም አለመያዛቸውን ተከትሎ--የየሱስ አነጋገር በጴጥሮስ ላይ ጥርጣሬ ቢጤ ያጫረ በሚመስል መልኩ “ ‘አንተ ካልክ ግን መረቦቹን እጥላለሁ’ ” በማለት ነበር የመለሰው፡፡ ሁናቴው ጴጥሮስ አስቀድሞ ስለ የሱስ የሚያውቀው አንዳች ነገር እንደ ነበር አመላካች ሲሆን--ይህን ማወቁ ደግሞ እንዲታዘዝ ገፋፍቶታል፡፡ ጴጥሮስ ከዚህ ክስተት አስቀድሞ ከየሱስ ጋር እንደ ነበር የሚያሳዩ ተጨባጭ አመላካቾች መኖራቸው እሙን ነው፡፡

ከዓሣዎቹ ታምራት አስቀድሞ ስለ ነበረው ሁናቴ ሉቃ. 5፡3 ቁልፍ ፍንጭ እንደ ያዘ ይታመናል፡፡ “ከጀልባዎቹም መካከል የስምዖን ወደ ነበረችው ገብቶ፣ ከምድር ጥቂት ፈቀቅ እንዲያደርጋት ለመነው፤ ከዚያም ጀልባዋ ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን ያስተምር ጀመር፡፡” ምናልባት በጴጥሮስ ላይ መጀመሪያ ጥልቅ አግራሞት የፈጠሩት እነዚህ የሱስ የተናገራቸው ቃላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ታምራቱ ገቢራዊ ከሆነ በኋላ ጴጥሮስ ከራሱ ኃጢተኝነት ጋር ሲያነጻጽር እጅግ ቅዱስ የሆነ ነገር በየሱስ ላይ አስተውሎ ነበር፡፡ ጴጥሮስ ኃጢአተኝነቱን ማስተዋሉና ይህንኑ በይፋ ለመቀበል ፈቃደኛ መሆኑ ልቡ ምን ያህል ለጌታ ክፍት እንደ ነበር ያሳያል፡፡ ከዚህ አኳያ በጌታ መጠራቱ ብዙም ላያስገርም ይችላል፡፡ ጴጥሮስ የቱንም ያህል ስህተት ቢኖርበት፣ ስህተቶቹ ብዙ ቢሆኑና የፈለገውን ያህል ዋጋ ቢያስከፍሉት--እርሱ ግን ጌታን ለመከተል የተዘጋጀ መንፈሳዊ ሰው ነበር፡፡

በሉቃ. 5፡11 የምናገኘው ወሳኝ መርኅ ምንድን ነው? ጥቅሱ የሱስ ከእኛ ስለሚፈልገው ቁርጠኝነት ምን ይነግረናል? ዓሣ አስጋሪዎቹ በምርት ተትረፍርፎ የተመለከቱትን ሙያቸውን ለመተው ፈቃደኞች መሆናቸው ምን ሊነግረን ይገባል?

መጋቢት 18
27-Mar

ክርስቶስን እንደ መሲህ መቀበል


ከታላላቆቹ የየሱስ ታሪኮች አንዱ ከጴጥሮስ ጋር ያደረገው ንግግር ነው፡፡ የሱስ እርግጠኛ መሲህነቱን ሊገልጥ የሚችል ምልክት እንዲያሳያቸው የፈለጉ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሊፈትኑት (ማቴ. 16፡1-4) ከመጡ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ የሱስ ቀደም ብሎ በጥቂት እንጀራና ዓሣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ስለ መገበባቸው ታምራቶች ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተነጋግሮ ነበር፡፡ ይህን ታምራት ያደረገው ደቀ መዛሙርቱ “ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን እርሾ” (ማቴ. 16:11) እንዲጠበቁ ከማስጠንቀቅ ዐውድ ነበር፡፡

በማቴ. 16፡13-17 ምን እየሆነ ነው? የሱስ ለጴጥሮስ የተናገራቸው ቃላት አንደምታ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በጥቅሱ--ጴጥሮስ በየሱስ ላይ ያለውን እምነት በድፍረት ሲናገር ይደመጣል፡፡ ጴጥሮስ ክርስቶስን እንደ መሲህ አምኖ የተቀበለበትን ይህን ትዕይንት ሌሎቹም ደቀ መዛሙርት ተጋርተውታል፡፡ ምንም እንኳ ጴጥሮስን ጨምሮ ደቀ መዛሙርቱ ገና ሊማሯቸው የሚገቡ ትምህርቶች ቢኖሩም ነገር ግን ይህ ለየሱስ አገልግሎት ወሳኝ ወቅት ነበር፡፡

“ደቀ መዛሙርቱ የክርስቶስን ምድራዊ ንግሥና አሁንም እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ዕቅዱን ረዘም ላሉ ጊዜያት ይፋ ሳያደርግ ቢቆይም ነገር ግን በድኽነትና ራሱን በመሰወር ሁሌም ሊቀጥል እንደማይችል ያምኑ ነበር፡፡ ስለዚህ መንግሥቱን የሚመሰርትበት ጊዜ እንደ ተቃረበ ተሰምቶአቸዋል፡፡ በተቃራኒው የካኅናቱና የኃይማኖት መምህራኑ ጥላቻ ሊገታ ወደ ማይችል ጽንፍ ማምራቱ፣ ክርስቶስ በራሱ ሕዝብ መነቀፉ፣ እንደ አታላይ ተቆጥሮ መኮነኑና እንደ ወንጀለኛ መሰቀሉ--ይህ አስተሳሰብ ፈጽሞ በደቀ መዛሙርቱ አእምሮ አልነበረም፡፡”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 415.

ደቀ መዛሙርቱ ክርስቶስን እንደ መሲህ ከተቀበሉት በኋላ መከራን ሊቀበልና ሊሞት የግድ መሆኑን ያስተምራቸው ጀመር (ማቴ. 16፡21-23)፡፡ ሆኖም ይህ ጽንሰ ሃሳብ ለጴጥሮስ ሊዋጥለት ባለመቻሉ የሱስን እስከ “መገሰጽ” ደረሰ፡፡ የሱስ ግን ወደ ጴጥሮስ ዞር አለና “ ‘አንተ ሰይጣን፤ ሂድ ከዚህ!’ ” (ማቴ. 16:23) አለው፡፡ የሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ከተናገራቸው ሻካራ ንግግሮች ይህ እንደ አንዱ ሊጠቀስ ቢችልም--ስለ እርሱ በጎ ሲል ያደረገው ነው፡፡ የጴጥሮስ ንግግር እርሱ ይፈልገው የነበረውን የገዛ ምኞቱንና በስስት የተሞላ አቋሙን የሚያንጸባርቅ ነበር፡፡ የሱስ ጴጥሮስን በዚያው ቅጽበትና ቦታ ሊያስቆመው የተገባ ነበር (ምንም እንኳ የሱስ በተጨባጭ ይናገር የነበረው ለሰይጣን ቢሆንም ጴጥሮስም መልእክቱን አግኝቶአል)፡፡ ጌታን ማገልገል መከራን መቀበልም እንደሚያካትት ጴጥሮስ መማር ነበረበት፡፡ ጴጥሮስ በዚህ ዙሪያ በተጨባጭ ትምህርት ያገኘ መሆኑን ኋላ ላይ ከጻፋቸው መልእክቶች ለመረዳት ይቻላል (1ጴጥ. 4፡12)፡፡

የግል ፍላጎቶችዎ እግዚአብሔር እንዲያደርጉ ከሚፈልግብዎ ነገሮች ጋር ምን ያህል ይጋጫሉ? በእንደነዚህ ዓይነት ሁናቴዎች መሃል ሆነው ማድረግ የሚኖርቦትን እንዴት ይወስናሉ?

መጋቢት 19
28-Mar

በውሃ ላይ መራመድ


ምንም እንኳ በማቴ. 14፡13-33 ለተጠቀሰው ታሪክ ጥቂት ማመሳከሪያዎችን ማለትም--ማር. 6፡30-52 እና ዮሐ. 6፡1-21 ብናገኝም--ደቀ መዛሙርቱ ከየሱስ ጋር በነበራቸው አብሮነት አያሌ አስደናቂ ነገሮች መመልከት ችለው ነበር፡፡ የሱስ አምስት ትናንሽ እንጀራና ሁለት ዓሣ ብቻ ተጠቅሞ ከአምስት ሺ በላይ ሰዎችን መግቦ ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን አስደናቂ ታምራት ከተመለከቱ በኋላ በአእምሮአቸው ሊመጣ የሚችለው አስተሳሰብ ምን ሊመስል ይችላል?

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ማቴ. 14፡22-33፡፡ ከጌታ ጋር ለምናደርገው የግል ጉዞ ከታሪኩ የምናገኘው አንኳር ነጥብ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሱስ ይህን ሁሉ ሰው የመገበበት ያልተለመደው ትዕይንት ሕዝቡ ለአስደናቂው ኃይል ምስክር እንዲሆን ያስቻለና የሱስ በተፈጥሮአዊው ዓለም ላይ ያለውን የበላይነት በእውነት ማሳየት የቻለ ነበር፡፡ ይህ ታምራት ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ፤ አንተ ከሆንህስ፣ በውሃው ላይ እየተራመድሁ ወደ አንተ እንድመጣ እዘዘኝ” (ማቴ. 14:28) ሲል ድፍረት የተሞላውን ጥያቄ እንዲጠይቅ መንስኤ ሊሆነው እንደቻለ ይገመታል፡፡

እንዴት ያለ እምነት የተገለጠበት መንገድ ነው!

ጴጥሮስ በየሱስ ላይ የነበረው እምነት ተቀባይነት ካገኘ በኋላ በውሃው ላይ ተራምዶ ወደ እርሱ እንዲመጣ ፈቀደለት፡፡ ይህ ሌላው የጴጥሮስ እምነት የተገለጠበት መንገድ ነበር፡፡ ውሃው ከወጀብ ነጻና ሰላማዊ ሆኖ መራመድ አንድ ነገር ሊሆን ቢችልም ነገር ግን ጴጥሮስ የተራመደው ወጀቡ በበረታበት ወቅት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

በዚህ ስፍራ ዐይኖቻችንን ከየሱስ ላይ መንቀል እንደሌለብን የሚያወሳውን--በስፋት የሚታወቀውን አስተምህሮ የምናገኝ ቢሆንም ነገር ግን ከዚህ ተጨማሪ ነጥብም አለ፡፡ የጴጥሮስ በየሱስ መታመን የግድ ነበር፡፡ ያለበለዚያ የጠየቀውን ጥያቄ ባለቀረበ--ያደረገውንም ባልሞከረ ነበር፡፡ ሆኖም ወደ ተግባር ከገባ በኋላ ግን ፍርሐት ፍርሐት ይለው ጀመር፡፡ ፍርሐቱም መስመጥ እንዲጀምር መንስኤ ሆነው፡፡

ይህ ለምን ሆነ? ጴጥሮስ ፍርሐት ቢይዘውም እንኳ በውሃው ላይ እንዲንሳፈፍ ሊያደርገው አይችልም ነበር? የሆነው ሆኖ ጴጥሮስ በራሱ ምንም ማድረግ እንደማይችል ተገንዝቦ ለእርዳታ እንዲጮህ ፈቀደ፡ “ጌታ ሆይ፤ አድነኝ!” (ማቴ. 14:30)፡፡ በዚህን ጊዜ የሱስ እጁን ዘርግቶ ጴጥሮስ የጠየቀውን አደረገ፡፡ የሱስ ምንም ዓይነት አካላዊ ንክኪ ሳያደርግ እንዳይሰምጥ ሊያደርገው ሲችል “እጁን ዘርግቶ” የመያዙ (ማቴ. 14:31) እውነታ ጴጥሮስ በየሱስ ላይ ምን ያህል ሊመካ እንዲሚገባው እንዲያስተውል ሳይረዳው እንዳልቀረ ይታመናል፡፡ በጌታ ኃይል ታምነን በአዲስ ጅማሮ ወደ ፊት በምናደርገው ግስጋሴ ሁናቴዎች አስፈሪ ገጽታ ተላብሰው ስንመለከት የሱስ “ ‘አንተ እምነት የጎደለህ፤ ለምን ተጠራጠርህ?’ ” (ማቴ. 14:31) በማለት ለጴጥሮስ የተናገራቸውን ቃላት እናስታውስ፡፡

መጋቢት 20
29-Mar

ጌታውን መካዱ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ሉቃ. 22:31–34፣ 54–62፡፡ ከጴጥሮስ ውድቀቶች የምንማራቸው ትምህርቶች ምንድን ናቸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በጴጥሮስ የተስተዋለው ቁርጠኝነት መልካም ነበር፡፡ በእርግጥ ጴጥሮስ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት የላቀ ወኔ ለማሳየቱ አንድና ሁለት የለውም፡፡ በየሱስ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ለመመልከት የፈለገው ጴጥሮስ የተከተለው ቢሆንም ነገር ግን ይህን ያደረገው እውነተኛ ማንነቱን ለመሸሸግ በመወሰን ነበር፡፡ እንዲህ ያለው በመልካምና በትክክለኛው ጎዳና ላይ የሚደረግ ተደራዳሪነትና አፈንጋጭነት የሱስ ቀደም ብሎ ያስጠነቀቀውን እንዲያደርገው መንስኤ በመሆን ሦስት ጊዜ ካደው፡፡

የጴጥሮስ ታሪክ እምነትን ወደ ድርድር ማምጣት ውጤቱ ምን ያህል የከፋ ሊሆን እንደሚችል በአሳዛኝ ምሳሌነቱ ጠንካራ ትምህርት ይሰጠናል፡፡

ክርስቲያኖች የእምነቶቻቸውን መሰረታዊ አስተምህሮዎች ለድርድር ሲያቀርቡ ምን ዓይነት አስከፊ ውጤቶች እንደ ተከሰቱ ከታሪክ እናውቃለን፡፡ ምንም እንኳ ራሷ ሕይወት በአብዛኛው በድርድር የተሞላች ከመሆኗ አኳያ ሰጥቶ የመቀበልን መርኅ ለመተግበር ፈቃደኞች ልንሆን የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ሊከሰቱ ቢችሉም ነገር ግን ድርድሩ ከእምነታችን አላባዎች ጋር የተጎዳኘ ሲሆን--ጽኑና ቆፍጣና መሆን ይጠበቅብናል፡፡ እንደ እግዚአብሔር ሕዝብ--በማንኛውም ሁናቴ ውስጥ ብንሆን ፈጽሞ ልንደራደርባቸው የማይገቡ ነገሮችን ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል (ለአብነት ያህል ራእዕ 14፡12 ይመልከቱ)፡፡

የጴጥሮስ ተደራዳሪነትና ውድቀት የጀመረው በጌተሰማኔ መጸለይ ሲገባው ባንቀላፋበት ወቅት ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ እርሱ ይገኝ የነበረበት መንፈሳዊ ሁኔታ ሊመጣ ላለው ነገር ዝግጁነት እንዲኖረው አላስቻለውም፡፡ ነገር ግን በጸሎት ተግቶ ቢሆን ኖሮ “ጌታውን ባልካደ ነበር፡፡”—The Desire of Ages, p. 714.

አዎ--ጴጥሮስ አይወድቁ ዓይነት ውድቀት ወደቀ፡፡ በእርግጥ የእርሱ አወዳደቅ የቱንም ያህል የከፋ ሊሆን ቢችል--የእግዚአብሔር ጸጋ ግን ከዚያ እጅግ የላቀ ነው፡ “ኃጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ” (ሮሜ 5:20)፡፡ ጴጥሮስን ከአውራዎቹ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንዱ ያደረገው ይኸው የየሱስ ይቅርታ ነበር፡፡ ይህ ስለ ተጨባጩ አምላካዊ ጸጋ ብርቱ ትምህርት ይሆነናል፡፡ ውድቀት ሊደርስብን ቢችል እንኳ በእምነት ወደ ፊት መገስገሳችንን እንቀጥል!

አዎ--ጴጥሮስ ይቅር የመባልን ትክክለኛ ትርጉም አውቆአል፡፡ ጴጥሮስ ተጨባጩን ሰብዓዊ ኃጢተኝነቱን ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ የፍቅሩን ጥልቀትና ለኃጢአተኛው ያዘጋጀውን ጸጋ በማጣጣሙ የወንጌልን አስተምህሮ በተዘዋዋሪ ሳይሆን በቀጥተኛ ተሞክሮ ለመገንዘብ ችሎአል፡፡

ጴጥሮስ የሱስን እንዳሳዘነ ሁሉ እኛም ያሳዘኑንን ይቅር ማለትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 21
30-Mar

ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያንን በመምራት ኃላፊነት


በየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ጴጥሮስ በተደጋጋሚ አሥራ ሁለቱን ደቀ መዛሙርት የመምራት ኃላፊነት ይወስድ ነበር፡፡ የተለመደው አፈ ቀላጤያቸውም እርሱው ነበር፡፡ ማቴዎስ የደቀ መዛሙርቱን ስም ሲጠቅስ “መጀመሪያ ጴጥሮስ…” (ማቴ. 10:2) እያለ ይቀጥላል፡፡ እንዲሁም ጴጥሮስ በቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን ስመ ጥር ሚና ነበረው፡፡ በየሱስ ላይ ክህደት በፈጸመው በአስቆሮቱ ይሁዳ ምትክ ደቀ መዝሙር የመሰየም ተነሳሽት የወሰደው ጴጥሮስ ነበር (ሐዋ. 1፡15 -25)፡፡ በጴንጤቆስጤ ዕለት እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ያፈሰሰውን ቃል የተገባ የመንፈስ ስጦታ እየተመለከቱ ለነበሩ ሕዝቦች ሁኔታውን ያብራራው ጴጥሮስ ነበር (ሐዋ. 2፡14-36)፡፡ በየሱስ ስለ ተገኘው የሙታን ትንሳኤ በማስተማሩ የታሰረውና ሊቀ ካህናቱና የአይሁድ ሸንጎ አባላት በተገኙበት የተናገረው ጴጥሮስ ነበር (ሐዋ. 4፡1-12)፡፡ ከአይሁድ ዝርያ ውጪ የመጀመሪያው የየሱስ ተከታይ በመሆን ተቀባይነት ወዳገኘው ቆርኔሌዎስ የተላከው ጴጥሮስ ነበር (ሐዋ. 10፡1-48)፡፡ ጳውሎስ ጌታን ከተቀበለ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ለ15 ቀናት የጎበኘው ጴጥሮስን ነበር (ገላ. 1፡18)፡፡ በእርግጥ ጳውሎስ በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበሩትን የየሱስ ተከታኞች ስብስብ ሲገልጽ ሦስቱን ሐዋርያት ማለትንም ጴጥሮስን፣ የየሱስን ወንድም ያዕቆብንና ተወዳጁን ደቀ መዝሙር ዮሐንስን “አዕማድ” በማለት ይጠራቸዋል (ገላ. 2፡9)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ገላ. 1፡18-19፣ 2፡9፣ 11-14፡፡ ምንም እንኳ ጴጥሮስ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የሰጠው አገልግሎት ሰፊ ቢሆንም ጥቅሶቹ ስለ እርሱ ምን ይናገራሉ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መሪ ቢሆንም፣ በጌታ የሱስ በግልጽ ቢጠራም (“በጎቼን መግብ” [ዮሐ. 21:17])፣ ሰዎችን ነገዳቸውን ባማከለ “ርኵስ ወይም ያልተቀደሰ” ብሎ እንዳይጠራ በራእይ ቢነገረውም (ሐዋ. 10፡28)--ገና እያደገ ሊሄድባቸው የሚገቡ አስፈላጊ ነገሮች ነበሩ፡፡

ቤተ ክርስቲያን በተቋቋመችባቸው በእነዚያ ቀደምት ዓመታት ሁሉም ክርስቲያኖች- ለሕጉ የሚቀኑ ነበሩ (ሐዋ. 21፡20)፡፡ ለሕጉ ይሰጡ ከነበረው ትርጓሜ አኳያ ከአይሁድ ዝርያ ውጪ ከሆነ ሰው ጋር አብሮ ገበታ መቅረብ ችግር ነበረው፡፡ ምክንያቱም ከአይሁድ ውጪ ያለው ዝርያ ንጹህ እንዳልሆነ ይታመን ስለነበር ነው፡፡ ከያዕቆብ ጋር የነበሩ አይሁድ ክርስቲያኖች ወደ ኢየሩሳሌም በመጡበት ወቅት ጴጥሮስ በአንጾኪያ አይሁድ ካልሆኑ ሰዎች ጋር መመገቡን አቁሞ ነበር፡፡

እንዲህ ያለው ባህሪ ለጳውሎስ በራሱ በወንጌል ላይ እንደ ተቃጣ ጥቃት ይቆጠር ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ የጴጥሮስ ድርጊት ግብዝነትን በገሃድ የሚያሳይ ሆኖ ስላገኘው በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረውን ተግዳሮት ለማሳየት ፍርሐት እንዳልነበረው ይታያል፡፡ ጳውሎስ ይህን ዕድል ተጠቅሞ የክርስትናን እምነት ቁልፍ አስተምህሮ--

ጽድቅ በእምነትን ሲገልጽ ይስተዋላል (ገላ. 2፡14-16)፡፡

ምንም እንኳ ጴጥሮስ በየሱስ የተጠራ ቢሆንም ነገር ግን ሊታረሙ ይገባቸው የነበሩ እንከኖች ነበሩት፡፡ ሌሎች የእኛን እንከን ሊያሳዩን ሲሞክሩ ምን ዓይነት ምላሽ እንሰጣቸዋለን?

መጋቢት 22
31-Mar

ተጨማሪ ሃሳብ:


Ellen G. White, The Desire of Ages, “The Call by the Sea,” pp. 244–251, “A Night on the Lake,” pp. 377–382. ጴጥሮስ በዓሣ ማጥመድ ሥራ ይተዳደር በነበረበት--ቀደም ባለው ጊዜ ኃጢአተኝነቱን አምኖ መቀበሉ፣ “ ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ’ ” (ማቴ. 16:16) ብሎ መናገሩ፣ በጌታው ላይ አስከፊ ክህደት መፈጸሙ እንዲሁም በቤተ ክርስቲያን መሪነቱ ከወጣባቸው ከፍታዎችም ሆኑ ካያቸው ዝቅታዎች አኳያ- -በእርግጥ የቁልፍ ስብዕና ባለቤት መሆኑ አያነጋግርም፡፡ በመሆኑም ጴጥሮስ በእንከን የለሹ መንፈስ ቅዱስ እየተመራ ንድፈ ሃሳባዊውን ዕውቀት ሳይሆን ነገር ግን ተጨባጭ ተሞክሮውን መጻፍ ይችላል፡፡ ጴጥሮስ የየሱስን አዳኝ ጸጋ ብቻ ሳይሆን የተለወጠ ሕይወት ባለቤት የሚያደርገውንም ጸጋ ጠንቅቆ ያውቃል፡ “ጴጥሮስ በዚያ ታላቅ ውድቀት ከመጎብኘቱ አስቀድሞ ሁልጊዜም ደፋር፣ አምባገነናዊና እንዳመጣለት የሚናገር ነበር፡፡ ሌሎችን ለማረምና ስለ ራሱ ወይም ስለ ሌላ ነገር ግልጽ መረዳት ሳይኖረው ሃሳቡን ለመግለጽ ሁልጊዜም ዝግጁ ነበር፡፡ ሆኖም ያ የድሮው ጴጥሮስ ተለወጠ፡፡ የተለወጠው ጴጥሮስ ችኩል ከነበረው ፍጹም የተለየ ሆነ፡፡ የቀድሞ ግለቱን እንደያዘ በቀጠለ ቁጥር የክርስቶስ ጸጋ የልቡን ቅንአት ያለማሰለስ ይመራ ነበር፡፡ ችኩል፣ በራሱ የሚመካና ራሱን ከፍ የሚያደርግ በመሆን ፋንታ የተረጋጋ፣ ራሱን የሚቆጣጠርና ለመማር ዝግጁ ሆነ፡፡ ይህም ጠቦቶችንና የክርስቶስን የበግ መንጋዎች ለመመገብ አስቻለው”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 5, pp. 334, 335.

ከእኛ መካከል በተወሰነ መልኩ ከጴጥሮስ ጋር መነጻጸር የማይችል ማን ነው? በሆነ አጋጣሚ ስለ እምነቱ በድፍረት--ማነው ያልቆመ? ይህን ማድረግ ያልሆነለትስ?


የመወያያ ጥያቄዎች:



ጴጥሮስ በየሱስ ላይ እንዲህ ያለውን ክህደት ከፈጸመ በኋላ በዘመኑ ለነበረችው ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለራሱ ለክርስትና እምነት የተጫወተው ሚና ስለ አምላካዊው ጸጋ ምን ይነግረናል? (በተጨማሪ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት አንዱ ክፍል የእርሱ መሆኑን ልብ ይሏል) ከአርሱ መመለስ ምን እንማራለን?

ሰጥቶ ስለ መቀበል ወይም ስለ መደራደር አደጋ ተወያዩ፡፡ ሰጥቶ የመቀበልን መርኅ ገቢራዊ ልናደርግ የምንችልባቸውን ነገሮች እንዴት ማወቅ እንችላለን? ይህን መርኅ ፈጽሞ ገቢራዊ የማናደርገው እንዴት ዓይነት ሁናቴዎች ሲገጥሙን ነው? መደራደር ወይም ሰጥቶ መቀበል በቤተ ክርስቲያን ላይ ውድቀት ካስከተለበት ታሪክ የትኛውን በምሳሌነት መጥቀስ ይችላሉ? ከእነዚህ ክስተቶች ምን ዓይነት ትምህርት መቅሰም እንችላለን?

 ጴጥሮስ አንዳንዶቹን ትምህርቶች የተማረው በአስቸጋሪ ሁናቴዎች ውስጥ በማለፍ ነው፡፡ ሳትዋጋ ንገሥ ቢሉት ግድ ተዋግቼ አለ--እንዲሉ፤ የእርሱን ስህተቶች በመመልከት--እርሱ ባለፈበት አስቸጋሪ መንገድ ሳይሆን ነገር ግን በቀላሉ መማር የምንችለው እንዴት ነው?