በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከግንቦት 19-25

አስረኛ ትምህርት

May 27- June 2


ትንቢትና መጽሐፍ ቅዱስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 53:1– 12፣ ዳን. 7:13-14፣ 2ጴጥ. 1:16–20፣ ማቴ. 17:1–6፣ 2ጢሞቴ. 3:15–17፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ” (2ጴጥ. 1:19)፡፡

የ ጴጥሮስን ደብዳቤዎች ማጥናታችንን ስንቀጥል--ጴጥሮስ በሚጽፈው ነገር ምን ያህል ልበ ሙሉና እርግጠኛ ነበር የተሰኘው ነጥብ መነሳቱ ተገቢ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተመሳሳይ ይህን ነጥብ--ግልጽና ጽኑ እምነት ተላብሰው ስለ የሱስ ክርስቶስና ስለ መስቀሉ ከሚያውጁት ከጳውሎስ መልእክቶችም አኳያ መመልከት እንችላለን፡፡

በዚህ ሣምንት በምናጠናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በጴጥሮስ ውስጥ የነበረውን እርግጥኝነት ጠለቅ ብለን እንመለከታለን፡፡ እንደውም ሐዋርያው ያን ያህል እርግጠኛ መሆን የቻለበትን ምክንያት ይነግረናል፡፡ እኛ “በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ተረት” (2ጴጥ. 1:16) አናምንም በማለት የሚናገረው ጴጥሮስ ሆኖም እንደዚያ ዓይነቱ ተረት እርሱ በኖረበት የባዕድ አምልኮ አራማጅ ማኅበረሰብ መሃል የተለመደ እንደ ነበር ይገልጻል፡፡ ጴጥሮስ በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ላመነበት ነገር እርግጠኛ ነበር፡፡

አንደኛው፡-- ለ “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” (2ጴጥ. 1:8) የዐይን ምስክር መሆኑ፤ ሁለተኛው (ሁሉም ሰው የዐይን ምስክር መሆን እንደማይችል ሁሉ) በእርግጥ በእጅጉ አስፈላጊ ሲሆን ይኸውም ይበልጥ የተረጋገጠልን ትንቢታዊው ቃል ነው (2ጴጥ. 1፡19)፡፡ ጴጥሮስ አሁንም ወደ ብሉይ ኪዳን አምርቶ ስለ የሱስ የተሰጡ ማረጋገጫዎችን--በተለይም ስለ እርሱ ወደ ሚናገረው ትንቢታዊ ክፍል ያመላክታል፡፡ ከነዚህ ጥቅሶች አንዳንዶቹ የሱስ ስለ ራሱ የተጻፉ ትንቢቶችን አስመልክቶ የጠቀሳቸው ለመሆናቸው ጥርጥር የለውም (ማቴ. 26:54፣ ሉቃ. 24:27)፡፡ የሱስና ጴጥሮስ ያን ያህል መጽሐፍ ቅዱስን በጽኑ ከተጠቀሙ እኛም የእነርሱን አርዓያ ለመከተል ምን ያህል መደፋፈር ይኖርብን ይሆን?

ግንቦት 20
28-May

የሱስ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት


እያንዳንዱ የጴጥሮስ ደብዳቤ ገጾች በመልእክቱ ላይ ያለውን ልበ ሙሉነትና እርግጠኝነት ይገልጹልናል፡፡ ስለ ማን እየተናገረ እንደ ነበር በትክክል ያውቅ የነበረው ጴጥሮስ ስለ ምን እንደሚናገር ዕውቀቱ ነበረው፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የብሉይ ኪዳን ጸሐፊዎች ወደ የሱስ ማመላከታቸውን ያውቅ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ጴጥሮስ “ቃልም ሥጋ መሆኑን” (ዮሐ. 1፡14) እንዲያውቅ የረዳው በአምላካዊው ቃል ላይ የነበረው መታመን ነበር፡፡

ጴጥሮስ በ2ጴጥ. 1፡10-12 መልእክቱ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ የሱስ ወዳስተማሩት ትምህርት አንባቢዎቹን ያመላክታል፡፡ ጴጥሮስ እንደሚነግረን ብሉይ ኪዳን ስለ የሱስ ሁለት ወሳኝ እውነቶችን ገልጦልናል፡ ስለ ክርስቶስ መከራና ያን ተከትሎ ስለሚመጣው ታላቅ ክብር (1ጴጥ. 1፡11)፡፡ እነዚህ ሁለት ዘለላዎች በመላው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ገጾች መገኘት ይችላሉ፡፡

ብሉይ ኪዳን ስለ የሱስ በትንቢት የተናገረውን አስመልክቶ የሚከተሉት ጥቅሶች በአንድነት ምን ይሉናል? መዝ. 22፣ ኢሳ. 53:1– 12፣ ዘካ. 12:10፣ 13:7፣ ኤር. 33:14- 15፣ ዳን. 7:13, 14፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------



--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሐዋርያው በ1ጴጥ. 1፡10-12 መልእክቱ አንባቢዎቹ በደኅንነት ታሪክ እጅግ የተለየ ስፍራ እንዳላቸው ያረጋግጥላቸዋል፡፡ እግዚአብሔር ለብሉይ ኪዳን ነቢያት ከገለጠው የበለጠውን ለእነርሱ ገልጦአል፡፡ ምንም እንኳ ነቢያት ለዘመናቸው ሕዝቦች መልእክት ቢሰጡም ነገር ግን የመልእክቶቻቸው ወሳኝ ክፍል እስከ ክርስቶስ የመጀመሪያው መገለጥ ፍጻሜ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡

ነቢያት አስቀድሞ ከተነበዩአቸው መካከል አንዳንዶቹ ፍጻሜ ያገኙት ጴጥሮስ መልእክቱን በጻፈላቸው አንባቢዎች ዘመን ነው፡፡ እነዚህ አንባቢዎች መላእክት ሳይቀሩ ሊያውቁት የተመኙትን ነገር “ከሰማይ በተላከ መንፈስ ቅዱስ ወንጌልን” ባበሠሩላቸው ወገኖች አማካይነት መስማት ችለው ነበር (1ጴጥ. 1፡12)፡፡ አዳኙ የደረሰበትን መከራና ውርደት ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ይልቅ ወንጌል የተሰበከላቸው ሕዝቦች በዝርዝር ብሎም በተጨባጭ ይረዳሉ፡፡ በእርግጥ “ከመከራው በኋላ ስለሚሆነው ክብር” (1ጴጥ. 1፡11) እንደ እኛ ሁሉ እነርሱም መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡ እነዚህ የትንቢቱ የመጀመሪያ ክፍሎች እውን ሲሆኑ መመልከታችን ለመጨረሻው ክፍል ፍጻሜ ማግኘት እርግጠኞች ያደርገናል፡፡

ስንቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በህይወትዎ ፍጻሜ ሲያገኙ መመልከት ችለዋል? ፍጻሜያቸውን ገና የሚጠባበቋቸውስ? ትንቢቶቹ ለእርስዎ ምን ማለት ናቸው? የመጣው ቢመጣ ትንቢቶቹን የሙጥኝ እንዳሉ ፍጻሜያቸውን ተስፋ ማድረግ መማር የሚችሉት እንዴት ነው?

ግንቦት 21
29-May

በታላቅ ግርማ ለተሞላው ትዕይንት የዓይን መስክር መሆን


ጴጥሮስ በየሱስ ላይ እንዴት እምነት ሊኖረው እንደቻለ አስመልክቶ የሚሰጠን ሌላው መረጃ ምንድን ነው? 2ጴጥ. 1:16–18፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ከትንቢታዊው ቃል ባሻገር ጴጥሮስ የሰበካቸው ብዙዎቹ መልእክቶች የራሱ የዓይን ምስክርነት ውጤቶች ናቸው፡፡ የክርስትና እምነት “በሰዎች ጥበብ የተፈጠረ ተረት” (2ጴጥ. 1:16) ሳይሆን ሐዋርያው ራሱ ምስክር በሆነባቸው የዓለም ታረክ አካል በሆኑ ተጨባጭ ክስተቶች የተሞላ እንደሆነ ይነግረናል፡፡

የየሱስ ህይወትና አገልግሎት በተገለጸባቸው በአብዛኞቹ የወንጌል አስፈላጊ ክፍሎች ጴጥሮስን ማግኘት የተለመደ ነው፡፡ በየሱስ ስብከቶች፣ ትምህርቶችና ታምራቶች መሃል ጴጥሮስ ነበር፡፡ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ለአገልግሎት ከተጠሩበትና እጅግ ብዙ ዓሣ ከያዙበት ከዚያ የቀደመ ታምራት (ሉቃ. 5፡ 4-6) አንስቶ የሱስን ከትንሣኤው በኋላ በገሊላ እስከተገናኙት (ዮሐ. 21፡15) ባሉት ጊዜያት ጴጥሮስ ለአብዛኛው ክስተት የዓይን ምስክር ነበር፡፡

በ2ጴጥ. 1፡17-18 እንደምንመለከተው ሐዋርያው ራሱ ምስክር ከሆነባቸው ትዕይንቶች መሃል ልዩ ትኩረት የቸረው በየትኛው ላይ ነበር? ይህን ክስተት የተለየ አጽንኦት ያሰጠው ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ የዓይን መስክር ከሆነባቸው ክስተቶች መካከል የየሱስ መልክ ለተለወጠበት ትዕይንት የተለየ አጽንኦት ይሰጣል፡፡ የሱስ--ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ለጸሎት ወደ ተራራው ጫፍ ይዟቸው ወጥቶ ነበር (ሉቃ. 9፡28)፡፡ በዚያ በአንድነት እያሉ ከዓይናቸው ፊት የየሱስ መልክ ተለውጦ እንደ ፀሐይ አበራ ልብሱም እንደ መብረቅ የሚያንጸባርቅ ሆነ (ማቴ. 17፡2፣ ሉቃ. 9፡29)፡፡ የሱስ ከሙሴና ከኤልያስ ጋር እየተነጋገረ እያለ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው” (ማቴ. 17:5) የሚል ድምፅ ከሰማይ ተሰማ፡፡

ጴጥሮስ ከየሱስ ጋር በነበረው አብሮነት ለአያሌ እንግዳ ክስተቶች ምስክር መሆን ቢችልም ነገር ግን ይህ የሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ የተገለጠበት፣ ምድራዊ ቆይታው በእግዚአብሔር እቅድ መሰረት የተተገበረ መሆኑ የታየበትና ከአብ ጋር ያለው ልዩ ትስስር ይፋ የሆነበት ትዕይንት--ከሌሎቹ ሁሉ በእጅጉ ነጥሮ መውጣት የቻለ ነው፡፡ “ይህ ድምፅ ከሰማይ ሲመጣ ሰምተናል” (2ጴጥ. 1:18) ሲል በጊዜው የነበረውን ሁኔታ የሚገልጸው ጴጥሮስ ክስተቱ ደብዳቤው ትኩረት ያደረገበት ርዕሰ ጉዳይ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡

በመንፈሳዊ ህይወትዎና በእምነትዎ ላይ የማይጠፋና ጥልቅ ተጽእኖ ማሳደር ስለ ቻለ ክስተት ወይም ክስተቶች አሰብ ያድርጉ፡፡ …ምን ነበር? እንዴት ተጽእኖ አደረገብዎ? ክስተቱ ዛሬም ለእርስዎ ያለው ትርጉም ምን ይመስላል? እንደዚያ ዓይነቱን ተጽእኖ በእርስዎ ላይ ማሳደር የቻለው ለምን ይመስሎታል? መልስዎን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ፡፡

ግንቦት 22
30-May

የንጋት ኮከብ በልባችን ውስጥ


“እንግዲያስ ትንቢታዊው ቃል ይበልጥ ተረጋግጦልናል፤ ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ፣ በጨለማ ስፍራ ለሚበራ መብራት ጥንቃቄ እንደሚደረግ እናንተም ለዚህ ቃል ብትጠነቀቁ መልካም ታደርጋላችሁ” (ጴጥ. 1:19)፡፡ ጥቅሱን በጥንቃቄ ለማንበብ ይሞክሩ፡፡ ዛሬ በዚህ ዘመንም እንኳ በእጅጉ አስፈላጊ ስለሆነው ነገር ጴጥሮስ ምን እያለን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ብርሃንና ጨለማ በመጽሐፍ ቅዱስ በሁለት ጎራ ተከፍለው መቀመጣቸውን ከአያሌ ጥቅሶች መረዳት እንችላለን (ዘፍ. 1:4፣ ዮሐ. 1:5፣ ኢሳ. 5:20፣ ኤፌ. 5:8)፡፡ ለጴጥሮስ የእግዚአብሔር ቃል “በጨለማ” ላይ የሚያበራ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ “ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችሁ እስኪበራ ድረስ” ለብርሃኑ ተገቢውን “ጥንቃቄ” ማድረግ አለባችሁ ሲል በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ እኛ በኃጢአት በወደቀና በጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ የምንኖር የወደቅን ፍጡሮች እንደመሆናችን፤ ከዚህ ጽልመት አውጥቶ ወደ ብርሃን ሊመራን የሚችል መለኮታዊ ኃይል ይኸውም የሱስ ያሻናል፡፡

ጴጥሮስ አንባቢዎቹን ወደ ግብ እያመላከተ እንደሆነ ይስተዋላል፡፡ ሐዋርያው “ሌሊቱ እስኪነጋ” በሚል ጥቅም ላይ ያዋለው አገላለጽ የየሱስን ዳግም መገለጥ ያመላክታል የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ በእርግጥ ውሎ አድሮ ይህ የሁላችንም ተስፋ ፍጻሜ ቢሆንም ነገር ግን በልባችን የሚያበራው “የንጋት ኮከብ” ጽንሰ ሃሳብ ከመቼውም በላቀ--ጊዜ ሳይወስድ ገቢራዊ የሚሆንና ግላዊ ባህሪን የተላበሰ ነው፡፡ “የንጋት ኮከብ” የሱስን ያመለክታል (ራእ. 2:28፣ 22:16)፡፡ የየሱስ በአማኞች ልብ ውስጥ ማብራት--ወገኖች እርሱን ከማወቃቸው፣ ሙሉ ለሙሉ አጥበቀው ከመያዛቸውና ሕያው የሆነውን ክርስቶስ በተጨባጭ ከመለማመዳቸው ጋር ብርቱ ቁርኘት አለው፡፡ የሱስ በኃይማኖታዊ አስተምህሮአችን እውነትነት ብቻ ሳይወሰን-- የህልውናችን ማዕከል እንዲሁም የተስፋችንና የእምነታችን ምንጭ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ ስለዚህ ጴጥሮስ የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና በሚያድነው “የንጋት ኮከብ” የሱስ መሃል ግልጽ ትስስር ሲፈጥር ይስተዋላል፡፡

በእኛ ላይ የበራውን ብርሃን ለሌሎች ማንጸባረቃችን ተገቢና የሚጠበቅ ነው፡፡ “መላው ምድር በእግዚአብሔር እውነት ክብር ከዳር እስከ ዳር ሊያበራ ይገባል፡፡ የብርሃን ጸዳል በሁሉም የምድር ጫፎችና ሕዝቦች ላይ ማንጸባረቅ ይኖርበታል፡፡ በሌሎች ላይ የሚያበራው--አምላካዊውን ብርሃን ከተቀበሉ ወገኖች ላይ የሚነሳው የብርሃን ጸዳል ነው፡፡ እነሆ የንጋት ብርሃን እንደ በራልን ሁሉ--እኛም በጨለማ በተዋጡ ሕዝቦች ጎዳና ላይ እናብራ፡፡”—Ellen G. White, Christian Experi- ence and Teachings of Ellen G. White, p. 220.

በግልዎ ቃሉን ማጥናትዎ የሱስን በተሻለ እንዲያውቁ የረዳዎ እንዴት ነው?

ግንቦት 23
31-May

ይበልጥ የተረጋገጠው ትንቢታዊ ቃል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1፡19-21፡፡ ጴጥሮስ እየተናገረ ያለው ስለ የትኞቹ ትንቢቶች ነው? ትንቢት ፈጽሞ በሰው ፈቃድ የመጣ አይደለም ሲል ምን ማለቱ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ ክርስትና በሰዎች ጥበብ የተፈጠረ ተረት አለመሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ ላቀረበው መልእክቱ (2ጴጥ. 1፡16) ሁለት ተጨባጭ ማስረጃዎችን ይሰጣል፡፡ የመጀመሪያው የዓይን ምስክርነቱ ሲሆን (2ጴጥ. 1፡16-18)፤ ሁለተኛው ቀደም ሲል የሞገተው (1ጴጥ. 1:10–12) የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ናቸው (2ጴጥ. 1:19–21)፡፡

እንዲሁም ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጉመው አይደለም” ሲል ይጠቅሳል (2ጴጥ. 1:20)፡፡ ጴጥሮስ እንዲህ ሲል መጽሐፍ ቅዱስን በየግል እንዳናጠና እየከለከለ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ያለው አስተሳሰብ “ልባችሁን አዘጋጁ” ወይም አእምሮአችሁን በቃሉ አንጹ ሲል ካደፋፈረው ሐዋርያ መልእክት አኳያ ሲታይ እጅግ የራቀ ስለሚሆን ነው፡፡ ወይስ የብሉይ ኪዳን ነቢያት ላደረጉት ትጉ የመጻሕፍት ፍተሻ የተለየ ምስጋናና አድናቆት የቸረው ጴጥሮስ እንዲህ ይላል ተብሎ ይታሰባል? (1ጴጥ. 1፡10)

ነገሩ እንዲህ ከሆነ ሐዋርያው ለማለት የፈለገው ምን ነበር? የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በአንድ ላይ ያድጉና ያጠኑ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች የአንዱ አካል ብዙ ብልቶች ነበሩ (1ቆሮ. 12፡12-14)፡፡ እዚህ ላይ ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን አካል የሆኑት ብልቶች የተቀዳጁትን ብርሃን የሚቃወመውን ዓይነት ጥናት እያስጠነቀቀ እንደነሆን ልብ ይሏል፡፡ ከሌሎች ጋር በሚኖረን አንድነት እንደ አንድ የአማኞች ኅብረት ማደግ እንችላለን፡፡ መንፈስ ከአማኞች ኅብረት ጋር እንዲሁም በግል ከእያንዳንዱ አባል ጋር ይሠራል፡፡ አባላት አዳዲስ ብርሃኖችን ማጋራት፣ ማበልጸግና በጥልቅ ማጎልበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የሌሎችን ግብአት ችላ እያለ ብቻውን የሚሠራ ወደ ተሳሳተ የመጽሐፍ ትርጓሜ መድረስ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው-- በተለይ ትንቢቶችን አስመልክቶ፡፡

ጴጥሮስ እንዲህ ያለውን ትዝብት የሰነዘረበትን ምክንያት በቀጣዮቹ ጥቅሶች እናገኛለን፡፡ ሐዋርያው መልእክቱን እየጻፈ ያለው በሐሰት ነቢያትና መምህራን መካከል ለነበሩ ክርስቲያኖች ነው (2ጴጥ. 2፡1)፡፡ አባላት የየራሳቸውን የመጻሕፍት ትርጓሜ ለአጠቃላዩ የቤተ ክርስቲያን አመራር አካላት እንዲያቀርቡ አጥብቆ እያስገነዘባቸው እንደሆን እንመለከታለን፡፡ በመንፈስ የተመራውን ኅብረት ለመቀበል አሻፈረኝ ማለታቸውን ተከትሎ ስንቶች በአክራሪነት ጽንፍ እና በተሳሳተ አቅጣጫ እንደ ዋለሉ ቀሩ? ይህ ቀደም ባለው ዘመን የነበረ አደጋ እነሆ ዛሬም እንደ ተጋረጠ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ከቤተ ክርስቲያን ለሚሰጥ ምሪትና ምክር ግልጽ መሆን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ይህ በእንዲህ እንዳለ ራሳችንን ለሌሎች መሥዋዕት በማድረጉ ረገድ ምን ያህል ርቀን መሄድ ይጠበቅብናል?

ግንቦት 24
1-Jun

የእግዚአብሔር ቃል በህይወታችን ውስጥ የሚኖው ሚና


ከላይ እንደተመለከትነው ጴጥሮስ ለአምላካዊው ቃል የሚሰጠው አጽንኦት እጅግ የላቀ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ለክርስትና ተሞክሮአችን ያለውን ጉልህ ጠቀሜታና በመለኮት ምሪት መጻፉን አስመልክቶ 2ጴጥ. 1፡19-21 ብርቱ ማረጋገጫ ይሰጠናል፡፡ ሐዋርያው በ2ጴጥ. 1፡21 ያስቀመጠው ነጥብ ግለጽ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሌሎቹ ሰብዓዊ የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ የሰው ፈቃድ ውጤት ወይም ፈጠራ ሳይሆን “ከእግዚአብሔር የተላኩ ሰዎች” በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፉት መጽሐፍ ነው፡፡

በ2ጢሞቴ. 3፡15-17 የቀረቡት ጥቅሶች አምላካዊው ቃል በሕይወታችን የሚኖረውን ሚና እንድናስተውል እንዴት ይረዱናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በጢሞቴዎስና በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለ ተጋረጠው አደጋ ሐዋርያውን ካስጠነቀቀ በኋላ አምላካዊው ቃል አስፈላጊ የሆነበትን ዋና ሃሳብ ያስቀምጣል፡፡ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” (2ጢሞቴ. 3:16) ፡፡

የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች ለመመልከት እንሞክር፡

ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች፡-- እነዚህ አስተምህሮዎች የቤተ ክርስቲያንን ቀኖናን የማንጸባረቅ ባህሪ ስላላቸው፤ አንድ ኅብረት በተለያዩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አስፈላጊ ብሎ የሚከተላቸውን ዘርፈ ብዙ የእምነት ክፍሎች ይገልጻሉ፡፡ ክርስቶስን ማዕከል እንዲያደርግ የሚጠበቀው እያንዳንዱ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ “ፍጹም ከሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ” (ሮሜ. 12:2) አኳያ መመላለስ እንድንችል ያስተምረናል ተብሎ ይታሰባል፡፡

ምሪት፡-- መጽሐፍ ቅዱስ “ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር” (2ጢሞቴ. 3:16) ይጠቅማል ሲል ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲነግረው ይደመጣል፡፡ ጴጥሮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች ዐቢይ ስፍራ የያዘው ትንቢት በጨለማ የሚያበራ ብርሃን እንደሆነ በመግለጽ ተመሳሳይ ነጥብ ሲጋራ ይታያል (2ጴጥ. 1፡19)፡፡ በሌላ አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ትክክል የሆነውንና ያልሆነውን ባህሪ እየጠቆመ እንዴት መመላለስ እንዳለብን ምሪት ይሰጠናል፡፡ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈው መጽሐፍ ቅዱስ ለሰብዓዊው ፍጡር ተገልጦ የታየ አምላካዊ ፈቃድ ነው ከማለት ውጪ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም፡፡

“መዳን የሚገኝበት ጥበብ”፡-- ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ “መዳን የሚገኝበት ጥበብ” ነው ሲል--አምላካዊው ቃል ወደ የሱስ የሚያመላክት መሆኑን መጠቆሙ ነው፡፡ ደኅንነታችን የተመሰረተው የሱስ ስለ ኃጢአታችን መሞቱን ማመናችንን ተከትሎ ነው፡፡

ኃይማኖታዊ አስተምህሮ፣ የሥነ ምግባር መመሪያ፣ የደኅንነት ዕውቀት፡-- ከመሆኑ አኳያ አምላካዊው ቃል ሌሊቱ እስኪነጋና የንጋት ኮከብ በልባችን አስኪበራ ድረስ በጨለማው ስፍራ የሚበራ (2ጴጥ. 1፡19) መሆኑ እምብዛም የሚደንቅ አይሆንም፡፡

ግንቦት 25
2-Jun

ተጨማሪ ሃሳብ፡-


“እውነትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምረው ለሌሎች ምሳሌ በሚሆን ብርሃን እየተመላለሱ ወገኖችን ማበረታታት የእያንዳንዱ ሚዛናዊ አስተሳሰብ ባለቤት ሰብዓዊ ፍጡር ተቀዳሚና ከፍ ያለ ኃላፊነት ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ በትጋት እያጠናን እያንዳንዱን ሃሳብ ልንመዝንና ጥቅስን በጥቅስ ልናስተያይ ይገባል፡፡ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፊት በግል ቀርበን ምላሽ እንደምንሰጥ ሁሉ--በመለኮት እርዳታ የየግላችን ውሳኔና አቋም ሊኖረን የተገባ ነው፡፡

“ተምረዋል፣ ሰፊ ዕውቀት አካብተዋል በሚሉ የመደለያ ቃላት የሚሞካሹ ግብዝ የሥነ መለኮት ምሑራን--በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ፍንትው ብለው የተገለጡ እውነቶችን በጥርጣሬና በጽልመት ዐይን እያዩ፤ መጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈበት ቃላት ግልጽ ሆኖ የተደረደረ ሳይሆን ስውርና ምስጢራዊ መንፈሳዊ ትርጉም አለው እያሉ ያስተምራሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሐሰት መምህራን ናቸው፡፡ የሱስ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትንና የእግዚአብሔርን ኃይል ስለማታውቁ’ (ማር. 12:24) ሲል የተናገረው ለእንደነዚህ ዓይነቶቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ነው፡፡ ከተምሳሌታዊ ወይም ፈሊጣዊ አነጋገር ባሻገር የቀረበ ማንኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ ከራሱ ሃቀኛ ትርጉም አኳያ ሊብራራ የተገባ ነው፡፡ ማንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማድረግ ቢፈልግ፣ እውነተኛውን አምላካዊ አስተምህሮ ያውቃል (ዮሐ. 7:17) ሲል ክርስቶስ ቃል ገብቶልናል፡፡ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንደወረደ ቢቀበሉ--አእምሮአቸው በአደናጋሪ የሐሰተኛ መምህራን አስተምህሮ ባልተታለለ፣ መላእክትን ደስ የሚያሰኘው ሥራ ክንዋኔ ባገኘና አሁን በየፊናው በተሳሳተ አቅጣጫ እየባዘኑ ያሉ ሰብዓዊ ወገኖች በብዙ ሺ እጥፍ ከክርስቶስ እቅፍ በሆኑ ነበር”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 598, 599.


የመወያያ ጥያቄዎች:



መጽሐፍ ቅዱስን በግልጽ ለማስተዋል መካተት የሚኖርባቸው መሰረታዊ የሚባሉ ሌሎች መርኅዎች ምንድን ናቸው?

ማርቲን ሉተር “አንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ የሌላው ብርሃን ነው” ብሎ መጻፉ ይታወቃል፡፡ በዚህም በአምላካዊው ቃል ውስጥ መሰረታዊ አንድነት መኖሩንና በአንደኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምናገኘው ሃሳብ ሌላውን ለማስተዋል ሊረዳን እንደሚችል እናያለን፡፡ ለዚህ መርኅ ከብዙ በጥቂቱ እንደ ምሳሌ የሚያቀርቧቸው የትኞቹ ናቸው?

 በክርስትና ተሞክሮዎ ላይ ጉልህ ተጽእኖ ስላሳደረ ክስተት ወይም ክስተቶች ዙሪያ በሰኞ ትምህርት መጨረሻ ለቀረበው ጥያቄ የሰጡትን ምላሽ ይመልከቱ፡፡ የክስተቶቹ የጋራ ባህሪ ወይም በአንድ የሚያመሳስላቸው ነገር ምን ይመስላል? ከሌሎች ተሞክሮ ምን መማር ይችላሉ?

 መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከጌታ ጋር የሚደረግን ጉዞ እንዴት ሊያጠነክር ይችላል ብሎ አንድ ሰው ቢጠይቅዎ ምላሽዎ ምን ይሆናል? ሕያው ቃሉን በማጥናት ጌታ የሱስን ለማወቅ ባደረጉት ጥረት--ከግል ተሞክሮዎ ምን ዓይነት መርኅዎችን መማር ችለዋል?