ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 3:1- 2፣ ዮሐ. 21:15–17፣ 2ጴጥ. 3:3–13፣ መዝ. 90:4፣ ማቴ. 24:43–51፣ 2ጴጥ. 3:14– 18፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እንግዲህ ሁሉም ነገር በዚህ ሁኔታ የሚጠፋ ከሆነ፣ እናንተ እንዴት ዐይነት ሰዎች ልትሆኑ ይገባችኋል? አዎን፣ በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት ልትኖሩ ይገባችኋል” (2ጴጥ. 3:11)፡፡
ቆ የት ባሉት ዘመናት በእግዚአብሔር የማያምኑ ሰዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ
ከነበራቸው ዝቅተኛ ተቀባይነት አኳያ ተአማኒነት እንደጎደላቸው ወይም
ከዚያም ባለፈ--እንደ አደገኛ ዜጋ ይቆጠሩ ነበር፡፡ ለምን? ጉዳዩ ያን ያህል
ውስብስብ አይደለም--ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ እምነት ከሌላቸው መጨረሻ ላይ
ለፍርድ በፊቱ ሲቀርቡ ላደረጉት ነገር የሚሰጡት ምላሽ አይኖራቸውም፡፡
በተጨማሪ ሰዎች መልካሙን ነገር ደግመው ደጋግመው እንዲያዘወትሩ
የሚያበረታታ ቅመም በውስጣቸው ከሌለ ክፉ የመሥራት ዕድላቸው እየሰፋ
ይሄዳል--የተሰኘው እሳቤ የዚህ አመለካከት መሰረት ነበር፡፡
ምንም እንኳ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሰዎችን መብት እንደሚጋፋና ጊዜው
እንዳለፈበት ተደርጎ ዛሬ ቢታይም--ከጽንሰ ሃሳቡ በስተጀርባ ያለውን ነገረ
አስተሳሰብ (አመክንዮ) ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ በእርግጥ ትክክለኛውን ነገር
ለማድረግ ስለ ወደፊቱ ፍርድ ማሰላሰል ተገቢ አለመሆን ዙሪያ ብዙዎች
ቢስማሙም ነገር ግን ለአምላካዊው ፈቃድ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ትክክለኛውን
ባህሪ ለበለጠ መልካም ተግባር ማነሳሳቱ እሙን ነው፡፡
ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን አደገኛ አስተምህሮዎች ይገጥሟታል ሲል አንባቢዎቹን
አስጠንቅቋል፡፡ ነጻ ትወጣላችሁ የሚል ተስፋ እየሰጡ ሰዎችን በክርስቶስ
ከተሰጠው ነጻነት በተቃራኒ ወደ ቀድሞ የኃጢአት ግዞት ስለሚሰዱ አስተምህሮዎች
ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል፡፡
ቤተ ክርስቲያንን የሚገጥማት የሐሰት አስተምህሮ በዚህ ብቻ አይወሰንም--ሌላም
አደገኛ ሁናቴ አለ፡፡ ሆኖም ጴጥሮስ በተለይ ወደዚህ ማስጠንቀቂያ ከማምራቱ
አስቀድሞ ሌላ የሚናገረው ነገር አለው፡፡
“ወዳጆች ሆይ፤ አሁን የምጽፍላችሁ ሁለተኛው መልእክት ነው፡፡ ሁለቱንም
መልእክቶች የጻፍኩላችሁ ቅን ልቦናችሁን እንድታነቃቁ ለማሳሰብ ነው፤ ደግሞም
ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት አማካይነት
በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው” (2ጴጥ. 3:1-2)፡፡
ጴጥሮስ አንባቢዎቹ ጆሮአቸውን ለመልእክቱ ሊሰጡ እንደሚገባ የሚያነሳው ነጥብ
ምን ይመስላል? (ዮሐ. 21:15–17)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የአንባቢዎቹን ትኩረት “በቅዱሳን ነቢያት” አማካይነት በጽሑፍ ወደ ሰፈሩት
አምላካዊ ቃላት የሚስበው ጴጥሮስ በድጋሚ ወደ ብሉይ ኪዳን የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍል በማመላከት--አብልጦ ስለተረጋገጠው ትንቢታዊ ቃል ያወሳል (2ጴጥ.
1:19)፡፡ የአንባቢዎቹ እምነት በእግዚአብሔር ቃል ጽኑ መሰረት ላይ መታነጹ ወሳኝ
እንደሆነ በግልጽ ሲያስቀምጥ ይስተዋላል፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሕጋዊነትና
ተገቢነት እንዳከተመለት አድርጎ የሚያንኳስስ ወይም የሚሽር የአዲስ ኪዳን
አስተምህሮ ፈጽሞ አናገኝም፡፡ በተቃራኒው ለአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ሕጋዊነትና
ተገቢነት ምስክርነታቸውን የሚሰጡንና ጴጥሮስ ስለ የሱስ እየተናገረ ያለውን
የሚያጸኑልን የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሌላ ነጥብ የምናገኝ ሲሆን ይኸውም--“በቅዱሳን ነቢያት”
ከተጻፈው ከብሉይ ኪዳን መጽሐፍ አንስቶ የ “ጌታችንና አዳኛችን” ሐዋርያነት
ሥልጣን እስከተሰጠው ጴጥሮስ ለተቀመጠው ግልጽ የሃሳብ ፍሰት ሐዋርያው
አጽንኦት መስጠቱ ነው፡፡ ጴጥሮስ እያደረገ ለነበረው ነገር ሁሉ መንስኤው ከጌታ
የተቀበለው ግልጽ ጥሪ መሆኑን ይናገራል፡፡ የመልእክቱን ምንጭ ያውቅ ለነበረው
ሐዋርያ--እንዲህ በእምነትና በእርግጠኝነት መናገሩ እምብዛም የሚገርም
አልነበረም፡፡
በህይወታችን ላይ የበላይ ሥልጣን ሊኖረው የሚገባ ባህላችን ወይም ግላዊ
አስተሳሰብና አመለካከታችን ሳይሆን ነገር ግን የእግዚአብሔር ቃል ሊሆን
የሚገባው ለምንድን ነው? (ለነገሩ ከሌሎቹ የሳምንቱ ቀኖች ይልቅ በሰንበት ቀን
የምናርፈው የእግዚአብሔርን ቃል ተከትለን አይደል?)
ጴጥሮስ “ደግሞም ቀድሞ በቅዱሳን ነቢያት የተነገረውን ቃል እንዲሁም በሐዋርያት
አማካይነት በጌታችንና በአዳኛችን የተሰጠውን ትእዛዝ እንድታስቡ ነው” (2ጴጥ.
3:2) በማለት አንባቢዎቹን ካስገነዘበ በኋላ ወደ ማስጠንቀቁ ያመራል፡፡ ምናልባት
የሚጽፍበትን ሥልጣን ተጠቅሞ ይህ አስተምህሮ ምን ያህል አደገኛ ሊሆን
እንደሚችል እጽንኦት ለመስጠት ሽቶ ሊሆን ይችላል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 3፡3-4፡፡ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ተጠራጣሪዎች
የሚያነሷቸው ሙግቶች ምንድን ናቸው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ሐሰተኛ ነጻነትን በሚሰብኩና የክርስቶስን ምጽአት በሚጠራጠሩ ሰዎች መሃል
አጽንኦት ሊቸረው የሚገባ መመሳሰል አለ፡፡ የመጀመሪያዎቹ “በርኩስ ምኞት የሥጋ
ፍላጎታቸውን የሚከተሉ” (2ጴጥ. 2:10) ሲሆኑ--የክርስቶስን ዳግም ምጽአት
የሚክዱት ደግሞ “የራሳቸውን ክፉ ምኞት የሚከተሉ” (2ጴጥ. 3:3) ሆነው
እናገኛቸዋለን፡፡ (ክፉ ምኞት ወደ ተሳሳተ አስተምህሮ መምራቱ እንደ አጋጣሚ
የሚታይ ይሆን? ሊሆን አይችልም!)
ዘባቾች “ ‘እመጣለሁ’ ያለው ታዲያ የት አለ?” (2ጴጥ. 3:4) ብለው ይጠይቃሉ ሲል
የሚያስጠነቅቀው ሐዋርያው፤ በዚህ አስተሳሰባቸው የየሱስን በቅርብ ወደዚህ
ምድር የመመለስ የቆየ የክርስቲያኖች እምነት ይፈታተናሉ ሲል ይናገራል፡፡ በተለይ
ጴጥሮስ የሚናገረው ስለ መጨረሻው ቀን ከመሆኑ አኳያ ዘባቾች የአያሌ
ክርስቲያኖችን ማንቀላፋት ተጨባጭ እውነታ እያወሱ ነገሮች እንደ ቀድሞው ሁሉ
ዛሬም ሆነ ወደፊት ተመሳሳይ ገጽታ እንደያዙ ይቀጥላሉ ይላሉ፡፡
አባባሉን እንደ ወረደ ከተመለከትነው ከንቱና የማይረባ ጥያቄ ሆኖ አናገኘውም፡፡
“የሙታን ሁኔታ በእጅጉ ይረብሸው የነበረው ሄኖክ ጻድቃንና ኃጥአን በአንድነት
ወደ አፈር እንደሚመለሱ በመገመት ይህ የእነርሱ ፍጻሜ እንደሆነ አድርጎ ያስብ
ነበር፡፡” የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 86 /አማርኛው ትርጉም/) በማለት ኤለን
ኋይት መመልከቷን ጽፋለች፡፡ ከውሃ ጥፋት አስቀድሞ የኖረው ቅዱስ ሰው--ሄኖክ
ሳይቀር ከዚህ ጥያቄ ጋር ከተፋለመ ከእርሱ ሺዎች ዓመታት በኋላና ከዳግም
ምጽአቱ አስቀድሞ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” የሚኖሩትን ምን ያህል ይረብሽ?
እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን--እኛስ ዛሬ ምን እንላለን? የቤተ
ክርስቲያናችን መጠሪያ በራሱ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ጽንሰ ሃሳብ ቢሰብክም
እርሱ ግን እስካሁን አልመጣም፡፡ ስለዚህ ጴጥሮስ በመጨረሻው ዘመን ይሆናል
ባለው መሰረት እነሆ ዘባቾችን በመጋፈጥ ላይ እንገኛለን፡፡
ክርስቶስ እስካሁን ያልመጣበትን እውነታ ከግል የክርስትና ተሞክሮዎ አኳያ
እንዴት ይመለከቱታል? መልስዎን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ፡፡
ሐዋርያው በ2 ጴጥ. 3:8–10 ዘባቾች ለሚያቀርቡት ሙግት የሚሰጠው ምላሽ ምን
ይመስላል? ክርስቶስ እስካሁን ያልተመለሰበትን--ዛሬም ለእኛ ጠቃሚነት ያለውን
ምክንያት እንዴት ያስቀምጣል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ የምድር ሁናቴ ሳይለዋወጥ እንደ ቀድሞው ይቀጥላል ለተሰኘው አባባል
ምላሽ በመስጠት ምድር ከፍጥረት አንስቶ በተመሳሳይ ሁኔታ አለች የሚለው
አባባል--ከእውነት የራቀ ነው ሲል አንባቢዎቹን ያስገነዝባል (እዚህ ላይ ሐዋርያው
ወደ ኋላ መለስ ብሎ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣንና የመልእክቱን ከዚያ መቀዳት
እንዴት እንዳስቀመጠ ልብ ይሏል)፡፡ በዓለም ላይ ርክስና መንሰራፋቱን ተከትሎ
እግዚአብሔር ምድርን በውሃ አጠፋ (2ጴጥ. 3፡6)፡፡ በእርግጥ የውሃ ጥፋት እነሆ
ዛሬ ድረስ አብሮን ያለ ታላቅ ለውጥ በዓለም ላይ እንዲከሰት መንስኤ ሆኗል፡፡
ጴጥሮስ ጽሑፉን ሲቀጥል ከዚህ በኋላ ምድር የምትጠፋው በውሃ ሳይሆን በእሳት
ነው ይለናል (2ጴጥ. 3:10)፡፡
ጴጥሮስ በተጨማሪ የሚከተለውን ሃሳብ አስፍሯል፡ “በጌታ ዘንድ አንድ ቀን እንደ
ሺህ ዓመት፣ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን መሆኑን ይህን አንድ ነገር
አትርሱ” (2ጴጥ. 3:8)፡፡ ሐዋርያው ይህን መልእክት ከመዝሙረ ዳዊት ወስዶ
እንዳንጸባረቀ ይታመናል “ሺህ ዓመት በፊትህ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣
እንደ ሌሊትም እርቦ ነውና” (መዝ. 90፡4)፡፡ በሌላ አነጋገር ስለ ጊዜ ያለን
አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ካለመሆኑ አኳያ ከጊዜ ጋር ቁርኝት ያለው
አስተያየት ስንሰጥ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የክርስቶስን ዳግም
ምጽአት ከሰብዓዊው አስተሳሰብ አኳያ ከተመለከትነው የዘገየ ሊመስል ይችላል፡፡
ሆኖም ምልከታችን ከሰብዓዊው መመዘኛ አኳያ ብቻ የተቃኘ ነው፡፡ እግዚአብሔር
ተጨማሪ ጊዜ የሰጠን ከምህረቱ የተነሳ በመታገሱ እንደሆነ ጴጥሮስ ይነግረናል፡፡
ማንም ይጠፋ ዘንድ የእርሱ ምኞት አይደለም (2ጴጥ. 3፡9)፡፡ ተጨማሪው ጊዜ
ብዙዎች በንስሐ ወደ እርሱ እንዲመጡ ዕድል ይሰጣል፡፡
የእግዚአብሔር መታገስ የሱስን የግል አዳኛችን አድርገን የምንቀበልበትን ወርቃማ
እድል ማዘግያ አይደለም ሲል የሚያስጠነቅቀው ጴጥሮስ--ሌባ ባልተጠበቀበት
ሌሊት እንደሚመጣ የጌታም ቀን በተመሳሳይ ሁናቴ ገቢራዊ ይሆናል ይለናል፡፡
ምናልባት ሌባ አድብቶ፣ ማንም ሳያየው በሌሊት ወደ ጉዳዩ ያመራ ይሆናል፡፡ ነገር
ግን የጌታ ቀን እንደ ሌባ ሲመጣ ያን ታላቅ ትዕይንት ሁሉም ያያል፡፡ ጴጥሮስ
እንደሚነግረን “በዚያች ቀን ሰማያት በታላቅ ድምፅ ያልፋሉ፤ የሰማይም ፍጥረት
በእሳት ይጠፋል፤ ምድርና በእርሷም ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይቃጠላል” (2ጴጥ. 3:10)፡፡
እዚህ ላይ የጴጥሮስ መልእክት ከጳውሎስ ጋር ገጣሚ እንደሆነ እንመለከታለን፡
“እነሆ ትክክለኛው ሰዓት አሁን ነው፤ የመዳንም ቀን አሁን ነው” (2ቆሮ. 6:2)፡፡
አንድ ወጣት ለእናቱ ለመመስከር ሞክሮ ነበር፡፡ ወጣቱ ስለ የሱስ ለኃጢአት
መሞት፣ ትንሳኤና የዳግም ምጽአት ተስፋ አንኳር ነጥቦች እያነሳ አበሰራቸው፡፡
እንዲህ ዓይነቱን ድንቅ የምስራች ማካፈል በመቻሉም በራሱ ኮራ፡፡ ሆኖም ስለ
የሱስ ዳግም ምጽአት የምታበስረውን አነስተኛ ስብከት መሳይ መልእክቱን
እንደቋጨ እናቱ ቀና ብለው ከተመለከቱት በኋላ “ታዲያ እኔን አሁን ምን አድርጊ
ነው የምትለኝ?” ሲሉ ጠየቁት፡፡
ሐዋርያው በ2ጴጥ. 3፡11-13 መልእክቱ “ታዲያ እኔን አሁን ምን አድርጊ ነው
የምትለኝ?” የሚለውን ጥያቄ እንዴት ይመልሳል? በተጨማሪ ይህን ጥቅስ
ይመልከቱ--ማቴ.24፡43-51፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ቀደም ብለን እንደተነጋገርነው ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የሚለው ስያሜያችን
በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተጨባጭ እውነታ ላይ ያለንን እምነት ያመለክታል፡፡
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከቤተ ክርስቲያናችን አንኳር አስተምህሮዎች አንዱ
እንደመሆኑ ያለ ዳግም ምጽአቱ፤ የክርስትና እምነታችን ተስፋዎች በአጠቃላይ
ትርጉም የለሽ በሆኑ ነበር፡፡
ነገር ግን በማቴ. 24፡43-51 ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ክፉ አገልጋይ የመሆን
አደጋ ሊገጥመን አይችል ይሆን? ምናልባት በምሳሌው ቃል በቃል የተጠቀሰው
ዓይነት ክፉ ድርጊት ባንፈጽምም (ምሳሌ ከመሆኑ አኳያ) ዋናው ነጥብ ግን ያ
አይደለም፡፡ ይልቁንም--ከፍ ካሉት አምላካዊ መርኅዎች መንሸራተት፣ ከሌሎች ጋር
ባለን ግንኙነት ቅንነት የጎደለው ባህሪ ማሳየት፣ በጌታ ዳግም ምጽአት ላይ የነበረን
የተጋጋለ እምነት በመቀዛቀዝ ዓለምን ወደ መምሰል ማዘንበል--እነዚህ ምሳሌው
የሚያስጠነቅቀን ነጥቦች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የቁጥር ሠንጠረዦችን እየሠሩና የትንቢታዊ ቀናት ቀመሮችን እያሰሉ
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት በዚህ ጊዜ ይሆናል የሚሉ ሰዎች ቀደም ባሉት ጊዜያትም
ሆነ ዛሬ አልታጡም፡፡ ሆኖም ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ላይ
የተጋረጠው አደጋ ባመዛኙ ክርስቶስ በዚህ ጊዜ ይመጣል ብሎ ቀን መቁረጡ ላይ
አይደለም፡፡ ፍራቻው--የተቀቆረጠው ቀን ያለ ዳግም ምጽአቱ ትዕይንት እንደ
ማንኛውም ቀን ባለፈ ቁጥር አማኞች በዳግም ምጽአቱ ላይ የነበራቸው ተስፋ ከጊዜ
ወደ ጊዜ እየከሰመ በመሄድ አስተምህሮው በአስተሳሰባችን ላይ ያለው ሚና
ኢምንት እንዳይሆን ነው፡፡
በእርግጥ በምድር ላይ ብዙ ዘመን በኖርን ቁጥር ለዳግም ምጽአቱ እየተቃረብን
መሄዳችን ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ጉዳዩን በሌላ አቅጣጫ ከተመለከትነው ያለ ዳግም
ምጽአቱ በምድር ረጅም ዘመናት ባስቆጠርን ቁጥር ርቆ ያለው ዳግም ምጽአቱ
በየዕለት ህይወታችን ላይ ተጽእኖ እንደ ሌለው አድርጎ ማሰብ እየቀለለን ሊሄድ
ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከእንዲህ ያለው ልል የአኗኗዘር ዘይቤ እንድንጠበቅ
ያስጠነቅቃል፡፡ ጴጥሮስ እንደ ተናገረው--የሱስ ዳግም የሚገለጥና በፍርድ ፊት
የምንቀርብ እስከ ሆነ ድረስ--ክርስቲያኖች በቅድስናና በእውነተኛ መንፈሳዊነት
ልንመላለስ ይገባል (2ጴጥ. 3፡11)፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውነታ መቼም
ይሁን--ነገር ግን በዛሬው አኗኗራችን ላይ አዎንታዊ ተጽእኖ እንዲኖረው
ይጠበቃል፡፡
የዳግም ምጽአቱ ተጨባጭ እውነታ በየቀን ህይወትዎና አስተሳሰብዎ ላይ ያለው
ተጽእኖ ምን ይመስላል? መልስዎ ስለ ህይወትዎና ስለ እምነትዎ ምን ሊል ይችላል?
በመጠነኛ ጽንሰ ሃሳቦች የጀመረው የጴጥሮስ ደብዳቤ ግዝፈት ያላቸውን ርዕሰ
ጉዳዮች አካቶና በቅድስና ስለ መኖር አውስቶ “በዐመጸኞች ስህተት ተስባችሁ
እንዳትወድቁ” (2ጴጥ. 7 3:17) ሲል መልእክቱን ይደመድማል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 2ጴጥ. 3፡14-18፡፡ ጴጥሮስ ተማጽኖ እያቀረበ ያለው ስለ
ማን ነው? የሚሰጠውስ ማስጠንቀቂያ ምን ይመስላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ መልእክቱን የሚደመድመው ስለ ተወዳጁ “ወንድማችን ጳውሎስ” ጽሑፎች
ተማጽኖ በማቅረብ መሆኑ ደስ ያስኛል (2ጴጥ. 3:15)፡፡ በተመሳሳይ ሐዋርያው
ጳውሎስም እንዲሁ የየሱስን ዳግም ምጽአት እየተጠባበቁ ከሰዎች ጋር በሰላም
ስለመኖር አስፈላጊነትና ጊዜያችንን የቅድስና ህይወት ለማጎልበት ማዋል እንዳለብን
ጽፎአል (ሮሜ. 2:4፣ 12:18፣ ፊልጵ. 2:12)፡፡
በተጨማሪ የጳውሎስ መልእክት በጥንቱ የክርስትና ታሪክ ምን ያህል ከፍ ያለ ዋጋ
እንደ ነበረው የሚያመለክተውን--ጴጥሮስ ለጳውሎስ መልእክት የሰጠውን ማጣቀሻ
ልብ ይበሉ፡፡ ጴጥሮስ በማመሳከሪያነት እየተጠቀመ ያለው--ዛሬ በአዲስ ኪዳን
መጻሕፍት የምናገኛቸውን ሙሉ የጳውሎስ መልእክቶች ስብስብ ይሁን ወይም
በከፊል--የጳውሎስ ደብዳቤዎች ከፍ ያለ ዋጋ እንደተሰጣቸው ከጴጥሮስ አስተያየት
መገንዘብ ይቻላል፡፡
በመጨረሻ--የጳውሎስ ጽሑፎች እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ሁሉ
በቀላሉ ላይስተዋሉ እንደሚችሉ ጴጥሮስ አስተያየቱን ይሰጣል፡፡ አዲስ ኪዳን
በተጻፈበት በግሪክ ቋንቋ ግራፋ በሚል የተቀመጠው ቃል “ጽሑፎች” የሚል ፍቺ
አለው፡፡ ሆኖም መልእክቱ ከጴጥሮስ ጽሑፍ ዐውድ ሲታይ “ቅዱስ ጽሑፎች”
የሚል ትርጉም ይሰጠናል፡፡ ይኸውም እንደ ሙሴና ነቢያት መጽሐፎች ማለት
ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ሥልጣን እንዳላቸው ሁሉ የጳውሎስም መልእክት
በተመሳሳይ ከፍታ ለመቀመጡ ጴጥሮስ የሚሰጠን ማስረጃ በጣም ቀዳሚው ነው፡፡
ነጻነት ታገኛላችሁ ብለው ስለ ሚሰብኩ የሐሰት መምህራን ቀደም ብለን
የተመለከትነውን ከግምት በማስገባት--ጳውሎስ ስለ ነጻነትና ጸጋ ያሰፈራቸውን
ጽሑፎች ሰዎች ለኃጢአተኛው ባህሪ መሸፋፈኛነት ሊጠቀሙ እንደሚችሉ መገመት
አያዳግትም፡፡ ጳውሎስ ለጽድቅ በእምነት አስተምህሮ ጽኑ አጽንኦት ከመስጠት
ውጪ (ሮሜ 3፡21-22) በየትኛውም ጽሑፉ ሰዎች ኃጢአት የሚሠሩበትን ነጻነት
የሰጠበት ቦታ የለም (ሮሜ 6:1–14)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ጽድቅ በእምነት
ከመስበኩና ከማስተማሩ አኳያ እርሱ ራሱ ይህን ስህተት መጋፈጥ ነበረበት፡፡
ሆኖም ጴጥሮስ--“ለገዛ ጥፋታቸው ያጣምማሉ” (2ጴጥ. 3:16) ሲል የጳውሎስን
ጽሑፎች ለመጠምዘዝ የሚሞክሩትን ያስጠነቅቃል፡፡
በክርስቶስ የሱስ እንድንኖር የተጠራነውን ህይወት እንዲኖሩ ሊረዳዎ የሚችሉ--
አሁን ሊመርጡ የሚችሏቸው ምርጫዎች ምንድን ናቸው?
የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ከሰብዓዊው እሳቤ አኳያ
ከተመለከትነው እጅግ የዘገየ ሊመስል ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ሊሰማን
እንደሚችል ጠንቅቆ ይረዳ የነበረው የሱስ በእነዚህ የመጨረሻ ጊዜያቶች ተግተን
የማንጠባበቅ ከሆነ ምን ሊሰከት እንደሚችል አንዳንድ ምሳሌዎችን በመጥቀስ
ነግሮናል፡፡ ለአብነት ያህል በማቴ. 24፡45-51 (በረቡዕ ትምህርታችን የተጠቀሰውን)
የሁለቱን አገልጋዮች ምሳሌ መመልከት እንችላለን፡፡ እነዚህ ሁለቱም አገልጋዮች
የጌታቸውን መመለስ ይጠባበቁ የነበረ ቢሆንም ነገር ግን በጌታቸው መመለስ ዙሪያ
የሁለቱም ድምዳሜ የተለያየ ነበር፡፡ አንደኛው--ጌታው በማንኛውም ሰዓት ሊመለስ
ቢችል ተዘጋጅቶ መጠበቅ እንዳለበት ሲወስን--ሌላው ግን ጌታው እንደሚዘገይ
በመገመት አጋጣሚውን ክፉ ድርጊት በመፈጸም ሊጠቀምበት እንደሚችል አሰበ፡፡
“ጌታ የመሚጣበትን ትክክለኛውን ጊዜ ስለማናውቅ ተግተን እንድንጠባበቅ
ታዝዘናል፡፡ ‘ጌታቸው በሚመጣበት ጊዜ ነቅተው የሚያገኛቸው አገልጋዮች ብፁአን
ናቸው’ ሉቃ. 12፡37፡፡ የጌታን ዳግም ምጽአት ተግተው የሚጠባበቁ ወገኖች
እጆቻቸውን አጣጥፈው አይቀመጡም፡፡ ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ ሲገለጥ
መጠባበቅ ማለት--ሰዎች ለጌታ ክብር እንዲሰጡና በኃጢአት ላይ የሚሰጠው ፍርድ
አስፈሪ መሆኑን እንዲያስተውሉ መርዳት ነው፡፡ የቀረበላቸውን የምህረት ግብዣ
በመቃወም ታላቅ ኃጢአት እንዳይሠሩ ካንቀላፉበት መቀስቀስ ነው፡፡ ጌታን
ተግተው እየተጠባበቁ ያሉ ወገኖች ለእውነት እየታዘዙ ነፍሳቸውን ያነጻሉ”—Ellen
G. White, The Desire of Ages, p. 634.
በሰኞ ትምህርት ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት በሰጡት መልስ ላይ
ተወያዩ፡፡ በዚህ ዙሪያ ከተነሱ ምላሾች ምን መማር እንችላለን?
እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ከባህል ወይም ከሰብዓዊው
አመክንዮ ውጪ--ከእግዚአብሔር ቃል ብቻ የወሰድናቸው
አስተምህሮዎች፣ ልምዶችና እምነቶች ምንድን ናቸው?
በዚህ ሣምንት ጥናታችን እንደተመለከትነው ጴጥሮስ ኃጢአተኛ
ዝንባሌንና ክፉ ምኞት መከተልን ከሰሐሐሰተኛ አስተምህሮ ጋር አያይዞ
አቀርብቧል፡፡ በሰኞ ትምህርት የሚከተለው ቀርቦ ነበር፡ “ክፉ ምኞት ወደ
ተሳሳተ አስተምህሮ መምራቱ እንደ አጋጣሚ የሚታይ ይሆን? ሊሆን
አይችልም!” አጋጣሚ ያልሆነው ለምንድን ነው? በሁለቱ መካከል ያሉት
የተለያዩ አያያዦች ምን ሊሆኑ ይችላሉ?
ታዋቂው የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይን አስደናቂ የተባለውን የጊዜ
ኢፍጹማዊ ጽንሰ ሃሳብ ለዓለም ማጋራት ችሎ ነበር፡፡ በአንድ የጊዜ
ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ሰው የሚገኝበት ሁናቴና የሚንቀሳቀስበት ፍጥነት፤
በሌላ የጊዜ ማዕቀፍ ካለው ግለሰብ ጋር ሲተያይ የተለያየ ነው፡፡ በዚህም
ጊዜ እጅግ ሽሽግ ባህሪ ያለው በመሆኑ የሚሠለጥንበትን አካሄድ ሙሉ
ለሙሉ ለማስተዋል አዳጋች ነው--የሚለውን ነጥብ በጉልህ መመልከት
እንችላለን፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ እግዚአብሔር ስለ ጊዜ ያለው እሳቤ እኛ
ካለን ማስተዋል ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑን ያሳየናል--በተለይ ከክርስቶስ
እስካሁን አለመገለጥ ዐውድ ሲታይ፡፡