በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከመጋቢት 23-29

ሁለተኛ ትምህርት

April 1 - 7


ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት መወለድ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 1:1-2፣ ዮሐ. 3:16፣ ሕዝ. 33:11፣ 1ጴጥ. 1:3–21፣ ዘሌዋ. 11:44-45፣ 1ጴጥ. 1:22– 25፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “እንግዲህ ለእውነት በመታዘዝ ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ፤ ለወንድሞቻችሁ ቅን ፍቅር ይኑራችሁ፤ እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” (1ጴጥ. 1:22)፡፡



መ ጽሐፍ ቅዱስ በምናጠናበት ጊዜ በተለይ ትኩረታችንን በአንድ መጽሐፍ ወይም የመጽሐፉ ክፍል ላይ ስናደርግ አንዳንድ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ ይገባል፡፡

በመጀመሪያ መልእክቱ የተጻፈለትን ተደራሲ ማወቅ መልካም ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ጽሑፉን ለማዘጋጀት ያስፈለገበትን ትክክለኛ መንስኤ ማወቅ ይበልጥ አስፈላጊ ሲሆን በሦስተኛ ደረጃ ጸሐፊው ሊያነሳ የፈለጋቸውን ርዕሰ ጉዳዮች ጠንቅቆ ለመገንዘብ መሞከር ተገቢ ነው (ለምሳሌ ጳውሎስ በጽድቅና በሕግ ዙሪያ የቀረቡ የተሳሳቱ አስተምህሮዎችን ለማረም ለገላትያ ሰዎች የጻፈው መልእክት)፡፡ ማንም ሰው ራቅ ብሎ ለሚኖር ዘመድ ወይም ወዳጅ አንድ የተለየ መልእክት ማስተላለፍ ሲፈልግ ደብዳቤ መጻፉ ወይም በዘመንኛው ኢሜይል ማድረጉ የተለመደ እንደመሆኑ አብዛኞቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት--በመልእክት ወይም በደብዳቤ መልክ መጻፋቸው እሙን ነው፡፡

በሌላ አነጋገር የጴጥሮስን መልእክት ስናጠና በተቻለን መጠን የመልእክቱን ታሪካዊ ዐውድ ማወቃችን መልካም ይሆናል፡፡ የጴጥሮስ መልእክት ምን ይመስላል? ለምን? በእርግጥ ከሁሉ በላይ--ከጽሑፉ (በመንፈስ ምሪት ከተጻፈው) የምናገኘው መልእክት ምንድን ነው? የሚለው ይበልጥ አጽንኦት ሊሰጠው የተገባ ነጥብ ነው፡፡

ምንም እንኳ ጴጥሮስ እነዚህን መልእክቶች ከጻፈ እጅግ ብዙ መቶ ዓመታት ቢያልፉም ነገር ግን በቀጣዮቹ ቁጥሮች የምንመለከታቸው--ይህ ሐዋርያ ሊገልጽልን የሚመኛቸው አያሌ ጠቃሚ እውነቶች አሉት፡፡

መጋቢት 24
2-Apr

በመጻተኝነት ለሚኖሩ


በአንድ ብጣሽ ወረቀት ላይ--ይድረስ “ለተወደድክ ወንድሜ” ወይም “ለተወደድሽ እህቴ” በሚል መግቢያ የተጻፈ መልእክት ቢደርስዎ ደብዳቤ እያነበቡ መሆኑን ለመገንዘብ ጊዜ አይወስድቦትም፡፡ ደብዳቤው ከቅርብ ሳይሆን ከሩቅ እንደመጣ ለመገመትም እንዲሁ አይቸገሩም፡፡ እንደ ዘመናዊው ሁሉ የጥንት ደብዳቤ አጻጻፍ መግቢያ--የራሱ ደንብና ሥርዓት ነበረው፡፡ የጴጥሮስ ደብዳቤ እንደ ማንኛውም ጥንታዊ መልእክት--የደብዳቤውን ጸሐፊና ደብዳቤው የተጻፈለትን አካል በመጥቀስ ይጀምራል፡፡

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 1፡1፡፡ በዚህ አንድ ጥቅስ--ስለ ታሪካዊው ዳራ ምን መማር እንችላለን?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ ስሙን በደብዳቤው መግቢያ ላይ በማስፈር ራሱን በግልጽ እንዳስተዋወቀ እናያለን፡፡ ማንነቱን ሲገልጽ የተጠቀመው ሃረግ “የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ” የሚል ነው፡፡ ጳውሎስ በተደጋጋሚ ያደርግ እንደነበረው (ገላ. 1:1፣ ሮሜ 1:1፣ ኤፌ. 1:1) ጴጥሮስም ለመለኮታዊው ጥሪ አጽንኦት በመስጠት ይህን ሃረግ እንደ “መጠሪያ ማዕረግ” ሲጠቀምበት ይስተዋላል፡፡ ጴጥሮስ “ሐዋርያ” የነበረ ሲሆን አገልግሎት እንዲሰጥ የላከው ደግሞ ጌታ የሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡

ጴጥሮስ ደብዳቤው የሚደርስባቸውን ስፍራዎች እንደሚከተለው ጠቅሶአል፡ ጳንጦስ፣ ገላቲያ፣ ቀጰዶቅያ፣ እስያ እና ቢታንያ፡፡ እነዚህ ሁሉም ክልሎች ይገኙ የነበረው በእስያ ማይነር ሲሆን--በግምት ከዛሬዋ የምስራቃዊ ቱርክ ግዛት ቦስፎረስ ጋር ይመጣጠናሉ፡፡

የጴጥሮስ መልእክት ወደ አይሁድ አማኞች ያመዝናል ወይስ አይሁድ ወዳልሆኑ አማኞች?--የሚለው ርዕሰ ጉዳይ ብርቱ መከራከሪያ በመሆን ይታወቃል፡፡ በ 1 ጴጥ.1፡1 መጨረሻ ላይ “በመጻተኝነት ለሚኖሩ” የሚለው አገላለጽ--አይሁድ ሆነው በአንደኛው ምዕተ ዓመት ከቅድስት ከተማ ውጪ ይኖሩ የነበሩትን ትውልደ እስራኤላውያን ዲያስፖራዎች ለማመልከት ጥቅም ላይ እንደዋለ ይታመናል፡፡ በ1ጴጥ. 1 እና 2 “ምርጦች” እና “ለተቀደሱት” በሚል የቀረቡት ቃላት ለአይሁዶችም ሆነ አይሁድ ላልሆኑ አሕዛብ ገጣሚነት አላቸው፡፡ ጴጥሮስ ከአይሁድ ማሕበረሰብ ውጪ የሆኑትን “አሕዛብ” (1ጴጥ. 2:12፣ 4:3) ብሎ በመጥቀስ መልእክቱን ለጻፈላቸው ለአይሁዳውያኑ ጸባይ አጽንኦት ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐያስያን ጴጥሮስ በ1ጴጥ. 1፡18 እና 4፡3 የጻፈውን ዋቢ በማድረግ መልእክቱ ከአይሁዶች ይልቅ ወደ ክርስትና ለተለወጡ አሕዛብ በተሻለ ገጣሚ ነው ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ጴጥሮስ “ከቀድሞ አባቶቻችሁ ከወረሳችሁት ከንቱ ከሆነ ሕይወት” ብሎ ለአይሁዳውያን ሊጽፍ ይችላል? ደግሞስ “አሕዛብ ፈቅደው እንደሚያደርጉት በመዳራት፣ በሥጋዊ ምኞት፣ በስካር፣ በጭፈራ፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል” (1ጴጥ. 4:3) በማለት ለአይሁድ አንባቢዎቹ እንዴት ይህን ሃሳብ ሊያካፍል ይችላል?

ለእኛ ይበልጥ አንገብጋቢው ነጥብ የመልእክቱ ተደራሲ ማን ነው--የሚለው ሳይሆን መልእክቱ ምንድን ነው--የሚለው ነው፡፡

መጋቢት 25
3-Apr

የተመረጡ


ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡- 1ጴጥ. 1፡2፡፡ ጥቅሱ ጴጥሮስ ይህን መልእክት ስለ ጻፈላቸው አካላት በተጨማሪ ምን ይነግረናል? ምን ብሎ ይጠራቸዋል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መልእክቱ የቀረበው ለአይሁድ ይሁን ወይም ለአሕዛብ አማኞች--ጴጥሮስ ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ የነበር ሲሆን ይኸውም--እግዚአብሔር አብ አስቀድሞ ላወቃቸው ምርጦች መጻፉን ነው (1ጴጥ. 1-2)፡፡

በዚህ ዙሪያ ብርቱ ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ ጴጥሮስ መልእክቱን የሚጽፍላቸው የጽድቅ ባለቤት እንዲሆኑ የተመረጡ እድለኞች--ሌሎች ደግሞ እንዲጠፉ በእግዚአብሔር የተወሰነባቸው ዕድለ ቢሶች አድርጎ የሚያቀርብ አመለካከት ማለትም--አንዳንዶች እንዲጠፉ ሌሎች ደግሞ እንዲድኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ ወስኖአል የሚል ትርጉም ፈጽሞ የለውም፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጢሞቴ. 2:4፣ 2ጴጥ. 3:9፣ ዮሐ. 3:16፣ ሕዝ. 33:11፡፡ ጴጥሮስ እነዚህን ሕዝቦች “ምርጦች” ብሎ የመጥራቱን ፍቺ ማስተዋል እንድንችል ጥቅሶቹ እንዴት ይረዱናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እያንዳንዱ ሰው ይድን ዘንድ የእግዚአብሔር እቅድ መሆኑንና ይህ እቅድ የወጣው ከምድር መፈጠር አስቀድሞ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይነግረናል፡ “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናልና” (ኤፌ. 1:4)፡፡ እርሱ ሁላችንንም የመረጠ እንደመሆኑ የአምላካዊው የቀደመ ዓላማ እያንዳንዳችን እንድንድንና ማንም እንዳይጠፋ ነው፡፡ መላው ሰብዓዊ ዘር የዘላለማዊ ሕይወት ባለቤት ይሆን ዘንድ እርሱ አስቀድሞ ወስኖአል፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው የተዘጋጀለትን ሥርየት ባይቀበል እንኳ አምላካዊው የደኅንነት እቅድ እያንዳንዱን ሰው ለመዋጀት በቂ ነው የሚል ፍቺ አለው፡፡

እግዚአብሔር የተመረጡትን አስቀድሞ ያውቃል የተሰኘው አባባል ወገኖች ከደኅንነት ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሰጣቸውን ነጻ የመምረጥ ችሎታ እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት አስቀድሞ ማወቁን ለማሳየት የቀረበ ነው፡፡ ይህ አስቀድሞ ማወቅ--ልጇ ከአረንጓዴዎቹ የቦሎቄ ዝርያዎች ይልቅ በቼኮሌት የተሠራውን ኬክ እንደሚመርጥ አስቀድማ ከምታውቀው እናት በተለየ በእነርሱ ላይ አስገዳጅነት የለውም፡፡ በመሆኑም አባባሉ--እናት የልጇን የቼኮሌት ምርጫ ማወቋ ልጇ እንዲመርጠው ብርታት ሆኖታል የሚል አንደምታ አለው፡፡

እርስዎ የዘላለማዊ ሕይወት ባለቤት እንዲሆኑ በእግዚአብሔር የተመረጡ ስለ መሆንዎ--ልብን ከሚያነቃቃው ከዚህ እውነት ያገኙት ማረጋገጫ ምንድን ነው?

መጋቢት 26
4-Apr

ቁልፍ ርዕሰ ጉዳዮች


በ1ጴጥ. 1:3–12--የጴጥሮስ ዋና መልእክት ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ በመልእክቱ መግቢያ ለአንባቢዎቹ ባቀረበው ሰላምታ--አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ተጠቅሰዋል (1ጴጥ. 1፡1-2)፡፡ እነዚህ ሦስቱም ከ 1ጴጥ. 1፡3-12 መልእክት አኳያ ቀርበዋል፡፡ አብ እና ወልድ የ 1ጴጥ. 1፡3-9 አበይት ርዕስ ሲሆኑ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ በ 1ጴጥ. 1፡10-12 ከፍ ያለውን አጽንኦት ይዞአል፡፡

ጴጥሮስ ስለ አብ፣ ወልድና የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በመጻፍ ኋላ ላይ የሚመለስባቸውን አያሌ ርዕሰ ጉዳዮች ከወዲሁ ሲያስተዋውቅ ይስተዋላል፡፡ ክርስቲያኖች የአዲስ ልደት ባለቤት መሆናቸውን በመንገር መልእክቱን የሚጀምረው (1ጴጥ. 1:3፣ ዮሐ፣. 3:7) ጴጥሮስ--የእነዚህ ሕዝቦች መላ ሕይወት በየሱስ ትንሳኤ ስለ መለወጡና በሰማይ ስለሚጠብቃቸው አስደናቂ ርስት ይናገራል (1ጴጥ. 1፡3-4)፡፡ የየሱስ ትንሳኤ እንደ ብዙዎቹ የአዲስ ኪዳን መልእክቶች ሁሉ በዚህ ስፍራም ቁልፍ የክርስቲያን ተስፋ መሆኑን እንመለከታለን፡፡

ምንም እንኳ አያሌ የአንደኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ አንባቢያን መልእክቱ ስለ ክርስቲያኖች ሥቃይ አብዝቶ ይናገራል በሚለው ሃሳብ ቢስማሙም ነገር ግን ይህ ተስፋ የክርስቲያኖች ደስታ መንስኤ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በእነርሱ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ሥቃይ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን--እምነታቸው ነጥሮ እንዲወጣ ይረዳቸዋል፡፡ ምንም እንኳ የጴጥሮስ መልእክት አንባቢያን እንደ መልእክቱ ጸሐፊ የሱስን በምድራዊ አገልግሎቱ ባያዩትም--ነገር ግን ይህን ጌታ ይወዱታል ያምኑታልም፡፡ በእርሱ ላይ ያላቸው እምነት ውጤቱ የደኅንነት ባለቤት መሆን ነው፡ --“እንዲሁም በሰማይ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደገና ወለደን” (1 ጴጥ. 1:4)፡፡

በተጨማሪ ጴጥሮስ “ለእናንተ ስለሚሰጠው ጸጋ” (1 ጴጥ. 1:10) በሚል ነቢያት አስቀድመው በትንቢት መናገራቸውን እንዲያውቁ ይገልጽላቸዋል፡፡ እነዚህ ሕዝቦች አሁን በየሱስ እየተለማመዱ ያለውን ደኅንነት--የብሉይ ኪዳን ነቢያት “ተግተው በጥንቃቄ ይመረምሩ ነበር”፡፡

ወገኖች የመጠነ ሰፊው የመልካምና የክፉ ውዝግብ አካል እንደመሆናቸው በእምነታቸው ሳቢያ ስደት ይደርስባቸዋል ሲል ጴጥሮስ ያመለክታል፡፡ በመጨረሻም--ፈተና ቢበዛም ለእውነት ታማኝ ሆነው እንዲጸኑ የተቻለውን ሊያደርግላቸው ምኞቱ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ይህም ርስት “ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል” (1962 ትርጉም) ስለዚህ ርስት የግል ባለቤትነትዎ ያስቡ፡፡ በሰማይ ለእርስዎ፣ ለግልዎ የተዘጋጀ ስፍራ አለ፡፡ ነገሩ እንዲህ ከሆነ--ለዚህ አስደናቂ ተስፋ የሚሰጡት ግላዊ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

መጋቢት 27
5-Apr

እንደ ዳነ ሰው መኖር


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 1፡13-21፡፡ በጥቅሶቹ መሰረት የክርስትና ባህሪ እንዲነሳሳና እንዲነቃቃ የሚያደርገው ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

1ጴጥ. 1፡13 የሚጀምርበት ሰለዚህ የሚለው ቃል ሐዋርያው በመቀጠል የሚናገረው- -ቀደም ብሎ ከተናገረው ላይ በልጽጎ የወጣ መሆኑን ያሳያል፡፡ ጴጥሮስ--ስለ እግዚአብሔር ጸጋና ክርስቲያኖች በየሱስ ክርስቶስ ላይ ስላላቸው ተስፋ መናገሩን በትናንቱ ጥናታችን ተመልክተናል (1ጴጥ. 1:3–12)፡፡

ለተሰጣችሁ ጸጋና ተስፋ “ራሳችሁን” በመግዛት (1ጴጥ. 1:13) አጸፋዊ ምላሽ አሳዩ ሲል ጴጥሮስ አጥብቆ አንባቢዎቹን ያስገነዝባል፡፡ ጽኑና ታማኝ ሆነው መቆም እንዲችሉ ልባቸውን ማዘጋጀት ከእነርሱ ይጠበቃል፡፡ ይህ አማኞች በየሱስ ላገኙት ደኅንነት የሚሰጡት ምላሽ ነው፡፡

ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡-- 1ጴጥ. 1፡13፡፡ ተስፋችንን ሙሉ በሙሉ በየሱስ የተገለጠው ጸጋ ላይ ማድረግ ስንል ምን ማለታችን ነው?

ነገሩ አጠያያቂም ባይሆን እነዚህ ወገኖች ተስፋቸውን በየሱስ ላይ ብቻ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጴጥሮስ ይነግራቸዋል፡፡ ክርስቲያኖች የዳኑ ሕዝቦች መሆናቸውን ተከትሎ ከወትሮው ማንነት የተለየ የባህሪ ለውጥ ከእነርሱ እንደሚጠበቅ ሐዋርያው አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል፡፡ ጴጥሮስ በክርስቲያኖች ልብ መነሳሳትና መነቃቃት በማምጣት ለባህሪ ለውጥ መንስኤ የሆኑ ሦስት ታላላቅ ነጥቦችን ያስቀመጠ ሲሆን እነርሱም፡--የእግዚአብሔር ጸባይ (1ጴጥ. 1፡15)፣ ፍርድ (1ጴጥ. 1፡17) እና ለደኅንነት የተከፈለው ዋጋ (1ጴጥ. 1፡17-21) ናቸው፡፡

በክርስቲያን ባህሪ ላይ መነሳሳትና መነቃቃት የሚያመጣው የመጀመሪያው ነገር የእግዚአብሔር ጸባይ ነው፡፡ ይህ አምላካዊ ጸባይ--እግዚአብሔር ቅዱስ ነው በሚል በጥቅሉ ሊቀመጥ ይችላል፡፡ ጴጥሮስ በዘሌዋ. 11፡44-45 የቀረበውን--“እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ” (1ጴጥ. 1:16) የተሰኘውን ጥቅስ ሲጠቅስ ይሰተዋላል፡፡ ከዚህ አኳያ የየሱስ ተከታይ የሆኑ ሁሉ ቅዱሳን ሊሆኑም የግድ ነው (1ጴጥ. 1፡15- 17)፡፡

ለክርስትና ባህሪ መነሳሳት ሁለተኛው መንስኤ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር ያለ አድሎ በእያንዳንዱ ላይ የመፍረዱ ሐቅ ነው (1ጴጥ. 1፡17)፡፡

በክርስቲያን ባህሪ ላይ መነሳሳትና መነቃቃት ለማምጣት በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ክርስቲያኖች የተዋጁበት ታላቅ እውነት ነው፡፡ ይህ ማለት ክርስቲያኖች በዋጋ ይኸውም እጅግ በከበረው በክርስቶስ ደም (1ጴጥ. 1፡19) ተገዝተዋል፡፡ የየሱስ ሞት በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ገቢራዊ የሆነ ክስተት ሳይሆን ነገር ግን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ የታቀደ ለመሆኑ አጽንኦት ይሰጣል (1ጴጥ. 1:20)፡፡

ክርስቲያን እንዲሆኑ ምክንያት የሆንዎት ነገር ምንድን ነው? አንድ ሰው ለምን ክርስቲያን ሆንክ / ሆንሽ ብሎ ቢጠይቅዎ ምን ይመልሳሉ? በመልስዎ ዙሪያ ተወያዩ፡፡

መጋቢት 28
6-Apr

እርስ በርስ መዋደድ


ጴጥሮስ በመቀጠል--የክርስቲያኖች የመጨረሻ መገለጫ የሆነው በቅድስና የተሞላና ታማኝ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል ይናገራል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ-- 1ጴጥ. 1፡22-25፡፡ ክርስቲያን ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ የሚያስቀምጠው ወሳኝ ነጥብ ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ክርስቲያኖች የነጹ ሕዝቦች (ነፍሳችሁን ስላነጻችሁ…) ስለሆኑ እውነትን በመታዘዝ ይኖራሉ በማለት ጴጥሮስ ጽፎአል (1ጴጥ. 1፡22)፡፡ ስላነጻችሁ (መንጻት) የተሰኘው ቃል ግስ ሲሆን ይህ ቃል ጴጥሮስ ቀደም ብሎ በ--1ጴጥ. 1፡15 ቅዱስ እና ቅድስና በሚል ከጠቀሰው ቃል ጋር ተቀራራቢ ዝምድና አለው፡፡ ክርስቲያኖች ለየሱስ በገቡት ቃል እንዲሁም በጥምቀት (1ጴጥ. 3፡21-22) ለእውነት ታዛዥ ሆነው ከእግዚአብሔር ጋር በመመላለስ ራሳቸውን አንጽተዋል፡፡

ይህ በሕይወታቸው ላይ ገቢራዊ የሆነ ለውጥ ያስከተለውን ተፈጥሮአዊ ውጤት ተከትሎ ስለ ዓለም ተመሳሳይ አመለካከት ከሚጋሩ ወገኖች ጋር ራሳቸውን በቅርበት ያገኙታል፡፡ ግንኙነቱ እጅግ ጠንካራ በመሆኑ ጴጥሮስ ቤተሰብ የሚለውን ቃል በገላጭነት ሲጠቀም ይስተዋላል፡፡ በክርስቲያን ወንዶችም ሆነ ሴቶች መሃል ቤተሰባዊ ፍቅር ሊኖር ይገባል፡፡ ጴጥሮስ “ለወንድሞቻችሁ…ፍቅር ይኑራችሁ” (1ጴጥ. 1፡22) በሚል ያሰፈረው የግሪኩ ቃል ፊላደልፊያ --ቃል በቃል ሲተረጎም የወንድም እህቶች ፍቅር የሚል ፍቺ አለው፡፡ ይህ ፍቅር በአንድ የቤተሰብ አባላት መሃል እንዲኖር የሚጠበቀው ዓይነት ነው፡፡

“ፍቅር” የተሰኘው ቃል በግሪክ ቋንቋ ልዩ ልዩ ፍቺዎች አሉት፡--ፊሊያ (የጓደኝነት ፍቅር)፣ ኢሮስ (የባልና የሚስት ፍቅር)፣ አጋፔ (ለሌሎች በጎ የሚመኝ ንጹህ ፍቅር) ፡፡ ጴጥሮስ “እርስ በርሳችሁም አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” (1ጴጥ. 1፡22) በማለት የጻፈው መልእክት ላይ የሚገኘው ቃል ስለ ሌሎች በጎ ከሚመኘው ንጹህ ፍቅር አጋፔ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ሐዋርያው “እርስ በርሳችሁም” ካለ በኋላ “አጥብቃችሁ ከልብ” የተሰኘውን ሃረግ የጨመረበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡ ይህ “ዳግመኛ ከመወለድ” (1ጴጥ. 1፡23፣ 1፡3) የሚገኝ ልብ በታማኙ የእግዚአብሔር ቃል አማካይነት የየግላችን የምናደርገው ነው፡፡ እንዲህ ያለው ፍቅር ራስ ወዳድ አይደለም፣ እኔነትን ማዕከል ያደረገ ወይም ለመለወጥ ዝግጁ ያልሆነ የሥነ ምግባር ጉድለትም እንዲሁ አይታይበትም፡፡ ለዚህ መንስኤው ይህ ፍቅር የሚመጣው ከእግዚአብሔር ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ ጴጥሮስ ስለ መንጻትና ለእውነት ስለ መታዘዝ አጽንኦት የሚሰጥበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡

አብልጠን አፍቃሪ መሆንን የምንማረው እንዴት ነው? ከ “ንጹህ ልብ” የሚመነጨውን ፍቅር ለማሳየት ምን ዓይነት ምርጫዎች ማድረግ ይኖርብናል?

መጋቢት 29
7-Apr

ተጨማሪ ሃሳብ፡-


Read Ellen G. White, “Perfect Obedience Through Christ,” pp. 374, 375 in Selected Messages, book 1. See also Ellen G. White, “Christ the Way of Life,” pp. 365–368, and “Perfect Obedience Through Christ,” pp. 373–376 in Selected Messages, book 1.

ይህ የመጀመሪያው የጴጥሮስ መልእክት የከበረ፣ ጥልቅና ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮችን መሸፈኑ በእርግጠኝነት አስደናቂ ያደርገዋል፡፡ ጴጥሮስ በእግዚአብሔር አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ባህሪ ላይ ተመስጦአዊ ማሰላሰል በማድረግ መልእክቱን መጻፍ ይጀምራል፡፡ አብ በልጁ በየሱስ ክርስቶስ አማካይነት አዳኝ የሰጠን ሲሆን--እኛም የተቀደሰና ታዛዥ ሕይወት እንድንኖር በእርሱ ተመርጠናል፡፡ በየሱስ ሞትና ትንሳኤ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት እንደገና የመወለዳችን ተስፋ በሰማይ ስላለን የሱስን በመውደድ ወደ እርሱ እንቀርባለን፤ በእርሱም ሐሴት እናደርጋለን፡፡ በእምነታችን የተነሳ በአስቸጋሪ ሁናቴ ውስጥ ሆነን እንኳ በክርስቶስ ባገኘነው ደስታ አብልጠን ሐሴት እናደርጋለን፡፡ “መልእክቶቹ በመከራና ሥቃይ ውስጥ የሚያልፉ ወገኖች መነቃቃትና መበረታታት የሚያገኙባቸው--እንዲሁም በተለያዩ ፈተናዎች መንስኤ እግዚአብሔርን የመልቀቅ አደጋ የተጋረጠባቸው እጆች መልካሙን ምግባር ዳግም እንዲያድሱ የሚያስችል ነው፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 517. በጴጥሮስ መልእክት መሰረት ክርስቲያኖች “ከንጹህ ልብ በሚመነጭ” ፍቅራቸው በማኅበረሰቡ ተለይተው የሚታወቁ፣ የተቀደሰ ሕይወት የሚኖሩና እውነትን ለመታዘዝ ፈቃደኛ ልብ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡


የመወያያ ጥያቄዎች:



በረቡዕ ጥናት መጨረሻ ላይ ለቀረበው ጥያቄ የሰጡትን መልስ ይመልከቱ፡፡ ክርስቲያን እንድንሆን ያነሳሳን ምንድን ነው? የእርስዎ መልሶች የሌሎችን የሚጋራው በየትኞቹ ነጥቦች ነው? የሚለዩትስ? ጴጥሮስ ስለ የሱስ ትንሳኤ በዚህ ምዕራፍ ሁለት ጊዜ ይናገራል (1ጴጥ. 1፡3፣ 21)፡፡ የየሱስ ትንሳኤ ለእምነታችን ወሳኝ የሆነበት ምክንያቱ ምንድን ነው?

 ጴጥሮስ ለማይጠፋ፣ ለማይበላሽና ለማይለወጥ ርስት ስለ መወለድ ይናገራል (በተጨማሪ ዳን. 7፡18 ይመልከቱ)፡፡ ምን ማለቱ ነው? በዚህ ዓለምና በዚህ ሕይወት ያሉ ነገሮች ሁሉ የሚጠፉ ስለመሆናቸው አሰብ ያደርጉ፡፡ ይህ--ቃል ስለተገባልንንና ስለምንወርሰው ርስት እርግጠኛ ተፈጥሮ ምን ሊነግረን ይገባል?

 እምነታችን በፈተና ውስጥ ማደግ የሚችለው እንዴት ነው? ይህ ማለት-- ሥቃይ ካየንባቸው ነገሮች ትምህርት እንድንቀስም ሊረዱን የሚችሉ ምን ዓይነት ምርጫዎችን ማድረግ እንችላለን?