ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 3:8–12፣ ገላ. 2:20፣ 1ጴጥ. 4:1, 2፣ ሮሜ. 6:1–11፣ 1ጴጥ. 4:3–11፣ 2ሳሙ. 11:4.
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “ምክንያቱም የጌታ ዐይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉና፤ ጆሮዎቹም ጸሎታቸውን ለመስማት የተከፈቱ ናቸው፤ የጌታ ፊት ግን በክፉ አድራጊዎች ላይ ነው” (1ጴጥ. 3:12)፡፡
የ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የሰብዓዊውን ኃጢአተኝነት በተጨባጭ
ያስተውሉ ነበር፡፡ ከዚህ ውጪ እንዴት ሊያውቁ አይችሉም ተብሎ
ይታሰባል? ዓለም በኃጢአት መጥፎ ጠረን ተሞልታለች፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን
የራሳቸውንም ኃጢአተኝነት ጠንቅቀው ያውቁ ነበር (1ጢሞቴ. 1፡15)፡፡ ኃጢአት
በዋዛ መታየት የማይችል ገዳይ መሆኑንም ያስተውሉ ነበር፡፡ ለኃጢአት ችግር
መፍትሔ ባመጣው የየሱስ ክርስቶስ መስቀል ላይ የሆነውን ማየት ለዚህ ጥሩ
ማስረጃ ይሆነናል፡፡ ኃጢአት ያን ያህል ጥልቅና የሚከረፋ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሕይወታችንን መለወጥ ስለሚችለውና በእርሱ አዲስ
ፍጥረቶች ስለሚያደርገን የክርስቶስ ኃይል የጠለቀ ግንዛቤ ነበራቸው፡፡
ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለእርሱ ሰጥተው ከተጠመቁ በኋላ በክርስቶስ
ስለሚኖራቸው አዲስ ህይወት የሚያወሳው--ተመሳሳይ የጴጥሮስ መልእክት በዚህም
ሳምንት ይቀጥላል፡፡ በእርግጥ ክርስቲያኖች በሚቀዳጁት አዲስ ህይወት የሚታየው
ለውጥ ከፍ ያለ ስለሚሆን በሌሎችም መስተዋል የሚችል ይሆናል፡፡ በእርግጥ
ለውጡ ሁሌም አልጋ ባልጋ እንደማይሆን የሚነግረን ጴጥሮስ፤ ቃል የተገባልን ድል
ባለቤቶች ለመሆን በሥጋ (1ጴጥ. 4፡1) ሊደስብን ስለሚችል ሥቃይ ያወሳናል፡፡
ጴጥሮስ በመጽሐፍ ቅዱስ በስፋት የቀረበው ርዕሰ ጉዳይ አካል ስለ ሆነውና፤ በየሱስ
ባመነው ክርስቲያን ሕይወት በተጨባጭ ስለሚታየው ፍቅር መንገሩን በመቀጠል
“ፍቅር ብዙ ኃጢአትን ይሸፍናል” (1ጴጥ. 4:8) ይለናል፡፡ ለሰዎች ፍቅር ሲኖረንና
ሌሎችን ይቅር ስንል--የሱስ ያደረገልንንና እያደረገልን ያለውን እናንጸባርቃለን፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 3፡8-12፡፡ ክርስቲያኖች እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባ
አስመልክቶ ጴጥሮስ የሚያነሳው ነጥብ ምን ይመስላል? ቀደም ብሎ 1ጴጥ. 2፡20-21
ከጻፈው ላይ በድጋሚ ያቀረበው ሃሳብ የትኛው ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ ሁሉም “በአንድ ሐሳብ” እንዲስማሙ በመንገር መልእክቱን ይጀምራል፡፡
መልእክቱ--የአንዱ ሰው አስተሳሰብና ድርጊት የሌላው ግልባጭ ይሁን ሳይሆን
የሁሉም እምነት ወጥና አንድ ዓይነት ይሁን የሚል አንደምታ አለው፡፡ በ1ቆሮ. 12፡1-
26 ለዚህ ጽንሰ ሃሳብ ምርጥ ምሳሌ እናገኛለን፡፡ አካል እንደ እጅና ዐይን ያሉ
የተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ቢኖሩትም መሰረታዊ አንድነቱ ግን የተጠበቀ ነው፡፡
በተመሳሳይ ቤተ ክርስቲያንም የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎች ባሏቸው ልዩ ልዩ
ግለሰቦች የተገነባች ናት፡፡ አባላት በእነዚህ ልዩነቶች መሃል የዓላማ አንድነትና አንድ
ዉሁድ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል በጋራ የመሥራት መንፈስ አላቸው፡፡
ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ አሳዛኝ ገጽታዎች በግልጽ መመልከት እንደምንችለው
እንዲህ ዓይነቱን ሕብረት ማምጣት ሁሌም ቀላል አይደለም፡፡ ሆኖም ጴጥሮስ
በዚህ ዙሪያ ከሰጠው ግሳጼ ቀጠል አድርጎ አንባቢዎቹ ይህን ክርስቲያናዊ እሴት
እንዴት መግለጽ እንደሚኖርባቸው ይናገራል፡፡
ለምሳሌ ክርስቲያኖች ትሁታን መሆን አለባቸው ( 1ጴጥ. 3፡8)፡፡ ይህ ማለት
በአንዱ ክርስቲያን ላይ ሥቃይ ሲደርስ ማጽናናትና የስሜቱ ተካፋይ መሆን ነው፡፡
ሌላው ክርስቲያን ደስ ሲሰኝም እንዲሁ የደስታው ተካፋይ ሆኖ አብሮ መደሰት ነው
(1ቆሮ. 12፡26)፡፡ ትህትና ወደ ኅብረት ሊያመጣን የሚችለውን መሰረታዊውን
የሌሎች አስተሳሰብ መጋራት ያስችለና፡፡ በመቀጠል ጴጥሮስ “እርስ በርሳችሁ
ተዋደዱ” (1ጴጥ. 3:8) ይለናል፡፡ እውተኛ ደቀ መዛሙርትን ለይተን ማወቅ
ከምንችልባቸው መንገዶች አንዱ የእርስ በርስ ፍቅራቸው መሆኑን የሱስ ራሱ
ነግሮናል (ዮሐ. 13፡35)፡፡ በተጨማሪ ክርስቲያኖች ርኅሩኅ ልብ እንዳላቸው
ጴጥሮስ ይነግረናል (1ጴጥ. 3፡8)፡፡ ክርስቲያኖች በሚገጥማቸው አስቸጋሪ ሁኔታም
ሆነ ውድቀት አንዱ ሌላው ርኅራኄ ይኖረዋል፡፡
“ራስን ለሌሎች መሥዋዕት ባደረገ ሕይወት እየተመላሱ ከራስ አስበልጦ ለሌሎች
ከፍተኛ ግምት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ሲሆን በክርስቶስ አንድ ወደ መሆን
እንመጣለን፡፡ የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች ለመሆናችን በሰማያዊው
አካላት፣ በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ፊት የማያጠራጥር ምስክር እንሆናለን፡፡
በእርስዎ ውስጥ በሚታየውም ምሳሌነት እግዚአብሔር ይከብራል፡፡”—Ellen G.
White, Testimonies for the Church, vol. 9, p. 188.
ጴጥሮስ “ክፉን በክፉ አትመልሱ” (1ጴጥ. 3:9) በማለት የሚሰጠውን መልእክት
ምን ያህል ተግባር ላይ እናውለዋለን? እነዚህን ቃላት መታዘዝ እንድንችል የሥጋን
ፈቃድ መግደል የሚኖርብን እንዴት ነው? ይህን ዓይነቱን የሥጋ ሞት ገቢራዊ
ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? (ገላ. 2፡20)፡፡
የሱስ ስለ እኛ በመሞቱ የመዳን ተስፋችን መሰረት የተጣለው በእርሱ ላይ ነው፡፡
የእርሱ ጽድቅ እኛን ስለሚሸፍን በአብ ፊት እንደ ጻድቅ እንታያለን፡፡ በየሱስ የተነሳ
“ኃጢአት እንዳልሠራ ሆነን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እናገኛለን”—Ellen G.
White, Steps to Christ, p. 62.
አምላካዊው ጸጋ ኃጢአታችን ይቅር መባሉን በመንገር ብቻ አያበቃም፡፡ ይልቁንም
ኃጢአት የምናሸንፍበትንም ኃይል እግዚአብሔር ይሰጠናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡- 1ጴጥ. 3:18፣ 21፣ 1ጴጥ. 4:1- 2፣ ሮሜ 6:1–11፡፡ አካላዊውን
ሥቃይና በኃጢአት ላይ አሸናፊነት ማግኘትን የሚያስተሳስራቸው ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በ1ጴጥ. 3፡18 ስለ የሱስ የመሥዋዕትነት ተፈጥሮ ሰፊነት አጽንኦት ለመስጠት ጥቅም
ላይ የዋለ የግሪክ ቃል አለ፡፡ ቃሉ hapax ሲሆን “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” በሚል
ተተርጉሟል፡፡ የሱስ ስለ እኛ የደረሰበት ሥቃይና ሞት ተፈጥሮው ሰፊ መሆኑን
አጽንኦት ለመስጠት ሲል ጴጥሮስ ይህን የግሪክ ቃል ጥቅም ላይ አውሏል፡፡
1ጴጥ. 4፡1 እና 2 ለማስተሳሰር በመግቢያው ላይ “እንግዲህ” በሚል የተጠቀሰው
ቃል ቀደም ሲል በ1ጴጥ. 3፡ 18-19 የቀረበውንም ሃሳብ በአንድ ያያይዛል፡፡ ክርስቶስ
ያለ ነቀፋ በእግዚአብሔር ፊት እንድንቀርብ ለማድረግ ሲል ስለ ኃጢአታችን
መሠቃየቱን ጴጥሮስ ቀደም ብሎ ጠቁሞናል (1ጴጥ. 3፡18)፡፡ “ይህም ውሃ አሁን
የጥምቀት ምሳሌ ሆኖ ያድናችኋል” (1ጴጥ. 3:21)፡፡
ምናልባት ጥምቀት የጴጥሮስን ዐውደ ሃሳብ በቅጡ እንድናስተውል ሊረዳን ይችላል
“ክርስቶስ በሥጋው መከራን ስለ ተቀበለ…” (1ጴጥ. 4:1)፡፡ ክርስቲያኖች በጥምቀት
የየሱስን ሥቃይ፣ ሞት፣ ህይወትና ትንሳኤ በአንድ ይጋራሉ፡፡ ክርስቲያኖች
“ከእንግዲህ በሚቀረው ምድራዊ ሕይወት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ
ሥጋ ምኞት” ላይኖሩ ምርጫ ያደርጋሉ (1ጴጥ. 4:2)፡፡ ይህ ገቢራዊ መሆን
የሚችለው “ሥጋን ከከፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር” (ገላ. 5:24) እየሰቀሉ ራሳቸውን
በየቀኑ ለጌታ ሲሰጡ ነው፡፡
በጥምቀት ክርስቲያኖች ከየሱስ ጋር በሞቱና በትንሳኤው አንድነት እንደሚፈጥሩ
ጳውሎስ በሮሜ 6፡1-11 ይነግረናል፡፡ በጥምቀት ለኃጢአት መሞታችንን
አሳይተናል፡፡ ስለዚህ አሁን ለኃጢአት በመሞት ያሳየነው ትዕይንት ተጨባጭ
የሕይወታችን ክፍል እንዲሆን ለማድረግ እንሻለን፡፡ “እንዲሁም ለኃጢአት እንደ
ሞታችሁ፣ ነገር ግን በክርስቶስ ኢየሱስ ለእግዚአብሔር ሕያዋን እንደ ሆናችሁ
ራሳችሁን ቁጠሩ” (ሮሜ 6:11)፡፡ የክርስትናን ህይወት ምስጢር ገልጦ መሳየት ከእኛ
ይጠበቃል፡፡
ለመጨረሻ ጊዜ “በሥጋ መከራ” የተቀበሉት መቼ ነው? መልስዎ ስለ ክርስትና
ሕይወትዎ ምን ይናገራል?
በክርስቶስ አዲስ ህይወትና አዲስ ጅማሮ አግኝተናል፡፡ የሁለተኛ ልደት
ባለቤትነትንም ተቀዳጅተናል፡፡ ክርስቶስን ከልጅነታቸው ሳይሆን ዘግየት ብለው
የተቀበሉ አዲሱን ህይወት ከቀድሞው ጋር ሲያስተያዩት ፍጹም የተለየ ሆኖ
እንደሚያገኙት አያጠራጥርም፡፡ ቀድሞ በዓለም በመመላለሳቸው አስደናቂውን
ታሪክ ያልሰሙ ወገኖች ከየሱስና ከአዳኝ ጸጋው የተነሳ--መሰረታዊና የተሟላ ለውጥ
የሚያመጣውን የእርሱን ኃይል አልተለማመዱምን?
ጴጥሮስ በሥጋ ስለ ኃጢአት ስለ መሞትና በየሱስ ስለምናገኘው አዲስ ህይወት
(በሞቱና ትንሳኤው ስለ መጠመቅ) ከተናገረ በኋላ አማኙ በህይወቱ
ስለሚለማመደው ለውጥ ያወሳል፡፡
ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 4፡3-6፡፡ በአማኙ ሕይወት ገቢራዊ የሚሆነው ለውጥ
ምን ይመስላል? ሌሎች ስለ ለውጦቹ የሚሰጡትስ አስተያየት ምን ሊሆን ይችላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጴጥሮስ የቀድሞው ሥጋዊ መመላለስ አካል የነበሩ እንደ ስካር ያሉ ዓለማዊ
ልማዶችን ይጠቅሳል፡-- “ያለ ልክ መጠጣት”፣ “ስካር”፣ “መዳራት” “ሥጋዊ
ምኞት”፣ “ጭፈራ”፡፡ የዛሬዎቹን አማኞች በአሮጌው ህይወት ያውቋቸው የነበሩ
የሚያዩት ነገር “እንግዳ ሆኖባቸው” እስኪደነቁ--የሱስን ከተቀበሉ በኋላ
በህይወታቸው የሚስተዋለው ለውጥ የቀድሞው ብክነት የማይታይበት--ታላቅ
ሊሆን ይገባል (1ጴጥ. 4፡4)፡፡ በዚህም ለማያምኑት መስበክ ሳያስፈልገን
በህይወታችን ብቻ ምስክር መሆን የምንችልበትን ዕድል መመልከት እንችላለን፡፡
እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚመላለስ ህይወት የሚመራ ክርስቲያን በዓለም ካሉ
ስብከቶች ሁሉ የላቀ ምስክር መሆን ይችላል፡፡
ጴጥሮስ ፍርድን አስመልክቶ ምን ይላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
እንደሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ሁሉ (ዮሐ. 5:29፣ 2ቆሮ. 5:10፣ ዕብ. 9:27)
በዚህም ላይ “እንደ ሥጋ ምኞት” (1ጴጥ. 4:2) መመላለስ አንድ ቀን በፍርድ ፊት
እንደሚያቆም ጴጥሮስ ይናገራል፡፡ ጴጥሮስ “ወንጌል ለሙታን እንኳ ሳይቀር
የተሰበከው” (1ጴጥ. 4:6) ብሎ መናገሩ፤ አሁን የሞቱ ሰዎች ቀደም ብለው
በህይወት በነበሩበት ወቅት የሚያድነውን አምላካዊ ጸጋ የሚያውቁበትን ዕድል
አግኝተዋል ማለቱ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ጻድቅ ፍርዱን ይሰጣቸዋል፡፡
አሁን የሱስን የግል አዳኝዎ አድርገው የተቀበሉ አማኝ እንደመሆንዎ የዛሬው
ህይወትዎ አማኝ ካልነበሩባቸው ዘመናት በምን ይለያል? የሱስ በህይወትዎ
ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው?
ሰዎች የሱስን ተቀብለው አማኝ ከመሆናቸው አስቀድሞ የሠሯቸው ብዙ ኃጢአቶች
የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ አንዱ “መዳራት” እንደሆነ ጴጥሮስ ይገልጽልናል፡፡
በተጨማሪ ጴጥሮስ ዝርዝር ውስጥ የሚያስገባቸው ምን፣ ምን ናቸው? (1ጴጥ.
4፡3)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በጥቅሱ ከሰፈሩት መሃል “መዳራት” እና “ሥጋዊ ምኞት” ከወሲብ ጋር ቀጥተኛ
ቁርኝት አላቸው፡፡
ይህም ሆኖ በሥነ ወሲብ ዙሪያ በክርስቲያኖች ላይ በቀላሉ የተሳሳተ ተጽእኖ
ሊፈጠር ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ወሲባዊ ግንኙነትን የሚቃረን አስተምህሮ
አያራምድም፡፡ ይልቁንም በእግዚአብሔር ተፈጥሮ--በታላቅ ስጦታነት ለሰብዓዊው
ፍጡር ተበርክቶአል፡፡ ገና በመጀመሪያ በኤድን የተቀደሰ ወሲባዊ ግንኙት ነበር
“ስለዚህ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ተለይቶ ከሚስቱ ጋር ይጣመራል፤ ሁለቱ አንድ
ሥጋ ይሆናሉ፡፡ አዳምና ሚስቱ፣ ሁለቱም ዕራቁታቸውን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ
አይተፋፈሩም ነበር” (ዘፍ. 2:24, 25)፡፡ ወሲባዊ ግንኙነት ባልና ሚስት ልጆች
የሚያፈሩበትና--የማይነጣጠሉ የህይወት ጓደኛሞች አድርገው ከሚያስተሳስሩ ቁልፍ
ቅመሞች አንዱ ተደረገ፡፡ ይህ የፍቅር ቁርኝትና አንድነት እግዚአብሔር
ከሕዝቡ ጋር እንዲኖረው የሚመኘው ግነኙነት ነጸብራቅ ነው (ኤር. 3፣ ሕዝ. 16፣
ሆሴ 1-3)፡፡
በጋብቻ የተሳሰሩ ወንድና ሴት በትክክለኛው ስፍራ የሚያደርጉት ወሲባዊ ግንኙነት
ጥልቅ እውነት ያዘለ በረከት አለው፡፡ ሆኖም በተሳሳተ ስፍራና ልክ ባልሆነ አግባብ
ከተደረገ--በዓለም አውዳሚ ከሆኑ ኃይላት አንዱ ይሆናል፡፡ አሁን እየተስተዋሉ
ያሉት የዚህ ኃጢአት አውዳሚ ውጤቶች በሰብዓዊው አእምሮ ሊገመቱ
አይችሉም፡፡ ይህ ድንቅ ስጦታ በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል በህይወት ላይ
ሊያስከትል የሚችለውን መመሰቃቀል ማስተዋል የሚሳነው ህሊና ይኖር ይሆን?
የሚከተሉት ጥቅሶች በጋራ የያዟቸው ሃሳቦች ምንድን ናቸው? 2ሳሙ. 11:4፣ 1ቆሮ.
5:1፣ ዘፍ. 19:5፣ 1ቆሮ. 10:8፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በእርግጥ እነዚህ ኃጢአቶች የፈጠሩትን ህመምና ሥቃዮች ለመገንዘብ አንድ ሰው
የግድ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክቶች ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡
ይህም ሆኖ ጠንቃቆች መንሆን ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ኃጢአት በሰዎች ላይ ግዙፍ
አሉታዊ ተጽእኖ የማሳደር ተፈጥሮ ስላለው ማኅበረሰቡ በጥላቻ ሲመለከተው
ይስተዋላል፡፡ እንደ ሌላው ኃጢአት ሁሉ የክርስቶስ ሞት የምንዝርንም ኃጢአት
ይሸፍናል፡፡ ክርስቲያኖች በተለይ በዚህ በእጅጉ ጥንቃቄ በሚጠይቅ ጉዳይ ዙሪያ
ጠንቃቆች ልንሆን ይገባል፡፡ “በመጀመሪያ በዐይንህ ውስጥ የተጋደመውን ግንድ
አውጣ፤ ከዚያ በኋላ በወንድምህ ዐይን ውስጥ ያለውን ጉድፍ ለማውጣት አጥርተህ
ታያለህ” (ሉቃ. 6:42)፡፡
የየሱስን ዳግም መገለጥና
በጴጥሮስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖችም እንኳ
የምድርን ፍጻሜ ተስፋ አድርገው ይመላለሱ ነበር፡ “የሁሉ ነገር መጨረሻ
ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም
የምትገዙ ሁኑ” (1ጴጥ. 4:7)፡፡ መልእክቱ በሌላ አነጋገር ለምድር መጨረሻ ዝግጁ
ሁኑ የሚል አንደምታ አለው፡፡ “መጨረሻ” የሚለው ቃል በብዙዎቻችን ዘንድ
ስንሞት ከሚል የዘለለ አንደምታ የለውም፡፡ ዐይኖቻችን በሞት ከተጨፈኑ
በሺህዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ወይም ጥቂት ቀናት ብቻ ቢቆጠሩ--በቀጣይ
የምናውቀው ነገር የየሱስን ምጽአት ወይም የምድርን መጨረሻ ነው፡፡
በጴጥሮስ መልእክት መሰረት “የሁሉ ነገር መጨረሻ” የተቃረበ እንደመሆኑ
የክርስቲያኖች ህይወት ምን ሊመስል ይገባል? (1ጴጥ. 4:7–11)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ክርስቲያኖች በጸሎት ከመትጋትና ተግቶ ከመጠባበቅ በተጨማሪ “ፍቅር ብዙ
ኃጢአት ይሸፍናልና ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ” (1ጴጥ. 4:8)፡፡
ፍቅር ብዙ ኃጢአት ይሸፍናል ማለት ትርጉሙ ምንድን ነው? ጴጥሮስ ጥቅም ላይ
ያዋለውን ይህን ጥቅስ የወሰደው ከመጽሐፈ ምሳሌ ነው፡ “ጥላቻ ጠብን ያነሣሣል፤
ፍቅር ግን ስህተትን ሁሉ ይሸፋፍናል” (ምሳ. 10፡12)፡፡ እርስ በርሳችን ስንዋድ
የጎዱንንና ያሳዘኑንን ይቅር ለማለት ሁሌም ዝግጁዎች እንሆናለን፡፡ ክርስቶስ ለእኛ
ያለው ፍቅር ይቅር እንዲለን እንዳስቻለው ሁሉ እኛም ሌሎችን በመውደድ ይቅር
ማለት ይጠበቅብናል፡፡ ፍቅር በተትረፈረፈበት--ትናንንሾቹም ሆኑ ትላልቆቹ ስሜት
የሚጎዱ ተግባራት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጣቸውና የሚረሱ ይሆናሉ፡፡
ሕግ ሁሉ እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ በመውደድና ባልንጀራን እንደ ራስ
በመውደድ እንደሚጠቃለል በየሱስና በጳውሎስ የቀረቡት ሃሳቦች ላይ ጴጥሮስም
ገለጻ ሲያደርግ ይስተዋላል (ማቴ. 22፡34-39፣ ሮሜ 13፡8-11)፡፡
ክርስቲያኖች እንግዳ ተቀባይ ሊሆኑ እንደሚገባ ጴጥሮስ ሲያደፋፍር ይታያል፡፡
ዳግም ምጽአቱ እየተቃረበ ቢመጣም ክርስቲያኖች በዚህ ምክንያት ከማኅበረሰብ
አቀፍ ግንኙነት ራሳቸውን ሊገቱ እንደማይገባ ይናገራል፡፡ በመጨረሻም--
ክርስቲያኖች በሚናገሩት የሚኖሩ የተግባር ሰዎች ሊሆኑ እንደሚገባ ጴጥሮስ
ይናገራል፡፡ በሌላ አነጋገር የጊዜው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነ መምጣት--በመንፈሳዊ
እውነት ዙሪያ ለነገ የማይባል ጽኑ ትስስር መፍጠር እንዳለብን ያስገነዝበናል፡፡
“ፍቅር ብዙ ኃጢአት ይሸፍናልና፡፡” በደል የፈጸመብዎ ሰው ማን ነው? እንዲህ
ያለውን በደል (ኃጢአት) “ለመሸፈን” የሚያስችል እንዴት ያለ ፍቅር ከእርሶ
መገለጥ ይኖርቦታል? ይህን በማድረግ ተጠቃሚው ራስዎ የሆኑት እንዴት ነው?
“ታጋሽና ደግ ፍቅር ዘለፋን ወይም ክፉ አድራጎትን
ይቅር ወደማይባል በደል አያገንም፡፡ ስህተቶች በትዕግሥትና በበጎ ህሊና
ሊስተናገዱ እንደሚገባ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ያስተምራል፡፡ ትክክለኛውን
አካሄድ የምንከተል ከሆነ ችኮ የሆነውን ልብ ለክርስቶስ ማሸነፍ እንችላለን፡፡ የየሱስ
ፍቅር አያሌ ኃጢአቶችን ይሸፍናል፡፡ የግድና በአዎንታዊ ጎኑ ካልሆነ በቀር--ጸጋው
የሌሎችን ስህተት አጋልጠን አሳልፈን እንድንሰጣቸው ሊያደርገን አይችልም፡፡”—
Ellen G. White, Counsels to Parents, Teachers, and Students, p. 267.
ለምሳሌ ስለ የሱስና በምንዝር ስለተያዘችው ሴት ያስቡ (ዮሐ. 8፡1-11)፡፡ ብዙውን
ጊዜ የዚህችን ሴት ታሪክ ከክርስቶስ ጸጋ ጋር አያይዘን ስናቀርብ ብንስተዋልም--
ትክክል ነን፡፡ ሆኖም ገዳዩ ከዚያም የጠለቀ መልእክት አለው፡፡ የሱስ ይህችን ሴት
ወደ እርሱ ካመጡ የኃይማኖት መሪዎች ጋር ባደረገው ፍጥጫ ጎንበስ ብሎ
“ምስጢራዊውን የህይወታቸውን በደል” (Ellen G. White, The Desire of Ages,
p. 461) በምድር ላይ ለምን ጻፈ? ስለነዚህ ከሳሾች ያውቅ የነበረው ጌታ ከእርሷ
የሚስተካከል ወይም የከፋ ኃጢአታቸውን አንድ በአንድ እየዘረዘረ በሰዎች ፊት
ለምን በግልጽ አልከሰሳቸውም? የሱስ ግን በዚያ ፋንታ ግብዝነታቸውንና
ክፋታቸውን እንደሚያውቅና--ለሌሎች ሊያጋልጣቸው ግን እንደማይፈልግ
አሳያቸው፡፡ ምናልባት የልባቸውን ሃሳብ እንደሚያውቅ ማሳየትና የሚድኑበትን
ዕድል መስጠት የሱስ ወደነዚህ ሰዎች መድረስ የሚችልባቸው ብቸኛው መንገዶች
ነበሩ፡፡ ታሪኩ በኃጢአት ከወደቁ ጋር የምንጋጠምባቸው አጋጣሚዎች ሲከሰቱ ምን
ማድረግ እንዳለብን አስመልክቶ ብርቱ ትምህርት ይሰጠናል፡፡
አማኞች የየራሳችንን ማንነት እንደ ያዝን፣ አንዱ ሌላውን ሳይመስል ልንመሰርት
ስለሚገባ ህብረት ተነጋገሩ፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን በፍጹም ህብረት
መንቀሳቀሳችንን የሚጠይቁ የአገልግሎት ክፍሎች ይኖሩ ይሆን? ካሉ የትኞቹ
ናቸው? ይህን አንገብጋቢ ህብረት ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? በተቃራኒው
ኃጢአት መሥራት ለማቆም “በሥጋ መከራ መቀበል” አስፈላጊ ስለመሆኑ
ከሚያወሳው ጽንሰ ሃሳብ ጋር በተያያዘ የግል ተሞክሮዎ ምን ይመስላል? ምን ይህ
ማለት ነው? በውስጣችን የሚኖረው የእግዚአብሔር ኃይል ይለውጠናል ማለት
አሸናፊዎች ለመሆን ሥቃይ አይደርስብንም የሚል ፍቺ አለው? ካልሆነ ለምን?
የአልኮል መጠጥ በብዙዎች ህይወት ላይ እያደረሰ ያለውን አስደንጋጭ ውጤት
ለመመልከት ይሞክሩ፡፡ ሌሎች የአልኮልን አደጋ መመልከት እንዲችሉ እንደ ቤተ
ክርስቲያን ምን ማድረግ እንችላለን? ወጣቶቻችን የዚህ ስህተት ሰለባ እንዳይሆኑ
ግንዛቤ በማስጨበጡ ረገድ የአልኮልን ገዳይነት በእንዴት ዓይነት ምሳሌ ወይም
ቤተ ሙከራ ልናሳያቸው እንችላለን?