በጎቼን መግብ፡ 1ኛ እና 2ኛ ጴጥሮስ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከግንቦት 12-18

ዘጠነኛ ትምህርት

May 20 -26


በተጠራነው መሰረት መመላለስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1:1– 15፣ ኤፌ. 2:8፣ ሮሜ 5:3–5፣ ዕብ. 10:38፣ ሮሜ 6:11፣ 1ቆሮ. 15:12–57፡፡


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - “በዚህም ምክንያት በሙሉ ትጋት በእምነታችሁ ላይ በጎነትን ለመጨመር ጣሩ፤ በበጎነት ላይ ዕውቀትን፣ በዕውቀት ላይ ራስን መግዛት፣ ራስን በመግዛት ላይ መጽናትን፣ በመጽናት ላይ እውነተኛ መንፈሳዊነትን፣ በእውነተኛ መንፈሳዊነት ላይ ወንድማዊ መተሳሰብን፣ በወንድማዊ መተሳሰብ ላይ ፍቅርን ጨምሩ” (2ጴጥ. 1:5–7)፡፡

በ ጣም ውሱን በሆነው ቦታ ውስጥ ምን ያህል እውነት መታጨቅ ይችላል-- የሚለው ከአዲስ ኪዳን አስገራሚ ነገሮች አንዱ ነው፡፡ ከ2ጴጥ. 1፡1-14 የሚሸፍነውን የዚህን ሳምንት ጥናታችንን ለመቃኘት ይሞክሩ፡፡ ጴጥሮስ በእነዚህ አስራ አራት ቁጥሮች ስለ ጽድቅ በእምነት ያስተምረናል፡፡ በመቀጠል ራሳቸውን ለየሱስ አሳልፈው በሰጡ ወገኖች ሕይወት የእግዚአብሔር ኃይል ማከናውን ወደሚችለው ነገር ያመራል፡፡ “ከመለኮታዊ ባሕርይ” (2ጴጥ. 1:4) ተካፋይ በመሆን ከምግባረ ብልሹነትና ከምንዝር ነጻ ህይወት መምራት የምንችልበትን አስደናዊ እውነት ጴጥሮስ ይነግረናል፡፡

ጴጥሮስ በዚህ መልእክቱ ክርስቲያኖች ሊኖራቸው የሚገባውን ምግባር መጥቀስ ብቻ ሳይሆን እንደ ቅደም ተከተላቸው አስቀምጦአቸዋል፡፡ አንዱ ምግባር እንዴት ሌላኛውን እንደሚከተልና ከሁሉም የላቀ እጅግ አስፈላጊ ወሳኝ ደረጃ እስኪደርስ ያለውን ሂደት አስቀምጧል፡፡

ጴጥሮስ በክርስቶስ ስለ መሆንና ከቀድሞ ኃጢአት ስለ “መንጻት” (2ጴጥ. 1፡9) ተጨባጭ እውነታ ከመጻፉ በተጨማሪ ስለ ተረጋገጠው ደኅንነታችንና በጌታ ስለ ተሰጠን “ዘላለማዊ መንግሥት” (2ጴጥ. 1፡11) ተስፋ ጽንሰ ሃሳብ ያወሳል፡፡

በመጨረሻ--አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ ስለሆነው የሙታን ሁናቴ ጴጥሮስ በጥቂቱ የሰነዘረውን ሃሳብ እናገኛለን፡፡ እነዚህን የበለጸጉና ጥልቀት ያላቸውን እውነቶች በአስራ አራት ቁጥሮች ውስጥ ማግኘት በእርግጥ ድንቅ ነው!

ግንቦት 13
21-May

ክቡር እምነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1:1–4፡፡ ጴጥሮስ በየሱስ ክርስቶስ ስለ ተሰጠን ነገር ምን ይላል? ስለ ጸጋ ተጨባጭ እውነታ የቀረበበት መንገድ ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ “በየሱስ ክርስቶስ በኩል እንደ ተቀበልነው ዓይነት ክቡር ሕይወት ለተቀበሉ” (2ጴጥ. 1:1) በሚሉ የመግቢያ ቃላት ይህን መልእክቱን ይጀምራል፡፡ በጥቅሱ “ክቡር” በሚል የቀረበው ቃል “እኩል ዋጋ ያለው” ወይም “እኩል መብትና ጥቅም ያለው” የሚል ፍቺ ይዞአል፡፡ ይህ የከበረ እምነት የድካማቸው ፍሬ ወይም የተገባቸው ሳይሆን ከእግዚአብሔር የተቀበሉት ነጻ ስጦታ ነው፡፡ “በእምነት፣ በጸጋ ድናችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም” (ኤፌ. 2፡8)፡፡ ይህ ክቡር የሆነበት ምክንያት “ያለ እምነት እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት” ስለማይቻል ነው (ዕብ. 11፡6)፡፡ ክቡር የሆነበት ምክንያት ይህ እምነት የአያሌ አስደናቂ ተስፋዎች ባለቤት ስለሚያደርገን ነው፡፡

ለሕይወትና ለእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚያስፈልገንን ሁሉ “የመለኮቱ ኃይል” ሰጥቶናል ሲል ጴጥሮስ በአጽንኦት ይናገራል (2ጴጥ. 1፡3)፡፡ ሕልውናችን የተመሰረተው በእግዚአብሔር ኃይል ብቻ እንደመሆኑ የቅድስና ባለቤት መሆን የምንችለውም እንዲሁ በእርሱ ኃይል ነው፡፡ ይህ መለኮታዊ ኃይል የተሰጠን “በገዛ ክብሩና በበጎነቱ የጠራንን እርሱን በማወቅ ነው” (2ጴጥ. 1:3፣ ዮሐ. 17:3)፡፡

እግዚአብሔር አምላክን እንድንወደው መጠራታችን እሙን ቢሆንም ለመሆኑ እንዴት ነው የማናውቀውን አምላክ መውደድ የምንችለው? እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ መምጣት የምንችለው በየሱስ፣ በሕያው ቃሉ፣ በፍጥረት ሥራው እንዲሁም የእምነትና የመታዘዝ ሕይወት በመኖር ነው፡፡ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚሠራው ሥራ እርሱን በተጨባጭ እንድናውቅ ከማስቻሉ ባሻገር በእርሱ ላይ ያለን ዕውቀት ህይወታችን የተለወጠ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ እርሱን ወደ ማወቅ የምንመጣው በነጻ በሚቸረው በጸጋው አማካይነት ነው፡፡

ጴጥሮስ “የመለኮታዊው ባህሪ ተካፋዮች” የሚያደርገን “እጅግ ታላቅና ክቡር የሆነው ተስፋ” (2ጴጥ. 1፡4)ተሰጥቶናል ሲል ወደር ስለማይገኝለት ስለ ሌላው የላቀ ነገር ያወሳናል፡፡ መጀመሪያ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፡፡ ሆኖም ያ አምላካዊ መልክ በከፍተኛ ደረጃ እየተበላሸና ዝቅ እያለ መጣ፡፡ ነገር ግን የሁለተኛ ልደት አካል ስንሆን የራሱን መለኮታዊ መልክ ዳግም የመመለስ ሥራ የሚሠራው የየሱስ የአዲስ ህይወት ባለቤትነታችን የተረጋገጠ ይሆናል፡፡ ይህ ለውጥ በህይወታችን ገቢራዊ መሆን ይችል ዘንድ ራሳችንን ከዓለማዊው ብልሹ አሠራርና ፍትዎት ማራቅ ከእኛ ይጠበቃል፡፡

እምነት ባይኖርዎት ህይወትዎ ምን ሊመስል ይችል ነበር? ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠው መልስ የእምነት ስጦታ በእርግጥም ክቡር መሆኑን እንድናስተውል እንዴት ይረዳናል?

ግንቦት 14
22-May

ፍቅር--የክርስቲያናዊ ምግባር ግብ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1:5–7፣ ሮሜ 5:3–5፣ ያዕ. 1:3- 4፣ ገላ. 5:22- 23፡፡ በጥቅሶቹ የምንመለከተው ኅብር ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መልካም ምግባሮችን በዝርዝር ማስቀመጥ በጥንቱ ዓለም ይኖሩ በነበሩ ፈላስፎች ዘንድ የተለመደ ነበር፡፡ ዝርዝሮቹ “የመልካም ምግባር መዝገብ” በሚል መጠሪያ ይታወቁ የነበረ ሲሆን ለዚህም አያሌ ምሳሌዎችን በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት እናገኛለን (ሮሜ 5:3–5፣ ያዕ. 1:3-4፣ ገላ. 5:22-23)፡፡ ምንም እንኳ ፈላስፎች ያስቀምጧቸው የነበሩ የምግባር ዝርዝሮች ከጴጥሮስ ዝርዝሮች ጋር ሲተያዩ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ ቢመስሉም--የጴጥሮስ አንባቢዎች ከእነዚህ ዝርዝሮች ጋር ትውውቅ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ እያንዳንዱ መልካም ምግባር የመጨረሻ ፍጻሜ የሆነው ፍቅር ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ ሌላውን እየተከተለ የሚገነባ መሆኑን በማሳየት ጴጥሮስ ዝርዝሮቹን እንደ ቅደም ተከተላቸው በጥንቃቄ ማስቀመጡን ልብ ይሏል፡፡

ጴጥሮስ ጥቅም ላይ ያዋለው እያንዳንዱ ምግባር ታላቅ ትርጉም አለው፡- እምነት፡-- ይህ ቃል ከመልእክቱ ዐውድ አኳያ በሚያድነው የሱስ ላይ ከሚኖር እምነት ያነሰ አይደለም (ገላ. 3:11፣ ዕብ. 10:38)፡፡

በጎነት፡-- በማንኛውም ረገድ ነጥሮ የወጣ ወደር የለሹ በጎነት በጣኦት አምላኪ ማኅበረሰብ ፈላስፋዎች ሳይቀር በጉልህ የሚሰበክ ነበር፡፡ በእርግጥ እምነት ወሳኝ ምግባር ቢሆንም ወደ ተለወጠ ሕይወት መምራት መቻል ግን አለበት፡፡

ዕውቀት፡-- ጴጥሮስ እየተናገረ ያለው ስለ አጠቃላዩ የዕውቀት ጽንሰ ሀሳብ ሳይሆን ከሚያድነው ከየሱስ ክርስቶስ ጋር በሚፈጠር ትስስር ስለ ሚቀዳው ዕውቀት ነው፡፡

ራስን መግዛት /ራስን መቆጣጠር/፡ በሳል ክርስቲያኖች ወደ ስህተት ሊመሯቸው የሚችሉ በተለይ አፈንጋጭ ባህሪዎችን የማረቅና ስሜታቸውን የመቆጣጠር ችሎታ አላቸው፡፡

መጽናትን/ ጽኑና የማያወላውል መሆን፡-- ጽኑና የማያወላውል መሆን በተለይ ፈተናና ስደት ሲመጣ በጽናት ማለፍ መቻል ነው፡፡

እውነተኛ መንፈሳዊነት፡-- ጣኦታትን ባማከለው በጥንቱ አረማዊ ዓለም እምነት መሰረት እውነተኛ መንፈሳዊነት አማልክቱን ማመንን ተከትሎ እንደሚመጣ የሚታመን ሲሆን--ሃቀኛ ሥነ ምግባር የሚል ፍቺ አለው፡፡ በተመሳሳይ የሃቀኛ ሥነ ምግባርን ጽንሰ ሃሳብ በአዲስ ኪዳን የምናገኝ ሲሆን ይኸውም በአንዱና እውነተኛ በሆነው አምላክ ማመንን ተከትሎ የሚመጣ ውጤት በመሆን ነው (1ጢሞቴ. 2፡2)፡፡

ወንድማዊ መተሳሰብ፡-- ክርስቲያኖች እንደ አንድ የቤተሰብ አባላት እንደ መሆናቸው እግዚአብሔርን መምሰል አንዱ ለሌላው ቸር የሆነበትን የአማኞች ማኅበረሰብ ወደ ማፍራት ያሸጋግራል፡፡

ፍቅር፡-- ጴጥሮስ ፍቅርን በመጥቀስ የመልካም ሥነ ምግባር ቅደም ተከተሉ ከፍ ያለ ደረጃ እንዲቆናጠጥ ያደርገዋል፡ “እንግዲህ እምነት፣ ተስፋ፣ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው” (1ቆሮ. 13:13)፡፡

ጴጥሮስ የመልካም ሥነ ምግባር ቅደም ተከተሎቹን ማስቀመጥ ከመጀመሩ በፊት የሥነ ምግባሮቹ ባለቤት ለመሆን “በሙሉ ትጋት” (2ጴጥ. 1፡5) መጣር እንዳለብን ይነግረናል፡፡ ሐዋርያው ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? እውነተኛ መንፈሳውያንና ታማኝ ሆነን እንኖር ዘንድ ሰብዓዊው ትጋት ድርሻው ምንድን ነው?

ግንቦት 15
23-May

በተጠራነው መሰረት መመላለስ


ጴጥሮስ እንደ ክርስቲያንነታችን ልንተጋባቸው ስለሚገቡ ምግባሮች በቅደም ተከተል ካስቀመጠ በኋላ ተከትለው የሚመጡት ውጤቶች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ይፋ ያደርግልናል፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 2ጴጥ. 1፡8-11፡፡ አንድ ክርስቲያን በተደረገለትና ሊኖር በሚገባው ህይወት መሃል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጴጥሮስ አንባቢዎቹ በየሱስ ባገኙት አዲስ እውነት መሰረት እንዲመላለሱ በማበረታታት የእምነት መለያ ጸባይ የሆኑት--በጎነት፣ ዕውቀት፣ ራስን መግዛት፣ መጽናናት፣ እውነተኛ መንፈሳዊነት፣ ወንድማዊ መተሳሰብና ፍቅር “ተትረፍርፈው ቢኖሯችሁ” (2ጴጥ. 1:8) ይለናል፡፡

ችግሩ ያለው ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ አዲስ እውነት መሰረት መመላለስ አለመቻላቸው ላይ ነው፡፡ አንዳንዶች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያላቸው ዕውቀት ውጤታማ ወይም ፍሬ የሚያፈራ ዓይነት አይደለም (2ጴጥ. 1፡8)፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ሰዎች ከቀድሞ ኃጢአታቸው መንጻታቸውን ከነ’አካቴው ረስተውታል (2ጴጥ. 1፡9)፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች በየሱስ ባገኙት አዲስ እውነት መሰረት ሊኖሩ የተገባ እንደሆነ ጴጥሮስ ይናገራል፡፡ አማኞች ይቅርታን፣ ከኃጢአት መንጻትና የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋይ የመሆንን መብት ከክርስቶስ ተቀብለዋል፡፡ ስለዚህ መጠራታቸውንንና መመረጣቸውን ለማጽናት ከፊት ይልቅ ሊተጉ የተገባ ነው (2ጴጥ. 1፡10)፡፡ እንደ ቀድሞው ለመኖር መሸፋፈኛ ምክንያት ማቅረብም ሆነ ለዳተኛው ወይም ፍሬ ቢሱ (2ጴጥ. 1፡10) ክርስትና ሰበብ መደርደር አይችሉም፡፡

“ስለ እምነት አብልጠን የምንሰማ ቢሆንም ነገር ግን ከዚያ በላቀ በሥራ ስለሚገለጠው እምነት ልንሰማ የተገባ ነው፡፡ ብዙዎች ፈተና ውስጥ ሊጥላቸው በሚችል፣ ወደ ምቾት ባዘመመና መስቀሉ በማይታይበት አካሄድ የገዛ ነፍሳቸውን ሲያታልሉ ይስተዋላሉ”—Ellen G. White, Faith and Works, p. 50.

ጥቅሱን ያንብቡ፡-- ሮሜ 6፡11፡፡ የጳውሎስ መልእክት ሐዋርያው ጴጥሮስ ለዛሬ ጥናታችን የጻፈውን የሚያንጸባርቅበት መንገድ ምን ይመስላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጳውሎስም ሆነ የጴጥሮስ መልእክት በተጠራነው መሰረት እንመላለስ የሚል ዐውድ ይዞአል፡፡ በክርስቶስ አዲስ የሆን እኛ ከኃጢአት ነጽተናል የመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮችም ሆነናል፡፡ እንድንኖር የተጠራንበትን ህይወት መኖር የምንችልበት ምክንያቱ ይኸው ነው፡፡ ህይወታችን “ክርስቲያን” ተብለን የተጠራንበትን እምነት ፍቺ የያዘውን ክርስቶስ መምሰል ይኖርበታል፡፡

እርስዎ ምን ያህል ክርስቶስን ይመስላሉ? ለውጥ የሚያሻቸው የህይወትዎ ክፍል የትኞቹ ናቸው?

ግንቦት 16
24-May

ምድራዊውን ድንኳን ጥሎ መሄድ


“በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ እናንተን መጎትጎት ትክክል ሆኖ ይታየኛል፤ ምክንያቱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ገለጠልኝ ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ” (2ጴጥ. 1:13-14)፡፡

ኦስካር ኩልማን ነፍስ አትሞትም ወይስ የሙታን ትንሣኤ የለም? ፡--የአዲስ ኪዳን ምስክርነት፤ የሚል ርዕስ የሰጡትን አጭር የጥናት ጽሑፋቸውን በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1956 ለንባብ አብቅተው ነበር፡፡ የትንሣኤ ጽንሰ ሃሳብ ከነፍስ አለመሞት አስተምህሮ ጋር ፍጹም ተዛምዶ የለውም ሲሉ በጥናት ጽሑፋቸው የሞገቱት ሚስተር ኩልማን፤ በተጨማሪ አዲስ ኪዳን በትክክል ከሙታን ትንሣኤን ጽንሰ ሃሳብ በኩል ይቆማል ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡-- 1ቆሮ. 15፡12-57፡፡ በሞት ወቅት ስለሚከሰተው ነገር ጳውሎስ ምን ይላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አዲስ ኪዳን ስለ ሞት እና ትንሣኤ የሚናገረውን በጥንቃቄ ያጥኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ኩልማን ትክክል እንደ ነበሩ መስክረዋል፡፡ በእርግጥ አዲስ ኪዳን በአካላዊው ሞት ወቅት ነፍስ አትሞትም ከሚለው አስተምህሮ ጋር ሳይሆን ከሙታን ትንሣኤ ጽንሰ ሃሳብ ጋር ስምሙ ነው፡፡ የሚወዷቸውን በሞት የተነጠቁ ወገኖች የሱስ ዳግም ሲገለጥ ከሞት እንደሚያስነሳቸው ማወቃቸው ሊያጽናናቸው እንደሚገባ ጳውሎስ በ1ተሰ. 4፡16-18 ይናገራል፡፡ ጳውሎስ በ1ቆሮ. 15፡12-57 ስለ ትንሳኤ ዘርዘር ያለ መግለጫ ይሰጣል፡፡ የክርስትና እምነት መሰረቱ የየሱስ ትንሳኤ መሆኑን በማመላከት መልእክቱን የሚጀምረው ሐዋርያው፤ የሱስ ከሙታን ባይነሳ ኖሮ በእርሱ ማመን ከንቱ እንደ ነበር ይገልጥና--ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኩራት ሆኖ በርግጥ ከሙታን ተነሥቷል ይለናል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ትንሣኤ እርሱን አምነው የሞቱ ሁሉ ዳግም መነሳታቸውን እውን አድርጓል፡፡

ጳውሎስ ስለ አካላዊው ትንሣኤ በ1ቆሮ. 15፡35-50 ይናገራል፡፡ ሐዋርያው በዚህ መልእክቱ በትንሣኤ ወቅት የምንወስደውን አዲስ አካል ከአሁኑ ጋር አነጻጽሮ ጽፎአል፡፡ ምድራዊው ሥጋችን ጠፊ--በትንሣኤ የምንለብሰው አካል ግን ዘላለማዊ እንደሆነ ይነግረናል፡፡

ማጠቃለያ፡- አዲስ ኪዳን ስለ ሞት የሚናገረው ከትንሣኤ አኳያ እንጂ ከነፍስ ዘላለማዊነት ጋር በተያያዘ አይደለም፡፡ ሃሳቡ የ2ጴጥ. 1፡12-14 ታሪካዊ ዳራ በቅጡ ለማስተዋል እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ግንቦት 17
25-May

በእምነት መጽናት--እስከ ሞት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1:12–15፡፡ ጴጥሮስ በቅርቡ ምድራዊውን ድንኳን ጥዬ እሄዳለሁ ሲል ምን ማለቱ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ሐዋርያው በ2ጴጥ. 1፡12-14 በጻፈው መልእክቱ ደብዳቤውን ሲጽፍ እየተከሰተ የነበረውን ሁናቴ ይገልጻል፡፡ የመሞቻው ጊዜ መቃረቡን የተረዳው ጴጥሮስ ደብዳቤው የመጨረሻውን መልእክቱን ወይም ምስክርነቱን እንደ ያዘ ተሰምቶታል፡፡

በቅርብ እንደሚሞት የተረዳው ጴጥሮስ ይህን አይቀሬ ክስተት በተለየ የቃላት አጠቃቀም ስልት ሲገልጽ ይስተዋላል “በዚህ ምድራዊ ድንኳን ውስጥ እስካለሁ ድረስ… ይህን ምድራዊ ድንኳን ቶሎ ጥዬ እንደምሄድ ዐውቃለሁ” (2ጴጥ. 1:13- 14) ፡፡ አካሉን በድንኳን (በመቅደስ) በመመሰል የሚያቀርበው ሐዋርያ ሲሞት ጥሎት እንደሚሄድ ይናገራል፡፡ ጴጥሮስ ጥሎ ስለ መሄድ ጥቅም ላይ ያዋለው ሃረግ አካሉን መመልከቱ ግልጽ ቢሆንም፤ ይህን አባባል ዘመናዊ ትርጉሞች እንደሚከተለው ያቀርቡታል “በዚህ አካል ውስጥ እስካለሁ ድረስ…ቶሎ እንደምሞት ዐውቃለሁ” (2ጴጥ. 1:13-14 NRSV)፡፡ ጴጥሮስ ምድራዊ ድንኳኑን ወይም አካሉን ጥሎ ስለ መሄድ በሰጠው መልእክት ነፍሱ ተነጥላ እንደምትኖር የገለጸበት አንዳችም መንገድ የለም፡፡

ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡-- (2ጴጥ 1:12–15)፡፡ ጴጥሮስ ከአይቀሬው ሞት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የተጋፈጠበት አካሄድ ምን ይመስላል? እንዲህ ያለው አኳኋን ስለ ሞት ምን ያስተምራናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በ2ጴጥ. 1፡12-15 የምናነባቸው ጥቅሶች የሐዋርያውን ቃላት ተጨማሪ ሞገስ አጎናጽፈዋቸዋል፡፡ ጴጥሮስ ይህን መልእክት የሚጽፈው በቅርቡ ምድራዊ ህይወቱ በሞት እንደሚደመደም እያወቀ ነበር፡፡ እንደሚሞት ማወቅ የቻለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በገለጠለት መሰረት መሆኑን ጴጥሮስ ቢናገርም--አንዳችም ፍርሐት፣ ሽብር ወይም ክፉ ነገር ይደርስብኛል የሚል ስሜት አይስተዋልበትም፡፡ ይልቁንም ሐዋርያው አጽንኦት የሚሰጠው ትቷቸው በሚሄደው ወገኖች ደህንነት ዙሪያ እንደሆን ልብ ይሏል፡፡ ወገኖች በያዙት ወቅታዊ እውነት እንዲጸኑ ምኞቱ የሆነው ጴጥሮስ በህይወት እስካለ ድረስ በታማኝነታቸው እንዲመላለሱ መገሰጹን አያቆምም፡፡

ከላይ የቀረቡት ሃሳቦች ጴጥሮስ ከጌታ ጋር የነበረውን ተሞክሮ በተጨባጭና በጥልቀት እንድንመለከት ያስችሉናል፡፡ በቅርብ የሚሞተው ጴጥሮስ ሞቱ አስደሳች ባይሆንም ( ዮሐ. 21:18; Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 537, ጴጥሮስ ባስተማረው እምነት መመላለስ የቻለ ሰው ነበር፡፡

እምነታችን ከአስፈሪው ሞት ጋር መጋፈጥ እንድንችል እንዴት ሊረዳን ይችላል? የሱስ ለእኛ ካደረገው አኳያ--ሞት ቢመጣ አኳያ አስደናቂውን ተስፋ አጥብቆ መያዝን እንዴት መማር እንችላለን?

ግንቦት 18
26-May

ተጨማሪ ሃሳብ፡-


ጴጥሮስ የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን እንደተገነዘበ ተመልክተናል፡፡ ሐዋርያው አሟሟቱ ምን ሊመስል እንደሚችል አስቀድሞ ያውቅ ነበር፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የሱስ ራሱ ነግሮት ስለነበር ነው፡፡ “ ‘እውነት እልሃለሁ፤ ወጣት ሳለህ ልብስህን ራስህ ለብሰህ ወደ ፈለግህበት ትሄድ ነበር፤ ስትሸመግል ግን እጅህን ትዘረጋለህ፤ ሌላም ሰው ልብስህን አስታጥቆህ ልትሄድ ወደ ማትፈልግበት ይወስድሃል’ ” (ዮሐ. 21:18)፡፡

የሐዋርያው መጨረሻ ምን ሆነ?

“ጴጥሮስ እንደ አይሁዳዊነቱና እንደ ባዕድ አገር ተወላጅነቱ እስከ ግርፋት ብሎም ሥቅላት የደረሰ ውግዘት ደረሰበት፡፡ ይህን አስፈሪ ሞት በምናቡ የሳለው ጴጥሮስ የሱስ ሸንጎ በቀረበበት በዚያ ሰዓት እርሱን በመካድ የፈጸመውን ታላቅ ኃጢአት አስታውሶ ነበር፡፡ በአንድ ወቅት መስቀሉን ለመቀበል ዝግጁነት ይጎድለው የነበረው ይህ ሐዋርያ አሁን ግን ስለ ወንጌል ተልዕኮ ህይወቱን አሳልፎ መስጠቱን እንደ ደስታ ቆጠረው፡፡ ጌታውን ክዶ የነበረ እንደ እርሱ ዓይነት ሰው መምህሩ በሞተበት አኳኋን መሞቱ እጅግ ታላቅ ክብር ሊያጎናጽው እንደሚችል ተሰማው፡፡ የመንጋውን በጎችና ጠቦቶች እንዲመግብ በተሰጠው ታላቁ ተልዕኮ እንደተመለከተው ጴጥሮስ ለሠራው ለዚያ ኃጢአት ከልቡ ንስሐ መግባቱን ተከትሎ ከክርስቶስ ይቅርታ ተቀብሎ ነበር፡፡ እነዚያ የመጨረሻዎቹ አስከፊ የመከራዎቹ ትዕይንቶች እንኳ የጸጸቱንና የንስሐውን መራራነት የማሳነስ ኃይል አልነበራቸውም፡፡ ጴጥሮስ አስከፊውን የሥቅላት መከራ በሚቀበልበት በዚያ አሠቃቂ ሰዓት በመስቀል ላይ እየቸነከሩት የነበሩት ጨካኞች አናቱን ቁልቁል አድርገው (ከክርስቶስ በተቃራኒ) በመስቀል ውለታ እንዲውሉለት ለመናቸው፡፡ ልመናው ተቀባይነት በማግኘቱ ታላቁ ሐዋርያ ጴጥሮስ በዚህ አኳኋን ሞተ”— Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 537, 538. ይህ ሁሉ መከራ በጴጥሮስ ላይ ቢደርስም ነገር ግን ሐዋርያውን ያሳስበው የነበረው የመንጋው ደኅንነት ነበር፡፡


የመወያያ ጥያቄዎች:



ክርስቲያኖች የተቀደሰ ህይወት ሊመሩ እንደሚገባ ጴጥሮስ (ቀሪዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጨምሮ) ቢጽፍም፤ ብዙዎቻችን በክርስቶስ በተጠራነው መሰረት ለመመላለስ ስናነክስ የምንስተዋለው ለምንድን ነው? 2ጴጥ. 1፡5-7 ካነበባችሁ በኋላ እያንዳንዱን ነጥብ እያነሳችሁ ተነጋገሩ፡፡ እነዚህን መልካም ምግባሮች በተሻለ ማሳየት የምንችለውና ሌሎችም እንዲሹ ልንረዳ የምንችለው እንዴት ነው?

 በወንጌል ስለ ጴጥሮስ የተዘገቡትን ከግምት በማስገባት የሐዋርያውን ውድቀቶች የምናውቅ ቢሆንም--ጽሑፉ ክርስቶስ ለእርሱ የሠራውን ታላቅ ሥራ በብርቱ ያሳያል፡፡ ከዚህ ምሳሌ ምን ዓይነት ተስፋና መጽናናት እናገኛለን?

 ሐዋርያው በ2ጴጥ. 1፡12 ስለ ወቅታዊው እውነት ጽፎአል፡፡ በጴጥሮስ ዘመን የነበረው ወቅታዊ እውነት ምን ነበር? በእኛ ዘመን ያለው ወቅታዊ እውነትስ ምን ይመስላል?

 “ከሞት ባሻገር ያሉ ሟቾች ሁኔታ ምን ያህል የተረጋገጠ ነው?” በሚል ሃሳቡን ያሰፈረ አንድ ጸሐፊ ጽሑፉን ሲቀጥል “ሞት ማለት በህይወት ያሉ ፍጡራን ተሸክመው የሚኖሩት ነገር ነው” ይላል፡፡ እኛ እንደ ክርስቲያን ሞትን “ተሸክመን” የምንኖረው እንዴት ነው?