ወንጌል በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከሐምሌ 8-14

አረተኛ ትምህርት

Jul 15-21
 

ጽድቅ በእምነት ብቻ

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ገላ. 2፡ 15-21፤ ኤፌ. 2፡ 12፤ ፊል.3፡ 9፤ ሮሜ 3፡ 10-20፤ ዘፍ. 15፡ 5፣ 6፤ ሮሜ 3፡ 8፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ከክርስቶስ ጋር ተሰቅዬአለሁ፤ እኔም አሁን ሕያው ሆኜ አልኖርም ክርስቶስ ግን በእኔ ይኖራል፡፡ አሁንም በሥጋ የምኖርበት ኑሮ በወደደኝና ስለ እኔ ራሱን በሰጠው በእግዚአብሔር ልጅ ላይ ባለ እምነት የምኖረው ነው›› (ገላ. 2፡ 20)፡፡

ባለፈው ሳምንት እንደተመለከትነው ጴጥሮስ እቀበላለሁ በሚለው እምነትና በሚያሳየው ባህርይ መካከል ወጥነት ስላልነበረው ጳውሎስ በአንጾኪያ በሕዝብ ፊት እንደተጋፈጠው ተመልክተን ነበር፡፡ ጴጥሮስ ቀድሞ አህዛብ ከነበሩ ጋር አብሮ ላለመብላት መወሰኑ እነርሱ ቢበዛ ሁለተኛ ደረጃ ክርስቲያኖች መሆናቸውን የሚጠቁም ነበር፡፡ የጴጥሮስ ድርጊት የሚያመለክተው በርግጥ የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት ለመሆንና አብሮ የመብላትን ሙሉ በረከቶች ማግኘት ከፈለጉ መጀመሪያ ለግዝረት ስርዓት ራሳቸውን ማስገዛት እንዳለባቸው ነበር፡፡ በዚያ ውጥረት በነገሰበት አጋጣሚ ጳውሎስ ለጴጥሮስ ያለው ምን ነበር? በዚህ ሳምንት ትምህርት ውስጥ ለሆነው ነገር ማጠቃለያ ሊሆን የሚችለውን ሀሳብ እናጠናለን፡፡ ይህ ንባብ በአዲስ ኪዳን ውስጥ እጅግ የታመቀ የቃላት አጠቃቀምን ከያዙት ጥቅት ክፍሎች አንዱ ሲሆን ወንጌልን ለማስተዋልና ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ሌላውን ክፍል ለመረዳት መሰረታዊ ከሆኑ ቃላትና ሐረጎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሚያስተዋውቀን እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ ቁልፍ የሆኑ ቃላት ጽድቅ፣ ቅድስና፣ የህግ ሥራ፣ እምነት እና እምነት ብቻ ሳይሆን በኢየሱስ ማመን የሚሉት ናቸው፡፡ ጳውሎስ እነዚህን ቃላት ሲጠቀም ምን ማለቱ ነው? ስለ ድነት እቅድስ ምን ያስተምሩናል?
 

ሐምሌ 9
Jul-16
 

የ‹‹ጽድቅ›› ጥያቄ (ገላ.2፡ 15፣ 16)

 

በገላትያ 2፡ 15 ላይ ጳውሎስ ‹‹እኛ በትውልድ አይሁድ ነን ኃጢአተኞችም የሆኑ አህዛብ አይደለንም›› በማለት ይጽፋል፡፡ እርሱ እየነገረን ያለው ነጥብ ምንድን ነው ብለው ያስባሉ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጳውሎስን ቃላት መረዳት የሚያስፈልገው ከአገባባቸው ነው፡፡ እንደ እርሱ ያሉ አይሁድ ክርስቲያኖች ከእርሱ ሀሳብ ጋር እንዲስማሙ ለማድረግ እነርሱ በሚስማሙበት ነገር-በአይሁድና በአህዛብ መካከል በነበረው ባሕላዊ ልዩነትይጀምራል፡፡ አይሁዶች የእግዚአብሔር ምርጦች፣ ሕጉ የተሰጣቸው፣ እና ከእርሱ ጋር ከነበራቸው የቃል ኪዳን ግንኙነት ተጠቃሚዎች ነበሩ፡፡ ነገር ግን አህዛብ ኃጢአተኞች ነበሩ፤ የእግዚአብሔር ሕግ ባሕርያቸውን ስለማይቆጣጠር ከቃል ኪዳን ተስፋ ውጭ ነበሩ (ኤፌ. 2፡ 12፤ ሮሜ 2፡ 14)፡፡ አህዛብ ኃጢአተኞች ሆነው ሳሉ ጳውሎስ በቁጥር 16 ላይ ማንም ሰው ‹‹በሕግ ሥራ›› በእግዚአብሔር ፊት መጽደቅ ስለማይችል የተሰጡአቸው መንፈሳዊ መልካም ዕድሎች በእግዚአብሔር ዘንድ ከአህዛብ በተሻለ ሁኔታ ተቀባይነት ሊያስገኙላቸው እንደማይችሉ የአይሁድ ክርስቲያኖችን ያስጠነቅቃል፡ ጳውሎስ በገላትያ 2፡ 16 እና 17 ላይ መጽደቅ የሚለውን ቃል አራት ጊዜ ይጠቀማል፡፡ ‹‹መጽደቅ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? ዘጸ. 23፡ 7፤ እና ዘዳ. 25፡ 1ን ያንብቡ፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጽደቅ የሚለው ቃል ለጳውሎስ ቁልፍ ቃል ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰላሳ ዘጠኝ ጊዜ ከተጠቀሰው መካከል ሃያ ሰባቱ ያለው በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ ነው፡፡ በገላትያ 2፡ 16 እና 17 ውስጥ የተጠቀሱትን ጨምሮ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ስምንት ጊዜ ተጠቅሞታል፡፡ መጽደቅ በፍርድ ቤቶች ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውል የሕግ ቃል ነው፡፡ አንድ ግለሰብ ተከሶ ወደ ፍርድ ቤት ከቀረበበት ወንጀል ነጻ ሆኖ ሲገኝ የሚሰጠውን ውሳኔ የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ የኩነኔ ተቃራኒ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጻድቅ እና ቅዱስ የሚሉ ቃላት ከአንድ የግሪክ ቃል የመጡ ስለሆነ አንድ ሰው ‹‹ጸደቀ›› ማለት ‹‹ቅዱስ›› ሆኖ ተቆጠረ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መጽደቅ ምህረትን ወይም ይቅርታን ከማግኘት የበለጠ ነገርን ያካትታል፤ ግለሰቡ ጻድቅ መሆኑን በአዎንታዊ መልኩ ማወጅ ነው፡፡ ነገር ግን ለአንዳንድ የአይሁድ አማኞች መጽደቅ በግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ከእግዚአብሔርና ከቃል ኪዳኑ ጋር በነበራቸው ግንኙነት ዙሪያ ይሽከረከር ነበር፡፡ አንድ ግለሰብ ‹‹ጸደቀ›› ሲባል ግለሰቡ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ማህበረሰብ፣ የአብርሃም ቤተሰብ ታማኝ አባል ሆኖ ተቆጠረ ማለት ነበር፡፡ ገላትያ 2፡ 15-17ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ቦታ ጳውሎስ ለእርስዎ ምን እያለ ነው? እነዚህን ቃላት ለራስዎ የክርስትና ልምምድ እንዴት ይጠቀማሉ?
 

ሐምሌ 10
Jul-17
 

የሕግ ሥራ

 

ጳውሎስ በገላትያ 2፡16 ላይ ሶሰት ጊዜ ሰው ‹‹በሕግ ሥራ›› አይጸድቅም ይላል፡፡ ‹‹የህግ ሥራ›› ሲል ምን ማለቱ ነው? እነዚህ ጥቅሶች (ገላ. 2፡16፣ 17፤ 3፡2፣ 5፣ 10፤ ሮሜ 3፡ 20፣ 28) የእርሱን ትርጉም እንድንረዳ እንዴት ይረዱናል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

‹‹የሕግ ሥራ›› የሚለውን ሀረግ ከማስተዋላችን በፊት ጳውሎስ ሕግ ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ሕግ የሚለው ቃል (በግሪክ ኖሞስ የሚባለው) በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ 121 ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያለውን ፈቃድ፣ የመጀመሪያዎቹን አምስቱን የሙሴ መጻሕፍት፣ መላውን ብሉይ ኪዳን ወይም አጠቃላይ መርህን ጨምሮ የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠቀምበት መንገድ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት ለሕዝቡ የሰጣቸውን ጠቅላላ የህግጋት ስብስብን ለማመልከት ነው፡፡ ስለዚህ ‹‹የህግ ሥራ›› የሚለው ሀረግ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጣቸውን በሕግጋት ውስጥ ያሉ መስፈርቶችን በሙሉ፣ የግብረ ገብ ሕግንም ሆነ ሜዳዊ ሥርዓቶችን ያካትታል፡፡ ጳውሎስ ግልጽ ለማድረግ የሚፈልገው ነጥብ ቢኖር ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ለመከተልና ለመታዘዝ የፈለገውን ያህል ቢሞክርም፣ የእኛ መታዘዝ እግዚአብሔር እንዲያጸድቀን ወይም በፊቱ ጻድቃን ናቸው ብሎ እንዲናገርልን ለማድረግ ብቃት የለውም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የእርሱ ሕግ አንዳንድ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ፣ በከፊል ሳይሆን ሁሉንም፣ በሀሳብም ሆነ በተግባር ፍጹም በሆነ ታማኝነት እንድንታዘዝ ስለሚፈልግብን ነው፡፡ ምንም እንኳን ‹‹የህግ ሥራ›› የሚለው ሐረግ በብሉይ ኪዳን ውስጥ ባይኖርም፣ በአዲስ ኪዳን ውስጥም ከጳውሎስ መልእክቶች ውጭ ባይገኝም በ1947 ዓ.ም በሙት ባሕር ውስጥ በተገኙ ጥቅሎች ውስጥ የትርጉሙ አስደናቂ የሆነ ማረጋገጫ ተገኝቷል፡፡ እነዚህ ጥቅሎች በክርስቶስ ዘመን በኖረ ኤሴኔስ በተባለ የአይሁድ ቡድን ተገልብጦ የተቀመጠ ነው፡፡ ምንም እንኳን በእብራይስጥ ቢጻፍም ከጥቅሎቹ አንዱ ይህን ሀረግ በቀጥታ ይዟል፡፡ የጥቅሉ ርዕስ ሚቅሳት ማኣስ ሃ-ቶራህ (Miqsat Ma’as Ha-Torah)የሚል ሲሆን ትርጉሙ ‹‹ጠቃሚ የሆኑ የሕግ ሥራዎች›› የሚል ነው፡፡ ጥቅሉ አይሁዶችን ከአህዛብ የሚለዩ በርካታ ነገሮችን ጨምሮ ቅዱስ ነገሮች እንዳይረክሱ የሚከለክሉ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሕግ ላይ የተመሰረቱ በርካታ ጉዳዮችን ይገልጻል፡፡ በመጨረሻ ላይ ጸሐፊው እነዚህ ‹‹የሕግ ሥራዎች›› ቢተገበሩ በእግዚአብሔር ፊት ‹‹ጻድቅ እንደሆንክ ትቆጠራለህ›› ይላል፡፡ ከጳውሎስ በተቃራኒ ጸሐፊው ለአንባቢው ጽድቅን የሚያቀርበው በእምነት ላይ ተመስርቶ ሳይሆን በባሕርይ ላይ ተመስርቶ ነው፡፡

በእርስዎ ልምምድ ሕግን ምን ያህል አሳምረው ይጠብቃሉ? ሕግን በመጠበቅዎ በእግዚአብሔር ፊት መጽደቅ እስከሚችሉ ድረስ በደንብ እየጠበቁ መሆንዎ ይሰማዎታልን? (ሮሜ 3፡ 10-20ን ይመልከቱ)፡፡ ካልሆነ በደንብ እየጠበቁ መሆንዎ ያልተሰማዎት ለምንድን ነው? መልስዎ ጳውሎስ በዚህ ቦታ እያቀረበ ያለውን ነጥብ እንዲያስተውሉ እንዴት ረዳዎት?
 

ሐምሌ 11
Jul-18
 

የመጽደቃችን መሰረት

 

‹‹በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ በእርሱ እገኝ ዘንድ…›› (ፊል. 3፡ 9)፡፡ የአይሁድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ማመን አስፈላጊ አይደለም እያሉ እንደሆኑ መገመት የለብንም፤ ሁላቸውም በክርስቶስ የሚያምኑ ነበሩ፡፡ ሁላቸውም በክርስቶስ እምነት ነበራቸው፡፡ ነገር ግን ባሕርያቸው እምነት በራሱ በቂ አለመሆኑን ያሳይ ነበር፤ መታዘዛችን በመጽደቃችን ላይ የሆነ ነገር የሚጨምር ይመስል በመታዘዝ መታገዝ ነበረበት፡፡ መጽደቅ የሚቻለው በእምነትና በሥራ ነው ብለው ተከራከሩ፡፡ ጳውሎስ በተደጋጋሚ በክርስቶስ ማመንን ከሕግ ሥራ ጋር ያነጻጸረበት ሁኔታ ሁለቱም መንገዶች ለጽድቅ አስፈላጊ ናቸው ለሚለው አመለካከት የነበረውን ጠንካራ ተቃውሞ ያሳያል፡፡ የጽድቅ መሰረቱ እምነት እና እምነት ብቻ ነው፡፡

ለጳውሎስም ቢሆን እምነት ዝም ብሎ የማይጨበጥ ጽንሰ ሀሳብ አይደለም፤ ሊለያይ በማይችልበት ሁኔታ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም በገላትያ 2፡ 16 ላይ ሁለት ጊዜ ‹‹በክርስቶስ በማመን›› ተብሎ የተተረጎመው ሀረግ ማንኛውም ትርጉም ሊያጠቃልለው ከሚችለው በላይ የበለጸገ ነው፡፡ ሀረጉ በግሪክ የክርስቶስ ‹‹እምነት›› ወይም ‹‹ታማኝነት›› ተብሎ ቃል በቃል ተተርጉሟል፡፡ ይህ ቃል በቃል ትርጉም ጳውሎስ እኛ በምናደርገው በሕግ ሥራና በእኛ ፈንታ በተፈጸመልን በክርስቶስ ሥራ፣ እርሱ በታማኝነቱ (‹‹የኢየሱስ ታማኝነት››) ለእኛ ባደረገልን መካከል እያደረገ ያለውን ኃይለኛ የሆነ ንጽጽር ያሳያል፡፡ እምነት በራሱ ዋጋ ያለው ይመስል ለጽድቃችን የሚጨምር ነገር እንዳለው አድርጎ መቁጠር እንደማያስፈልግ ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡ እምነት ክርስቶስንና እርሱ በእኛ ፈንታ ያደረገልንን ነገር የምንጨብጥበት መንገድ ነው፡፡ የጸደቅነው በእምነታችን መሰረት ሳይሆን በእምነት የራሳችን እንደሆነ አድርገን በምንቆጥረው ክርስቶስ ለእኛ ባሳየው ታማኝነት ነው፡፡

ክርስቶስ እያንዳንዱ ግለሰብ ማድረግ ያቃተውን ነገር አደረገ፤ ባደረገው ነገር ሁሉ ለእግዚአብሔር ታማኝ የነበረው እርሱ ብቻ ነበር፡፡ ተስፋችን በእኛ ታማኝነት ላይ ሳይሆን በክርስቶስ ታማኝነት ላይ ነው፡፡ ይህ የፕሮቴስታንት ተሃድሶን ካቀጣጠሉ እውነቶች መካከል ትልቅና ጠቃሚ የሆነ እውነት ነው፡፡ ይህ እውነት ማርቲን ሉተር ከመቶ አመታት በፊት መስበክ በጀመረ ጊዜ አስፈላጊ የሆነውን ያህል ዛሬም አስፈላጊ ነው፡፡

በጥንት የሶሪያ ቋንቋ ወይም በአረማይክ የተጻፈው የገላትያ 2፡ 16 የጳውሎስን ትርጉም በደንብ ያስተላልፋል፡- ‹‹ስለዚህ ሰው በሕግ ስራ መሲህ በሆነው በኢየሱስ እምነት እንደሚጸድቅ እናውቃለን፣ መሲህ ከእርሱ እምነት የተነሳ እንጂ በሕግ ሥራ ስለማንጸድቅ በእርሱ መሲህ በኢየሱስ እናምናለን፡፡››

ትርጉም ሳይሆን ከሆነው በሆነው ሮሜ 3፡ 22፣26፤ ገላ. 3፡ 22፤ ኤፌ. 3፡ 12 እና ፊል. 3፡ 9ን ያንብቡ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች እና ከላይ ያነበብናቸው ጥቅሶች ክርስቶስ ለእኛ ያሳየው ታማኝነት፣ ለእግዚአብሔር ያሳየው ፍጹም መታዘዝ የድነታችን መሰረት የመሆኑን አስደናቂ እውነት እንድናስተውል የሚረዱን እንዴት ነው?
 

ሐምሌ 12
Jul-19
 

የእምነት መታዘዝ

 

እምነት ለክርስቲያን ሕይወት ፍጹም መሰረታዊ መሆኑን ጳውሎስ ግልጽ ያደርጋል፡፡ በክርስቶስ ያሉንን ተስፋዎች የምንጨብጥበት መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን እምነት ምንድን ነው? ምንንስ ያካትታል?

ስለ እምነት መነሾ (አመጣጥ) የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል? ዘፍ. 15፡ 5፣ 6፤ ዮሐ. 3፡ 14-16፤ 2ቆሮ. 5፡ 14፣ 15፤ ገላ. 5፡ 6፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ትክክለኛ የሆነ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት ሁል ጊዜ ለእግዚአብሔር የሚሰጥ ምላሽ ነው፡፡ እምነት እግዚአብሔር ስለሚፈልግባቸው ሰብአዊ ፍጥሮች አንድ ቀን የሚወስኑት የሆነ አይነት ስሜት ወይም አመለካከት አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የእውነተኛ እምነት መነሻው እግዚአብሔር ላደረገው መልካምነት አመስጋኝ በሆነና በፍቅር ስሜት በተነካ ልብ ውስጥ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እምነት ሲናገር እምነት ሁል ጊዜ እግዚአብሔር የወሰደውን ተነሳሽነት የሚከተለው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ የአብርሃምን ሁኔታ ስንመለከት እምነት እግዚአብሔር ለእርሱ ለገባለት አስደናቂ ቃል ኪዳኖች ምላሽ ሲሆን (ዘፍ. 15፡ 5፣ 6) በአዲስ ኪዳን ደግሞ እምነት ክርስቶስ ለእኛ በመስቀል ላይ ያደረገልንን ነገር በመገንዘብ ላይ የተመሰረተ ነው በማለት ጳውሎስ ይናገራል፡፡

እምነት ለእግዚአብሔር ምላሽ ከሆነ ያ ምላሽ ምንን ማካተት አለበት? ስለ እምነት ተፈጥሮ የሚከተሉት ጥቅሶች የሚሉትን ልብ ይበሉ፡፡ ዮሐ. 8፡ 32፣ 36፤ የሐዋ. 10፡ 43፤ ሮሜ 1፡ 5፣ 8፤ 6፡ 17፤ ዕብ. 11፡ 6፤ ያዕ. 2፡ 19፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ብዙ ሰዎች እምነትን ‹‹ኃይማኖት›› ብለው ይተረጉማሉ፡፡ በግሪክ ቋንቋ ‹‹እምነት›› የሚለው ቃል ‹‹ማመን›› ለሚለው ግስ ስሙ ስለሆነ እምነት ኃይማኖት ነው የሚለው ትርጉም ችግር ያለበት ነው፡፡ አንዱን ለመተርጎም ሌላውን መልክ መጠቀም ‹‹እምነት ማለት ማመን ነው›› እንደ ማለት ነው፡፡ ምንም የሚነግረን ነገር የለም፡፡

መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መመርመር እምነት ስለ እግዚአብሔር ማወቅን ብቻ የሚያካትት ሳይሆን የአእምሮ መስማማትን ወይም ያንን እውቀት መቀበልን ያካትታል፡፡ የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ምስል ማግኘት ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ የተዛቡ አመለካከቶች ማመንን የበለጠ ከባድ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ‹‹አጋንንትም ስለሚያምኑ›› ከወንጌል ጋር የአእምሮ መስማማት በቂ አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት ግለሰቡ የሚኖርበትን የአኗኗር መንገድ ይነካል፡፡ በሮሜ 1፡ 5 ላይ ጳውሎስ ስለ ‹‹እምነት መታዘዝ›› ይጽፋል፡፡ ጳውሎስ መታዘዝ ከእምነት ጋር አንድ አይነት ነው እያለ አይደለም፡፡ እውነተኛ እምነት አእምሮን ብቻ ሳይሆን የግለሰቡን መላ ሕይወት የሚነካ ነው ማለቱ ነው፡፡ ከደንቦች ዝርዝር በተቃራኒ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መሰጠትንም ያካትታል፡፡ እምነት ምን እንደምናምን የሚነግረውን ያህል ምን እንደምናደርግ፣ እንዴት እንደምንኖርና በማን እንደምንታመንም ይነግረናል፡፡
 

ሐምሌ 13
Jul-20
 

እምነት ኃጢአትን ያስፋፋልን?

 

በጳውሎስ ላይ ይሰነዘሩ ከነበሩ ውንጀላዎች አንዱ ጽድቅ በእምነት ብቻ የሚለው ወንጌሉ ሰዎች ኃጢአትን እንዲሰሩ አደፋፍሯል የሚል ነበር (ሮሜ 3፡ 8፣ 6፡ 1ን ይመልከቱ)፡፡ የከሳሾቹ መከራከሪያ ሰዎች በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ሕግን መጠበቅ ካላስፈለጋቸው ለምን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ግድ ይላቸዋል? የሚል ነው፡፡ ሉተርም ተመሳሳይ ክስን ተጋፍጧል፡፡

ጽድቅ በእምነት ብቻ የሚለው አስተምህሮ ኃጢአተኛ ባሕርይን ያደፋፍራል ለሚለው ክስ ጳውሎስ መልስ የሚመልሰው እንዴት ነው? ገላ. 2፡ 17፣ 18፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ለተቃዋሚዎቹ ክስ መልስ የሚመልሰው ሊጠቀማቸው የሚችላቸውን እጅግ ጠንካራ ቃላትን በመምረጥ ነው፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አያድርገውና!›› ሰው ወደ ክርስቶስ ከመጣ በኋላ ወደ ኃጢአት ሊወድቅ የሚችል ስለሆነ ኃላፊነቱ የክርስቶስ አይደለም፡፡ ሕግን ከጣስን እኛ ራሳችን ሕግ ተላላፊዎች ነን፡፡

ጳውሎስ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ሕብረት እንዴት ይገልጸዋል? ይህ መልስ በተቃዋሚዎቹ የሚነሱ ተቃርኖዎችን በምን መንገድ ያስተባብላል? ገላ. 2፡ 19-21፡፡

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹ የሚያቀርቡአቸው መከራከሪያዎች ዝም ብሎ የማይረቡ መሆናቸውን ያገኛል፡፡ ክርስቶስን በእምነት መቀበል ዝም ብሎ ዋጋ ቢስ ነገር አይደለም፤ ግለሰቡ በአኗኗሩ ትክክለኛ የሆነ ለውጥ ሳያሳይ እግዚአብሔር እንደ ጻድቅ አድርጎ የሚቆጥርበትና ሰማይ እንድናምን የፈጠረው ጨዋታ አይደለም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ክርስቶስን በእምነት መቀበል እጅግ መሰረታዊ ነገር ነው፡፡

ከክርስቶስ ጋር በሞቱና በትንሳኤው ሙሉ በሙሉ አንድነት መፍጠርን ያካትታል፡፡ በመንፈሳዊ ቋንቋ ሲገለጽ ጳውሎስ እኛ ተሰቅለናል፣ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሰረቱ አሮጌ ኃጢአተኛ መንገዶቻችን አልቀዋል ይላል (ሮሜ 6፡ 5-14)፡፡ ከቀድሞ ሕይወት ጋር መሰረታዊ መለያየት አድርገናል፡፡ ሁሉም ነገር አዲስ ነው (2ቆሮ. 5፡ 17)፡፡ በክርስቶስ አዲስ ሕይወት ለመኖር ተነስተናል፡፡ ከሙታን የተነሳው ክርስቶስ በየቀኑ የበለጠውን እርሱን እንድንመስል እያደረገን በውስጣችን ይኖራል፡፡

ስለዚህ በክርስቶስ ማመን ኃጢአትን ለመስራት ሰበብ ሳይሆን በሕግ በተመሰረተ ኃይማኖት ውስጥ በፍጹም ሊገኝ በማይችልበት ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር እጅግ የጠለቀና የበለጸገ ግንኙነት ለመፍጠር የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

ያለ ሕግ ሥራ ጽድቅ በእምነት ብቻ የሚለውን ሀሳብ እንዴት ትናገራለህ? ምናልባት ኃጢአትን ለመስራት ምክንያት መስጠት ነው ብለህ እንድታስብ በማድረግ ትንሽ ያስፈራሃልን ወይስ ደስ ይልሃል? መልስህ ስለ ድነት ስላለህ መረዳት ምን ይላል?
 

ሐምሌ 14
Jul-21


 

የውይይት ጥያቄዎች፡

 

ከላይ በተጠቀሰው የመጀመሪያው ንባብ ውስጥ ኤለን ጂ ኋይት ከጽድቅ በእምነት የበለጠ አጽንዖት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ርዕስ የለም ትላለች፡፡ እንደ ክፍል እሷ የሰጠቻቸው አስተያየቶች ከዛሬ መቶ አመታት በፊት በጻፈች ጊዜ አስፈላጊ የሆኑትን ያህል ዛሬ ላለን ለእኛም የሚያስፈልጉ መሆን አለመሆናቸውን ተወያዩ፡፡ ዛሬም አስፈላጊ ከሆኑ ለምን?

ስለ ፕሮቴስታንት ተሃድሶና ስለ ሉተር አስቡ፡፡ ምንም እንኳን ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታዎች የተለያዩ ቢሆኑም በዚህ ቦታ ጳውሎስ ያቀረበው እውነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ከሮም መንፈሳዊ ባርነት ነጻ ለማውጣት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነገር የነበረው ለምን ነበር?

ማጠቃለያ፡- ጴጥሮስ በአንጾኪያ ያሳየው ባሕርይ የቀድሞ አህዛቦች አስቀድመው ካልተገረዙ በስተቀር እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆን እንደማይችሉ ሀሳብ ይሰጣል፡፡ ጳውሎስ ደግሞ የዚህ ዓይነት አስተሳሰብን ስህተትነት አመለከተ፡፡ ከሰው ሁሉ የተሻለ ሰብአዊ ፍጡር እንኳን ፍጹም ስላልሆነ እግዚአብሔር ማንንም ቢሆን በሚያሳየው ባሕርይ ላይ ተመስርቶ ጻድቅ ነህ አይለውም፡፡ ኃጢአተኞች በፊቱ ከበደል ነጻ መሆን የሚችሉት እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ለእኛ ያደረገልንን ነገር በመቀበል ብቻ ነው፡፡