ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንበቡ፡- ገላ. 3፡ 26- 4፡ 20፤ ሮሜ 6፡ 1-11፤ ዕብ. 2፡ 14-18፤ 4፡ 14፣ 15፤ ሮሜ 9፡ 4፣ 5፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - ‹‹ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ ነህ እንጂ ባሪያ አይደለህም፤ ልጅም ከሆንህ ደግሞ በክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሽ ነህ›› (ገላ. 4፡ 7)፡፡
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች እንደ ባሪያዎች ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆች ከሙሉ መብቶቹና ጥቅሞቹ ጋር መኖርና መስራት እንዳለባቸው ይነግራል፡፡ ይህ ወጣቱ ማርቲን ሉተር መስማት የፈለገው እውነት ነበር፡፡ የኃጢአተኛነት ስሜቱ እየጠለቀ ሲሄድ ወጣቱ በራሱ ሥራ ይቅርታንና ሰላምን ለማግኘት ፈለገ፡፡ የመነኮሴነት (የገዳም) ሕይወት በባሕርዩ ውስጥ ካሉት ክፋቶች ሊያላቅቀው ስላልቻለ በጾም፣ ነቅቶ በመጠበቅ፣ እና ራሱን በጅራፍ በመግረፍ እነዚህን ክፋቶች ለማስገዛት እጅግ ጥብቅ የሆነ ሕይወትን መራ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት እንዲቆም የሚያችለውን የልብ ንጽህና ሊያስገኝለት ከሚችል ከማንኛውም መስዋዕትነት ወደ ኋላ አላለም፡፡ በኋላ ስለ ራሱ ሲናገር በጊዜው የነበሩትን ደንቦች በጥብቅ የተከተለ ኃይማኖተኛ መነኮሴ እንደ ነበር ይገልጻል፡፡ ‹‹መነኩሴ በምንኩስና ስራው ሰማይ ማግኘት የሚችል ከሆነ በእርግጠኝነት ለዚህ የተገባሁ እሆን ነበር፡፡›› ነገር ግን ይህ ለእርሱ አልሰራለትም፡፡ ኋላ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ እንደተገለጠው በክርስቶስ አማካይነት ስለሚገኘው ድነት መረዳት ሲጀምር ለነፍሱ መንፈሳዊ ነፃነትና ተስፋ ማግኘት ጀመረ፡፡ ከዚህ የተነሳ ዓለማችን እንኳን ከድሮው የተለየ ሆኗል፡፡
ገላትያ 3፡ 25ን በአእምሮዎ ይዘው ገላትያ 3፡ 26ን ያንብቡ፡፡ አሁን በኢየሱስ ለተዋጀን ይህ ጥቅስ ከሕግ ጋር ያለንን ግንኙነት እንድንረዳ እንዴት ይረዳናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በቁጥር 26 ጅምር ላይ ያለው ‹‹ለ›› የሚለው ቃል ጳውሎስ በዚህ ቁጥርና ከዚህ በፊት ባለው ቁጥር መካከል ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት መመልከቱን ያመለክታል፡፡ እንደ ጳውሎስ አባባል የጌታው ልጅ ለአካለ መጠን እስኪደርስ ድረስ በሞግዚት ሥር የነበረ ሲሆን ወደ ክርስቶስ እምነት የሚመጡ ሰዎች በሞግዚት ስር ከመሆን ያለፉ ናቸው፤ አሁን የጎለመሱ ‹‹ልጆች›› ስለሆኑ ከሕግ ጋር ያላቸው ግንኙነት ተለውጦአል፡፡
ልጅ የሚለው ቃል ለወንዶች ብቻ የተሰጠ አይደለም፤ ጳውሎስ በዚህ ምድብ ውስጥ ግልጽ በሆነ ሁኔታ ሴቶችንም ያካትታል (ገላ. 3፡28)፡፡ ጳውሎስ ልጆች በማለት ፈንታ ወንድ ልጆች የሚለውን ቃል የሚጠቀምበት ምክንያት ለወንድ ልጅ የሚተላለፈው የቤተሰብ ውርስ አእምሮው ውስጥ ስላለ እና በብሉይ ኪዳን ውስጥ ‹‹የእግዚአብሔር ልጆች›› የሚለው ሀረግ ለእስራኤል ልጆች የተሰጠ ልዩ ስያሜ ስለሆነ ነው (ዘዳ. 14፡1፣ ሆሴእ 11፡1)፡፡ መጀመሪያ ለእስራኤላውያን ብቻ የነበረውን ይህን ልዩ ግንኙነት በክርስቶስ አህዛቦችም ያገኛሉ፡፡ ጥምቀትን ይህን ያህል ወሳኝ ክስተት እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምንድር ነው? ገላ. 3፡ 27፣ 28፤ ሮሜ. 6፡ 1-11፤ 1 ጴጥ. 3፡ 21፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በቁጥር 27 ላይ ‹‹ለ›› የሚለውን ቃል መጠቀሙ በድጋሚ የሚያቀርበው ሀሳብ የቀረበ ምክንያታዊ እድገት እንዳለው ያመለክታል፡፡ ጳውሎስ ጥምቀትን የሚያየው ራሳችንን ከክርስቶስ ጋር አንድ ለማድረግ የምናደርገው መሰረታዊ ውሳኔ እንደሆነ ነው፡፡ በሮሜ 6 ላይ ጥምቀት ምሳሌያዊ በሆነ ሁኔታ ከኢየሱስ ጋር በሞቱና በትንሳኤው አንድ መሆን እንደሆነ ይገልጻል፡፡ በገላትያ መጽሐፍ ውስጥ ጳውሎስ የተለየ ዘይቤአዊ አነጋገር ይጠቀማል፡- ጥምቀት ክርስቶስን የመልበስ ተግባር ነው፡፡ ጳውሎስ የሚጠቀማቸው ቃላት በብሉይ ኪዳን ውስጥ በጽድቅና በድነት ስለመሸፈን የሚናገሩ አስደናቂ ንባቦችን የሚያስታውሱ ናቸው (ኢሳ. 61፡ 10፣ ኢዮብ 29፡ 14ን ያንብቡ)፡፡ ‹‹ጳውሎስ ጥምቀትን የሚመለከተው ክርስቶስ አማኙን እንደ ልብስ የሚሸፍንበት ጊዜ እንደሆነ አድርጎ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጳውሎስ ቃሉን ባይጠቀምም ለአማኞች የሚሰጠውን ጽድቅ እየገለጸ ነው፡፡”— FrankJ. Matera, Galatians (Collegeville, Minn.: The LiturgicalPress, 1992), p. 145.
በጥምቀት ምሳሌ የተገለጸው ከክርስቶስ ጋር የምንፈጥረው አንድነት ማለት ስለ ክርስቶስ እውነት የሆነው ነገር ለእኛም እውነት መሆኑን ነው፡፡ ክርስቶስ የአብርሃም ‹‹ዘር›› ስለሆነ አማኞችም ‹‹ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች›› (ሮሜ 8፡ 17) በመሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጡ የቃል ኪዳን ተስፋዎች ሁሉ ወራሾች ናቸው፡፡ ለክርስቶስ እውነት የሆነው ነገር ለእኛም እውነት ነው በሚለው ሀሳብ ላይ ተነጋገሩ፡፡ ይህ አስደናቂ የሆነ እውነት በእያንዳንዱ የኑሮ ሁኔታ ላይ ተጽእኖ ማሳደር ያለበት እንዴት ነው?
ጳውሎስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ከልጆችና ከወራሾች ጋር ካነጻጸረ በኋላ ይህን ዘይቤያዊ አነጋገር በገላትያ 4፡ 1-3 ላይ ያለውን የውርስ ዋና ሀሳብ በማካተት ያብራራል፡፡ ጳውሎስ የተጠቀማቸው የተለያዩ ቃላት ትልቅ ርስት የነበረው ሰው ንብረቱን ለበኩር ልጁ በመስጠት የሞተበትን ሁኔታ ያሳስባል፡፡ ነገር ግን ልጁ ለአቅመ አዳም ያልደረሰ ነው፡፡ ዛሬ እንኳን ኑዛዜ እንደሚደረግ ልጁ እስኪያድግ ድረስ በአሳዳጊዎችና በጠባቂዎች ክትትል ስር እንዲሆን አባት ይናዘዛል፡፡ ባለው ስልጣን የአባቱ ርስት ጌታ ቢሆንም ለአቅመ አዳም ካለመድረሱ የተነሳ በተግባራዊ ሁኔታ ሲታይ ከባሪያ የሚበልጠው በጣም በጥቂቱ ነው፡፡
የጳውሎስ ንጽጽር በገላትያ 3፡ 24 ላይ ካለው ሞግዚት ጋር ተመሳሳይ ነው፣ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ የመጋቢዎችና የጠባቂዎች ኃይል እጅግ ከፍ ያለና እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ የእነርሱ ኃላፊነት የጌታን ልጅ ለማሳደግ ብቻ ሳይሆን ልጁ እነዚህን ስራዎች በራሱ መስራት እስከሚችል ድረስ ገንዘብንና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ሁሉ የመቆጣጠር ኃላፊነትም አለባቸው፡፡
ገላትያ 4፡ 1-3ን አንብቡ፡፡ አሁን በክርስቶስ ሆነን ሳለን የህግ ሚና በእኛ ሕይወት ምን መሆን እንዳለበት ግልጽ ለማድረግ እንዲረዳ በዚያ ቦታ ጳውሎስ እየነገረን ያለው ነገር ምንድር ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ‹‹መጀመሪያ ትምህርት›› ወይም ‹‹ተራ መርሆዎች›› የሚለውን ሀረግ ሲጠቀም በትክክል ምን ማለቱ እንደሆነ እስካሁን አጨቃጫቂ ነው (ገላ. 4፡3፣ 8) ፡፡ እስቶይቼይያ የሚለው የግሪክ ቃል ‹‹መሰረታዊ ነገሮች›› የሚል ትርጉም አለው፡፡ አንዳንዶች ዩኒቨርስ የተሰራባቸውን መሰረታዊ ነገሮች ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል አድርገው አይተውታል (2 ጴጥ. 3፡10፣ 12)፤ ወይም ይህን ክፉ ዘመን የሚቆጣጠሩ አጋንንታዊ ኃይሎች እንደሆኑ አድርገው ተመልክተዋል (ቆላ. 2፡15)፤ ወይም የኃይማኖታዊ ሕይወት መርሆዎች ጥልቀት የሌላቸው ሀሳቦች፣ የኃይማኖት ኤቢሲ እንደሆኑ አድርገው ተመልክተዋል (ዕብ.5፡ 12)፡፡ ጳውሎስ ከክርስቶስ በፊት እንደ ‹‹ሕጻናት›› ባለው የሰብአዊነት ሁኔታ ላይ አጽንዖት መስጠቱ (ገላ. 4፡ 1-3) እርሱ እየጠቀሰ ያለው ጥልቀት የሌላቸውን የኃይማኖት ሕይወት መርሆዎችን መሆኑን ያሳያል፡፡ እንዲህ ከሆነ የብሉይ ኪዳን ዘመን ከሕጎቹና ከመስዋዕቶቹ ጋር የድነትን መሰረታዊ ነገሮች የዘረዘረ የወንጌል ዐውደ ንባብ (የጀማሪዎች ማስተማሪያ መጽሐፍ) ነው እያለ ነው፡፡ ሜዳዊ ስርዓቶች ለእስራኤላውያን አስፈላጊና አስተማሪ ቢሆኑም ሊመጣ ላለው ጥላ ብቻ ነበሩ፡፡ የክርስቶስን ቦታ እንዲወስዱ በፍጹም የታቀዱ አልነበሩም፡፡ ከክርስቶስ ይልቅ በእነዚህ መርሆዎች ዙሪያ የአንድን ሰው ሕይወት መቆጣጠር በጊዜ ወደ ኋላ ለመሄድ እንደመፈለግ ነው፡፡ ለገላትያ ሰዎች ክርስቶስ ከመጣ በኋላ ወደ እነዚያ ጥልቀት ወደሌላቸው መሰረታዊ ነገሮች መመለስ ለአቅመ አዳም የደረሰ ልጅ ተመልሶ ሕጻን ለመሆን እንደመፈለግ ነው! የሕጻንን የመሰለ እምነት አዎንታዊ መሆን ቢችልም (ማቴ. 18፡ 3)፣ ይህ ከመንፈሳዊ ብስለት ጋር በትክክል ተመሳሳይ ነገር ነውን? ወይም በመንፈሳዊነት የበለጠ ባደጋችሁ መጠን እምነታችሁ የበለጠውን ሕጻን የመሰለ ይሆናልን? እምነታችሁ ምን ያህል ሕጻን የመሰለ ‹‹ተንኮል የሌለበት›› እና የሚታመን ነው?
“ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ” (ገላ. 4፡ 4)፡፡ ጳውሎስ የዘመኑ ፍጻሜ የሚለውን ቃል መምረጡ የሚያመለክተው እግዚአብሔር በሰብአዊ ታሪክ ውስጥ ዓላማውን በመፈጸም ረገድ የነቃ ሚና እንዳለው ነው፡፡ ኢየሱስ የመጣው ዝም ብሎ በማንኛውም ጊዜ አይደለም፤ እግዚአብሔር ባዘጋጀው በትክክለኛው ጊዜ ነው የመጣው፡፡ ከታሪክ አንጻር ሲታይ ያ ጊዜ ፓክስ ሮማና (የሮማውያን ሰላም) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በሮም ግዛት ውስጥ ለሁለት መቶ አመት አንጻራዊ የሆነ ሰላምና መረጋጋት የነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ሮም የሜደትራኒያን ዓለም መውረሯ ሰላምን፣ የጋራ መግባቢያ ቋንቋን፣ ምቹ የመጓጓዣ መንገድን እና ወንጌል በፍጥነት እንዲስፋፋ የረዳውን የጋራ ባሕል አመጣ፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ አንጻር ደግሞ ቃል የተገባው መሲህ እንዲመጣ እግዚአብሔር የወሰነው ጊዜ ጅምር ነበር (ዳን. 9፡ 24-27ን ይመልከቱ)፡፡ ክርስቶስ እኛን ለማዳን የእኛን ሰብአዊነት መቀበል ለምን አስፈለገው? ዮሐ. 1፡14፤ ገላ. 4፡4፣ 5፤ ሮሜ 8፡3፣ 4፤ 2 ቆሮ. 5፡21፤ ፊል. 2፡5-8፤ ዕብ. 2፡14-18፤ 4፡14፣ 15፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ገላትያ 4፡ 4፣ 5 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እጅግ ግልጽና አጭር የሆነ የወንጌል ዘገባን ይዟል፡፡ ኢየሱስ በሰብአዊ ታሪክ ውስጥ መምጣቱ አጋጣሚ አልነበረም፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ልጁን ላከ፡፡›› በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር በእኛ የድነት ጉዳይ ተነሳሽነትን ወሰደ፡፡ በእነዚህ ቃላት ውስጥ ያልተገለጸው ሌላኛው ነገር በክርስቶስ ዘላለማዊ አምላክነት ውስጥ መሰረታዊ የሆነ የክርስቲያን እምነት ነው (ዮሐ. 1፡ 1-3፣ 18፤ ፊል. 2፡ 5-9፤ ቆላ. 1፤ 15-17)፡፡ እግዚአብሔር ሰማያዊ መልእክተኛን አልላከም፡፡ እርሱ ራሱ መጣ፡፡ ኢየሱስ አስቀድሞ የነበረ መለኮታዊ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም ‹‹ከሴት ተወለደ፡፡›› ምንም እንኳን ከድንገል መወለዱ በዚህ ሀረግ ውስጥ በተዘዋዋሪ ቢጠቀስም የበለጠ የሚያጸናው ትክክለኛ ሰብአዊነቱን ነው፡፡ ‹‹ከሕግ በታች የተወለደ›› የሚለው ሀረግ የሚያመለክተው የኢየሱስን የአይሁድነት ውርስ ብቻ ሳይሆን የእኛን ኩነኔ መሸከሙንም ጭምር ነው፡፡ እኛ ራሳችንን ማዳን ስላልቻልን የክርስቶስ የእኛን ሰብአዊነት መውሰድ አስፈላጊ ነበር፡፡ የእርሱን መለኮታዊ ባሕርይ ከእኛ የወደቀ ሰብአዊ ባሕርይ ጋር አንድ በማድረግ ክርስቶስ ህጋዊ በሆነ ሁኔታ የእኛ ምትክ፣ አዳኝ እና ሊቀ ካህን ለመሆን በቅቷል፡፡ እንደ ሁለተኛ አዳም፣ የመጀመሪያው አዳም ባለመታዘዙ ምክንያት ያጣውን ነገር ሁሉ ለመመለስ መጣ፡፡ (ሮሜ 5፡12-21)፡፡ በመታዘዙ አሳዛኝ የሆነውን የአዳምን ውድቀት በመዋጀት የሕግን ጥያቄ በትክክል አሟላ፡፡ ስለዚህ በእውነተኛ እምነትና ራስን አሳልፎ በመስጠት ወደ እርሱ የሚመጡትን ሁሉ ለማዳን መብት በማግኘቱ በመስቀል ላይ በመሞት ሕግ የኃጢአተኛውን ሞት የሚጠይቀውን የፍትህ ጥያቄ መለሰ፡፡
ጳውሎስ በገላትያ 4፡ 5-7 ላይ ክርስቶስ አሁን ‹‹ከሕግ በታች የነበሩትን ዋጀ›› (ቁ. 4፣ 5) በሚለው ሀሳብ ላይ አጽንዖት በመስጠት ዋና ሀሳቡን ያብራራል፡፡ መዋጀት የሚለው ቃል ‹‹መልሶ መግዛት›› ማለት ነው፡፡ ምርኮኛን ወይም ባሪያን ነጻ ለማውጣት የሚከፈል ዋጋን ያመለክታል፡፡ ይህ አገባብ እንደሚያሳየው መዋጀት አሉታዊ የሆነ ዳራን ያመለክታል፡- ግለሰቡ ነጻ መውጣት ያስፈልገዋል፡፡
ታዲያ ከምንድር ነው ነጻ የምንወጣው? አዲስ ኪዳን ከብዙዎች መካከል አራቱን ያቀርባል፡- (1) ከሰይጣንና ከማታለያው ነጻ መውጣት (ዕብ. 2፡ 14፣ 15)፣ (2) ከሞት ነጻ መውጣት (1 ቆሮ. 15፡ 56፣ 57)፣ (3) በተፈጥሮ ባርያ ከሚያደርገን ከኃጢአት ኃይል ነጻ መውጣት (ሮሜ 6፡ 22)፣ (4) ከሕግ ኩነኔ ነጻ መውጣት (ሮሜ 3፡ 19-24፣ ገላ. 3፡ 13፤ 4፡ 5)፡፡
በእርሱ ባገኘን መዋጀት አማካይነት ክርስቶስ ለእኛ ምን አዎንታዊ ዓላማ ነው ያሳካልን? ገላ. 4፡ 5-7፤ ኤፌ. 1፡5፤ ሮሜ 8፡ 15፣ 16፣ 23፤ 9፡ 4፣ 5፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ብዙ ጊዜ ክርስቶስ ለእኛ ስላደረገልን ነገር ስንናገር ‹‹ድነት›› እንደሆነ እንናገራለን፡፡ ይህ እውነት ቢሆንም ጳውሎስ ጉዲፈቻነት ወይም የልጅነት ማዕረግ (huiothesia) እንደሚለው ልዩ ቃል ግልጽና ገላጭ አይደለም፡፡ ጳውሎስ ይህን ቃል የተጠቀመው ብቸኛው የአዲስ ኪዳን ጸሐፊ ቢሆንም ልጅን በጉዲፈቻ ተቀብሎ ማሳደግ በግሪክና በሮም ዓለም በደንብ የሚታወቅ ሕጋዊ ስርዓት ነበር፡፡ በጳውሎስ ዘመን በርካታ የሮም ነገስታት ወራሽ ከሌላቸው ልጅን በጉዲፈቻ ማሳደግን እነርሱን የሚተካ ሰው የመምረጫ መንገድ አድርገው ይጠቀሙ ነበር፡፡ ጉዲፈቻነት የሚያስገኛቸው በርካታ ጥቅሞች የሚከተሉት ናቸው፡- ‹‹ (1) በጉዲፈቻነት የተወሰደው ልጅ ጉዲፈቻ አድርጎ ለተቀበለው ሰው እውነተኛ ልጅ ይሆናል…፡፡ (2) ጉዲፈቻ አድርጎ የተቀበለው ሰው ልጁን በተገቢ ሁኔታ ለማሳደግና አስፈላጊ የሆነውን ምግብና ልብስ ለመስጠት ይስማማል፡፡ (3) ጉዲፈቻ የተቀበለው ሰው የጉዲፈቻ ልጁን ልጄ አይደለም ብሎ መካድ አይችልም፡፡ (4) ልጁ ወደ ባርነት ደረጃ ዝቅ አይደረግም፡፡ (5) የልጁ የሥጋ ወላጆች ልጃችን ነው ብለው የመጠየቅ መብት የላቸውም፡፡ (6) ጉዲፈቻነት የውርስ መብት ይሰጣል፡፡›› —Derek R. MooreCrispin,“Galatians 4:1–9: The Use and Abuse of Parallels,” TheEvangelical Quarterly, vol. LXI/ No. 3 (1989), p. 216.
እነዚህ መብቶች በምድር ላይ ዋስትና ካላቸው እንደ እግዚአብሔር ጉዲፈቻ ልጆች ያሉን መብቶች ምን ያህል ከዚህ እጅግ እንደሚበልጡ አስቡ! ዛሬ ልጆች ወላጆቻቸውን አባባ ወይም አባዬ ብለው እንደሚጠሩ ሁሉ በገላትያ 4፡ 6 ላይ አባ ተብሎ የተጠቀሰው ቃል ልጆች ወላጆቻቸውን ለመጥራት ይጠቀሙበት የነበረ ቅርበትን የሚያሳይ ቃል መሆኑን በመገንዘብ አንብቡ፡፡ ይህን ቃል ኢየሱስ በጸሎት ውስጥ ተጠቅሞአል (ማር. 14፡36)፣ እኛም እንደ እግዚአብሔር ልጅነታችን እርሱን ‹‹አባ›› ብለን የመጥራት መብት አለን፡፡ በሕይወትዎ ከእግዚአብሔር ጋር እንደዚህ ዓይነት ቅርበት ያለው ግንኙነት ቢኖርዎ ያስደስትዎታልን? ካላስደሰተዎ ችግሩ ምንድር ነው? ይህን ቅርበት ለማምጣት ምን ለውጥ ማድረግ ይችላሉ?
ገላ. 4፡ 8-20ን ያንብቡ፡፡ በዚያ ቦታ ጳውሎስ እያለ ያለውን ነገር ቀጥለው ባሉት መስመሮች ላይ በአጭሩ ይጻፉ፡፡ በገላትያ ሰዎች መካከል የነበሩት የሀሰት ትምህርቶች ምን ያህል አሳስበውት ነበር?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የገላትያ ሰዎች የነበራቸው ኃይማኖታዊ ስርዓት ባሕርይ ምን እንደሚመስል ጳውሎስ በትክክል አይገልጽም፣ ነገር ግን ወደ መንፈሳዊ ባርነት የመራቸው ሀሰተኛ የአምልኮ ስርዓት እንደ ነበራቸው በአእምሮው ውስጥ በግልጽ ይዞ ነበር፡፡ እንዲያውም የነበራቸው ሀሰተኛ አምልኮ አደገኛና አጥፊ እንደሆነ ስላመነበት የገላትያ ሰዎች እያደረጉ ያሉት ነገር ከልጅነት ወደ ባርነት መመለስ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ስሜታዊ ደብዳቤ ጻፈ፡፡
ጳውሎስ ነጥቦቹን ለይቶ ባይናገርም የገላትያ ሰዎች እያደረጉት ስለነበረው የሚያስጠላ ነገር ምን አለ? ገላ. 4፡ 9-11፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ ስለ ‹‹ቀናት፣ ወራት፣ ዘመናትና አመታት›› (ገላ. 4፡ 10) መጥቀሱን ብዙዎች ሜዳዊ ስርዓትን ብቻ ሳይሆን ሰንበትንም ጭምር እንደተቃወመ አድርገው ትርጉም ሰጥተውታል፡፡ ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ትርጉም ማስረጃ የለውም፡፡ በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ በርግጥ ሰንበትንና ሌሎች የተለዩ የአይሁድ ልምምዶችን ነጥሎ ማውጣት ፈልጎ ቢሆን ኖሮ በቀላሉ ስማቸውን ነቅሶ ማውጣት እንደሚችል በቆላ. 2፡ 16 ላይ ግልጽ ሆኗል፡፡ ሁለተኛ፣ የገላትያ ሰዎች እያደረጉት ያለው ነገር ምንም ቢሆን በክርስቶስ ካላቸው ነጻነት ወደ ባርነት እንደመራቸው ግልጽ አድርጓል፡፡ ‹‹ሰባተኛ ቀን ሰንበትን መጠበቅ ሰውን በባርነት ቀንበር ስር የሚያደርግ ከሆነ ፈጣሪ ራሱ የዓለምን የመጀመሪያውን ሰንበት በጠበቀ ጊዜ ወደ ባርነት ገብቷል ማለት ነው!›› — The SDA BibleCommentary, vol. 6, p. 967.
ሰንበትን በተገቢ ሁኔታ መጠበቅ ሰዎች በእርሱ ያገኙትን ነጻነት በሆነ መንገድ እየከለከለ ከሆነ ኢየሱስ ሰንበትን ራሱ ከመጠበቁ አልፎ ሌሎችም እንዲጠብቁት ያስተማረው ለምንድር ነው? (ማር. 2፡27፣ 28፤ ሉቃስ 13፡10-16ን ያንብቡ፡፡) በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነት ውስጥ በክርስቶስ ያገኘነውን ነጻነት የሚቀሙን ልምምዶች ይኖሩ ይሆን? ወይም ልምምዶቹ በራሳቸው ችግር አስከታይ ከመሆናቸው ይልቅ ስለ ልምምዶቹ ያሉን አመለካከቶች ምን ይመስላሉ? የተሳሳተ አመለካከት ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን እንደዚህ አምርሮ ወደሚያስጠነቅቀው ባርነት ሊመራ የሚችለው እንዴት ነው?
“በሰማይ ጉባኤ፣ ሰዎች ሕግ ተላላፊዎች ቢሆኑም ባለመታዘዛቸው እንዳይጠፉ፣ ነገር ግን ክርስቶስ ምትካቸውና ዋስትናቸው መሆኑን በማመናቸው የእግዚአብሔር ምርጦች እንዲሆኑ እንደ እግዚአብሔር በጎ ፈቃድ የጉዲፈቻ ልጆች ሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ለራሱ አስቀድመው ተወሰኑ፡፡ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሰዎች ሁሉ እንዲድኑ ነው፤ ይህ የሆነበት ምክንያት ሰውን ከባርነት ለማስለቀቅ በአንድያ ልጁ ቤዛነት በቂ መሰናዶ በማድረጉ ነው፡፡ የሚጠፉ ሰዎች የሚጠፉት በክርስቶስ አማካይነት የእግዚአብሔር ጉዲፈቻ ልጆች መሆን ስለማይፈልጉ ነው፡፡ የሰው ትዕቢት የድነትን መሰናዶ እንዳይቀበል ይከለክለዋል፡፡ ነገር ግን የሰብአዊ ዘር መልካም ስራ ነፍስን ወደ እግዚአብሔር ፊት አያቀርብም፡፡ ሰው በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነትን እንዲያገኝ የሚያደርገው በስሙ በማመን የተሰጠው የክርስቶስ ጸጋ ነው፡፡ ሥራን ወይም በደስታ የተሞሉ የስሜት በረራዎችን ሰዎች በእግዚአብሔር የመመረጣቸው ማረጋገጫዎች አድርገን ልንደገፍባቸው አንችልም፤ ምርጦች የተመረጡት በክርስቶስ አማካይነት ነው፡፡ .”—Ellen G. White, “Chosen in Christ,” Signs of the Times, January 2, 1893.
ከእግዚአብሔር ጋር አብረን በምናደርገው ጉዞ እንደ ልጆች መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና ምን ማለት እንዳልሆነ በሚገልጸው ሀሳብ ላይ ጊዜ ውሰዱ፡፡ ከእምነታችንና ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት አንጻር መውሰድ ያለብን የትኞቹን የልጅነት ገጽታዎች ነው? በተመሳሳይ ሁኔታ ይህን ሀሳብ እጅግ ወደራቀ ደረጃ የምንወስድባቸው መንገዶች ምንድር ናቸው? ተወያዩ፡፡
ሰብአዊ ፍጡራን ስለ ጸጋ፣ መዳን በእምነት ብቻ መሆኑን የሚገልጸውን ሀሳብ እንዲፈሩ የሚያደርጋቸው ነገር ምንድር ነው? በራስ ስራ መዳን የማይቻል ቢሆንም ብዙ ሰዎች ድነትን ሰርተው ለማግኘት ጥረት የሚያደርጉት ለምንድር ነው?
እንደ ሰንበት ትምህርት ክፍል በሐሙስ ትምህርት ውስጥ ወዳለው የመጨረሻው ጥያቄ ሂዱ፡፡ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ከዚህ በፊት ነጻ በወጣንበት ባርነት ውስጥ የምንያዘው በምን መንገዶች ነው? ይህ በእኛ ላይ የሚፈጸመው እንዴት ነው? እንዲህ ከሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን? እንዴትስ ነጻ መውጣት እንችላለን?
ማጠቃለያ፡- በክርስቶስ አማካይነት እንደ እግዚአብሔር ወንድና ሴት ልጆች ሆነን የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባል እንድንሆን ተቀባይነት አግኝተናል፡፡ የእግዚአብሔር ልጆች እንደመሆናችን የቤተሰብ ግንኙነት የሚያስገኛቸውን መብቶችና ጥቅሞች ሁሉ ማግኘት እንችላለን፡፡ በሕጎችና ደንቦች ላይ ብቻ ተመስርቶ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት መፍጠር ሞኝነት ነው፡፡ እንዲህ ማድረግ ማለት ልጅ ባሪያ ለመሆን በመፈለግ ያለውን ሥልጣንና ውርስ ለመተው እንደመፈለግ ነው፡፡