ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንበቡ፡- ገላ 4: 12-20 1ቆሮ 11:1 ፊል 3:17 1ቆሮ 9:19-23 2ቆሮ 4:7-12::
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ - "ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ሆኜአለሁና፦ እንደ እኔ ሁኑ ብዬ እለምናችኋለሁ" (ገላ 4:12)
እስካሁን እንዳየነው ጳውሎስ ከገላትያ ሰዎች ጋር የፍርሃት ቃላት አልተነጋገረም፡፡ ነገር ግን ጠንከር ያለ ቋንቋው ያንጸባረቀው እርሱ ራሱ ለመሰረተው ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ደህንነት የተሰማውን ከውስጥ የተነሳሳ ስሜት ነበር፡፡ ጳውሎስ እየተናገረ ካለው ወሳኝ ከሆነ ስነ-መለኮታዊ ጉዳይ ባሻገር ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ በስፋት ሲታይ ትክክለኛ የሆነ አስተምህሮ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ያመንናቸው ነገሮች ያን ያህል ጠቃሚ ካልሆኑ፣ የአስተምህሮ ትክክለኛነት ያን ያህል የማያሳስብ ከሆነ፣ ጳውሎስ ደብዳቤውን ሲጽፍ ይህን ያህል ግለት ያለውና የማይደራደረው ለምንድር ነው? በርግጥ እውነታው፣ በተለይ በመላው የወንጌል ጥያቄ ውስጥ፣ የምናምነው ነገር በከፍተኛ ደረጃ ልዩነት ያመጣል፡፡
በገላትያ 4፡12-20 ላይ ጳውሎስ አቀራረቡን በመጠኑ ቀይሮም ቢሆን ንግግሩ ይቀጥላል፡፡ የገላትያ ሰዎች ስህተቶቻቸውን እንዲቀበሉ ለማሳመን በርከት ያሉ ዝርዝር ያላቸውንና በስነ-መለኮታዊነታቸው ውስብስብ የሆኑ መከራከሪያዎችን ካቀረበ በኋላ አሁን ግላዊና የመጋቢነት ተማጽኖውን ያቀርባል፡፡ በገላትያ ሰዎች ላይ እውነተኛ ፍላጎት ከሌላቸው ሀሰተኛ መምህራን በተቃራኒ መልካሙ እረኛ ለጠፋው መንጋ ያለውን እውነተኛ ጭንቀት፣ ስጋት፣ ተስፋና ፍቅር ይገልጻል፡፡ ዝም ብሎ ስነመለኮታዊ አስተምህሮን እያረመ አልነበረም፤ የሚወዳቸውን ሰዎች ለማገልገል እየፈለገም ነበር፡፡
ገላትያ 4፡12-20ን አንብቡ፡፡ ጳውሎስ በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ያስተላለፈው መልእክት ዋናው ሀሳብ ምንድር ነው?
በጳውሎስ ልብ ውስጥ ከባድ የሀላፊነት ስሜት እንደተሰማው የሚገልጸው የመጀመሪው ምልክት የሚታየው በቁጥር 12 ላይ ባደረገው የግል ተማጽኖው ነው፡፡ ይህ ተማጽኖ የመጣው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ‹‹እኔን ምሰሉ›› ብሎ ከተናገረው ተከትሎ ወዲያውኑ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ መማጸን ወይም መለመን የሚለው ቃል ትርጉም በአንዳንድ ትርጉሞች በትክክል አልተላለፈም፡፡ ይህ ቃል በግሪክ ቋንቋ ዲኦማይ (deomai) ይባላል፡፤ ምንም እንኳን ‹‹ማነሳሳት›› ወይም ‹‹መለመን›› ተብሎ ሊተረጎም ቢችልም የግሪኩ ቃል ግን ጠንከር ያለ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት አለው (2 ቆሮ. 5፡ 20፣ 8፡ 4፣ 10፡ 2ን ያንብቡ)፡፡ ጳውሎስ ‹‹እየለመንኳችሁ ነኝ!›› እያለ ነው ያለው፡፡
የጳውሎስ ጭንቀት ስለ ስነ-መለኮታዊ ሀሳቦችና አስተምህሮአዊ አመለካከቶች ብቻ አልነበረም፡፡ ልቡ በአገልግሎቱ አማካይነት ወደ ክርስቶስ ከመጡ ሰዎች ሕይወት ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ ራሱን ከተራ ወዳጅ በላይ አድርጎ ተመለከተ፤ እርሱ መንፈሳዊ አባታቸው ስለነበር እነርሱም ልጆቹ ነበሩ፡፡ ከዚያም በላይ ለገላትያ ሰዎች ያለውን ጭንቀት እርጉዝ ሴት ልጅ ስትወልድ ከሚገጥማት ስቃይና የምጥ ጣር ጋር አመሳስሎታል (ገላ. 4፡19)፡፡ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን በመሰረተ ጊዜ የመጀመሪያው ‹‹ምጥ›› ‹‹ለሰላማዊ መወለድ›› በቂ እንደሆነ አስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን የገላትያ ሰዎች ከእውነት ስለጠፉ ደህንነታቸውን ለማግኘት እንደገና ያንን የምጥ ጣር እየተለማመደ ነው፡፡
ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በአእምሮው ምን ግብ ነበረው? በእነርሱ ፈንታ ከሚደርስበት ‹‹ምጥ›› ምን ውጤት ማየት ፈለገ? ገላ. 4፡ 19፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በመጀመሪያ የገላትያ ሰዎች በማህጸን ውስጥ እየተፈጠሩ እንደሆነ ከገለጸ በኋላ አሁን የገላትያን ሰዎች የመውለጃ ቀናቸውን እንደሚጠባበቁ እናቶች ይገልጻቸዋል፡፡ ‹‹መፈጠር›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በሕክምና ቋንቋ የጽንስ ዕድገትን ለማሳየት ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዚህ ዘይቤያዊ አነጋገር አማካይነት ክርስቲያን መሆን በግለሰብ ደረጃም ሆነ እንደ ቤተ ክርስቲያን በጅምላ ምን ማለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ የክርስቶስ ተከታይ መሆን ማለት እምነቱን መቀበል ብቻ ማለት አይደለም፤ መሰረታዊ በሆነ ሁኔታ ክርስቶስን ወደ መምሰል መለወጥን ያካትታል፡፡ ጳውሎስ በገላትያ ሰዎች ውስጥ ይፈልግ የነበረው ጥቂት መጠነኛ ለውጦችን ሳይሆን እነርሱን መመልከት ክርስቶስን መመልከት እንደሆነ የሚያሳይ ለውጥን ነበር፡፡›› —Leon Morris, Galatians (Downers Grove, Ill.:InterVarsity Press, 1996), p. 142.
የክርስቶስ ባሕርይ በሕይወትዎ ተገልጦ ያዩት በምን መንገዶች ነበር? ገና ብዙ እድገት የሚያስፈልግዎ በምን አከባቢዎች ነው?
1 ቆሮ. 11፡1፤ ፊል. 3፡17፤ 2 ተሰ. 3፡7-9፤ እና የሐዋ. 26፡20፣ 29ን ያንብቡ፡፡ በእነዚህ ንባቦች ውስጥ ጳውሎስ በገላ. 4፡ 12 ላይ የገለጸውን ምን ነገር እያለ ነው? የእርሱን ሀሳብ እንዴት እናስተውላለን?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በደብዳቤዎቹ ውስጥ ብዙ ጊዜ ክርስቲያኖች እርሱን እንዲመስሉ ያደፋፍራቸዋል፡፡ በእያንዳንዱ ሁኔታ ጳውሎስ ራሱን የሚያቀርበው አማኞች መከተል እንዳለባቸው ሥልጣን ያለው ምሳሌ አድርጎ ነው፡፡ በ2ኛ ተሰሎንቄ 3፡ 79 ላይ በተሰሎንቄ ያሉ አማኞች በሌሎች ላይ ሸክም ከመሆን ይልቅ በራሳቸው ሰርተው ኑሮአቸውን እንዲያሸንፉ ራሱን እንደ ምሳሌ ያቀርብላቸዋል፡፡ በ1ኛ ቆሮንቶስ 11፡ 1 ላይ የቆሮንቶስ ሰዎች የሌሎችን ደህንነት በማስቀደም የእርሱን ምሳሌ እንዲከተሉ ጥሪ ያቀርብላቸዋል፡፡ ጳውሎስ በገላትያ ሰዎች ዘንድ የነበረው ጭንቀት የተለየ ይመስላል፡፡
በገላትያ 4፡ 12 ላይ ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች እርሱን እንዲመስሉ አይጠይቃቸውም፤ በዚህ ፈንታ ‹‹እንደ እርሱ እንዲሆኑ›› ይጠይቃቸዋል- በዚህ ላይ እየተናገረ ያለው ስለመሆን እንጂ ስለማድረግ አይደለም፡፡ ለምን? በገላትያ የነበረው ችግር በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንደነበረው ስነምግባር የጎደለው ባሕርይ ወይም እግዚአብሔርን የማይመስል የአኗኗር ዘይቤ አልነበረም፡፡ በገላትያ የነበረው ጉዳይ ስር የሰደደው በራሱ በክርስትና ውስጥ ነበር፡፡ ችግራቸው ስለ ‹‹መሆን›› ሳይሆን ስለ ‹‹ባሕርይ›› ነበር፡፡ ጳውሎስ እየነገራቸው የነበረው እንደ እኔ አድርጉ ሳይሆን እኔ የሆንኩትን ሁኑ ነበር፡፡ በገላትያ 4፡ 12 ላይ ያለው አባባል በተመሳሳይ ሁኔታ ጳውሎስ በሐዋ. 26፡ 29 ላይ ለሄሮድስ አግሪጳ 2ኛው ‹‹አንተ ብቻ ሳትሆን በዚህ ቀን የሚሰሙኝ ሁሉ ከዚህ ከእስራቴ በስተቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ እፈልጋለሁ›› በማለት ባቀረበው ተማጽኖ ውስጥ ይገኛል፡፡ በሌላ አነጋገር ጳውሎስ እየጠቀሰ ያለው እንደ ክርስቲያን ያለውን ልምምድ፣ በክርስቶስ ላይ ብቻ የሚያርፈውን መሰረት፣ በሕግ ሥራ ሳይሆን ክርስቶስ ለእርሱ ባደረገው ነገር ላይ የሚታመን እምነትን ነው፡፡ የገላትያ ሰዎች በክርስቶስ ካላቸው ማንነት ይልቅ ለባሕርያቸው ትልቅ ዋጋ እየሰጡ ነበር፡፡
ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች እንደ እርሱ እንዲሆኑ እንዴት እንደሚፈልግ ነጥቡን ባያስቀምጥም በገላትያ ሰዎች ዘንድ ያለው ሁኔታ አገባብ የሚያመለክተው አባባሉ የሕይወቱን እያንዳንዱን ገጽታና ዝርዝር የሚሸፍን ብርድ ልብስ አለመሆኑን ነው፡፡ የእርሱ ችግር የገላትያ ሰዎች ትኩረት ሕግን ማዕከል ያደረገ ኃይማኖት ስለነበር ጳውሎስ በአእምሮው የነበረው በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘው አስደናቂ ፍቅር፣ ደስታ፣ ነጻነት፣ እና የድነት እርግጠኝነት ነበር፡፡ ከአእምሮ በላይ በሆነው የክርስቶስ ድንቅ ብርሃን አንጻር ሲመለከተው ጳውሎስ ሁሉንም ነገር እንደ ጉድፍ መቁጠርን ተምሮአል (ፊል. 3፡ 5-9)፤ የገላትያ ሰዎችም ተመሳሳይ ልምምድ እንዲኖራቸው ይናፍቃል፡፡
ከኢየሱስ ሌላ ጥሩ ምሳሌ ሊሆንልዎ የሚችል ሰው አለን? እንደዚያ ዓይነት ሰው ካለ በዚያ ሰው ላይ ምሳሌ ሊሆንልዎ የሚችሉ ምን ጥሩ ነገሮችን አገኙ? እነዚያን ጥሩ ነገሮች በሕይወትዎ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
1 ቆሮ. 9፡19-23ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 4፡12 መጨረሻ ክፍል ያቀረበውን ነጥብ እንድናስተውል እንዲረዳን በእነዚህ ቁጥሮች ላይ ምን ይላል? (የሐዋ. 17፡1634፣ 1 ቆሮ. 8፡ 8-13፣ ገላ. 2፡11-14ን ደግሞ ያንብቡ፡፡)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ገላትያ 4፡12 ትንሽ ግራ የሚያጋባ ሊመስል ይችላል፡፡ ጳውሎስ እንደ ገላትያ ሰዎች ከሆነ እነርሱ እንደ እርሱ መሆን ለምን ያስፈልጋቸዋል? በትናንቱ ጥናት እንደተመለከትን ጳውሎስ ለድነት ክርስቶስ በቂ እንደሆነ ፍጹም እምነትና መተማመን ስለነበረው እነርሱም እንደ እርሱ እንዲሆኑ ፈለገ፡፡ እርሱ እንደ እነርሱ ስለመሆኑ የሰጠው አስተያየት የሚያስታውሰን እርሱ ምንም እንኳን አይሁዳዊ ቢሆን በመካከላቸው የነበሩትን አህዛቦች በወንጌል ለመድረስ ሲል ‹‹ሕግ የሌለው›› አህዛብ መሆኑን ነው፡፡ ለአህዛቡ ዓለም ትልቅ ሚስዮናዊ እንደመሆኑ ጳውሎስ ለአህዛብም ሆነ ለአይሁድ ወንጌልን እንዴት እንደሚሰብክ ተምሮአል፡፡ እንዲያውም እንደ 1 ቆሮ. 9፡ 19-23 ከሆነ ወንጌል የማይለወጥ ቢሆንም ጳውሎስ ወንጌልን የሚሰብክበት ሁኔታ ሊደርሳቸው በሚፈልጋቸው ሰዎች ሁኔታ ይለዋወጥ ነበር፡፡ ‹‹ዛሬ ወንጌልን እንደ አገባቡ ማስተማር (contextualization) ለሚለው ዘዴ፣ ማለትም ወንጌልን መልእክቱ እየተላለፈለት ያለው ሕዝብ ሊያስተውል በሚችልበት ሁኔታ ማቅረብ ለሚለው ዘዴ ጳውሎስ ፈር ቀዳጅ ነበር፡፡››— Timothy George, The NewAmerican Commentary: Galatians (Nashville, Tenn.: Broadman& Holman Publishers, 1994), p. 321.
ጳውሎስ በ1 ቆሮ. 9፡ 21 ላይ የሰጣቸው የራሱ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ አንድ ሰው አውዱን ጠብቆ ወንጌልን ማቅረብ ገደብ እንዳለው ያምን ነበር፡፡ አንድ ሰው የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅሞ አይሁድንና አህዛብን የመድረስ ነጻነት ቢኖረውም፣ ክርስቲያኖች ‹‹ከክርስቶስ ሕግ›› በታች ስለሆኑ፣ ይህ ነጻነት ሕገ-ወጥ የሆነ ሕይወት የመኖርን ነጻነት አያካትትም፡፡
ምንም እንኳን አውዱን ጠብቆ ወንጌልን ማቅረብ ሁል ጊዜ ቀላል ባይሆንም ‹‹የወንጌልን ልብ ከባህላዊ ሽፋኑ መለየት እስከቻልን ድረስ በመሰረታዊ ሀሳብ ላይ ሳይደራደሩ የክርስቶስን መልእክት አውዱን ጠብቆ ለማቅረብ እኛም ጳውሎስን የምንቀዳ መሆን አለብን፡፡›› —Timothy George, Galatians, pp.321, 322.
መደራደር ቀላል ነው፣ አይደለም እንዴ? አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው በክርስትና ብዙ ጊዜ በቆየ መጠን መደራደር እየቀለለው ይመጣል፡፡ እንደዚህ የሚሆነው ለምንድር ነው? እስኪ ራስዎን በታማኝነት ይመልከቱ፡፡ በሕይወትዎ ምን ያህል ድርድር ሾልኮ ገብቷል? እነዚህን ነገሮች ትክክል እንደሆኑ አድርገው የተቀበሉአቸው መንገዶች ምንድር ናቸው? ይህን ነገር እርስዎ በሚፈልጉአቸው ቦታዎች ወደ ኋላ መመለስ የሚችሉት እንዴት ነው?
ጳውሎስ ከገላትያ አማኞች ጋር የነበረው ግንኙነት አሁን እንደሆነው ሁል ጊዜ ከባድና የቀዘቀዘ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ጳውሎስ መጀመሪያ ወንጌልን ለገላትያ ሰዎች የሰበከበትን ጊዜ ሲያስብ እንዴት በጥሩ ሁኔታ እንደተቀበሉት ሞቅ ባለ መንፈስ ይገልጻል፡፡ ጳውሎስ ወንጌልን በገላትያ እንዲሰብክ የመራው ክስተት ምን ይመስልዎታል? ገላ. 4፡ 13፡፡
በመጀመሪያ ጳውሎስ በገላትያ ወንጌልን የመስበክ ሀሳብ አልነበረውም፡፡ ነገር ግን የሆነ ሕመም በመንገድ ላይ ያዘውና በገላትያ ከተጠበቀው ጊዜ በላይ እንዲቆይ ወይም ከሕመሙ ለማገገም ወደ ገላትያ እንዲሄድ አስገደደው፡፡ የጳውሎስ ሕመም ትክክለኛ ባሕርዩ ምስጢራዊ ነው፡፡ አንዳንዶች ወባ ይዞት ነበር ይላሉ፤ ሌሎች ደግሞ (ጳውሎስ የገላትያ ሰዎች ዓይናቸውን እንኳን አውጥተው ሊሰጡት ፈቃደኞች እንደሆኑ በተናገረው መሰረት) ምናልባት በሽታው የዓይን ሕመም ሳይሆን አይቀርም ይላሉ፡፡ ሕመሙ በ2ኛ ቆሮ. 12፡7-9 ላይ ከጠቀሰው ‹‹በሥጋው ውስጥ ያለው መውጊያ እሾክ›› ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል፡፡
የጳውሎስ ህመም ምንም ቢሆን ምን የማይመች ከመሆኑ የተነሳ ለገላትያ ሰዎች ፈተና ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ በሽታ እንደ መለኮት አለመደሰት በሚታይበት ዓለም ውስጥ (ዮሐ. 9፡1፣ 2፤ ሉቃስ 13፡1-4) የጳውሎስ ሕመም የገላትያ ሰዎች እርሱንም ሆነ መልእክቱን እንዳይቀበሉ ምክንያት ሊሆንላቸው ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን ጳውሎስን በሙሉ ልባቸው ተቀበሉት፡፡ ለምን? ለዚህ ምክንያቱ ልቦቻቸው በመስቀሉ ስብከት ስለጋሉ (ገላ. 3፡1) እና መንፈስ ቅዱስ ስላሳመናቸው ነበር፡፡ አሁን ለተፈጠረው የአመለካከት ለውጥ ምን ምክንያት ሊሰጡ ይችላሉ?
ጳውሎስ እንዲሰቃይ እግዚአብሔር የፈቀደበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ጳውሎስ ከራሱ ችግሮች ጋር እየታገለ ሳለ እንዴት አድርጎ ሌሎችን ማገልገል ይችላል? ሮሜ 8፡ 28፣ 2 ቆሮ. 4፡ 7-12፣ 12፡7-10፡፡
የጳውሎስ ሕመም ምንም ቢሆን ከባድ ሕመም ስለነበር ለችግሮቹ እግዚአብሔርን ተጠያቂ ለማድረግ ወይም ወንጌልን መስበኩን ለማቋረጥ ቀላል ምክንያት ሊሆንለት ይችል ነበር፡፡ ጳውሎስ ከእነዚህ ሁለቱ አማራጮች አንዱንም አላደረገም ነበር፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች እንዲያሸንፉት ከመፍቀድ ይልቅ በእግዚአብሔር ጸጋ ላይ ሙሉ በሙሉ ለመደገፍ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቀመበት፡፡ ‹‹እግዚአብሔር በተደጋጋሚ በሕይወት ውስጥ የሚመጡ ችግሮችን--ሕመምን፣ ስደትን፣ ድህነትን፣ የተፈጥሮ መቅሰፍቶችንና ሊብራሩ የማይችሉ አሳዛኝ ክስተቶችን--የእርሱን ምህረትና ጸጋ ማሳያ መንገዶችና እንደ ወንጌል ማስፋፊያ መንገዶች ሊጠቀም ይችላል፡፡›› —TimothyGeorge, Galatians, pp. 323, 324. ፈተናዎችዎና ስቃይዎ የበለጠውን በጌታ እንዲደገፉ እንዲያደርጎት መፍቀድን እንዴት መማር ይችላሉ? (ምን ሌሎች አማራጮች አለዎት?)
ገላትያ 4፡ 16ን ያንብቡ፡፡ በዚያ ቦታ ጳውሎስ ምን ኃይለኛ የሆነ ነጥብ እያቀረበ ነው? እርስዎ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር የተለማመዱት በምን መንገዶች ነው? (ዮሐ. 3፡ 19፤ ማቴ. 26፡ 64፣ 65፤ ኤር. 36፡ 17-23ን ይመልከቱ፡፡)
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በተለይ እውነትን መናገር እንደ አለመደራደር፣ በሁኔታዎች ያለመገደብ እና ጠላትን ችላ ብሎ ያለማለፍ ስልት ተደርጎ ሊታይ በሚችልበት በእኛ ጊዜና ዘመን እውነትን መናገር የማይመች ወይም የማይፈለግ ስለሆነ ለአንድ ሰው ‹‹እውነትን መናገር›› የሚለው አባባል ብዙ ጊዜ አሉታዊ ትርጉም አለው፡፡ ጳውሎስ በገላትያ 4፡ 12-20 ላይ የሰጣቸው አስተያየቶችና በሌሎች ደብዳቤዎቹ ውስጥ ተበታትነው ያሉ ጥቂት አስተያየቶች ባይኖሩ ኖሮ (ገላ. 6፡9፣ 10ን ይመልከቱ) እርሱ በወንጌል እውነት ላይ ያለው ፍላጎት ከማንኛውም የፍቅር መግለጫ በልጧል ወደሚል የስህተት ድምዳሜ ላይ መድረስ ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ አስቀድመን እንደተመለከትነው፣ ምንም እንኳን የገላትያ ሰዎች ‹‹የወንጌልን እውነት›› ማወቃቸው ግድ ቢለውም (ገላ. 2፡5፣ 14ን ይመልከቱ) ይህ ፍላጎት የመጣው ለእነርሱ ካለው ፍቅር ነበር፡፡ አንድን ሰው መገሰጽ ወይም ለምንም ምክንያት ቢሆን መስማት የማይፈልጉትን እውነት ግልጽ በሆነ ቋንቋ መናገር ምን ያህል አስጨናቂ እንደሆነ በግሉ ያልተለማመደ ሰው ማን ነው? አንዳንድ ጊዜ የምንናገራቸው ቃላት ወዲያውኑ የሚያስከትሉት ውጤት መጎዳት ወይም ቁጣና ቅያሜ ቢሆንም የምንናገረው ለዚያ ሰው ግድ ስለሚለን ነው እንጂ ልንጎዳው ስለምንፈልግ አይደለም፡፡ ግለሰቡ ለመስማት ቢፈልግም ባይፈልግም መስማት ያለበት ነገር እንደሆነ ስለምናውቅ እንናገራለን፡፡ በገላትያ 4፡17-20 ላይ ጳውሎስ ስለሚቃወማቸው ሰዎች ምን እያለ ነው? ከስነ መለኮት ትምህርታቸው ሌላ ምን አስቸጋሪ ነገር አለ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ የገላትያ ሰዎችን ቁጣ ሊቀሰቅስ እንደሚችል እያወቀ ካስተላለፈው የወንጌል ግልጽነት በተቃራኒ ተቃዋሚዎቹ በገላትያ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ተግተው እየሰሩ ነበር፤ ያን ያደርጉ የነበረው ለገላትያ ሰዎች ካላቸው ፍቅር የተነሳ ሳይሆን ከራስ ወዳድነት ፍላጎታቸው የተነሳ ነበር፡፡ ጳውሎስ ስለ ጠላቶቹ ሲያስጠነቅቅ ‹‹በውጭ ዘግተው ሊያስቀሩአችሁ ይፈልጋሉ›› ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ይህ ማለቱ ምናልባት ለግዝረት ሕግ ካልተገዙ በስተቀር ከወንጌል ጥቅሞች ዘግተው ሊያስቀሩአቸው የሚያደርጉትን ጥረት ለማመልከት ሊሆን ይችላል፡፡
እርስዎ የተናገሩአቸው ቃላት እውነተኛና አስፈላጊ ቢሆኑም የሆነ ሰው እንዲናደድብዎ ያደረጉበትን አጋጣሚ ያስቡ፡፡ ከዚያ ልምምድ በሚቀጥለው ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ሲፈልጉ ሊረዳዎ የሚችል ምን ትምህርት አገኙ?
‹‹በገላትያ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ ግልጽ የሆነና ያልተሸፈነ ስህተት የወንጌልን መልእክት ቦታ እየወሰደ ነበር፡፡ የእውነተኛ እምነት መሰረት የሆነው ክርስቶስ ጊዜ ላለፈባቸው የአይሁድ ስርዓቶች ሲባል በግልጽ እየተካደ ነበር፡፡ በገላትያ ያሉ አማኞች እያሰጉአቸው ካሉት አደገኛ ተጽእኖዎች መዳን ካለባቸው እጅግ ወሳኝ የሆኑ እርምጃዎች መወሰድና ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች መሰጠት እንዳለባቸው ሐዋርያው ተመለከተ፡፡
‹‹እያንዳንዱ የክርስቶስ አገልጋይ መማር ያለበት ጠቃሚ ትምህርት ቢኖር ሥራውን ሊጠቅማቸው ከሚፈልጋቸው ሰዎች ሁኔታ ጋር እንዲስማማ ማድረግ ነው፡፡ ገርነት፣ ትዕግስት፣ መወሰን መቻል፣ እና ጽናት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው፤ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች መተግበር ያለባቸው በተገቢ ሁኔታ ተለይተው ነው፡፡ በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ካሉና ከተለያየ የኑሮ ደረጃ ከመጡ አእምሮዎች ጋር በጥበብ መስራት በእግዚአብሔር መንፈስ የበራና የተቀደሰ ጥበብንና ውሳኔን የሚፈልግ ስራ ነው፡፡
‹‹ጳውሎስ በሆነ ጊዜ በሕይወታቸው የእግዚአብሔርን ኃይል ያወቁ ሰዎችን ወደ መጀመሪያው የወንጌል ፍቅር እንዲመለሱ ተማጸናቸው፡፡ መልስ ሊሰጥበት በማይችል መከራከሪያ በክርስቶስ በሚያስተሰርይ ጸጋ አማካይነት ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ አሳልፈው የሚሰጡና በእርሱ የጽድቅ ልብስ የተሸፈኑ ሁሉ በክርስቶስ ነጻ ወንዶችና ሴቶች የሆኑበትን ዕድል በፊታቸው አስቀመጠላቸው፡፡ እያንዳንዱ መዳን ያለበት ነፍስ በእግዚአብሔር ጉዳዮች ላይ ትክክለኛ የሆነ ግላዊ ልምምድ እንዲኖረው አቋም ወሰደ፡፡
በስቃይ ጥያቄ ላይ እና እግዚአብሔር እንዴት እንደሚጠቀምበት ተወያዩ፡፡ ከስቃይ ውስጥ ምንም ጥሩ ነገር የማይገኝ በሚመስልባቸው ሁኔታዎች ውስጥ ምንድር ነው የምናደርገው?
ክርስቶስ በእኛ ውስጥ መቀረጽ አለበት በሚለው ሀሳብ ላይ አሰላስሉ፡፡ ይህ አባባል ተግባራዊ በሆነ አነጋገር ሲገለጽ ምን ማለት ነው? ይህ ነገር ለእኛ እየሆነ እንደሆነ እንዴት ማወቅ እንችላለን? መሆን አለበት ብለን በምናስበው ፍጥነት እየሆነ ካልሆነ ተስፋ ከመቁረጥ ራሳችንን የምንጠብቀው እንዴትነ ው?
ማጠቃለያ፡- በርካታ የሆኑ ዝርዝር ያላቸውንና በስነ-መለኮታዊ ሁኔታ ውስብስብ የሆኑትን መከራከሪያዎች ካደረገ በኋላ ጳውሎስ አሁን ለገላትያ ሰዎች ግላዊና ስሜታዊ የሆነ ተማጽኖ ያደርግላቸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የተጋሩትን አዎንታዊ ግንኙነትና እንደ መንፈሳዊ አባት ለእነርሱ የነበረውን እውነተኛ ፍቅር በማስታወስ ምክሩን እንዲሰሙ ይመክራቸዋል፡፡