መዳን በእምነት ብቻ:ሮሜ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2017

ከጥቅምት 25-ህዳር 1

ስድስተኛ ትምህርት

November 4–November 10
 

አዳምና ኢየሱስ ክርስቶስ

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት:- ሮሜ 5ን ያንብቡ፡፡

 

የመታሰቢያ ጥቅስ፦ “ እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ፤ በእርሱም ደግሞ ወደቆምንበት ወደ ጸጋው መግባትን በእምነት አግኝተናል፤ በእግዚአብሔር ክብርም ተስፋ እንመካለን፡፡ ” (ሮሜ 5፡1-2)

ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት እና ቅድስና ሊመጣ የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባለን እምነት ብቻ እንደሆነ ፣ የእርሱ ጽድቅ ብቻውን እኛን ወደ እግዚአብሄር ሊያቀርበን እንደሚችል

አስረድቷል፡፡ ጳውሎስ በዚያ ታላቅ እውነት መሠረት ላይ በመሆን ይህንን መሪ ሀሳብ ያሰፋዋል፡፡ እንደ አብረሃም ጻድቅ ለተባለ ሰው ጭምር መዳን በእምነት እንጂ በሥራ አለመሆኑን በመግለጽ ጳውሎስ ወደ ኋላ አንድ ደረጃ በመሄድ ኃጢአትንና መከራን ምን እንዳመጣው፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል መፍትሔ እንዴት እንደተገኘና እርሱ ለሰብዓዊ ዘር ምን እንዳደረገ ወደሚያሳየው ትልቅ ስዕል ይሄዳል፡፡

በአንዱ ሰው አዳም መውደቅ ምክንያት የሰው ዘር በሙሉ ኩነኔን ከእግዚአብሔር መለየትንና ሞትን ወርሷል፤ በአንዱ ሰው በጌታችን ድልና አሸናፊነት ዓለም ሁሉ በአዲስ ሁኔታ በእግዚአብሔር ፊት እንዲቆም ተደርጓል፡፡ በክርስቶስ ባላቸው እምነት፣ የኃጥአት መዝገባቸውና የሚያስከትለው ቅጣት ተደምስሶ ለዘላለም ይቅርታ ተደርጎላቸዋል፡፡

ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት በአዳም የተበላሸውን ለመመለስ እንደመጣ በማወዳደር ይነግረናል፣ እናም የአዳም ኃጢአት ተጎጂ የሆኑ ሁሉ በአዳኙ ኢየሱስ እንዴት ነጻ እንደሚወጡ ያሳየናል፡፡ እርሱን በእምነት ለሚቀበሉና በደሙ መዳናቸውን ለሚያምኑ አይሁድም ሆኑ አህዛብ የድነታቸው ሁሉ መሰረት ኢየሱስ በሰዎች ፋንታ የሞተው ሞት ነው፡፡

በእርግጥ ይህ ታላቅ ዋጋ ያለው የጥናታችን መሪ ሀሳብና የተስፋችን ሁሉ መሰረት ነው፡፡

*ለህዳር 2 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያንብቡ፡፡
 

ጥቅምት 26
November 5
 

በእምነት መጽደቅ

 

ሮሜ 5:1–5ን ያንብቡ፡፡ በታች በተሰጡ መስመሮች የጳውሎስን መልዕክት በአጭሩ ያስቀምጡ፡፡ ከዚህ ለራስዎ ምን ይወስዳሉ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“መጽደቅ” በውጫዊ ትርጉሙ “ጽድቅን ማግኘት” የግሪኩ ግስ እንደሚያመለክተው ድርጊቱ ተፈጽሟል፡፡ በማንኛውም የጽድቅ ሥራችን ሳይሆን ክርስቶስን በመቀበላችን ጻድቅ እንደሆንን ታውጇል ወይም እንደ ጻድቅ ተቆጥረናል፡፡ ክርስቶስ በምድር ላይ የኖረው ፍጹም ህይወትና፣ የእርሱ ፍጹም የሆነው ህግን መጠበቅ ለእኛ ተቆጥሮልናል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የእኛ ኃጢአት በክርስቶስ ላይ ተጫነ፡፡ እኛ የሚገባንን ቅጣት እንድናመልጥ እግዚአብሔር እነዚያን ኃጢአቶች የፈጸምነው እኛ ሳንሆን ክርስቶስ እንደፈጸመው አድርጎ ቆጠረው፡፡ ቅጣቱን እኛ በራሳችን በፍጹም እንዳንጋፈጠው በእኛ ምትክ ፣ ያ ቅጣት ስለ እኛ በክርስቶስ ላይ ወደቀ፣ ለኃጢአተኛ ከዚህ የሚበልጥ ምን ክቡር ዜና ሊኖር ይችላል?

በሮሜ 5፡3 ‹‹ክብር›› ተብሎ የተተረጎመው ቃል በሮሜ 5፡2 ላይ ‹‹ደስታ›› ተብሎ የተተረጎመው ነው፡፡ በአንዳንድ ጥቅሶች ላይ እንደምናገኘው በሮሜ 5፡3 ላይም‹‹ደስታ›› ተብሎ ተተርጉሞ ቢሆን ኖሮ የሁለቱ ጥቅሶች ግንኙነት የበለጠ ግልጽ በሆነ ነበር፡፡ የጸደቁ ህዝቦች በመከራ ደስ ይላቸዋል ምክንያቱም እነርሱ መታመናቸውን በክርስቶስ ላይ ስላደረጉ ነው፡፡ እነርሱ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ለበጎ እንደሚያደርጋቸው ጽኑ እምነት አላቸው፡፡ እነርሱ ስለ ክርስቶስ መከራን መቀበል እንደ ክብር ያዩታል፡፡ (1ጴጥ. 4፡13፡፡)

በሮሜ 5፡3- 5 ያለውን ዕድገት ለማጤን ይሞክሩ፡፡

6. ትዕግስት፡ የግሪኩ ቃል hupomone ማለት “የማይነቃነቅ ጽናት፡፡” በመባል ተተርጉሟል፡፡ ይህ ጽናት በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ እምነቱን ባጸና ሰው ላይ የሚታይ ወይም ህይወትን ተስፋ በሚያስቆርጥ ፈተና ውስጥ በክርስቶስ ላይ ያለው ተስፋ ሁልጊዜ ከእይታው የማይሰወርበት ሰው ላይ የሚታይ ጽናት ነው፡፡

7. ልምድ፡ የግሪኩ ቃል dokime ማለት ‹‹ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ›› ባህርይ ‹‹ትክክለኛ የሆነ ባህርይ›› ማለት ነው፡፡ በትዕግስት መከራን የሚቀበል ትክክለኛ የሆነ ባህርይን ይለማመዳል፡፡

8. ተስፋ፡ ጽናትና መልካም ባህርይ በክርስቶስ የሚገኝ የመዳን ተስፋን ይሰጣል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ እስከተጣበቅን ድረስ የእምነት፣ የንሰሐ እና የመታዘዝ ተስፋ አለን፡፡

በህይወትዎ ከምንም በላይ ተስፋ የሚያደርጉት ነገር ምንድንው? ይህ ተስፋ በክርስቶስ ሊፈጸም የሚችለው እንዴት ነው? ሊፈጸም ይችላል? ይህ የማይሆን ከሆነ የበለጠ ተስፋ በእርሱ ላይ መጣል ይችላሉ?
 

ጥቅምት 27
November 6
 

ገና ኃጢአተኞች ሳለን

 

ሮሜ 5:6–8ን ያንብቡ፡፡ ይህ ስለ እግዚአብሔር ባህርይ ምን ይነግረናል፣ እነዚህ ቃላት ተስፋን የተሞሉት ለምንድነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አዳምና ሄዋን በሚያሳፍርና ይቅርታ በማያሰጥ ሁኔታ የመለኮትን ህግ ሲተላለፉ፣ እግዚአብሔር መልሶ የማደስን ሥራ የመጀመሪያ እርምጃ ወሰደ፡፡ እግዚአብሔር የመዳንን መንገድ በማዘጋጀት ተነሳሽነቱን ካሳየበት ጊዜ ጀምሮ የሰውን ወንዶችና ሴቶች ልጆች እንዲቀበሉት እየጠራቸው ነው፡፡ ‹‹የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ›› (ገላ. 4፡4)

ሮሜ 5፡9 ከእግዚአብሔር ቁጣ መዳን የምንችለው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ የምናስተውለው እንዴት ነው?

-------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------- ከግብጽ ከመውጣታቸው ቀደም ብሎ በነበረው ምሽት የግብጻውያንን በኩር ከገደለው መቅሰፍት የእስራኤላውያን በኩሮቻቸው የዳኑት በበራቸው መቃን ላይ በቀቡት የበጉ ደም ነበር፡፡ በተመሳሰይ ሁኔታ የክርስቶስ ደም እግዚአብሔር የዓለምን ኃጢአት በዘመናት ፊጻሜ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲያጠፋ በእርሱ ጽድቅን ያገኙ ዋስትና ይኖራቸዋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔርን ከመቅሰፍቱ ጋር ስለ መውደድ ይታገላሉ፡፡ ነገር ግን በአጭሩ መቅሰፍቱ ያለው በፍቅሩ ምክንያት ነው፡፡ ዓለምን የሚወድ እግዚአብሔር በኃጢአት ላይ እንዴት ቁጣ አይኖረውም? እርሱ እንደ እኛ ቢሆን ኖሮ በዚህ ስለሚሆነው ነገር ግድ አይኖረውም ነበር፡፡ እስቲ በዙሪያዎ ባለው ዓለም ኃጢአት በተፈጥሮ ላይ ያደረገውን ይመልከቱ፡፡

ታዲያ እግዚአብሔር በዚህ ዓይነት ክፋትና ጥፋት ላይ ቁጣ የማይሞላው እንዴት ነው?

እንድንደሰት የተሰጡን ሌሎች ምክንያቶች ምንድናቸው? ሮሜ 5:10, 11፡፡

አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች ሮሜ 5፡10ን ክርስቶስ ዛሬ ለእኛ እንዲቆጠርልን በዚህ ምድር ላይ የኖረውን ፍጹም ህይወት የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡ ምንም እንኳ ይህ ክርስቶስ ፍጹም ህይወት ያከናወነው ቢሆንም፣ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ እያተኮረ ያለው ክርስቶስ የሞተ ቢሆንም መነሳቱንና ለዘለዓለም ህያው መሆኑን ነው (ዕብ. 7፡ 25ን) ይመልከቱ፡፡ እርሱ በህይወት ስላለ እኛ ድነናል፡፡ እርሱ በመቃብር ቀርቶ ቢሆን ኖሮ የእኛ ተስፋ ከእርሱ ጋር በጠፋ ነበር፡፡ ሮሜ 5፡11 በአምላካችን የምንደሰትበትን ምክንያት በመቀጠል ምክንያቱ ክርስቶስ ለእኛ ያደረገው ነገር መሆኑን ይነግረናል፡፡
 

ጥቅምት 28
November 7
 

ሞት በኃጢአት ምክንያት

 

ሞት የመጨረሻው ጠላት ነው፡፡ እግዚአአብሔር የሰውን ቤተሰብ በፈጠረ ጊዜ ፣ ዕቅዱ የቤተሰቡ አባላት ሁሉ ለዘለዓለም እንዲኖሩ ነበር፡፡ የሰው ልጆች መሞት አይፈልጉም፣ ቢፈልጉም ከብዙ ስቃይና መከራ በኋላ ነው፡፡ ሞት ከመሰረታዊው የህይወታችን ባህርይ ተቃራኒ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያው የተፈጠርነው ለመኖር ስለሆነ ነው፡፡ ሞት እኛ የምናውቀው ጉዳይ አልነበረም፡፡

ሮሜ 5:12ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ሥፍራ ጳውሎስ እየገለጸ ያለው ምንድነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ተንታኞች ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶ የበለጠ በዚህ ላይ ተከራክረዋል፡፡ ምናልባትም ዋና ምክንያቱ በአድቬንቲስት የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ መስጫ መጻህፍት ጥራዝ 6 ገጽ 529 ላይ ተጽፎ እንደሚገኘው ይሆናል፡፡ ‹‹እነዚህ ተንታኞች ጰውሎስ ንባቡን ከተጠቀመበት ዓላማ ውጪ ሲጠቀሙበት ይታያሉ፡፡››

የሚከራከሩበት ነጥብ አንዱ የአዳም ኃጢአት ወደ ተከታዩ ትውልድ የሚተላለፈው እንዴት ነው የሚለው ነው? የአዳም ትውልዶች የእርሱን ኃጢአት በደለኝነት ይከፈላሉ፣ ወይስ እነርሱ በደለኞች የሚሆኑት ስለራሳቸው ኃጢአት ነው? የተወሰኑ ቡድኖች ለጥያቄው መልስ ለማግኘት ይህንን ጥቅስ ተጠቅመዋል ነገር ግን ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ይህንን አይደለም፡፡ በአጠቃላይ መናገር የፈለገው ይህንን አይደለም፡፡ እርሱ ደግሞ እያሳሰበ ያለው ‹‹ሁሉም በድለዋል›› (ሮሜ 3፡23) ኃጢአተኞች መሆናችንን መገንዘብ አለብን፣ ምክንያቱም አዳኝ እንደሚያስፈልገን የምንረዳበት መንገድ ይህ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ሥፍራ ጳውሎስ ሊያስገነዝብ የፈለገው ነገር ኃጢአት ምን ያህል መጥፎ ነገር መሆኑንና በአዳም ምክንያት ወደ አለም የመጣውን ነገር ነው፡፡ ከዚያም እግዚአብሔር በአዳም ኃጢአት ምክንያት በዚህ ዓለም ለመጣው ሥቃይ መድኃኒት ይሆን ዘንድ ኢየሱስን መስዋዕት አድርጎ እንደላከው ያሳያል፡፡

ሆኖም ይህ ጥቅስ በአዳም ስለ ገባው ችግርና ሞት እንጂ ፣ በክርስቶስ ስለተገኘው መፍትሄ አይደለም፡፡ እጅግ ክቡርና ወርቃማ ከሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዱ ሞት በህይወት የሚዋጥ መሆኑ ነው፡፡ ኢየሲስ የሞትን ደጆች የመቃብርን ሰንሰለት በጥሷል፡፡ ‹‹ ሞቼ ነበርሁ አነሆ ከዘላላም እስከ ዘላላም ህያው ነኝ የሞትና የስዖል መክፈቻ አለኝ›› (ራዕይ 1፡18) ክርስቶስ ቁልፉ በእጁ ስለሆነ ጠላት ተጠቂዎቹን በመቃብር ልያቆያቸው አይችልም፡፡

ስለ ሞት እውነታና ስለሚያደርሰው ጉዳት የእርስዎ ተሞክሮ ምን ይመስላል? ይህን በመሰለ ክፉ ጠላት ፊት ከራሳችን በላይ በሆነና ይህ ዓለም ልሰጠን ከሚችለው ነገር በላይ ተስፋ የሚገባን ለምንድነው?
 

ጥቅምት 29
November 8
 

ከአዳም እስከ ሙሴ

 

ሮሜ 5:13, 14ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ ስለ ህግ ምን እያስተማረን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በዚህ ምን እየተናገረ ነው? ‹‹ እስከ ህግ ድረስ›› የሚለው ሐረግ ‹‹ ከአዳም እስከ ሙሴ ››ከሚለው ሐረግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ እርሱ እየተናገረ ያለው ከፍጥረት ጀምሮ እስከ ሲና፣ ይህም ማለት አሥርቱ ትዕዛዛት ለእስራኤላውያን መተዳደሪያ ደንብ ሆነው እስከተሰጠበት ጊዜ ድረስ ማለት ነው፡፡

“እስከ ህግ ደረስ ” ማለት በተለያየ መልኩ የተሰጡ የእግዚአብሔር ህጎች በዝርዝር በሲና ለእስራኤል ልጆች እስከተሰጠበት ድረስ ማለት ነው፡፡ ኃጢአት ከሲና በፊት ነበር፡፡ ማመንዘር መግደል ውሸት መናገር ህግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጥአት አልነበሩም? በእርግጥ ናቸው፡፡

ከሲና በፊት ሰዎች ስለ እግዚአብሄር ያላቸው መገለጥ የተወሰነ ቢሆንም ለተጠያቂነት ግን በቂ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ቅን ፈራጅ በመሆኑ ማንንም ያለ አግባብ አይቀጣም፡፡ ከሲና በፊት የነበሩ ሰዎች ሥፍራ ጳውሎስ በዚህ እንደተናገረው ሞተዋል፡፡ ሞት በሁሉ ላይ ነገሰ፡፡ ምንም እንኳ በህጉ የተጻፉትን ትዕዛዛት ባይጥሱም እነርሱ ኃጢአትን አድርገዋል፡፡ እነርሱ ምላሽ ያልሰጡት በተፈጥሮ የእግዚአብሔር መገለጥ ስላላቸው በደለኞች ናቸው፡፡ ‹‹ የማይታየው ባህሪይ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሰሩ ታውቆ ግልጽ ሆኖ ይታያል.. ስለዚህ ማመከኛ የላቸውም›› (ሮሜ 1፡20)

እግዚአብሄር ራሱን ሙሉ በሙሉ ‹‹በህጉ›› ላይ መግለጽ የፈለገው ለምንድነው? ሮሜ 5:20, 21::

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

አሥርቱ ትዕዛዛት ከዚያ በፊት የነበሩ ቢሆንም በሲና በተሰጠው መመሪያ እንደገና ተሰጥቷል፡፡ ቢሆንም እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ህግ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጽፎ የታወጀው በዚህ ስፍራ ነው፡፡

እስራኤላውያን ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ህግ ጋር ሲያስተያዩ፣ እነርሱ እጅግ ብዙ የሚጎድላቸው መሆኑን ተረዱ፡፡ በሌላ አነጋገር በደላቸው ብዙ ነው ማለት ነው፡፡ በፍጥነት የመተላለፋቸውን ብዛት ተረዱት፡፡ የዚህ መገለጥ ዋና ዓላማ አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸውና እግዚአብሔር በነጻ የሰጣቸውን ጸጋ እንዲቀበሉ ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ትኩረት ተሰጥቶት እንደነበር እውነተኛው የብሉይ ኪዳን እምነት በህግ ላይ የተመሰረተ አይደለም፡፡ ስህተትና እውነት በሰው አስተሳሰብ እንደዚህ ከሆነ፣ ዘላለማዊ የእግዚአብሄር ህግ እንዴት ይሆን ?

ጥቅምት 30
November 9

ኢየሱስ፡- ሁለተኛው አዳም

 

‹‹በአንዱም በደል በኩል ሞት ከነገሰ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ሥጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በህይወት ይነግሳሉ፡፡ እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ለሰው ሁሉ እንደመጣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ሥጦታው ህይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ፡፡ (ሮሜ 5፡17-18)፡፡ በዚህ ሥፍራ የቀረበልን ምን ዓይነት ማወዳደር ነው? በክርስቶስ የተሰጠን ምን ዓይነት ተስፋ ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እንደ ሰው ከአዳም የወረስነው ከሞት በቀር ምንም የለም፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ አዳም ባለፈበት መንገድ በመሄድ ፈተናውን ሁሉ በሰው ፋንታ ተቋቋመ፡፡ የእኛ ምትክ በመሆን የአዳምን ክብረ-ነክ የሆነውን ጥፋትና ውድቀት ነጻ በማውጣት እኛን ከእግዚአብሔር ጋር በነጻነት ሥፍራ እንድንቀመጥ አደረገን፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ‹‹ሁለተኛው አዳም ነው፡፡››

‹‹ሁለተኛው አዳም ለባህርዩ ኃላፊነት የሚወስድ የነጻ ግብረ-ገብ ተወካይ ነው ፡፡ እጅግ በተጠላለፈና በቀላሉ ለመለየት በሚያስቸግር ወደ ስህተት በሚመራ ተጽዕኖ የተከበበ ሆኖ ከመጀመርያው አዳም ይልቅ ኃጢአት አልባ ህይወት ለመምራት በማይመች ሁኔታ ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በኃጢአተኞች መካከል ሆኖ እያንዳንዱን ፈተና ተቋቁሞ እና ታማኝነቱንም ጠብቆ ኖረ፡፡ እርሱም ለዘላለም ኃጢአት አልባ ነበር፡፡ ” —Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1074.

በሮሜ 5 ፡ 15 - 19 የአዳምና የክርስቶስ ድርጊቶች የተወዳደሩት እንዴት ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

እነዚህን ተቃራኒ ነገሮች ተመልከቱ፡ ሞት፣ ህይወት ፤ መታዘዝ ፣ አለመታዘዝ፤ ኩነኔ፣ ቅድስና፤ ኃጢአት ጽድቅ፡፡ ክርስቶስ መጥቶ አዳም የሰራውን ሁሉ ቀለበሰው!

በሮሜ 5:15 -17 ድረስ ሥጦታ የሚል ቃል አምስት ጊዜ መጠቀሱ የሚገርም ነው፡፡ አምስት ጊዜ! ነጥቡ ግልጽ ነው፡፡ ጳውሎስ ትኩረት እየሰጠ ያለው ጽድቅ ለበጎ ተግባር የሚከፈል ዋጋ አለመሆኑን ሲሆን የሚገኘው በሥጦታ ነው፡፡ ይህም የተገባን ነገር አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ሥጦታ ደርሰን የምንቀበለውና የሚገባን የሚሆነውም በእምነት ነው፡፡

እስከዛሬ ካገኙት ሥጦታ ሁሉ የላቀ ሥጦታ ምንድነው? ይህንን ሥጦታ ጥሩና የተለየ የሚያደርገው ምንድነው? ሥጦታ መሆኑ ሰርተው ካገኙት የበለጠ እንዲያደንቁት የሚሆነው ለምንድነው? ሆኖም በክርስቶስ ያገኘነው ስጦታ ከዚህ ጋር የማይወዳደረው ለምንድነው?
 

ህዳር 1
November 10
 

ለተጨማሪ ጥናት፡-

 

የሚከተሉትን የኤሌን ዋይት መጻህፍት ያንብቡ፡፡ “Help in Daily Living,” pp. 470–472, in The Ministry of Healing; “Christ the Center of the Message,” pp. 383, 384, in Selected Messages, book 1; “The TemptatCtion and Fall,” pp. 60–62, in Patriarchs and Prophets; “Justification,” pp. 712–714, in The SDA Encyclopedia.

ብዙዎች ስለ ልባቸው ተሳስተዋል ፡፡ ተፈጥሮአዊው ልብ ከሁሉ በላይ አታላይና እጅግም ኃጢአተኛ መሆኑንም ዘንግተዋል፡፡ ማንነታቸውን በራሳቸው ጽድቅ በመሸፈን በሰው ዘንድ ተፈላጊውን የጽድቅ ባህርይ ደረጃ በመድረስ ረክተዋል፡፡” Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 320.

‹‹ ብቸኛው መድኃኒትና ተስፋ ክርስቶስ መሆኑን መስበክ በእጅጉ አንገብጋቢ ነው፡፡ ጽድቅ በሃይማኖት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀርብ ለተጠማ መንገደኛ እንደቀረበ ውኃ ነበር ፡፡ የክርስቶስ ጽደቅ ከእግዚአብሔር ነጻ ሥጦታ ሆኖ ተሰጠን የሚለው ሀሳብ በጣም ውድ ነበር፡፡›› —Page 360.

ሊመጣ ያለው ምሳሌ ማን ነው? (5፡14 ) አዳም የክርስቶስ ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? ምንም እንኳ የአዳም ዝርያዎች ከተከለከለው ዛፍ ባይበሉም፣ አዳም ለተከታዩ ትውልድ የሞት ምክንያት እንደሆነ ሁሉ፣ እንዲሁ የሰው ልጆች ምንም ጽድቅ ባይገባቸውም (ባይኖራቸውም) ክርስቶስ የራሱ ለሆኑት የጽድቅ ደራሲ በመሆን በመስቀሉ አማካይነት ለሰው ልጆች ሁሉ ጽድቅን ሰጣቸው፡፡ የአዳም የመተላለፍ ምሳሌ በእኛ ውስጥ በመኖሩ እርሱ እንደሞተ እኛም እንሞታለን፡፡ የክርስቶስ ምሳሌነትም በእኛ ውስጥ ነው፣ በመሆኑም ጽድቅን ሁሉ እንደፈጸምን በህይወት እንኖራለን ምክንያቱም እርሱ ፈጽሞታልና፡፡” —Martin Luther, Commentary on Romans, pp. 96, 97.
 

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. የሚከተለውን የኤሌን ዋይት ጥቅስ እንዴት ያስተውሉታል? ‹‹የእግአብሄርን ቃል በጣም በቅርበት ማጥናት ያስፈልጋል፤ በተለይም ዳንኤልና ራዕይ በታሪካችን ከነበረው ይልቅ ትኩረት ኣስፈልጓቸዋል፡፡ ስለ ሮም ጳጳስ እና ሥልጣኑ በአንዳንድ መስመሮች የምንለው ጥቂት ይሆናል ፣ ነገር ግን ሐዋሪያትና ነብያት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ወደ ጻፉት የሰዎችን ትኩረት መሳብ እንችላለን፡፡” —Ellen G. White, Evangelism, p. 577.

  2. ስለ ሞት ያለውን እውነታ ያስቡ፣ ህይወት ባይኖር ምን ትርጉም ይኖረው ነበር? ብዙ ጸሐፊዎችና ፈላስፋዎች ህይወት መጨረሻው በሞት የሚጠናቀቅ በመሆኑ እጅግ አልቅሰዋል፡፡ እኛ እንደ ክርስትያን ለእነዚህ ሰዎች ያለን ምላሽ ምንድነው? ለዚህ ትርጉም የለሽነት በክርስቶስ ያለን ተስፋ ብቸኛ መፍትሄ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

  3. ልክ የአዳም ውድቀት በሁላችንም ላይ የወደቀ ማንነት እንድንወርስ እንዳደረገ ፣ የክርስቶስም ድል ለሁላችንም በእምነት የሚሆን የዘላላም ህይወት ተስፋ እንዲኖረን አድርጓል፡፡ እንዲህ አስደናቂ የሆነ ሀብት በዚያ ስላለን ሰዎችን ወደዚህ እንዳይደርሱ እና በትጋት እንዳይከታተሉ ተስፋውን የራሳቸው እንዳያደርጉወደ ኋላ የሚጎትታቸው ምንድነው? ክርስቶስ ለእነርሱ ያደረገላቸውንና የሰጣቸውን ሥጦታ በተሻለ ደረጃ ሊያስተውሉ የሚፈልጉትን ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?