ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 14:9፣ ሶፎን. 3:17፣ ዮሐ. 1:1–3፣ ሮሜ 8:38-39፣ መዝ. 91:15-16፣ ራእ. 14:6-7፣ ኤፌ. 1:4-5፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ፍቅር ይህ ነው፤ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው ሳይሆን እርሱ እንደ ወደደንና ስለ ኃጢአታችን ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን መላኩ ነው፡፡” (1ዮሐ. 4፡10)፡፡
በክርስትና እና ከክርስትና ውጪ በሚገኙ እምነቶች መካከል አንድ
አስደናቂ--ደግሞም መሰረታዊ ልዩነት አለ፡፡ ከክርስትና ውጪ ያሉ ቤተ
እምነት ተከታዮች መሥራቾቻቸው ላስተማሯቸው ትምህርቶች እንጂ
ስላደረጉላቸው ነገር አጽንኦት አይሰጡም፡፡ ይህ የሆነው መሥራቾቻቸው
ምንም ቢያደርጉላቸው ሊያድናቸው ስለማይችል ነው፡፡ እነዚህ መሪዎች
ሊያደርጉ ይችሉ የነበረው ሕዝቡ እንዴት ራሱን ማዳን እንዳለበት ለማስተማር
መሞከር ብቻ ነበር፡፡
በተቃራኒው የክርስትና እምነት አጽንኦት የሚሰጠው የሱስ ስላስተማረው
ነገር ብቻ ሳይሆን ስላደረገውም ጭምር ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ክርስቶስ
ያደረገው ነገር ብቸኛው የመዳናችን መንስኤ በመሆኑ ነው፡፡ የክርስቶስ
ሰብዓዊውን ሥጋ መልበስ (ሮሜ 8፡3)፣ የመስቀል ላይ ሞቱ (ሮሜ 5፡8)፣
ትንሣኤው (1ጴጥ. 1፡3)፣ ሰማያዊ አገልግሎቱ (ዕብ. 7፡25)--እነዚህ ብቻቸውን
የመዳናችን መንስኤ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጪ ከእኛ ውስጥ አንዳችም የለም፡፡
“ከሰው ልጆች ወስጥ መልካም መልካሙ፣ ቅዱስ የሆነው፣ የከበረና የተወደ
የተባለው ማንኛውም ነገር በአንድ ላይ ተሰብስቦ ለሰብዓዊው ፍጡር መዳን
እንደ ድርሻ ይቆጠር ዘንድ ለእግዚአብሔር መላእክት ቢበረከት--እቅዱ
በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ እንደተደረገ ብርቱ ክህደት ተቆጥሮ ተቃውሞ
ይገጥመዋል፡፡”—Ellen G. White, Faith and Works, p. 24.
ይህ አስደናቂ እውነት በተለይ በአስጊ ሁናቴዎች እና ማታለያዎች ለተከበብነው
ለእኛ ለመጨረሻው ጊዜ ሕዝቦች በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
የሱስ በመስቀል ላይ መሥዋዕት ከመሆኑ ጥቂት ቀደም ባሉት ቀናት ሰዎች
እንዴት በእርሱ በኩል ወደ አብ እንደሚመጡ እጅግ ቅርቡ ከነበሩ ወገኖች ጋር
ይነጋገር ነበር፡፡ ታዲያ በመሃል ፊልጶስ “ ‘ጌታ ሆይ፤ አብን አሳየንና ይበቃናል’ ”
አለው (ዮሐ. 14፡8)፡፡
የሱስ ለፊልጶስ ምን ዓይነት ምላሽ ሰጠው? እርሱ የሰጠው መልስ ስለ አብ ምን
ያስተምረናል? የተዛባውን አመለካከትስ እንዴት ያጠራል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
አንዳንዶች ሲናገሩ እንደሚደመጠው--የብሉይ ኪዳኑ እግዚአብሔር የፍትሕና
ርትዕ አምላክ፡ የአዲስ ኪዳኑ ደግሞ የምህረት፣ የጸጋና የይቅርታ ጌታ ነው-ይላሉ ሁለቱን በማነጻጸር፡፡ ሆኖም በሁለቱ መጽሐፎች መካከል
የሚያስቀምጧቸው እነዚህ ልዩነቶች ህጋዊም ተገቢም አይደሉም፡፡
በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት የምናገኘው እግዚአብሔር
አንድ ዓይነት ባህሪ የተላበሰ ያው አምላክ ነው፡፡
ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣበት አንዱ ምክንያት የእግዚአብሔር አብን
እውነተኛ ማንነት ለመግለጥ ነበር፡፡ ለአያሌ መቶ ዓመታት ስለ እርሱ ብሎም
ስለ ባህሪው የተሳሳቱ ጽንሰ ሀሳቦች ሲነገሩና ሲሰራጩ ኖረዋል፡፡ ይህ የሆነው
እርሱን በማያውቁ አረማውያን ሳይሆን በራሳቸው በተመረጡ የእግዚአብሔር
ሕዝቦች ነበር፡፡ “ምድር እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ በማስተዋሏ
በድቅድቅ ጨለማ ተውጣ ነበር፡፡ ድቅድቁን ጨለማ ለመግፈፍ እና ዓለምን
ዳግመኛ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ--የሰይጣን አሳች ኃይል መሰበር
ነበረበት፡፡”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 22. የሱስ ወደዚህ
ምድር ከመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር፡፡
እግዚአብሔር አይለወጥም፡፡ የብሉይ ኪዳንን ነባራዊ እውነታዎች በሚገባ
ከተገነዘብን በመጻሕፍቱ ውስጥ የምናገኘውን በምህረት የተሞላ አምላክ
በአዲስ ኪዳንም እናገኘዋለን፡፡ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” (1ዮሐ. 4፡8) እርሱ
አይለወጥም፡፡ “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንት፣ ዛሬም ለዘላምም ያው ነው” (ዕብ.
13፡8)፡፡
በቀራኒዮ መሥቀል ላይ የተቸነከረው የብሉይ ኪዳኑ እግዚአብሔር
መሆኑን ጭምር ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡
ደግሞም ይህ አምላክ ቸር፣ ርኅሩኅ፣ ለቁጣ የዘገየ፣ ምሕረቱ የበዛ ነው
(መዝ. 145፡8)፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር የሚተማመኑትና እርግጠኛ ነው (መዝ.
143፡8)፣ በምሕረቱ በሚታመኑ ደስ ይለዋል (መዝ. 147፡11)፣ እግዚአብሔር
ፍጻሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ ዕቅድ አለው (ኤር. 29፡11)፡፡ በፍቅር
የተሞላው አምላክ ከሕዝቡ ጋር በዝማሬ ሐሴት ያደርጋል (ሶፎን. 3፡17)፡፡
እነዚህና አያሌ ሌሎች ጥቅሶች የእውነተኛውን አብ ማንነት ገልጠው ያሳያሉ፡፡
የሱስ ክርስቶስ አብን ስለ መወከሉ እውነታ ያስቡ፡፡ ይህ በተለይ
እግዚአብሔርን ለሚፈሩ አስደናቂና በተስፋ የሚሞላ እውነት መሆን የቻለው
ለምንድን ነው?
ኃጢአት ሰብዓዊውን ዘር ከእግዚአብሔር በመነጠሉ በሁለቱ መሀል ጥልቅ
ገደል ተፈጠረ፡፡ ይህ ገደል መዘጋት ካልቻለ በቀር ሰብዓዊነት ለዘላለም ተኮንኖ
የሚቀር ሆነ፡፡ ክፍተቱ ጥልቅና አደገኛ ነበር፡፡ ለኃጢአት ችግር መፍትሔ
አምጥቶ ኃጢአተኛውን ሰብዓዊ ፍጡር ከጻድቁ እና ቅዱሱ አምላክ ጋር ዳግም
ኅብረት እንዲፈጥር ለማድረግ እጅግ ለማመን የሚከብድ ተግባር ተጠየቀ፡፡
በመሆኑም ከራሱ እግዚአብሔር ጋር ዘላለማዊ የሆነውና መለኮታዊ ባህሪ
ያለው አምላክ ሰብዓዊ ፍጡር እንዲሆን በመጠየቁ--በዚያ ሰብዓዊነት ራሱን
ስለ ኃጢአታችን መሥዋዕት አድርጎ ሰጠ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡1-3፣ 14፣ ፊልጵ. 2፡5-8፡፡ ስለ የሱስ ማንነት
ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ክርስቶስ ዘላለማዊ አምላክ እንደመሆኑ ሕልውናው በማንም ወይም በምንም
ላይ ጥገኛ አይደለም፡፡ አምላክነቱ ውጪያዊና የታይታ ሳይሆን ነገር ግን እርሱ
ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ እርሱ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው መለኮታዊና
ዘላለማዊ ተፈጥሮ ባለቤት ነው፡፡ የሱስ ይህን መለኮታዊ ተፈጥሮ እንደያዘ
የሚኖር አምላክ ቢሆንም እርሱ ግን አምላካዊውን ሕግ በሰብዓዊው ሥጋ
ጠብቆ ሕጉን በጣሱት ምትክ ይኸውም ለእኛ ለሁላችን ለመሞት ሲል
ሰብዓዊውን ሥጋ ለበሰ (ሮሜ 3፡23) ፡፡
ክርስቶስ ከማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር የተለየ ልዩ ጥቅም ወይም ብልጫ
ሳይኖረው ሰብዓዊውን ሥጋ በእኩል ለበሰ፡፡ አምላካዊውን ሕግ መጠበቅ
የቻለው በዘላለማዊ መለኮታዊ ኃይሉ ሳይሆን ለማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር
ዝግጁ ለሆነው ውጪያዊ መለኮታዊ ኃይል በመታመን ነበር፡፡
የሱስ ፍጹም አምላክ እና ፍጹም ሰው ነበር፡፡ ይህ ማለት “በህያው ቃሉ
ሁሉን ደግፎ የያዘው” (ዕብ. 1፡3) እርሱ “በግርግም ተኝቶ የነበረው
ሕፃን” (ሉቃ. 2፡16) ነበር፡፡ ይህ ማለት “እርሱ ከሁሉ በፊት” የነበረውና
“ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ በእርሱ የጸናው” (ቆለ. 1፡17) እንዲሁም
“በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት” ያድግ የነበረው
ነው (ሉቃ. 2፡52)፡፡ ይህ ማለት “ከተፈጠረው ሁሉ ያለ እርሱ የተፈጠረ
ምንም የሌለ” (ዮሐ. 1፡3) እና “በእንጨት ላይ ተሰቅሎ የተገደለው” ነው (ሐዋ.
5፡30)፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚገልጽ ከሆነ-ክርስቶስ ለእኛ ያለው ፍቅር አብ ለእኛ ያለው ፍቅር መገለጫ እንደመሆኑ
ሐሴት የምናደርግባቸውና የምናመሰግንባቸው አያሌ ምክንያቶች መኖራቸው
ብዙም ሊያስገርም አይችልም፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 8፡38-39፡፡ በዛሬው ጥናታችን ያነበብነው ጳውሎስ
በዚህ ቦታ የጠቀሰውን እንድናምን ብርቱ ምክንያት ሊሰጠን የሚችለው
እንዴት ነው?
እግዚአብሔር አብ በስህተት የተስተዋለውን ያህል ለማለት በሚያስደፍር
መልኩ መንፈስ ቅዱስም በስህተት ተስተውሎአል፡፡ አንዳንድ የነገረ መለኮት
ምሑራን መንፈስን በአብ እና በወልድ መካከል እንዳለ ፍቅር አድርገው
ያስባሉ፡፡ በሌላ አነጋገር መንፈስ በአብ እና በወልድ መካከል የሚገኝ ፍቅር
ብቻ ነው፡፡ አባባሉ እርሱን ከሁለቱ የመለኮት ባህሪያት በማሳነስ ከሥላሴ
አካልነት ያወጣዋል፡፡
ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ የራሱ መለኮታዊ ባህሪ እንዳለው መጽሐፍ ቅዱስ
ይነግረናል፡፡ ክርስቲያኖች ከአብ እና ከወልድ በተጨማሪ በመንፈስ ስም
ተጠምቀዋል (ማቴ. 28፡19)፡፡ መንፈስ ክርስቶስን ያከብረዋል (ዮሐ. 16፡14)፡፡
መንፈስ ሰዎችን ይወቅሳል (ዮሐ. 16፡8)፡፡ ያዝናል (ኤፌ. 4፡30)፡፡ አጽናኝ ነው
(ዮሐ. 14፡16)፣ ረዳት፣ አማካሪ ነው፡፡ አስተማሪ ነው (ሉቃ. 12፡12)
ይማልድልናል (ሮሜ 8፡26)፡፡ ይቀድሰናል (1ጴጥ. 1፡2)፡፡ መንፈስ ሰውን ሁሉ
ወደ እውነት እንደሚመራ ክርስቶስ ተናግሯል (ዮሐ. 16፡13)፡፡
በአጭሩ መንፈስ ቅዱስ እንደ አብ እና ወልድ እርሱም እግዚአብሔር
ነው፡፡ እነዚህ ሦስቱ አንድ አምላክ ናቸው፡፡
መንፈስ ቅዱስ የሚያደርገው ነገር ሁሉ መለኮታዊውን ፍቅር ገልጦ ያሳያል፡፡
እርሱ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መሃል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ሉቃ. 12:12፣
ዮሐ. 16:8–13፣ ሐዋ. 13:2፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መንፈስ ቅዱስ መለኮታዊ ባህሪ ያለው እግዚአብሔር ለመሆኑ ከፍ ያለው
ማስረጃ የክርስቶስ ሥጋ መልበስ ነው፡፡ የሱስ የተወለደው በመንፈስ ቅዱስ
ነበር (ማቴ. 1፡20)፡፡ እግዚአብሔር ብቻ በዚያ መልኩ “መፍጠር” ይችላል፡፡
መንፈስ ቅዱስ ሁለት ተቃራኒ ታምራቶችን ለክርስቶስ ማድረግ ችሎአል፡፡
በመጀመሪያ በአንድ ጊዜ ሁሉም ስፍራ የመገኘት ችሎታ ያለውን ክርስቶስ ወደ
ማርያም ማህጸን አመጣው፡፡ ክርስቶስ በዚያ አካል ውስጥ ተወስኖ በሰብዓዊ
አካል ወደ ሰማይ አረገ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መንፈስ በሰብዓዊቱ የተገደበውን
ክርስቶስ በማምጣት በሌላ ምስጢራዊ ታምራት በአለም ዙሪያ በሚገኙ
ክርስቲያኖች ፊት እንዲገኝ ያደርገዋል፡፡
መንፈስ ቅዱስ በዚህ መልኩ ከአብ እና ከወልድ ጋር ስለ እኛ በመሥራት
ላይ ይገኛል፡፡ “እግዚአብሔር ስለ ሰብዓዊው ዘር ክፉኛ በማዘኑ አብ፣ ወልድ
እና መንፈስ ቅዱስ ዘላለማዊውን የደኅንነት ዕቅድ አወጡ፡፡””—Ellen G.
White, Counsels on Health, p. 222
እኛን በእኩል የሚወዱን--አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ የደኅንነት
ባለቤትና የእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ወራሾች እንድንሆን በመሥራት
ላይ ይገኛሉ፡፡ እንግዲያውስ ይህን ታላቅ መዳን እንዴት ችላ ማለት እንችላለን?
አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ስለ እኛ ዘላለማዊ በጎነት በሥራ ላይ
የመጠመዳቸው እውነታ ምን ያህል መጽናናት ሊሰጠን ይገባል?
አንዳንድ አድቬንቲስቶች ስለ መዳናቸው ገና እርግጠኞች አይደሉም፡፡
መዳናቸውን ማረጋገጥ ስለሚቸገሩ በዘላለማዊው ህይወት ዙሪያ
መጨረሻቸውን ለማወቅ ይመኛሉ፡፡ መልካም ለመሆን አብልጠው ቢደክሙም
ይህ የትም እንደማያደርስ ያውቃሉ፡፡ ወደ ውስጣቸው ይመለከቱና ለሕይወት
ጉዞአቸው ጥቂት የሚያበረታታቸው ነገር ያገኛሉ፡፡
በየሱስ ጸባይና በራሳችን መሃል ያለውን ግዙፍ ክፍተት ስንመለከት ወይም
“ወደ ሕይወት የሚያደርሰው ግን መንገዱ ቀጭን፣ በሩም ጠባብ ነው፤
የሚገቡበትም ጥቂቶች ብቻ ናቸው” (ማቴ. 7፡14) የሚለውን ስናነብ--እንዴት
ነው ነገሩ ጎበዝ የሚል አግራሞት ያልያዘው ማነው?
ሰዎች ለመጨረሻው ጊዜ መዘጋጀት እንዲችሉ ዛሬ ለመዳናቸው ዋስትና
ሊኖራቸው ይገባል፡፡ የወደፊቱን ሳይፈሩ በልበ ሙሉነት መጋፈጥ ይችሉ ዘንድ
ተጨባጭ በሆነው ደኅንነት ሐሴት ማድረጋቸው የግድ ይሆናል፡፡ ቀደም ብለን
እንደተመለከትነው እግዚአብሔር አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ እኛን
ለማዳን በሥራ ላይ ናቸው፡፡ በዚህ የተነሳ በመዳናችን እርግጠኞች ሆነን
መመላለስ እንችላን፡፡
ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ከደኅንነትና እግዚአብሔር
ከሰጠን ተስፋ አኳያ ከጥቅሶቹ ምን ዓይነት ተስፋና ዋስትና እናገኛለን?
መዝ. 91:15-16____________________________________________________________________
ኢዮኤ. 2:31-32___________________________________________________________________
ዮሐ. 10:28________________________________________________________________________
ሮሜ 10:9–13_____________________________________________________________________
1ዮሐ. 5:11–13_____________________________________________________________________
የተቀደሰ ህይወት እንድንኖር ተጠርተናል--ታዘንማል፡፡ ሆኖም ይህ
የተቀደሰ ህይወት በክርስቶስ የመዳናችን ውጤት እንጂ የዚያ ደኅንነት ባለቤት
የመሆን ምክንያት አይደለም፡፡ እስከ ሞት መታመን ቢኖርብንም፤ ሁሌም
ቢሆን የደኅንነትን ስጦታ እንደ ብቸኛው ተስፋችን ልንደገፍ የግድ ይሆናል፡፡
የእግዚአብሔር ሕዝቦች በመጨረሻው ዘመን ታማኞችና ጌታን የሚታዘዙ
ሆነው ይገኛሉ፡፡ የዚህ ታማኝነታቸውና ታዛዥነታቸው መንስኤ ክርስቶስ
ለእነርሱ ያደረገው ነገር ነው፡፡
በራእ. 14፡6-7 የቀረበው “የዘላለም ወንጌል” ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በዚህ ቦታ ወንጌል “የዘላለም” በሚል ተጠቅሶአል፡፡ አባባሉ እግዚአብሔር
የማይለወጥ አምላክ የመሆኑ ተጨማሪ መስረጃ ነው፡፡ የማይለወጠው አምላክ
የማይለወጥ ወንጌል ባለቤት ነው፡፡ ይህ የዘላለም ወንጌል ሊቀበሉት ፈቃደኞች
ለሆኑ ሁሉ ዋስትና ይሰጣል፡፡ ወንጌል የማይለወጠውን የእግዚአብሔር ፍቅር
ገልጦ የሚያሳየን እንደመሆኑ፤ ይኸው መልእክት ወደ ዓለም ሊሄድ የተገባ
ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ይህን ወንጌል የመስማት ዕድል ሊያገኝ ስለሚገባ
የእግዚአብሔር ሕዝብ ይህን ለዓለም እንዲያደርስ ተጠርቶአል፡፡
“በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ
በእርሱ መርጦናልና፡፡ በፍቅር፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ልጆቹ እንሆን ዘንድ፣ እንደ
በጎ ፈቃዱ አስቀድሞ ወሰነን” (ኤፌ. 1፡4-5)፡፡ ወንጌል በእርግጥ እንዴት
“ዘላለማዊ” እንደሆነ አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
“ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእርሱ መርጦናል” የሚለው ሃረግ ስለ
“ዘላለማዊ” ወንጌል ይናገራል! ገና ይህ ምድር ከመፈጠሩ አስቀድሞ፤ በእርሱ
የደኅንነት ባለቤቶች እንሆን ዘንድ የእግዚአብሔር እቅድ ነው፡፡
በጥቅሶቹ የቀረቡትን አንዳንድ ቃላት እንመልከት፡ “መርጦናል” ፣ “እንደ
በጎ ፈቃዱ”፣ “ልጆቹ እንሆን ዘንድ”…፡፡ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ያደረገው
ለዘላለም የመሆኑ (2ተሰ. 2፡13፣ 2ጢሞቴ. 1፡9) እውነታ በግልጽ ወደ ጸጋው
ያመላክተናል፡፡ ይኸውም የደኅንነት ባለቤቶች የሆንነው ከበጎ ተግባራችን
ወይም ከመልካም ፍጥረትነታችን ሳይሆን ከእግዚአብሔር በመነጨና የእርሱ
ብቻ ከሆነ የፍቅር ባህሪ ነው፡፡ ገና ከመፈጠራችን አስቀድሞ በእርሱ የዚያ
ደኅንነት ባለቤቶች እንድንሆን ከተመረጥን--ማንኛውም ልናደርግ የምንችለው
ነገር ለመዳናችን እንዴት መንስዔ መሆን ይችላል? መዳንን ለመቀበል ወይም
ለመቃወም ምርጫው የገዛ ራሳችን ነው!
ለመሆኑ ይህ መመረጥ በተመራጩ ግለሰብ ህይወት የሚታየው እንዴት
ነው? “በፊቱ ቅዱሳንና ነውር አልባ እንድንሆን” (ኤፌ. 1፡4)፡፡ እንግዲህ
የተመረጥነው ለዚህም ነው…፡፡
ስለ መዳናችን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፡፡ ሆኖም ከልክ ያለፈ መመጻደቅ ውስጥ መግባት ግን የለብንም፡፡ ለመሆኑ የተሳሳተ የደኅንነት ማረጋገጫ የሚባል ነገር አለ? በእርግጥ አለ፡፡ የሱስም ቢሆን በዚህ ዙሪያ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶአል “በሰማይ ያለውን የአባቴን ፈቃድ ሳይፈጽም ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ’ የሚለኝ ሁሉ ወደ መንግሥተ ሰማይ አይገባም፡፡ በዚያ ቀን ብዙዎች ‘ጌታ ሆይ፤ ጌታ ሆይ፤ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን? በስምህ አጋንንት አላወጣንምን? በስምህስ ብዙ ታምራት አላደረግንምን?’ ይሉኛል፡፡ በዚያ ጊዜ፤ ‘ከቶ አላውቃችሁም፤ እናንት ክፉዎች፤ ከእኔ ራቁ’ ብዬ በግልጽ እነግራቸዋለሁ!” (ማቴ. 7፡21-23)፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ሁለት ብርቱ ስህተቶች ሠርተዋል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ-የቱንም ዓይነት ታላቅ ሥራ በጌታ ስም ቢሠሩም የጌታን ፈቃድ ይኸውም ሕጉን እየታዘዙ አልነበረም፡፡ የሱስ “ከእኔ ራቁ” እናንት “ኃጢአት ያልሠራችሁ” አላለም ወይም “ያለ ነቀፋ” የተመላለሳችሁ ወይም ደግሞ “ፍጹም ያልሆናችሁ” አላለም፡፡ ይልቁንም እነዚህን ሕዝቦች የገለጻቸው “ክፉዎች” ወይም “ሕገ ጠሎች” በሚል ቃል ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ--ስለ ራሳቸውና ስለሠሯቸው ነገሮች የሚሰጡትን አጽንኦት ልብ ይበሉ፡ ይህን በስምህ አላደረግንም? ወይም ያንን በስምህ አላደረግንም? ራሳቸውን በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ አድርገው ለማቅረብ ምን ያህል ከክርስቶስ ርቀው ሄደዋል? እኛን የሚያድኑ ብቸኛ ሥራዎች የክርስቶስ ሲሆኑ፤ እነርሱም በእምነት ለእኛ ተቆጥረዋል፡፡ ዋስትናችን የራሳችን ማንነት ወይም ሥራችን ሳይሆን ክርስቶስ ለእኛ ያደረገው ነገር ብቻ ነው፡፡ ለመዳንዎ ዋስትና ይፈልጋሉ? እንግዲያውስ የእግዚአብሔርን ሕግ ይጠብቁና በክርስቶስ የጽድቅ ሥራ ብቻ ይረፉ፡፡ ያን ጊዜ የሚያስፈልጎትን ማረጋገጫ ያገኛሉ፡፡ የመወያያ ጥያቄዎች፡ 1.ታዋቂው የክርስትና ተሐድሶ አራማጅ ማርቲን ሉተር እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ወደ ራሴ ስመለከት እንዴት መዳን እንደምችል አላውቅም፡፡ ወደ የሱስ ስመለከት ደግሞ እንዴት መጥፋት እንደምችል አላውቅም፡፡” በእነዚህ ቃላት ውስጥ እንዴት ዓይነት ታላቅ ጥበብ አለ? ይህን ስሜት ሁሌም ከፊታችን ማኖር መልካም ሀሳብ የሚሆነው ለምንድን ነው? 2.ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በመመረጣችን ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ተወያዩ፡፡ አባባሉ እያንዳንዱ ሰው ይድናል የሚል አንደምታ ያልኖረው ለምንድን ነው? ሰዎች ሳይድኑ የሚቀሩት እግዚአብሔር ስላልመረጣቸው ነው ወይስ እነሱ ስላልመረጡት? ጥያቄዎቹን በክፍል ተወያዩ፡፡ 3.የታላቁ ተቃርኖ ትዕይንት አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ በሚወዱት ዓለም የክፉውን በተጨባጭ መከሰት በተሻለ ማስተዋል እንድንችል የሚረዳን እንዴት ነው?