ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሮሜ 8:1፣ 7:15–25፣ ሮሜ 7:1–14፣ ዮሐ. 20:19–23፣ ሐዋ. 20:6-7፣ ዳን. 7:23–25፣ ራእ. 13:1–17፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “በልዑል ላይ የዐመፅ ቃል ይናገራል፤ የልዑልንም ቅዱሳን ያስጨንቃል፤ ለበዓላት የተመደበውን ጊዜና ሕግን ለመለወጥ ይሞክራል፤ ቅዱሳንም ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም ለእርሱ ዐልፈው ይሰጣሉ” (ዳን. 7፡25)፡፡
የመጨረሻውን ጊዜ ክስተቶች ለመረዳት ዋናውና ማዕከላዊው ክፍል
በእግዚአብሔር ሕግ ዙሪያ የሚነሳው ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ
ጠለቅ ብለን ስንመለከተው በአራተኛው ትእዛዝ ማለትም በሰባተኛው
ቀን ሰንበት ላይ የሚነሳ ጥያቄ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ምንም እንኳ መዳን
የሚገኘው በእምነት ብቻ መሆኑን ብናስተውልም፤ ሰንበትን ጨምሮ ሕጉን
መጠበቅ ደኅንነት ሊያስገኝ እንደማይችል ብንረዳም፤ ነገር ግን በመጨረሻው
ጊዜ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ጨምሮ የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዛችን
የእውነተኛ ታማኝነታችን ውጪያዊ ምልክት መሆኑን እናውቃለን፡፡
ይህ ልዩነት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ የሚመጣው በተለይ በራእ 13 እና 14
በተገለጹት የመጨረሻው ጊዜ ክስተቶች መሀል ሲሆን ይኸውም የፖለቲካና
የኃይማኖት ኃያላን፤ በምድር ሕዝቦች ላይ ሐሰተኛ አምልኮ እንዲተገበር
የሚያስገድድ ኅብረት በሚፈጥሩበት ወቅት ነው፡፡ እነዚህ አካሄዶች “ሰማይንና
ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” (ራእ. 14፡7) ከሚለው
የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከተጠሩበት ፈጣሪን ከማምለክ ጋር የሚቃረኑ
ናቸው፡፡
በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን በእግዚአብሔር ሕግ፤ በተለይ
ሰንበት ላይ ትኩረት በማድረግ ይህ ሕግ የከበበውን ሁኔታና ለመለወጥ
የተደረጉ ሙከራዎችን እንዳስሳለን፡፡ መጨረሻው እየተቃረበ በመጣ ቁጥር
ሰንበት ለእኛ የሚኖረውን አንደምታም እንዲሁ እንፈትሻለን፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው ታላላቅ ተስፋዎች አንዱ ሮሜ 8፡1-2 ነው፡
“ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም፤ ምክንያቱም
የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ
አውጥቶአችኋል፡፡” እነዚህ ቃላት እንደ ባቡር ፉርጎ ተቀጣጥለው ለመጡ
ሀሳቦች እንደ አክሊል ወይም መደምደሚያ ናቸው፡፡ ጳውሎስ ቀደም ሲል
ያነሳቸውን ከእነዚህ ቁጥሮች ኋላ ያሉትን ሀሳቦች በማጥናት በውስጣቸው
የያዙትን ተስፋዎች በተሻለ መጨበጥ እንችላለን፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 7፡15-25፡፡ ሐዋርያው በሮሜ 8፡1-2 የተናገረውን
የሚያረጋግጥልን የዚህ መልእክቱ መሰረታዊ ነጥብ ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ምንም እንኳ በጳውሎስ መልእክቶች ዙሪያ በተለይም እንደ አንድ አማኝ
ስለ ራሱ በጻፋቸው መልእክቶች በክርስትናው ዓለም ከፍ ያሉ ሙግቶች
ቢነሱም አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፡ በእርግጥ ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ስለ
ኃጢአት ተጨባጭ ሁኔታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው፣ ክርስቲያኖችም ቢሆኑ
ጳውሎስ ከጠቀሰው ትግል ጋር በተመሳሳይ ራሳቸውን ሊያገኙ ይችላሉ፡፡
የሥጋ ፈቃድ ዝንባሌ እና በውስጥ “የሚኖረው ኃጢአት” ማድረግ የሌለበትን
እንዲያደርግ ያልገፋፋው ወይም ማድረግ እንደሌለበት እያወቀ ያላደረገ ማን
ነው? ለጳውሎስ ችግሩ ያለው ሕጉ ላይ ሳይሆን የሥጋው ፈቃድ ላይ ነው፡፡
ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እየፈለገ ነገር ግን የተሳሳተውን እያደረገ ራሱን
ያላገኘ ማን አለ? ጳውሎስ ዳግም በተወለደው ክርስቲያን ሕይወት የኃጢአትን
አይቀሬነት ባያወራ እንኳ እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ብርቱ ምኞት ያለው ሁሉ
ሰርክ ስለሚጋፈጠው ትግል ብርቱ ማሳያ አቅርቦአል፡፡
ጳውሎስ እንዲህ ሲል ዝነኛውን መልእክት ያቀርባል “እኔ ምን ዓይነት
ጎስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል?” (ሮሜ.
7:24)፡፡ ለጥያቄው መልስ ያገኘው በየሱስ ሲሆን ይኸውም በየሱስ የሚያምኑና
እንደ መንፈስ ፈቃድ በጸጋው የሚመላለሱ “ኩነኔ የለባቸውም” የሚል ነው፡፡
አዎ--አማኞች ሁሌም ትግል ውስጥ እንደመሆናቸው ይፈተናሉ፣ ኃጢአትም
ይሠራሉ፡፡ ነገር ግን አማኞች በየሱስ ላይ በሚኖራቸው እምነት በሕጉ ኩነኔ
የለባቸውም፡፡ በእርግጥ የመታዘዝ ሕይወት ግን ይኖራሉ፡፡ በዚህ የተነሳ
“በሥጋ ፈቃድ” ሳይሆን በመንፈስ መመላለስ ይማራሉ፡፡
በዛሬ ጥናታችን የተመለከትናቸውን ጥቅሶች መልሰው ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ
እየተናገረ ካለው ነገር ጋር ራስዎን እንዴት ያዛምዱታል? ሮሜ 8፡1-2 አስደናቂ
ተስፋ የሆነው ለምንድን ነው?
በትናንቱ ጥናታችን ክርስቲያኖችን ጨምሮ ሁሉም ሰው ኃጢአት የመሥራቱን
እውነታ በሮሜ 7፡15-25 ተመልክተን ነበር፡፡ ሆኖም ጳውሎስ ከእነዚህ ቁጥሮች
ቀደም ባሉት መልእክቱ ኃጢአት ምን ያህል ተስፋፊና ገዳይ መሆኑን ወደ ሕጉ
በማመላከት ያሳየናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 7፡1-14፡፡ በሕጉ እና በኃጢአት መካከል ያለው
ግንኙነት ምንድን ነው? በሕጉ አማካይነት መዳን የማይቻል ስለ መሆኑ
በተጨማሪ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጳውሎስ በዚህ ስፍራ ከሚያስተምረው ትምህርት ሁለት ወሳኝ ነጥቦች ነጥረው
ይወጣሉ፡፡ በመጀመሪያ ሕጉ ችግር አለመሆኑን ያሳየናል፡፡ ሕጉ “ቅዱስ፣
ጻድቅና መልካም ነው”፡፡ ስለዚህ ችግሩ ያለው ወደ ሞት የሚመራው ኃጢአት
ላይ ነው፡፡ ሌላው ነጥብ ሕጉ እኛን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን ኃይል የሌለው
መሆኑ ነው፡፡ ሕጉ የኃጢአትንና የሞትን ችግር ነቅሶ በማውጣት ይበልጥ ግልጽ
አድርጎ ከማቅረብ ውጪ ለችግሩ መወገጃ የሚያቀርበው አንዳችም መፍትሔ
የለም፡፡
ይህን መልእክት በጥልቀት ሳይሆን ላይ ላዩን የሚያነብ ብቻ ከእነዚህ
ጥቅሶች ተነስቶ ሕጉ ማለትም አስሩ ትእዛዛት ተሽረዋል የሚል ሙግት ሊያነሳ
ይችላል፡፡ ሕጉ ዛሬም ጸንቶ መኖሩን የሚያመላክቱ አያሌ ጥቅሶችን ችላ
በማለት ይህ ሲፈጸም ይስተዋላል፡፡ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ጳውሎስ ካነሳው
ነጥብ ፍጹም ተቃራኒ ነው፡፡ ሕጉ ተሽሮ ቢሆን ኖሩ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ
ትርጉም ያለው ነገር ባልጻፈ ነበር፡፡ የእርሱ መሟገቻ ነጥብ ሕጉ ዛሬ ድረስ
እንደ ጸና በመኖሩ ምክንያት ኃጢአትን በተጨባጭ እያሳየን ነው፤ በውጤቱም
የወንጌልን አስፈላጊነት እንገነዘባለን “እንግዲህ ምን እንላለን? ሕግ በራሱ
ኃጢአት ነውን? በፍጹም አይደለም፤ ነገር ግን በሕግ በኩል ባይሆን ኖሮ፣
ኃጢአት ምን እንደ ሆነ ባላወቅሁም ነበር፤ ሕጉ ‘አትመኝ’ ባይል ኖሮ፣ ምኞት
ምን እንደ ሆነ በእርግጥ አላውቅም ነበር” (ሮሜ 7፡7)፡፡
ጥቅሱን በጥንቃቄ ያንብቡ፡ ሮሜ 7፡13፡፡ ጳውሎስ ስለ ሕጉ ብቻ ሳይሆን
ነገር ግን ዛሬም አስፈላጊ ስለመሆኑ ምን እያለ ነው?
ሞት የሚያስከትለው ሕጉ ሳይሆን ኃጢአት ነው፡፡ ኃጢአት ምን ያህል
ገዳይ እንደሆነ የሚያሳየን ሕጉ ነው፡፡ ሕጉ መልካም በመሆኑ ወደ ኃጢአት
ያመላክታል፡፡ ከዚህ ውጪ ከወንጌል በቀር ሕጉ ለኃጢአት መልስ የለውም፡፡
የጳውሎስ መልእክት--እንደ ክርስቲያን፣ በክርስቶስ እንደ ዳኑ ሕዝቦች “አዲስ
በሆነው በመንፈስ መንገድ” (ሮሜ 7፡6) ልናገለግል ይገባል--የሚል ነው፡፡
አባባሉ ከየሱስ ጋር በእምነት ግንኙነት እየተመላለስን እርሱ ለእኛ በሠራው
የጽድቅ ሥራና ባስገኘልን ደኅንነት እንታመን የሚል አንደምታ አለው፡፡
ሕጉን የመጠበቅ የግል ተሞክሮዎ አምላካዊው ጸጋ እንደሚያስፈልግዎ
ያሳዮት እንዴት ነው?
እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን በሌሎች የክርስትና ተቋም የሚገኙ
ወንድምና እህቶች የሕጉ ጉዳይ እንዳበቃለት ሲናገሩ ወይም ከጸጋ በታች እንጂ
ከሕግ በታች አይደለንም የሚል የክርክር ሃሳብ ሲያነሱ እንሰማለን፡፡ በእርግጥ
በትክክል እያሉ ያሉት--አራተኛው ትእዛዝ ብቻ ተወግዶአል ነው፡፡ እንዲያውም
ብዙዎች የሚሉት እንዲህ ሳይሆን--ለየሱስ ትንሳኤ ክብር ለመስጠት ሲባል
ሰባተኛው ቀን ሰንበት የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በሆነው እሁድ ተተክቶአል
ነው፡፡
ይህን አባባላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንደሚደግፉም ያስባሉ፡፡
ብዙ ክርስቲያኖች ሰንበት ከብሉይ ኪዳኑ ሰባተኛ ቀን ወደ አዲስ ኪዳን
የመጀመሪያው ቀን ለመለወጡ አመለካች ናቸው ብለው የሚያምኑባቸው ጥቂት
የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ከዚህ በታች ቀርበዋል፡፡ ጥቅሶቹን ስናነብ በእውነት ስለ
ቀን መለወጥ የሚናገሩ መሆናቸውን ወይም የቀን ለውጥ ደረጃ ላይ ሳይደርሱ
በዚያ ቀን ገቢራዊ የሆኑ ክስተቶችን ብቻ እየገለጡ እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ
ያስፈልገናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 20፡19-23፡፡ ደቀ መዛሙርቱ በዚያ ክፍል ውስጥ
ለተሰባሰቡበት የቀረበው ምክንያት ምን ነበር? አንዳንዶች እንደሚሉት የየሱስን
ዕርገት ለመዘከር የተደረገ የአምልኮ አገልግሎት ስለመሆኑ እነዚህ ጥቅሶች ምን
ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 20፡ 6-7፡፡ ሰንበት ከቅዳሜ ወደ ሣምንቱ የመጀመሪያ
ቀን እሁድ ስለ መለወጡ የሚያሳይ አንዳች ነገር አለ? ሐዋ. 2፡46፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 16፡1-4፡፡ በሣምንቱ መጀመሪያ ላይ በየቤቱ ይደረግ
የነበረው የገንዘብ ማሰባሰብ መርኀ ግብር ሰንበት ወደ እሁድ ቀን ለመቀየሩ
ምን የሚያስተምረው ነገር አለ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የሣምንቱ የመጀመሪያው ቀን ሰባተኛውን ቀን ሰንበት የመተካቱን ኃይማኖታዊ
አስተምህሮ ለማበረታታትና ለማዳበር ጥቅም ላይ የዋለው ዋንኛው የጥቅስ
“ማስረጃ” ይዘት ይኸው ነው፡፡ አማኞች ለጥቂት ጊዜያት በተለያዩ ምክንያቶች
መገናኘታቸው ከመገለጹ ውጪ ይህ መሰባሰባቸው ሰባተኛውን ቀን ሰንበት
በመተካት በሣምንቱ መጀመሪያ ቀን የተደረገ የአምልኮ አገልግሎት መሆኑን
አንድ እንኳ ጥቅስ አያመለክትም፡፡ እነዚህን ጥቅሶች በመከራከሪያ ነጥብነት
የሚያቀርበውና ገና ከመጀመሪያው ፈጽሞ ያልነበረውን ሀሳብ በጥቅሶቹ ውስጥ
ያኖረው የእሁድ አምልኮ ልማድና ወግ፤ በክርስትናው ዓለም አያሌ መቶ
ዓመታት አስቆጥሮአል፡፡
በትናንቱ ጥናታችን እንደ ተመለከትነው እሁድ በቅዳሜ ሰንበት የመተካቱን
ጽንሰ ሃሳብ ለማራመድ በተለምዶ ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ ጥቅሶች
እንደሚባለው አይናገሩም፡፡ ይልቁንም በአዲስ ኪዳን ስለ ሰባተኛው ቀን
ሰንበት የሚቀርቡ ማስረጃዎች ከእግዚአብሔር አስርቱ ትእዛዛት እንደ አንዱ
ይጠበቅ እንደ ነበር ይፋ ያደርጉልናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 4:14–16፣ 23:55-56፡፡ ከክርስቶስ ሞት በፊትም ሆነ
በኋላ ስለ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ምን ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ከገሊላ ጀምሮ የመጡት ሴቶች “ሕጉ በሚያዘው መሰረት በሰንበት ቀን
ዐረፉ” (ሉቃ. 23፡56) የሚለውን ጥቅስ ልብ ይበሉ፡፡ በእርግጥ ይህ ሕግ በሲና
ተራራ ተጽፎ የተሰጠው አራተኛው ትእዛዝ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡
ደቀ መዛሙርቱ ከየሱስ ጋር በነበሩባቸው ጊዜያቶች የቱንም ዓይነት ትምህርት
ቢማሩ ሰንበትን ጨምሮ የእግዚአብሔርን ሕግ ከመጠበቅ ውጪ የቀሰሙትን
የሚጠቁም ነገር የለም፡፡ እንደውም ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ያላቸው
“‘ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ’ ” (ዮሐ. 14፡15) ነበር፡፡ እርሱ ራሱ የጠበቃቸው
የራሱ ትእዛዛት ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ያካተቱ ነበሩ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 13:14፣ 42–44፣ ሐዋ. 16:12- 13፡፡ ሰባተኛውን ቀን
ሰንበት ስለ መጠበቅ ምን ዓይነት ማስረጃ ይሰጣሉ? የሣምንቱን የመጀመሪያ
ቀን ስለ መጠበቅ የሚሰጡት ማስረጃስ ምንድን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የሰንበት ቀን ወደ እሁድ ስለ መቀየሩ ምንም ዓይነት ማስረጃ በጥቅሶቹ ተሰጥቶ
አናገኝም፡፡ ይልቁንም ሰባተኛውን ቀን ሰንበት መጠበቅ በመጀመሪያዎቹ የየሱስ
አማኞች መሃል ይተገበር እንደ ነበር በግልጽ ያመለክተናል፡፡
በተለይ ሐዋ. 16፡ 13 የቀረበው መልእክት ከተለመደው የቤተ ክርስቲያን
ጉባዔ ዐውድ ወጣ ያለ በመሆኑ መሳጭ ነው፡፡ አማኞች በአንድ ወንዝ ዳር
ተሰባስበው እንደ ልማዳቸው አምልኮ ያደርጉ ነበር፡፡ ከየሱስ ሞት እና ትንሣዔ
አያሌ ዓመታት በኋላም እንኳ በሰባተኛው ቀን ሰንበት ለአምልኮ ይሰባሰቡ
ነበር፡፡ በአምልኮ ቀን ላይ ለውጥ ለመደረጉ በእነዚህ ጥቅሶች የሚያመላክት
አንዳችም ነገር የለም፡፡
እሁድን እንደ ሰንበት በመቁጠር በዕለቱ አምልኮ የሚያደርጉትን በማይኮንን
መንገድ ስለ ሰባተኛው ቀን ሰንበት መመስከር የሚችሉባቸው መንገዶች
የትኞቹ ናቸው?
የእግዚአብሔር ሕግ የሆኑት አስርቱ ትእዛዛት ዛሬ ድረስ ጸንተው ያሉ ሲሆን
(ያዕ. 2፡10-12) ሰባተኛው ቀን ሰንበት ደግሞ የዚህ ሕግ አካል ነው፡፡ ታዲያ
ብዙ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ የሌለውን እሁድ ቀን የሚጠብቁት
ለምንድን ነው?
ዳን. ምዕ. 7 ስለ አራቱ የዓለም ልዕለ ኃያላን መንግሥታት መነሳት
ይናገራል፡፡ ባቢሎን፣ ሜዶንና ፋርስ፣ ግሪክ እንዲሁም በመጨረሻ ሮም፡፡
በሮም መንግሥት መጨረሻ አካባቢ አንድ ትንሽ ቀንድ (ኃይል) ከዚህ ልዕለ
ኃያል መንግሥት ውስጥ ሲወጣ ተገልጾአል (ዳን. 7፡8)፡፡ ይህ ቀንድ የሮም
መንግሥት ቀጣይ ምዕራፍ አካል በመሆን ዛሬ ድረስ አለ፡፡ በቀጥታ ከሮም
የሚወጣው ኃይል ጳጳሳዊው ሥርዓት ከመሆን ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?
ቶማስ ሆብስ ከአራት መቶ ዓመታት በፊት ማለትም በሺ ስድስት መቶዎቹ
አካባቢ የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡ “አንድ ሰው የዚህን ታላቅ የቤተ ክርስቲያን
ተቋም አመጣጥ ለመመርመር ቢሞክር፤ ጳጳሳዊው ሥርዓት የዓለም ልዕለ ኃያል
የነበረውና ግብአተ መሬቱ የተፈጸመው፣ የሮም መንግሥት መቃብር ላይ
አክሊል የጫነ ቅሪተ አካል መሆኑን በቀላሉ መገንዘብ ይችላል፡፡”—Thomas
Hobbes, Leviathan, (Oxford: Oxford University Press, 1996), p. 463.
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 7፡23-25፡፡ የእሁድን ቀን አምልኮ መሰረታዊ አመጣጥ
ማስተዋል እንችል ዘንድ ምን ያስተምሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የቀደመው አረማይክ ቋንቋ የትንሹ ቀንድ ኃይል ጊዜና ሕግን ለመለወጥ
“ያቅዳል” ቁ. 25 ሲል ይጠቁማል፡፡ ለመሆኑ የእግዚአብሔርን ሕግ መለወጥ
የሚችለው እንዴት ያለ ምድራዊ ኃይል ነው?
ምንም እንኳ ከረጅሙ የታሪክ ሂደት አኳያ እያንዳንዱ ነጥብ በጉልህ
መታየት ባይችልም ነገር ግን በሮም ጳጳሳዊው ሥርዓት ትእዛዝ ሰባተኛው ቀን
ሰንበት በባህላዊው የእሁድ አምልኮ መተካቱን እናውቃለን፡፡ ይህ ባህላዊ
ወግና ልማድ ሥር የሰደደ ከመሆኑ የተነሳ የፕሮቴስታንት ተሐድሶም እስከ ሃያ
አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጠብቆ አኑሮታል፡፡ ዛሬ አብዛኛው ሕዝበ
ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰባተኛው ቀን የሚያዘውን በመከተል ፋንታ
ዛሬም እሁድን እየጠበቀ ይገኛል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡1-17 እና ከሚከተሉት ጋር ያስተያዩ፡ ዳን.7፡1-8፣
21፣ 24-25፡፡ የመጨረሻውን ጊዜ ክስተቶች ለማስተዋል የሚረዱን ምን ዓይነት
ተመሳሳይነት ያላቸው ምስላዊ አቀራረቦች ጥቅም ላይ ውለዋል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የራእይ መጽሐፍ የሮምን ቀጣይ ምዕራፍ (ጳጳሳዊውን ሥርዓት) ያካተተውን
የዳንኤልን ምስላዊ አቀራረብ በቀጥታ ጥቅም ላይ በማዋል በመጨረሻው ጊዜ
የአስገዳጁን ኃይል “አምልኮ” በሚቃወሙ ላይ የሚደርሰውን ስደት
ያመላክታል፡፡
በራእ. 14፡ 6-7 በተለይ ከአራተኛው ትእዛዝ (ዘፀ. 20፡10) የተወሰደውን
ቋንቋ የሚያንጸባርቀው ቁ. 7--ሰንበት በመጨረሻው ጊዜ ከአምልኮ ጋር
በተያያዘ ለሚነሳው ብርቱ ቀውስ እጅግ ወሳኝ መሆኑን መመልከት እንድንችል
አይረዳንም?
በምድር “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጠብቁ” (ራእ. 12፡17፣
13፡2፣ 4) ሕዝቦች ላይ ጦርነት የከፈተው፤ በሰማይ አምላክ እግዚአብሔር ላይ
ጦርነት አውጆ የነበረው ያው ዘንዶ ወይም ሰይጣን ነው (ራእ. 12፡7)፡፡ በእርግጥ
ሰይጣን ራሱ ስግደት ይቀበላል (ራእ. 13፡4)፡፡ ስለዚህ ሰይጣን በእግዚአብሔር
ላይ በሰማይ የጀመረውን ውጊያ በምድርም ለመቀጠል ብርቱ ምኞቱ ነው፡፡
በእግዚአብሔር ላይ ለከፈተው ጦርነት ዋንኛ ኢላማው ደግሞ ሕጉ ነው፡፡
“እግዚአብሔር ከሁሉም ሐሰተኛ አማልክት ተለይቶ የሰማይና የምድር ፈጣሪ
ሆኖ በአራተኛው ሕግ ላይ ተገልጾአል፡፡ የፍጥረት ሥራ መታሰቢያ የሆነው
ሰባተኛው ቀን ለሰው የዕረፍት ቀን ሆኖ ተቀደሰ፡፡ ዕለቱ ሕያው አምላክ ሁሌም
በሰብዓዊው አእምሮ--የፍጥረት ባለቤት፣ የቅድስናና የአምልኮ ምልክት ሆኖ
እንዲታሰብ ተነደፈ፡፡ ሰዎች ለእግዚአብሔር ያላቸውን ታማኝነት ለማስቀየስና
ሕጉን በመታዘዝ ምላሽ እንዳይሰጡ ሰይጣን በመዋጋት ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ
በተለይ የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት ከሚያመለክተው ትእዛዝ በተቃራኒ በመሥራት
የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp.
53, 54.
ጌታ “የሰማይና ምድር” ፈጣሪ በመሆኑ እናመልከዋለን፡፡ ሰባተኛው ቀን ሰንበት
ደግሞ ወደ ኋላ እስከ ፍጥረት ሣምንት በመሄድ የፈጣሪነቱ ምልክት መሰረት
መሆኑን ያሳያል (ዘፍ. 2፡1-3)፡፡ ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ የሚሰነዝረው ጥቃት
አበይትና መሰረታዊ የሥልጣኑ ምልክት በሆነው፡ ሰባተኛ ቀን ሰንበት ላይ መሆኑ
እምብዛም ላይደንቅ ይችላል፡፡
እግዚአብሔር በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች--ለአምልኮአችን ብቸኛ ዋጋ ያለውንና
ጌታን እንደ ፈጣሪ የሚጠቅሰውን ትእዛዝ ጨምሮ ሁሉንም ትእዛዞች በመጠበቁ
ረገድ ጽኑና የማያወላውል አቋም ያላቸው ሕዝቦች ይኖሩታል፡፡
1.በአንድ በኩል ስለ ኃጢአት መኖር እያወሩ በሌላው የእግዚአብሔር ሕግ ተወግዷል የሚሉ ሰዎች ችግር ምንድን ነው? በእንዲህ ዓይነቱ ነገረ አስተሳሰብ ውስጥ ምን ዓይነት እርስ በርስ የሚጻረሩ ነጥቦችን ማውጣት ይችላሉ? 2.በቅዳሜ ሰንበት ፋንታ እሁድን ከሚጠብቁ ሰዎች ጋር ያደረጓቸው ሙግቶች ተሞክሮ ምን ይመስላል? ለመሟገቻ የተጠቀሟቸው ነጥቦች ምን ይመስላሉ? ምን ያህልስ ውጤታማ ነበሩ? ሰባተኛውን ቀን ሰንበት መጠበቅ በጸጋ ሳይሆን በሥራ ለመዳን መሞከር ነው በሚል የሚነሳውን የተለመደ ሙግት የሚጋፈጡበት መንገድ ምን ይመስላል? 3.ለመጨረሻው ጊዜ በምናደርገው ዝግጅትና ሰንበትን አስመልክቶ ከሌሎች ጋር በምናደርገው የሃሳብ መለዋወጥ በ “አውሬው ምልክት” ዙሪያ የሚነሱ ፈታኝ ነጥቦች ገና ገቢራዊ አለመሆናቸውን ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?