ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 2:13፣ 24፣ 2ቆሮ. 11:13–15፣ መዝ. 146:4፣ ዘፍ. 1–2:3፣ ራእ. 13:1–17፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ” (ራእ. 12፡9)፡፡
ሰይጣን ከሰማይ ከመባረሩ አስቀድሞ መላእክትን ለማሳት ሠርቶአል፡፡
“በእግዚአብሔር ፊት የነበረውን ስፍራ ለቅቆ እንደ ወጣ ሉሲፈር
በመላእክቱ መካከል ያለመርካትና የቅሬታ መንፈስ የመዝራት ጉዞውን
ጀመረ፡፡ ባለ ስውር ደባው ሰይጣን ለጊዜው እውነተኛ ዓላማውን ደብቆ፣
ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን የአምልኮ ገጽ ሳይለውጥ፤ ሰማያዊውን አካላት
በአንድነት የሚገዛው አምላካዊ ሕግ በፍጡራኑ ላይ አላስፈላጊ እቀባ ያደርጋል
በሚል አለመርካት እንዲፈጠር ማነሳሳት ጀመረ፡፡”—Ellen G. White, The
Great Controversy, p. 495.
በኤድን የአትክልት ስፍራ እውነተኛ ማንነቱን ሰውሮና በእባብ ተመስሎ
ሔዋንን አታለለ፡፡ ሰይጣን ይህን ማታለሉን ከጥንት አንስቶ ዛሬ ድረስ-እንደውም ጻድቃን ሺ ዓመት ከነገሡ በኋላም እንኳ (ራእ. 20፡8) እስከ
መጥፊያው ድረስ ይገፋበታል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ እርሱ ከእኛ በላይ ብልህ፣ የላቀ አቅም ያለውና ወደር
የማይገኝለት አታላይ ነው፡፡ ስለዚህ ከእርሱ ማታለያ ለመጠበቅ ያለን ብቸኛው
አማራጭ የሱስንና አምላካዊውን ቃል አጥብቆ መያዝ ነው፡፡ “አምላካችሁን
እግዚአብሔርን የተከተላችሁት እናንተ ሁላችሁ ግን ይኸው እስከ ዛሬ በሕይወት
አላችሁ” (ዘዳ. 4፡4)፡፡ ይህ ተቀባይነት ያለው መርኅ እነሆ ዛሬም በእርግጠኝነት
እውነት እንደሆነ አለ፡፡
በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እጅግ ውጤታማ የሆኑትን አንዳንድ
የሰይጣን ማታለያዎችንና ከእነርሱ እንዴት መጠበቅ እንደምንችል
እንመለከታለን፡፡
የዚህ ሩብ ዓመት የመጀመሪያው ትምህርት ከምድራችን ባሻገር ወዳለው
“ዩኒቨርስ አቀፉ ተቃርኖ” በማምራት አንዳንድ ጠቃሚ ጽንሰ ሃሳቦችን መዳሰሱ
ይታወሳል፡፡
የሚያሳዝነው ክርስቲያኖችን ጨምሮ ብዙዎች በዚህ ታላቅ ተቃርኖ ላይ እምነት
የላቸውም፡፡ ለዚህ መንስዔው ደግሞ በሰይጣን ነባራዊ ሁኔታ አለማመናቸው
ነው፡፡ ስለ ሰይጣን ወይም ዲያብሎስ የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች
ለእነርሱ በምድር ላይ የነበረውን ክፋትና ሥቃይ ሊያብራራ የሚሞክር ቅድመ
ሳይንስ ባህልና ወግ ነው፡፡ በሰብዓዊው ፍጡር ላይ ክፉና በተንኮል የተሞላ
መሰሪ እቅድ ያለውን ነገር ብዙዎች የሚመለከቱት ከደራሲና ጸሐፊ ተውኔት
ዳርት ቫንደር “ስታር ዎርስ” የሣይንስ ልቦለድ ጽንሰ ሃሳብ በተመሳሳይ ነው፡፡
የሚከተሉትን ከራእይ መጽሐፍ የተወሰዱ ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ስለ ሰይጣን
በተጨባጭ መኖርና በተለይ ደግሞ በመጨረሻዎቹ ቀናት ስለሚኖረው ሚና ምን
ይነግሩናል? ራእ. 2:13፣ 24፣ 12:3፣ 7–9፣ 12፣ 17፣ 13:2፣ 20:2፣ 7፣ 10፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰይጣን በአያሌ የምድር ሕዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኃይል
እንደሚኖረው የራእይ መጽሐፍ ይነግረናል፡፡ ሰይጣን እነርሱን ከደህንነት
መንገድ የማራቅ ሥራ ብቻ አይሠራም ይልቁንም ለየሱስ ታማኝ ሆነው
የጸኑትንም ይዋጋል፡፡
ምናልባት ከሰይጣን የማታለያ “ዕቅድ” (2ቆሮ. 2፡11) የላቀው ሰዎች ሰይጣን
የለም ብለው እንዲያምኑ አእምሮአቸውን ማሳመን ነው፡፡ ለነገሩ መኖሩን
ከማያምኑት ግዙፍ ባላጋራ መጠጊያ ፍለጋ ማን ሊሄድ ይችላል? ራሳቸውን
ክርስቲያን ብለው እየጠሩ ላፈጠጠውና ላገጠጠው የሰይጣን መኖር ጽንሰ ሃሳብ
ብርቱ ትኩረት አለመስጠታቸው በእጅጉ የሚገርም ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እንዲህ
ያለውን አቋም የያዙበት ምክንያት አንድም አምላካዊውን ቃል ቸል በማለት
አልያም በመጽሐፍ ቅዱስ የቀረቡትን የዚህ ዓለም ሥራዎቹንና ድርጊቶቹን
አጣምመው በመተርጎም ነው--በተለይ ወደ መጨረሻው ጊዜ እየተቃረብን
ስንመጣ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰይጣን መኖር አያሌ ማስረጃዎች እያቀረበ ነገር
ግን ብዙዎች ገሀዱን እውነታ መቃወማቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን
በትክክል ማስተዋላችን ምን ያህል ቁልፍ እንደሆነ እንድናስታውስ ይረዳናል፡፡
የራእይ መጽሐፍ በተለይ በመጨረሻዎቹ ቀናት ገቢራዊ ስለሚሆኑት የሰይጣን
ብልህ ማሳቻዎች ቢነግረንም፤ በራእ. 12፡11 ምን ዓይነት ታላቅ ተስፋ እናገኛለን?
ከዲያብሎስ መጠበቂያ የኃይል ምንጫችን ምንድን ነው?
ከዚህ በታች የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ፡፡ ሰይጣን ስላለው የማሳቻ ኃይል ምን
ይነግሩናል?
2ቆሮ. 11:13–15 _____________________________________________________________________
2ቆሮ. 2:9, 10_______________________________________________________________________
ራእ. 12:9____________________________________________________________________________
ራእ. 20:10__________________________________________________________________________
የሱስ ስለ መጨረሻው ጊዜ ማታለያዎች ተከታዮቹን ማስጠንቀቁን ቀደም ባለው
ትምህርታችን ተመልክተናል፡፡ በተለይ ከሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች መሃል
የሐሰተኛ ክርስቶሶች እና “‘ብዙዎችን የሚያስቱ’” ሐሰተኛ ነቢያት መነሳት
ይጠቀሳሉ (ማቴ. 24፡5)፡፡
ሆኖም በመጨረሻው ጊዜ እንድንጠነቀቃቸው የተነገሩን አሳቾች ሐሰተኛ
ክርስቶሶች እና ሐሰተኛ ነቢያት ብቻ አይደሉም፡፡ በዚህ በታላቁ ውዝግብ
ጠላታችን በተቻለው ለማሳት የሚጠቀምባቸው አያሌ ዘዴና ብልሀቶች አሉት፡፡
እኛ እንደ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን በማወቅና የሚያስተምረውን በመታዘዝ
በእነዚህ የማሳቻ ዘዴዎች ላይ ግንዛቤ ሊኖረን ይገባል፡፡
ኤለን ኋይት ስለ ሁለቱ ታላላቅ የማሳቻ ዘዴዎች እንዲህ ትላለች፡ “ሰይጣን
በሁለቱ የተሳሳቱ አስተምህሮዎች ማለትም--በ ነፍስ አትሞትም እና በእሁድ
ቅድስና ሕዝቡን ያስታል፡፡ የመጀመሪያውና ነፍስ አትሞትም የሚለው
አስተምህሮ (ስፕሪቹዋሊዝም) ከሙታን መንፈስ ጋር ስለ መገናኘት ለሚያወሳው
አፈንጋጭ ስህተት መሰረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት ጋር
ውል አለው፡፡ የዩኤስ አሜሪካ ፕሮቴስታንቶች ሸለቆውን አልፈው
የስፕሪቹዋሊዝምን ፍልስፍና አራማጆች ለመጨበጥ ቀዳሚዎች ይሆናሉ፡፡
ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ በተቃራኒ እንጦሮጦስ ወርደው ከሮም ኃይል ጋር
እጅ ለእጅ ይያያዛሉ፡፡ ታዲያ ይህ የሦስትዮሽ ኅብረት ተጽእኖ ይህች አገር
(ዮኤስ አሜሪካ) የአምልኮ ነፃነትን ረግጣ የሮምን ዱካ ተከትላ እንድትሄድ
ያደርጋታል፡፡”—The Great Controversy, p. 588.
ኤለን ኋይት ይህን መልእክት ያሰፈረችው ከአያሌ ዓመታት በፊት ቢሆንም
“ሁለቱ ታላላቅ ስህተቶች” ዛሬ በክርስትናው ዓለም እንዲህ ተስፋፍተው
መመልከታችን የሚደንቅ ነው፡፡
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ዕውቀት እና እነዚህን እውነቶች ለመታዘዝ የሚኖር
ፈቃደኝነት ለዲያብሎስ ማታለያ ዓይነተኛ መሣሪያ የሆነው ለምንድን ነው-በተለይ በመጨረሻዎቹ ቀናት?
ከዚህ በታች የቀረቡት ጥቅሶች ስለ “ሙታን ሁኔታ” ምን ይነግሩናል? ጥቅሶቹ
ከላይ ከተመለከትናቸው ከሁለቱ ታላላቅ ስህተቶች ለአንደኛው ምን ዓይነት
ብርቱ ከለላ ይሰጠናል? መክ. 9:5-6፣ 10፣ መዝ. 115:17፣ 146:4፣ 1ቆሮ. 15:16–
18፣ ዳን. 12:2፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሉ አሥርተ ዓመታት--ልባቸው መምታት ካቆመና
ትንፋሻቸው ከተቋረጠ በኋላ መልሰው በማንሰራራት ወደ ሕሊናቸው
ተመልሰዋል--በሚል ስለ “ሞቱ” ሰዎች ሁኔታ የተዘገቡ ብዙ ዕንግዳ ታሪኮች
ይሰማሉ፡፡ “ሞቱ” ከተባሉ በኋላ በዚህ ተሞክሮ አለፉ የሚባሉ ብዙዎች
አስገራሚ የሚባሉ ታሪኮችን ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ አንዳንዶች እንዴት በአየር
ላይ ተንሳፈው ቁልቁል የገዛ አካላቸውን እንደተመለከቱ ሲናገሩ፤ ሌሎች ደግሞ
ከበድኑ አካላቸው ወጥተው እንደተንሳፈፉ--በእውነት፣ በደግነት፣ በፍቅር እና
በአስደናቂ ብርሃን ውስጥ ያለ ማንነት ሲገናኛቸው መመልከታቸውን
ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሞቱ ዘመዶቻቸውን እንደ ተገናኙ የተናገሩም
ብዙዎች ናቸው፡፡
ይህ ክስተት እጅግ የተለመደ ከመሆኑ የተነሳ--ለሞት የቀረቡ ተሞክሮዎች
(Near Death Experiences (NDEs) የሚል ሳይንሳዊ ስያሜ እስከ ማግኘት
ደርሶአል፡፡ ምንም እንኳ ጉዳዩ አወዛጋቢ እንደሆነ ቢቀጥልም ብዙ ክርስቲያኖች
ሰው ሲሞት ነፍስ ግን ህልውናዋን እንደጠበቀችና የማገናዘብ ችሎታዋን
እንደያዘች በሌላ ዓይነት ሁናቴ መኖሯን ትቀጥላለች ለሚለው አስተምህሮ እንደ
ማስረጃ ይጠቀሙበታል፡፡
ነገር ግን ለሞት የቀረቡ ተሞክሮዎች በሚል ሳይንሳዊ ስያሜ ያገኘው ይህ
ክስተት ሌላው “የሁለቱ ታላላቅ ስህተቶች” መገለጫ ነው፡፡ አንድ ሰው--ሰው
ሲሞት ነፍሱ በሌላ ቅርጽ መኖር ትቀጥላለች በሚለው አፈንጋጭ አስተምህሮ
እስካመነ ድረስ ግለሰቡ ከፍ ያለውን የምትሀትና ጥንቆላ ማሳቻዎች ለመቀበል
በጣም የቀረበ ነው፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ማሳቻዎች--የሱስ አያስፈልግህም
የሚለውን ማታለያ በቀላሉ በግልጽ ወይም በስውር ማበረታታት ይችላሉ፡፡
የሚገርመው በተሞክሮው ውስጥ አለፉ የሚባሉ ብዙዎች ሲናገሩ እንደ
ተደመጠው--የተገናኟቸው መንፈሳዊ አካላት ወይም የሞቱ ዘመዶቻቸው ስለ
ሰጧቸው አጽናኝ ቃላት፣ ፍቅር፣ መልካምነት እንጂ መሰረታዊ የሆኑትን
የመጽሐፍ ቅዱስ ምልከታዎች ማለትም--በክርስቶስ ስለሚገኝ ደኅንነት፣ ስለ
ኃጢአት ወይም ስለ ፍርድ አንዳች ስለ መተንፈሳቸው የተዘገበ ነገር የለም፡፡
ከህይወት በኋላ አለፍንበት ባሉት ተሞክሮ የክርስትናን ህይወት አጣጣምን
ብለው ከተናገሩ፤ በነካ እጃቸው እጅግ መሰረታዊውን የክርስትና አስተምህሮ ለዛ
ሊያጣጥሙም የተገባ ይሆናል ሲሉ አንዳንዶች ይሞግታሉ፡፡ ለሞት የቀረቡ
በተባሉት ተሞክሮዎች ውስጥ ያለፉ ከተናሯቸው ነገሮች ውስጥ አብዛኞቹ ኒው
ኤጅ በመባል ከሚታወቀው አፈንጋጭ ኃይማኖታዊ ቀኖና ጋር ተመሳሳይነት
አላቸው፡፡ አብዛኞቹ “ሞቱ” የተባሉት ክርስትና ራሱ እዚህ ግባ የሚሉት ዓይነት
ሆኖ አናገኘውም፡፡
ኅሊናችን የሆነ ያልተለመደ ነገር ሹክ ሊለን ቢችል እንኳ--እንደ ክርስቲያን
ከእግዚአብሔር ቃል ጋር አጥብቀን መጣበቅ ያለብን ለምንድን ነው?
ሰይጣን ነፍስ አትሞትም በሚለው አስተምህሮው ብዙዎችን በማሳት ስኬት
እንዳገኘ ሁሉ፤ በክርስትና ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሰንበት ወደ እሁድ
በመለወጥ ምናልባትም የላቀውን ክንውን አግኝቶአል (ስድስተኛውንና
ስምንተኛውን ትምህርት ይመልከቱ)፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዲያብሎስ ሰባተኛው ቀን ሰንበት በሕዝቡ አእምሮ
አነስተኛ ስፍራ እንዲኖረው የሚያደርግ ሌላ የማሳሳቻ ዘዴ ይዞ የመጣ ሲሆን
ይኸውም፡ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳብ በመባል ይታወቃል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1-2፡3፡፡ ገጾቹ ጌታ እንዴት ዓለማችንን እንደ ፈጠረና
የፍጥረት ሥራ ምን ያህል ጊዜ እንደ ወሰደበት ምን ይነግሩናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ጥቅሶቹ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊው የፍጥረት ሥራ ሁለት ነጥቦችን በስፋት
እንዲሁም በጥልቀት ይገልጣሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ--ማንኛውም ነገር በዕቅድና
በስሌት መተግበሩን፡፡ በዘፈቀደ፣ በደመነፍስ ወይም እንደ ዕድል የሆነ አንዳች
ነገር አልነበረም፡፡ የፍጥረት ሂደት ባጋጣሚ ወይም በዕድል መተግበሩን
የሚጠቁም አንድም ፍንጭ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አልተተወም፡፡
በሁለተኛ ደረጃ--እያንዳንዱ ፍጥረት ከራሱ አምሳያ አኳያ መፈጠሩን
በማያሻማ ሁኔታ ይገልጹልናል፡፡ ይህ ማለት እያንዳንዱ የፍጥረት ሥራ ከሌሎቹ
ተለይቶና የራሱን ልዩ ባህሪ ይዞ ነው የተፈጠረው፡፡ ሕይወት ያለው ነገር ሁሉ
የመጣው ከአንድ የጋራ ህዋስ ነው የሚለውን አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ አናገኘውም፡፡
ቃል በቃል ፍቺ የመስጠት መርኅን የማይከተሉት እንኳ ከዘፍጥረት
መጽሐፍ አኳያ የቀረቡትን ሁለት ነጥቦች ይጋራሉ፡፡ በፍጥረት ሥራ በአጋጣሚ
የተከሰተ ነገርም ሆነ የጋራ ተፈጥሮአዊ ዝርያ የሚባል አንዳች ነገር የለም፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚመጣው የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳብ
ከያዛቸው የተለያዩ ቅርጾች አኳያ ሁለት ነገሮችን ያስተምራል፡--የውጤቶች
ባህሪያት እኩል እና ተመሳሳይ መሆን የመቻል ዕድል እና ለሁሉም ዝርያዎች
የጋራ ተፈጥሮአዊ ቅድመ አያት--የሚሉ፡፡
ብዙዎች የዘፍጥረት መጽሐፍን ከመሰረታዊ ባህሪያቱ በሚቃረን የንድፈ
ሀሳብ መነጽር ለማየትና ለመተርጎም የሚሞክሩት ለምንድን ነው? እንደ እውነቱ
ከሆነ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳብ ግድፈት ጠራርጎ የወሰደው በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ዓለማዊያንን ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ራሳቸውን ክርስቲያን ብለው
የሚጠሩ አያሌዎች በዚህ ሁሉ ያፈጠጠ ተቃርኖ መሃል ከክርስትና እምነታቸው
ጋር አዋህደው መያዝ እንደሚችሉ ያምናሉ፡፡
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብ ከመጨረሻዎቹ ቀናት አንደምታ ሲታይ
የማታለሉን አደጋ ይበልጥ ጉልህ ያደርገዋል፡፡ የፍጥረት ሂደት ስድስት ቀናት
ሳይሆን 3 ቢሊዮን ዓመታት ገደማ ወስዶ እያለ፤ አንዱ ቀን ማለትም ሰባተኛው
ቀን ሰንበት እንደ መታሰቢያ የሚወሰደው ለምንድን ነው? የዝግመተ ለውጥ
ንድፈ ሃሳብ የስድስቱን ቀናት የፍጥረት ሥራ በምናባዊው “ታሪኬ ባጭሩ”
ዓይነት ልቦለድ ስለሚተካው ሰንበት ባዶና ትርጉም አልባ ይሆናል፡፡ ደግሞም
የፍጥረት ሥራ ስድስት ቀናት ሳይሆን ቢሊዮን ዓመታት ወስዶአል የሚለውን
ንድፈ ሃሳብ በውስጣቸው እያመኑ፣ ነገር ግን እሁድን ተቃውመው ለሰንበት
ቢቆሙ ሊመጣ ያለውን የስደት ወይም የሞት አደጋ ተጋፍጦ ለመቆም
የሚያስችል ጽናት ሊኖራቸው ይችል ይሆን?
እግዚአብሔር በሦስት ባህሪያት የመገለጹ ጽንሰ ሃሳብ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ
ገጾች ይገኛል፡፡ ሆኖም ራእይ 13 ከመጨረሻው ጊዜ ማታለያና ስደት ዐውድ
ዲያብሎስ ሦስት አካል ይዞ ብቅ የሚል ሲሆን እነርሱም፡ ዘንዶው፣ ከባህር
የሚወጣው አውሬ እና ከምድር የወጣው አውሬው ናቸው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12፡17፣ 13፡1-2፡፡ በእነዚህ ስፍራዎች ምን ተገልጾ
እናገኛለን?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በዚህ ስፍራ የቀረበውና የአብን ስፍራ በመያዝ የሚያስመስለው ዘንዶ
ሁሉም ነገር በእርሱ ቁጥጥር ስር እንደሆነ በግልጽ ይስተዋላል፡፡ ክርስቶስን
ለሚያስመስለው ከባሕር የወጣው አውሬ ደግሞ--ኃይል፣ ሥልጣን እና ዙፋን
ሲሰጠው ይታያል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሁለተኛው ኃይል ክርስቶስን የሚያስመስል
ሆኖ የታየው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡2-5፡፡ ለመሆኑ የዚህ ከባሕር የወጣ አውሬ ባህሪያት
ምንድን ናቸው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የሱስ ሥልጣን ከአብ እንደተቀበለ (ማቴ. 28፡18) አውሬውም ከዘንዶው
ኃይል መቀበሉ፤ ከባህር የወጣው አውሬ እንደ የሱስ ሞት እና ትንሣኤ
የሚመስል (ራእ. 13፡3) አስመሳይ ትዕይንት ውስጥ ማለፉ፤ እንዲሁም ይህ
አውሬ ሥልጣኑን “ለአርባ ሁለት ወራት” ወይም ለሦስት ዓመት ተኩል ጥቅም
ላይ እንዳዋለ የተገለጸ ሲሆን ክስተቱ የክርስቶስን ሦስት ዓመት ተኩል የፈጀ
ምድራዊ አገልግሎት ማስመሰልን ያመለክታል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡11-17፡፡ ከምድር የወጣው አውሬ የተገለጸበት
መንገድ ምን ይመስላል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
መንፈስ ቅዱስ ራሱን ሳይሆን የሱስን ከፍ ከፍ እንዳደረገ ሁሉ ይህ ከምድር
የወጣ አውሬም ከባሕር የወጣውን አውሬ ፍላጎት የሚያስፋፋና የሚያዳብር
ሥራ ይሠራል (ዮሐ. 16፡13-14)፡፡ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ “እሳት”
እንዳወረደ (ሐዋ. 2፡3) ከምድር የወጣውም አውሬ ተመሳሳይ የማስመሰል
ድርጊት ይፈጽማል (ራእ. 13፡13)፡፡
“በስተ መጨረሻ ከምድር የወጣው አውሬ በጴንጤቆስጤ ወቅት ገቢራዊ የሆነው
ዓይነት የማስመሰል ሥራ ይሠራል፡፡ ለምን ዓላማ? አስመሳዩ ሦስት አካል
እግዚአብሔር እንደሆነ የሚገልጽ ማረጋገጫ ለመስጠት”—Jon Paulien, What
the Bible Says About the End-Time (Hagerstown, Md.: Review and Herald®
Publishing Association, 1998), p. 111.
በንቃት ልንከታተላቸው የሚገቡ ሌሎቹ የመጨረሻው ጊዜ ክስተቶች ምንድን
ናቸው? ሌሎች ወገኖች እነዚህን ማታለያዎች መገንዘብ ይችሉ ዘንድ እንዴት
ልንረዳቸው እንችላለን?
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብን ከመጨረሻው ጊዜ ክስተቶች
ዐውድ ጠለቅ ብለን ለመመልከት እንሞክር--በተለይ ከሰንበት ጋር ከሚኖረው
ሚና፡፡ የዚህ ንድፈ ሃሰብ አመንጪ የሆነው ቻርለስ ዳርዊን ይህን ሃሳብ
ያበረታታበት አንዱ ምክንያት በብርሃን እና በጨለማው ኃይል መካከል
እየተካሄደ ያለውን ታላቁን ተቃርኖ ማስተዋል አለመቻሉ ነው፡፡ ዳርዊን
ክፉውንና በሥቃይ የተሞላውን ትዕይንት በቸርነት ከተሞላውና አፍቃሪ ከሆነው
ፈጣሪ ጽንሰ ሃሳብ ጋር ለማስታረቅ በእጅጉ ተቸግሮ ነበር፡፡ በዚህ ስህተት
መንስኤ ምላሽ ፍለጋ ወደ ሌላ አቅጣጫ አማተረ፡፡ ጊዜው በ1800 ዓ.ም. አጋማሽ
እና መጨረሻ አካባቢ ነበር፡፡ ነገሩ አጋጣሚ ይሁን ወይም አይሁን--ዳርዊን
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳቡን እየፈተሸና እያደራጀ በነበረበት በዚያን ወቅት
እግዚአብሔር ለንድፈ ሃሳቡ አጸፋዊ ምላሽ ለመስጠት የፈለገ ይመስል የሰባተኛ
ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ አስነሳ፡፡ ለአምላካዊው የፍጥረት
ሥራ ያላት ድጋፍና መሰረት በስያሜዋ የተገለጠው ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ
ክርስቲያን፤ የዳርዊን ንድፈ ሃሳብ ከተጸነሰበት ተመሳሳይ ጊዜ አንስቶ እነሆ
እያደገችና እየተመነደገች መሄዷን ማወቅ በእርግጥም መሳጭ ነው፡፡
ምናልባት ኤለን ኋይት ከዚህ እንደሚከተለው የጻፈቻቸውን አጭር
መስመሮች ዳርዊን አንብቦና አገናዝቦ ቢሆን ኖሮ ማን ያውቃል--ዓለም ከእንዲህ
ዓይነቱ የጅል ስህተት መጠበቅ በቻለች ነበር፡፡ “ምንም እንኳ ምድር በመቅሰፍት
ብትመታም፤ ተፈጥሮ አሁን ድረስ የሰው ልጆች መማሪያ መጽሐፍ ነው፡፡
እዚህም፣ እዚያም በየስፍራው የተሰራጨው ክፉው በጣር ውስጥ የሚገኘውን
የብስ፣ ባሕርም ሆነ አየር እያረከሰ በመሆኑ--ተፈጥሮ መልካም የሆነውን ነገር
ብቻ መወከል አይችልም፡፡ በአንድ ወቅት የመልካም ዕውቀት መገለጫ የነበረውና
የእግዚአብሔር ባህሪ ብቻ የተጻፈበት ተፈጥሮ፤ አሁን ግን የክፉው ዕውቀት
የሆነው--የሰይጣንም ባህሪ አረፈበት፡፡ ሰው ዛሬ የመልካሙንና የክፉውን
ዕውቀት ገልጦ ካሳየውና የኃጢአትን ውጤት ካመጣው ከተፈጥሮ እንዲጠበቅ
በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ነበር፡፡”—Education, p. 26.
ዳርዊን ተፈጥሮን፣ የእግዚአብሔርን ባህሪ እና የምንኖርባትን የወደቀች
ምድር በተሳሳተ መንገድ በማስተዋሉ በሐሰት ላይ በተመሰረተ መላ ምት
የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሃሳብን ፈጠረ፡፡ የእርሱ ንድፈ ሃሳብ አንደምታዎች
በተለይ በመጨረሻው ቀውስ ሰዎችን የሰይጣን ማታለያ ታዳኝ ማድረጋቸው
በእጅጉ አሳዛኝ ነው፡፡
1.ብዙዎች የሰይጣንን መኖር ጽንሰ ሃሳብ የሚቃወሙት ለምንድን ነው? በግልጽ
የቀረበውን የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መቃወም ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ
ይህ አመለካከት ምን ያስተምረናል?
2.ለሞት በቀረበ ተሞክሮ በማለፍ ከሞት በኋላ ህያው እንደሆንን እንቀጥላለን
የሚል ሰው ቢገጥሞት ምን ዓይነት ሀሳብ ሊያካፍሉት ይችላሉ? (የማክሰኞ
ትምህርት)
3.በዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብ የሚያምኑ ሰዎች ለመጨረሻዎቹ ቀናት
ማታለያዎች በጣም የተጋለጡ ስለ መሆናቸው እርስዎ ሊያቀርቡ የሚችሉት ለየት
ያለ ምክንያት ምንድን ነው?