የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

መስከረም 5-11

አስራ ሁለተኛ ትምህርት

Sept 15-21

በቄሳርያ መታሰር

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህን ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሐዋ. ሥራ 24፣ ሐዋ. ሥራ 25፣ ሐዋ.ሥራ 26፣ 1 ቆሮ. 1፡23፡፡

መታሰቢያ ጥቅስ፡- “በቀላሉም ሆነ በብዙ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ከዚህ ከታሰርኩበት ሰንሰለት በስተቀር እንደ እኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” (ሐዋ. ሥራ 26፡29)

ጳ ውሎስ ወደ ቂሳርያ ሲዘዋወር በከተማይቱ (ሐዋ. 24፡27) በተለይም በሄሮድስ ግቢ ውስጥ በእስር የሁለት አመታት ቆይታው ተጀመረ፡፡ ይህ ስፍራ ደግሞ የሮም አመራሮች መኖሪያ ነበር(ሐዋ. 23፡35)፡፡ በነዚህ አመታት ውስጥ በሁለቱ የሮም ገዥዎች (ፊሊክስና ፊስጦስ) እና በንጉሱ (አግሪፓ 2ኛ) ፊት ቀርቧል፤ በዚህም እግዚአብሔር የሰጠውን የወንጌል አደራ መፈፀም ቻለ(ሐዋ. 9፡15)፡፡ በዚህ ሁሉ ምርመራ እርሱን ጥፋተኛ የሚያስብል ምንም አይነት ማስረጃም ሆነ ምስክር ስላልተገኘ ጳውሎስ ሁልጊዜም ንጹህ ሰው መሆኑን ያስረዳ ነበር፡፡ እንደውም ትረካው ፍንትው አድርጎ የሚያሳየን ጳውሎስ ለመታሰር የሚያበቃው ምንም ነገር እንደሌለና ለቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ ሊለቀቅ እንደሚችል ነበር(ሐዋ. 26፡32)፡፡ እነዚህ ምርመራዎች ጳውሎስ ስለየሱስና በትንሳኤ ላይ ስላረፈው ታላቁ የተስፋ ቃል ለሌሎች ለመመስከር ምቹ አጋጣሚ ፈጠሩለት፡፡

ሆኖም እነዚያ አመታት የስጋትና በየሩሳሌም ከምትገኘው ቤተክርስትያን ምንም አይነት ድጋፍ ያላገኘባቸው አታካች የሆኑ የእስራት ጊዜያት ነበሩ፡፡ የተወሰኑት የቤተክርስትያን መሪዎቹም ‹‹ለተፈጠረው ምክንያት አልባ ጥላቻና ውግዘት ባብዛኛው ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ጳውሎስ እንደሆነ ይሰማቸው ነበር፡፡›› Ellen G. white, The Acts of the Apostles, P. 403

የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለመስከረም 12 ሰንበት ይዘጋጁ፡፡

መስከረም 6
Sep 16

በፊሊክስ ፊት

ጳውሎስ ወደ ቄሳርያ ከተዘዋወረ ከአምስት ቀናት በኋላ ወሳኝ የሚባሉ የአይሁድ አመራሮች ሊቀ ካህናቱና አንዳንድ የሸንጎ አባላት ጠርጠሉስ ከተባለ እውቅ ጠበቃ ጋር በአንድነት ሆነው ከየሩሳሌም በመምጣት በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክሳቸውን በፊሊክስ ፊት አቀረቡ (ሐዋ. 24፡1-9)

በሐዋሪያት ስራ መጽሐፍ ውስጥ ከሳሾቹ ጠበቃ ቀጥረው የምናገኛቸው በዚህ ስፍራ ብቻ ነው፡፡ ጠርጠሉስ በንግግሩ ላይ የአገረ ገዥውን ይሁንታ ለማግኘት አስገራሚ ስትራቴጂ ለመጠቀም ጥረት አደረገ፡፡ በፊሊክስ አገዛዝ ወቅት አይሁዳውያን ለረጅም ጊዜ በሰላም ስለመኖራቸው የተናገረው ንግግር እውነት አልነበረም፡፡ እንደውም ከየትኛውም የአገዛዝ ጊዜ በበለጠ ጨቋኝና አስጨናቂ ከመሆኑ የተነሳ አይሁዳውያን በሮማውያን አመራር ላይ ያላቸው ጥላቻ እጅግ መራር እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ጠርጠሉስ ብዙ ብልሃትን በመጠቀም በዚህም ሁኔታ ቢሆን የራሱን የአገረ ገዥውን የአመራር ፖሊሲ ማለትም መራር የሆነ ጭቆናን ማሳደር ብቻ ፖለቲካዊ መረጋጋትን እንደሚያመጣለት ሊያሳምነው ጣረ፡፡

በመቀጠልም በጳውሎስ ላይ ሶስት ዝርዝር ክሶችን አቀረበ 1. በአገዛዙ ውስጥ በሚገኙ አይሁዳያን መካከል ሁከትን በማስነሳት ያውካል (ሐዋ. 24፡5) 2. የናዝራውያን ወገን ቀንደኛ መሪ ነው፤ (ሐዋ. 24፡5) ይህም የክርስትና እንቅስቃሴ ብጥብጥን ፈጣሪ እንደሆነ ያመላክታል 3. ቤተመቅደሱን ለማርከስ ሞክሯል (ሐዋ. 24፡6)

ሐዋ. 24፡10-19ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ለቀረቡበት ክሶች የሠጠው ምላሽ ምን ይመስል ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ለክሱ ከሰጠው ምላሽ ሁለቱ የከሳሾቹን ክስ ያፈረሱ ነበሩ፡- 1. ከእስያ አውራጃ የመጡ ምስክሮች (ሐዋ. 24፡18-19) አለመኖራቸውና እነርሱ ቢኖሩ ኖሮ ክሱን ውድቅ ማድረግ እንደሚቻላቸው 2. በዚያ የነበሩት አይሁዶች ሊናገሩ የሚችሉት ከሳምንት በፊት በሸንጎ ፊት ሲቀርብ (ሐዋ. 24፡20) ስለ ሙታን ትንሳኤ ከማመኑ በቀር ሌላ ምንም የሚከሰስበት ነገር እንዳላገኙበት (ከሐዋ. 23፡6 ጋር ያነፃፅሩ) ተናገረ፡፡

ፊሊክስ ወዲያውኑ የጳውሎስ የመከራሪያ ነጥብ ሚዛን እንደሚደፋ ተረዳ፡፡ ይህም ምናልባት ባለቤቱ ድሩሲላ አይሁዳዊ ስለነበረች ከክርስትና ጋር በተወሰነ መልኩ የቀረበ ስለነበር ይሆናል፡፡ ስለዚህ ተጨማሪ ግፊት እስኪመጣ ድረስ ነገሩን በይደር አቆየው (ሐዋ. 24፡22)፡፡

የፊሊክስ ምላሽ (ሐዋ. 24፡24-27) የእርሱ ባህሪ ምን እንደሚመስል ገልጦ ያሳያል፡፡ ጉዳዩን በይደር አቆየው፤ ጉቦ ይቀበል ነበር፤ እንዲሁም አጋጣሚዎቹን ለራሱ ጥቅም የሚያውል ሰውም ነበር፡፡ ጳውሎስ እንደ ፊሊክስ ባለ ሰው ፍትሐዊ ፍርድ ለማግኘት ጥቂት እድል ብቻ ነበረው፡፡

ሐዋ. 24፡16ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ‹‹ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት ንጹህ ህሊና እንዲኖረው›› ሁልጊዜ እንደሚጥር ተናግሯል ይህን ሲል ምን ማለቱ ነው? ይህን ተመሳሳይ ነገር ለማለት መለወጥ የሚገባዎ ምን ነገር አለ ብለው ያስባሉ?

መስከረም 7
Sep 17

በፊስጦስ ፊት

አይሁዳውያንን ለማስደሰት ሲል ጳውሎስን ለሁለት አመት በእስር ካቆየው በኋላ ፊሊክስ በጶርቅዮስ ፊስጦስ ተተካ (ሐዋ. 24፡27)፡፡ ፊስጦስም ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ60 እስከ 62 ዓ.ም. ድረስ መራ፡፡ ሐዋ. 25፡1-5ን ያንብቡ፡፡ ይህ እውነትን የሚሰብኩ ሰዎች ያንን ማመን በማይሹ ሰዎች አማካኝነት ስለሚደርስባቸው ጥላቻ እንድንገነዘብ የሚያግዘን እንዴት ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ምናልባትም ፊሊክስ በጳውሎስ እንዲፈርድ ያደረጉት ጥረት ስላልሰመረላቸው መሪዎቹ በድጋሚ ሌላ እድል እንዲያመልጣቸው አልፈለጉም፡፡ ፊስጦስ ወደ ኢየሩሳሌም የመጀመሪያውን ጉብኝት ሲያደርግ አንድ ውለታ እንዲያደርግላቸው ማለትም የቀድሞውን ውሳኔ ቀይሮ ጳውሎስን ለነርሱ መልሶ እንዲሰጣቸውና በአይሁዳውያን ህግ መሰረት በሸንጎው እንዲዳኝ ጠየቁት፡፡

ነገር ግን ጥያቄያቸው የውስጥ ሴራቸውን ማለትም ጳውሎስን ለመግደል ያሰቡትን ኃሳብ ለመደበቅ ብቻ ታስቦ የመጣ ጥያቄ ነበር፡፡ ፊስጦስ ጉዳዩን ደግሞ ለማየት ፈቃደኛ ቢሆንም ጉዳዩ መታየት ያለበት ኢየሩሳሌም ሳይሆን ቄሳርያ መሆን እንዳለበት ነገራቸው፡፡ ይህም ጳውሎስ የሚዳኘው በሮማውያን ህግ ነው ማለት ነው፡፡ ፊስጦስ ወደ ቄሳርያ እንደተመለሰ የሚመለከታቸውን አስጠርቶ የፍርድ ሂደቱ ተጀመረ፤ የጳውሎስ ባላንጣዎችም በጳውሎስ ላይ ያላቸውን ክስ ማቅረብ ጀመሩ (ሐዋ. 25፡7)፡፡ እዚህ ጋር ሉቃስ ሲተርክልን ስለክሱ ይዘት በድጋሜ አላነሳም፤ ነገር ግን የጳውሎስን ምላሽ መሰረት በማድረግ (ሐዋ. 25፡8) ከሁለት ዓመታት በፊት ያቀረቡትን ተመሳሳዩን ክስ እንዳቀረቡና ጳውሎስ አመጽን ስለሚያነሳሳ ለአገዛዙ ስጋት በመሆኑ ላይ አፅንዖት ስለመስጠታቸው መረዳት ይቻላል፡፡

ሐዋ. 25፡9-12ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ንጉሱ ፊስጦስ በአይሁድ ዘንድ ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት ሊጠቀምበት እንደሚችል ሲረዳ ምን ምላሽ ሰጠ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በስተመጨረሻ ፊስጦስ በፖለቲካዊ ስትራቴጂው ከፊልክስ እምብዛም ያልተለየ አቋም አሳየ (ሐዋ. 24፡27)፡፡ ጳውሎስ ንጹህ ሰው እንደሆነ በማወጅ ገና ብዙም ሳያስተዳድር የአይሁዳውያንን ድጋፍ ማጣት ስላልፈለገ የመጀመሪያ ጥያቄያቸውን ለማስተናገድ አሰበ፡፡ ይህም ጳውሎስ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የአይሁድ ሸንጎ እንዲዳኝ ማድረግ ነበር፡፡

ነገር ግን ይህ ኃሳብ በጳውሎስ ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፤ ምክንያቱም ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ እንደማይዳኝና ለጠላቶቹ እንደሚሰጥ ስለተረዳ ነው፡፡ ስለዚህ የሮማዊነት መብቱን በማጉላት በሮማውያን ሸንጎ ጉዳዩ እንዲታይ መብት እንዳለውና በዚያ ካልሆነ ከዚህ አስጨናቂ ሁኔታ መውጣት እንደማይቻል በመገመት ወደ ላይኛው የሮም ፍርድ ቤት ማለትም ወደ አገረ ገዥው ይግባኝ አለ፡፡

መስከረም 8
Sep 18

በአግሪጳ ፊት

ፊስጦስ ጳውሎስ ሮም ለመዳኘት ያቀረበውን የይግባኝ ጥያቄ ተቀበለ(ሐዋ. 25፡12)፡፡ በዚህ ወቅት ግን ለጉብኝት ወደርሱ የመጣውን ሄሮድስ አግሪፓን(2ኛው) ስለ ጳውሎስ ጉዳይ በተለይም ለሮም ገዢ መላክ ስለሚገባው ኦፊሴላዊ መረጃ ለማማከር ያገኘውን እድል ተጠቀመበት፡፡ ፊስጦስ በአይሁዶች ጉዳይ ብዙም ልምድ አልነበረውም እናም አግሪፓ ሊረዳው ይችል ነበር (ሐዋ. 26፡2-3) ሐዋ. 25፡13-22ን ያንብቡ፡፡ ፊስጦስ ስለ ጰውሎስ ለአግሪጳ ምን ነገረው? ንጉሱስ ምን ምላሽ ሰጠ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የሄሮድሶች የመጨረሻ የነበረው አግሪጳ(2ኛ) ወደ ቂሳሪያ ከእህቱ በርኒቄ ጋር የመጣው አዲስ የተሾመውን አገረ-ገዥ ፊስጦስን እጅ ለመንሳት ነበር፡፡ ፊስጦስ ስለ ጳውሎስ ጉዳይ በዝርዝር ሲያስረዳ ጉዳዩ ከፍተኛ(ትልቅ የሚባል) አለመሆኑ ወይም ከፖለቲካዊም ሆነ ከወንጀል ተግባር ጋር የማይያያዝ መሆኑ እንዳስደነቀው ገለፀ፡፡ ነገር ግን ክሶቹ ስለ አይሁድ ሃይማኖት በተለይም “ሞቶ ስለነበረውና ጳውሎስ ግን ህያው ነው ስለሚለው” ስለ ኢየሱስ ነበሩ(ሐዋ. ሥራ 25፡ 19)፡፡ ጳውሎስ አስቀድሞ በሸንጎው መማክርት ጉባኤ ላይ ለፍርድ የቀረበው በኢየሱስ ትንሳኤ በማመኑ የተነሳ እንደሆነ ገልጧል፡፡ አሁን ደግሞ ፊስጦስ ጉዳዩ በትክክልም ስለዚያ እንደሆነ አረጋገጠ፡፡ ሐዋ. ሥራ 25፡23-27ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት ስለቀረበበት ሁኔታ ሉቃስ የተረከው እንዴት ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

“ጳውሎስ አሁንም በሰንሰለት ታስሮ በጉባኤው ፊት ቆመ፡፡ እዚህ ጋ አስገራሚ ንፅፅር አለ፤ አግሪጳ እና በርኒቄ ስልጣን ስለነበራቸው በአለም ተቀባይነትን አገኙ፡፡ በእግዚአብሔር እይታ ግን ያልተገባ ባህሪ ያላቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ ህጉን የሚተላለፉ፣ ልባቸውም ህይወታቸውም የተበላሸ ነበር፡፡ ተግባራቸው በሰማይ ዘንድ አጸያፊ ነበር፡ ፡” Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 434

ይህ ታሪክ የውጭ መልክ ለሰዎች አስደሳች ሆኖ ቢታይም ከእይታው በስተጀርባ ስላለው እውነታ ምን ያህል አታላይ ሊሆን እንደሚችል ምን ያስተምረናል? እኛስ ብንሆን እንዴት ነን? ከላይ የሚታየው ማንነታችን ከእውነታው ምን ያህል ይለያል?

መስከረም 9
Sep 19

የጳውሎስ መከላከያ

ከአገረ ገዥው ጎን ከፍተኛ መኮንኖች ተቀምጠው እስረኛው የመከላከያ ነጥቡን እንዲያቀርብ ተደረገ፡፡ ፊስጦስ ጉዳዩን ቀድሞ ስለሰማ በዋናነት አግሪጳ እንዲሰማ ታስቦ ነው ይህ የሆነው (ሐዋ. 25፡8-11)

ሐዋ. 26፡1-23ን ያንብቡ፡፡ በአግሪጳ ፊት ባደረገው ንግግር ጳውሎስ ምን አይነት መንገድን ተጠቀመ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በርግጥም ጳውሎስ እየተናገረ የነበረው ከመለወጡ በፊትና ከተለወጠ በኋላ ስለሆነው የራሱ ግለ ታሪክ ነበር፡፡ የንግግሩ ይዘት በኢየሩሳሌም ለተሰበሰበው ህዝብ ያደረገውንና በሐዋ. ሥራ 22፡1-21 የሰፈረውን ንግግር የሚያስታውስ ነው፡፡

ሐዋርያው የአግሪጳን ይሁንታ በሚያረጋግጥለት መንገድ ንግግሩን ጀመረ፡፡ አግሪጳ ስለ አይሁድ ልማዶችና የውስጥ ጉዳዮች ጥሩ እውቀት ስለነበረው በዚያ ታዋቂ ሰው ፊት ጉዳዩን ለማቅረብ እድልን በማግኘቱ ምስጋናውን አቀረበ፡፡ በዚህ ምክንያት አግሪጳ የሮማው መሪ በጳውሎስ ላይ የተነሳው ክስ ሐሰት ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ትልቅ እገዛ ማድረግ የሚችል ሰው ነበር፡፡

ንግግሩም በሶስት ሊከፈል ይችላል፡፡ በመጀመሪያው ክፍል (ሐዋ. 26፡4-11) ጳውሎስ ፈሪሳዊ ስለመሆኑና ስለነበረው ቅናት በኢየሩሳሌም ያሉ በእድሜ አቻው የሆኑ አይሁዳውያንም እንደሚያውቁ ገለፀ፡፡ እንደ ፈሪሳዊነቱ ደግሞ የእስራኤል የዘመናት ተስፋ እንዲፈፀም አስፈላጊ ስለሆነ በሙታን ትንሳኤ ያምናል፡፡ ስለዚህ አይሁዳዊ መሠረት የሌለውን ነገር ስላላስተማረ አይሁዳውያኑ ትምህርቱን ሲቃወሙ ያልፀና አቋም እያሳዩ ነበር፡፡ ኃሳባቸውን በደንብ ተረድቷል፤ ያም በአንድ ወቅት እርሱ ራሱም እግዚአብሔር ኢየሱስን ማስነሳቱ የማይታመን ነገር አድርጎ ከማየቱ የተነሳ ኢየሱስ ተነስቷል ብለው የሚያምኑትን ሰዎች ያሳድድ ስለነበረ ነው፡፡

ሁለተኛው ክፍል (ሐዋ. ሥራ 26፡12-18) ላይ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ኢየሱስን ከተገናኘና ለአህዛብ የወንጌልን መልእክት ለማድረስ ጥሪ ከተቀበለ በኋላ አመለካከቱ እንዴት እደተለወጠ ገለፀ፡፡

ጳውሎስ የዚህን ክፍል ንግግር ሲደመድም ያየው ነገር (ሐዋ. ሥራ 26፡19-23) እንዲታዘዝና የወንጌል ማዳረስ ተግባሩን እንዲፈፅም ከማስቻል ውጪ ሌላ አማራጭ እንዳይኖረው ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተናገረ፡፡ ወደ ሸንጎ የቀረበውም በዚህ ምክንያት ነበር፡፡ ስለዚህ ከመታሰሩ በስተጀርባ ያለው ትክክለኛ መንስኤ የአይሁድን ህግ መተላለፍ ወይም ቤተመቅደስን ማርከሱ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጣጣመውንና አማኝ የሆኑ አህዛብ እኩል የድነት መብት አግኝተው እንዲድኑ የሚፈቅደውን የኢየሱስን ሞትና ትንሳኤ በመስበኩ ነበር፡፡

ሐዋ. ሥራ 26፡18ን ያንብቡ፡፡ በዚህ ጥቅስ መሠረት በክርስቶስ ድነትን ባገኙ ሰዎች ላይ ምን ይሆናል? ይህንን እውነታ እርስም የተለማመዱት እንዴት ነው?

መስከረም 10
Sep 20

ጳውሎስ በመሪዎች ፊት

ጳውሎስ እየተናገረ ያለው ለአግሪጳ ቢሆንም በሐዋ. 26፡24 ላይ የመጀመሪያውን ምላሽ ሲሰጥ የምናገኘው ፊስጦስን ነው፡፡ ፊስጦስ ጳውሎስ ስለ ነፍስ አለመሞት እየተናገረ ቢሆን ኖሮ ግድ አይለውም ነበር፤ ነገር ግን ጥንታዊ የሮም ግሪካውያን እንኳን ሁለቱ እሳቤዎች ማለትም ነፍስ አትሞትምና የሙታን ትንሳኤ አብረው እንደማይሄዱ ያውቃሉ፡፡ ስለዚህ የመጀመሪያውን ተቀብለው ሁለተኛውን ኃሳብ ግን ተዉት፡፡ ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ላይ ሲናገር ወንጌል ለአህዛብ ሞኝነት ነው ያለው ለዚህ ነው(1ኛ ቆሮ. 1፡23)፡፡

ጨዋነት በተሞላበት መንገድ ጳውሎስ የሀሳቡን ትክክለኝነት ሊያስተውለውና እየተናገረ ያለው ከዕብራውያን ነብያት ጋር እንደሚስማማ ሊያረጋግጥ ለሚችለው ለአግሪጳ ኃሳቡን አቀረበ (ሐዋ. 26፡25-26)፡፡

ሐዋ. ሥራ 26፡27-28ን ያንብቡ፡፡ ለጳውሎስ ያልተጠበቀ ጥያቄ የአግሪጳ ምላሽ ምን ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የጳውሎስ ጥያቄ አግሪጳን አጣብቂኝ ውስጥ ከተተው፡፡ እንደ አይሁዳዊነቱ በቅዱስ መጽሐፍ ላይ ያለውን እምነት ሊክድ አይቻለውም፤ በሌላ በኩል ደግሞ አዎንታዊ ምላሽ ልስጥ ቢል ኢየሱስን መሲህ እንደሆነ ከመቀበል ውጪ ሌላ ምርጫ ላይኖረው ነው፡፡ ብልሃት የተሞላበት ምላሹ ግን ከገባበት ወጥመድ አስመልጦታል፡፡ “እንዲህ በቀላሉ ክርስትያን የምታደርገኝ ይመስልሃል?” የሚለው (ሐዋ. 26፡28ን ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ጋር ያነፃፅሩ) ከተለመደው የግሪኩ ትርጉም ማለትም “ክርስትያን ልታደርገኝ ጥቂት ቀረህ” ከሚለው የተሻለ ነው፡፡

የጳውሎስ ምላሽ ለወንጌል ያለውን ቆራጥ የሆነ አቋም ያንፀባረቀ ነበር ‹‹አሁንም ሆነ ወደፊት አንተ ብቻ ስትሆን ዛሬ የሚሰሙኝ ሁሉ ከዚህ ከታሰርኩበት ሰንሰለት በቀር እንደኔ ይሆኑ ዘንድ እግዚአብሔርን እለምናለሁ፡፡›› (ሐዋ. 26፡29) በንግግሩ ማሳረጊያ ላይ ጳውሎስ ሰሚዎቹ ነጻ እንደሆኑት ነፃ ይሆን ዘንድ አልተማፀነም፤ በዚህ ፈንታ ከታሰረበት ሰንሰለት በቀር እንደርሱ ይሆኑ ዘንድ ተመኘ፡፡ የጳውሎስ የወንጌል እንቅስቃሴ ግለት ለራሱ ደህንነት ከመጠንቀቅም ያለፈ ነበር፡፡

ሐዋ. ሥራ 26፡30-32ን ያንብቡ፡፡ አግሪጳ ጳውሎስ ንፁህ እንደሆነ ስለማመኑ የገለፀው እንዴት ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ፊስጦስ የአግሪጳን እርዳታ የፈለገው ሪፖርቱን ሙሉ ለማድረግ ብቻ ነበር (ሐዋ. 25፡ 25-27)፡፡ ጳውሎስ ለቄሳር ይግባኝ ማለቱ ቀድሞውኑ ተቀባይነት አግኝቷል (ሐዋ. 25፡12)፡፡ እስረኛው ጳውሎስ ከዚህ በኋላ በአገረ ገዥው ፍርድ ስር አልነበረም፡፡ ሐዋ. 26፡24-28ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ በስተመጨረሻ ይግባኝ ያለው ነገር ምን ነበር? ለእኛስ በእምነታችን የመጨረሻ ስልጣን ሊኖረው ስለሚገባው ነገር ምን ያስተምረናል? መስከረም 11

መስከረም 11
Sep 21

ተጨማሪ ጥናት፡-

እነዚያ ቃላት የአግሪጳን ኃሳብ ወደ ቀደሙት የቤተሰቦቹ ታሪክ እና ጳውሎስ እየተናገረለት ያለውን(ኢየሱስን) ለማስቆም ወደ ተደረገው ፍሬ አልባ ጥረት ትውስታ መልሰውት ይሆን? ስለ ቅድመ-አያቱ ሔሮድስና በቤተልሔም ስለተጨፈጨፉት ንፁሀን ጨቅላ ህፃናት አስቦ ይሆን? ስለ አያቱ ወንድም ስለ አንቲጳስና ስለተገደለው መጥምቁ ዮሐንስስ? የራሱ አባት ስለነበረው አግሪጳ(1ኛ)ና ስለ ሐዋርያው ያዕቆብ ሰማዕትነትስ? በነዚህ ነገስታት ወዲያው የመጡት ጥፋቶች እግዚአብሔር በርሱ አገልጋዮች ላይ በፈፀሙት ወንጀል ያልተደሰተ በመሆኑ ምክንያት የመጡ ስለ መሆናቸው ምልክት ሰጥቶት ይሆን? ይህ በደመቀ አቀባበል የታጀበ ስነ ስርአት በስልጣኑ ከርሱ ከፍ ብሎ ስለነበረውና በአንፀባራቂ ልብስ ስላሸበረቀው በዚያችም ከተማ ህዝቡ አምላክ ነው ብለው ስለጮሁለት ስለአባቱ ሁኔታ አስታውሶት ይሆን? ያ አድናቆት ከማብቃቱ በፊት እጅግ ጉረኛ በሆነው ንጉስ ላይ አስከፊና ፈጣን በቀል እንዴት እንደመጣ ረስቶ ይሆን? እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከአግሪጳ ትውስታ አልጠፉም ነገር ግን በፊቱ የሚታየው አስደናቂ ክስተት አእምሮውን ወሰደ፤ ኩራትና የራስ ክብር ክቡር ኃሳቡን አጠፉበት፡፡” Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, pp. 1066, 1067

የመወያያ ጥያቄዎች

1. በመወያያ ክፍሎቻችሁ ውስጥ ጳውሎስ ለቄሳርያ ይግባኝ ለመጠየቅ ስለ መወሰኑ ጉዳይ ተወያዩ፡፡ ውሳኔው ትክክል ነበርን? (ከሐዋ. 25፡25ና 26፡ 31-32 ጋር ያነፃፅሩ)? በእግዚአብሔር ጥበቃ ላይ ሙሉ በሙሉ ከመታመን ባለፈ ተገቢ በሆነ መንገድ ብልሃት የተሞላባቸውን ውሳኔዎች መወሰን የምንችለው እስከምን ድረስ ነው?

2. ጰውሎስ ለአግሪጳ የተናገረው ማለትም ‹‹እንግዲህ ንጉስ አግሪጳ ሆይ ከሰማይ ለታየኝ ራዕይ አልታዘዝም አላልኩም›› (ሐዋ. 26፡19) ይህ ስለ ጳውሎስ ምን ይነግረናል? እንደ ክርስትያንነታችን ለተጠራንበት ተልዕኮ ምን ያህል ታማኞች ነን(1 ጴጥ. 2፡9-10)?

3. ጳውሎስ ለሰዎች የጋለ ስሜትና ፍቅር ነበረው፡- ለቁጥር ብዛት ሳይሆን ለራሳቸው ለሰዎቹ፡፡ በቄሳርያ በነበረው የመጨረሻ ክስ ላይ ለአድማጮቹ የእርሱ የልቡ ጥማት ሁሉ እንደርሱ እንዲሆኑ ነበር፤ ያም በእግዚአብሔር ፀጋ እንዲድኑ ነበር (ሐዋ. 26፡29)፡፡ ለራሱ ነጻ መውጣት ወይንም ፍትህን ከመፈለግ ይልቅ እነርሱ የእግዚአብሔርን ማዳን እንዲለማመዱ ፈለገ፡፡ ከዚህ ምሳሌነት ምን የምንማረው ነገር አለ? ወንጌል ይስፋፋ ዘንድ ራሳችንን መስዋዕት ለማድረግ ምን ያህል ፈቃደኞች ነን?

4. አግሪጳ ከጳውሎስ አንደበት ወንጌልን ለመስማት እድልን አገኘ፡፡ ነገር ግን አልተቀበለውም፡፡ እንደዚህ አይነት ታላቅ እድሎች በፊቶቻችን ላይ ሳሉልን ሳያመልጡን በዕድሎቹ መጠቀም ያለብን እንዴት ነው? ማለትም መንፈሳዊነታችንን በዙሪያችን ካለው እውነታ ጋር ማዋሀድ የሚገባን እንዴት ነው?