የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ሰኔ 30- ሐምሌ 6

ሁለተኛ ትምህርት

Jul 7- 13


ጴንጤቆስጤ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡-ሐዋርያት ሥራ 2፡1-4፣ዮሃንስ 14፡16፣ ሐዋ.ሥራ 2፡5-13፣ ኢዮኤል 2፡28-32፣ ሐዋ.ሥራ 2፡22-39፣ መዝ.110፡1-3


መታሰቢያ ጥቅስ፡- “ይህን ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ከሞት አስነሳው፤ እኛም ሁላችን ለዚህ ነገር ምስክሮች ነን፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ፣ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው፡፡” /ሐዋሪያት ሥራ 2፡32-33/

“ጴንጤቆስጤ” የግሪክ ቃል ሲሆን የአይሁድን የሰባት ሱባኤ በዓል /ዘፀ.34፡ 22/ ለመግለፅ እንዲሁም በሌላ ስሙ የመከር በዓል /ዘሁልቅ 28፡26/ የሚባለውን ለመግለፅ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው፡፡ ጥሬ ቃሉ “ሃምሳኛው” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ከፋሲካ በዓል ቀጥሎ ባለው ቀን ከቀረበው የእህል ቁርባን ጀምሮ ሲቆጠር በ50ኛው ቀን ስለሚከበር ይህ ስም ተሰጥቶታል፡፡ የእስራኤል ሕዝብ “ከስንዴው መከር በኩራትን” በእግዚአብሔር ፊት ሲያቀርብ የደስታና የምስጋና ቀን ይሆን ነበር/ ዘፀ. 34፡22/፡፡ ይህ በዓል መንፈስ ቅዱስ ከሌላው ጊዜ ይልቅ በሙላት በቤተክርስቲያን ላይ በወረደበት ቀን ከተሰበሰበው መከር ማለትም በዚያ ቀን ከተጠመቁት ሶስት ሺህ ነፍሳት መከር ጋር ገጣሚ የሆነ ምልክት ሆነ/ሐዋ ሥራ 2፡41/፡፡ የክርስቶስን ማረግና በሰማያዊ ስፍራ መክበር ተከትሎ ይህ የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ድንገተኛና መለኮታዊ ክስተት ሲሆን ሐዋሪያቱን ከተራ ገሊላውያን ዓለምን ወደሚለውጡ ቆራጥና ብርቱ ሰዎች ለውጧቸዋል፡፡ በአብዛኛው ጴንጤቆስጤ የክርስቶስ ተከታይ የሆኑ አይሁድና በኋላም አሕዛብ እንደ አዲሱ በምድር ያለ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተቀባይነት ያገኙበት ስለሆነ የቤተክርስትያን ልደት ቀን ተብሎ ይጠራል፡፡ለሐምሌ 7 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ፡፡

ሐምሌ 1
Jul 08

የመንፈስ ቅዱስ አመጣጥ


የክርስቶስን ትዕዛዝ በመታዘዝ አማኞቹ ከልብ በሆነ ፀሎት፣ ምስጋናና ንስሐ በኢየሩሳሌም ቃል የተገባውን መንፈስ ቅዱስን እየጠበቁ ነበር፡፡ ያ ቀን ሲደርስ ሁሉም በአንድነት በአንድ ስፍራ”/ሐዋ.2፡1/፡፡ ምናልባት ሐዋርያት ሥራ 1 ላይ በተጠቀሰው በላይኛው ክፍል /ሰገነት/ ውስጥ ነበሩ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ብዙዎች ወደሚሰበሰቡበት ቦታ ሊሻገሩ ነበር/ሐዋ.ሥራ 2፡6-13/፡፡ ሐዋሪያት ሥራ 2፡1-3ን ያንብቡ፡፡ መንፈስ ቅዱስ በሚወርድበት ጊዜ ምን አይነት

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ታላቅ ክስተት ነበር፤ መጀመሪያ እንደ ታላቅ አውሎ ነፋስ አይነት ድምፅ ቤቱን በድንገት ሞላው፤ ከዚያም በዚያ በነበሩበት ራስ ላይ እንደ እሳት ነበልባል አይነት ነገሮች አረፉባቸው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ንፋስና እሳት በአብዛኛው ከመለኮታዊ ኃይል መገለጥ /ቲዮፋኒ/ ጋር ተገናኝቷል (ለምሳሌ ዘፀ. 3፡2፣19፡18፣ዘዳ. 4፡15)፡፡ በተጨማሪም ንፋስና እሳት የእግዚአብሔርን መንፈስ ለመግለፅም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል /ዮሐ.3፡8፣ ማቴ.3፡ 11/፡፡ ወደ ጴንጤቆስጤ ቀን ስንመጣ የክስተቱ ትርጉም ምንም ይሁን ምን በድነት ታሪክ ውስጥ የልዩ ቅፅበት ጅማሮ ምልክት ነበር፤ ያም ተስፋ የተገባው የመንፈስ ቅዱስ መውረድ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ሁልጊዜም በስራ ላይ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን ዘመን በነበሩ የእግዚአብሔር ሰዎች ላይም የመንፈስ ተፅዕኖ ግልፅ በሆነ ሁኔታ በተደጋጋሚ የተገለጠ ሲሆን በሙላት ግን አልተገለጠም፡፡ “በአበው ዘመን የመንፈስ ቅዱስ ተፅዕኖ በተደጋጋሚ በግልፅ የታየ ቢሆንም በሙላት ግን አልተገለጠም፡፡ የአዳኛቸውን ቃል በመታዘዝ ደቀመዛሙርቱ መንፈስ ቅዱስን እንዲልክላቸው ለመኑ፤ ክርስቶስም በሰማይ ማለደላቸው፡፡ አባቱ መንፈስ ቅዱስን በሕዝቡ ላይ ያፈስ ዘንድ ጠየቀ፡፡” Ellen G. white, the acts of the apostles, pg 37 መጥምቁ ዮሐንስ አስቀድሞ መሲሁ በመንፈስ እንደሚያጠምቅ የተናገረ ሲሆን /ሉቃ.3፡16ን ከሐዋ.ሥራ 11፡16 ጋር ያነፃፅሩ/ ኢየሱስም በተደጋጋሚ ስለዚህ ጉዳይ ተናግሯል /ሉቃስ 24፡49፣ሐዋ.ሥራ 1፡8/፡፡ ይህ የመንፈስ መውረድ ኢየሱስ በአባቱ ፊት ያደረገው የመጀመሪያ ምልጃው ነበር / ዮሐንስ 14፡16፣26፣15፡26/፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን ተስፋው ተፈፀመ፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን የተፈፀመው የመንፈስ ቅዱስ ጥምቀት ክርስቶስ በመስቀሉ ከተቀዳጀው ድልና በሰማይ ከመክበሩ ጋር የተያያዘ ልዩ ክስተት ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ መሞላት በአማኞች ህይወት በቀጣይነት መደገም ያለበት ልምምድ ነው፡፡ / ሐዋ.ሥራ 4፡8፣31፣11፡24፣ 13፡9፣ ኤፌ. 5፡18/ መንፈስ ቅዱስ በህይወትዎ እየሰራ ለመሆኑ ምን ማስረጃ አለዎት?

ሐምሌ 2
Jul 09

የልሳን ስጦታ


በሐዋርያት ሥራ 2፡4 ላይ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በልሳን ውስጥ ተገልጧል፡፡ ይህ ግን ከብዙዎቹ የመንፈስ ስጦታዎች አንዱ ብቻ ነበር /ሐዋ.ሥራ 10፡45-46፣19፡6/ ሌሎቹ ስጦታዎች የትንቢት /የወደፊቱን መናገር /ሐዋ.ሥራ 11፡28/፣ ራዕይ /ሐዋ.ሥራ 7፡ 55/ ስብከት /ሐዋ.ሥራ 2፡8፣28፡25/፣ መፈወስ /ሐዋ.ሥራ3፡6፣12፣5፡12፣16/ ለተለየ አገልግሎት መሾም /ሐዋ. 6፡3-5/ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ የልሳን ስጦታ በጴንጤቆስጤ ቀን የተሰጠው የመንፈስ ቅዱስ መኖር ብቸኛው መገለጫ ወይም በጣም ቅልቁ ማስረጃ ስለሆነ አይደለም፡፡ በዚህ ጊዜ የተገለጠው የቤተክርስቲያኗን አለም አቀፋዊ ተልዕኮ በይፋ ለማስጀመር ነበር፡፡ ይህ ማለት በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ የተሰጠው ተልዕኮ የልሳንን ስጦታ ይጠይቅ ነበር ማለት ነው፡፡ ሐዋርያቱ የባህልን ግድግዳ አልፈው እስከ ዓለም ዳርቻዎች በወንጌል አለምን ለመድረስ በሰሚዎቻቸው ቋንቋዎች መናገር ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ሐዋሪያት ሥራ 2፡5-12ን ያንብቡ፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን ሐዋርያቱ በዚያን ዘመን በነበሩ ሌሎች ቋንቋዎች ለመናገራቸው ምን ማስረጃ አለ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ከስምንት እስከ አስር ሚሊዮን አይሁዶች እንደነበሩ የሚገመት ሲሆን ከነዛ ውስጥ 60 በመቶው ከአይሁድ ውጪ ይኖሩ ነበር፡ ፡ ሆኖም በዓሉን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት አብዛኞቹ ከሌሎች አገሮች የመጡና አይሁዳውያን በጊዜው ይናገሩት የነበረውን አረማይክ ቋንቋ የማይናገሩ ነበሩ፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን ከተጠመቁት አብዛኞቹ ከሌሎች ሃገሮች የመጡና ወንጌሉን በራሳቸው ቋንቋ የሰሙ አይሁዶች ለመሆናቸው ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ሐዋርያት ከማይስተዋል ቋንቋ ይልቅ የሌሎች አገር ሰዎች በሚናገሯቸው ቋንቋዎች ለመናገራቸው ማስረጃው ድያሌክቶስ /ሐዋ.ሥራ 2፡6-8/ የሚለውና የአንድ አገር ወይም አካባቢ ቋንቋ የሚል ትርጓሜ ያለው ቃል ነው /ከሐዋ.ሥራ21፡40፣22፡2ና 26፡14 ጋር ያነፃፅሩ/፡ ፡ ስለዚህ በግልፅ በነዚህ የተለያዩ ቋንቋዎች ይናገሩ ነበር ማለት ነው፡፡ አስደናቂው ነገር ከሰዓታት በፊት ያንን ቋንቋ መናገር የማይችሉ የነበሩት ተራ የገሊላ ሰዎች አሁን መናገር መቻላቸው ነው፡፡ እነዚያን ቋንቋዎች የማያውቁት፣ በአካባቢው ይኖሩ የነበሩትና ይህንን ትዕይንት የተከታተሉት አይሁዳውያን እነርሱ የማይገባቸውን ቋንቋ ሲናገሩ ሲሰሙ ሐዋሪያት ጠጥተው እንደሰከሩ ገመቱ፡፡ “ሌሎች ግን እያፌዙባቸው ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል፡፡ አሉ፡፡” /ሐዋ. ሥራ 2፡13/ ታላቅ የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ እየተካሄደ በአይናቸው እያዩ እንኳን ስካር ብቻ ነው ብለው አሰቡ፡፡ እኛ ራሳችን መንፈሳዊ አይነ ስውሮች እንዳንሆን መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 3
Jul 10

የጴጥሮስ ስብከት


ጠጥታችሁ ሰክራችኋል መባላቸው ጴጥሮስ ምን እየተከሰተ እንደሆነ እንዲናገር እድል ሰጠው፡፡ በንግግሩ መጀመሪያ ሐዋርያውያ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ የትንቢት ፍፃሜ እንደሆነ በመጠቆም ወደ መጽሐፍ ቅዱስ አመላከተ /ሐዋ. ሥራ 2፡16-21/፡፡ ሐዋርያት ሥራ 2፡17ን ከኢዮኤል 2፡28 ጋር ያነፃፅሩ፡፡ የኢዮኤል ትንቢት የሚፈፀምበትን ጊዜ ጴጥሮስ እንዴት አስተዋለ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

የኢዮኤል ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ መውረድና በታላላቅ ተአምራት ስለሚገለፀው የወደፊት የመዳን ዘመን ነበር/ኢዮኤል 2፡32/፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን የተከሰተውን ክስተት ከእንደዚህ አይነት ትንቢት ጋር ጴጥሮስ ያያያዘው የክስተቱን ታሪካዊ ቦታ አጠንክሮ ለማስቀመጥ ስለፈለገ ነው፡፡ ኢዮኤልን ሲጠቅስ ግን አንድ አስፈላጊና ለየት ያለ ነገርን እናገኛለን፡፡ ወደ አንድ የወደፊት ጊዜ በሚያሳየውና ኢዮኤል “ከዚህ በኋላ” ባለው አገላለፅ ምትክ ጴጥሮስ “በመጨረሻው ዘመን” /ሐዋ. ሥራ 2፡17/ አለ፤ ይህም የታላቁ የመዳን(የድነት) ድራማ የመጨረሻ ተግባር እየጀመረ መሆኑን የሚያሳይ ነበር፡፡ ይህ በርግጥ የመጨረሻው ዘመን ክስተቶችን በሙላት የሚገልጽ ባይሆንም በተለይ የቀደመችዋ ቤተክርስቲያን እጅግ በፍጥነት ማድረግ ስላለባት ስራ እንደ ማስረጃ የሚቀመጥ ነበር፡፡ ፍፃሜው መቼ እንደሚሆን ባያውቁም ብዙ ሊቆይ እንደማይችል ግን ተረድተው ነበር፡፡

ሐዋርያት ሥራ 2፡22-32ን ያንብቡ፡፡ ጴጥሮስ ስለ ወንጌል በተናገረው ውስጥ ዋናው ነጥብ ምን ነበር? የጴንጤቆስጤውን ክስተት ትንቢታዊነት ከጠቀሰ በኋላ ጴጥሮስ ቅርብ ወደነበረው ወደ ኢየሱስ ህይወት፣ ሞትና ትንሳኤ ተሻገረ:: ትልቅ ትኩረት የተሰጠው ግን ትንሳኤው ነበር፤ ምክንያቱም በወንጌል ታሪክ ውስጥ ወሳኙን ሁኔታ ስለሚገልፅ ነበር፡፡ ለጴጥሮስ የክርስቶስ ትንሳኤ ተቀባይነት የማግኘቱ ብቸኛ መገለጫ /ሐዋ. ሥራ 2፡22፣27/ ሲሆን የትንሳኤውን ትርጉም ለመግለፅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ተጠቅሟል፡፡ ኢየሱስ መሲሁ/የተቀባው/ ስለነበር ሞት ሊይዘው አይችልም፡፡ ስለዚህ ለጴጥሮስና ለሌሎች የአዲስ ኪዳን ፀሐፊዎች የክርስቶስ ትንሳኤ ስለ መሲህነቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ስለ ድነት መልዕክት ጠንካራ ማስረጃ ሆነ፡፡ ሞት በዙሪያችን እኛንና በአካባቢያችን ያሉትን የምንወዳቸውን ሁልጊዜ እያስፈራራን ባለንበት ሁኔታ የኢየሱስ መነሳት አስፈላጊ እውነት የሆነው ለምንድነው?

ሐምሌ 4
Jul 11

የኢየሱስ መክበር


“ስለዚህ በእግዚአብሔር ቀኝ ከፍ ከፍ ካለ በኋላ የመንፈስ ቅዱስን ተስፋ ከአብ ተቀብሎ አሁን የምታዩትንና የምትሰሙትን አፈሰሰው፡፡”/ሐዋ. ሥራ 2፡33/ በንግግሩ በሦስተኛ ደረጃ ሰዎቹን በቅድሚያ ስለሳባቸው ስለ ልሳን ጉዳይ መናገር ጀመረ፡፡ ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ ያልተለመደ ከሆነው ጠጥቶ መስከር ይልቅ መንፈስ ቅዱስ ከሰማይ ስለፈሰሰባቸዉ በቋንቋቸው /በልሳን / እየተናገሩ ነበረ፡፡ ሐዋ.ሥራ 2፡33-36ን ያንብቡ፡፡ የኢየሱስ በእግዚአብሐር ቀኝ መክበርና የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ምን ግንኙነት አላቸው?

የእግዚአብሔር ቀኝ እጅ ስልጣንን የሚገልፅ ነው /መዝ.110፡1-3/፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመስርቶ ጴጥሮስ ሲሞግት ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ መንፈስን ያፈሰሰው በሰማይ ስለከበረ ነው ይላል፡፡ ያ መክበር ክርስቶስ በፊት ያልነበረውን ስልጣን የሰጠ አልነበረም (ዮሐንስ 1፡1-3፣17፡5) በተቃራኒው እንደ ጌታና እንደ አዳኝ ያለውን ቦታ አብ የገለፀበትን ሁኔታ ይወክላል (ሐዋ. ሥራ 2፡36)፡፡ ይህ ክስተት በርግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ወደሆነው መልዕክት ይመራናል፡- በመልካምና በክፉው መካከል ስለሚካሄደው ታላቁ ተጋድሎ፡፡ ነጥቡ ኢየሱስ ካልከበረ መንፈስ ቅዱስ በሙላት ሊመጣ አይችልም(ዮሐ. 7፡39)፤ኢየሱስ በመስቀል ላይ ድል ባያደርግ ደግሞ አይከብርም ነበር (ዮሐ. 17፡4-5)፡፡ በሌላ አማርኛ መንፈስ ቅዱስ ከመውረዱ በፊት ኢየሱስ መክበር ነበረበት፤ምክንያቱም ያ ሁኔታ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቀዳጀው ድል እንዲሁም የዚህ ዓለም ገዢነትን በጉልበቱ የወሰደው የሰይጣን ሽንፈት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱን የሚያሳይ ክስተት ስለነበረ ነው (ዮሐ. 12፡31)፡፡

የኃጢአት ወደ ዓለም መግባት በእግዚአብሔር ላይ ጥያቄ እንዲነሳ አድርጓል፡፡ የኢየሱስ መሞት ሰብአዊ ዘርን ለመዋጀት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፃድቅነትና የሰይጣንን ተንኮለኝነት ለማጋለጥ አስፈላጊ ነበር፡፡ በኢየሱስ አገልግሎት የተወደደችው የጌታ ዓመት ጀምራለች (ሉቃስ 4፡18-21)፡፡ አጋንንትን ሲያስወጣና ኃጢአትን ይቅር ሲል የሰይጣን ምርኮኞች የነበሩትን ነፃ እያወጣ ነበር፡፡ ሆኖም ያንን ለማድረግ ሙሉ ስልጣን የሚሰጠው መስቀሉ ነበር፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ራሱን መስጠት በሰማይ ተቀባይነትን ሲያገኝ ሰይጣን ታላቅ ሽንፈት ደረሰበት፤ ለክርስቶስ ዳግም ምፃት ህዝቦችን ለማዘጋጀትም መንፈስ ቅዱስ ወረደ፡፡

ሐምሌ 5
Jul 12

የመጀመሪያዎቹ ፍሬዎች


የጴጥሮስ አዳማጮች በተናገራቸው ቃላት ልባቸው ተነካ፡፡ አንዳንዶቹ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ እንዲሰቀል ከሚጠይቁት መካከል ሊሆኑ የሚችሉ ነበሩ (ሉቃስ 23፡ 13-25)፡፡ አሁን ግን የናዝሬቱ ኢየሱስ የተቀባው የእግዚአብሔር መሲህ መሆኑን አምነው ‹‹ምን እናድርግ?›› ብለው ጮኹ (ሐዋ. ሥራ 2፡37)፡፡ ሐዋ.ሥራ 2፡38ን ያንብቡ፡፡ ይቅርታን ለማግኘት ሁለቱ ቅድመ ሁኔታዎች ምንድናቸው?

ንስሐ ከሐዘን ወይም ፀፀት ስሜት ይልቅ የህይወት አቅጣጫ ለውጥ፣ ለኃጢአትም ጀርባን መስጠት ነው፡፡ ልክ እንደ እምነት ንስሐም የእግዚአብሔር ስጦታ ሲሆን ላለመቀበል መምረጥ እንችላለን (ሐዋ. ሥራ 5፡31-33፣26፡19-21፣ ሮሜ 2፡4)፡፡ ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ ንስሐ ከጥምቀት ጋር ተያይዟል (ማርቆስ 1፡4)፡፡ ማለትም ጥምቀት ከኃጢያት የመንፃትና በመንፈስ እንደገና የመወለድ ምልክት ሆኖ የንስሐ መገለጫ ሆኗል (ሐዋ. ሥራ 2፡38፣22፡16ን ከቲቶ 3፡5-7 ጋር ያነፃፅሩ)፡፡ ሐዋ.ሥራ 2፡38-39ን ያንብቡ፡፡ ንስሐ ለገቡና ለተጠመቁ ምን የተለየ ቃል ተገብቶላቸዋል?

በጴንጤቆስጤ የነበሩት ሰዎች ያገኙት የኃጢአትን ይቅርታ ብቻ ሳይሆን ለመንፈሳዊ ዕድገት፣በቤተክርስቲያን ለማገልገልና በዋናነት ወንጌልን ለማዳረስ የሚያግዘውን የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ነበር፡፡ ይህ ከበረከቶቹ ሁሉ የበለጠው ነው፤ ምክንያቱም ቤተክርስቲያን ያለችው የወንጌልን መልካም ዜና ለማካፈል ስለሆነ ነው (1 ጴጥ. 2፡9)፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጊዜ በኋላ ለመዳናቸው ማረጋገጫና ቤተክርስትያን ለተጠራችበት ተልዕኮ ለማብቃት የመንፈስ ቅዱስን ኃይል አግኝተዋል፡፡ ‹‹የኃጢአት ይቅርታ›› ማግኘታችንን መረዳታችን ወንጌልን ለመናገር ለሚፈልግ ሰው ሁሉ እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ቀድሞውኑስ ቢሆን እርስዎ ያ ተስፋ ከሌለዎት ለሌሎች ያንን ተስፋ እንዴት ሊሰጡ ይችላሉ?

ሐምሌ 6
Jul 13

ተጨማሪ ጥናት፡-


በጴንጤቆስጤ ቀን የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በሰማይ ስለተካሄደው ነገርና አብ ለኃጢአት የተደረገውን የክርስቶስን መስዋዕት የመቀበሉን እውነት ግልፅ አድርጓል፡፡ ይህ የመንፈስ ቅዱስ መውረድ በምድር ላይ መስዋዕት በመሆኑ ላይ የተመሠረተውን ክርስቶስ በሠማይ የሚሰራውን የምልጃ ሥራ በይፋ አስጀምሯል፡፡ እነዚህ አስደናቂ ክስተቶች ምድርና ሰማይ አሁን ሙሉ ለሙሉ ልናስተውል በማንችለው መልኩ የተቆራኙ (የተገናኙ) የመሆናቸው አስደናቂ እውነታ መገለጫ ናቸው፡፡ ‹‹የክርስቶስ ወደ ሰማይ ማረግ የርሱ ተከታዮች ቃል የተገባላቸውን በረከት ሊቀበሉ እንደሆነ ምልክት የሚሆናቸው ነበር፡፡… ክርስቶስ የሰማይን በሮች አልፎ ሲገባ መላዕክት በውዳሴ አጅበውት ነበር፡፡ይህ ስርዓት እንደተጠናቀቀ መንፈስ ቅዱስ በሐዋሪያት ላይ በታላቅ ኃይል ወረደ፤ ክርስቶስም ከጥንት ጀምሮ በአባቱ ዘንድ በነበረው ክብር ከበረ፡፡ በጴንጤቆስጤ ቀን መንፈስ ቅዱስ መውረዱ ሰማይ የአዳኙ አገልግሎት መጀመሩን ያሳወቀበት ክስተት ነበር፡፡ ቃል እንደገባው እንደ ካህንና ንጉስ በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ስልጣን መቀበሉን በሚገልፅ ሁኔታ ለተከታዮቹ መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል፡፡›› Ellen G.white, The Acts of the Apostles, PP.38,39


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ዛሬ ቤተክርስቲያን በጴንጤቆስጤ ቀን ከሆነው የትኛውን ልትጠብቅ ይገባታል? የሚደገመው የትኛው ነው? የማይደገመውስ የቱ ነው? 2. ጴጥሮስ በመልዕክቱ የኢየሱስን ትንሳኤ እጅግ ጠቃሚ አድርጎ ማስቀመጡ ላይ ያሰላስሉ፡፡ ትንሳኤውን እጅግ አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ አይሁዶች ስለ መሲሁ የሚጠብቋቸው ነገሮች ቢኖሩም መሲሁ ከሞት ይነሳል ብሎ የሚጠብቅ ማንም አልነበረም፡፡ ይህ በማንም መንፈሳዊ ግምት ውስጥ ስለ መሲሁ በነበራቸው ምልከታ ውስጥም አልነበረም፡፡ በዘመናችን ከሚስተማሩትና ብዙ እውቅና ከተሰጣቸው ትምህርቶች በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ በነዚያ ጉዳዮች ላይ ስለሚናገረው ነገር ማወቅ ያለብን ለምንድነው? 3. ሐዋ. ሥራ 2፡38 ስለ ጥምቀት አስፈላጊነት ይናገራል፡፡ ስለዚህ ይህ ማለት አንድ በየሱስ ያመነና ከመጠመቁ በፊት የሞተ ሰው ይጠፋል ማለት ነው? መልስዎትን ያብራሩ::