የሐዋሪያት ስራ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2018

ሐምሌ 21-27

አምስተኛ ትምህርት

Jul 28 - Aug 3


የጳውሎስ መለወጥ



ሰንበት ከሰዓት

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብበው ለዚሀ ሳምንት ትምርት ይዘጋጁ፡- ሐዋ.26፡9-11፣ ዘዳ.21፡23፣ ሐዋ.9፡1-20፣ 1ኛ ቆሮ.9፡1፣ ገላ.1፡1፣ ሐዋ.9፡20-30፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ፡-‹‹ሂድ! ይህ ሰው በአሕዛብና በነገስታት ፊት እንዲሁም በእስራኤል ሕዝብ ፊት ስሜን እንዲሸከም የተመረጠ እቃዬ ነው፡፡›› (ሐዋ.9፡15)

የ ጠርሴሱ ሳውል (በኋላ ጳውሎስ የተባለው) መለወጥ በሐዋሪያት ቤተክርስቲያን ታሪክ ከተከናወኑ አስደናቂ ክስተቶች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሆኖም የጳውሎስ ጥቅም ከመለወጥ ያለፈ ነው፤ ምክንያቱም ለቤተክርስቲያን ባላንጣ ከነበሩት ውስጥ ተለውጦ ቀናተኛ ክርስቲያን በመሆን ጳውሎስ ብቸኛው ሰው አልነበረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ግን ወሳኙ ጉዳይ ለወንጌል ሲል ከሰራው ገድል ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ጳውሎስ ለቀደምት አማኞች ወደኋላ የማይል ተቃዋሚ ሲሆን በዚያች ጨቅላ በሆነችዋ ቤተክርስቲያን ላይ ብዙ አስከፊ ነገር ሊፈፅም ይችል ነበር፡፡ ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት ከነበረው ቁርጠኝነት በተጨማሪ የባለስልጠኖች እገዛ ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገር ግን በደማስቆ መንገድ ላይ ሲሄድ የመጣለትን የእግዚአብሔርን ጥሪ በታማኝነት ሳያመነታ ተቀበለና ከሐዋሪያትም ሁሉ የላቀ ስፍራን ያዘ፡፡ ‹‹ከነዚያ መራርና ምህረት የለሽ የክርስቶስ ቤተክርስቲያን አሳዳጆች መሃል ቤተክርስቲያንን የሚጠብቅና ወንጌልን በስኬታማነት የሚያበስር ሰው ብቅ አለ››Ellen G. white, sketches from the life of Paul, P.9:: ጳውሎስ ቀድሞ ሲያደርግ የነበረው ቀዳሚዋን ቤተክርስቲያን የማሳደድ ተግባሩ ያልተገባ ስለመሆኑ በጥልቀት እንዲረዳ ቢያደርገውም የእግዚአብሄር ፀጋ በርሱ ላይ ከንቱ ሆኖ እንዳልቀረ በማሰብ ከልቡ ያመሰግናል፡፡ በጳውሎስ መለወጥ ምክንያት ክርስትና ለዘላለም ተቀየረ፡፡

የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለ ሐምሌ 28 ሰንበት ይዘጋጁ፡፡

ሐምሌ 22
Jul 29

የቤተክርስቲያን አሳዳጅ


ጳውሎስ የግሪክ ሥር ያለው አይሁዳዊ ነበር፡፡ የተወለደውም የኪልቅያ ዋና ከተማ በሆነችው ተርሴስ ነው (ሐዋ.21፡39)፡፡ ሆኖም ወደ እየሩሳሌም መጥቶ በጊዜው ታላቅ በነበረው ፈሪሳዊ አስተማሪ ገማልያል ስር በመማሩ (ሐዋ. 22፡3) በተወሰነ መልኩ ከግሪካዊነት ዘረኝነት አፈንግጧል፡፡ እንደ ፈሪሳዊነቱ ጳውሎስ ወግ አጥባቂ ቢሆንም ቅናቱ ወደአክራሪነት መራው(ገላ.1፡14)፡፡ እስጢፋኖስ ወደ ሞት እንዲሄድ የመራውና በማሳደድ ሂደት ውስጥ ቁልፍ ሚና የተጫወተው ለዚህ ነው ፡፡ ሐዋ.26፡9-11ን አንብቡ፡፡ ጳውሎስ እንዴት ቤተክርስቲያንን ይቃወም እንደነበረ የገለፀው በምን መልኩ ነበር?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ በሌላ ስፍራ ላይ ወንጌል ለአይሁድ መሰናከል እንደሆነ ተናግሮአል(1ቆሮ.1፡ 23)፡፡ የሱስ አይሁዶች እንደጠበቁት ንጉስ ሆኖ ስላልመጣና የእግዚአብሄር ቃል እንደሚናገር “በመስቀል የሚሰቀል የተረገመ ነው” (ዘዳ. 21፡23) ስለሚል በመስቀል ላይ የተሰቀለን መሲህ መቀበል አዳገታቸው፡፡ ስለዚህ ለአይሁዳውያን ስቅለቱ በራሱ ከጠበቁት ጋር ስለተጋጨባቸው ቤተክርስቲያን ስለ የሱስ የነበራት ግልፅ መረጃ ራሱ ሀሰት ሆነባቸው፡፡

ሐዋ.9፡1-2 እንደሚተርክልን የተርሴሱ ሳውል አማኞችን ተቃውሞ ወደ እንቅስቃሴ ገባ፡፡ ደማስቆ ከእየሩሳሌም በስተሰሜን አቅጣጫ መቶ ሰላሳ አምስት ማይል የሚርቅና አይሁዶች ተከማችተው የሚገኙበት ትልቅና ወሳኝ ከተማ ነበር፡፡ ከአይሁድ ውጪ የሚኖሩ አይሁዳውያን ዋና መቀመጫቸው እየሩሳሌም (የሸንጎ ስፍራ) በሆኑ ማህበራት የተሳሰሩ ሲሆን ምኩራቦቻቸው ደግሞ ለአገሬው ማህበረሰብ እንደ ዋነኛ ማዕከላት ይቆጠሩ ነበር፡፡ በሸንጎውና በእነዚህ ማህበራት መካከል የማያቋርጥ የደብዳቤ ልውውጥ ያለ ሲሆን ይህንንም ደብዳቤ የሚያደርሰው ሻሊያ “ Shaliah” ወይም ልዑክ (የተላከ) ነበር::ይህ ልዑክ ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችን እንዲሠራ በሸንጎው የተሾመ ባለስልጣን ነው፡፡

ጳውሎስ የሸንጎውን መሪ ሊቀ ካህን በደማስቆ ለሚገኙት ምኩራቦች ደብዳቤ ለማድረስ ሲጠይቅ ሻሊያ ሆኖ የየሱስ ተከታዮችን በሙሉ እያሰረ ወደ እየሩሳሌም እንዲያመጣ ስልጣን ተሰጠው ማለት ነው (ከሐዋ. 26፡12 ጋር ያነፃፅሩ):: በግሪኩ “shaliah” ለሚለው ቃል አቻ የሚሆነው ቃል Apostolos(አፖስቶሎስ)የሚለው ሲሆን ሐዋሪያ(apostle) የሚለው ቃል የመጣውም ከዚህ ቃል ነው፡፡ ስለዚህ ጳውሎስ የየሱስ ክርስቶስ ሐዋሪያ ከመሆኑ አስቀድሞ የሸንጎው ሐዋሪያ ነበር ማለት ነው፡፡

መቼ ነው እርስዎ ለመጨረሻ ጊዜ (ለማይጠቅም ነገር) ቀናተኛ የሆኑትና በኋላ ግን ሀሳቦን የቀየሩት? ከዚህ የህይወት ተሞክሮዎ ምን ይማራሉ?

ሐምሌ 23
Jul 30

በደማስቆ መንገድ ላይ


ሐዋ.9፡3-9ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ወደ ደማስቆ እየተቃረበ ሲመጣ ምን ገጠመው? በሐዋ.9፡5 ላይ የሱስ የተናገረው ቃል ወሳኝነት ምን ያህል ነው (ሐዋ.26፡14ን ይመልከቱ)?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስና አብረውት የነበሩ ሰዎች ወደ ደማስቆ ሲቃረቡ ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ፡ ፡ በቀትር ፀሐይ ሃይለኛ ብርሃን በራባቸው አንድ ድምጽም ተናገራቸው፡፡ በትንቢት አንፃር እንደምናየው አይነት ራዕይ ሳይሆን በተለይ ለጳውሎስ የታሰበ መለኮታዊ መገለጥ ነበረ፡፡ አብረውት የነበሩት ብርሃን ያዩ ቢሆንም የታወረው ጳውሎስ ብቻ ነበር፤ ድምጹን ቢሰሙም ነገሩን ያስተዋለው ጳውሎስ ብቻ ነበር፡፡ ብርሃኑ ከሞት የተነሳው የየሱስ መለኮታዊ ክብር ሲሆን ለጳውሎስም በዚያች ቅጽበት ለግሉ ተናገረው(ሐዋ.22፡ 14)፡፡ በሌላ ስፍራ ጳውሎስ የሱስን እንዳየው በማረጋገጥ የእርሱን ትንሳኤ ለማወጅ ሐዋሪያዊ ስልጣን እንዳለውና በዚህም ከአስራ ሁለቱ ሐዋሪያት ተርታ እንደሚሰለፍ ይናገራል (1ቆሮ. 9፡1፣15፡8)፡፡

ጳወሎስ ከየሱስ ጋር ያደረገው ንግግር ከብርሃኑ በበለጠ ልቡን ሰብሮታል፡፡ ጳውሎስ የሱስ የናዝሬቱን የሚከተሉ አማኞችን ማሳደድ አይሁዳዊነትን ከሚያረክስና አደጋ ላይ ከሚጥል ነገር በመከላከል የእግዚአብሄርን ስራ እያከናውነ እንዳለ በፍጹም ልቡ አምኖ ነበር፡፡ ነገር ግን እርሱ በስራው ያፍር ዘንድ የሱስ ህያው እንደ ሆነ ከማመንም ባለፈ በአማኞች ላይ ያደርስ የነበረው ስቃይና እንግልት በየሱስ በራሱ ላይ እያደረሰ እንደሆነም ተረዳ፡፡

የሱስ ከጳውሎስ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ጳውሎስ ሊገነዘበው በሚችለውና የግሪክ መነሻ አለው ተብሎ በሚታመን ምሳሌያዊ ንግግር አስጠነቀቀው፡- ‹‹የመውጊያውን ብረት ብትረግጥ ላንተ ይብስብሃል››(ሐዋ.26፡14)፡፡ ምስሉ ልክ በቀንበር ውስጥ ያለ በሬ ከቀንበሩ በሌላ አቅጣጫ ለመሄድ ሲጣጣር የሚሆነውን ትዕይንት ይገልጻል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ይህ እንስሳ የበለጠ ራሱን እየጎዳ ይመጣል፡፡

ይህ አባባል በጳውሎስ አዕምሮ ውስጥ የነበረውን ሙግት የሚያሳይ ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይህ የመንፈስ ቅዱስ ስራ እንደሆነ በማረጋገጥ(ዮሐ.16፡ 8-11) በእስጢፋኖስ ላይ የሆነውን ነገር ያስታውሰናል፡፡ ‹‹ሳኦል እስጢፋኖስ ወደ ሸንጎ ቀርቦ እንዲፈረድበት በማድረግ ትልቁን ድርሻ የተወጣ ሲሆን ከሰማዕቱ ጋር የእግዚአብሄርን መገኘት የሚያሳዩ አስደናቂ ማስረጃዎች የየሱስን ተከታዮች በማሳደድ ፅድቅ ይገኛል ብሎ ማመኑን እንዲጠራጠር አደረገው፡፡ አዕምሮው እረፍት እስኪያጣ ደረስ ተበጠበጠ፡፡ በዚህ ግራ መጋባት ውስጥ ሆኖ ጥበብና ቅን ፍርድ አላቸው ብሎ ሙሉ መተማመን ለጣለባቸው ሰዎች አቤት ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡ ከገዥዎችና ካህናት ጋር ባደረገው ክርክርም እስጢፋኖስ የእግዚአብሄርን ስም የተሳደበ ሰው እንደሆነ አመነ፡፡ ሰማዕቱ የሰበከው ክርስቶስ አጭበርባሪ እንደነበርና በትልልቅና ቅዱስ ስፍራ ያሉ አገልጋዮች ትክክል እንደሆኑ አመነ፡፡›› Ellen G. white, The acts of the Apostles, Pp.112,113፡፡ ህሊናችሁን በደንብ ማድመጥ ብልህነት ያለው አካሄድ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 24
Jul 31

የአናንያ ጉብኝት


ሳኦል እየተነጋገረ ያለው ከየሱስ ጋር መሆኑን ሲረዳ የሱስ በርሱ እንዲሰራ እድል የሚሰጥን ጥያቄ ጠየቀ ‹‹ጌታ ሆይ ምን ላድርግ?›› (ሐዋ. 22፡10)፡፡ ጥያቄው እስከዚያች ሰዓት ድረስ ስላደረጋቸው ነገሮች መፀፀቱን ቢያመለክትም ከዚህ በላይ ግን ከዚያን ሰአት አንስቶ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሱስ እንዲመራው ፈቃደኛ መሆኑን አመላካች ነበር፡፡ ሳኦል ወደ ደማስቆ ከተወሰደ በኋላም ተጨማሪ መመሪያ ለመቀበል መጠበቅ ነበረበት፡፡

በሐዋ.9፡10-19 ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ሲተርክልን ጌታ የደማስቆው ሳኦል ሐዋሪያው ጳውሎስ ሆኖ ለሚኖረው አዲስ ህይወት እንዴት እንዳዘጋጀው ይናገራል፡፡ የሱስ በራዕይ አናንያ ጳውሎስን ሄዶ እንዲጎበኘውና አይኑም ያይ ዘንድ እጁን እንዲጭንበት ተናገረው፡፡ አናንያ ደግሞ ቀድሞውኑ ሳኦል ምን አይነት ሰው እንደሆነና ወገኖች በብዙ እንዲሰቃዩና ብሎም ህይወታቸውን እንዲያጡ ማድረጉን ያውቃል፡፡ ሳኦል ወደ ደማስቆ ለምን አላማም እንደሚሄድ ተነግሮታል በዚህ የተነሳ ወደርሱ ሄዶ የመጀመርያው የጥቃቱ ሰለባ መሆን አይፈልግም፡፡ በዚህ ምክንያት ማቅማማቱ ሊስተዋል የሚገባ ነው፡፡

ነገር ግን አናንያ ያላወቀው ነገር ቢኖር ሳኦል ከየሱስ ጋር ፊት ለፊት መገናኘቱንና በዚህም የተነሳ ህይወቱ ለዘላለም መቀየሩን ነው፡፡ ይህንን ባይረዳም አናንያን ይድነቅህ ሲለው ጳውሎስ ለሸንጎው ከመስራት ይልቅ ለየሱስ ይሰራ ዘንድ ተጠርቷል፡፡ ይህም ማለት ከዚህ በኋላ ሳኦል የሸንጎው ሐዋሪያ ሳይሆን ወንጌልን ለአይሁድና ለአህዛብ የሚያደርስ ለየሱስ የተመረጠ ዕቃ ሆኗል ማለት ነው፡፡

ገላ.1፡1፣11-12ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ሐዋሪያዊ አገልግሎቱን በተመለተ ከምን የመነጨ እንደሆነ ተናገረ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በገላትያ መጽሐፍ ጳውሎስ መልእክቱን የተቀበለውና ሐዋሪያነቱን ያገኘው ከሰው ሳይሆን ቀጥታ ከየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡ ሆኖም አናንያ በጳውሎስ መጠራት ውስጥ የተጫወተው ሚና ይህንን ይቃወማል ማለት አይደለም፡፡ የአናንያ ጉብኝት ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ ላይ ከየሱስ የተቀበለውን ተልእኮ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እውነት ለመናገር በሳኦል ላይ የታየው የህይወት ለውጥ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ በሰብአዊ ተፅዕኖ ምክንያት እንደመጣ ለማሰብ የማይቻል ነው፡፡ የየሱስ ቀንደኛ ተቃዋሚ የነበረው ሰው እንዴት ብሎ በድንገት ሁሉን ትቶ ማለትም ዝናውን፣ ቀድሞ የነበረውን ስራና የፀና እምነቱን ትቶ የሱስን እንደ አዳኙና ጌታው በመቀበል የተሰጠ አስደናቂ ሐዋርያ ስለመሆኑ ሊገልፅልን የሚችለው መለኮታዊ ሀይል ብቻ ነው፡፡ የሳውል መለወጥ የእግዚአብሄርን አስደናቂ ፀጋ የገለጸው በምን መንገድ ነው? በህይወትዎ አይመለሱም የምትሏቸው ሰዎች ሳይቀር ወደ እውነተኛው እምነት ሊመጡ እንደሚችሉ ይህ ታሪክ ምን ያስተምራል?

ሐምሌ 25
Aug 01

የጳውሎስ አገልግሎት ጅማሮ


ሐዋ.9፡19-25 እንደሚያስቀምጥልን ጳውሎስ ከተቀየረ በኋላ ወደ እየሩሳሌም ከመመለሱ በፊት ለጥቂት ጊዜ በደማስቆ ቆይቷል(ሐዋ.9፡26) ፡፡ እንደውም ገላ.1፡ 17 ላይ ጳውሎስ ሲያክል ወደ እየሩሳሌም ከመመለሱ አስቀድሞ ለብቻው ጥቂት ወደኖረበት አረብ አገር ሄዷል፡፡ ‹‹በዚያ ገለልተኛ ሆኖ በበረሃ ሲኖር ጳውሎስ ለማጥናትና ለማሰላሰል ሰፊ ጊዜን አገኘ፡፡›› Ellen. G white, The Acts of the Apostles, P.125::

ሐዋ.9፡20-25ን ያንብቡ፡፡ ሉቃስ ጳውሎስ በደማስቆ የነበረውን አገልግሎት እንዴት አደርጎ ነበር የገለጸው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጳውሎስ ከሊቀ ካህናት የተቀበለውን ደብዳቤ ይዞ ከየእሩሳሌም ለቆ የሄደበት አላማ ያነጣጠረው በደማስቆ ምኩራቦች ጥገኛ ሆነው እየኖሩ ባሉ አይሁድ አማኞች ላይ ነው (ሐዋ. 9፡2)፡፡ አሁን ከአረብ አገር ከመጣ በኋላ ግን ወደነዚያ ምኩራቦች መጣ፡ ፡ አማኞችን ለማሰር ሳይሆን እንደውም ቁጥራቸውን ለመጨመር፤ የሱስ አሳሳች ነው ብሎ ስሙን ለማጥፋት ሳይሆን ነገር ግን የእስራኤል መሲህ እንደሆነ ለማወጅ ወደነርሱ መጣ፡፡ አሳዳጃቸው እንደሆነ የሚያውቁት ሰው ስለ የሱስ ሲመሰክር ሲሰሙ በአዕምሮአቸው ውስጥ ምን ይመላለስ ይሆን? የጠርሴሱ ሳኦል ስለ መለወጡና ለቤተክርስቲያን ስላደረገው ነገር በማሰብ ከመደመም በቀር ምን ሊያደርጉ ይችላሉ? (ይህ አዲስ የተለወጠ ሰው የኋላ ኋላ ስለሚፈጥረው ትልቅ ተጽእኖ ምናልባት ማናቸውም ላይገምቱ ይችላሉ)፡፡

አንዳንድ ጳውሎስን ይቃወሙ የነበሩ ሰዎች ኃሳቡን ሊሞግቱ ባይቻላቸውም ህይወቱን ግን ሊያጠፉ አድመውበት ነበር፡፡ ጳውሎስ ታሪኩን እንደገለፀው (2ቆሮ.11፡32-33) የርሱ ባላንጣዎች በስፍራው በሚገኙ ባለ ስልጣናት ፊት ስሙን በማውገዝ አለማቸውን ለማሳካት አልመው ነበር፡፡ ነገር ግን አማኞች ጳውሎስን በከተማው አጥር በመስኮት በኩል በቅርጫት አድርገው አስመለጡት፡፡

ጳውሎስ ተግዳሮት እንደሚገጥመው ቀድሞውኑ ተገንዝቧል (ሐዋ. ሥራ 9፡16)፡ ፡ተቃውሞ፣ ስደት እና ስቃይ ከተለያየ አቅጣጫ በሚያደርገው አገልግሎቱ ላይ ሳይቋረጥ እንደሚመጣበት ያውቃል፡፡ ነገር ግን ከየሱስ ጋር በጀመረው አዲስ ህይወት በእያንዳንዱ እርምጃው የሚገጥሙት ግድድሮሾች እምነቱን አላናወጡትም፤ ተግባሩንም አልገቱትም(2ቆሮ.4፡8-9)፡፡

ብዙ ተግዳሮትና ተቃውሞ ቢደርስበትም ጳውሎስ ግን ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠም፡፡ በተስፋ መቁረጥ እና ተቃውሞ መሃል ሆነን በእምነታችን ፅኑዎች መሆን እንደሚገባን እንዴት ልንማር እንችላለን?

ሐምሌ 26
Aug 02

ወደ እየሩሳሌም መመለስ


ከደማስቆ ካመለጠ በኋላ ጳውሎስ አሳዳጅ ሆኖ ወደ ወጣበት እየሩሳሌም ለመጀመሪያ ጊዜ ተመለሰ፡፡ ይህ የሆነው ከተለወጠ ከሦስት አመታት በኋላ ነው(ገላ.1፡ 18)፡፡ ችግሮች ከቤተክርስቲያን ውስጥና ውጪ እየገጠሙት ባለበት ወቅት ወደ እየሩሳሌም መመለስ ቀላል አልነበረም፡፡ ሐዋ.ሥራ 9፡26-30ን ያንብቡ፡፡ ጳውሎስ ወደ እየሩሳሌም ሲደርስ ምን ገጠመው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

በእየሩሳሌም ጳውሎስ ከሐዋሪያት ጋር አብሮ ለመቀላቀል ጣረ፡፡ ክርስትያን ሆኖ ለሦስት አመታት ከቆየ በኋላ ቢመጣምሐዋሪያት ልክ ቀደም ብሎ አናንያ እንዳደረገው መለወጡን የተመለከቱት በጥርጣሬ አይን ነበር፡፡ ነገሩ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ ድራማ አድርገው በማሰብ ስጋት ውስጥ ገቡ፡፡ በቆጵሮስ ይኖር የነበረው ሌዋዊው በርናባስ (ሐዋ.4፡36-37) ነበር የሐዋሪያትን ተቃውሞ ጥሶ ጳውሎስን ወስዶ ያስተዋውቃቸው፡ ፡ እነርሱም ቢሆኑ የእውነቱን መሆኑን ሲረዱ እግዚአብሄር በጳውሎስ ላይ ስለሰራው ስራ ተደንቀዋል፡፡

እንዲህ አይነት ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ይወገዳል ማለት አይቻልም፡፡ ጳውሎስ ቀድሞ ቤተክርስቲያንን ሲያሳድድ ስለነበረ ባይሆን እንኳን በሰበከው ወንጌል ምክንያትየማይቀር ነበር፡፡ የእስጢፋኖስንም ታሪክ ስናይ አይሁዳውያን አማኞች ሐዋሪያትን ጨምሮ በብሉይ ኪዳን ስርአት በተለይም መስዋዕት የማቅረብ ስርአት በየሱስ የመስቀል ሞት መደምሰሱን የሚያምኑትን መሰረታዊ የክርስትና እምነት ለመረዳት እጅግ ዘግይተው ነበር፡፡ ጳውሎስ በይሁዳ ቤተክርስቲያን የነበረው የጠበቀ ግንኙነት ከበርናባስ በተጨማሪ በጥንት ግሪክ ይኖሩ ከነበሩት አማኞች ጋር ነበር፡፡ ከሰባቱ መካከል አንዱ ሆኖ የተመረጠው ፊሊጶስ (ሐዋ.21፡8) እንዲሁም የቆጵሮሱ ሚናሶንም ይገኝበት ነበር (ሐዋ.21፡16)፡፡ ከአያሌ አመታት በኋላ የእየሩሳሌም ቤተክርስቲያን መሪዎች ጳውሎስን እስጢፋኖስ ሲሰብክ የነበረውን ትምርህት ይሰብካል በሚል ክስ አቀረቡበት (ሐዋ.21፡21)፡፡

ለ15 ቀናትበእየሩሳሌም በቆየባቸው ቀናት (ገላ.1፡18) ጳውሎስ ከጥቂት ጊዜያት በፊት እስጢፋኖስን ለማስወገር ላነሳሳቸውና አማኝ ላልሆኑት አይሁዳውያን በግልጽ ወንጌልን ለማካፈል ወሰነ፡፡ ልክ እንደ እስጢፋኖስ ጥረቱ ለህይወቱ እስኪያሰጋው ድረስ ከባድ ተቃውሞን አመጣበት፡፡ የሱስ በራዕይ ተገልጦ ለደህንነቱ ሲል እየሩሳሌምን ለቆ እንዲሄድ ተናገረው (ሐዋ.22፡17-21)፡፡ በወገኖች እገዛ ወደ ቄሳርያ ከተማ ሄደ ከዛም ይኖርበት ወደነበረበት ከተማ ወደ ኬልቂያ በመሄድ የወንጌል ጉዞውን ከመጀመሩ በፊት ለብዙ አመታት ቆየ፡፡

ሐምሌ 27
Aug 03

ተጨማሪ ጥናት፡


‹‹ በጦርነት አውድማ የተሰዋ ጄነራል ለራሱ ወታደሮች ሽንፈት ቢሆንም ሞቱ ለጠላቶቹ ምንም ያህል ተጨማሪ ጥንካሬን አያመጣላቸውም፡፡ ይህ የታወቀ ሰው የተቃዋሚውን ሃይል ሲቀላቀል አገልግሎቱ ብቻ አልነበረም የጠፋው የተቀላቀላቸው ሰዎች ግን በርሱ መኖር ተጠቃሚ ሆኑ፡፡ የጠርሴሱ ሳውል ደማስቆ መንገድ ላይ ሳለ በቀላሉ በጌታ ሀይል ተመቶ ሊሞት እና አሳዳጅ የነበሩ ሃይሎች ጥንካሬያቸው ሊዳከም ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን እግዚአብሄር በበጎ ፈቃዱ የጳውሎስን ህይወት መታደግ ብቻ ሳይሆን ለወጠውና ጀግናውን ከጠላት ወገን ወደ የሱስ ወገን አሸጋገረው፡፡››-Ellen G. white , The Acts of the Apostles, P.124. ‹‹ ክርስቶስ ደቀመዛሙርቱን ወደ አህዛብ ሁሉ ሄደው እንዲሚያስተምሩ አዘዛቸው፡ ፡ ነገር ግን ቀድሞ ከአይሁድ የተማሩት ትምህርት ስለነበር የጌታቸውን ቃል ሙሉ በሙሉ ለመያዝ ተቸግረው ነበር፡፡ ስለዚህም ወደ ተግባር ለመግባት ከብዙ አመታት በኋላ ነበር ጌታ ወደ ሰማይ ሲያርግ የየሱስን ቃላት በሙላት ለመረዳት አዕምሮአቸው ክፍት መሆን የጀመረውና አህዛብ ብሎም አይሁዳውያንን ይለውጡ ዘንድ ስራ መስራትን የጀመሩት፡፡›› Ellen. G wihte, sketches form the life of paul, P38.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. በደማስቆ መንገድ ላይ የሱስ ጳውሎስን በጠየቀው ጥያቄ ላይ ሙሉ ትኩረትዎን ያድርጉ ‹‹ ለምን ታሳድደኛለህ›› (ሐዋ.9፡4)፡፡ ለጳውሎስ ይህ ጥያቄ የሱስ የናዝሬቱ በእርግጥም ከሞት ስለመነሳቱ ያረጋገጠለት ክስተት ነበር፡፡ ከዚሀ በላይ ግን በየሱስ እና በቤተክርስቲያን መካከል ያለውን መንፈሳዊ ተዛምዶ ያመለክታል (ማቴ.25፡34-45ን ተመልከቱ)፡፡ የሚያሳየን ነገር ግልጽ ነው ቤተክርስቲያን ላይ የደረሰ ጉዳይ በሙሉ የሱስ ላይ የደረሰ ጉዳት ነው፡፡ ተግባራዊ በሆነ ሁኔታ ስንቃኘው ዛሬ ይህ ለኛ ምን አይነት ትርጉም አለው?

2. ለየሱስ መመስከር ለየሱስ ሲሉ ስቃይ መቀበልን ያካትታል፡፡ የግሪኩ ስርወ ቃል ‹‹ መመስከር ›› የሚለውን ቃል ከስቃይ ጋር ያዛመደው በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ለየሱስ ሲሉ ስቃይ መቀበል ማለት ምን ማለት ነው?

3. የጥንት የላቲን አባባል አለ ‹‹አስተውል ዘንድ አምናለሁ›› የሚል ይህ አባባል በጠርሴሱ ሳውል ላይ ከደረሰው ነገር አኳያ ምን እንድናስተውል ያደርገናል? ይህም ማለት ጳውሎስ ከመለወጡ አስቀድሞና በየሱስ ከማመኑ በፊት ምንም የተረዳው ነገር አልነበረም ፡፡ በህይወቱ ያንን ልምምድ ከተለማመደ በኋላ ነው ነገሩን የተነዘበው፡፡ ግልጽ የሆነውን እውነት ማመን የማይፈልጉ ሰዎችን ለማሰብ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?