በክርስቶስ አንድ መሆን
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከኀዳር 29-ታህሳስ 5

አስራ አንደኛ ትምህርት

Dec 08 - Dec 14



አንድነት በአምልኮ ውስጥ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 4:8፣ 11፣ ማቴ. 4:8-9፣ ዳን. 3:8–18፣ ራእ. 14:9፣ ራእ. 14:6-7፣ ሐዋ. 4:23–31፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-- “ከዚያም ሌላ መልአክ በሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ እርሱም በምድር ላይ ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ የሚሰብከውን የዘላለም ወንጌል ይዞ ነበር፤ ባታላቅ ድምፅም፣ ‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና፣ ሰማይንና ምድርን ባሕርንም የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ’ አለ” (ራእ. 14፡6-7)፡፡

የ ቀደሙት ክርስቲያኖች ከጴንጤቆስጤ በኋላ አብዛኛውን ጊዜያቸውን ያውሉ የነበረው ለአምልኮ ነበር፡፡ “እነርሱም በሐዋርያት ትምህርት በኅብረት፣ እንጀራውንም በመቁረስና በጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ. 2፡42)፡፡ የሱስን እንደ መሲህ በማወቃቸው ያገኙት ደስታና የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜ--ልባቸው በምስጋናና በውለታ እንዲሞላ አደረገ፡፡ ይህን አስደናቂ እውነት ማወቅ አብልጦ መታደል ነው፡፡ እነዚህ የቀደሙ ክርስቲያኖች በአንድነት ሆነው አምልኮ በማድረግ፣ ከቃሉ በማጥናትና በጸሎት በመትጋት በሕይወታቸው ላደረገላቸው ነገርና--የየሱስን ሕይወት፣ ሞትና ትንሣኤ የገለጠላቸውን አምላክ ለማመስገን ጊዜ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተሰምቶአቸው ነበር፡፡

የየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የተሰኘው አባባል--አምልኮ የሚያደርግ ማኅበረሰብ የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን፤ ይህ ማኅበረሰብ “ቅዱሳት ካኅናት በመሆን እንደ ሕያዋን ድንጋዮች መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ይሠራል” (1ጴጥ. 2፡5)፡፡ ለእግዚአብሔር ምስጋና የሚቀርብበት ማኅበረሰባዊ አምልኮ የሰዎችን ልብ እና አእምሮ ወደ አምላካዊው ባህሪ በመለወጥ ለአገልግሎት ያዘጋጃቸዋል፡፡ በዚህ ሣምንት ትምህርታችን በአምልኮ ፍቺ እና አምልኮ የየሱስ አማኞችን አንድነት እንዴት እንደሚያጸና እንመለከታለን፡፡

ሕዳር 3
Nov12

ፈጣሪያችንን እና ቤዛችንን ማምለክ


ስለ አምልኮ ውይይት ሲደረግ ብዙውን ጊዜ መሰረታዊ ለሚባሉ አላባዎች አጽንኦት ይሰጣል፡፡ አምልኮ ምን ምን እንደሚያካትትና እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆንም ሳይጠቀስ አያልፍም፡፡ ሆኖም ግን የአምልኮ ጥልቅ ትርጉም ምንድን ነው? እግዚአብሔርን ማምለክ ስንል ምን ማለታችን ነው? ይህን የምናደርገው ለምንድን ነው? ዳዊት በመዝሙር 29፡2 እንዲህ ይላል፡ “ለስሙ የሚገባ ክብር ለእግዚአብሔር ስጡ፤ በቅድስናው ግርማ ለእግዚአብሔር ስገዱ፡፡” ይህ መልእክት የአምልኮን ትርጉም የምናስተውልበትን ትክክለኛውን አቅጣጫ ይሰጠናል፡፡ ጌታን ማምለክ ማለት ለእርሱ የሚባውን ምስጋናና ክብር መስጠትነው፡፡

የሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ እንዴት እንደ ከበረ በራእ. 4 እና 5 ተብራርቶ እንመለከታለን፡፡ የሰማይ ቅዱሳን እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር በግ የሆነውን የሱስ ስለ ማምለካቸው የሚሰጡት ምክንያት ምንድን ነው? ጥቅሶቹን ይመልከቱ፡ ራእ. 4፡8፣ 11፡5፣ 9-13፡፡



ይህ የሱስ እንደ እግዚአብሔር በግ እና የዓለም አዳኝ ሆኖ የተዋወቀበት የሰማያዊው ዙፋን አምልኮ ገጽታ እጅግ ታላቅና በብርቱ አክብሮት የተሞላ ነው፡፡ እግዚአብሔር ላደረገው ነገር የእርሱ ፍጡር በአክብሮትና በፍቅር በተሞሉ ቃላት የሚያቀርበው የምስጋና ምላሽ ከአምልኮ ይመደባል፡፡ አምልኮ ለእግዚአብሔር የፍጥረትና የማዳን ሥራ የሚቸር የምስጋና ምላሽ ነው፡፡ በዘመን ፍጻሜ ላይ በበጉ ደም የተዋጁ ወገኖችም እንዲሁ ለአምላካዊው ማዳን በታላቅ ፍቅርና አክብሮት ምላሽ ይሰጣሉ፡፡ “ሁሉን ቻይ ጌታ ሆይ፤ ሥራህ ታላቅና አስደናቂ ነው፡፡ የዘመናት ንጉሥ ሆይ፤ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው፡፡ ጌታ ሆይ፤ አንተን የማይፈራ፣ ስምህን የማያከብርስ ማን ነው? አንተ ብቻ ቅዱስ ነህና፡፡ የጽድቅ ሥራህ ስለ ተገለጠ፣ ሕዝቦች ሁሉ ይመጣሉ፤ በፊትህም ይሰግዳሉ፡፡” ራእ. 15፡ 3-4)፡፡

ስለዚህ አምልኮ ለእግዚአብሔር ኃያል ሥራ የምንሰጠው የእምነታችን ምላሽ ሲሆን ይኸውም--በአንደኛ ደረጃ እኛን በመፍጠሩ፤ በሁለተኛ ደግሞ እኛን በማዳኑ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር በምንሰጠው አምልኮ እርሱ አክብሮት፣ ውዳሴ፣ ምስጋና፣ ፍቅርና መታዘዝ እንደሚገባው እናምናለን፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ፈጣሪያችንና አዳኛችን መሆኑን ማወቅ የቻልነው በመጽሐፍ ቅዱስ በገለጠልን እውነት መሰረት ነው፡፡ በተጨማሪ የየሱስ በአካል መምጣትና አገልግሎቱ የእግዚአብሔርን ማንነት ለክርስቲያኖች በሙላት መግለጥ ቻለ፡፡ (ዮሐ. 14፡8-14)፡፡ የየሱስ የመሥዋዕት ሞትና ትንሣኤ የአምልኮ አስኳል ነው፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች እርሱን እንደ አዳኝና ቤዛቸው ያመልኩታል፡፡

ክርስቲያኖች በአንድ ላይ ስንሰባሰብ አምልኮአችን በታላቅ አክብሮትና ውዳሴ መቀጠል የሚገባው በዚህ የተነሳ ነው፡፡ ስለ እኛ ለመሞት ፈቃደኛ በመሆኑ የተነሳ ክርስቶስ እንደ ፈጣሪነቱና እንደ አዳኝነቱ ከም ን እንዳዳነንና ም ን እንደሰጠን ያስቡ፡፡ እነዚህ እውነቶች የአም ልኮአችን መሰረት መሆን ያለባቸው ለምንድን ነው?

ታህሳስ 1
Dec10

የሐሰት አምልኮ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 4፡8-9፡፡ የሱስ በምድረ በዳ የተፈተነው ሦስተኛው ፈተና ምን ነበር?



ሰይጣን ይህን ዓለም የፈጠረ ይመስል በውስጧ ያለው ሐብት፣ ክብርና ዝና ሕጋዊ ገዢና ባለቤት መሆኑን በትዕቢትና በግብዝነት እያወጀ በውስጧ የሚኖሩ ሁሉ ለእርሱ ክብር ሊሰጡ እንደሚገባ ተናገረ፡፡ ይህ መመጻደቁ የዚህ ዓለም ፈጣሪ ለሆነው ጌታ እንዴት ዓይነት ስድብ ነው! ሰይጣን በዚህ አነጋገሩ የአምልኮን ትክክለኛ ፍቺ አበጥሮ እንደሚያውቅ ገለጸ--ለሕጋዊው የዩነቨርስ ባለቤት ክብርና ምስጋና መስጠት፡፡ በዳንኤል ምዕ. 3 የቀረቡትን የሦስቱን ዕብራውያን ተሞክሮ (በተለይ ከቁ. 8-18) እና በራእ. 13፡4፣ 14፡9-11 ስለ መጨረሻው ጊዜ ኃይል የቀረበውን ያስተያዩ፡፡ በመጨረሻው ጊዜ ያለው አደጋ ምንድን ነው? በሁለቱም ታሪኮች የሚስተዋለው ፍሬ ነገርስ?



ሰይጣን ከአቤልና ቃየን እንዲሁም በባቢሎን ከነበሩት ሦስቱ ዕብራውያን ወጣቶች እስከ “የአውሬው ምልክት” (ራእ. 16፡2) ድረስ ያሉ ክስተቶችን በመጠቀም፤ ሰዎችን እጅግ በረቀቀ መንገድ ከእውነተኛው አምላክ ነጥሎና አምልኮን በቀጥታ ወደ ራሱ አዙሮ የሐሰት አምልኮ ሥርዓት ለማቋቋም ሲጥር ኖሮአል፡፡ ለነገሩ ሰይጣን ከውድቀቱ አስቀድሞም ቢሆን እንደ እግዚአብሔር መሆን ፈልጎ ነበር (ኢሳ. 14፡14)፡ ሦስቱ ወጣቶች “ለምስሉ” ካልሰገዱ በቀር እንደሚገደሉ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ በተመሳሳይ በመጨረሻዎቹ ቀናት የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች “ለምስሉ” ካልሰገዱ እንደሚገደሉ ከሚወጣው ሕግ ጋር አንድ መሆኑ አጋጣሚ አይደለም፡፡ እውነተኛውን አምላክ እንድናመልክ ጥሪ ቀርቦልን እያለ በዚያ ፋንታ ለማንኛውም “ምስል” የምንሰግደው ለምን ይሆን?

“በዱራ ሜዳ ከነበሩ ዕብራውያን ወጣቶች ተሞክሮ እንድንማር የቀረቡልን ትምህርቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው… “በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የሚደርስ ከፍ ያለ የሥቃይ ወቅት የማያቅማማ የእምነት ባለቤት ያደርጋቸዋል፡፡ እርሱ ብቸኛው የአምልኮቸው አስኳል መሆኑን ልጆቹ ገልጠው ማሳየታቸው የግድ ነው፡፡ ራሷን ሕይወትን ጨምሮ የቱንም ዓይነት አስተሳሰብ በሐሰት አምልኮ ላይ ቅንጣት ታክል እምነት እንዲኖራቸው ሊያግባባቸው አይችልም፡፡ እሥር ወይም ግዞት ወይም ሞት ቢደርስባቸው እንኳ እውነትን ከመታዘዝ ወደ ኋላ አይሉም፡፡”—Ellen G. White, Prophets and Kings, pp. 4 512, 513. ዛሬም ቢሆን አምልኮ ከሚገባው ብቸኛ አምላክ ውጪ አምልኮ እንድናቀርብ በተለያየ መንገድ ሊፈትኑን የሚችሉ ነገሮች ምንድን ናቸው? ሐሰተኛ አምልኮ ልንገነዘብ ከምንችለው በላይ ረቂቅ ስጋት መሆን የሚችለው እንዴት ነው? እንድናመልካቸው የምንፈተን አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ታህሳስ 2
Dec11

የመጀመሪያው መልአክ መልእክት


ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ከየሱስ ዳግም ምጽአት አስቀድሞ ገቢራዊ የሚሆነውን በራእ. 14፡6-12 የቀረበውን የሦስቱ መላእክት መልእክት የተልዕኮአቸው ገላጭና የመልእክታቸው እምቡጥ አድርገው ይመለከቱታል፡፡ የሦስቱ መላእክት መልእክት ለመላው የምድር ሕዝቦች “በታላቅ ድምጽ” መሰበክ ያለበት እጅግ ወሳኝ መልእት ነው፡፡ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-7፡፡ የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ምንድን ነው? ስለ እግዚአብሔር ምን ይናገራል? በዚህ መልእክት ሰለ አምልኮ የተጠቀሰው ለምንድን ነው?



ከሦስቱ መላእክት መልእክት የመጀመሪያው ለመላው የምድር ሕዝብ የታወጀውን መልእክት ይዞአል፡፡ ይህ የሱስ በማቴ. 24፡14 የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው፡፡ የሦስቱን መላእከት መልእት ገጽታና ተልእኮ ስንመለከት በአስቸኳይነትና በጥድፊያ የተሞላ ሁናቴ ይታይበታል፡፡ “ ‘የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና’ ” (ራእ. 14፡7) የሚለው የመጀመሪያው መልእክት ሰዎች ትኩረታቸውን በእግዚአብሔር ላይ እንዲያደርጉ ጥሪ ያደርጋል፡፡ ሁለተኛው የየሱስ ምጽአት የፍርድ ሂደቱ አቀጣጣይ ነው፡፡ “ ‘እግዚአብሔርን ፍሩ’ ” (ራእ. 14፡7) ሲል መልአኩ ያውጃል፡፡ አምላካዊውን ነገር እንደ ብርቱ ጉዳይ ለማይቆጥሩ ይህ መልእክትና የድርጊት ጥሪ በአእምሮአቸው ፍርሐት መፍጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ የየሱስ ተከታዮች ሆነው ለዘለቁ ግን ልባቸው በታላቅ አክብሮትና ፍቅር እንዲሞላ ያደርጋል፡፡ ወደ እግዚአብሔር ቀና ብለው የአምላካዊውን ተስፋ ፍጻሜ ይመለከታሉ፡፡ ውስጣቸው ከበሬታ ባለው ብርቱ ውለታና ምስጋና ይሞላል፡፡

“‘ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ’” (ራእ. 14፡ 7)፡፡ ይህ ፍጥረትን በማጣቀስ የቀረበ ቋንቋ ስለ ሰንበት ለተሰጠው ትእዛዝ ፍንትው ያለ ፍንጭ ይሰጠናል ( ዘፀ. 20፡8-11)፡፡ ሰንበትን ለፍጥረት ሥራው በመታሰቢያነት ያቋቋመው ይህ አምላክ ሊመለክና ሊፈራ የተገባው ነው፡፡ በምድር ታሪክ መደምደሚያ ላይ አምልኮ በታላቁ ተጋድሎ ቁልፍ የሰብዓዊው ዘር ታማኝነት መለኪያ ሆኖ መቅረቡን መገንዘባችን በእጅጉ መሳጭ ነው፡፡ ይህ መመለክ ያለበት ሰማይና ምድርን የፈጠረው አምላክ ብቻ መሆኑን ለመላው የምድር ነዋሪ ለማስታወቅ የቀረበ ጥሪ ነው፡፡

“በመጨረሻ ለሚነሳው ቀውስ የጉዳዩ ማዕከል አምልኮ ይሆናል፡፡ ፈተናው አምልኮ የመከልከል ሳይሆን በሚመለከው ኃይል ማንነት ላይ ያነጣጠረ እንደሚሆን የራእይ መጽሐፍ በግልጽ ያስቀምጥልናል፡፡ በመጨረሻ ሁለት ዓይነት ቡድኖች ብቻ በምድር ይኖራሉ፡ እውነተኛውን እግዚአብሔር የሚፈሩ፣ የሚያመልኩ (ራእ. 11፡1፣ 18፣ 14፡ 7) እና እውነትን ጠልተው ለዘንዶውና ለአውሬው የሚሰግዱ (13፡4-8፣ 14፡9-11)፡፡ “አምልኮ የመጨረሻው ቀውስ ዐቢይ ጉዳይ እስከ ሆነ ድረስ እግዚአብሔር የመጨረሻውን ጊዜ ወንጌል ልኮ የምድር ነዋሪዎች እንደ ፈጣሪነቱ እርሱን ብቻ እንዲያመልኩ ጥሪ ማድረጉ ብዙም ሊያስገርም አይችልም፡፡”—Ranko Stefanovic, Revelation of Jesus Christ: Commentary on the Book of Revelation (Berrien Springs, Mich.: Andrews University Press, 2002), pp. 444, 445.

ታህሳስ 3
Dec12

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትና የአማኞች ኅብረት


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሐዋ. 2፡42፡፡ የቀደመው ክርስትና አምልኮ አንዳንድ መሰረታዊ ባህሪያት ምን ነበሩ?



“እነርሱም በሐዋርያት ትምህርትና በኅብረት.. ይተጉ ነበር” (ሐዋ. 2፡42)፡፡ አምልኮ ከእነዚያ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያን ጊዜያቶች አንስቶ በሐዋርያት በተሰጠን የእግዚአብሔር ቃል ማዕከላዊነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ስለ መሲሁ የሱስ የሚናገረውን አምላካዊ ቃል በማጥናቱ ረገድ ታማኞች ነበሩ፡፡ እግዚአብሔር የሰጣቸውን በረከቶች ለሌሎች በማጋራት፣ አንዱ ሌላውን በማበረታታትና ከእርሱ ጋር በነበራቸው አረማመድ የማያቋርጥ ኅብረት የነበራቸው አማኞች፤ የመልእክቶቻቸው መሰረት የሆኑትን የአምላካዊውን ቃል የተቀደሱ እውነቶች በልባቸው ይጠብቁ ነበር፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች በዚህ ሣምንት እያጠናነው ስላለነው አስራ አንደኛ ትምህርት ማለትም ከሌሎች አማኞች ጋር ኅብረት ፈጥሮ የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ማጥናት ምን ይላሉ? 2ነገሥ. 22:8–13



ሐዋ. 17:10-11



2ጢሞቴ. 3:14–17



“ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ ከልባቸው የሚመኙ ወገኖች፤ የወንጌል እውነት ሲሰበክ ሲሰሙ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት የማንበብ ምኞት በውስጣቸው ያድራል፡ ፡ በምድር ታሪክ መዝጊያ ትዕይንት ላይ እነዚያ ፈታኝ እውነቶች የሚሰበኩላቸው ወገኖች የቤርያን ሰዎች ምሳሌ በመከተል ዕለት ዕለት መጽሐፍ ቅዱስን እየመረመሩ የመጡላቸውን መልእክቶች ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ያስተያያሉ፡፡”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 232.

እኛ ከአምላካዊው ቃል ተነስተን ከምናውጃቸው እውነቶች አኳያ በአንድ የተዋሃድን ሕዝቦች ነን፡፡ ይህ በቀደመችው የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እውነት እንደ ነበር በዛሬዋም ነው፡፡ የሦስቱን መላእክት መልእክት ለዓለም እንድናውጅ የተጠራንበትን አምላካዊውን ቃል ማጥናት ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርስ ባለን ግንኙነት መሰረታዊውን የአምልኮአችንን ቅርጽ ይፈጥራል፡፡ ለአምልኮ ብሎም ከአማኞች ጋር ኅብረት ለመፍጠር እንደ አንድ ቤተሰብ ስንሰባሰብ ከእግዚአብሔር የተላከው አምላካዊ ቃል እኛን ለተልዕኮአችንና ለየሱስ ዳግም ምጽአት እያዘጋጀ ሕይወታችንን ይመራል፡፡

የእምነታችን መሰረት በሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሎት ጽናት ምን ይመስላል? እምነትዎ በሞት ፊት ተጋፍጠው እንደ ቆሙት ሦስቱ ዕብራውያን ወጣቶች ምን ያህል ጥብቅ ነው?

ታህሳስ 4
Dec13

እንጀራ በመቁረስና በጸሎት


የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ተግዳሮቶች የቱንም ያህል ብርቱ ቢሆኑም አማኞች በየሱስ ላይ የነበራቸው የጋራ እምነትና ለዓለም እንዲያሰራጩ የተሰጣቸው እውነት በአንድ አስተሳስሮአቸው ነበር፡፡ ጴጥሮስ ይህንን--ወቅታዊ እውነት በማለት ይጠራዋል (2ጴጥ. 1፡12)፡፡ የአማኞች የቤተ ክርስቲያን አንድነት በብዙ መንገዶች የተገለጸ ነበር፡፡ “እነርሱም… እንጀራውንም በመቁረስና በጸሎት ይተጉ ነበር” (ሐዋ. 2፡42)፡፡ ይህ እንጀራን አብሮ የመቁረስ ልምድ አማኞች የአምልኮ መርኀ ግብር ሲኖራቸው ወይም በመደበኞቹ ቀናት የሚተገብሩት ሊሆን ይችላል፡፡ አልፎ አልፎ በዚህ የኅብረት ማዕዳቸው ወቅት ከመካከላቸው አንዱ ዳግም ምጽአቱን ተስፋ በማድረግ ስለ የሱስ ሞትና ትንሣዔ መታሰቢያ እንዲሆን ለቀረበው ምግብና መጠጥ ልዩ ምስጋና ያቀርባል፡፡ የየሱስን ሕይወትና አገልግሎት እያስታወሱ ረዘም ያሉ ጊዜያቶችን ያጠፉ የነበሩት እነዚያ የቀደሙ ክርስቲያኖች በኅብረት ማዕድ ወቅትም ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ አውርተው አይጠግቡትም ነበር፡፡ በመሆኑም በኅብረት እንጀራ የሚቆርሱበትም ቢሆን--የአምልኮአችው ጊዜ ነበር፡፡ “በየዕለቱ በቤተመቅደስ በአንድነት እየተገናኙ፣ በቤታቸውም እንጀራ እየቆረሱ በደስታና በቀና ልብ ይመገቡ ነበር፤ እግዚአብሔርንም እያመሰገኑ፣ በሕዝቡ ሁሉ ፊት ሞገስ ነበራቸው፤ ጌታም የሚድኑትን በቁጥራቸው ላይ ዕለት ዕለት ይጨምር ነበር፡፡” (ሐዋ. 2፡46-47)፡፡ ይህ የኀብረት ጊዜያቸው በየሱስ የነበራቸውን የአንድነት ስሜት እንዲያጠነክሩ ለመርዳቱ ጥርጥር የለውም፡፡

የቀደሙት ክርስቲያኖች በአንድ ላይ በጸሎት ስለ መትጋታቸው በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የተሰጡን ምን ዓይነት ምሳሌዎች አሉን? የጸለዩት ስለ ምን ነበር? ሐዋ. 1:14



ሐዋ. 4:23–31



ሐዋ. 12:12



አማኞች በአንድነት ለአምልኮ ሲሰባሰቡ ልመናዋን ለእርሱ ከማቅረብ ተሰናክላ የማታውቀው የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ጋር በቀጥታ መገናኘት የመቻሏን ዕድል ጠብቃ ይዛ ነበር፡፡ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው የመጀመሪያው ደብዳቤ ክርስቲያኖች በአንድነት ሲሰባሰቡ መጸለያቸው አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቅሳል (1ጢሞቴ. 2፡1)፡፡ እንዲሁም ስለ ጸሎት አስፈላጊነት ለኤፌሶን ሰዎች በብርቱ ይናገራል “በሁሉ ዐይነት ጸሎትና ልመና፣ በማንኛውም ሁኔታ በመንፈስ ጸልዩ፤ ይህንም በማሰብ ንቁ፤ ስለ ቅዱሳንም ሁሉ በትጋት ልመና አቅርቡ፡፡” (ኤፌ. 6፡18-19)፡፡

ለጋራ ጥቅም ለሆነ የምልጃ ጸሎት ኃይል--ጥልቀት ያለውን አንድነት መለማመድ የም ንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? እንደ ቤተ ክርስቲያን ይህ ጸሎት አንድ ሊያደርገን የሚችለው እንዴት ነው?

ታህሳስ 5
Dec14


ተጨማሪ ሀሳብ


Read the articles “Prayer,” pp. 1044–1046, and “Worship,” pp. 1290, 1291, in The Ellen G. White Encyclopedia. “ ‘ሰንበት የፍጥረት መታሰቢያ የሆነበት ዋንኛ ምክንያት እግዚአብሔር ሁሌም አምልኮ የሚገባው አምላክ የመሆኑን እውነተኛ ምክንያት ይኸውም--እርሱ ፈጣሪ እኛ ደግሞ የእርሱ ፍጥረቶች መሆናችንን ስለሚገልጥ ነው፡፡

“ሰንበት ከሌላ ከማንኛውም ተቋም ይልቅ እጅግ መሳጭ በሆነ መልኩ ይህን የመለኮታዊ አምልኮ መሰረት የሆነውን ታላቅ እውነት ያስተምራል፡፡ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ለመለኮት አምልኮ የሚቀርብበት እውነተኛ መሰረት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን በሁሉም አምልኮዎች--በፈጣሪና በፍጥረታቱ መካከል ልዩነት መኖሩንም ያሳያል፡፡ ይህ ታላቅ ሐቅ ፈጽሞ ሊሻርም ሆነ ሊዘነጋ አይችልም፡፡’—J. N. Andrews, History of the Sabbath, chapter 27. እግዚአብሔር ሰንበትን በኤደን የአትክልት ስፍራ ያቋቋመው ይህ እውነት ሁሌም በሰብዓዊው አእምሮ ተጠብቆ እንዲቆይ በማሰብ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ፈጣሪነት እርሱን የምናመልክበት መንስዔ መሆኑ እስከ ቀጠለ ድረስ፤ ሰንበትም ምልክትና መታሰቢያ ሆኖ ይኖራል፡፡ ሰንበት በምድር ዳርቻ ተጠብቆ ቢሆን ኖሮ የሰው አስተሳሰብና ፍቅር በታላቅ አክብሮትና አምልኮ ወደ ፈጣሪው ባዘነበለና-ጣኦት አምልኮ፣ የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብም ሆነ ኢ-አማኒነት ባልኖረ ነበር፡፡ ሰንበትን መጠበቅ ‘ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው’ እውነተኛ አምላክ ያለንን ታማኝነት የምናሳይበት ምልክት ነው፡፡ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያመልኩና ትእዛዛቱን እንዲጠብቁ በሚያዘው መልእክት አራተኛውን ትእዛዝ እንዲጠብቁ የተለየ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 437, 438.


የመወያያ ጥያቄዎች





1. መጽሐፍ ቅዱሳዊው የአምልኮ፣ የፍጥረትና የደኅንነት ጽንሰ ሃሳብ እጅግ በቅርብ የተሳሰሩ እንደመሆናቸው ሰንበት እንዴት አምላካዊ የሐሰት አምልኮ ማርከሻ መሆን የሚችል ይመስሎታል? በራእ. 14፡6-7 ስለ መጨረሻው ዘመን በቀረበው ትንቢት ሰንበት ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል? ሰንበት በአንደኛው መልአክ መልእክት የተጠቀሰው ለምንድን ነው?

2. ብዙውን ጊዜ በአምልኮ ወቅት መደረግ ስላለባቸውና ስለሌለባቸው ነገሮች ስናወራ እንደመጣን፡፡ ይህ ብቻውን በቂ ሊሆን ይችላል? ለመሆኑ አምልኮ ምንድን ነው? አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ትርጉም ያለውን አምልኮ እየተለማመደች የምትገኝበት መንገድ ምን ይመስላል?

3. የክርስትና ማኅበረሰባዊ አምልኮ ልማድ አድቬንቲስቶችን ጨምሮ በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ቀስ በቀስ እየተረሳና እየተተወ የሄደ ይመስላል፡፡ ይህ ልማድ እንዲያንሰራራ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ምን ማድረግ ትችላለች? ማጠቃለያ፡ አምልኮ እግዚአብሔር ለሰጠን የደኅንነት ስጦታ ክርስቲያኑ አማኝ የሚያቀርበው አመስጋኝ ምላሸ ነው፡፡ በተጨማሪ የክርስትናው ማኅበረሰብ አንድነትና ኅብረት ተሞክሮ መሰረታዊ አላባ ነው፡፡ ያለ ጸሎትና መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እግዚአብሔር ለእኛ ያዘጋጀውን እውነት ለማወቅ የምንጓጓ ከሆነ ማኅበረሰባችን በክርስቶስ አንድ የመሆንን ተሞክሮ ሳያገኝ ይቀራል፡፡