ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 14:1–3 ኢሳ. 11:1–10፣ ራእ. 21:1–5፣ 1ተሰ. 4:13–18፣ ራእ. 22:1–5፣ ኢሳ. 35:4–10፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ :-- “እኛ ግን ጽድቅ የሚኖርበትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር በተስፋ ቃሉ መሰረት እንጠባበቃለን” (2ጴጥ. 3፡13)፡፡
አ
ብልጠው ልብ ከሚያሞቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች አንዱ የየሱስ ዳግም
ምጽአት ነው፡፡ የተስፋችን መሰረት ዳግም ምጽአቱ እንደመሆኑ ያለ እርሱ
መና ሆነን በቀረን ነበር፡፡ ክርስቶስ በሰማያት ደመና ዳግም ሲገለጥ በአንድ
ወቅት ትርጉም ይሰጥ የነበረው ምድራዊው፣ ሰው ሠራሹና ጊዜያዊው ሁሉ ተጠራርጎ
ይነጉዳል፡፡ በሰማይ አንድ ሺህ ዓመት ከነገሥን በኋላ ይህች በጦርነት አረር፣ በረሃብ፣
በበሽታና በአሳዛኝ ሁኔታ ስትማቅቅ የኖረች ምድር በእሳት ትነጻለች፡፡ በመጨረሻ
በበጉ ደም የተዋጁ ከጌታቸው ጋር እንዲሁም እርስ በርስ ዳግም ይገናኛሉ፡፡
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ የአዲስ ኪዳን አበይት ርዕሰ ጉዳይ እንደመሆኑ
ክርስቲያኖች የዚህን ተስፋ ፍጻሜ ለማየት አብልጠው ሲጓጉ ኖረዋል፡፡ እንደ ሰባተኛ
ቀን አድቬንቲስት እኛም ዳግም ምጽአቱን እንናፍቃን፡፡ ለነገሩ መጠሪያ ሰማችን በራሱ
ይህን ተስፋ ያውጃል፡፡
በሩብ ዓመቱ የመጨረሻ ትምህርታችን ወደዚህ ተስፋ እንመለከታለን፤ ለክርስትና
አንድነት ያለውን አንደምታም እንፈትሻለን፡፡ በክርስቶስ ያለን አንድነት በገዛ ራሳችን
ሰብዓዊ ውሱንነትና ደካማነት ተደጋግሞ ፈተና ሲገጥመው ይስተዋላል፡፡ ያን ጊዜ
ግን ለመከፋፈላችን መፍትሔ ፍለጋ መሮጥ አያስፈልገንም ምክንያቱም መከፋፈል
አይኖርም፡፡ መጨረሻው ደርሶ ዳግም ምጽአቱ ገቢራዊ ሲሆን ከጌታ ጋር አንድ
እንሆናለን፤ ዳግመኛ አንድነት ፈጥረን አንድ ቤተሰብ እንሆናለን፡፡
ስለ የሱስ ዳግም ምጽአት ከሚናገሩ ዝነኛ ጥቅሶች መካከል ዮሐ. 14፡1-3-- አንዱ ነው፡ ፡ የዳኑት ወገኖች በአዲሲቱ ምድር ስለሚኖሩት ሕይወት ተስፋው ምን ይነግሮታል?
የቀደሙት ክርስቲያኖች የክርስቶስን ዳግም ምጽአት “የተባረከ ተስፋችን” (ቲቶ 2፡
13) የሚል ከፍ ያለ ምልከታ ሰጥተውታል፡፡ ዳግም ምጽአቱ የክርስትና መንፈሳዊ
ጉዞ ዓላማና ግብ በመሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ የተሰጡት ሁሉም ዓይነት ትንቢቶችና
ተስፋዎች በዚህ ወቅት ፍጻሜ እንደሚያገኙ ጠብቀዋል፡፡ ክርስቶስን የሚወዱ ሁሉ
ከእርሱ ጋር ፊት ለፊት ኅብረት የሚያደርጉባትን ያቺን ዕለት አሻግረው በተስፋ
ይጠባበቃሉ፡፡ በጥቅሶቹ የቀረቡት ከእርሱ አንደበት የወጡ ቃላት ከየሱስ ጋር ብቻ
ሳይሆን እርስ በርሳችን ጭምር የምንጋራቸውን የቅርብ ግንኙነቶችና ወዳጅነቶች
ያመለክታሉ፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ትንቢቱ ፍጻሜ ማረጋገጫ ስለሚሰጠን ክርስቲያኖች በዚህ ተስፋ
ያምናሉ፡፡ ማረጋገጫው ደግሞ የሱስ “ዳግመኛ እመጣለሁ” (ዮሐ. 14፡3) ብሎ የነገረን
እኛም አምነን የምንቀበለው ነው፡፡ የክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት ትንቢት አስቀድሞ
እንደተነገረ ሁሉ ዳግም ምጽአቱም በራሱ በብሉይ ኪዳን ጭምር ተነግሮአል፡፡ በክብር
የሚገለጠው መሲህ ለኃጢአት ፍጻሜ ያመጣል ሲል በምድር ላይ የውሃ ጥፋት
ከመድረሱ አስቀድሞ እግዚአብሔር ከእምነት አባቶች አንዱ ለነበረው ሄኖክ ነግሮት
ነበር፡፡ “‘እነሆ፤ ጌታ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል፤ ይህም በሰው ሁሉ
ላይ ለመፍረድ እንዲሁም ዐመጸኞችን ሁሉ በክፋት መንገድ በሠሩት የዐመጽ ሥራና
በክፋት በእርሱ ላይ ስለ ተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ አጥፊነታቸውን ይፋ ለማድረግ
ነው’ ” (ይሁዳ 14-15)፡፡
የሱስ ወደዚህ ምድር ከመምጣቱ ከአንድ ሺ ዓመት በፊት መሲህ የእግዚአብሔርን
ሕዝብ በአንድነት ለመሰብሰብ እንደሚመጣ ንጉሥ ዳዊት በትንቢት ተናግሮ ነበር፡
“አምላካችን ይመጣል፤ ዝም አይልም፤ የሚባላ እሳት በፊቱ፣ የሚያስፈራ ዐውሎ
ነፋስም በዙሪያው አለ፡፡ በሕዝቡ ይፈርድ ዘንድ፣ በላይ ያለውን ሰማይንና ምድርን
እንዲህ ብሎ ይጠራል፤ ‘በመሥዋዕት ከእኔ ጋር ኪዳን የገቡትን፣ ቅዱሳኔን ወደ እኔ
ሰበሰብኳው’ ” (መዝ 50፡3-5)፡፡
የየሱስ ሁለተኛው ምጽአት ከመጀመሪያው ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው፡፡ በውልደቱና
ምድራዊ አገልግሎቱ ዙሪያ የተሰጡ ትንቢቶች (ዘፍ. 3:15፣ ሚክ. 5:2፣ ኢሳ. 11:1፣ ዳን.
9:25-26) የዳግም ምጽአቱ ተስፋችንና የመታመናችን መሰረት ናቸው፡፡ ክርስቶስ
“ኃጢአትን ለማስወገድ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገልጦአል… ክርስቶስ የብዙ
ሰዎችን ኃጢአት ለመሸከም፤ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኖአል፤ ሁለተኛ ጊዜም
ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኃጠአትን ለመሸከም
አይደለም” (ዕብ. 9፡26፣28)፡፡
ከዳግም ምጽአቱ የተስፋ ቃል ዛሬም ቢሆን ተስፋና መጽናናት ማግኘት የሚችሉባቸው
መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 11፡1-10፡፡ ለእስራኤል የተሰጠው የተስፋ ቃል ምንድን ነው? ስለ ዳኑት ዘላለማዊ መኖሪያስ ምን ይላል?
መጽሐፍ ቅዱስ የምድርን አፈጣጠር ትርክት በመንገር ይጀምራል (ዘፍ. 1፣2)፡፡
ትርክቱ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አዳምና ሔዋን በዐደራ ስለ ተሰጠችው ውብ እና
ስምሙ ዓለም በቂ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ምድር ለሰብዓዊው ዘር መኖሪያ እንድትሆን
በእግዚአብሔር የተፈጠረች ፍጹም ስፍራ ነበረች፡፡ ሁለቱ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ
ምዕራፎችም እንዲሁ እግዚአብሔር ለተቤዠው ሰብዓዊ ዘር ፍጹም የሆነ መኖሪያ
እያዘጋጀ መሆኑን ቢናገሩም (ራእ. 21-22) ነገር ግን በዚህ ወቅት ገቢራዊ የሚሆነው
ምድርን ከኃጢአት ውድመት ወደ ቀደመ ንጽህናዋ የመመለስና ዳግመኛ የመፍጠር
ዓይነት ሥራ ይሆናል፡፡
ይህ ለዳኑ ወገኖች የተጋጀ ዘላለማዊ መኖሪያ በተጨባጭ ገቢራዊ እንደሚሆን አያሌ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በይፋ ይናገራሉ፡፡ የዳኑት በሚኖራቸው አዲስ ሕይወት፣
የሚያዩ፣ የሚሰሙ፣ የሚያሸቱ፣ የሚዳስሱ እንዲሁም ስሜት የሚኖራቸውና የአዳዲስ
ተሞክሮዎች ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ትንቢተ ኢሳይያስ የመሲህን ምጽአት ተከትሎ ገቢራዊ
ስለሚሆነው የአዲስ ዘመን ጅማሮ ውብ የሆኑ መልእክቶችን አስፍሯል፡፡ ለአመጻ
ፍጻሜ በማምጣት ዘላለማዊ ሰላም ያሰፍናል፡፡ የእግዚአብሔር በአዲሲቱ ምድር
መንገሥ ዩኒቨርስ አቀፍ ለዛና መዋሃድ ያመጣል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 21፡1-5፡፡ ይህን አዲስ ውህደት ተከትሎ ለዘላለም የሚወገደው
ምንድን ነው?
የዳኑት ምን እንደሚጠብቃቸው አስመልክቶ ኤለን ኋይት የሚከተለውን ጽፋለች፡
“ዘላለማዊዎቹ ዓመታት በተዟዟሩ ቁጥር ስለ እግዚአብሔርና ስለ ክርስቶስ ታላቅና
የከበረ ማንነት በጥልቅ መግለጣቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ዕውቀት ታዳጊ እንደመሆኑ
ፍቅር፣ አክብሮትና ደስታም በተመሳሳይ እየተስፋፉና እየበለጸጉ የሚሄዱ ናቸው፡፡
ሰዎች አብልጠው ስለ እግዚአብሔር በተማሩ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የባህሪው አድናቂ
ይሆናሉ፡፡ የሱስ የቤዛነቱን ምስጢርና ከሰይጣን ጋር የተደረገውን ታላቅ ውዝግብ
ውጤት በሙላት ሲገልጥላቸው--የተዋጁት ወገኖች ልብ በብርቱ አምልኮና ስግደት
መምታት ይጀምራል፤ ከዚያም የወርቅ በገናቸውን አንስተው በእነዚያ ጽኑ እጆቻቸው
መጫወት ይጀምራሉ፡፡ የበገናዎቹን ድምጸት ተከትሎ አሥር ሺ ጊዜ አሥር ሺ ኅብረ
ድምጾች ይደጣሉ፡፡”—Ellen G. White, The Story of Redemption, pp. 432,
433.
ዛሬም በዚህ ምድር የእግዚአብሔርን ጸባይ የምናስተውልባቸው መንገዶች
የተኞቹ ናቸው? ከሌሎች ጋር ለዛ ያለው ስምምነትና አንድነት መፍጠር ዛሬም
ቢሆን አምላካዊውን ጸባይና ተፈጥሮ የሚገልጠው እንዴት ነው?
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የተስፋ ቃል ከቤተ ክርስቲያን የቀደሙ ቀናት አንስቶ
ምናልባትም ከማንኛውም ነገር በላቀ የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች ልብ መጽናኛ
ሆኖ ኖሮአል--በተለይ በፈተና ወቅት፡፡ አማኞች የትኛውንም ዓይነት አስፈሪ ትግል፣
መራር ሐዘንና ሥቃይ ቢጋፈጡም--የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የተስፋ ቃል እና
መገለጡ የያዛቸው አስደናቂ ተውህቦዎች ነበሯቸው፡፡
በሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት የተስፋ ቃሎች ተካተዋል--1ተሰ. 4፡13-18? ወደ
ቀድሞ ንጽሕናቸው ስለ ተመለሱ ግንኙነቶችስ ምን ይላል?
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት መላውን ሰብዓዊ ዘር በጥልቅ ይነካል፡፡ የእግዚአብሔር
መንግሥት መቋቋም አንዱ አስፈላጊ ገጽታ የተመረጡትን በአንድ መሰብሰብ ነው፡
“‘መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፤ እነርሱም ምርጦቹን
ከአራቱም ነፋሳት፣ ከሰማያት ከአንዱ ዳርቻ ወደ ሌላው ዳርቻ ይሰበስባሉ፡፡’ ” ማቴ.
24፡31)፡፡ በዚህ የመሰብሰብ ወቅት የሞቱ ጻድቃን በትንሣኤ የማይሞተውን አካል
ይወስዳሉ (1ቆሮ. 15፡52-53)፤ “በክርስቶስ የሞቱም አስቀድመው ይነሳሉ” (1ተሰ. 4፡
16)፡፡ ይህ ሁላችንም ስንጠባበቀው የኖርነው ክስተት ነው፡፡ የትንሣኤ ባለቤት የሆኑ
ሁሉ የእነርሱን መገኘትና ፍቅራቸውን ሲናፍቁ ከቆዩ ወገኖች ጋር ዳግም ይገናኛሉ፡፡
ጳውሎስ ይህን አስደናቂ ሁኔታ እንዲህ በሚሉ ቃላት ያወድሰዋል፡ “ ‘ሞት ሆይ፤ ድል
መንሳትህ የት አለ? ሞት ሆይ፤ መንደፊያህስ የት አለ?’ ” (1ቆሮ. 15፡55)፡፡
በበሽታ ማቅቆና መንምኖ፣ በዕድሜ ብዛት ገርጅፎና ጃጅቶ ወይም ትክክለኛ
ገጽታውን አጥቶ ወደ መቃብር የወረደ ሁሉ ያን የቀድሞ ሁኔታ እንደ ያዘ አይነሳም፡
፡ ይልቁንም የኃጢአት ነቁጥ የሌለው አዲስ፣ የማይሞትና የማይበሰብስ ፍጹም አካል
ለብሶ ይነሳል፡፡ የትንሣኤ ባለቤት የሆኑት ጻድቃን በፍጥረት ወቅት ታቅዶ የነበረውን
ፍጹም አምላካዊ አምሳል እያንጸባረቁ የክርስቶስን ሥራ ፍጻሜ ይለማመዳሉ፡፡
የየሱስ ዳግም ምጽአት ገቢራዊ ሲሆን የተዋጁት ጻድቃን በትንሣኤ ከመቃብር ሲነሱ፤
በምድር ላይ በሕይወት ያለነው የዳንን ወገኖች ደግሞ እንለወጥና ፍጹም የሆነውን
አካል እንወስዳለን፡ “የሚጠፋው የማይጠፋውን፣ የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ
ይገባዋልና” (1ቆሮ. 15፡53)፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሁለት ቡድኖች--በትንሣኤ የተነሱት
እና በሕይወት እያለን የተለወጥነው--“ጌታን በአየር ለመቀበል ከእርሱ ጋር በደመና
እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንኖራለን” (1ተሰ. 4፡17)፡፡
በምንኖርበት በሣይንስና ቴክኖሎጂ የረቀቀ ዘመን አንዳንድ ክርስቲያኖች
ለማንኛውም ነገር ተፈጥሮአዊ ማብራሪያ ለማግኘት ይሞክራሉ--ታምራትን
ጨምሮ፡፡ እኛን ሊያድን የሚችለው ከተፈጥሮ ውጪ ብቻ ያለው አምላካዊ ኃይል
ስለ መሆኑ የትንሣኤው የተስፋ ቃል ምን ያስተምረናል?
“‘እነሆ፤ እኔ፣ አዲስ ሰማያትንና አዲስ ምድርን እፈጥራለሁ፤ ያፉት ነገሮች አይታሰቡም፤
አይታወሱም’ ” (ኢሳ. 65:17)፡፡ ኢሳይያስ እና ዮሐንስ ተስፋ የተገባችውን የአዲሲቱን
ምድር በራእይ አይተው ነበር፡፡
ዮሐንስ የዳኑት ከተማ የሆነችውን አስገራሚዋን አዲሲቱን የሩሳሌም እንዴት እንደ
ገለጻት ልብ ብለው ይመልከቱ--(ራእ. 21፡2፣ 9-12)፡፡ በዚህች ከተማ ስለሚሰፍነው
አንድነትና ውህደት ጥቅሶቹ በተዘዋዋሪ ምን ይላሉ?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 22፡1-5፡፡ ከእግዚአብሔርና ከበጉ ዙፋን የሚወጣው
የሕይወት ወንዝ ከሕይወት ዛፍ ጋር ተደምሮ--ሌሎቹ ሁለት የአዲሲቱ ከተማ አስፈላጊ
ገጽታዎች ናቸው፡፡ በአዲሲቱ ምድር የሚኖራቸው ጥቅም ምን ይሆናል?
አዳም አምላካዊውን ሕግ በመጣሱ ወደ ሕይወት ዛፍ እንዳይደርስ ተከልክሎ
የነበረ ቢሆንም (ዘፍ. 3፡22-24) አሁን ግን አጥቶት የነበረውን በክርስቶስ አማካይነት
በአዲሲቱ የሩሳሌም ያገኛል፡፡ ድል ለሚነሱ ከተገባው ቃል አንዱ ወደ ሕይወት ዛፍ
መድረስ ነው (ራእ. 2፡7)፡፡ ይህ ዛፍ በየወሩ እያፈራ ዐሥራ ሁለት ጊዜ ፍሬ መስጠቱ
በአዲሲቱ ምድር “ ‘ከአንዱ ወር መባቻ እስከ ሌላው፣ እንዲሁም ከአንዱ ሰንበት
እስከ ሌላው፣ የሰው ልጅ ሁሉ በፊቴ ሊሰግድ ይመጣል’” (ኢሳ. 66፡23) በማለት
እግዚአብሔር የተናገረበትን ምክንያት የሚጠቁም ሊሆን ይችላል፡፡ “ሕዝቦች
የሚፈወሱባቸው” በሚል የቀረበው ማመሳከሪያ በህዝቦች መካከል ያለውን ግድግዳ
የማፍረስና ሰብዓዊውን ዘር ወደ ቀደመው ዓላማ የመመለስ አምላካዊ እቅድ የሚያሳይ
ሲሆን ይኸውም--ለእግዚአብሔር ክብር በመስጠት ኅብረት የፈጠሩ ሕዝቦችን፣
ነገዶችንና ብሔሮችን ወደ አንድ የማይከፋፈል የቀደመ ቤተሰብ በመመለስ በአንድ
ልብ እና በሰላም መኖር ነው፡፡
“ ‘ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው’ የሚሉት ቃላት በሕዝቦች መካከል ያለውን የብሔርና
ቋንቋ ግድግዳና መለያየት መወገድ የሚወክል ምሳሌያዊ አነጋገር ነው. . . የሕይወት ዛፍ
ቅጠሎች በሕዝቦች መካከል ያሉ ቅሬታዎችን ይፈውሳሉ፡፡ ሕዝቦች እንደ እውነተኛ
የእግዚአብሔር ቤተሰብ አንድ ይሆናሉ እንጂ ‘አሕዛብ’ ተብለው አይጠሩም (21፡2426)፡፡ ከአያሌ መቶ ዓመታት አስቀድሞ ሚክያስ የተነበየው አሁን ፍጻሜ ያገኛል፡
‘እያንዳንዱ ሰው በገዛ ወይኑ ሥር፣ ከገዛ በለሱም ሥር ይቀመጣል፣ የሚያስፈራቸው
አይኖርም’ (ሚክ. 4፡3-4፣ ኢሳ. 2፡4)፡፡ የተዋጀው ወገን በሕይወት ወንዝ ዳርቻ
ከተከለው ወይንና በለስ ‘ባልንጀራውን ይጋብዛል’ (ዘካ. 3፡10)፡፡ የዛፉ ቅጠሎች
ሰብዓዊውን ዘር ለዘመናት ሲከፋፍሉ የኖሩትን ሁሉንም ዓይነት የዘር፣ የብሔር፣ የነገድ
ወይም የቋንቋ ደዌዎች የመፈወስ ኃይል አላቸው፡፡”—Ranko Stefanovic, Revelation of Jesus Christ: Commentary on the Book of Revelation, p. 593.
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 35፡4-10፣ 65፡21-25፡፡ በዚያን ወቅት ሕይወት ከአሁኑ ተሞክሮ ምን ዓይነት የተለየ ገጽታ ይኖረዋል?
በኢሳይያስ መጽሐፍ አዲስ የሚሉ ቃላትን በተደጋጋሚ እናነባለን፡ “አዲስ ነገር” (ኢሳ.
42፡9፣ 48፡6)፣ “አዲስ መዝሙር” (42፡10)፣ “አዲስ ነገር” (ኢሳ. 43፡19)፣ “አዲስ ስም”
(62፡2)፡፡ በኢሳይያስ 65 የምናገኘው አዲስ ነገር--አዲስ የሥርዓት አደረጃጀት ነው፡
፡ በመላው የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሀል ሰላምና አንድነት ሰፍኖአል፡፡ ከእንግዲህ
ኃጢአት ስለሌለ በዐመጻዋና ባለመታዘዟ ምድሪቱን ይረግም የነበረው ኪዳን (ዘሌዋ.
26:14–17፣ ዘዳ. 28:30) ለዘላለም ይወገዳል፡፡ በዚያ ፋንታ የምንኖትበት ቤት እና
የምንበላው ምግብን ጨምሮ የተትረፈረፉ በረከቶች ባለቤት እንሆናለን፡፡
ሕይወት በእንዲህ ያለ ውብ ስፍራ ምን ትመስል ይሆን? የማይሞተውን አካል ከለበስንና
ሙሉ ለሙሉ አምላካዊን አምሳል ከወሰድን በኋላ አንዳንዶች ቤተሰቦቻችንንና
ወዳጆቻችንን ለይተን ማወቅ እንችል ይሆን--ሲሉ ያስባሉ፡፡ ክርስቶስ ካረገ በኋላ
ደቀ መዛሙርቱ እርሱን ለመገንዘብ አልተቸገሩም፡፡ ማርያም የለየችው በድምፁ ነበር
(ዮሐ. 20፡11-16)፡፡ ቶማስ የየሱስን አካል ሲያይ እርሱ መሆኑን ተገንዝቦአል (ዮሐ.
20፡27-28)፡፡ ሁለቱ የኤማሁስ መንገደኛ ደቀ መዛሙርት ከየሱስ ጋር በገበታ ሲቀርቡ
በአኳኋኑ አውቀውት ነበር (ሉቃ. 24፡30-31፣35)፡፡ ስለዚህ በትንሣኤ የእኛም አካል
ከየሱስ ጋር ተመሳሳይ እስከሆነና አንዳችን ሌላችንን ለይተን ማወቃችንና መገንዘብ
መቻላችን እውነት እስከሆነ ድረስ--ወደ ፍጹም ንጽህናና ዘላማዊነት የሚመለሰውን
ግንኙነት ከወዲሁ አሻግረን ለመመልከት እንጣር፡፡ በዚያ ስፍራ አብረውን ከሚሆኑ
ከምንወዳቸው ቤተሰቦቻችንና ጓደኞቻችን ጋር የሚኖረን ግንኙነት እንደሚቀጥል
ተስፋ ማድረግ እንችላለን፡፡
“በዚያን ወቅት የዳኑት ሌሎችን ያውቃሉ፤ እነርሱም ይታወቃሉ፡፡ ራሱ እግዚአብሔር
በነፍስ ውስጥ የተከለው ፍቅርና ርኅራኄ--በዚያ ስፍራ መታንና ጣፋጭ ልምምድ
ያገኛል፡፡ ቅዱስ ከሆኑ ነገሮች ጋር የሚኖር ንጹህ መንፈሳዊ አንድነት፣ በዘመናት ታማኝ
ሆነውና ልብሶቻውን በበጉ ደም አጥበው እንደ በረዶ ያነጹ ጻድቃን ከእግዚአብሔር
የተባረኩ መላእክት ጋር የሚኖራቸው ስምሙ የአብሮነት ሕይወት፣ ‘በሰማይና በምድር
ያለ ቤተሰብ ሁሉ’ (ኤፌ. 3፡15) ቅዱስ በሆነ ኅብረት ይተሳሰራል፡፡ ይህ ለዳኑት የደስታ
ምንጭ ይሆናል”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 677.
“ስለዚህ ተስፋ አንቆርጥም፤ ውጫዊው ሰውነታችን እየጠፋ ቢሄድም እንኳ
ውስጣዊው ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል፤ ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው
መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል፡፡ ስለዚህ ዐይናችን
የሚያተኩረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው
ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው፡፡”
Ellen G. White, “ ‘Behold, I Come Quickly,’ ” pp. 355–
359, in Counsels for the Church. Read the articles “Resurrection,” pp.
1082–1084, and “Heaven and New Earth,” pp. 863, 864, in The Ellen G.
White Encyclopedia.
የጌታችን ትንሣኤና ዕርገት ቅዱሳን በሞትና በመቃብር ላይ ባለ ድል መሆናቸውን
የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው፡፡ የባህሪያቸው መገለጫ የሆነውን ልብሶቻቸውን በበጉ
ደም አጥበው ለሚያነጹ ሰማይ ክፍት መሆኑን የሚያሳይ የተስፋ ቃል ነው፡፡ የሱስ
ሰብዓዊውን ዘር በመወከል ወደ አብ አረገ፡፡ አምላካዊውን አምሳል የሚያንጸባርቁ
ክብሩን ይጋሩ ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡
“ለምድር መናኞች የተዘጋጀ ሰማያዊ ቤት አለ፡፡ ለዳኑት የጽድቅ ልብስ፣ አክሊልና
የድላቸው ማብሰሪያ የዘንባባ ዝንጣፊ ተዘጋጅቶአል፡፡ በዚህ ዓለም ግራ አጋብተውን
የነበሩ ነገሮች ሁሉ በእግዚአብሔር ቸርነት በአዲሲቱ ምድር ግለጽ ይሆኑልናል፡፡
ለማስተዋል አስቸጋሪ የነበሩ ነገሮች ሁሉ ማብራሪያ ያገኛሉ፡፡ የጸጋ ምስጢር ወለል
ብሎ በፊታችን ይገለጣል፡፡ ግራ መጋባት፣ የታጠፉ ቃሎችንና ተስፋዎችን ብቻ ያውቅ
የነበረው ውሱኑ አእምሮአችን እጅግ ፍጹምና ውቡ የሆነውን ኅብር ይመለከታል፡
፡ ከዉሱን ባሻገር--መጨረሻ የሌለውን ፍቅር ተሞክሮ በዚያን ጊዜ እናውቃን፡፡
ነገሮች ለእኛ በጎ እንዲሰለጥኑ የሚሠራውን፣ በርኅረኄ የተሞላ ጥንቃቄውን መገንዘብ
ስንጀምር በቃላት ሊገለጽ በማይችል ሐሴትና ክብር እንሞላለን፡፡”—Ellen G. White,
Counsels for the Church, p. 358.
1.
ምንም እንኳ ክርስቲያኖች (ሁሉም ባይኑም) በየሱስ ዳግም ምጽአት
ብናምንም፤ ነገር ግን በዚህ ዙሪያ ለየት ያለው የአድቬንቲስቶች ተስፋ ምንድን ነው?
2.
በአንድ ወቅት ሁሉት ዓሣዎች እየዋኙ እያለ አንደኛው “ውሃው እንዴት
ነው?” ብሎ ቢጠይቅ ሌላው “ለመሆኑ ውሃ ምንድን ነው?” በማለት ጥያቄውን
በጥያቄ መለሰ ይባላል፡፡ ለምሳሌ እኛ በኃጢአት የተወለድን፣ በኃጢአት የተሞላንና
በኃጢአተኛ ዓለም ውስጥ የምንኖር እንደመሆናችን በዚያ ግሩም አዲስ ሰማይና አዲስ
ምድር የሚኖረንን ሕልውና ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? የቱንም ዓይነት
ዉሱንነት ቢኖረንም--ምን ሊመስል እንደሚችል በዐይነ ኅሊናችን መመልከት አንችል
ይሆን?
3.
በአዲሲቱ ምድር የሚኖረን ሕልውና የቱንም ዓይነት ሊሆን ቢችል
ከእያንዳንዱ ጋር በኅብር መኖራችን ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ ራሳችንን ለዚያ ጊዜ
ለማዘጋጀት አሁን ምን ማድረግ እንችላለን?
ማጠቃለያ፡
ይህች ምድር ዳግም እንደምትፈጠርና ለዘላለም ከኃጢአት ሥር
እንደምትነጻ መጽሐፍ ቅዱስ በይፋ ይናገራል፡፡ በመጨረሻ ሰብዓዊው ዘር አስቀድሞ
ወደ ታለመለት የቀደመ ንጽህናው ይመለሳል፡፡ ሰው ሁሉ ስምሙ ሆኖ በአንድ ላይ
ይኖራል፡፡ ምንም እንኳ ዛሬ ከክርስቶስ ጋር ያለን መንፈሳዊ አንድነት ፍንትው ብሎ
የሚታይ ባይሆንም፤ የዚያን ጊዜ ግን ሕያውና ዘላለማዊ ሐቅ ይሆናል፡፡