የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከመጋቢት 7 -13

12ኛ ትምህርት

Mar 16 – Mar 22




በባቢሎን ላይ የተሰጠ ፍርድ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 17:1–18 ኤር. 51:13፣ ራእ. 13:1–10፣ ዘጸ. 28:2:20–23፣ 13:5–8፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :-“ከዚያም ከሰማይ ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ ‘ሕዝቤ ሆይ፤ በኃጢአቷ እንዳትተባበሩ፣ ከመቅሠፍቷም እንዳትካፈሉ፣ ከእርሷ ውጡ፤ ኀጢአቷ እስከ ሰማይ ድረስ ተከምሮአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታውሶአል፡፡” (ራእ. 18፡4-5)፡፡

የ ስድስተኛው መቅሰፍት መውረድ ተምሳሌታዊው የኤፍራጥስ ወንዝ እንዲደርቅ መንስዔ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በዚህም እንዳሰቡት ያልተሳካላቸው የዓለም ሕዝቦች ለመጨረሻዋ ዘመን ባቢሎን ይሰጡ የነበረውን ድጋፍ ያቋርጣሉ፡፡ የሆነው ሆኖ ውድቀቷ የእግዚአብሔርን ሥራ አስመስለው በሚሠሩ ርኩሳን መናፍስት መጠን የለሽ እንቅስቃሴ የታጀበ ይሆናል፡፡ ታምራዊ ምልክቶችን ያደርጋሉ--ምናልባትም የሐሰተኛ ኀይማኖት የማንቂያ ደወል የሆነውን እሳት ከሰማይ ሳይቀር ያወርዳሉ (ራእ. 13፡13)፡፡ መላውን ዓለም አንድ አድርጎ በእግዚአብሔር ታማኝ ትሩፋን ላይ ለሚከፈተው የአርማጌዶን ጦርነት በማዘጋጀቱ ረገድ ርኩሳን መናፍስት ስኬታማ ይሆናሉ፡፡

በጥቃቱ መጀመሪያ የሰባተኛው መቅሰፍት አካል የሆነ ታላቅ የመሬት መናወጥ ይከሰታል፡፡ የመሬት መናወጡ በባቢሎንና በርኩሳን መናፍስት መሃል የነበረውን አንድነት ብትንትኑን አውጥቶ ለሦስት ይሰነጥቀዋል (ራእ. 16፡18-19)፡፡ የከተማ ቅርጽ ይዛ የቀረበችው የመጨረሻዋ ዘመን ባቢሎን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በመቃወም ከዓለም ኃይማኖታዊ ኀይላት ጋር ባላት ሕብረት ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚዘልቀውን የዘንዶውን፣ ከባሕር የወጣውን አውሬና ከምድር የወጣውን አውሬ ሰይጣናዊ ኅብረት ታመለክታለች፡፡ የመጨረሻ ዘመኗ ባቢሎን መፈረካከሷን ተከትሎ ይህ ሕብረት እንኩትኩቱ ይወጣል፡፡ እዚህ ላይ የመጨረሻ ዘመኗ ባቢሎን መፈረካከሷን የሚያውጀው ራእ. 16፡19 ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ምዕ. 17 እና 18 ደግሞ ይህ ውድቀት እንዴት ገቢራዊ እንደሚሆን ይነግረናል፡፡ ጥቅሶቹ (ራእ. 17፡12-18፡24) የመጨረሻ ዘመኗ ባቢሎንን ውድቀትና የውድቀቷን መንስዔ ከማብራራታቸው አስቀድሞ--ይህች ክህደት የፈጸመች ተቋም በጉያዋ ካቀፈቻቸው መሰል ተቋማት ጋር ባላት ኅብረት በአውሬው ላይ ተቀምጣ መላው ዓለም በእግዚአብሔር ላይ እንዲነሳ ታደርጋለች (ራእ. 17፡1-11)፡፡

መጋቢት 8
Mar 17

አመንዝራዋ ባቢሎን


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡1፡፡ ባቢሎን የተቀመጠችበት “ብዙ ውሃ” የኤፍራጥስ ወንዝ መሆኑን ኤር. 51፡13 ያሳየናል፡፡ ብዙ ውሃ በራእ. 17፡15 መሰረት ምን ያመለክታል?



በመጽሐፍ ቅዱስ ሴት የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ትወክላለች፡፡ በራእይ መጽሐፍ የእግዚአብሔር እውነተኛ ቤተ ክርስቲያን በንጽህት ሴት ተመስላ ቀርባለች (ራእ. 12፡ 1፣ 22፡17)፡፡ በተቃራኒው አመንዝራዋ ሴት ክህደት የፈጸሙትን እና ታማኝ ያልሆኑትን ሕዝቦች ትወክላለች፡፡ ይህች አመንዝራ ሴት በራእ. 17፡5 ታላቂቷ ባቢሎን በሚል ስያሜ ትታወቃለች፡፡ የጥንታዊቷ ባቢሎን ህልውና የቆመው በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ እንደነበር ሁሉ የመጨረሻ ዘመኗም ባቢሎን እቅዷን ለመተግበር የምትተማመነው በብዙሃኑ ላይ ይሆናል፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡2፣ 14፡8፣ 18፡2-3፡፡ ከመጨረሻ ዘመኗ ባቢሎን ጋር ሕገ ወጥ ግንኙነት ውስጥ የገቡና በሐሰተኛ ሽንገላዋ ስር የወደቁ በሁለት ቡድን የቀረቡ ሕዝቦች እነማን ናቸው?



የመጀመሪያው ቡድን ሕዝብን የመግዛትና የማስተዳደር ሥልጣን ያላቸው የፖለቲካ ኀይላት ሲሆኑ እነርሱም የምድር ነገሥታት በሚል ቀርበዋል፡፡ ይህ ቡድን ከአመንዝራዋ ባቢሎን ጋር አብሮ እንዳመነዘረ ሆኖ ቀርቦአል፡፡ በብሉይ ኪዳን-ጣዖቶቿን ተከትላ በእግዚአብሔር ላይ ክህደት የፈጸመችውን እስራኤል ለማመልከት ምንዝር የተሰኘው ቃል በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ውሎአል (ኢሳ. 1፡21፣ ኤር. 3፡1-10)፡፡ በምድር ነገሥታትና በአመንዝራዋ መካከል የቀረበው የምንዝር ግንኙነት በመጨረሻ ዘመኗ ባቢሎን እና በገዢዎቹ የፖለቲካ ኃይላት መካከል የሚከሰተው ያልተገባ ሕብረት ተምሳሌት ነው፡፡

ከአመንዝራዋ ባቢሎን ጋር ሕገ ወጥ ግንኙነት ውስጥ የሚገባው ሁለተኛው ቡድን--ተገዢው ማለትም ብዙሃኑ የምድር ነዋሪ ይሆናል፡፡ እነዚህ--ከመንፈሳዊው የባቢሎን ምንዝር ወይን ጠጅ እንዲጠጡ የሆኑ ናቸው፡፡ በሥልጣን ላይ ካሉት የፖለቲካ ኃይላት በተጓዳኝ፤ ባቢሎን ጥላ ከለላ ትሆነናለች ብሎ በስህተት ያሰበው አብላጫው ሕዝብ በተቋሟ አሳች አስተምህሮና ልማድ ይሰክራል፡፡ ሰው ሲሰክር በአልኮል ተጽእኖ ስር ስለሚወድቅ በአግባቡ ማሰብ ይሳናቸዋል (ኢሳ. 28፡7)፡፡ ከእግዚአብሔር ታማኝ ትሩፋን ውጪ የተቀረው ዓለም በተሳሳተ መንገድ ይመራል፡፡ በቀደሙት ጊዜያት እንዲሁም ዛሬ እየሆነ እንዳለው በመጨረሻውም ጊዜ አብላጫው ሕዝብ በተሳሳተ አቅጣጫ ያመራል፡፡ ይህ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ዝነኛ አመለካከቶች ተከትሎ መንጎድ ስለሚያስከትለው አደገኛ ውጤት ምን ሊነግረን ይገባል?

መጋቢት 9
Mar 18

በአውሬው ላይ የተቀመጠችው አመንዝራ ሴት


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡3፡፡ አመንዝራዋ ሴት በብዙ ውሃ ላይ መቀመጧን የሚነግረን ዮሐንስ በአውሬው ላይ መቀመጧንም ይገልጽልናል፡፡ የውሃ እና አውሬ ተምሳሌት የባቢሎንን ደጋፊዎች ጥሩ አድርጎ የሚገልጸው እንዴት ነው?



ዮሐንስ በራእይ ወደ በረሃ ከተወሰደ በኋላ በውሃዎች ሳይሆን በቀይ አውሬ ላይ የተቀመጠች ሴት እንዲመለከት ይደረጋል፡፡ አመንዝራነቷ ኃይማኖታዊውን አካል ሲወክል አውሬው ደግሞ የፖለቲካዊው ሥልጣን ተምሳሌት ነው፡፡ ኃይማኖታዊው ኀይል እምነት ዐልባውንና የፖለቲካዊውን ኃይል መጋለቡን የሚያሳየው ትዕይንት፤ በቀደሙት ዘመናት ኃይማኖትና ፖለቲካ ጋብቻ ሲፈጥሩ ያልታየ ክስተት ነው። ትንቢቱ እንደሚያሳየን ከሆነ በመጨረሻ ላይ እነዚህ ሁለቱ ሕብረት ይፈጥራሉ። አውሬን የመጋለብ ጽንሰ ሃሳብ--የበላይነትን ያሳያል፡፡ ይህ ደግሞ በመጨረሻው ጊዜ እምነት ዐልባውና የፖለቲካው ዓለም በኃይማኖታዊ ሥርዓት ተጽእኖ ስር እንደሚውሉ ያሳያል፡፡

በራእ. 12 እና 13 ከቀረቡት ከባሕር ከወጣው አውሬ እና ከምድር ከወጣው አውሬ የትኛው ባህሪ ወደ ዘንዶው ያመላክታል? ሐምራዊ ቀይ ልብስ በመጎጸናፍ፣ በወርቅ፣ በከበሩ ድንጋዮችና በዕንቁዎች በማጌጥ ተሽሞንሙና የቀረበችው የዚህች አመንዝራ ሴት ሁኔታ፤ በጥንት ዘመን ሴተኛ አዳሪዎች የሰዉን ልብ ለማማለል ይጠቀሙበት የነበረ ዓይነተኛ ዘዴ ነው (ኤር. 4፡ 30)፡፡ የተጎናጸፈችው ልብስ የደም ዓይነት ቅላት፤ ያዚህን ኃይማኖታዊ ሥርዓት ጨቋኝ ባህሪ ያመለክታል፡፡

በተጨማሪ አመንዝራዋ የለበሰችው ልብስ በብሉይ ኪዳን--ከሐምራዊ፣ ቀይ ማግ እና ወርቃማ የሊቀ ካህናቱ ልብሰ ተክኅኖ አንዱን ያመለክታል (ዘፀ. 28፡5-6)፡፡ እንዲሁም በማኅተም ተቀርጾ በካኅኑ ግምባር በጥምጣም ከሚታሰረው “ቅድስና ለእግዚአብሔር” ከሚለው በተመሳሳይ በእርሷም ግምባር ላይ የምስጢር ሥም ተጽፎ ነበር፡፡ በእጇ የያዘችው ጽዋ በመቅደሱ በግልባጭ የቀረበ የመጠጥ መሥዋዕት ነው (ዘፀ. 30፡9)፡፡ ይህ የመጨረሻው ዘመን ኃይማኖታዊ ሥርዓት በዚያው ታሪካዊ አቋሙ ጸንቶ ዓለምን እያማለለ ከአምላካዊው መንገድ በማሳት የሰይጣን ብርቱ መሣሪያ ይሆናል፡፡ ኃይማኖታዊ ተቋሟ የቱንም ዓይነት ውጪያዊ ገጽታ ልትላበስ ብትችልም፤ ነገር ግን አመንዝራና የአመንዝራዎች እናት ናት፡፡

ከዚህ ባለፈ አመንዝራዋ ሴት በቅዱሳን እና ለክርስቶስ ምስክር በመሆናቸው በተሰዉ የየሱስ ሰማዕታት ደም የሰከረች ሆና ተገልጣለች፡፡ ይህ ደግሞ የመጨረሻዋን ዘመን ባቢሎን በመካከለኛው ዘመን በጳጳሳዊው ሥርዓት ይመራ የነበረውንና ለወንጌል ታማኝ ሆነው በመጽናታቸው ሰማዕት በሆኑ በሚሊዮን በሚቆጠሩ የምዕራብ አውሮፓ ክርስቲያኖች ላይ ከተፈጸመው የክህደት ሁኔታ ጋር ያስተሳስራታል፡፡ ክህደት የፈጸመችው አመንዝራዋ ባቢሎን የተገለጠችበት መንገድ በትያጥሮን ቤተ ክርስቲያን የቀረበችውን ኤልዛቤል ያንጸባርቃል (ራእ. 2፡ 20-23)፡፡ በእነዚህ ሁለት ሴቶች መካከል የቀረበው መመሳሰል የዘመን መጨረሻዋን ባቢሎን ባህሪ እንዴት ያብራራል?

መጋቢት 10
Mar 19

የአውሬው መለያ ባህሪ


ዮሐንስ በራእ. 17፡6-7 በተመለከታት አመንዝራ ሴት በእጅጉ ተደንቆአል፡፡ ምናልባት የተደነቀበት ምክንያት አንዳንድ ባህሪዎቿ ቅዱሳንን እንዲዋጋና ድል እንዲነሳ (ራእ. 13፡5-7) ኃይል ከተሰጠው ከራእ. 13ቱ ከባሕር የወጣው አውሬ ጋር ካለው መመሳሰል አኳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ኃይል ሴቲቱ ለ1200 ዓመታት (መካከለኛው ዘመን) ወደ በረሓ እንድትሰደድ መንስዔ ሆኗታል፡፡

ፕሮቴስታንቶች ያለፈውን አስከፊ የስደት ዘመን በማስታወስ በክርስትና ድርጅቶች መሃል የተሻለ መግባባትና የቀረበ ትብብር ሊኖር ይገባል ለሚለው ለዚህ ዘመኑ ኃይማኖታዊ ፍልስፍና የተሻለ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ዕድል ሊጠቀሙ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ትንቢቱ እንደሚናገረው ከሆነ፤ ካለፈው ጋር የሚመሳሰል ግን የከፋ ሁኔታ ዳግም መከሰቱ አይቀሬ ነው፡፡ ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡8፡፡ የዚህን ጥቅስ የቃላት አገባብ ከራእ. 13፡8 ጋር ያስተያዩ፡፡ ራእ. 13፡3 የአውሬውን የሕልውና እና እንቅስቃሴ ሦስት ምዕራፎች እንዴት ያብራራቸዋል?



ቀዩ አውሬ--ቀደም ሲል የነበረ፣ አሁን ግን የሌለ፣ በኋላ ከጥልቁ ጉድጓድ የሚወጣና ወደ ጥፋት የሚሄድ በሚል ተገልጾአል፡፡ ሲጀመር ይህ ሦስት የለውጥ ምዕራፍ-የሚንቀሳቀሰው በሐሰተኛ መለኮታዊ ስያሜ ነው--“ካለው፣ ከነበረውና ከሚመጣው” (ራእ. 1፡4፣ 4፡8)፡፡ በተጨማሪ አውሬው ያለፈባቸውን የሚከተሉትን ሦስት ምዕራፎች ያመላክታል፡

(1)አውሬው ቀደም ሲል “ነበረ”፡፡ ይህ ቃል አውሬው በትንቢታዊዎቹ 1,260 ቀናት የነበረውን እንቅስቃሴ ይጠቁማል (ራእ. 13፡5)፡፡

(2)“የሌለ፡፡” አውሬው በገጠመው ለሞት የሚያደርስ ቁስል (ራእ. 13፡3) ወደ የሌለ ሁናቴ ውስጥ ለመግባት ተገደደ (1798)፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያቶች ከዓለም ዕይታ ቢሰወርም--ተርፎ ማንሰራራት ችሎአል፡፡

(3)በመጨረሻ ለሞት ያደርሰው ከነበረው ቁስል መፈወሱን ተከትሎ፤ አውሬው በሙሉ ሰይጣናዊ ቁጣ ወደ ህይወት ይመለሳል፡፡ በራእ. 13፡1-8 የቀረበው አውሬው ከቁስሉ በተፈወሰበት ወቅት ያለውን ሁናቴ ራእ. ምዕ. 17 ይገልጸዋል፡፡ እንዲሁም አመንዝራዋ ባቢሎን በዚህ በዳነው አውሬ ላይ ተቀምጣበታለች፡፡

በመካከለኛው ዘመን እንደሆነው ሁሉ አሁንም በኃይማኖትና በፖለቲካ መሃል ለአጭር ጊዜ የሚዘልቅ ሕብረት ይፈጠራል፡፡ ከዚያም ስደት ዳግም ያገረሻል፡፡ “ተቃውሞ ቢነሳ፣ አክራሪነትና አለመቻቻል ቢያገረሽ፣ ስደት ዳግም ቢቀጣጠል፣ በግማሽ ልብ ያሉ ቢዋልሉም--እውነተኛ ክርስቲያን ግን ከብልጽግናዎቹ ዘመናት ይልቅ በዚህ ወቅት እንደ ዐለት ጸንቶ ይቆማል፣ እምነቱ የበረታ፣ ተስፋውም ያበራ ይሆናል፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 602. የመጨረሻዎቹ አስፈሪ ክስተቶች ተግባራዊ ከመሆናቸው አስቀድሞ የዛሬው የክርስትና ተሞክሮአችን ምን ሊመስል እንደሚገባ ከዚህ መልእክት ልንወስድ የሚገባው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

መጋቢት 11
Mar 20

ሰባቱ የአውሬው ራሶች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡9-11፣ ራእ. 13፡18፡፡ ሰባቱን ራሶች ለማስተዋል ጥበብ ያለው አእምሮ ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ የቀረበው ጥበብ ምን ዓይነት ነው? ለመሆኑ አንድ ሰው ይህን በመለኮት የሚሰጥ ጥበብ ማግኘት የሚችለው እንዴት ነው (ያዕ. 1፡5)?



ሰባቱ ራሶች ሰባት ተራሮች መሆናቸውን መልአኩ ሲገልጽ ይታያል፡፡ አንዳንድ ተርጓሚዎች እነዚህ ሰባት ተራሮች የሮም ከተማ የምትገኝባቸው ሰባት ኮረብታዎች እንደሆኑ ያስባሉ፡፡ በዚህ የተነሳ በግርክኛው oroi ወይም ተራሮች የሚለውን ቃል ኮረብቶች ብለው ይተረጉማሉ፡፡ እንዲሁም በሰባቱ ተራሮች የተመሰሉ ሰባት ነገሥታት አሉ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ተራሮች ተከታታይ ቢሆኑም--በአንዴ ፍጻሜ የሚያገኙ አይደሉም፡፡

የራእይ መጽሐፍ ተዛምዶ ወጥነት ካለው ሥርዓት ጋር በመሆኑ፤ የሥርዓቱ አካል ሳይሆኑ የሚነሱ ነገሥታትን እነዚህ ተራሮች አይወክሉም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ ተራሮች የዓለም ልዕለ ኃያል መንግሥታትን ይወክላሉ (ኤር. 51፡ 25፣ ሕዝ. 35፡2-3)፡፡ “ነገሥታት” በመጽሐፍ ቅዱሳዊው ትንቢት--መንግሥታት የሚል ፍቺ አለው (ዳን. 2፡37-39፣ 7፡17)፡፡ በዚህ የተነሳ ሰባቱ ተራሮች ሰይጣን እግዚአብሔርን ሲቃወምና የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ሲጎዳ በኖረባቸው፣ በዘመናት በዓለም ላይ ተጽእኖ ያሳደሩ ልዕለ ኃያል መንግሥታትን እንደሚወክሉ ይታሰባል፡፡ ዮሐንስ በነበረበት ዘመን ከእነዚህ መንግሥታት አምስቱ ሲወድቁ አንዱ ግን ነበር፤ ሌላኛው ደግሞ ገና አልመጣም፡፡ እነዚህ በብሉይ ኪዳን ዘመን የነበሩ፣ የወደቁ ልዕለ ኃያል መንግሥታት አልፎ አልፎ በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ጉዳት ያደረሱ ሲሆን እነርሱም፡ ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ፋርስ እና ግሪክ ናቸው፡፡

“ገና ያልመጣው” ሰባተኛው መንግሥት በራእ. 13 የተጠቀሰው አውሬ ሲሆን ይኸውም በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ተጽእኖና ጉዳት ያደረሰ በመካከለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያንን የመራ ጳጳሳዊ ሥርዓት ነው፡፡ ሥርዓቱ ከዮሐንስ በኋላ እና ከአረማዊው ሮም ውድቀት በኋላ የመጣ ነበር፡፡ እነዚህ ክስተቶች ከመገለጣቸው ከአያሌ መቶ ዓመታት አስቀድሞ ለተጻፉት ትንቢቶች እውነትነት ታሪክ እማኝነቱን ይሰጣል፡፡

ቀዩ አውሬ ወደ ስምንተኛ ራስነት የማምራት ሂደት ላይ መሆኑን ዮሐንስ አክሎ ቢናገርም ሆኖም ይህ ራስ ከሰባቱ አንዱ እንደሆነ ይገልጽልናል፡፡ ከሰባቱ መሃል ስምንተኛ የሆነው የቱ ነው? ራሶቹ የዘመንን ቅደም ተከተል ጠብቀው የሚሄዱ እንደመሆናቸው ስምንተኛው ራስ ለሞት የሚያደርስ ቁስል ደርሶበት የነበረው ሰባተኛ ራስ መሆኑን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ቀዩ አውሬ አመንዝራዋን ባቢሎን በስምንተኛው ራስ የተሸከማት በዚህ ወቅት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ እነሆ ዛሬ ለሞት የሚያደርሰው ቁስል የተፈወሰበት ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡ የምድር መጨረሻ ሊደርስ ጥቂት ሲቀር የስምንተኛው ራስ ትዕይንት ተገልጦ ወደ ዘላለማዊ ጥፋት ያመራል፡፡

መጋቢት 12
Mar 21

የባቢሎን ውድቀት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡12-15፣ ራእ. 16፡12-16፡፡ ከጥቅሶቹ ስለ “ዐሥሩ ነገሥታት” ምን ይማራሉ?



ዐሥሩን ነገሥታት አስመልክቶ የተለያዩ ፍቺዎች ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ ለነገሩ የራእይ መጽሐፍ የነገሥታቱን ማንነት አይነግረንም፡፡ ከጥቅሶቹ የምናገኘውን መረጃ ለማጠናከር ስንሞክር መጨረሻው ከመምጣቱ ጥቂት ቀደም ብሎ የሚከሰቱና አመንዝራይቱን በመደገፍ ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ የፖለቲካ ኅብረት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ቁጥራቸው ለአውሬው ታማኝነታቸውን የሚገልጹትን የዓለም ኃይላት ድምር ይወክላል፡፡ ቀደም ሲል በራእ. 12፡12-17 የተዋወቀውን የአርማጊዶን ጦርነት ራእ. 17፡13-14 በአጭሩ ደጋግሞ ይናገረዋል፡፡ በሰይጣናዊው ኅብረት የተዋወቀው ዓለማቀፉ የፖለቲካ ኪዳን ጥምረት በበጉ ላይ ጦርነት ይከፍታል፡፡ የመጨረሻው ዐውደ ውጊያ በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረግ ወታደራዊ ትንቅንቅ ሳይሆን--ሰይጣንና የፖለቲካ ኪዳን ጥምረቱ እንዲሁም ክርስቶስና ታማኝ ሕዝቦቹ የሚያደርጉት ፍልሚያ ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 17፡16-18፡፡ በራእ. 16፡2-12 መሰረት ዐሥሩ ነገሥታት በባቢሎን ላይ ያላቸውን አመለካከት ከመለወጣቸው ጀርባ ምን አለ? በባቢሎን ላይ ከተከሰተው ነገር ጀርባ ማን አለ?



የኤፍራጥስ ወንዝ መድረቅ ሌላው የታሪኩ አጠቃላይ ገጽታ መግለጫ መንገድ ነው (ራእ. 16፡12)፡፡ በጥላቻ ተሞልተው የነበሩት ዐሥሩ ቀንዶች ሳይታሰብ በአመንዝራዋ ባቢሎን ላይ ይነሱና ባዶዋን ማለትም ራቁቷን ያስቀሯታል፡፡ ሥጋዋንም በልተው በእሳት ያቃጥሏታል፡፡ ዮሐንስ በአመንዝራዋ የሩሳሌም ላይ የተሰጠውን ይህን ፍርድ የሚያመለክተውን ትዕይንት ለመግለጽ ጥቅም ላይ ያዋለውን ቋንቋ የወሰደው ከብሉይ ኪዳን ነው (ኤር. 4፡30)፡፡ በእሳት የማቃጠል ቅጣት ሥራ ላይ ይውል የነበረው የካህን ሴት ልጅ ዝሙት አዳሪ ሆና ስትገኝ እንደ ነበር በዘሌዋ. 21፡19 እንመለከታለን። ባቢሎን ከሚወርደው መቅሰፍት ለሳቱት የፖለቲካ ኃይላት ጥላ ከለላ ልትሆን አለመቻሏ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ እንዳደረገባቸው በራእ. 16፡10-12 ቀርቦአል፡፡ እነዚህ ኃይላት እንደ ተታለሉ ስለገባቸው በብርቱ ጥላቻ ጥቃት ይሰነዝሩባታል፡፡ ይህ በመጨረሻው ዘመን ክህደት የሚፈጽም ኃይማኖታዊ ተቋምና ራሳቸውን ከዚህ ሥርዓት ጋር ለመፈረጅ የሚመርጡ ሁሉ አምላካዊውን ፍርድ በሙላት ይቀበላሉ፡፡

ከመጨረሻው ጊዜ አኳያ አሁንም ገና ያልተመለሱና ግራ ሊያጋቡ የሚችሉ አያሌ ጥያቄዎች መኖራቸው እሙን ነው፡፡ በራእ. 17፡14 ምን ዓይነት ፍቱን ተስፋ ተሰጥቶአል? ይህ ተስፋ ለእኛ ምን ማለት ሊሆን ይችላል?

መጋቢት 13
Mar 22


ተጨማሪ ሀሳብ


በባቢሎን ላይ ውድቀት ከመድረሱ አስቀድሞ “‘ ሕዝቤ ሆይ፣ ከእርሷ ውጡ’ ” (ራእ. 18፡4) የሚል ከሰማይ የመጣ ድምፅ በባቢሎን ለሚገኙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጥሪ ያቀርባል፡፡ አያሌ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ወገኖች በተለያዩ ምክንያቶች ዛሬም በባቢሎን አሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ክህደት ከፈጸመችው ኃይማኖታዊ ተቋም ኃጢአት ጋር እንዳይተባበሩ እግዚአብሔር የመጨረሻዋን ዘመን ቤተ ክርስቲያኑን ተጠቅሞ ጥሪ ያደርግላቸዋል፡፡ ከሚደርስባት አስከፊ መጨረሻ ለማምለጥ ከእርሷ መውጣታቸው የግድ ይሆናል፡፡

በባቢሎን ያለ ማንም ሰው ይጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፍላጎት አይደለም፡፡ አያሌ በባቢሎን የሚገኙ ፈሪሐ እግዚሓር ያላቸው ወገኖች ለዚህ ጥሪ ምላሽ እንደሚሰጡ ራእ. 19፡1-10 ይናገራል። እንደ እግዚአብሔር ትሩፋን ሕዝብነታችን የተጣለብንን ብርቱ ኃላፊነት ያስቡ። የእግዚአብሔር ኃይል በእጅጉ በሕይወታችን ማስፈለጉን አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?


የመወያያ ጥያቄዎች




1.እግዚአብሔር “ሕዝቤ” ብሎ የሚጠራቸው፤ እርሱን የሚፈሩ እጅግ ብዙ ሕዝቦች እንዳሉት ራእ. 18፡4 ያሳየናል፡፡ “ይህ መልእክት መሰጠቱ የግድ ቢሆንም ነገር ግን ይህ ሲሆን፤ እኛ ብርሃን ያለን--ብርሃን የሌላቸውን እንዳናስገድድ፣ እንዳናስጨንቅና እንዳንኮንን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ካቶሊኮችን በጣም በመጫን ከመንገዳችን ማፈንገጥ የለብንም፡፡ በካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሃል የሚበራላቸውን ብርሃን ተከትለው የሚራመዱና እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የሚሠራላቸው አያሌ ጥንቁቅ ክርስቲያኖች አሉ፡፡ ታላላቅ ጥቅሞችና አጋጣሚዎች እጆቻቸው ገብተው እያሉ አካላዊውን፣ አእምሮአዊውንና ሥነ ምግባራዊውን ማንነት ከማጎልበት የተሰናከሉ. . . በተሳሳተ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ውስጥ እየተመላለሱ ለሌሎች መልካም ለማድረግ ከሚጥሩት ይልቅ በከፋ አደጋና ኩነኔ ውስጥ ናቸው፡፡”—Ellen G. White, Evangelism, p. 575. ሌሎችን እንዴት ልንቀርብና ተገቢውን ጥንቃቄ ልናደርግ እንደሚገባ አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?

2.ራእ. 17 በቀይ አውሬ ላይ ስለ ተቀመጠችው አመንዝራ ሴት ገለጻ ያደርጋል፡፡ በራእ. 12 የምናገኛት ሴት የእግዚአብሔርን ታማኝ ቤተ ክርስቲያን ስትወክል፤ በምዕ. 17 የምናገኛት ደግሞ ዓለምን እያባበለች ከእግዚአብሔር የምታርቀዋ ተምሳሌት ነች፡፡ በእርስዎ አመለካከት በእነዚህ በሁለቱ መካከል ያለው መመሳልና መለያየት ምንድን ነው? በዋነኝነት-ከዚህ ንጽጽር ምን እንማራለን?

3.በዚህ ሣምንት የተመለከትናቸው ጥቅሶች ክርስቶስ በድል አድራጊነት ዳግም ከመመለሱ አስቀድሞ ባሉት የመጨረሻ ምዕራፎች ኃይማኖታዊውና ፖለቲካዊው ዓለም የሚገኝበትን አስጠሊታ ሁናቴ ያስቃኛሉ፡፡ እግዚአብሔር ለሰጠን መልእክቶች አሁኑኑ ታማኝ፣ እውነተኛ እና ንጹህ መሆናችን በእጅጉ አስፈላጊ ስለ መሆኑ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል? ዓለም በክህደት ስትጥለቀለቅ እኛ ግን በታማኝነት እንድንራመድ ስለ ቀረበልን ጥሪ ራእ. 16፡15 ያንብቡ፡፡ ይህን ማስጠንቀቂያ አሁኑኑ በየግላችን መተግበር የምንችለው እንዴት ነው?