የዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከጥር 25 - የካቲት 1

6ኛ ትምህርት

Feb 02 – Feb 08




የታተሙት የእግዚአብሔር ሕዝቦች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 7፣ 2ጴጥ. 3:9– 14፣ ዘዳ. 8:11–17፣ ራእ. 14:4-5፣ 12፣ 17:5፣ ሮሜ 3:19–23፡፡


መታሰቢያ ጥቅስ :- “ ‘እነዚህ ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው አንጽተዋል’” (ራእ. 7፡14)፡፡

በ ክርስቶስ አምናለሁ የሚል እያንዳንዱ ግለሰብ ስለታማኝነቱ አምላካዊውን በረከት ሲቀበል፤ በተቃራኒው በዐመጻ የቀጠሉ--ከኩነኔ ጋር እንደሚጋፈጡ የሰባቱ ማኅተሞች መከፈት መልእክት ያሳየናል፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራት ማኅተሞች እግዚአብሔር ሕዝቡን ከመንፈሳዊ ልፍስፍስነት አንቅቶ ባለ ድል የሚያደርግበትን ቅጣት ነክ አካሄዶች ይገልጻሉ፡፡ በተጨማሪም የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለወንጌል ጸለምተኛ ብሎም ጸር በሆነው በዚህ ዓለም ኢፍትሐዊ ፍርድና የመከራ ገፈት ይቀበላሉ፡፡

እግዚአብሔር ሕዝቦቹን የጎዱትን ለማስተናገድ ያለው ዝግጁነት በስድስተኛው ማኅተም መከፈቻ ላይ ይታያል፡፡ እዚህ ላይ ምዕራፍ 7 በተለይ በስድስተኛውና በሰባተኛው ማኅተሞች መካከል መግባቱን ልብ ይሏል፡፡ ስድስተኛው ማኅተም ወደ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይዞን ይመጣል፡፡ በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዐመጸኞች ፍርድ ሲጠብቃቸው፤ በታማኝነት ጸንተው የቆሙት ግን ይታተማሉ ሲል ራእ. 7 ይነግረናል፡፡

ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ያሉትን የእግዚአብሔር የመጨረሻ ዘመን ሕዝቦች ራእ. 7 ለይቶ ያስቀምጣቸዋል፡፡ የእነዚህ ሕዝቦች ሌሎች መለያ ባህሪዎች በራእ. 14፡ 1-5 ቀርበዋል፡፡ ስድስተኛውና ሰባተኛው መለከት በሚነፋበት ወቅት በመሃል የገባ አንድ ሌላ የዕረፍት ጊዜ አለ (ራእ. 10፡1፣ 11፡14)፡፡ ይህ የዕረፍት ጊዜ ከምዕ. 7ቱ ትዕይንት የጊዜ ሁናቴ ጋር ስምሙ በመሆን የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ጊዜ ሕዝቦች ተሞክሮና ተግባር ይገልጻል፡፡

ጥር 26
Jan 10

ነፋሳቱን መያዝ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 7:1–3፣ 2ጴጥ. 3:9–14፡፡ መላአክቱ ነፋሶቹን የሚይዙት እስከ መቼ ነው? በግንባር ላይ የማተሙ ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ ምን ይከሰታል?



ነፋሳት በብሉይ ኪዳን አውዳሚውን ኃይል ይወክላሉ፡፡ ነፋስ እግዚአብሔር በዐመጸኞች ላይ የሚሰጠውን ፍርድ የሚያስፈጽምበት መንገድ በመሆን ይታወቃል፡ ፡ዳግም ምጽአቱ እውን ከመሆኑ ጥቂት ቀደም ብሎ ንስሐ ባልገቡ ዐመጸኞች ላይ የሚወርዱት መቅሰፍቶች፤ የመጨረሻዎቹ ሰባት መቅሰፍቶች የሚገለጡበት ሌላው መንገድ ነው (ራእ. 16)፡፡ ሆኖም የእግዚአብሔር ሕዝቦች መታተም እስኪጠናቀቅ እነዚህ አውዳሚ ኃይላት ከሚያደርሱት ጥፋት እንዲገቱ ይደረጋሉ፡፡

ጥንታዊው የማኅተም ተቀዳሚ ፍቺ ባለቤትነትን ያመላክታል፡፡ በአዲስ ኪዳን መታተም ማለት “ ‘ጌታ የእርሱ የሆኑትን ያውቃል’ ” (2 ጢሞቴ. 2:19) የሚል ተምሳሌታዊ ፍቺ አለው፡፡ የገዛ ሕዝቦቹን ጠንቅቆ የሚያውቀው እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ያትማቸዋል (ኤፌ. 1፡13-14፣ 4፡30)፡፡ በመጨረሻዎቹ ቀናት በግንባር ላይ የሚታተመው የእግዚአብሔር ማኅተም በእርሱ በኩል ለመቆም የመረጡትን ወገኖች የሚያመላክት ይሆናል (ራእ. 14፡1)፡፡ የእግዚአብሔር ማኅተም በዐይን የሚታይ ምልክት ሳይሆን “እንዳይናወጡ ሆኖ በአእምሮም ሆነ በመንፈስ በእግዚአብሔር እውነት ላይ ተረጋግቶ ማረፍ ነው”—Ellen G. White, Last Day Events, p. 220. ፈቅደውና ዐውቀው በአውሬው ወገን የቆሙ የአውሬውን ምልክት ይቀበላሉ (ራእ. 13፡16-17)፡፡

በአምላካዊው ማኅተም የታተሙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ታማኝነት በያንዳንዱ ትውልድ ሲፈተን ኖሮአል፡፡ ሆኖም ታማኞች በመጨረሻው አስከፊ ወቅት የሚደርስባቸው ፈተና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ያለ ጥሰት መጠበቅ ይሆናል (ራእ. 12፡17፣ 14፡12)፡፡ በተለይ አራተኛው ትእዛዝ እግዚአብሔርን የመታዘዛችን መፈተኛ ይሆናል (ራእ. 14፡7)፡፡ በረጅሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሰንበት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ምልክት እንደ ነበር (ዘፀ. 31:12–17፣ ሕዝ. 20:12፣ 20) ሁሉ በመጨረሻውም ቀውስ ወቅት ለእግዚአብሔር የሚኖረን ታማኝነት ምልክት ይሆናል፡፡ በተጨማሪ ማኅተም በኋለኛው ዘመን ገቢራዊ ከሚሆኑት የመጨረሻዎቹ አውዳሚ ሰባት መቅሰፍቶች መጠበቂያ ምልክት ሆኖ ያገለግላል (ሕዝ. 9፡1-11፣ ራእ. 7፡1-3)፡፡ ይህን ተከትሎ በራእ. 6፡17 ለሚነሳው ጥያቄ የመጨረሻ ምላሽ ይሰጣል፡ በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ከለላ አግኝተው መቆም የሚችሉት የታተሙት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይሆናሉ፡፡

ጳውሎስ ለቤዛ ቀን የታተምንበትን መንፈስ ቅዱስ ማሳዘን እንደ ሌለብን ያስጠነቅቀናል (ኤፌ. 4፡30)፡፡ ሐዋርያው ምን ማለቱ ነው? ለመሆኑ አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝነው እንዴት ነው? መልሱን ካገኙ፤ እርሱን እንዳያሳዝኑ ሊረዳዎ የሚችሉ ምን ዓይነት ምርጫዎች ማድረግ ይችላሉ?

ጥር 27
Jan 10

የታተሙት የእግዚአብሔር ሕዝቦች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 7፡4-8፡፡ ለመሆኑ የታተሙት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቁጥር ምን ያህል ነው? የዚህ ዉሱን ሆኖ የቀረበ አኻዝ ትርጉም ምንድን ነው?



የታተሙት ወገኖች ቁጥር የተቀመጠበት አካሄድ የኅትመት ሥራው ፍጻሜ ማግኘቱን ያመለክታል፡፡ ከ12ቱ የእስራኤል ነገዶች የተውጣጡት 144 ሺ መሆናቸውን ዮሐንስ የሰማው ቁጥር ይገልጻል፡፡ እዚህ ላይ የቀረበውን የቁጥር ማጣቀሻ ቃል በቃል በመውሰድ ፋንታ በተምሳሌትነት ሊያመላክት ለፈለገው ነጥብ አጽንኦት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ ይህ አኻዝ 12 x 12 x 1,000 = 144,000 ውጤት ነው፡፡ አሥራ ሁለት ቁጥር የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተምሳሌታዊ አኻዝ ነው፡፡ 12ቱ የእስራኤልን ነገዶች እንዲሁም በ12ቱ ሐዋርያት መሠረት ላይ የታነጹት ቤተ ክርስቲያናት (ኤፌ. 2፡20) ለአብነት መወሳት ይችላሉ፡፡

ስለዚህ ይህ የጥንቷ እስራኤል ዘመናዊ ማሳያ የሆነ ተምሳሌታዊ 144,000 የመጨረሻውን ዘመን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይወክላል፡፡ በእርግጥ በራእ. 7 የቀረቡት 12ቱ የእስራኤል ነገዶች ተምሳሌታዊ አይደሉም፡፡ ምክንያቱም 12ቱን የእስራኤል ነገዶች ዛሬ አናገኛቸውም፡፡ እስራኤላውያን በአሦራውያን ሽንፈት በገጠማቸው ወቅት ዐሥሩ ነገዶች በምርኮ ተወስደው የነበረ ሲሆን (2ነገሥ. 17፡6-23) በዚህም ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተዋህደው ነበር፡፡ ስለዚህ የዛሬው ይሁዲነት 12ቱን ነገዶች የሚያሟላ አይደለም፡፡

እንዲሁም በራእ. 7 የቀረቡት 12 ነገዶች መደበኛውን ዝርዝር አያመላክቱም፡፡ በሮቤል ነገድ ፋንታ ይሁዳ በመጀመሪያ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ዳን እና ኤፍሬም ግን ከነጭራሹ አልተጠቀሱም፡፡ በእነርሱ ምትክ ዮሴፍ እና ሌዊ ተካትተዋል፡፡ ዳን እና ኤፍሬም ያልተካተቱበት ዋንኛ ምክንያት በብሉይ ኪዳን ዘመን ክህደት የፈጸሙና በጣኦት አምልኮ የወደቁ ስለነበሩ ነው (ይሁዳ 18:27–32፣ ሆሴ 4:17)፡፡ በራእ. 7 የተጠቀሱት ነገዶች ዝርዝር ታሪካዊ ሳይሆን መንፈሳዊ ነው፡፡ የዳን እና ኤፍሬም ነገዶች ታማኝ አለመሆን--ከታተሙት የእግዚአብሔር ሕዝቦች መሃል ስፍራ እንደሌላቸው ያሳየናል፡፡ እንዲሁም የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን እንደ 12ቱ የእስራኤል ነገዶች መጠቀሷን እንመለከታለን፡፡ በራእ. 7 የተጠቀሱት 12ቱ ነገዶች አይሁዳውያንንና አረማውያንን ጨምሮ መላውን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይወክላሉ፡፡

እነዚህ 144000 የቀረቡበት መንገድ የጥንት እስራኤላውያን ለውጊያ ሲሄዱ ይከተኩት በነበረ ዓይነት የጦር አሰላለፍ ነው፡፡ በጥንታዊቷ እስራኤል ተዋጊው የጦር ክፍል 1ሺ ወታደሮች ነበሩት (ዘኁ. 31፡3-6)፡፡ ተምሳሌታዊ አኻዝ የሆነው 144,000 ለመጨረሻው ውጊያ ዝግጁ የሆኑ በ1ሺ የጦር ክፍል ውስጥ ያሉ 144 ምድብተኞችን የያዘ የቤተ ክርስቲያን ተዋጊ ሰራዊት ነበር(ራእ. 17፡14)፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚገኘው የጠላት ሰራዊት ደግሞ 200 ሚሊዮን ነበር (ራእ. 9:16)፡፡

ምንም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ የተለመደ ቢሆንም በወታደራዊ አኻዞችና አገላለጾች ሁሌም ምቾት ላይኖረን ይችላል፡፡ የታላቁን ተቃርኖ ተጨባጭ ሁኔታ ጠብቀን መጓዛችን ወታደራዊውን አኻዝና አገላለጽ መገንዘብ እንድንችል እንዴት ይረዳናል?

ጥር 28
Jan 10

እጅግ ብዙ ሕዝብ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 7፡9-14፡፡ ዮሐንስ የሚመለከተው እንዴት ያለውን የቅዱሳን ወገን ነው? እነዚህ ወገኖች የተገለጹበት መንገድ ምን ይመስላል? ከወዴትስ ነው የመጡት? በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት በታላቅ ድምፅ ምን ብለው ጮኹ?



ዮሐንስ የተመለከታቸው እነዚህ እጅግ ብዙ ሕዝቦች “ ‘ከታላቁ መከራ የመጡ፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ያነጹ’ ” (ራእ. 7፡14) ነበሩ፡፡ ታማኝነታቸውን በሚያመለክት ፍጹም በሆነ የእርሱ የጽድቅ ሸማ የተሸፈኑ ሲሆን፤ ይህም በየትኛውም ዓይነት አሰቃቂ መከራ ውስጥ ቢያልፉም ለየሱስ በነበራቸው ታማኝነት ጸንተው የኖሩ ልዩ ሕዝቦች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የምናገኘው ታላቁ የጽድቅ በእምነት ርዕሰ ጉዳይ እነሆ በዚህ ስፍራም ቀርቦ እንመለከታለን፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ከየትኛውም ዓይነት የሕብረተሰብ ክፍል ቢመጡ፣ ከረጅሙ የምድር ታሪክ ወይም የምድር የመጨረሻዎቹ ቀናት 144000 አካል ቢሆኑ-የደኅንነት፣ የዘላለማዊ ህይወት፣ የአዲስ ሰማይና አዲስ ምድር ባለቤት መሆን የቻሉት በጸጋው በተሰጣቸው የክርስቶስ ጽድቅ ብቻ ነው!

“ከዙፋኑ አጠገብ ያሉት ወገኖች ለክርስቶስ በነበራቸው ቅንአት ከሰይጣን ጋር ብርቱ ተጋድሎ ያደረጉ ከእሳት የተነጠቁ ትንታጎች ሲሆኑ፤ አዳኛቸውን ጥልቅ በሆነና በማያባራ አምልኮ ተከትለዋል፡፡ በቀጣይ ያሉት ደግሞ ሐሰተኝነትና ኪዳን ማፍረስ በተንሰራፋበት ዓለም የክርስትናን ባህሪ ጠብቀው በንጽሕና የተመላለሱ፣ የክርስትናው ዓለም አፉን ሞልቶ ተሽረዋል ላላቸው አምላካዊ ሕጎች ተገቢውን ዋጋ የሰጡ፣ በረጅሙ እልህ አስጨራሽ ግብግብ ስለ እምነታቸው ሰማዕት የሆኑ ናቸው፡፡ ‘እነሆ፤ በዙፋኑና በበጉ ፊት ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን፣ ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ቆመው ነበር፤ እነርሱም ነጭ ልብስ ለብሰው፣ የዘንባባ ዝንጣፊ በእጃቸው ይዘው ነበር’ ራእ. 7፡9፡፡ ከእንግዲህ የውጊያቸው ዘመን አክትሞ የድል ባለቤቶች ሆነዋል፡፡

ሩጫቸውን በአሸናፊነት ጨርሰው ሽልማታቸው ላይ ደርሰዋል፡፡ በእጃቸው የያዙት የዘንባባ ዝንጣፊ የድል አድራጊነታቸው ተምሳሌት ሲሆን ነጩ ልብስ ደግሞ አሁን የራሳቸው ያደረጉት የክርስቶስ እንከንየለሽ ጽድቅ ነው፡፡”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 665. አዎ፡ የእምነት ስጦታ በሆነው በክርስቶስ ጽድቅ ተሸፍነናል፡፡ ሆኖም ፈተናና ታላቅ መከራ ሊገጥመን ቢችል እንኳ ታማኝነታችንን ሳናጓድል የእምነታችንን ንጽህና እንደ ጠበቅን መጓዝ የምንችለው እንዴት ነው? ወይም ምቾት በበዛበትና ብልጽግና በተንሰራፋበት ህይወት ያንን እምነትና ታማኝነት ጠብቀን መዝለቅ የምንችለው እንዴት ነው? (ዘዳ. 8:11–17)፡፡

ጥር 29
Jan 10

በጉን የሚከተሉ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡1-5፡፡ የ144000ዎቹ ሦስት ዓይነተኛ መለያ ባህሪያት ምንድን ናቸው? ባህሪያቱ በራእ. 14፡12 ከቀረቡት የመጨረሻው ጊዜ ቅዱሳን ጋር እንዴት ይዛመዳሉ?



አንድ መቶ አርባ አራት ሺዎቹ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የየሱስ እምነት ያላቸው (ራእ. 14፡12) ሕዝቦች አድርጎ ራእ. 14፡4-5 ያቀርባቸዋል፡፡ ምንም እንኳ በምድር የመጨረሻ ምስቅልቅል ወቅት የሰይጣንን ቁጣ በሙላት ቢጋፈጡም፤ ከየሱስ ጋር በነበራቸው የቀረበ ግንኙነት በጽናት መቆም ችለዋል፡፡ ራእ. 17፡5 ከሚሰጠን ብርሃን አኳያ--አንድ መቶ አርባ አራት ሺዎቹ ከሴቲቱ ጋር እንዴት ሳይረክሱ ቀሩ? ይህ “ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት” (ራእ. 14፡4) ሆነው ከሕዝቦች መካከል ከመዋጀታቸው እውነታ ጋር እንዴት ይዛመዳል?



ፆታዊ እርክስና ለእግዚአብሔር ታማኝነትን የማጉደል ተምሳሌት ነው፡፡ ራእ. 17፡ 5 በምድር ታሪክ መዝጊያ ከመላው የዓለም ሕዝቦች ጋር ምንዝር ስለምትፈጽመው ባቢሎንና ልጆቿ ይናገራል (ራእ. 18፡3)፡፡ ሆኖም አንድ መቶ አርባ አራት ሺዎቹ ግን ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው በመጽናት፤ ከባቢሎንና በክህደት ካሉ ኃይማኖታዊ ተቋማት ጋር ሊያረክሱ የሚችሉ ግንኙነቶችን ተቋቁመው ይዘልቃሉ፡ “በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል” (ራእ. 14፡4)፡፡

“ለእግዚአብሔርና ለበጉ በኵራት እንዲሆኑ ከሰዎች መካከል የተዋጁ” (ራእ. 14፡ 4) በሚል ስለ 144000ዎቹ ተጨማሪ መግለጫ ተሰጥቶአል፡፡ በጥንታዊቷ እስራኤል ምርጦቹ የመኸር በኵር ፍሬዎች ለእግዚአብሔር ይቀርቡ ነበር፡፡ በኵራት የተሰኘው ቃል ከዓለም ሕዝቦች በተለየ የዳኑትን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይወክላል (ኤር. 2፡ 3፣ ያዕ. 1፡18)፡፡ 144000ዎቹን የተለዩ የሚያደርጋቸው የዳኑበት መንገድ ሳይሆን ሞትን ሳይቀምሱ መለወጣቸው ነው፡፡ ስለዚህ ረጅም ዘመን ላስቆጠረው መከር በኵራት ናቸው (ራእ. 14፡14-16)፡፡

ሳይታወቀን በመንፈሳዊ ምንዝር አደጋ ላይ ልንወድቅ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? በእንዲህ ዓይነቱ አደጋ ላይ እንዳልሆን እያሰብን ራሳችንን ለምን እናሞኛለን?

ጥር 30
Jan 11

ማዳን የአምላካችንና የበጉ ነው


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡5፣ 2ጴጥ. 3፡14፡፡ የራእይ መጽሐፍ የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ጊዜ ሕዝቦች “ነቀፋም የለባቸውም” ሲል ይገልጻቸዋል፡፡ ለመሆኑ በእንዲህ ዓይነት የንጽህና ሁናቴ መድረስ የሚቻለው እንዴ ነው?



“ከአፋቸው ምንም ዓይነት ውሸት አልተገኘም፤ ነቀፋም የለባቸውም” (ራእ. 14፡5) ይህ 144000ዎቹ የመጨረሻ የባህሪያቸው ሁኔታ ነው፡፡ “ውሸት” በሚል የተነገረው ቃል በመጨረሻው ጊዜ የሚገለጡትን የሰይጣን ማታለያዎች ያመለክታል (ራእ. 13፡14)፡፡ አብዛኛው የዓለም ሕዝብ እነዚህን ውሸቶች አምኖ ለመቀበል ሲመርጥ፤ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ጊዜ ሕዝቦች ግን መዳን የሚያገኙበትን እውነት የሚወዱበት ፍቅር ይቀበላሉ (2ተሰ. 2፡10-11)፡፡ “ነቀፋም የለባቸውም” የተሰኘው አባባል 144000ዎቹ ለክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነት ያመላክታል፡፡ የብሉይ ኪዳን ዘመኖቹ አብርሃም (ዘፍ. 17፡1) እና ኢዮብ (ኢዮ. 1፡1) ምንም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው ኃጢአት ቢሠሩም ነገር ግን ያለ ነቀፋ ነበሩ፡፡ ከሁለት ሺ ዓመታት በፊት ክርስቲያኖች ቅዱስና ጉድፍ የሌለው ህይወት እንዲኖሩ ጥሪ ቀርቦላቸዋል (ኤፌ. 5፡ 27፣ ፊልጵ. 2፡15)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡19-23፡፡ ሁሌም ቢሆን ይህን ወሳኝ እውነት ከፊታችን እንደ ጠበቅን መራመድ የሚኖርብን ለምንድን ነው?



የዚህ ዓለም ታሪክ ወደሚዘጉባቸው ቀናት እየተቃረብን ስንመጣ 144000ዎቹ የክርስቶስን ፀባይ በብርቱ ኃይል ያንጸባርቃሉ፡፡ ከቅድስናቸውና መልካም ሥራቸው ይልቅ መዳናቸው ክርስቶስ ለእነርሱ ያደረገውን ያንጸባርቃል (ኤፌ. 2፡8-9)፡ ፡ 144000ዎቹ ልብሶቻቸውን በበጉ ደም አጥበው በማንጻታቸው (ራእ. 7፡14) በእግዚአብሔር ፊት “ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ” (2ጴጥ. 3፡14) መገኘት ችለዋል፡፡

“‘የመለኮታዊው ተፈጥሮ ወራሾች’ መሆን እስክንችልና የአዳኛችንን አምሳል በሙላት እስከምናንጸባርቅ ልንነጥርና ከማንኛውም ምድራዊነት ልንጠራ ይገባል… “በውዝግብ የተሞላው ይህ ህይወት ሲያበቃ፣ ጥሩርና ሠልፍ በየሱስ እግሮች ስር ሲውል፣ የእግዚአብሔር ቅዱሳን ሲከብሩ፣ ያኔና ያኔ ብቻ--እነሆ ዳንን ያለ ኃጢአትም ሆንን ብለን ባስተማማኝ መናገር እንችላለን፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages, book 3, pp. 355, 356. ወደፊት ለሚጠብቀን ዘላለማዊ ህይወት ንቁ ዝግጅት እያደረግን--ከአክራሪ ፍጹማዊነትና ወግ አጥባቂ ቅድስና ወጥመድ ተጠብቀን በቅድስና የተሞላ ህይወት መኖር የምንችለው እንዴት ነው? በሮሜ 3፡19-23 የምናገኛቸውን ታላላቅ እውነቶች ሁሌም መመሪያችን አድርገን መጓዝ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

የካቲት 1
Feb 08


ተጨማሪ ሀሳብ


Read Ellen G. White, “Sinlessness and Salvation,” pp. 353–357, in Selected Message, book 3. የ144000ዎቹ ማንነት ሁሌም ትኩስ መከራከሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን ይስተዋላል። ቅዱሳኑ በምድር ታሪክ መዝጊያ የሚገኙ የመጨረሻ ትውልዶች መሆናቸው በጣም ግልጽና ሁሉም የሚስማማበት ነጥብ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ሰባቱ መቅሰፍቶች የሚወርዱባቸውን ብርቱ የመከራ ወቅቶች እንደሚያልፉና (ራእ. 7፡ 15-17) ታማኝነታቸው ከእነርሱ አስቀድሞ በየትኛውም ትውልድ ባልታየ መልኩ እንደሚፈተን እናውቃለን፡፡

ሆኖም እነማን የዚያ አኻዝ አካል እንደሚሆኑ ግልጽ ሆኖ አልቀረበልንም፡፡ እግዚአብሔር ለራሱ በምስጢር ከያዛቸው ነገሮች መሃል እንደ አንዱ ልንወስደው እንችላለን (ዘዳ. 29፡29)፡፡ የዳኑት ቅዱሳን ስብስብ እነማን እንደሚሆኑ የወደፊቱ ጊዜ ብቻ የሚገልጠው ይሆናል፡፡ ሆኖም በዚህ ዙሪያ የሚከተለው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል፡

“ተረትና የይሆናል ልቦለዶችን በቤተ ክርስቲያን የሚያቀርቡ እንደሚኖሩ ክርስቶስ ተናግሮአል፡፡ እግዚአብሔር በአንጡራ ሐብትነት በልብ ጓዳ ተጠብቆ እንዲቆይ በማሰብ እነሆ የከበረውን፣ የሚያንጸውንና ባለ ግርማውን እውነት ሰጠ፡፡ ሰዎች ሊያውቁት ብዙም የማያስፈልጋቸውን ይህን ንድፈ ሃሳብ የሙጥኝ ብለው ልዩ የማወቅ ጉጉት ሲያድርባቸው በእግዚአብሔር ምሪት ስር መሆናቸው ይቀራል። ሰዎች--ሊሆን ይችላል ወይም--እንበልና በሚል መነሾ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ድምዳሜ ላይ ይደርሱ ዘንድ የእርሱ ፈቃድ አይደለም፡፡ የመቶ አርባ አራት ሺዎቹ አካል የሚሆኑት እነማን ናቸው? በሚሉ ለመንፈሳዊ ህይወታቸው አንዳችም ፋይዳ በሌላቸው ጥያቄዎችና ተቃርኖዎች ውስጥ ሕዝቦቹ እንዲወድቁ አምላካዊው ፍላጎት አይደለም፡፡ እነዚህ በእግዚአብሔር የተመረጡ--ያለ አንዳች ጥያቄ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ይረዳሉ፡፡”—Ellen G. White, Selected Messages, book 1, p. 174.




የመወያያ ጥያቄዎች




1.“ከመቶ አርባ አራት ሺዎቹ መካከል መገኘት እንድንችል እግዚአብሔር በሰጠን በሙሉ ኃይላችን እንትጋ፡፡”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 7, p. 970. እነዚህን አባባሎች ወደ ተግባር መለወጥ የሚችሉት እንዴ ነው? ይህ ትግል የየቀኑ ውሳኔዎ ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችለው እንዴ ነው?

2.በምድር መጨረሻ የሚኖሩት የመቶ አርባ አራት ሺዎቹ አዲስ ዝማሬ ሌላው አጽንኦት የሚሰጠው ቁልፍ ባህሪያቸው ነው፡፡ ስለ ራስዎ ሕይወት ሲያስቡ--የዛሬው መንፈሳዊ ሁናቴዎ ከእግዚአብሔር ጋር ያሎትን ትኩስ ተሞክሮ ያንጸባርቃል? ወይስ የዛሬው ሕይወትዎ የሚያንጸባርቀው የአሁኑን ሳይሆን እግዚአብሔር ቀደም ባሉት ጊዜያት በእርስዎ ውስጥ ያደረገውን ታሪክ ብቻ ነው? የዛሬው ህይወትዎ የመንፈሳዊ ህይወትዎን አዲስ ዝማሬና ከክርስቶስ ጋር ያሎትን ተሞክሮ የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው? 3.ክርስቶስን በማወቅና እርሱን በእውነት በማወቅ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? አንድ ሰው “ክርስቶስ ምን ይመስላል?” ብሎ ቢጠይቅዎ መልስዎ ምን ይሆናል? ለምን?