የሕይወት ምዕራፎች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2019

ከሰኔ 15 - 21

13ኛ ትምህርት

Jun 22 - Jun 28




በመጨረሻው ዘመን ልቦችን መመለስ



ሰንበት ከሰዓት

የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ሚል. 4:5, 6፣ ማቴ. 11:14-15፣ 17:10፣ 1ነገሥ. 16:29– 17፣ 24 1ነገሥ. 18:20–45፣ ማቴ. 3:2።


መታሰቢያ ጥቅስ:-“እነሆ ታላቅና የሚያስፈራው የእግዚአብሔር ቀን ከመምጣቱ በፊት፣ ነቢዩ ኤልያስን እልክላችኋለሁ፡፡ መጥቼ ምድርን በርግማን እንዳላጠፋ፣ እርሱ የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል፡፡” (ሚልክ. 4፡5-6)፡፡

የ ምንኖረው ሕይወት በተለያዩ ምዕራፎች የተከፋፈለ ነው። እነዚህ ምዕራፎች ደግሞ አንዳንዴ በመልካም ሁኔታ ላይ ሲገኙ ሌላ ጊዜ ግን እንደ ተጠበቀው ላይሆኑ ይችላሉ። ቤተሰባዊው ግንኙነት አንዳንዴ ጥብቅ እና ነፋስ የማይገባው ሲሆን አልፎ አልፎ ግን ተሰባሪና ስሜት የሚጎዳ ሆኖ ይታያል።

አሁን የምንገኝበት ግላዊም ሆነ ቤተሰባዊ ሁኔታ የቱንም ዓይነት ቢሆንና በየትኛውም ዓይነት የህይወት ምዕራፍ ወይም ዑደት ልናልፍ ብንችል፤ በአምላካዊው ተስፋ ብርሃን መኖራችን የግድ ይሆናል። ልባችንንና ነፍሳችንን ከእነዚህ ነገሮች ጋር እናቆራኛለን፤ ምክንያቱም በስተመጨረሻ ብቸኛ ተስፋችን ናቸውና! እንዴት ግሩም ተስፋዎች ናቸው! የገዛ ህይወታችንም ሆነ ቤተሰባችን በየትኛውም ምዕራፍ ሊገኝ ቢችል እንኳ ለግላችን፣ ለምንወዳቸው ወገኖች፣ ለቤተሰባችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ልንጠይቅና ልንወስድ የምንችለው--እንደ ወንዝ የሚፈስ የእግዚአብሔር ቃል ተስፋ አለን።

በዚህ የሩብ ዓመቱ የመጨረሻ ሣምንት ከተለያዩ ዐውዶች አኳያ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን፣ ተስፋዎችንና ተሞክሮዎችን እንመለከታለን። ሁኔታችን ቢለያይም፤ ይህን የምናደርገው ዛሬ ለየግላችን አስፈላጊ የሆኑ ትምህርቶችን ለመውሰድ በመሻት ነው። ሰዎች በየትኛውም የማኅበራዊ ሁናቴ፣ የኑሮ ደረጃ ወይም የዕድሜ ክልል ቢገኙም አብዛኛውን ጊዜ--ትግል፣ ስጋትና አስጨናቂ ነገር አያጣቸውም። እንደ እድል ሆኖ የምናመልከው አምላክ የምንጋፈጠውን የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን የተጋፈጠ ጭምር በመሆኑ ከፊት ለፊታችን ካለው ባሻገር ስላለው ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን።

ሰኔ 16
Jun 23

የተለወጡ ልቦች ትንቢት


የኤልያስን መምጣት ትንቢት ከአዲስ ኪዳን ማጣቀሻዎች ጋር ያስተያዩ፡ ሚልክ. 4:5-6፣ ማቴ. 11:14-15፣ 17:10፣ ማር. 6:15፣ ሉቃ 1:17።



በነቢዩ ሚልክያስ ዘመን እግዚአብሔር ሕዝቡን “‘ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” ሲል ቢማጸንም፤ እነርሱ ግን “‘የምንመለሰው እንዴት ነው?’” በማለት ግብዝ ምላሽ ሰጡ (ሚልክ. 3፡7)። ግራ የተጋባው ነቢይ መነቃቃት የሚደረግበት አንድ የመጨረሻ አመቺ ሁናቴና ጊዜ ሊሰጥ እንደሚችል አስታወቀ።

በኤልያስ የተጀመረውን ልብን የመመለስ ተሐድሶ (1ነገሥ. 18፡37) በማስታወስ እርሱ እንደ ገና መጥቶ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፣ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” (ሚልክ. 4፡6) ሲል ሚልክያስ ትንቢት ተናገረ።

ኤልያስ የመሲህ አብሳሪ ሆኖ በግል ይመጣል የሚል የቆየ የአይሁድ ብሂል እያደገና ተቀባይነት እያገኘ ሄዶ ነበር (ማቴ. 17፡10፣ ማር. 6፡15)። የሆነው ሆኖ አዲስ ኪዳን መጥምቁ ዮሐንስን የትንቢቱ ፍጻሜ አድርጎ ያቀርባል (ማቴ. 11፡14-15፣ ሉቃ. 1፡17)። “ልቦችን ይመልሳል” የሚለው ሀረግ ፍቺ ምን ይመስሎታል?



እነዚህ ሀረጎች ለአያሌ አተገባበሮች ጥቅም ላይ መዋል ይችላሉ፡ የእስራኤል ሕዝብ ከጌታ ጋር ስለሚያደርገው እርቅ ይናገራሉ፡ እግዚአብሔር እንደ አባት (ኢሳ. 63፡16) ቁጣውን ከማውረድ ወደ ልጆቹ መመለሱ (ሚልክ. 7፡ 18-19) እና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ጥሪ ማቅረቡ (ኢሳ. 44፡22፣ ሚልክ. 3፡7)። የፊተኞቹን ትውልዶች በታደሰ ኪዳን ከታማኝ አባቶቻቸው ጋር ዳግም ስለ ማስተሳሰር ይጠቅሳል፡ የእግዚአብሔር ህዝቦች የኃይማኖት አባቶችን እምነት ይከተሉ ዘንድ በተደጋጋሚ በብሉይ ኪዳን ጥሪ ቀርቦላቸዋል። የምድሪቱ በበረከት የተሞላች መኖሪያ ስፍራ ሆና መቀጠል ከኪዳናዊው ታማኝነታቸው ጋር ቀጥተኛ ትስስር ነበረው (ዘዳ. 4፡29-31)። ቤተሰባዊውን ግንኙነት ወደ ቀደመው የተሻለ ንጽህናና መታደስ ስለመመለስ ይናገራል፡ የወላጆችና የልጆች ግንኙነቶች ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረንን ኪዳናዊ ታማኝነት በተጨባጭ ይገልጣሉ። እዚህ ላይ ልጆች ለወላጆቻቸው ያለባቸውን ኃላፊነት ሲወጡ ከቀጣይ በበረከት የተሞላ የአምላካዊው ምድር ባለቤትነታቸው ጋር ድርና ማግ መሆናቸውን ያሳያል (ምሳ. 2፡22)።

ግንኙነትን ከእግዚአብሔር ጋር ከማደስና ቤተሰባዊ ግንኙነትን በማደስ መሃል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? አንዱ ሌላውን መከተል ያለበት ለምንድን ነው?

ሰኔ 17
Jun 24

የቤተሰብ ዳግም መገናኘት


የንጉሥ አክአብ ሚስት በነበረችው በሲዶናዊቷ ኤልዛቤል አማካይነት ለእስራኤላውያን የተዋወቀው የበኣል ባዕድ አምልኮ፤ አገሪቱን በግብረገብ ተዳፋት ቁልቁል አንደረደራት። በቤተሰብ መሀል የሚፈጸም የግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ዝሙትና ሌሎች የተጣመሙ ፍትዎቶች--ቤተሰብን ወደ ከፍታ አውጥቶት በነበረው የትዳር ህይወት፣ የተቀደሰ መኝታና አምላካዊ አስተምህሮ ላይ ጥላ አጠሉ። ታዲያ በዚህ አምልኮን ማዕከል ባደረገ ብርቱ ፍልሚያ መሃል “የማመልከው ሕያው እግዚአብሔርን ነው” ብሎ በኣልን የሚገስጽ ኤልያስ ብቅ አለ።

የአረማውያን አምልኮን በመገርሰስና ለቤተሰብ አዲስ ህይወት በማምጣት ረገድ ከእርሱ ተሞክሮ ጋር የማን ይመሳሰላል? 1ነገሥ. 16:29–17፣ 24፣ ሉቃ. 4:25-26።



ኤልያስ በምድሪቱ ላይ ስለሚመጣው የድርቅ ርግማን መናገሩ ጉልህ እውቅና አሰጠው። እግዚአብሔርም ከኤልዛቤል የትውልድ ከተማ አጠገብ ባለችው ሲዶና ከተማ ሄዶ በአንድ የማይመስል ስፍራ--አንዲት ሰራፕታዊት መበለት እንድትመግበው አደረገ። ኤልያስ መበለቲቱ በቤቷ ያለቻትን እፍኝ ዱቄትና አነስተኛ ዘይት አሟጣ ለእርሱ የሚበላ ጋግራ ከሰጠች በኋላ እግዚአብሔርን ተስፋ እንድታደርግ በሚጠየቅ አሰቃቂ ሊባል በሚችል ዓይነት ፈተና ተገናኛት። ሆኖም የዚህች ሴት እምነት ዝናን አተረፈላት። ኋላ ላይ የሱስ ራሱ ስለዚህች በሰራፕታ ስለነበረች ሴት ተናግሮላታል (ሉቃ. 4፡26)። የማሰሮዋ ዘይትም ሆነ የማድጋዋ ዱቄት ሳይጎድል ለብዙ ቀናት በመዝለቁ ይህች ሴት ስለ እግዚአብሔር ብዙ አስተዋለች። በመሃል ብቸኛው ልጇ ሳይታሰብ ታመመ። ህመሙ እየጠናበት በመሄዱ በመጨረሻ ትንፋሹ ቀጥ አለ።

መበለቲቱ ሐዘኗን ለኤልያስ ስትገልጽ በወቅቱ እስራኤልን አናውጦ የነበረውን ዙሪያዋን የተንሰራፋ ኃይማኖት፤ ማለትም የአንድን ሰው ኃጢአት ለማስተሰረይ ልጅን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ይጠይቅ የነበረውን ዕንግዳ እምነት አንጸባርቃ ነበር (1ነገሥ. 17:18፣ ኤር. 19:5፣ ሚክ. 6:7)።

ሴቲቱ ከልጇ ጋር ዳግም መገናኘቷ በመንፈሳዊ ተሞክሮዋ ላይ ምን ዓይነት ውጤት አስከተለ? 1ነገሥ. 17፡24። ከእርሷ አስተያየት ምን መማር እንችላለን?



የእናቲቱ ምላሽ የኤልያስን መልእክት ውጤት ያንጸባረቀ ነበር። እግዚአብሔር ኃይሉን ተጠቅሞ የተቋረጠውን እስትንፋስ ሲቀጥልና ቤተሰብ ዳግም ሲገናኝ፤ በእርሱና በቃሉ ላይ የሚኖር እምነት ይነቃቃል፣ ያድጋልም። ዛሬ በኃይማኖት ትምህርት ሰበካ ብዙዎች መስማማታቸውን ሊገልጹ ቢችሉም ነገር ግን መንፈሳዊ ህይወታቸው በለብታ ውስጥ ነው። የሆነው ሆኖ የአምላካዊውን ቃል እውነት በግል ስንለማመድ እንዲሁም በቤት ውስጥ ግንኙነታችን መነቃቃትና ወደ ቀደመው ንጽህና መመለስ ሲኖር ልባችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ለእውነት የተሰበረ ይሆናል።

እርስዎ ዛሬ በተስፋ ከሚጠባበቁአቸው አንዳንድ ቤተሰብ የሚገናኝባቸው ክስተቶች መሃል አንዳንዶቹን ይጥቀሱ። ስለዚያ ዳግም መገናኘት መስመር ከአምላካዊው ተስፋዎች የትኛውን ይጠማጠማሉ?

ሰኔ 18
Jun 25

በመሰዊያው ላይ ልቦችን መመለስ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 18፡20-45። በአጠቃላይ ይህ ክፍል በትክክል ስለ ምን እንደሚናገር ከታች በቀረቡት መስመሮች ይጻፉ። ምንም እንኳ ዐውደ ሀሳቡ ሙሉ ለሙሉ የተለየ ቢሆንም በዚህ ታሪክ የታዩት መርኅዎች ቤተሰባዊ ህይወት ላይ እንዴት መተግበር ይችላሉ?



በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የነበረው ኤልያስ እነዚህ ሕዝቦች ወደ አባቶቻቸው እምነት ተመልሰው ለህይወታቸው፣ ለቤታቸውና ለምድራቸው ፈውስ ለማምጣት የሚያስችላቸውን ኪዳን እንዲያድሱ ናፍቆ ነበር።

የምሽት መሥዋዕት ሰዓት፡ የበኣል ነቢያት የሚሰግዱለት አምላክ ያቀረቡለትን መሥዋዕት በእሳት መመለስ ሲሳነው ኤልያስ ተራውን ወሰደ። እርሱ የሚያደርገውን በሚገባ ያውቅ ነበር። የሠርክ መሥዋዕት የሚቀርብበት ጊዜ የሕዝቡን ትኩረት በቤተ መቅደሱ አገልግሎት ወደ ተገለጠው የእግዚአብሔር ማዳን ዕቅድ ስቦ ነበር (ዘፀ. 29፡41)። “ወደ እኔ ቅረቡ” (1ነገሥ. 18፡30) በሚል የቀረበው ግብዣ፤ አዳኙ ኃጢአተኞችን መቀበሉን ያስታውሰናል (ማቴ. 11፡28)።

ልጃቸው ፈር በመልቀቁ ውስጣቸው የቆሰለ ወላጆች እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በእውነት እንደ ወደደ ሁሉ የእነርሱንም ልጅ እንደሚወድ ማረጋገጫ ማግኘት ይችላሉ። እግዚአብሔር ከመስመር ያፈነገጡትን ወደ ራሱ ለመሳብ ያለማቋረጥ ይሠራል።

የኤልያስ ትኩረቱን ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ ማድረግ--በእኛ ጊዜ የሱስና አዳኝ ጸጋው በቤተሰብ መሃል ከፍ ከመደረጉ ጋር ተመሳሳይ ነው። የቤተሰብ አምልኮ ጊዜ ከእርሱ ጋር በጸሎት የምናወራበት፣ እርስ በርሳችን ስለ እርሱ የምንነጋገርበት፣ ተጨማሪ ነጻ የደኅንነት ስጦታውን የምንቀበልበትና የእርሱን አስተምህሮ እንዲያስተጋቡ ለልቦቻችን ጊዜ የምንሰጥበት ነው። ኤልያስ ለጠየቀው ነገር የሰጠው ምላሽ እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች መልሶ ንብረቱ የማድረጉ ምልክት ነው። አንደኛ ነገሥት እንዲህ ይላል “ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር… ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን” (1ነገሥ. 18፡37)። ልባችንን ወደ እግዚአብሔር መመለስ አንችልም። እኛ ማድረግ የምንችለው ለጸጋው ምላሽ መስጠት ብቻ ነው። ያ ደግሞ የእርሱ ነፃ ስጦታ ነው።

አንድም ሳያስቀር ሁሉንም ነገር ላስ ያደረገው ከላይ የወረደው እሳት የበላው ኃጢአተኞችን ሳይሆን የቀረበውን መሥዋዕት መሆኑ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን…ስለ እኛ ኃጢአት” ያደረገውን ወደፊት የሚመጣውን የሱስ የሚያመላክት ነበር (2ቆሮ. 5፡21)። የኃጢአት ኑዛዜ እና ምስጋና ከየሰዉ ከንፈር እያፈተለከ ወጣ። ሐሰተኞቹ ነቢዮች ለአምላካዊው ጥሪ ምላሽ ባለመስጠታቸው ተገደሉ። በመጨረሻ ምድሪቱን የሚያረሰርስ ዝናብ ወርዶ የእርግማኑን ዘመን ወደ ፍጻሜ አመጣው።

የቤትዎ “መሠዊያ” በምን ዓይነት ሁናቴ ላይ ይገኛል? የቤትዎ መሠዊያ በእርግጥ ዳግም መገንባት የሚያስፈልገው ከሆነ በምን ዓይነት ልዩ መንገድ መልሰው መገንባት ይችላሉ?

ሰኔ 19
Jun 26

በዮርዳኖስ ወንዝ ላይ ልቦችን መመለስ


ከገብርኤል ትንቢት በመቀጠል (ሉቃ. 1፡17) እርሱ አስቀድሞ የተነገረው ኤልያስ ስለ መሆኑ የሱስ ከሰጠው ማረጋገጫ (ማቴ. 11፡14፣ 17፡12-13) በመነሳት መጥምቁ ዮሐንስ ለጌታ መንገድ የሚጠርግ (ማቴ. 11:10፣ ማር. 1:2፣ ሉቃ. 7:27፣ ሚልክ. 3:1) “መልእክተኛው” መሆኑን የወንጌል ጸሐፊዎች ያረጋግጣሉ።

የዮሐንስን መልእክት ዋንኛ ባህሪዎች ለመመልከት ይሞክሩ። የእርሱ መልእክት “ልብ የሚመልስ” ዓይነት የሆነው እንዴት ነው? ማቴ. 3:2፣ 8፣ 14:4፣ ማር. 1:4፣ ሉቃ. 3:3፣ 8-9፣ 11፣ 13-14።



ገበሬው መሬቱ ዘር እንዲቀበል ለማዘጋጀት ጉልበቱን አፍስሶ እንደሚያርስ፤ ዮሐንስም ኃጢአትን ያወግዝና ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ አጥብቆ ያሳስብ ነበር። አንድ ሰው ራሱን ሳይመረምርና ስለ ሚገኝበት እውነተኛ ሁናቴ ግንዛቤ ሳይኖረው ለሆነ የተሻለ ነገር የሚጎተጉት ስሜት በውስጡ አይኖረውም። የሰብዓዊው ተፈጥሮ ባህሪ ይኸው ነው። መጥምቁ ዮሐንስ በመልእክቱ ሰዉ ፊቱን አምላካዊው ቅድስና ወደሚሻው ነገር እንዲመልስና የጌታ ፍጹም ጽድቅ አስፈላጊያቸው መሆኑን እንዲገነዘቡ አደረገ።

ከልብ የመነጨ ንስሐ ሁሌም ቢሆን በትህትናና ራስን ለመለወጥ የእግዚአብሔርን እርዳታ በመሻት የታጀበ ነው። አብርሃም አባታችን ነው እያለ በባዶ የሚፎክረውን፣ ግብዝ፣ ጥራዝ ነጠቅና ራስ ወዳድ ማንነት ገልጦ በማውጣት እውነተኛውን የአባቶቻቸውን ጥልቅ እምነት ፍቺ ሊያሳያቸው ተመኘ። የመጥምቁ ዮሐንስ መልእክት መንገዱን ለየሱስ ያዘጋጀው እንዴት ነበር? ዮሐ. 1:35– 37፣ 3:27–30።



የሱስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን አምላካዊው ማንነት ለዮሐንስ ገልጦለት ነበር። እርሱ መሲሁን በዚህ መልኩ በገለጠው ጊዜ (ዮሐ. 1፡29-36) ሕዝቡን በተጨባጭ ወደ ጌታ መለሰ። እንድርያስ እና ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙሮች አንዱ የነበረው ሌላው ዮሐንስ (በዚያ ቀን የሆነውን የመዘገበውና ወንጌልን የጻፈው) የመጥምቁን ጎራ ትተው የየሱስ ደቀ መዝሙሮች ሆኑ።

የኤልያስ መልእክት ንስሐ የሚያስፈልግ መሆኑን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ያዳነንንም ለይቶ ያስቀምጣል፣ ስለ እርሱ ሐሴት እንድናደርግ ያነሳሳናል፣ ሰዎች እርሱን እንዲተዋወቁም ያደርጋል። መጥምቁ ዮሐንስ ወደ ቤትዎ ዘልቆ ቢገባ ምን የሚሎት ይመስሎታል?

ሰኔ 20
Jun 27

በመጨረሻዎቹ ቀናት ልቦችን መመለስ


እኛ የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ዓይነት ሚና እንዳለን አድርገን ራሳችንን እንመለከታለን። የተሐድሶና የንስሐ አዋጅ ነጋሪዎች ለየሱስ የመጀመሪያ ምጽአት መንገዱን እንደ ጠረጉ ሁሉ እኛም እንደ ንቅናቄ፤ ለዳግም ምጽአቱ ተመሳሳይ ሥራ እንደምንሠራ አድርገን ራሳችንን እንመለከታን። ጥቅሱን በጸሎት መንፈስ ያንብቡ፡ ሉቃ. 1፡17። እነዚህ ቃላቶች መልእክቶቻችንን ጥሩ አድርገው የሚገልጡት እንዴት ነው?



ሰማያዊው አባት በክርስቶስ መስቀል አማካይነት የልጆቹን ልብ ወደ ራሱ መለሰ፤ የተመለሰውም ያልተመለሰው ላይ እንዲሠራ ሆነ። አምላካዊው መንፈስ የፍቅር መከር እንዲያፈራና በጸጋው የተሞሉ ህዝቦች ይሆኑ ዘንድ የኤልያስ መልእክት ቤተሰብ ይህን አስደናቂ መልካም የምሥራች እንዲያምን ይማጸናል (2ቆሮ. 5:18–21፣ ኤፌ. 2:11–18)።

ዓለም ራስ ወዳድ ያልሆነ ጥንቃቄ የሚያደርግ፣ ጽኑ ቁርጠኝነት ያለውንና ለእግዚአብሔር ታማኝና የማይለወጥ አምልኮ የሚያቀርበውን ሰው አጥብቆ ይሻል። ክርስቲያን ቤተሰቦች በእግዚአብሔር ጸጋ እንዲህ ዓይነቱን የከበረ ማንነት ገልጠው ማሳየት ይችላሉ። የወንጌል መርኅዎች፣ ሕብረት፣ ፍቅርና ራስን መሥዋዕት ማድረግ በእኛ ውስጥ፣ በተለይም በቤተሰቦቻችን እስካልታዩ ድረስ፤ ይህን መልእክት ለሌሎች ለማስተላለፍ የሚያስችል ኃይል አይኖረንም።

ከአንደበተ ርቱዕ ከንፈር የሚፈልቁ ስብከቶች፣ አመክንዮዎችና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማሳያዎች ብቻቸውን በቂ አይደሉም። እነዚህ ስለ ንስሐ፣ ስለ ልብ መለወጥ፣ ስለ ፍቅርና ስለ ቁርጠኝነት የምንሰብካቸው ስብከቶች በህይወታችን በተለይም በቤተሰባችን ተገልጠው ማየት ይህ ዓለም ይሻል። መጥምቁ ዮሐንስ ህይወትን የለወጠና ስብከቱን ውጤታማ ማድረግ የቻለ ኃይል እንደ ነበረው ሁሉ እኛም ልንተባበር ፈቃደኞች በምንሆነው መጠን በእግዚብሔር ጸጋ ተመሳሳይ ሥራ መሥራት እንችላለን። እኛ በየሱስ አማካይነት የሰማያዊው ቤተሰብ አባሎች ነን (ኤፌ. 3፡15)። በመሆኑም አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቤተሰብ ብንሆን እንኳ እርሱን እናገለግላለን የምንል ሁሉ ለእግዚአብሔር ምስክሮች እንድንሆን ተጠርተናል። መጠኑ ይብዛም ይነስ፤ ይህን በወንጌል ኃይል የምንቀዳጀውን ምስክርነታችንን ከቤተሰብ በላይ ለዓለም ውጤታማ አድርጎ ማሳየት የሚችል ነገር አይኖርም።

የቅርብ ቢሆን ወይም የሩቅ ቤተሰብ አባል ወይም ሌላ--የሚወዱትና የሚጠነቀቁለት መሆንዎን ለማሳየት ምን የተለየ ነገር ማድረግ ይችላሉ?

ሰኔ 21
Jun 28

ተጨማሪ ሀሳብ


Ellen G. White, “Carmel,” pp. 143–154, in Prophets and Kings; “The Voice in the Wilderness,” pp. 97–108, in The Desire of Ages. “መልእክታችን እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ቀጥተኛ መሆኑ የግድ ነው። እርሱ ነገሥታትን ለሠሩት ግፍ ይገስጻቸው ነበር። ህይወቱን አደጋ ላይ ሊጥል ቢችልም እንኳ እውነት ከአንደበቱ ተልፈስፍሶ እንዲወጣ አይፈቅድም ነበር። የዚህ ዘመን ሥራችን በታማኝነት ሊተገበር ይገባል”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 4, p. 1184.


የመወያያ ጥያቄዎች




: 1.የኤልያስ መልእክት ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ባለው አግባብ ዙሪያ ተወያዩ። ቤተ ክርስቲያንዎ መልእክቱን እንድታስተውልና እንድታሰራጭ በሚኖራት ሚና ዙሪያ ምን ዓይነት እገዛ ማድረግ ይችላሉ?

2.“ልቦችን በመመለስ” ረገድ የግል ተሞክሮአቸውን ለማካፈል ፈቃደኞች ካሉ እድል ይሰጣቸው። ምን ዓይነት ለውጦች ተገኙ? ይህ ተሞክሮ በእነርሱና በቤተሰባቸው ህይወት ላይ ምን ዓይነት ልዩነት አመጣ? 3.ራሳችንን ከመጥምቁ ዮሐንስ ሚና አኳያ የምንመለከተው ከሆነ፤ በእኛ ላይ ምን እንዲሆን እንጠብቅ? በመልሱ ያልተገለጠው የመልእክቱ ክፍል የቱ ነው?

4.የሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የቤተሰብ ጽንሰ ሀሳብ ጠቅለል አድርጎ የሚይዝ--“የቤተሰብ መርኅ ድንጋጌ” በሚል ርዕስ ምርጥ ሀሳቦች የተካተቱበትን አንቀጽ ጻፉ። እነዚህን መርኅዎች በጥንቃቄ ለማውጣት ምን ዓይነት መስፈርት ተጠቀማችሁ? በዚህ ሩብ ዓመት እነዚህን መርኅዎች በተገቢው መንገድ ለማስቀመጥ ያስቻሎትን ምን ዓይነት ዕውቀት መገብየት ቻሉ? መልስዎን ይዘው ለመቅረብ ይዘጋጁ።

5.ገና በወጣትነት አፍላ ዕድሜያቸው ከጌታ ርቀው ስለሄዱ ልጆች፤ እንደ ወላጅ በየትኛው አምላካዊ የተስፋ ቃል መጽናናት ያገኛሉ?




የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ ማሳሰቢያ




የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡

እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡

ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡

ድርጅቱ