ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 2:14– 16፣ ዘፀ. 32:1–14፣ 1ጴጥ. 2:12፣ ፊልጵ. 2:15፣ ኤፌ. 2:19፣ ዕብ. 10:23–25፡፡
መታሰቢያ ጥቅስ:-“የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ፡፡ እርስ በርሳችንም ለፍቅርና ለመልካም ሥራ እንዴት እንደምንነቃቃ እናስብ” (ዕብ. 10፡23-24)
ክ
ርስቲያናዊውን ተልዕኮ ከፍጻሜ ለማድረስ ላለን ብርቱ መሻት ቤተ ክርስቲያን
እንደ አንድ የተደራጀ አማኝ ማህበረሰብ ያላትን ጉልበት ዝቅ አድርገን ማየት
የለብንም፡፡ ከኢፍትሐዊነትና ድኽነት ጋር ለምናደርገው ትግል ሊገጥሙን የሚችሉ
ተግዳሮቶችን ቀደም ባለው ጥናታችን ለማየትና ግንዛቤ ለማግኘት ሞክረናል፡፡
እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ስንሆን ቤተ ክርስቲያን ዓለምን እንድታገለግል
በእግዚአብሔር የተፈጠረች፣ የተሰየመችና ይህን ተከትላ መጓዝ እንዳለባት ትኩረት
ከማድረግ እየዘነጋን እንፈተናለን፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን አካልነታችን በዙሪያችን
እየተከሰተ ያለውን ሥቃይና ክፉ እያየን እንዳላየ ማለፍ የለብንም፡፡ ክርስቶስ ችላ
ካላለው እኛም ችላ ማለት የለብንም፡፡ ወንጌልን እንድንሰብክ ለተሰጠን ኃላፊነት
ታማኞች ልንሆን ይገባል፡፡ ለተጨቆኑት፣ ለተራቡት፣ ለታረዙትና ለረዳት አልባዎች
መሥራት ወንጌልን ከመስበክ ጋር በተጓዳኝ ይሄዳል፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብና ድርጅት እኛ ሁላችን በአንድ ላይ የክርስቶስ
አካል ነን (1ቆሮ. 12:12–20)፡፡ ይህን ተከትሎ እንደ አንድ ማኅበረሰብ የሱስ እንደ
ተራመደ ልንራመድ፣ ወደ ሰብዓዊው ወገን እንደ ደረሰ ልንደርስ፣ ለዛሬዋ ዓለም የየሱስ
እጆች፣ እግሮች፣ ድምጾችና ልቦች ሆነን እንድናገለግልና ወደ ሁሉም እንድናመራ
ተጠርተናል፡፡
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን አማኞች በመካከላቸው ለነበሩ ችግረኞች እንክብካቤ
በማድረግ፣ በአንድነት ሆነው ከእነርሱ ማኅበረሰብ ውጪ ወደነበሩ ምስኪኖች በመድረስ
እና እግዚአብሔር በመካከላቸው ያደርግ የነበረው በጎነት ተካፋይ እንዲሆኑ በመጋበዝ
እንዴት በዓይነቱ ልዩ የሆነ ማኅበረሰብ እንደ መሰረቱ ቀደም ባሉት የሐዋርያት ሥራ
ምዕራፎች ተመልክተናል፡፡
የሱስ ስለ ጨው እና ብርሃን በሰጠው ምሳሌ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ያከለው ጳውሎስ፤
ቤተ ክርስቲያን በዓለም ስላላት ኃላፊነት በርካታ ዘይቤዎችን ተጠቅሞአል። ከእነዚህም
መሃል የእግዚአብሔር ተወካይ ሕዝቦች ሆነው የሚመላለሱትን እንደ መሥዋእት (ሮሜ
12፡1)፣ የክርስቶስ አካል (1ቆሮ. 12፡12-20)፣ አምባሳደሮች (2ቆሮ. 5፡18-20)፣ ሽቶ
(2ቆሮ. 2፡14-16) አቅርቦአል፡፡ ምድራችን በታላቅ ተቃርኖ እየጠፋች ባለችበት በዚህ
ወቅት--እነዚህ እያንዳንዳቸው እንደ እግዚአብሔር መንግሥት ተወካይነታችን ስላለን
ሚና ይናገራሉ፡፡
ከላይ የቀረቡትን የእግዚአብሔር ተወካይ ሕዝቦች ማንነት ይከልሱ፡፡ እርስዎ
እግዚአብሔርን ለመወከል የሚመርጡትን መንገድና ለማኅበረሰብዎ ያለውን ዓላማ ጥሩ
አድርጎ የሚገልጸው የትኛው ነው? ለምን?
እነዚህ እያንዳንዳቸው--ከየራሳቸው ጋር ተያያዥነት ያላቸው ድርጊት አላቸው ይህን
የሚያደርጉት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ለማግኘት ሳይሆን፤ ነገር ግን በክርስቶስ
መሥዋእትነት በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት እንዳገኙ ሕዝቦች እየተጎዳና እየሞተ
ላለው ዓለም የእርሱ ወኪል ሆነው ለአምላካዊው ፍቅርና ጸጋ ምላሽ የሚሰጡ ናቸው፡፡
ሆኖም እነዚህ ወገኖች አሁንም ጥልቀት ባለው ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ሆነው መታየት
ይኖርባቸዋል፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት አምላካዊው ፍቅርና ጸጋ
እንደመሆኑ በዚህ መልኩ ስንንቀሳቀስ፣ በፍቅርና በጸጋ ለሌሎች ስንንጸባረቅ፣ ዛሬም
የዚያ ዘላለማዊ መንግሥት ተዋናዮችና ተሳታፊዎች እንሆናለን፡፡
የአንድ አገር ኤምባሲ ምንም እንኳ የሚወክለው አገር ሕዝብና መንግሥት በብዙ
ርቀት ሊገኝ ቢችልም፤ ነገር ግን በዓለማቀፍ ሕግ መሰረት አገሩን በአካል ወክሎ
እንደተገኘ ይቆጠራል፡፡ በተመሳሳይ እንደ እግዚአብሔር መንግሥት ዜጋ መመላለስና
ዛሬ በዚህ ምድር የዘላለማዊውን ነገር ተጨባጭነት በውልብታ መግለጽ፤ በመጨረሻ
ገቢራዊ የሚሆነውን የክፉውን ሽንፈት ከወዲሁ አሻግሮ ለመመልከትና ለማጣጣም
ያስችላል፡፡ ይህን በማድረግ፤ እንደ ክርስቲያን አምባሳደርነታችንና እንደ ክርስቶስ
ወኪልነታችን የፍቅሩንና የፍትሕ አምላክነቱን ተጨባጭነት በገዛ ሕይወታችን፣
በቤተ ክርስቲያንና ልናገለግል በምንመኛቸው ሰብዓዊ ወገኖች ህይወት መለማመድ
እንችላለን፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 2፡16፡፡ በሁለቱ ሽታዎች መካከል ያለው
ልዩነት ምንድን ነው? እኛ የትኛው እንደሆን እንዴት ማወቅ እንችላለን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተገልጸው ለሚገኙት ትሩፋን ሕዝቦች የቀረበው ፍቺ በራእ.
12፡17 ይገኛል፡ “እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር
አጥብቀው የያዙ ናቸው” (ራእ. 14፡12)፡፡ እነዚህ ባህሪያት በምድር ታሪክ መዝጊያ ወቅት
የሚገኙትን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ለይተው ያመላክታሉ፡፡ እንዲሁም ስለ እነዚህ
ትሩፋን ሕዝቦች ድርጊት፤ በተለይ እነዚህ ሕዝቦች እንዴት ሌሎችን እንደሚያገለግሉ
አንዳንድ ምሳሌዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ማግኘት እንችላለን፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 32፡1-14፡፡ በታሪኩ የምንመለከተው የሙሴ ምሳሌ አስፈሪና
ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡ የዚህ ታሪክ የሙሴ ሁናቴ በራእ. 12፡17 ከቀረበው የትሩፋን
ሁናቴ ጋር እንዴት ይነጻጸራል?
እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ላይ በነበረው ብርቱ ቁጣ ከምድር ገጽ ሊያጠፋቸውና-ዘርህ ታላቅ ሕዝብ ይሆናል ሲል ለአብርሃም የገባለትን ኪዳን ወደ ሙሴና ቤተሰቦቹ
ለማስተላለፍ ዝቶ ነበር (ዘፀ. 32፡10)፡፡
ሙሴ ግን ይህ እንዲሆን አልፈለገም፡፡ ይልቁንም ሙሴ--ጌታ አደርገዋለሁ ብሎ የዛተው
ነገር መልካምነቱን እንደሚያጠፋ በመንገር እግዚአብሔርን ለመሞገት የደፈረ ሰው ነበር
(ዘፀ. 32፡11-13)፡፡ ከዚያም ሙሴ አንዳንድ ነጥቦችን ከነካካ በኋላ ራሱን በአምላካዊው
ምኅረት ስር በማስገዛት ለእግዚአብሔር ተማጽኖ ያቀርባል፡፡
ሙሴ እነዚህን ሕዝቦች በምድረ በዳ ለመምራት ብርቱ ትግል ውስጥ ነበር፡፡ እነርሱን
ወደ ነጻነት መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከማጉረምረምና መጨቃጨቅ ታቅበው
አያውቁም፡፡ ታዲያ ይሄ ሁሉ ሆኖ “ ‘እነርሱን ይቅር ማለት ካልቻልክ ከጻፍኸው መጽሐፍ
እኔን ደምስሰኝ’” (ዘፀ. 32፡32) ሲል ለእግዚአብሔር ነግሮት ነበር፡፡ ሙሴ የጉዞው አካል
ያደረጋቸውን ሕዝቦች ለማዳን ሲል ዘላለማዊውን ህይወት እስከ መተው ደርሶ ነበር፡፡
ለማይገባቸው ሲባል ራስ መሥዋእት ሆኖ የቀረበበት እንዴት ያለ ብርቱ የምልጃ ምሳሌ
ነው! ለአጠቃላዩ የደኅንነት እቅድ ግዙፍ ምሳሌ ነው!
“ሙሴ ለእነዚያ በእግዚአብሔር እጅ ለተያዙ ሰዎች ከነበረው ጥልቅ ፍቅርና ፍላጎት አኳያ
ስለ እነርሱ ሲማልድ ቁጣና ንዴቱ ጠፍቶ ነበር፡፡ ሙሴ ከራስ ወዳድነት የጸዳውን ጸሎት
አቀረበ፤ ጌታም ልመናውን ሰማ፡፡ ለእግዚአብሔር ያለው ታማኝነት እንዲሁም ለሳተውና
ምስጋና ቢስ ለሆነው ሕዝብ ያለው ፍቅር ተፈተነ፡፡ ሙሴም ባሳየው ላቅ ያለ ሞራላዊ
መርኅ ፈተናውን አለፈ፡፡ ሙሴ ለእስራኤል ያለው ብርቱ ፍላጎት ከእራስ ወዳድነት ከጸዳ
ተነሳሽነት የመነጨ ነበር፡፡
የእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች ብልጽግና ከግል ክብሩ
የላቀና የታላቅ ሕዝብ አባት መሆኑ ከሚሰጠው ዕድል የከበረ ነበር፡፡ በሙሴ ታማኝነት፣
የልብ ንጽህናና ሐቀኝነት ደስ ተሰኝቶ የነበረው እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ ተስፋው
ምድር የመምራት ኃላፊነት ሰጠው፡፡” የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 361፡፡
በዙሪያችን በስህተት ውስጥ ላሉት በተቻለ መጠን ሳንታክት መሥራት
እንዳለብን ይህ ምን ይነግረናል?
አልፎ አልፎ በቤተ ክርስቲያን ውይይቶች--ትኩረታችንን በማኅበራዊ እንቅስቃሴ
ላይ እናድርግ ወይስ በወንጌል ሥራ፣ በበጎ አድራጎት ወይስ በምስክርነት፣ በፍትሕ
ነክ ወይስ በወንጌል ጉባዔ--የትኛውን መምረጥ እንዳለብን እንቸገራለን፡፡ ነገር
ግን እነዚህን እያንዳንዳቸውን ጽንሰ ሀሳቦች በተሻለ ማስተዋል ስንችልና የየሱስን
አገልግሎት ስናጤን ልዩነቱ ይጠብና፤ ወንጌልን መስበክና የተቸገሩትን ለመርዳት
መሥራት በቅርብ የተቆራኙ መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡
“ወደ ሕዝቦች ለመድረስ፤ የክርስቶስ ዘዴ ብቻውን እውነተኛ ስኬት ያስገኛል፡፡
አዳኙ የሰዎችን በጎ እንደሚመኝ በሚገልጽ አኳኋን ከሰዎች ጋር ተቀላቀለ፡፡ ርኅራኄ
አሳያቸው፣ በሚያስፈልጋቸው አገለገላቸው፣ በዚህም መተማመናቸውን አሸነፈ፡፡
ከዚያም “ተከተሉኝ” ሲል ጥሪ አቀረበላቸው…
“ድኾች አንዳች የሚያስታግስ ነገር አገኙ፣ ህመምተኞች ተፈወሱ፣ ያዘኑና የተከዙ
መጽናናት አገኙ፣ ትምህርት ያልነበራቸው የዕውቀት ባለቤት ሆኑ፣ ልምድ
ያልነበራቸው ምክረ ሀሳብ ተቀበሉ፡፡ ከሚያለቅሱ ጋር እናለቅሳለን፣ ደስ ካላቸውም
ጋር ሐሴት እናደርጋለን፡፡”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, p. 143.
የአምላካዊው መንግሥት መገለጫዎቹ ፍትሕ እና ወንጌልን መስበክ በቅርብ የቆራኙት
በየሱስ አገልግሎት ብቻ ሳይሆን እርሱ ለደቀ መዛሙርቱ በሰጣቸው የመጀመሪያ
ተልዕኮ ጭምር ነው፡ “ሄዳችሁም ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች’ ብላችሁ ስበኩ።
በሽተኞችን ፈውሱ፤ ሙታንን አስነሡ፤ ለምጻሞችን አንጹ፤ አጋንንትን አስወጡ፤
በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ፡፡” (ማቴ. 10፡7-8)፡፡ በአጭሩ መልእክታችንን
ለሌሎች ለማድረስ ከሚችሉ እጅግ ምርጥ መንገዶች አንዱ በሚያስፈልጋቸው
ማገልገል ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2፡12፣ ፊልጵ. 2፡15፡፡ በእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚተገበር
መልካም ሥራ ስላለው የምስክርነት ኃይል ጴጥሮስና ጳውሎስ ምን ይላሉ?
የአምላካዊው የምሥራች ሰፋ ባለ የማስተዋል ዐውድ ሲቀርብ፤ ለሰዎች ርኅራኄ
የሌለው የወንጌል ሥራ ፋይዳ ቢስ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እንደ 1ዮሐ. 3፡16-18 እና
ያዕ. 2፡16 ያሉት ቁጥሮች ወንጌልን ሳንኖርበት መስበክ ስላለው ተቃርኖ አጽንኦት
ይሰጣሉ፡፡ የወንጌል ሥራ የተስፋውን የምስራች ይዞ መምጣት፣ ማዳን፣ ወደ ንስሐ
መምራት፣ መለወጥ ሲሆን--የእግዚአብሔር አቃፊ ፍቅር ደግሞ የፍትሕ መገለጫ
ነው፡፡
ወንጌልን መስበክ እና ለፍትሕ የሚኖር ቅንአት እግዚአብሔር ለጠፉ፣ ለተቸገሩና
ለተጎዱ ያለውን ፍቅር ከመገንዘብ ይመነጫል፡፡ ይህ ፍቅር እግዚአብሔር
በሕይወታችን ላይ በሚኖረው ተጽእኖ በልባችን የሚያድግና የሚጎለብት ነው።
አንዱን ከሌላው ሳናበላልጥ እግዚአብሔር የሰጠንን ማንኛውንም ስጦታ ጥቅም
ላይ እያዋልን፤ የሰዎችን እውነተኛ ፍላጎት ለማሟላት ከእግዚአብሔር ጋር ለእነርሱ
እንሠራለን፡፡
ለሌሎች መልካም ሥራ ስንሠራ በተጓዳኝ የደኅንነት መልካም የምሥራች
የሆነውን ወንጌል መስበክ ችላ ላለማለታችን እርግጠኞች መሆን
የምንችለው እንዴት ነው?
በኢዮብ መጽሐፍ መግቢያ ላይ ኢዮብ ታማኝ ስለመሆኑ፣ የአምላካዊውን መንገድ
የሚከተልና እግዚአብሔር ከወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ጋር ባለው መስተጋብር
ቅንነቱን በማሳየት ምስክርነት ሲሰጥለት ይታየል (ኢዮ. 1፡8)፡፡ አምላካዊው መልካም
ስምና ዝና በምድር ላይ በሚኖሩ ሕዝቦቹ ሕይወት እንዲገለጥ ጌታ መፍቀዱ እጅግ
አስደናቂ ነው፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ይህን እግዚአብሔር በአንዳንድ “ቅዱስ” ሰዎች
ያለውን እምነት የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብን በማካተት አስፋፍቶታል፡ “አሳቡም
በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ
በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው” (ኤፌ. 3፡10)፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡19፡፡ ቤተ ክርስቲያናዊው ማኅበረሰብ እንደ እግዚአብሔር
“ቤተሰብ” በተገለጸበት ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ ምን የተካተተ ይመስሎታል? በመዋቅር
የተደራጀው ቤተ ክርስቲያን እንዴት መሥራት እንዳለበት አስመልክቶ ይህ አገላለጽ
ምን ዓይነት ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል?
ማንኛውም ማኅበረሰብ ወይም ድርጅት ከአባላቶቹ ጋር የሚኖረው አግባብ የቡድኑን
መሰረታዊ እሴት ያንጸባርቃል፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንደ እግዚአብሔር ቤተሰብ፤
የክርስቶስ አካል እና የመንፈስ ቅዱስ ማኅበረሰብነቷ--እግዚአብሔር የሰላም አምላክ
እንጂ የሁከት አምላክ አለመሆኑን የማሳየት ከፍ ያለ ኃላፊነት አለባት (1ቆሮ. 14፡
33)፡፡
በአምላካዊው ፍትሕ፣ ጸጋና ፍቅር እንደታየው--የፍትሕ፣ የጸጋና የፍቅር እሴቶች
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚከሰቱትን ነገሮች በሙሉ መግዛት አለባቸው።
እነዚህ መርኅዎች ከአጥቢያ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ እስከ ዓለማቀፉ የቤተ
ክርሰቲያን መዋቅር፤ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለሚሰጡት ምሪት፣ ውሳኔ እና
“ከእነዚህ አነስተኛ ከሆኑት” ለአንዱ ጥንቃቄ የማድረግ አቅጣጫ ሊያሳዩ ይገባል።
ከዚህ በተጨማሪ ከጊዜ ወደ ጊዜ በአባላት መካከል የሚነሱ ቅራኔዎችን እንዴት
መፍታት እንደሚኖርባቸውም ምሪት መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመካከላችን
ያሉትን በቅንነትና በአክብሮት ማስተናገድ ሳይሆንልን ከውጪ ያሉትን እንደምን
ልናስተናግድ እንችላለን?
የቤተ ክርስቲያን ድርጅት ሰዎችን ለአገልግሎት ሲመድብ ሁሉንም በእኩል
የማየትና ከማንኛውም አድሎ የተጠበቀውን ተግባር በደግነት ሊያከናውን ይገባል።
ቤተ ክርስቲያኖች ሁሉም አባላት ለጉዳት ተጋላጮችን በመከላከል የተቻላቸውን
የሚያደርጉበት ደኅንነታቸው የተጠበቀ ስፍራ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የመጀመሪያዋን
ቤተ ክርስቲያን ሁኔታ እንደ ተመለከትነው አባላት በተለይ የቤተ ክርስቲያን
“ቤተሰብ” ለነበሩ ችግረኞች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁዎች ነበሩ፡፡
የሱስ የሚከተለውን እንደ ትእዛዝ ሲሰጥ--ለውጥ የሚያመጣው በአማኝ
ማኅበረሰቡ ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም ፊት እምነታቸውን በተጨባጭ ስለሚያሳይ
ነበር “ ‘አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ ይኸውም እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ ነው፤
እንግዲህ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፡፡ እርስ በርሳችሁ
ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ’” (ዮሐ.
13፡34-35)፡፡
ምርጥ በሆኑ መነሳሳቶች፣ ውጥኖችና እምነት በእግዚአብሔር እንዲሁም መልካም
በሆነው ነገር በኩል ቆመናል እያልን እንኳ ለጌታ መሥራት አስቸጋሪና ተስፋ አስቆራጭ
ሊሆን ይችላል፡፡ ዓለማችን በአስከፊና ህመም ባለው ሁኔታ ውስጥ መውደቋ
የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብ ያስፈለገበት አንዱ ምክንያትም
ይሄው ነው፡፡ የሱስ እንዲህ ያለውን ድጋፍ ሰጭ ሕብረተሰብ በደቀ መዛሙርቱ
ምሳሌ አሳይቶአል፡፡ እርሱ ሰዎችን በግል የላከባቸው አጋጣሚዎች እምብዛም
ባይኖሩም ነገሩ ቢሆን እንኳ ምንም ያህል ጊዜ ሳይወስዱ እንደገና ታሪካቸውን
ለመናገር፣ ጉልበታቸውንና ድፍረታቸውን ለማደስ በአንድነት ይገናኛሉ፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 10፡23-25፡፡ ዕብ. 10፡25 ከሁሉም በላቀ የሚታወቅ ጥቅስ
እንደመሆኑ ቀደም ያሉት ሁለት ጥቅሶች ለዚህ በስፋት የሚታወቅ ጥቅስ ምን
ያክላሉ? “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ” እርስ በርሳችን ከምንበረታታባቸው መንገዶች
አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
በማንኛውም ዓይነት ሥራ ወይም ፕሮጀክት በቡድን ሆነው የሚሠሩ፤ ሁሉም
በተናጥል ቢሆኑ ሊሠሩት ከሚችሉት የላቀ ውጤት ያስመዘግባሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ቤተ
ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ አካል ያላትን ምስል በመስጠት እኛ ሁላችን የተለያየ ግን
የተሟላ ሚና እንደምንጫወት ያስታውሰናል (ሮሜ 12፡3-6)፡፡ እያንዳንዳችን በተሻለ
መሥራት የምንችለውን ነገር ስንሠራና የመሥራት ክህሎታችን አብሮ ለመሥራት
በሚፈቅደው መንገድ ስንሠራ፤ ህይወታችንና ሥራችን ዘላለማዊ ልዩነት ማምጣት
የሚችል ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል መገመት እንችላለን፡፡
ትክክል የሆነውን ነገር ለመሥራት ፍላጎት የሚኖረውን ያህል ከሰዎችና ከሰዎች
ህይወት ጋር ተያያዥነት ያለው ውጤትም እንዲሁ በእጅጉ አስፈላጊ ከመሆኑ
አኳያ--ሊገኝ የሚችለው ውጤት ምንም ይሁን ምን በእግዚአብሔር ላይ መታመን
ይኖርብናል፡፡ የድኽነትን ሥቃይ ለማስታገስ፣ ለጥቃት ተጋላጩን ለመከላከል፣
የተጨቆነውን ቀንበር ለመስበርና ድምጹ ለማይሰማው ለመናገር በምናደርገው
እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ አነስተኛ መሻሻሎችን እንመለከታለን፡፡ ነገር ግን በበለጠና
በተሳካ ሁኔታ በድል አድራጊነት ለመስራት ተስፋ አለን “በጎ ነገር ከማድረግ አንታክት፤
ተስፋ ካልቆረጥን ጊዜው ሲደርስ መከሩን እናጭዳለን፡፡ ስለዚህ ዕድሉ ካለን ለሰው
ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ፡፡” (ዕብ. 6፡9-10)፡፡
አንዱ ሌላውን እንዲያበረታታ የተጠራንበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡ በታማኝነት
መኖር አስደሳችም አስቸጋሪም ነው፡፡ የፍትሕ አምላካችን እና ፍትሐዊ ማኅበረሰባችን
ሌሎችም እንዲቀላቀሉን ግብዣችንን እንድናቀርብ የሚያደፋፍሩን አጋዦቻችን
ናቸው፡፡
የሌሎችን ሥቃይና እንግልት ለማስታገስ በመደበኛ ከሚሠራ ሰው
ማንን ያውቃሉ? ይህ ግለሰብ ወይም ቡድን ለሚሠራው መልካም ሥራ
የሚሰጡት ማበረታታት ምን ይመስላል?
Read Ellen G. White, “A Faithful Witness,” pp. 546–
556, in The Acts of the Apostles; “Kindness the Key to Hearts,” pp.
81–86, in Welfare Ministry.
“ደቀ መዛሙርቱ የሠሩትን ሥራ እኛም እንዲሁ መሥራት ይኖርብናል፡፡
እያንዳንዱ ክርስቲያን ወንጌላዊ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ በችግር ውስጥ የሚገኙትን
ሰብዓዊ ወገኖች ከራስ ወዳድነት ርቀን የሐዘናቸው ተካፋይ በመሆን በጽኑ ርኅራኄ
እናገልግላቸው…
“የተራቡትን እንመግብ፣ የታረዙትን እናልብስ በሥቃይና በጉዳት ያሉትንም
እናጽናና፡፡ ተስፋ የቆረጡትን እያገለገልን ተስፋቸውን እናለምልም፡፡
“ከራስ ወዳድነት ፍጹም ነጻ በሆነ አገልግሎት የተገለጸው የክርስቶስ ፍቅር ከሰይፍ
ወይም ከፍርድቤት ፍትሕ የበለጠ ውጤታማ ተሐድሶ በክፉ አድራጊው ላይ
ማምጣት ይችላል. . . በዘለፋና ግሳጼ የደነደነ ልብ በክርስቶስ ፍቅር ስር ሲውል
ይቀልጣል”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, pages 104, 106.
“ባርነት፣ መድልዎአዊ ሥርዓት፣ ኢፍትሐዊ የዘር ጭፍን ጥላቻ፣ የድኻው ጭቆና፣
ረዳት የሌላቸውን ችላ ማለት--ክርስቲያናዊ ያልሆኑና ለሰብዓዊው ዘር ደህንነት አስጊ
ጠንቆች በመሆናቸው እነዚህን የክፉ ተግባራት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አሽቀንጥራ
እንድትጥል በጌታዋ ሥልጣን ተሰጥቷታል፡፡”—General Conference president
A. G. Daniells, speaking of the work of Ellen G. White at her funeral, Life
Sketches of Ellen G. White, p. 473.
1.በዓለም ውስጥ የሚስተዋለውን እጦት ለማስታገስ የሚሠሩ በጣም
ብዙ ሰዎች፣ ቡድኖችና ድርጅቶች አሉ፡፡ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት
ቤተ ክርስቲያን ለእዚህ ኃላፊነት ምን ዓይነት ልዩ ጉልበት፣ ራእይና
ሐብት ማጋራት ትችላለች?
2.ከቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብዎ መበረታታትና ድጋፍ ያገኙበትን ጊዜ
ያስታውሳሉ? ከዚያ ተሞክሮ በመማር እርስዎም ለሌሎች ተመሳሳይ
ማበረታቻ ማበርከት የሚችሉት እንዴት ነው?
3.መልካም በማድረግ መዛል እንዳይገጥሞት የቤተ ክርስቲያን ማኅበረሰብን
ድጋፍ ጨምሮ ሌሎች ምን ዓይነት ሊረዱ የሚችሉ ነገሮች ይኖራሉ?
4.ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በዓለም ዙሪያ ድጋፍ
ከምትሰጣቸው አንዳንድ የፍትሕና የድኽነት ቅነሳ ወይም ልማት መርኀ
ግብሮች እርሶ የሚያውቋቸው የትኞቹን ነው? ለዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ
አንደኛው ተግባር ድጋፍዎን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው
ማጠቃለያ፡ አዎ--እንደ ክርስቲያን በተለይ በጉዳት፣ በሥቃይና
በጭቆና ቀንበር ስር ያሉትን እንድናገለግል ተጠርተናል፡፡ ምንም እንኳ
በዚህ ዙሪያ የግል ኃላፊነት ቢኖርብንም፤ ሌሎችን ለማገልገል ትኩረት
ባደረገ እንደ ማኅበረሰብ፤ ማለትም እንደ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ
ይበልጥ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡