ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 115:1–8፣ ዘዳ. 10:17–22፣ መዝ. 101:1፣ ኢሳ. 1:10–17፣ ኢሳ. 58፣ ማር. 12:38–40።
መታሰቢያ ጥቅስ:- “ ‘እንግዲህ እኔ የመረጥሁት ጾም፣ የጭቆናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቆኑትን ነጻ እንድታወጡ፣ ቀንበርን ሁሉ እንድትሰብሩ አይደለምን? ምግብህን ለተራበ እንድታካፍለው፣ ተንከራታቹን ደኻ ወደ ቤትህ እንድታስገባው፣ የተራቆተውን ስታይ እንድታለብሰው፣ የሥጋ ዘመድህንም ፊት እንዳትነሳው አይደለምን? (ኢሳ. 58፡6-7)።
የ
ብሉይ ኪዳን ነቢያትን መልእክት ላይ ላዩን ገረፍ አርገነው ብናልፍ እንኳ፤ ስለ
ደኻውና ስለ ተጨቆነው ሰብዓዊ ወገን በደል የጻፏቸው መልእክቶች ጉዳዩን
አሳሳቢ አድርገን እንድንወስድ ያስገድዱናል። ነቢያትም ሆኑ መልእክቱን የሰጣቸው
ራሱ እግዚአብሔር ዙሪያ ገባውን ባሉ ሕዝቦች ዘንድ እየሆነ በነበረው ነገር (አሞጽ
ምዕ. 1 እና 2) ክፉኛ ተቆጥቶ ነበር--በተለይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው መለኮታዊ
በረከቶች ተቀባይ በነበሩት በራሳቸው በእግዚአብሔር ሕዝቦች ይፈጸሙ በነበሩ
የርኩሰት ተግባራት። የአስደናቂ አርነት ታሪክና የእግዚአብሔር ሕግ ባለቤት የነበሩት
እነዚህ ሕዝቦች በተሻሉ ነገሮች ሊታወቁ ሲገባ፤ የሚያሳዝነው ባብዛኛው ይህ ሳይሆን
ቀርቶአል። እነዚህን አሳዛኝ ክስተቶች ተከትሎም ነቢያት እጅግ ብዙ ብለዋል።
የብሉይ ኪዳን ነቢያት ስለ ፍትሕ እና ኢፍትሐዊነት ከሰጧቸው ዝነኛ መልእክቶች
ውስጥ አብዛኞቹ የተበረከቱት ስለ አምልኮ ከተሰጡ መመሪያዎች ዐውድ መሆኑን
መገንዘብ ደስ ያሰኛል። እውነተኛ አምልኮ እንደው በአንድ ኃይማኖታዊ ሥነስርአት
ላይ ገቢራዊ የሚሆን ነገር ብቻ አይደለም። ይልቁንም እውነተኛ አምልኮ እግዚአብሔር
ስለ ሌሎች ምቾትና ደስታ ያለውን ጭንቀትና ሥጋት የመጋራት ብሎም የተጨቆኑትና
የተረሱት አንገቶቻቸውን ቀና እንዲያደርጉ የሚታትር ህይወት መኖር ነው።
እግዚአብሔር የእስራኤልን ሕዝብ እየመራ ከግብጽ ካወጣቸው በኋላ ብዙም
ሳይቆይ በሲና ተራራ ላይ ተገናኛቸው። ከዚያም የመጀመሪያዎቹን ሁለት ትእዛዛት
ማለትም ሌሎች አማልክት አይኑሩህ እና ለራስህ ጣኦት አታብጅ የሚሉትን ጨምሮ
በድንጋይ ጽላት ላይ የተቀረጹትን ዐሥርቱን ትእዛዛት ሰጣቸው (ዘፀ. 20፡2-6)።
በምላሹም ሕዝቡ ማንኛውንም የታዘዙትን ነገር ለመፈጸምና እንደ እርሱ ሕዝቦች
ሆነው ለመኖር ቃል ኪዳን ገቡ (ዘፀ. 24፡1-13)።
በመሃል ሙሴ ወደ ተራራው እንደ ወጣ ሳይመለስ ስድስት ሣምንታት ገደማ
በመቆጠራቸው ምን አግኝቶት ይሆን ብለው ማሰብ ጀመሩ። ለዐመጽ በተነሳሳው
ህዝብ ጫና ውስጥ የወደቀው አሮን ከወርቅ የጥጃ ምስል ጣኦት ሠርቶ በመስጠት
በምስሉ ፊት መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ነገራቸው፡ “ከዚህም በኋላ ይበሉና ይጠጡ ዘንድ
ተቀመጡ፤ ሊዘፍኑም ተነሱ” (ዘፀ. 32፡6)። ሕዝቡ በፍጥነት ፊቱን ከእግዚአብሔር
መልሶ ወደ ጣኦት አምልኮ መግባቱ ጌታንም ሆነ ሙሴን በእጅጉ አስቆጣ።
እስራኤላውያን ለዚህ ጥፋታቸው ተመጣጣኝ ቅጣት ከመቀበል ያተረፋቸው የሙሴ
ልመና ነበር (ዘፀ. 32፡30-34)። የእግዚአብሔርን ሕዝቦች በተደጋጋሚ የሚፈትንና
የሚወድቁበት ኃጢአት ቢኖር ጣኦት አምልኮ ነበር። የእስራኤልና የይሁዳ ነገሥታት
የንግሥና ዘመናት በጣኦት አምልኮ ታሪክ የታጀቡ ቢሆኑም፤ ይባስ ብሎ ከነገሥታቱ
መሃል አንዳዶቹ ሕዝባቸው ለእነዚህ ባእዳን አማልክት እንዲሰግዱ የሚያስገድዱ
አሰቃቂ ተግባሮችን ይፈጽሙ ነበር። ሕዝቡን ከእንዲህ ያለው ታማኝነት የጎደለው
ተግባር ወደ እግዚአብሔር እንዲጠሩ የተላኩ ነቢያት ተደጋጋሚ ትኩረት ይኸው
ነበር። በሕዝቡ መሃል ተሐድሶና መነቃቃት እንዲመጣ ይቀርብ ከነበረው ጥሪ
በተጓዳኝ ለድኾች፣ ለችግረኞችና ረዳት ለሌላቸው ወገኖች የተሻለ አያያዝ እንዲደረግ
የሚጠይቁ ተማጽኖዎችም ይቀርቡ ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 115፡1-8። ባለ መዝሙሩ እያነሳ ያለው ወሳኝ ነጥብ ምን
ይመስላል?
የምናመልከውና ትኩረት እንደምናደርግበት ነገር ግልባጭ መሆን የእኛ የሰው ልጆች
ዝንባሌ ነው። ይህን ተከትሎ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ዐይኖቻቸውን ከእርሱ ላይ
አንስተው የጦርነት ወይም የመራባት (ፍሬያማነት) ጣኦቶች የነበሩትን የአጎራባች
ሕዝቦችን ሐሰተኛ አማልክት ሲያመልኩ፤ ስለ ሰብዓዊ ወገኖች ብሎም ስለ
ፍትሕ ይኖራቸው የነበረ የመቆርቆር ስሜት እየደበዘዘ መሄዱ ተፈጥሮአዊ ነበር።
እስራኤላውያን ከእውነተኛው አምልኮ ማፈንገጥ በመረጡ ቁጥር፤ እንዴት ለሌሎች
ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ጨምሮ፣ አመለካከታቸው በብዙ ይለዋወጥ ነበር።
እነዚህ ሕዝቦች ለጌታ ታማኝ እንደሆኑ ቢጸኑ ኖሮ እግዚአብሔር በዙሪያቸው በእጦት
ማዕበል ለሚንገላቱ ሰብዓዊ ወገኖች የነበረውን የመቆርቆር ስሜት በተጋሩ ነበር።
የምናመልከው ግልባጭ በመሆናችን ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ ጠለቅ ያለ
ምልከታ ያድርጉ። ዛሬ በእኛ ዘመን የዚህን መርኅ መገለጫዎች እንዴት
እንመለከታቸዋለን?
የእግዚአብሔር ሕዝቦች እርሱን ያመልኩ ዘንድ የቀረበላቸውን ያላሰለሰ ጥሪ በመላው የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች የምንመለከት ሲሆን፤ እኛም ይህን የምናደርግበት ምክንያት በተደጋጋሚ ቀርቦልናል። እርሱ--እርሱ በመሆኑ፣ ለእኛ ባደረገው ነገር እና በባህሪው የተነሳ እነሆ እንድናመልከው ጥሪ ቀርቦልናል። መልካምነቱ፣ የፍትሕ አምላክ መሆኑና በምኅረት መሞላቱ በዋነኝነት ከሚጠቀሱት መሃል ናቸው። እግዚአብሔር ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ መለስ ብለን ስናስብ፣ ለእኛ ስላደረገልን ነገር (በተለይ በክርስቶስ መስቀል)፣ እንዲሁም ስለ ሰጠን የተስፋ ቃላት--አንዳችንም ብንሆን እርሱን ለማምለክና ለማወደስ ምክንያተ ቢሶች መሆን አንችልም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 10፡17-22፣ መዝ. 101፡1፣ 146፡5-10፣ ኢሳ. 5፡16፣ 61፡11። እግዚአብሔርን ለማምለክና ለማወደስ መነሻ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
እነዚህ የአምልኮ መነሾዎች ለእግዚአብሔር ሕዝቦች አዲስ አልነበሩም። የአዲስ
ነጻነት ባለቤት በነበሩት እስራኤላውያን መሃል ይተገበሩ የነበሩ አንዳንድ አስደሳችና
አጓጊ የአምልኮ ጊዜያት መንስኤዎች እግዚአብሔር ስለ እነርሱ ጣልቃ የመግባቱ
ምላሽ መሆናቸው ግልጽ ነበር። ለአብነት ያህል ከግብፅ እንዲወጡና ቀይ ባሕርን
እንዲሻገሩ ከተደረጉ በኋላ እግዚአብሔር እነርሱን ለመታደግ ያደረገውን ሁሉ
በገዛ ዐይኖቻቸው በማየታቸው በሙሴና ማርያም ምሪት ለእግዚአብሔር ውዳሴ
አቅረበው ነበር (ዘፀ. 15)።
አምላካዊው ፍትሕና ምሕረት እንዳይረሳ ሆኖ በእንደነዚህ ዓይነቶቹ ልዩ ሥነ
ስርዓቶች ቀርቦ ነበር። ሰዎች እነዚህን ታሪኮች ደጋግመው ለሌሎች በመንገር ህይወት
በዘሩባቸው ቁጥር፤ ጌታ የሠራቸው ሥራዎች ለቀጣይ አምልኮ ዘመናቸው ብሎም
ለመጪው ትውልድ አነሳሽ ኃይል መሆናቸው ቀጥሎ ነበር። ለዚህ አንድ ምሳሌ-ዘዳ. 10፡17-22 መመልከት ይቻላል።
በቅድሚያ--አምላካዊው ፍትሕ የእርሱ ባህሪ ወሳኝ ክፍል ነው። “በእውነት
እግዚአብሔር ክፋትን አይሠራም፤ ሁሉን የሚችል አምላክ ፍትሕን አያጣምምም።”
(ኢዮ. 34፡12)። እግዚአብሔር ጻድቅ አምላክ እንደ መሆኑ የፍትሕ ጉዳይ ያሳስበዋል።
ይህ እርሱን እንድናመልከውና እንድናወድሰው ያደርገናል።
ሁለተኛ--አምላካዊው ፍትሕ ስለ ሕዝቡ እና ባጠቃላይ ለድኾችና ለተጨቆኑ
ሰብዓዊ ወገኖች ባደረጋቸው ጻድቅ ተግባራት ታይቶአል። አምላካዊው ፍትሕ
ብቻውን የባህሪው መገለጫ ሆኖ አያውቅም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ
ምድር በገሃድ የሚስተዋለውን “የመከረኞችን ጩኸት ሰማ” (ኢዮ. 34፡28) በማለት
እግዚአብሔርን ይስለዋል። ይህ ጉዳይ ውሎ አድሮ በአምላካዊው የመጨረሻ ፍርድ
እና እንደ አዲስ የመፍጠር ሥራው ሙሉ ለሙሉ እውቅና የሚቸረው ይሆናል።
ጥንት እስራኤላውያን ጌታን የሚያወድሱበት ምክንያት ከነበራቸው፤
ከመስቀሉ በኋላ ያለነው እኛ እርሱን ለማወደስ ምን ያህል የላቀ
ምክንያት ሊኖረን ይችላል?
ምንም እንኳ ያኔም ቢሆን አምልኮአቸው ዙሪያቸውን ከበዋቸው ከነበሩ ህዝቦች
ጥሰው ከሚገቡ የጣኦት አምልኮ ጋር አልፎ አልፎ የተጠላለፈ ቢሆንም፤ የእስራኤልና
የይሁዳ መንግሥታት በተሻለ ሁኔታ ይገኙ በነበሩባቸው ወቅቶች ህዝቡ ፊቱን ወደ
ቤተ መቅደስ መልሶ እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። ነቢያቱ እንደሚሉት ከሆነ ግን-ሕዝቡ በተሻለ ኃይማኖተኛ ለመሆን ያደረጋቸው ሙከራዎች እንኳ ሳይቀሩ፤ በየቀኑ
ህይወታቸው ምድሪቱ ላይ ጠብቀው ካቆዩት የክፉ ተግባር እነርሱን ለመመለስ በቂ
አልነበሩም። ይፈጽሟቸው በነበሩ የአምልኮ ሥርዓቶች አማካይነት ኃይማኖተኛ
ለመሆን የቱንም ያህል ጠንክረው ቢታትሩም፤ የመዝሙሮቻቸው ቅላጼ ከደኻውና
ከተጨቆነው ልቅሶ መነጠል የሚችሉ አልነበሩም።
አሞጽ “ችግረኞችን የምትረግጡ፣ የምድሪቱንም ድኾች የምታጠፉ” (አሞጽ 8፡4)
ሲል የእርሱን ዘመን ሕዝቦች ይገልጻቸዋል። ኃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ከፈጸሙ
በኋላ ተመልሰው ወደ ገበያ ወርደው መደብሮቻቸውን በመክፈት ያንኑ ወስላታ
ንግዳቸውን ለማጧጧፍ የነበራቸውን የልባቸውን ምኞት አሞጽ ተመልክቶ ነበር
“ድኻውን በብር፣ ችግረኛውንም በጥንድ ጫማ እንገዛለን” (አሞጽ 8፡6)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 1:10–17፣ አሞጽ 5:21–24፣ ሚክ. 6:6–8። እነዚህ ሕዝቦች
ይፈጽሙ ስለነበረው ኃይማኖታዊ ሥርዓት ጌታ ምን እያላቸው ነበር?
ራሳቸውን ከኃይማኖትና አምልኮ ነጥለው በሚሳለቁና በዙሪያቸው ከነበሩ ሰብዓዊ
ወገኖች ሥቃይና ጭቆና በተጻራሪ በቆሙ ላይ እግዚአብሔር በነቢያቱ አማካይነት
ጠንካራ ቋንቋ ተጠቅሞ ሲናገር ይደመጣል። “ተጸይፌአለሁ፣ ጠልቼውማለሁ” በማለት
በአጠቃላይ በአምልኮአቸው መንገፍገፉን በአሞጽ 5፡21-24 እናነባለን። ጉባዔዎቻቸው
የሚከረፉ መሥዋዕታቸውና መዝሙራቸውም ከንቱ እንደሆነ ይናገራል።
ሕዝቡ እንዴት ተገቢ በሆነ መንገድ እግዚአብሔርን ማምለክ እንደሚችል አስመልክቶ
በሚክ. 6 እየገነነ የሚሄድ አነጋገር የቀረበ ሲሆን፤ መልእክቱ ፌዝ ቀመስ አስተያየት
ሳይቀር እንደ ተቀላቀለበት እናያለን። ነቢዩ ሕዝቡ ለሚቃጠል መሥዋዕት ይዞ ይቀርቡ
ስለ ነበረው ነገር በመሳለቅ መጠኑን “በአንድ ሺህ አውራ በጎች፣ በዐሥር ሺህ የዘይት
ፈሳሽ” (ሚክ. 6፡7) እያጎነ አስተያየት ይሰጣል። ይህን የሚለው አምላካዊውን ሞገስና
ይቅርታ ለማግኘት ሲባል የበኩር ልጅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ የደረሰውን
ጽንፍ የያዘ አሰቃቂ ድርጊት ከመንካቱ አስቀድሞ ነው።
በጽሑፉ መጨረሻ እግዚአብሔር በእውነት ይፈልግ የነበረው ነገር “ፍትሕን ታደርግ
ዘንድ፣ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፣ በአምላክህም ፊት በትህትና ትራመድ ዘንድ
አይደለምን?” (ሚክ. 6፡8) በማለት ይደመድማል።
በዙሪያዎ የሚገኙ እርዳታዎ የሚያሻቸው ምስኪኖችን ከመጎብኘት ይልቅ
በኃይማኖታዊ ቅርጽና ሥነ ስርዓት ላይ ይበልጥ በመጨነቅዎ የጸጸት ስሜት
ተሰምቶት ያውቃል? ከዚህ ተሞክሮ ምን ተማሩ?
ነቢያቱ በአምልኮ እና በፍትሕ መካከል ስላለው ግንኙነት በሚያቀርቡት ማብራሪያ
መሃል አጥብቀው የሚያሳስቡት አንድ ሌላ ቅደም ተከተል የነበረ ሲሆን ይኸውም
የደኻውና የተጨቆነው ሰብዓዊ ወገን ጉዳይ እንደሚያሳስባቸውና በዕጦት የነበሩትን
መርዳት ራሱን የቻለ አስፈላጊ የአምልኮ ክፍል መሆኑን ማስገንዘብ ነበር። ኢሳ. 58 ይህን
የግንኙነት ሰንሰለት ግልጽ አድርጎ ያቀርባል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. ምዕ. 58። በዚህ ምዕራፍ የቀደመ ክፍል እንደ ተገለጠው
በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል በነበረው ግንኙነት ላይ የተፈጠረው ስህተት ምን
ነበር?
ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ይህ ትችት የተሰነዘረው በንቁ ኃይማኖተኛ ሕዝቦች ላይ
ነበር። እግዚአብሔርን በጽኑ የሚሹ ቢመስሉም ነገር ግን አካሄዳቸው እየሠራ አለመሆኑ
በገሃድ የሚስተዋል ነበር። ስለዚህ የቀድሞውን የአምልኮ ዘይቤ በመለወጥ እርሱን
ከወትሮው በተለየ መንገድ ማገልገል እንደሚኖርባቸው በእግዚአብሔር ተነገራቸው።
አምልኮአቸው እንዴት መሆን እንደሚኖርበት እርሱ የሚመርጥላቸው ቢሆን ኖሮ
የእርሱን ፈቃድ እንዲህ ሲል ነግሮአቸዋል “የጭቆናን ሰንሰለት እንድትበጥሱ፣ የቀንበርን
ገመድ እንድትፈቱ፣ የተጨቆኑትን ነጻ እንድታወጡ” (ኢሳ. 58፡6)። በተጨማሪ
የተራቡትን ይመግባሉ፣ ቤት ለሌላቸው መጠለያ ይሰጣሉ፣ በእጦት ለሚገኙትም
የእርዳታ እጆቻቸውን ይዘረጋሉ።
ምንም እንኳ እነዚህ እንቅስቃሴዎች እንደ ብቸኛ የአምልኮ መንገድ ባይቀርቡም ነገር ግን
የአምልኮአቸው አካል ያደርጓቸው ዘንድ እግዚአብሔር አጥብቆ ሲያሳስባቸው ይታያል።
በዚህም አምልኮ ትኩረት የሚያደርገው ወደ ውስጠኛው ማንነታችን ብቻ ሳይሆን ነገር
ግን በመላው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ወገኖች ዙሪያ በረከት የሚያመጣ ይሆናል።
“የኃይማኖት እውነተኛ ዓላማ ሰዎችን ከተጫናቸው ኃጢአት እያላቀቁ፣ ጠባብነትንና
ጭቆናን እያስወገዱ ፍትሕን፣ ነጻነትንና ሰላምን ማስፋፋት ነው”—The SDA Bible
Commentary, vol. 4, p. 306.
አምልኮ እንዲህ ዓይነቱን ቅርጽ ሲይዝ ስለሚመጣው አምላካዊ በረከት እግዚአብሔር
የሰጠው ተስፋ በኢሳ. 58፡8-12 ቀርቦአል። እርሱ እንደሚላቸው ከሆነ--ሰዎች ስለ ገዛ
ራሳቸው የሚሰጡትን ትኩረት ጋብ ቢያደርጉ ኖሮ፤ አምላካዊው ፈውስና ወደ ቀደመው
ንጽህና የመመለስ ሥራ በውስጣቸው እየሠራ መሆኑን በተጨባጭ በተመለከቱ ነበር።
ደስ የሚለው ነገር በተጨማሪ ምዕራፉ እንዲህ ዓይነቱን አምልኮ በ “ደስታ” ከተሞላው
ሰንበትን የመጠበቅ ትእዛዝ ጋር በአንድ አስተሳስሮታል። በሰንበትና በአገልግሎት
መካከል ያሉትን አንዳንድ ጠንካራ ግንኙነቶች ቀደም ብለን የተመለከትን ቢሆንም፤
እነዚህ ቁጥሮች ግን ሁለቱንም ተግባራት ማለትም ሕዝቡ በአምልኮው እንዲነቃቃና
አምላካዊውን በረከት እንዲያገኝ የቀረበውን ጥሪ አጣምረው ይዘዋል። ኤለን ኋይት
በእነዚህ ጥቅሶች ላይ አስተያየቷን ስትሰጥ እንዲህ ትላለች፡ “የምሕረትና የቸርነት ተግባር
ኃላፊነቶች የጌታን ሰንበት በሚጠብቁ ወገኖች ላይ አርፎአል”—Welfare Ministry, p.
121.
የሱስን “ከኃጢአተኞች” ጋር ለምን በላህ ብለው ከተቹት አንዳንድ የዘመኑ
የኃይማኖት መሪዎች ፊት ለፊት በተጋፈጠበት ወቅት “ከመሥዋዕት ይልቅ
ምሕረትን እወዳለሁ” (ማቴ. 9፡13 /ሆሴዕ 9፡13/) ተብሎ በነቢዩ ሆሴዕ የተጻፈውን
ከጠቀሰላቸው በኋላ ወደ ቅዱሳን መጻሕፍት መለስ ብለው እግዚአብሔር ምን
ለማለት እንደፈለገ እንዲፈትሹ ነገራቸው።
የሱስ ለሌሎች ጥንቃቄ የማድረግና አገልግሎት የመስጠት ህይወት ኖሮአል።
የሱስ ከሌሎች ጋር መስተጋብር ፈጥሮ ባደረጋቸው ፈውሶች፣ ታምራቶች እንዲሁም
ምሳሌያዊ አነጋገሮች--እርሱ የመራው ዓይነት ህይወት እውነተኛ አምልኮን ምርጥ
በሆነ መንገድ እንደሚገልጽ የመሰከሩ ነበሩ። የኃይማኖት መሪዎች ዋንኞቹ ተቺዎቹ
ቢሆኑም፤ የእርሱ ጠንካራ ሒስ ኢላማዎችም ነበሩ። እንደ ኢሳይያስ ዘመን
የኃይማኖት መሪዎች ሁሉ እነዚህም ድኾችን እየበዘበዙና በዕጦት ያሉትን ቸል እያሉ
በሚፈጽሟቸው ኃይማኖታዊ ሥነ ስርዓቶች ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸው
የተለየ ግንኙነት እንደ ተረጋገጠ ያምኑ ነበር። አምልኮአቸው የድርጊቶቻቸውን
ቅደም ተከተል ጠብቆ መጓዝ ባለመቻሉ፤ የሱስ እንዲህ ያለውን ግብዝነት ሳያወግዝ
ማለፍ አልቻለም።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 12፡38-40። የሱስ “የመበለቶችን ቤት ያራቁታሉ” በሚል
የሰጠው አስተያየት ከመልእክቱ ዐውድ ውጪ ነው ወይስ በዋነኝነት ሊናገር የፈለገው
ሀሳብ ነው? “እነዚህ የባሰ ፍርድ ይቀበላሉ” የሚለውን አባባል እንዴት ይገልጹታል?
የሱስ በተለይ ለኃይማኖተኛ ሰዎች የሰጠው እጅግ አስፈሪ መልእክት ምናልባት
በማቴ. 23 የሚገኘው ነው። የሱስ የእነርሱን እምነት ከገለጸበት መንገድ መረዳት
እንደሚቻለው፤ እንዲህ ያለው ኃይማኖት በዕጦት ለሚኖሩ ምስኪኖች ህይወት
ድጋፍ የማይሰጥ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ ሸክም ነው። የኃይማኖት መሪዎች በእነዚህ
ድርጊቶቻቸው--ሰዎች ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዳይገቡ በሩን ይዘጉባቸዋል (ማቴ.
23፡13)።
ከብዙ መቶ ዓመታት ቀደም ብለው የነበሩ የነቢያት ድምጾች በዚህ ዙሪያ
ማስተጋባታቸው እንዳለ ሆኖ፤ የሱስም ይፈጽሟቸው በነበሩ ኃይማኖታዊ
ሥርዓቶችና ግብረገብነት በጎደላቸውን ባህሪያት መካከል የነበረውን ክፍተት ፊት
ለፊት አቅርቦአል። “ ‘እናንት ግብዞች የኦሪት መምህራንና ፈሪሳውያን፤ ወዮላችሁ
ከአዝሙድ፣ ከእንስላልና ከከሙን ዐሥራት እየሰጣችሁ በሕጉ ውስጥ ዋንኛ የሆኑትን
ማለትም ፍትሕን፣ ምሕረትንና ታማኝነትን ግን ንቃችኋልና፤ እነዚያን ሳትተዉ
እነዚህን ማድረግ በተገባችሁ ነበር’ ” (ማቴ. 23:23)። ኃይማኖታዊ ስርዓቶችና
አከባበሮች በራሳቸው ስህተት አለመሆናቸውን በፍጥነት እክሎ የተናገረው የሱስ-ነገር ግን ለሌሎች በጎ የመሆንን ስፍራ ሊወስዱ እንደማይገባ ተናገረ።
እውነት አለኝ፣ እውነትን ማወቄ በቂ ነው የሚለውን ወጥመድ የሆነ
አስተሳሰብ እንዴት ማስወገድ እንችላለን?
Read Ellen G. White, “Isaiah 58—A Divine Prescription,” pp. 29–34, in Welfare Ministry; “Woes on the Pharisees,” pp.
610–620, in The Desire of Ages.
“የኃይማኖተኝነትን ተጨባጭ እሴቶች በጥብቅ ያሳስቡ የነበሩት ነቢያት ከመቶዎች
ዓመታት ቀደም ብለው ለእስራኤላውያን የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን እየደጋገሙ
ያቀርቡ ነበር . . . ዘመን አልፎ ዘመን በተተካ ቁጥር የኃይማኖትን ቅርጽ ብቻ ይዘው
ምሕረት ለማድረግ ዝንጉ የመሆን አደጋ ላይ እየወደቁ ለነበሩ፤ እነዚህ ምክረ ሀሳቦች
በእግዚአብሔር ታማኞች በተደጋጋሚ ይቀርቡላቸው ነበር።”—Ellen G. White,
Prophets and Kings, pp. 326, 327.
“በኢሳይያስ መጽሐፍ ምዕራፍ 58 ላይ የቀረበውን መልእክት ለሕዝባችን
እንድጠቅስ ታዝዤ ነበር። ይህን ምዕራፍ በጥንቃቄ በማንበብ ለቤተ ክርስቲያኖች
ህይወት የሚያመጣውን አገልግሎት ማስተዋል ያሻል። የወንጌል ሥራ በልግስናችን
እንዲሁም በአገልግሎታችን ወደ ፊት ሊራመድ ይገባል። እርዳታ ከሚያሻቸው
በሥቃይ ያሉ ነፍሳት ጋር ሲገናኙ የልግስና እጅዎን ይዘርጉ። የተራቡትን ሲያገኙ
ይመግቡ። ይህን ሲያደርጉ ከክርስቶስ አገልግሎት ጋር በተጓዳኝ ይራመዳሉ። የጌታ
ቅዱስ ሥራ የደግነት ተግባር ነበር። በየቦታው የሚገኙ ሕዝቦቻችን በዚህ ድርሻ
ይኖራቸው ዘንድ ይበረታቱ።”—Ellen G. White, Welfare Ministry, p. 29.
1.ፍትሕ ማድረግንና ምሕረት መውደድን እንደ አምልኮ አካል አስበውት
ያውቃሉ? ይህ ሁኔታ ለሌሎች ጥንቃቄ በማድረግ ዙሪያ ያሎትን
አቋም እንዴት መለወጥ ይችላል? ስለ አምልኮ ያሎትን እሳቤስ እንዴት
ይቀይራል?
2.በክርስትና ሕይወታችን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ቤተ ክርስቲያን
“በሕጉ ውስጥ ዋነኛ የሆኑትን” (ማቴ. 23፡23) ችላ ከማለት እንዴት
መጠበቅ እንችላለን? ምናልባት እርስዎ ትንኝን አጥርተው ግመልን ግን
የዋጡበትን (ማቴ. 23፡24) ምሳሌ ከገዛ ተሞክሮዎ ማስታወስ ይችላሉ?
3.ግብዝነት እንደ ኃጢአት የሚታየው ለምንድን ነው? ቢያንስ መልካም
ለማድረግ እየሞከርን መታየታችን የተሻለ አይሆንም?
4.በነቢያቱ እንደተገለጸው እግዚአብሔር ለድኾችና ለችግረኞች ያለው
ራእይና ጥልቅ ስሜት በዚህ ዓለም ላይ ያሎትን አመለካከት መለወጥ
የሚችለው እንዴት ነው? ነቢያትን በዐይንዎ ቢመለከቱና በጆሮዎ ቢሰሙ
የዛሬዎቹን የዜና ዘገባዎች ምን ይህል በተለየ መንገድ ያደምጧቸው ነበር?
ማጠቃለያ፡ ምንም እንኳ ምድሪቷ ላይ የተንሰራፋው ክፋት ነቢያትን
ቢያሳስባቸውም፤ በተለይ ትኩረታቸው እግዚአብሔርን እንደ ራሳቸው
አምላክ የሚመለከቱና እርሱን የሚያመልኩ ይሠሩት በነበረው የክፋት ሥራ
ላይ ያነጣጠረ ነበር። ለነቢያትም ሆነ ለየሱስ--አምልኮ ከኢፍትሐዊነት ጋር
መሳ ለመሳ አይሄድም። እንደውም እንዲህ ዓይነቱ ኃይማኖት ግብዝ ነው።
እግዚአብሔር የሚሻው እውነተኛ አምልኮ ከጭቆና በተቃራኒ የሚሠራና
ለድኻውና ለችግረኛው ጥንቃቄ የሚያደርግ ነው።