ትንቢተ ዳንኤል
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከጥር 16 - 22

5ኛ ትምህርት

Jan 25 - Jan 31




ከኩራት ወደ ትህትና



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዳንኤል 4፡-1-33፣ ምሳሌ 14፡-31፣ 2ኛ ነገስት 20፡-2-5፣ ዮናስ 3፡-10፣ ዳንኤል 4፡-34-37፣ ፊሊጵስዩስ 2፡- 1-11


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ:- “ተአምራቱ እንዴት ታላቅ ነው! ድንቁም እንዴት ጽኑ ነው! መንግሥቱም የዘላለም መንግሥት ነው፥ ግዛቱም ለልጅ ልጅ ነው።” (ዳንኤል 4፡-3)

ኩ ራት እውነተኛው የኃጢያት ስር ነው ይባላል፡፡ መጀመሪያ የተጀመረው እና የታየው በሰማይ የመላእክት አለቃ፣ በሉሲፈር ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር ለሕዝቅኤል እንዲህ አለው ‹‹በውበትህ ምክንያት ልብህ ኰርቶአል ከክብርህ የተነሣ ጥበብህን አረከስህ በምድር ላይ ጣልሁህ ያዩህም ዘንድ በነገሥታት ፊት ሰጠሁህ። ›› (ሕዝቅኤል 28፡-17) ፡፡ ኩራት የሉሲፈርን ውድቀት መርታለች፣ እናም አሁን ይህንን ኩራቱን በመጠቀም ለቁጥር የሚታክቱ ብዙዎችን ወደ ጥፋት ጎዳና መርቷል፡፡ ሁላችንም ለመኖር በእግዚአብሔር ላይ ተደግፈን ያለን የወደቅን ሰብአዊ ዘሮች ነን፡፡ ያለን ማንኛውም መክሊት፣ በዚያ ተጠቅመን ያሳካነው ነገር ሁሉ ምንጩ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

እንደ እውነቱ የምናደርገው ሁሉ ትህትና ሊላበስ ሲገባው እንዴት ነው የምንኮራው፣ የምንፎክረው ወይም የምንታበየው? የትህትናን አስፈላጊነት ለመገንዘብ ናቡከደነጾር ብዙ ሰዓት ወስዶበታል፡፡ በእቶን እሳቱ ውስጥ የአራተኛው ሰው መከሰት ( ያለፈውን ሳምንት ጥናት ይመልከቱ) እንኳን ሕይወቱን ሊቀይረው አልቻለም፡፡ ደረጃውን ያወቀው እግዚአብሔር ግዛቱን ከወሰደበት እና ከአራዊት ጋር እንዲኖር ከላከው በኋላ ነበር፡፡ የዚህን ሳምንት ትምህርት ለ ጥር 23 ሰንበት በማጥናት ይዘጋጁ፡፡

ጥር 17
Jan 26

ይህች ባቢሎን ታላቅ አይደለችምን?


ዳንኤል 4፡-1-33ን ያንብቡ፡፡ በንጉሱ ላይ ምን ሆነ፣ ለምን?



እግዚአብሔር ለናቡከደነጾር ሁለተኛ እድልን ሰጠው፡፡ በዚህ ጊዜ፣ ንጉሱ ሕልሙን አልረሳም፡፡ ነገር ግን የባቢሎን ጠቢባን እንደገና ስላልሆነላቸው፣ ዳንኤል የህልሙን ትርጓሜ እንዲነግረው አስጠራው፡፡ በህልሙ ንጉሱ ሰማይ ላይ የሚደርስ ዛፍን ያያል እናም ዛፉ እንዲቆረጥ ይታዘዛል፡፡ ስሩ እና ጉቶው ብቻ በምድር ውስጥ እንዲቀሩ ይሆንና በሰማይ ጠል እንዲረሰርስ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ንጉሱን የረበሸው ነገር በህልሙ ውስጥ ከሰማይ ‹‹ ልቡም ከሰው ልብ ይለወጥ፥ የአውሬም ልብ ይሰጠው ሰባት ዘመናትም ይለፉበት።›› (ዳንኤል 4፡-16 ) የተባለው ነገር ነበር፡፡ የህልሙን አሳሳቢነት በመገንዘብ ዳንኤል በትህትና ህልሙ የንጉሱን ጠላት የሚመለከት ይሆን ዘንድ ሐሳቡን ገለጸ፡፡ ቢሆንም ግን ፣ በህልሙ ላለው መልዕክት ታማኝ በመሆን ፣ ህልሙ በእርግጥ የሚመለከተው ንጉሱን እንደሆነ ተናገረ፡፡

ዛፎች በመጽሐፍ ቅዱስ አብዛኛውን ጊዜ የነገስታት፣ የህዝብ፣ እና የግዛት ምሳሌዎች ናቸው( ሕዝቅኤል 17፣ 31፣ ሆሴዕ 14፣ ዘካሪያስ 11፡-1፣2፣ ሉቃስ 23፡-31)፡፡ ስለዚህ ትልቁ ዛፍ ትዕቢተኛውን ንጉስ ለመወከል ገጣሚ ነበረ፡፡ እግዚአብሔር ለናቡከደነጾር ግዛትን እና ሐይልን ሰጠው፣ ሆኖም ግን እርሱ ያለው ሁሉ ከእግዚአብሔር እንደመጣ መገንዘብን በተደጋጋሚ አልቻለም፡፡

በዳንኤል 4፡-30 ላይ ትኩረት አድርጉ፡፡ ጌታ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ላለመያዙ እንደማሳያ እንዲሆን፣ ንጉሱ ያለው ምን ነበር?



ምን አልባት የኩራት አደገኛነቱ በሁሉም ነገር በእግዚአብሔር ምን ያህል ጥገኞች እንደሆንን እንድንረሳ መምራቱ ነው፡፡ እናም ይህን አንድ ጊዜ እረሳን ማለት በጣም አደገኛ በሆነ የመንፈሳዊ አቋም ላይ ነን ማለት ነው፡፡ በህይወታችሁ ምን አይነት ነገሮችን አከናውናችኋል? በእነዚህ ሳትኮሩ ክብርን ልትወስዱ ትችላላችሁ? ከተቻለ እንዴት?

ጥር 18
Jan 27

ማስጠንቀቂያ በነብዩ


ዳንኤል 4፡27ን ያንብቡ፡፡ ስለሚሆነው ነገር ከተሰጠው ማስጠንቀቂያ በላይ ዳንኤል ንጉሱ ያደርግ ዘንድ የነገረው ምንድን ነው? ለምንስ ነው? (ምሳሌ 14፡-31ን እንዲሁ ይመልከቱ)



ዳንኤል ሕልሙን መተርጎም ብቻ ሳይሆን ናቡከደነጾር ከዚህ ሁኔታ የሚወጣባቸውን ነጥቦችም ጠቁሟል፡፡ ‹‹ንጉሥ ሆይ፥ ስለዚህ ምናልባት የደኅንነትህ ዘመን ይረዝም እንደ ሆነ ምክሬ ደስ ያሰኝህ ኃጢአትህንም በጽድቅ፥ በደልህንም ለድሆች በመመጽወት አስቀር። ›› (ዳንኤል 4፡-27) ናቡከደነጾር ባቢሎንን ለመገንባት ታላቅን ስራ አከናውኗል፡፡ የአትክልቱ ስፍራ ፣ የውሃ መውረጃው ቦይ ስርዓት፣ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ መቅደሶች እና የህንጻ ግንባታ ስራዎች ከተማዋን ከጥንታዊ ከተሞች መካከል አስገራሚዋ እንድትሆን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ይህ ማማር እና ውበት በከፊልም ቢሆን የተከናወነው በባሪያዎች ጉልበት ብዝበዛ እና ድሆችን በመጨቆን/በማግለል ነው፡፡

በተጨማሪ የመንግስቱ ሐብት ጥቅም ላይ የዋለው ለንጉሱ እና ለአጃቢዎቹ ደስታ ነው፡፡ ስለዚህ የናቡከደነጾር ኩራት ለእግዚአብሔር እውቅናን መስጠትን ብቻ ሳይሆን ያላደረገው ነገር ግን ውጤቱ ችግረኞች ያሉበትን መከራ እንዲረሳ አድርጎትም ጭምር ነበር፡፡ እግዚአብሔር ለድሆች የሚያደርገውን ልዩ ጥንቃቄ በመስጠት፣ ዳንኤል ለንጉሱ ከጠቀሳቸው ሌሎች ኃጢያቶች ጋር ፣ ድሆችን የመርሳት ኃጢያት ላይ ትኩረት ማድረጉ አያስገርምም፡፡

ለናቡከደነጾር መልዕክቱ በምንም አይነት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ የብሉይ ኪዳን ነብያት ድሆችን ስለመጨቆን የእግዚአብሔር ሕዝቦችን ብዙ ጊዜ ያስጠነቅቃሉ፡፡ በእርግጥም ለንጉሱ መዋጫ ይሆን ዘንድ ጎላ ካሉ ኃጢያቶች መካካል ችግረኞችን መርሳት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ለድሆች ፍቅርን ማድረግ ትልቁ የክርስቲያን የችሮታ መገለጫ ነው፣ በተቃራኒው ድሆችን መርሳት እና መበዝበዝ ደግሞ በእግዚአብሔር በራሱ ላይ ጥቃትን ማቋቋም/ማድረግ ነው፡፡ ለችግረኞች በመጠንቀቅ እግዚአብሔር የሁሉም ባለቤት መሆኑን እውቅና እንሰጣለን፣ ያም ማለት እኛ ባለቤት ሳንሆን እንዲያው ለእግዚአብሔር ንብረት ባላአደራዎቹ መሆን ማለት ነው፡፡

በንብረታችን ሌሎችን ስናገለግል ፣ እግዚአብሔርን እናከብራለን ጌትነቱንም እንገነዘባለን፡፡ የንብረት ባለቤትነትን፣ ዋጋ እና ተግባር የመጨረሻ የሚወስነው የእግዚአብሔር ባለቤትነት ሊሆን ይገባል፡፡ እዚህ ላይ ነው ናቡከደነጾር የወደቀው፣ እኛም የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት በመከናዎናችን እውቅና ካልሰጠን እና ችግረኞችን በመርዳት ይህንን ካላሳየን በስተቀር፣ ለመውደቅ እንጋለጣለን፡፡

ጥር 19
Jan 28

ልዑል ይሰለጥናል …


ንስሃ እንዲገባ እና የእግዚአብሔርን ይቅርታ እንዲጠይቅ ቢነገረውም፣ የናቡከደነጾር ያላላ ኩራት የሠማይ አዋጅን ተፈጻሚ እንዲሆን አስገደደ (ዳንኤል 4፡- 28-33) ፡፡ ንጉሱ በቤተ መንግስቱ እየተንጎራደደ እና ስላከናወናቸው ነገሮች እራሱን ሲያመሰግን፣ ከቤተ መንግስቱ ወጥቶ እንዲሔድ ባደረገው የአእምሮ መነካት ሁኔታ ተጎዳ፡፡ ምን አልባት በአእምሮ በሽታ ክሊኒካል ላይካንትሮፊ ወይም ዞአንትሮፊ ተብሎ በሚጠራ በሽታ ተጠቅቶ ሊሆን ይችላል፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታ በሽተኛው እንሰሳዊ ድርጊቶችን እንዲያደርግ ያደርገዋል፡፡ በዘመናዊው ጊዜ ይህ በሽታ ‹‹ እስፒሼስ ዳያስፎሪያ ›› ይባላል፣ የአንድ ሰው አካል የሌላ ዝርያ እንደሆነ የሚሰማ ስሜት ነው፣ እናም እንደ እንስሳ የመሆን ፍላጎት ነው፡፡

2ኛ ነገስት 20፡-2-5ን፣ ዮናስ 3፡-10ን ፣ እና ኤርሚያስ 18፡-7፣8ን ያንብቡ፡፡ እነዚህ ጥቅሶች ንጉሱ ከዚህ ቅጣት ዘወር ስለ ሚልበት ነገር ምን የሚነግሩን ነገር አለ?



እንዳለመታደል ሆኖ ናቡከደነጾር በከባዱ መንገድ መማር ነበረበት፡፡ ናቡከደነጾር በንጉሳዊ ስልጣኑ ላይ በነበረ ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነቱን ለማሰብ አቅም/ችሎታ አልነበረውም፡፡ ስለዚህ የንጉሳዊ ስልጣኑን በመውሰድ እና ከዱር አራዊት ጋር እንዲኖር በመላክ እግዚአብሔር ለንጉሱ ሙሉ በመሉ በእርሱ ላይ ጥገኛ እንዲሆን የሚገነዘብበትን ሌላ ዕድል ሰጠው፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔር ይህን ትዕቢተኛ ንጉስ እንዲማር የፈለገው የመጨረሻ ትምህርት ‹‹ስልጣን ከሰማያት›› መሆኑን ነው (ዳንኤል 4፡-26)፡፡ በእርግጥም በእግዚአብሔር ዕቅድ መሰረት በንጉሱ ላይ የመጣው ፍርድ፣ በሰማዩ አዋጅ እንደታወጀው፣ ትልቅ አላማ ነበረው፣ ‹‹ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለወደደውም እንዲሰጠው፥ ከሰውም የተዋረደውን እንዲሾምበት ሕያዋን ያውቁ ዘንድ ይህ ነገር የጠባቂዎች ትእዛዝ፥ ይህም ፍርድ የቅዱሳን ቃል ነው። ›› (ዳንኤለ 4፡-17)፡፡

በሌላ አባባል፣ በናቡከደነጾር ላይ የተተገበረው መርህ ለሁላችንም እንዲሁ ትምህርት ሊሆን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የምንመደበው ‹‹ በህያዋን ›› ምድብ ውስጥ ነው፣ የተሻለ ትኩረትን ለዋነው ትምህርት ልንሰጥ ይገባል፣ ያም ‹‹ልዑሉ በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን›› የተባለው ነው፡፡

ለምንድን ነው ልዑል በመንግስት ላይ እንዲሰለጥን የሚለው አስፈላጊ ትምህርትን መማር ለእኛ የሚያስፈልገን? ይህ እውቀት፣ ለምሳሌ እኛ በሐይል የምንሰለጠንባቸውን በምንይዝበት መንገድ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርገው?

ጥር 20
Jan 29

አይኖችን ወደ ሰማይ ማንሳት


ዳንኤል 4፡- 34-37ን ያንብቡ፡፡ እንዴት እና ለምን ነገሮች ለንጉሱ ተቀየሩ?



እግዚአብሔር እንግዳ በሆነ በሽታ ናቡከደነጾር እንዲመታ አደረገ፣ ነገር ግን እንደገና ወደ መልካም የአእምሮ ጤንነት እንዲመለስ አደረው፡፡ በሚገርም ሁኔታ ፣ በነብዩ በተተነበየው መሰረት ከሰባት አመታት በኋላ ሁሉም ነገር ተቀየረ፡፡ በሽተኛው ንጉስ አይኖቹን ወደ ሰማይ አነሳ (ዳንኤል 4፡34)፡፡ ‹‹ለሰባት አመታት ናቡከደነጾር ስለ ትምህርቶቹ ሲደነቅ ነበር፣ ለሰባት አመታት በአለም ሁሉ ፊት ትሁት ሆኖ ነበር፡፡ ከዚያ የማመዛዘን ብቃቱ ተመለሰለት እናም፣ በትህትና የሰማይን አምላክ አሻቅቦ ተመለከተ፣ በቅጣቱ ውስጥ የመለኮትን እጅ ተመለከተ፡፡ በሁሉ ፊት በደለኝነቱን እና በመታደሱ ውስጥ የእግዚአብሔርን ታላቅ ምህረት አወጀ፡፡ ››(ኤለን ጂ. ኋይት፣ ፕሮፌትስ ኤንድ ኪንግስ፣ ገጽ 520 )ምንም ጥያቄ የለውም አይናችንን ወደ ሰማይ ስናነሳ ታላቅ ለውጥ ይሆናል፡፡ ማስተዋሉ እንደ ተመለሰ ንጉሱ እነዚህን ትምህርቶች መማሩን አረጋገጠ፡፡

ነገር ግን ታሪኩ ስለ ናቡከደነጾር ሳይሆን ብዙውን ስለ እግዚአብሔር ምህረት ነው፡፡ ንጉሱ የእስራኤልን አምላክ ጌታው ለማድረግ ቀደም ሲል ሶስት እድሎችን አሳልፏል። እንዲህ አይነት አጋጣሚ ወደ እርሱ የመጣው በዕብራውያኑ ምርኮኛ ወጣቶች የእንግዳ ጥበብ(ዳንኤል1)በታየበት ጊዜ፣ ዳንኤል ሕልሙን በፈታ ጊዜ( ዳንኤል 2)፣ እና ሶስቱ ዕብራውያን ከእቶኑ እሳት በወጡ ጊዜ ነበር(ዳንኤል 3)፡፡ ከሁሉም በኋላ ያ አተራረፍ ትሁት ካላደረገው ምን ያደርገዋል? ከገዥው ችኮነት ይልቅ እግዚአብሔር አራተኛን እድል ሰጠው፡፡ በመጨረሻም፣ የንጉሱን ልብ ማረከ፣ እናም ወደ ንግስናው ስፍራ መለሰው( ዳንኤል 4)፡፡ የናቡከደነጾር ሁኔታ እንደሚያሳያው ከእርሱ ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዲኖረን ከአንድ እድል ደግሞ ሌላ እድል ይሰጠናል፡፡

ከብዙ ዘመናት በኋላ ጳውሎስ እንደ ጻፈው ጌታ ‹‹ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። ›› (1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡-3፣4 )ይላል፡፡ በዚህ ታሪክ ውስጥ ያንን እውነት የሚያሳየን ኃይለኛ ምሳሌን እናያለን፡፡ በእግዚአብሔር ትሁታን የሆናችሁባቸው መንገዶች ምን ምን ናቸው? ከዚያ ልምምድ ምን ተማራችሁ? ትምህርቱን እንደገና ከመማር ሊያድናችሁ የሚችል ምን አይነት ለውጥ ይሆን የሚያስፈልጋችሁ?

ጥር 21
Jan 30

ትሁት እና አመስጋኝ/ታላቅ


ንስሃ ገቢው ንጉስ እንዲህ ሲል አወጀ ‹‹ በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ›› (ዳንኤል 4፡-35)፡፡ በተሰጠው አውድ ምን አይነት አስፈላጊ ነጥቦችን ነው እያስቀመጠ ያለው?



በእርግጥ ናቡከደነጾር ከልቡ እውነተኛውን አምላክ መቀበሉን እንዴት እናውቃለን? ናቡከደነጾር ከጻፈው ዳንኤል ምዕራፈ 4 ላይ ዋና የሚባል መረጃን በእርግጥ እናገኛለን፡፡ በእርግጥ የዚህ ምዕራፍ አብዛኛው ክፍል ንጉሱ በግዛቱ ያሰራጨው ደብዳቤ ግልባጭ ይመስላል፡፡ በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ንጉሱ ስለ ኩራቱ እና ስለ እብደቱ፣ እንዲሁም በሕይወቱ በትህትና ስለተገነዘበው የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ተናግሯል፡፡ የጥንት ገዥዎች ጥቂቶቹ ናቸው ስለ እራሳቸው ክብርን የሚነካን አይነት ነገር የሚጽፉ፡፡ ልክ ሁሉም የጥንት ነገስታት መዛግብት እንደሚታወቀው ንጉስን ያሞካሻሉ/ያከብራሉ፡፡

እንደዚህ አይነት ዶሴ፣ ንጉሱ ኩራቱን እና እንሰሴአዊ ባህሪውን ያመነበት የንግግሩን ተአማኒነት ይጠቁማል፡፡ በተጨማሪ ልምምዱን የሚመለከት ደብዳቤን መጻፉ እና በትህትና የእግዚአብሔርን ሉአላዊነት ማመኑን መናዘዙ፣ ንጉሱን እንሚሲዮናዊ አድርጎታል፡፡ የተለማመደውን ልምምዱን እና ከእውነተኛው አምላክ የተማረውን ከዚህ በኋላ ሊደብቅ አልተቻለውም፡፡ እዚህ ያየነው እና የንጉሱ ጸሎት እና ምስጋና (ዳንኤል 4፡-34-37)፣ የልምምዱን እውነተኛነት የሚገልጽ ነው፡፡ ንጉሱ አሁን የተለያዩ አይነት እሴቶች ስብስብ አለው፣ የሰብአዊ ዘርን ውስንነት መገንዘብም ችሏል፡፡ ጠንከር ባለው የምስጋና ጸሎቱ የዳንኤልን አምላክ ኃይል ከፍ አደረገ እና ይህን ‹‹በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ምናምን ይቈጠራሉ ››(ዳንኤል 4፡ -35) ሲል አመነ፡፡ ይህ ሰብአዊ ዘሮች ሊኩራሩበት የሚችል ምንም የላቸውም፣ እንደ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ በዳንኤል መጽሐፍ ናቡከደነጾር በመጨረሻ ያነጸባረቀው፣ የንጉሱን ትህትና እና አመስጋኝነት፣ የእግዚአብሔርን ምስጋና የመዘመር እና ስለ ኩራት እኛን ያስጠነቀቀበትን ያሳያል፡፡

በእርግጥ እግዚአብሔር ሕይወትን መለወጡን ቀጥሏል፡፡ ምንም ያህል ሰዎች ኩራተኞች እና ኃጢያተኛ ቢሆኑም በእግዚአብሔር ዘንድ ግን ምህረት እና አማጺ ኃጢያተኞችን ወደ የሰማይ አምላክ ልጅነት የሚቀይር ኃይል አለ። ፊሊጲስዩስ 2፡-1-11ን ያንብቡ። በዚህ ስፍራ ኩራትን ከሕይወታችን የሚያስወግድን ምን ነገር እናገኛለን?

ጥር 22
Jan 31


ተጨማሪ ሐሳብ


‹‹ አንድ ወቅት ይኩራራ የነበረው ንጉስ ትሁት የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ፡፡፣ ጨካኝ፣ የሰውን ሐሳብ የሚያጣጥል ገዥ፣ ጠቢብ እና አፍቃሪ ንጉስ ሆነ፡፡ እግዚአብሔርን ሲቃወም እና ስሙን በክፉ ሲያነሳ የነበረ ንጉስ፣ አሁን የልዑልን ሀይል እውቅና ሰጠ፣ እናም በቅንነት የጆሆባን መፈራትን እና በእርሱ ትምህርት መደሰትን አስተዋወቀ፡፡ የነገስታት ንጉስ እና የጌቶች ጌታ ከሆነው ከእርሱ ግሳጼ፣ ናቡከደነጾር ሁሉም ገዥዎች ሊማሩት የሚገባን ትምህርት እውነተኛ ታላቅነት በእውነተኛ መልካምነት ውስጥ መሆኑን ተማረ፡፡

ጆሆቫ ህያው አምላክ መሆኑን እውቅና ሰጠ፣ እንዲህም አለ ‹‹ አሁንም እኔ ናቡከደነፆር የሰማይን ንጉሥ አመሰግናለሁ፥ ታላቅም አደርገዋለሁ፥ አከብረውማለሁ። ሥራው ሁሉ እውነት፥ መንገዱም ፍርድ ነውና፥ በትዕቢትም የሚሄዱትን ያዋርድ ዘንድ ይችላልና። ›› ‹‹ የአለም ትልቋ መንግስት የእርሱን ምስጋና እንድታሳይ የነበረው የእግዚአብሔር አላማ አሁን ተሳካ፡፡ ይህ ለሁሉ የሚሆን አዋጅ፣ ናቡከደነጾር የእግዚአብሔርን ምህረት ፣ መልካምነት እና ባለስልጣንነት የተናገረበት በታሪክ ተመዝግቦ የሚገኝ የሕይወቱ የመጨረሻ ድርጊት ነበር፡፡ ››(ኤለን ጂ. ኋይት፣ ፕሮፌትስ ኤንድ ኪንግስ ፣ ገጽ 521 )


የመወያያ ጥያቄዎች




1.‹‹ ኩራት ወደ ሌሎች መጥፎ ተግባራት ሁሉ ይመራል፡፡ ይህ ፍፁም የሆነ ፀረ-እግዚአብሔራዊ የአእምሮ ደረጃ ነው፡፡ ይህ ለእርስዎ በጣም የተጋነነ ይመሰልዎታል? ከሆነ እንደገና ያስቡ… አንድ ሰው አንድ ተጨማሪ ኩራት ካለበት፣ አንድ ተጨማሪ የማይወደው ኩራት በሌላው ይኖራል፡፡ በእርግጥ ምን ያህል ኩራተኛ መሆንዎን ማወቅ ከፈለጉ ቀላሉ መንገድ እራስን መጠየቅ ነው፣ ‹ ምን ያህል ነው ሌሎች ሰዎች ሲንቁኝ የምጠላው፣ ወይም ዝቅ አርገው ሲያዩኝ ወይም ሲረሱኝ የምጠላው? › እዚህ ላይ ነጥቡ የእያንዳንዱ ሰው ኩራት ከሌሎች ሰዎች ኩራት ጋር ንፅፅር ውስጥ ነው፡፡ ይህም ምክንያቱ በሆነ ስፍራ ሌላ ሰው ተሰሚነት ባለበት ቦታ እኔ ተሰሚነትን ለማግኘት እፈልጋለሁ፡፡ አብረው ሊሄዱ የማይችሉ ጉዳዮች ናቸው ››(ሲ.ኤስ . ሉይዝስ፣ ሜር ክርስቲያኒቴ (ኒዮርክ፣ ተች ,እስቶን፣ 1996)፣ ገጽ 110)፡፡ ሉይስ፣ ምን አልባት በእራስዎ ሕይወት ኩራትን ማየት እንዲችሉ እንዲረዳዎት ምን እያለ ነው ያለው?

2.በዚህ ምዕራፍ ፣ እንዲሁም ተከትለው በሚመጡት ውስጥ ያለው ዋና መልዕክት የእግዚአብሔር ሉአላዊነት ነው፡፡ ለምንድን ነው ይህ ሊገነዘቡት የሚገባ አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ የሆነው? ይህን አንገብጋቢ እውነት ለማስተዋል ይረዳን ዘንድ ሰንበት ያለው ሚና ምንድን ነው?