መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት እንተርጉም
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከመጋቢት 26- ሚያዚያ 02

2ኛ ትምህርት

Apr 04 - Apr 10




የመጽሐፍ ቅዱስ ምንጭ እና ተፈጥሮ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- 2ኛ ጴጥሮስ 1፡19-21፣ 2ኛ ጢሞ 3፡16፣ 17 ፣ ዘዳ 18፡18፣ ዘጸ 17፡14፣ ዮሐ 1፡14፣ ዕብ 11፡3፣6


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ ‹‹ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁ ጊዜ፥ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት፥ እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን። ›› (1ኛ ተሰ 2፡13)

የ መጽሐፍ ቅዱስን ምንጭ እና ተፈጥሮ የምንገነዘብበት መንገድ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በህይወታችን በሚኖረው ሚና በጣም በኃይል እና በሰፊው ደግሞ በቤተክርስቲያን ላይ ተጽእኖ አለው። መጽሐፍ ቅዱስን የምንተረጉምበት መንገድ የሚሆነው በተገለጠበት ሂደት እና የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ላይ ባለን ግንዛቤ የተወሰነ እና ተጽዕኖ ያረፈበት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በትክክል ማስተዋል ስንሻ በቅድሚያ መጽሐፍ ቅዱሱ እራሱ እንዴት ሊታይ እንደሚገባው ያስቀመጣቸውን መለኪያዎች እንዲወስን ልንፈቅድለት ይገባል። የሒሳብ ትምህርትን ለማጥናት ለባይዮሎጂ ወይም ለሶሾሎጂ የምንጠቀምባቸውን ልማዳዊ ሐቆችን መጠቀም አንችልም።

ታሪክን ለማጥናት በምንጠቀምባቸው መንገዶች ወይም መሳሪያዎች ፊዚክስን ልናጠና አንችልም። በተመሳሳይ መልኩ መንፈሳዊ የሆነው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትም ከክህደት መንገዶች ላይ በመነሳት እና እግዚአብሔር የለም ከሚል መነሻ በሚቀርቡ መንገዶች ሊታወቅ አይችልም። ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎማችን በጸና የመጽሐፍ ቅዱስን መለኮት-ሰብአዊን አቅጣጫ/እይታ ሊያማክል ይገባል። ስለዚህ ትክክለኛ ለሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም በክህደት ወይም በጥርጣሬ አቀራረብ ከመቅረብ ይልቅ በእምነት መቅረቡ አስፈላጊ ነው። በዚህ ሳምንት ጥናታችን በአተረጓጎማችን እና ማስተዋላችን /መረዳታችን ላይ ተጽዕኖ በሚያደርጉ መሰረታዊ የሆኑ ጉዳዮች፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ምንጭ እና ተፈጥሮን እንመለከታለን። የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሚያዚያ 03 ሰንበት አጥንተው ይዘጋጁ።

መጋቢት 27
Apr 05

የመጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ መገለጥ


2ኛ ጴጥሮስ 1፡ 19-21ን ያንብቡ። ጴጥሮስ ስለ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትንቢቶች መልዕክት ምንጭ ያለውን መረዳት የገለጸው እንዴት ነው?





መጽሐፍ ቅዱስ ልክ እንደ ሌሎች መጽሐፎች አይደለም። እንደ ሐዋሪያው ጴጥሮስ አባባል ነብያት መልዕክታቸው ከእግዚአብሔር ስለሆነ የጻፉት በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ነበር። እራሳቸው የፈጠሩት አይደለም። ከዚያ ይልቅ ‹‹በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል ›› (2ኛ ጴጥ 1፡16)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ መልዕክቶች ምንጫቸው መለኮታዊ ነው። እናም ስለዚህ እውነተኛ እና ታማኝ ነው። ‹‹ ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፥ ዳሩ ግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ። ›› (2ኛ ጴጥ 1፡21)። በመገለጡ ሒደት ውስጥ ለተመረጡት ሰብአዊያን ፈቃዱን ለማሳወቅ እግዚአብሔር ስራ ላይ ነበረ።

በእግዚአብሔር እና በተለዩት ሰብአዊ ፍጥረታት ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የነበረው ቀጥተኛ የሆን የቃል በቃል ግንኙነት ሊታለፍ የማይችል ሐቅ ነው። ለዚህም ነው መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ፣ መለኮታዊ ስልጣን ያለው። እናም ይህንን የመለኮታዊ ክፍሉን ስንተረጉም እሳቤ ውስጥ ልናስገባ ይገባል። ቅዱሱን አምላካችንን ልክ እንደ መጨረሻው ደራሲ አድርገን ልንወስድ ይገባል እናም የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፎች ‹‹ ቅዱሳን መጻሕፍት ››(ሮሜ 1፡2 ፣ 2ኛ ጢሞ 3፡15) በሚል ሊጠሩ የተገባው። እንዲሁ መጽሐፎቹ ለተግባራዊ ልምምድም የተሰጡ ናቸው። ‹‹የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል። ›› (2ኛ ጢሞ 3፡16፣17)።

እግዚአብሔር በቃሉ የገለጸውን በሕይወታችን ለመተግበር የመንፈስ ቅዱስ ድጋፍ ያስፈልጋል። እንደ ሐዋሪያው ጴጥሮስ መለኮታዊ ሆኖ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ቃል መተርጎም የእኛ የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል እና መንፈስ ቅዱስ በትክክል ትርጉሙን እንድንረዳ ያስፈልጉናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲሁ ‹‹ በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም። ›› (አሞጽ 3፡7) ይላል። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቃል ‹‹ሬቪሌሽን›› ( በተለያየ አይነት መልኩ የሚገልጠው) የሆነ ቀደም ሲል የተደበቀ ነገር አሁን ሲገለጥ ወይም ግልጽ እና የታወቀ ሲሆን ለሁሉም የታየ ነገርን የሚገልጽ ነው። እንደ ሰበአዊ ፍጥረት እንደዚህ አይነት መገለጥ ወይም ራዕይ ያስፈልገናል፣ እንደ ሐጢያተኛ ፍጥረታት፣ በሐጢያታችን ምክንያት ከእግዚአብሔር ተለይተናል እናም ፍቃዱን ለማወቅ በእርሱ ላይ እንደገፋለን። ምንም እንኳን ምንጩ መለኮት ቢሆንም፣ መጽሐፍ ቅዱስን መከተል በእራሱ ከባድ ነው ። በእርሱ ባንታመን እና የመለኮትን ምንጭነት እንዳልነው ባንቀበል ምን ሊሆን ይችላል?

መጋቢት 28
Apr 06

በመንፈስ የመነዳት ሒደት


እግዚአብሔር ፈቃዱን ለሰዎች ለመግለጽ ቋንቋን በመጠቀሙ ምክንያት የመለኮት መገለጥ መጻፍ ችሏል። ሆኖም ግን ቀደም ሲሰል እንደተመለከትነው መጽሐፍ ቅዱስ በሰብአዊያን መሳሪያ ውስጥ ጠብቆ ባስተላለፈው በመንፈስ ቅዱስ ስራ አማካኝነት የተገለጠው የእግዚአብሔር እውነት ውጤት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ድረስ (ለምሳሌ ዘፍጥረት 3፡14፣ 15 እና 12፡17 ) ልናይ የቻልነውን መሰረታዊ አንድነቱን ለመጠበቁ ምክንያቱ ይህ ነው ። 2ኛ ጴጥሮስ 1፡21፣ 2ኛ ጢሞ 3፡16 እና ዘዳግም 18፡ 18ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ መንፈሳዊ መነዳት ምንድን ነው የሚሉት?





ሁሉም መጽሐፎች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የመጡ ናቸው። ምንም እንኳን ሁሉም እኩል የማያነቃቁ እና በህይወታችን የማንተገብራቸው ቢሆንም (ለምሳሌ የዕብራውያን በዓላት ያለበት ፣ ምን አልባት ዛሬ ልንጠብቃቸው ባያስፈልጉም) ግን ከሁሉም ክፍሎች ልንማር ያስፈልገናል። ለማንበብ እና ለመረዳት ቀላል ካልሆኑም ክፍሎች ወይም አሁን ለእኛ ገጣሚ ያልሆኑም ክፍሎች ጭምር ልንማር ያስፈልገናል። እንዲሁ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁሉም እኩል መለኮታዊ መገለጥን አላገኙም። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስን ጸሐፊዎች ነገሮችን በጥንቃቄ የሚመረምሩትን ወይም ያሉ ዶሴዎችን ( ኢያሱ 10፡13፣ ሉቃስ 1፡ 1-3 ይመልከቱ ) የሚጠቀሙ ጸሐፊዎችን መልዕክቱን እንዲያደርሱ ተጠቅሟል።

ሆኖም ግን ሁሉም ጽሑፎች በመንፈስ የተመሩ ናቸው(2ኛ ጢሞ 3፡ 16)። ይህ ነው ጳውሎስ ‹‹የተጻፈው ሁሉ ›› ለእኛ ምሪት ነው እናም ስለዚህም ‹‹ በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።›› (ሮሜ 15፡4) የሚልበት ምክንያት። ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ደራሲው እንደሆነ ያመላክታል፣ ሆኖም ግን የተጻፈው በሰብአዊያን እጅ ነው፣ እንዲሁም በተለያየ አይነት አቀራረብ የተለያዩ መጽሐፎች በተለያዩ ጸሐፊ ባህሪዎችም ቀርበዋል። የተገለጡት እውነቶች ‹ በእግዚአብሔር ምሪት › (2ኛ ጢሞ 3፡16) የተሰጡ ነገር ግን በሰብአዊያን ቃላት የተገለጹ ናቸው። ›› (Ellen G. White, The Great 4 Controversy, p. 7)

ዛሬ ብዙ የመጸሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ የመለኮት ስልጣን መኖሩን የካዱ ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች/ተመራማሪዎች አሉ። በጣም አንገብጋቢ በሆኑ ትምህርቶችም ላይ ያነጣጠሩ ናቸው፣ ፍጥረት፣ ነጻ መውጣትን እና ትንሣኤን ክደዋል። ለምንድን ነው ይህ በጣም አስፈላጊ/ አንገብጋቢ የሆነው በር ላለመክፈት ትንሽም እንኳን ላለመክፈት? ከሁሉም በላይ በእግዚአብሔር ቃል ላይ እኛ መፍረድ አለብን?

መጋቢት 29
Apr 07

የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል


‹‹እግዚአብሔርም ሙሴን በእነዚህ ቃሎች መጠን ከአንተና ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን አድርጌአለሁና እነዚህን ቃሎች ጻፍ አለው። በዚያም አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ከእግዚአብሄር ጋር ነበረ፡ እንጀራም አልበላም ውኃም አልጠጣም። በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ ›› (ዘጸ 34፡27)። ለምንድን ነው ጌታ ሙሴ እነዚህን ቃላቶች እንዲጽፍ ያደረገው፣ ሙሴ ለሕዝቡ ብቻ እንዲናገር /እንዲያሰማ ከማድረግ ይልቅ፣ ግልጽ የሆነው የተጻፈ ቃል ጠቀሜታ ምንድን ነው?

የሚናገረው እና የሰብአዊያንን ቋንቋ የፈጠረው እግዚአብሔር የተገለጠውን የመለኮት እውነት እና በመለኮት ተነድቶ የመጣውን ሐሳብ በታማኝ እና በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያስተላልፉ የተመረጡትን ሰዎች አስቻለ። ስለዚህ እግዚአብሔር የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊያንን ትእዛዛቱን እና መገለጡን በጽሑፍ እንዲያደርጉ ማዘዙ አያስደንቅም። ስለተጻፉ መገለጦች የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል ? ዘጸ 17፡ 14፣ 24፡4



ኢያሱ 24፡26



ኤር 30፡2



ራዕ 1፡11፣ 19፣ 21፡5፣ 22፡18፣ 19



ለምንድን ነው እግዚአብሔር ራዕዩ እና መልዕክቶቹ እንዲጻፉ ያዘዘው? የታወቀው መልስ በቀላሉ እንዳንረሳው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፉት ቃላት ወደ እግዚአብሔር እና ወደ ፈቃዱ የሚመሩን ቋሚ ምልክቶች/አመላካች ናቸው። ብዙ ጊዜ የተጻፉ መረጃዎች የተሻለ ብዙ ጊዜ መቆየት ይችላሉ፣ እንዲሁም በቃል ከሚነገር ብዙ ጊዜ ደግሞ ደጋግሞ የሚናገሩት ሊናገሩት ከሚገባው ይልቅ አስተማማኝም ናቸው። የተጻፉ ቃላት ደግመው ደጋግመው ሊቀዱ ይችላሉ፣ ከሚነገር ይልቅ ጽሑፍ እጅግ ብዙ ሰዎች ሊያገኙትም የተመቸ ነው። በመጨረሻ አንድ ጊዜ እና በአንድ ስፍራ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ ልንናገር እንችላለን የተጻፈ ነገር ግን ሊቆጠሩ በማይችሉ አንባቢዎች በተለያየ ስፍራ እና አህጉር እንዲሁም ኋላም ለበርካታ ትውልድ ሁሉ በመተላለፍበረከት ይሆናል። በእርግጥ ሰዎች በእራሳቸው ካላነበቡ አንኳ ሌሎች የተጻፈን መረጃ ሊያነቡላቸው ይችላሉ።

መጋቢት 30
Apr 08

በክርስቶስ እና በመጽሐፍ ቅዱስ መካከል ያለ መመሳሰል


ዮሐ 1፡ 14፣ ዮሐ 2፡22፣ ዮሐ 8፡ 31፣ 32 እና ዮሐ 17፡17ን ያንብቡ። በ ኢየሱስ፣ ቃልም ስጋ ሆነ እና መጽሐፍ ቅዱስ (የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል) መካከል ምን አይነት መመሳሰልን ያያሉ?





በእግዚአብሔር ቃል እና ስጋ ሆነ በሚለው መካከል መመሳሰል አለ ( ለምሳሌ ኢየሱስ ክርስቶስ) እና የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል (ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ)። ልክ ኢየሱስ በመንፈሳዊ ሀይል በመንፈስ ቅዱስ ተጸንሶ ከሴት መወለዱ፣ ቅዱስ መጽሐፍም አንዲሁ በመንፈስ የመጣ እና በሰብአዊያን የተወለደ/የተሰጠ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ በጊዜ እና በስፍራ ተገድቦ ሰው ሆነ። በተወሰነ ጊዜ እና ስፍራ ኖረ። ቢሆንም ግን ይህ እውነታ መለኮትነቱን አላሳጣውም ወይም ከታሪክ ጋር የተያያዘ ብቻ አላደረገውም። በአለም ሁሉ በዘመናት ሰዎች ሁሉ የሚድኑበት ብቸኛው አዳኝ እርሱ ነው (ሐዋ 4፡12ን ይመልከቱ)። እንደዚሁ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተሰጠው በተወሰነ ጊዜ እና በተለየ ባህል ውስጥ ነው። ልክ እንደዚሁ ክርስቶስ ኢየሱስ በጊዜ የተገደበ አይይለም ያም ማለት ለተወሰነ ጊዜ እና ቦታ ብቻ የተገደበ አይደለም። ከዚያ ይልቅ በመላው አለም ለሰዎች ሁሉ የተሰጠ ነው።

እግዚአብሔር እራሱን ሲገልጽ ወደ የሰው ደረጃ ወረደ። የኢየሱስ ሰብአዊ ተፈጥሮ የሰብአዊያንን ደካምነት የ 4000አመታት የትውልድን ተጽእኖ ያሳያል። ሆኖም ግን ያለ ሐጢያት ነበረ። በተመሳሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ቋንቋ የሰብአዊ ነው። ‹‹እንከን አልባ የላቀ የሰብአዊያን ቋንቋ ›› ማንም የማይናገረው ወይም የማያስተውለው አይደለም። የትኛውም ቋንቋ የእራሱ የሆነ ውሱንነት ቢኖረውም የሰብአዊ ፍጥረት ፈጣሪ ቋንቋቸውንም የፈጠረው ፈቃዱን ለሰብአዊያን በሚያስተማምን ሁኔታ ያለምንም የተዛባ አመራር ለማስተላለፍ ይችላል። በእርግጥ እያንዳንዱ ንጽጽር የእራሱ የሆነ ውሱንነት አለው። ኢየሱስ ክርስቶስ እና ቅዱሳን መጽሐፍት ሙሉ ለሙሉ አንድ አይደሉም። መጽሐፍ ቅዱስ ስጋ ለባሽ አምላክ አይደለም።

እግዚአብሔር መጽሐፍ አይደለም። በኢየሱስ ክርስቶስ ያለው እግዚአብሔር ግን ሰብአዊ ሆነ። መጽሐፍ ቅዱስን እንወዳለን ምክንያቱም በገጾቹ የታወጀውን አዳኝ እናመልካለን። መጽሐፍ ቅዱስ የተለየ ነው ምክንያቱም ሊለያዩ የማይችሉ የመለኮት እና ሰብአዊ ጥምረት ነው። ኤለን ጂ ኋይት በግልጽ አይታለች ይህን ስትጽፍ ‹‹መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር የሰጠውን እውነት በሰው ቋንቋ የተገለጸውን የመለኮት እና የሰብአዊ ጥምረትን ያቀርባል። እንደዚህ አይነት ጥምረት የእግዚአብሔር ልጅ እና የሰው ልጅ በሆነው በክርስቶስ ተፈጥሮ ውስጥ አለ። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ እንደነበረው፣ እውነት ነው ‹ ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥› (ዮሐ 1፡14) ›› (ኤልን ጂ ኋይት ፣ ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 8) መጽሐፍ ቅዱስ ለእምነታችን መሰረታዊ ሊሆን የሚገባው ለምንድን ነው? ያለ እርሱ የት እንሆን ነበር?

ሚያዚያ 01
Apr 09

በእምነት መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት


ዕብራውያን 11፡3፣ 6ን ያንብቡ። ለምንድን ነው እምነት እግዚአብሔርን እና የእርሱን ቃል ለመረዳት አስፈላጊ የሚሆነው? እግዚአብሔርን ያለ እምነት ደስ ማሰኘት የማይቻለው ለምንድን ነው?





ሁሉም ትክክለኛ ትምህርት የሚካሔደው በእምነት አውድ ነው። ልጅ አዲስን ነገር የሚማረው፣ ለወላጆቹ በውስጡ ባለ ነገር ግን ባልተገለጸ እምነቱ አማካኝነት ነው። ልጅን መሰረታዊ እና ወሳኝ የሆኑ የህይወት እና የፍቅር ነገሮችን እንዲማር ምሪትን የሚሰጠው በመተማመን ላይ ያለው ግንኙነቱ ነው። ስለዚህ እውቀቱ እና ማስተዋሉ የሚያድገው ለፍቅር እና ለመተማመን ካለው ግንኙነት የተነሳ ነው። በተመሳሳይ ስሜት በጣም ጥሩ ሙዚቃ ተጫዋች አንድን ሙዚቃ በደንብ የሚጫወተው ወይም የምትጫወተው ቴክኒካል ብቃት ስላለው/ስላላት፣ መሳሪያውን ለመጫዎት ይረዳል፣ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለሙዚቃው፣ ለአቀናባሪው እና ለመሳሪያው ያለውን/ ያላትን ፍቅር ሲያሳይ/ስታሳይ ነው። በተመሳሳይ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስንም በፍቅር መንፈስ እና በእምነት እንጅ በጥርጣሬ አስተሳሰብ እና በክህደት መንገድ ብንቀርበው ልንረዳው አንችልም። ሐዋሪያው ጳውሎስ ‹‹ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም ›› (ዕብ 11፡6) ሲል ጽፏል። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በእምነት መቅረብ መተኪያ የለውም፣ መጽሐፍ ቅዱስን ልክ እንደ ሰብአዊያን መጽሐፍ ከማየት ይልቅ መንፈሳዊ ምንጭ እንዳለው እውቅና ሊሰጥ ይገባል።

የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶች ይህን አመለካከት፣ መንፈሳዊ ምንጭ እንዳለው በመሰረታዊ የአድቬንትስቶች እምነት ላይ በመጀመሪያ አስቀምጠዋል፣ እንዲህ ይላል ‹‹ ቅዱሳት መጽሐፍት ፣ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በመንፈስ ተነድተው የተጻፉ የእግዚአብሔር ቃላት ናቸው። በመንፈስ የተነዱት ጸሐፊያን በመንፈስ ሲመሩ ሳል የተናገሩት እና የጻፉት ነው። በዚህ ቃል እግዚአብሔር ለሰብአዊያን ድነት አስፈላጊ የሆኑ እውቀቶችን አስቀምጧል። ቅዱሳት መጽሐፍት የበላይ፣ ስልጣን ያላቸው እና የማይሳሳት ፈቃዱ የተገለጠባቸው ናቸው።

የባህሪ መለኪያ ናቸው፣ የልምምድ መፈተኛም ናቸው፣ የስነመለኮት አስተምህሮ መፍቻ መግለጫ እና በታሪክ ውስጥ የእግዚአብሔር ድርጊት ተመዝግቦ የሚገኝባቸው ታማኝ መዛግብት ናቸው። (መዝ 119፡105፣ ምሳሌ 30፡5፣ 6፣ ኢሳ 8፡20፣ ዮ 17.17፣ 1ኛ ተሰ 2፡13፣ 2ኛ ጢሞ 3፡16፣ 17፣ ዕብ 4፡12፣ 2ኛ ጴጥ 1፡20፣21) ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት፣ ጽሑፎችን በእምነት ከሆነ አመለካከት ሳይቀርቡ ሳለ የሚስቱት ምን ምን ነገሮችን ነው? ለምንድን ነው ይህ እምነት እውር ያልሆነው? ያም ማለት ለዚህ እምነት ምን አይነት ጥሩ ምክንያቶች አሉን እናም ለምንድን ነው እምነት አሁንም ከመጽሐፍ ቅዱስዊ እውነት ጋር ካለን ግንኙነት አንጻር በጣም አስፈላጊ የሚሆነው?

ሚያዚያ 02
Apr 10


ተጨማሪ ሐሳብ


“Methods of Bible Study” ከሚለው ዶሴ ላይ ፡ “2. Presuppositions Arising From the Claims of Scripture,” part a) Origin, and part b) Authority. (“Methods of Bible Study” የሚለው የሚገኘው በሚከተለው ድረ-ገጽ ላይ ነው www.adventistbiblicalresearch.org/materials/bible- interpretation-hermeneutics/methods-bible-study ለእምነታችን መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፣ በሕይወታችን ፣ በልባችን እና በአእምሮአችን ስናነብ እና ስናጠና ያለ መንፈስ ቅዱስ ተጽዕኖ ብቻውን ምንም አይነት ጥቅም የለውም። ‹‹በቃሉ እግዚአብሔር ለሰዎች ድነት አስፈላጊውን እውቀት አስቀምጧል።

ቅዱሳት መጽሐፍት ስልጣን እንዳላቸው፣ የማይለወጥ የፈቃዱ መገለጥ እንደሆኑ መቀበል ያስፈልጋል። የባህሪ መለኪያ፣ የስነ-መለኮት አስተምህሮ መግለጫ፣ እና የልምምድ መፈተኛ … ሆኖም ግን እውነታው እግዚአብሔር ፈቃዱን ለሰዎች በቃሉ ውስጥ ገልጧል። ይህ ግን የመንፈስ ቅዱስ ተከታታይ እና የማያቋርጥ ምሪት አያስፈልግም ማለት ግን አይደለም ። ለአገልጋዩ እንዲከፈት፣ እንዲያበራ እና በትምህርቱ እንዲኖር መንፈሱ በአዳኛችን ቃል ተገብቶልናል። የእግዚአብሔር መንፈስ ነድቶ ስላጻፈው የመንፈስ ቅዱስ ትምህርት ከቃሉ ጋር ተጻራሪ ሊሆን ከቶ አይችልም ›› (ኤለን ጂ ኋይት ፣ ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 9)


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ለምንድን ነው እግዚአብሔር እራሱን እና ፈቃዱን ለእኛ የገለጸው? ለምንድን ነው መገለጽ ያስፈለገን?

2. እግዚአብሔር እንዴት ነው እራሱን የገለጸው? እግዚአብሔር ስለራሱ ለመግለጽ የተለያዩ መንገዶች ይጠቀማል። ጠቅለል ባለ ሁኔታ በተፈጥሮ ውስጥ ይህን አድርጓል ነገር ግን የበለጠ በትኩረት ደግሞ በሕልሞች ( ዳንኤል 7፡1)፣ በራዕይዎች(ዘፍ 15፡1)፣ ምልክቶች (1ኛ ነገስት 18፡24፣38 )፣ እናም በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ (ዕብ 1፡1፣2)። በግል እግዚአብሔር እራሱን ገልጾሎታል? ልምድዎን ያካፍሉ።

3.አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተመራማሪዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎችን ትተዋል፣ አንደ አፈታሪክ ያዩአቸዋል። ልክ እንደ የፍጥረትን ታሪክ፣ አዳም እና ሔዋን፣ ከግብጽ መውጣት እና የዳንኤል ታሪክ እንደ ምሳሌ የሚቀርቡ (ከብሉይ ኪዳን) አንደ ምንም ሳይቆጠሩ የተወገዱ አስተምህሮዎች ናቸው። ነገር ግን መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተማር ሰው ሰራሽ ታሪኮች ተቀርጸዋል። ሰው በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሲተላለፍ የሚሆነው ይህ ነው። ይህ እንደዚህ አይነት አስተሳሰብ አደገኛ እንደሆነ ምንድን ነው በግልጽ ሊነግረን የሚችለው ?

4.እግዚአብሔር ፈቃዱን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሐይለኛ በሆነ መንገድ ገልጧል። ቢሆንም ግን እግዚአብሔር የእርሱን ፈቃድ እና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ብቻ ያለውን ድነት መልካም ዜና/የምስራች እንዲያሰራጩ እርዳታዎን ይፈልጋል። ሰዎች ሲመለከቱዎት በእርስዎ ውስጥ እና በባህሪዎ ምን አይነት አምላክን ነው የሚያዩ?