የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 4ኛ ሩብ ዓመት 2020

ከኅዳር 19 – 25

10ኛ ትምህርት

Nov 28 - Dec 04




ክርስቲያናዊው ሥነ ትምህርት በሥነ ጥበባት እና ሣይንስ ዘርፍ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሮሜ. 1:18– 21፣ መዝ. 19:1–6፣ 96:9፣ ዘፍ. 3:6፣ 1ጢሞቴ. 6፣ ምሳ. 1፣ ኢዮ. 38።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያውጃሉ” (መዝ. 19፡ 1)፡፡

ሥ ነ ትምህርት የሥነ ጥበባት እና ሣይንስ ዘርፎችንም ያካትታል። ሥነ ጥበባትን እና ሣይንስን ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ የመማራችንና ማስተማራችን አንደምታው ምንድን ነው? ለምሳሌ ከዘመናዊው ሕክምና ወይም የሥነ-ጥበባት ታሪክ ገጽታ ተዛምዶ ያላቸውን የተመረጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እያቀረብን ነው? ይህን በማድረግ ተግባራዊው ትምህርታችን ውስብስብ የሆነችውን ዓለማችንን ከፈጠረው አስደናቂ አምላካዊ ኃይል ጋር ዝምድና የሚፈጥርበትን መንገድ ማመቻቸት እንችላለን። ነገር ግን በመማሪያ መጽሐፍ ውስጥ እንዲካተት የሚደረግ አነስተኛ መጠን ያለው የደኅንነትና መቤዠት አምላካዊ ቃል--የእውነተኛው ትምህርት ቅምሻ ከመሆን አይዘልም።

እንዲህ ዓይነቱ ትምህርት በትክክል እንዲሠራ ከተፈለገ ከሰብዓዊው ፍጡር እስከ ሞሎኪውላር ባዮሎጂ የዘለቀ እያንዳንዱን ተግሳጽ የሚጠቁም አምላካዊ ቃል ያስፈልገናል። ይህ ካልሆነ--የእግዚአብሔርን ታላቅነት፣ ሉዓአላዊ ፈጣሪነቱንና ዓለምን ጠብቆ መያዙን ለማየት የሚሳነን እንሆናለን። እግዚአብሔር የፍጥረት ሥራውን ምሉዕ እና ዓላማ መር አድርጎ መመልከቱን ስንማር፤ አንዳንድ ተግሳጽ ነክ ጽንሰ ሀሳቦች እንዴት ትምህርት ላይ መዋል እንደሚኖርባቸው መረዳት እንጀምራለን።

በዚህ ሣምንት ጥናታችን ሥነ ጥበባትን እና ሣይንስን ከክርስትና እና ዓለማዊ ዐውድ እንዴት ማስተማር እንደምንችል የቀረቡ አንዳንድ መርኅዎችን እንመለከታለን።

ኅዳር 20
Nov 29

ጌታ ብቻ


ፍጡራን የሕያው አምላክን ሕልዎት ይመሰክራሉ--የተሰኘው አባባል እጅግ ተደጋግሞ ከመወሳቱ የተነሳ ለዛው እንደ ተሟጠጠ አነጋገር ሊወሰድ ይችላል። ለምሳሌ እግዚአብሔር ይህን ዓለም ሲፈጥር በልቡ የነበረውን ነገር ማሰባችንና ሰዎች እንዴት ወደ ውድመትና ጥፋት እንደ ጠመዘዙት መመልከታችን፤ ሥነ ጥበባትን እና ሣይንስን ምርጥ በሆነ መንገድ ማስተማር ወደምንችልበት ዐውድ ያስጠጋናል። ለአብነት ያህል የሰውን የእርግዝና ጊዜ እንመልከት። ሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) እንደሚነግረን አዲስ የማሰብ ችሎታ ያለው ሰብዓዊ ሕይወት በአንድ የዳበረ እንቁላል ከተጠነሰሰ ጊዜ አንስቶ በቀጣዮቹ ዘጠኝ ወራት እስከ ሙሉ የእርግዝና ጊዜ ያድጋል። በፍቅር የተሞላው ፈጣሪ ሁሉም ዓይነት ምልክቶች በዚህ ዑደት ውስጥ አሉ። በጽናት ከሚመታው የእናቲቱ ልብ ዝቅ ብሎ በሚገኘው የጽንሱ ዕድገት-የእግዚአብሔር አፍቃሪነትና ርኅራኄ መታየት ይችላል። ጽንሱ እያደገ በሄደ መጠን የእናቲቱም ሆድ እየገፋ፣ እየተለጠጠ ይሄዳል። ሰማያዊው አባት ሁሌም ልቡ ከልጆቹ የተቆራኘ እንደመሆኑ--ድርስ የሆነችውም እናት የዘወትር ሀሳብ ልጇ ይሆናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 1፡18-21፣ መዝ. 19፡1-6፣ ነኽ. 9፡6። ፈጣሪያችን እግዚአብሔር አምላክ ስለሚሠራው ሥራ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



በምድር ላይ ኃጢአት ከሰፈነ ከ6,000 ዓመታት በኋላ፤ ብሎም የጥፋት ውሃ በምድር ላይ ውድመት ካስከተለ ከሺዎች ዓመታት በኋላ እንኳ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን መሆኑን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ኃያልነቱን፣ አፍቃሪነቱንና ቸርነቱን የሚያሳዩ ሕልቁ መሣፍርት ማስረጃዎች አሉ። ይህን አምላክ የሚቃወሙ ሰዎች በፍርድ ቀን “ማመካኛ የላቸውም” ምክንያቱም እርሱ ከፈጠረው ነገር በቂ ትምህርት ማግኘት ይችሉ ነበር ሲል ጳውሎስ በሮሜ 1፡18-21 ቆምጨጭ ያለ መልእክት ያስተላልፋል። ሕግን አለማወቅ ከጥፋተኝነት አያድንም--ይባል የለ? ስለዚህ አላወቅንም ነበር የሚል ሙግት ማንሳት አይችሉም!

በተለይ አያሌዎች ከፈጣሪ ይልቅ ለፍጥረት አምልኮ እያቀረቡ በሚገኙበት ቀንና ዘመን--ሥነ ጥበባትንና ሣይንስን ሁሌም ከእግዚአብሔር ፈጣሪነትና ፍጥረትን ደግፎ ከመያዙ ዐውድ የሚሠራው ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት እንዴት ወሳኝ ነው! በመጨረሻ፤ እግዚአብሔርን የሚክድ ወይም የሚነጥል ማንኛውም ዓይነት ርዕዮተዓለም ሊመራ የሚችለው ወደ ስህተት ብቻ ነው። ዓለማዊው ሥርዓተ ትምህርት እግዚአብሔር የለም ከሚለው ግምት አኳያ ብቻ መሥራቱ የአደባባይ ምስጢር ቢሆንም፤ ክርስቲያናዊው ሥነ ትምህርት በዚያ ወጥመድ መሰናከል የለበትም ወይም እግዚአብሔር የለም በሚለው መርኅ ላይ ተመርኩዞ ላመል እንኳ ለመሥራት ሊዳዳው አይገባም። አንዳቸውም መንገዶች ሰብዓዊውን ፍጡር ጉዞውን በስህተት እንዲያጠናቅቅ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም።

ዓለማችን በኃጢአት ከወደቀች በኋላም እንኳ ስለተላበሰችው ወደር የለሽ ውበት አሰብ ያድርጉ። በተለይ በግላችን ሥቃይና መከራ ሲገጥመን ከዚህ ውስጥ ተስፋና መጽናናት ማግኘትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ኅዳር 21
Nov 30

የተቀደሰ ውበት


“በተቀደሰ ውበት ለእግዚአብሔር ስገዱ፤ ምድርም ሁሉ በፊቱ ተንቀጥቀጡ” (መዝ. 96፡9) ። ለመሆኑ “የተቀደሰ ውበት” የሚለውን ሀረግ ጽንሰ ሀሳብ የምናስተውለው እንዴት ነው? ይህ ለክርስቲያን ምን ዓይነት ትርጉም አለው? በምናስተምረው ሥነ ጥበብ እና አዘውትሮ በማይነጠለው ውበት ላይ ተጽእኖ ማሳደር የሚችለው እንዴት ነው?



ምንም እንኳ “ቁንጅና እንደ ተመልካቹ ነው” ቢባልም፤ ሲጀመር ቁንጅናን ማየት የቻለውን ዐይን የፈጠረውን መዘንጋት የለብንም (ምሳ. 20፡12)። ደግሞም ራሱን ፍጥረትን እንዳናመልክ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል (የትናንቱ ጥናታችን)። ከፍጥረት ውበት ስለ እግዚአብሔር--ብሎም ይህ አምላክ ስለ ውበት ስላለው ፍቅር መማር እንችላለን። የወደቀችው ዓለማችን ዛሬም ውበቷ መንጸባረቁን ቢቀጥልም፤ ከውድቀት አስቀድሞ የነበራት ማማር ምን ሊመስል እንደሚችል ማን መገመት ይችላል? ይህ ደግሞ በእርግጥም እግዚአብሔር የውበት አምላክ መሆኑን ያስተምረናል።

የሥነ ጥበብ እና ሣይንስ ጥናት ወደ እግዚአብሔር ባህሪ እና ልብ ሊስበን ይችላል-ይገባልም። እኛ የራሱ የእግዚአብሔር ሥነ ጥበባዊ ሥራው ውጤት እና የሣይንስ ክስተት አካል በመሆናችን፤ በተጨማሪ በክርስቶስ ውስጥ ስላለን ማንነት አብልጠን መማር እንችላለን።

“እግዚአብሔር ምድራችንን ባስጌጠባቸው ቀለል ያሉ ውበቶች--ልጆቹ የእርሱን ሥራዎች እንዲያደንቁና እንዲደሰቱባቸው ይፈልጋል። እርሱ ውበት ወዳድ አምላክ ቢሆንም፤ ከውጪያዊ መስህብ በላቀ በባህሪ ውበት ይማረካል። አበቦች እንደተላበሱት የተረጋጋ ግርማ፤ ንጽህናን እና ያልተወሳሰበ ስብእናን ያለማ ዘንድ ይተባል።”—Ellen G. White, Steps to Christ, p. 85. ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡6። ውበት ብቻውን የግድ መልካም ወይም ቅዱስ ሊሆን እንደማይችል አስመልክቶ ይህ ምን ያስተምረናል? ምሳ. 6፡25፣ 31:30።



እግዚአብሔር የሚሠራውን በተቃራኒ እያመሳቀለ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ የሚያውል ጠላት አለን። ለነገሩ ያ ውበት እና የውበት ጽንሰ ሀሳብ በእኛው ላይ በተቃራኒ ቢውል እምብዛም የሚገርም አይሆንም። በመሆኑም በተለይ በሥነ ጥበቡ መስክ፤ ውበት የተላበሰ ሁሉ የግድ መልካም ወይም ቅዱስ አለመሆኑን ማስተዋል እንችል ዘንድ መጽሐፍ ቅዱስ መር ክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት ሊረዳን ይገባል።

ውበት ቢላበሱም ነገር ግን የግድ ቅዱስ ወይም መልካም ያልሆኑ ነገሮች የትኞቹ ናቸው? ወይም እንደ ሁኔታው ቅድስና የጎደላቸው ወይም መጥፎ መሆን የሚችሉ ውብ ነገሮች ምንድን ናቸው? እነዚህን ልዩነቶች ነቅሰን ለማውጣት ምን ዓይነት መስፈርቶች ጥቅም ላይ ማዋል እንችላለን?

ኅዳር 22
Dec 01

የስህተት ባለሙያዎች


ዓለማችን ለእግዚአብሔር ክብር የማይሰጡ አያሌ የጥበብ ሥራዎችና ፍልስፍናዎች እንዳሏት እናውቃለን። ክርስቲያኖች በእንዲህ ያለው ድንኳን ሥር ማደር የለባቸውም ሲሉ አያሌዎች ይሞግታሉ። በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ክርስቲያኖች የንግድ ተቋሞቻቸው ስለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ቆም ብለው ማሰብ ይኖርባቸዋል።

ልናስወግዳቸው የሚገቡ ነገሮችን አስመልክቶ 1ጢሞቴ. 6 መመሪያዎች እና በቂ ማብራሪያዎች ይሰጠናል። ጳውሎስ በቁ. 9 እና 10 ምን ከማሳደድ መቆጠብ እንዳለብን ይነግረናል?



ቀሪውን 1ጢሞቴ. 6 ምዕራፍ ያንብቡ። ጳውሎስ ያቀረባቸው ቁልፍ ነገሮች ምንድን ናቸው?



ጳውሎስ በ1ጢሞቴ. 6፡20 “በውሸት ዕውቀት ከተባለ ፍልስፍና” እንዴት መጠንቀቅ እንዳለብን የተናገረውን ልብ ይሏል። ምንም እንኳ ጽንሰ ሀሳቡን ለየት ካለ ዐውድ ቢያቀርበውም ተቀባይነት ያለው መርኅ ነው። በዘመናችን ብቻ ሳይሆን በረጅሙ ሰብዓዊ ታሪክ ጭልጥ ያሉ ስህተቶች ቢሆኑም፤ ነገር ግን በስፋት ስለተሰራጩ መረጃዎች፣ አስተምህሮዎችና እምነቶች አሰብ ያድርጉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሰዎች የስህተት ባለሙያዎች ሊሆኑ ይችላሉ ቢባል ማጋነን አይሆንም።

በጥልቅ ማሰብ ይችላሉ የሚባሉ ብልህ ሰዎች ለ2ሺ ዓመታት ገደማ ምድር በዩኒቨርስ ፍጹም አማካይ ስፍራ ላይ የማትንቀሳቀስ ሆኖ የተተከለች--ከዋክብትና ፕላኔቶች የሚዞሯት አድርገው ያስቡ ነበር። ምንም እንኳ ይህ መላ ምታቸው በሁሉም ረገድ የተሳሳተ ቢሆንም ነገር ግን እምነታቸውን የሚደግፍ በጣም የተወሳሰበ የሒሳብና ሣይንስ ቀመር ነበራቸው። ስለሆነም እነዚህ ሰዎች የስህተት ባለሙያዎች ናቸው ማለት እንችላለን። አስተምህሮውም በትክክል “በውሸት ዕውቀት የተባለ ፍልስፍና” ነው።

ለምሳሌ ህይወት ያለ ፈጣሪ እና ያለ አንዳች ዓላማ እንደ እንደ አጋጣሚ ከቢሊዮን ዓመታት በፊት መጀመሩን የባዮሎጂካል ሣይንስ ይተነብያል። በተመሳሳይ በዚህ አስተምህሮ ላይ መሰረት ያደረጉ አስገራሚ ብዛት ያላቸው ውስብስብ ሣይንሳዊ የምርምር ጽሑፎች ቀርበዋል። ሰዎች እንዴት የስህት ባለሙያዎች መሆን እንደሚችሉ አስመልክቶ ከዚህ ምን ዓይነት ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን? ይህ ግንዛቤ በአጠቃላይ ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት ላይ፤ በከፊል ደግሞ የሣይንስ አስተምህሮ ላይ ተጽእኖ የሚያደርገው እንዴት ነው?

ኅዳር 23
Dec 02

ሞኝነት እና አስተዋይነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. ምዕ. 1። ስለ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት ምን ያስተምረናል?



መጽሐፍ ቅዱስ በሞኝነት እና አስተዋይነት መሃል ሚዛናዊ ንጽጽር ያቀርባል። መጽሐፈ ምሳሌ--ሞኝነት ስለ ሞላው ባህሪ እና ከሞኞች ጋር ማኅበርተኛ መሆን የሚያስከትለውን አደጋ ጥሩ አድርጎ በማስቀመጥ ጠቃሚ ምክረ ሃሳብ ይለግሳል። ልዩነቱ ግልጽ ነው፡ ሕዝቦቹ ማስተዋልን (ጥበብን) ገንዘባቸው ለማድረግ እንዲጥሩና እንዲትረፈረፍላቸው የእግዚአብሔር ምኞት ነው።

የሥነ ጥበብ እና ሣይንስ ተማሪዎች ዕውቀት ለመገብየት ብሎም በጥናታቸው የላቀ ውጤት ለማግኘት ችሎታቸውን ይጠቀማሉ። የእነዚህ ደቀ መዛሙርት መምህራንም እንዲሁ በተመሳሳይ ያደርጋሉ። ዕውቀት እና ችሎታ በመጠቀም የድንቅ ጥበብ እና ሣይንሳዊ ግኝት ባለቤት መሆን ይቻላል።

ሆኖም ከክርስቲያናዊው ዕይታ አኳያ--ትክክል በሆነው እና በተሳሳተው፣ በመልካም እና በክፉው፣ በእውነት እና በሐሰት መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅን ማካተት ካልቻለ--የሥነ ጥበብ እና ሣይንስ ዕውቀት ምኑን ዕውቀት ሆነው? ለምሳሌ አንድ ሰው--ታላላቅ የዓለም የኪነ ጥበብ ሰዎች ሕይወት ዙሪያ የተጻፉ ጽሑፎችን በጥቂቱ ቢፈትሽ፤ እነዚህ ሰዎች መጥቀው እንዲወጡ ያደረጋቸው አስደናቂ ችሎታ እና ስጦታ ከግብረገባዊ ወይም ትክክለኛው የህይወታቸው ዐውድ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ሆኖ አያገኘውም። የባዮሎጂካል ወይም ኬሚካል ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪያዎችን በመፈልሰፍ ተሳታፊ የሆኑ አንቱ የተባሉ የዓለማችን ሳይንቲስቶች ከፍተኛ ትምህርት ያላቸው እና የብርቱ ተሰጥኦ ባለቤት ቢሆኑም ነገር ግን የሥራቸው ፍሬ ምንድን ነው? ቀደም ሲል እንደ ተወሳው ዕውቀት ብቻውን፣ ማለትም በራሱ መልካምነት ይጎድለዋል።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ምሳ. 1፡7። የእውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት ቁልፉ ምንድነው ይለናል?



ስለ ዩኒቨርስ እና ከበስተኋላው ስላሉት አካላዊ ኃይላት ጥናት የሚያካሂዱ የዝግመተ ለውጥ ሣይንስ አራማጅ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የሆኑ አንድ ሰው እንዲህ ጽፈዋል፡ “ዩኒቨርስን በተሻለ ለማስተዋል የማያስቸግር በመሰለ ቁጥር፤ የዚያኑ ያህል ፍሬ ቢስ እና የማይጨበጥ ይሆናል።” ዕውቀት በራሱ ብቻውን--ትርጉም የለሽ ብቻ ሳይሆን ከዚያም በከፋ ወደ መጠነ ሰፊ ስህተት ሊመራ እንደሚችል አስመልክቶ ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?

ኅዳር 24
Dec 03

ጌታ ለኢዮብ መለሰለት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢዮ. 38። እግዚአብሔር ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መላውን ህይወት ደግፎ የያዘ አምላክ መሆኑን አስመልክቶ ከጥቅሶቹ ምን እንማራለን? ይህ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነ እውነት በሥነ-ጥበባት እና ሣይንስ አረዳዳችን ላይ ተጽእኖ ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?



“ብዙዎች ቁስ አካል ውስጥ በእጅጉ አስፈላጊ ኃይል አለ ብለው ያስተምራሉ። ቁስ አካላዊ ተፈጥሮ ያላቸው አንዳንድ ባህሪያት ውስጥ የሚገኝ እምቅ ኃይል . . . ያለማቋረጥ እንዲሠሩ እንዳደረጋቸው በመናገር--ተፈጥሮ አንዴ ተቀምረው ከተቀመጡ ሕግጋት ጋር ያለ ተቃርኖ እንደምትኖር በማውሳት በምትከውናቸው ተግባራት ውስጥ እግዚአብሔር እራሱ እንኳ ጣልቃ ሊገባ አይችልም ብለው ይናገራሉ። ይህ ሐሰተኛ የሳይንስ ግኝት እንደመሆኑ በእግዚአብሔር ቃል የተደገፈ አይደለም። ተፈጥሮ የፈጣሪዋ አገልጋይ ናት። እግዚአብሔር ሕግጋቱን አይሽርም ወይም ከሕግጋቱ በተቃራኒ አይሠራም።

ይልቁንም ያለማቋረጥ ይሠራባቸዋል። ተፈጥሮ ሕግጋቶቿን ተከትሎ በውስጧ በብርቱ ኃይል የሚሠራ ኃያል ስለመኖሩ ምስክርነቷን ትሰጣለች። በተፈጥሮ ውስጥ የማያቋርጥ የአብና የወልድ ሥራ አለ። ክርስቶስ እንዲህ ይላል ‘አባቴ እስካሁን እየሠራ ነው፤ እኔም ደግሞ እሠራለሁ።’ (ዮሐ. 5፡17)። (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 121-122)

እንደ አለመታደል ሆኖ፤ ቀደም ሲል እንደ ተገለጸው ሣይንስ በአብዛኛው የሚከተለው የዝግመተ ለውጥ እና ቁስ አካላዊ ንድፈ ሃሳብን ነው። ይህ ማለት አንድ ሳይንቲስት የላቀ ውበት ያለውን አንድ የሆነ ነገር በአትኩሮት ተመልክቶና፣ ይህ ውብ ነገር አስገራሚ ውስብስብ ባህሪንም አዳብሎ መያዙን አይቶ ሲያበቃ--ያለ አንዳች የቀደመ አግባብ ወይም እቅድ እንደው እንደ አጋጣሚ ተከሰተ ብሎ ያስባል እንደ ማለት ነው።

እንደ እውነቱ ከሆነ ይህ ሁሌም ሣይንስ የሚለው ነገር ነው። ከቢራቢሮ አንስቶ እስከ ሰው--የምድራዊው ሕይወት እጹብ ድንቅ ውበት ብሎም ውስብስብ ባህሪ ከቢሊዮን ዓመታት አስቀድሞ እንደ ዕድል በተፈጠሩ ኬሚካሎች አማካይነት በተከሰተ ድንገተኛ ኢ-መደበኛ ለውጥ መንስኤ ሕይወት ገቢራዊ መሆኑን ተከትሎ ይኸው እስከ ዛሬ አለ--ይላል።

ልዕለ ተፈጥሮ የሆነ ፈጣሪ አለ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ ሣይንሳዊ በሆነ መንገድ በቤተ ሙከራ መረጋገጥ የማይችልና ሣይንስ የማይፈታው በመሆኑ “ኢ-ሣይንሳዊ” ሲል ይሞግተዋል--ሣይንሱ። ይህ እምነት ነክ ጉዳይ ሣይንስ ራሱ የሚያስተምረው ነገር አይደለም፤(በዓለም ያሉ ውብ ነገሮች ከእነ-ውስብስብ ባሕሪያቸው ወደ ፈጣሪያቸው ቢያመለክቱም፤ ሣይንስ የሚያስተምረው ግን ተቃራኒውን በመሆኑ) ይልቁንም ይህ ድምዳሜ በራሳቸው በሣይንቲስቶቹ የተያዘና እነርሱ የሚገዙበት ፍልስፍናዊ አቋም ነው።

ችግሩ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የፈጠረ አምላክ ብቻ ሳይሆን፤ እያንዳንዱን ደግፎ የያዘ ጭምር መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማሩ ነው። ይህ ማለት ማንኛውም ሣይንስ አካታች እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት፤ ከአጠቃላዩ ሣይንሳዊ አስተምህሮ ፍጹም የተለየ አመለካከት ይዞ መሥራት ይጠበቅበታል። በተለይ ከሥረ መሰረት ጋር በተያያዘ ግጭቶች መከሰታቸው አይቀሬ ሊሆን ይችላል።

ኅዳር 25
Dec 04


ተጨማሪ ሀሳብ


አያሌ ትክክል ነገሮችን አቅፎ የያዘው ሣይንስ፤ ሥረ መሰረት ላይ ሲመጣ የተሳሳተ አመለካከት እንዲያራምድ መንስኤ የሆኑ ሁለት ምክንያቶች ያሉ ሲሆን፡ የመጀመሪያው ስለ ተፈጥሮአዊው ዓለም ጥናት የሚያደርገው ሣይንስ መልሱን ለማግኘት ወደ ተፈጥሮ ብቻ አለማማተሩ ነው። ሁለተኛው፡ የተፈጥሮ ሕግጋት ያለ ተለዋዋጭ ባህሪ ጸንተው መኖር አለባቸው ብሎ ማመኑ ነው። ሆኖም ወደ ሥረ መሰረቱ ስንመጣ እነዚህ ሁለቱም ስህተት ሆነው እናገኛቸዋለን። ለተፈጥሮአዊው ክስተት ተፈጥሮአዊ መንስኤ የሚለውን የመጀመሪያውን ነጥብ እንውሰድ። ይህ አካሄድ ሂዩሪኬን በመባል የሚታወቀውን ከባሕር ላይ የሚነሳ ዐውሎ ነፋስ ከመነሾው ለማግኘት ቢሠራም፤ ነገር ግን “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፡1) ብሎ ለሚጀምረው ሥረ መሰረት ከንቱ ከመሆንም ያለፈ ነው። ልዕለ ተፈጥሮ ስለ ሥረ መሰረት የሚናገረውን የሚክድ ሣይንስ፤ ሙሉ ለሙሉ ልዕለ ተፈጥሮ ስለነበሩት ሥረ መሰረቶች እንዴት ማስተማር ይችላል?

የተፈጥሮ ኢ-ተለዋዋጭነት? ይህ ጽንሰ ሀሳብ ትርጉም የሚሰጥ ቢመስልም፤ ከሮሜ. 5፡12 አኳያ ግን የሚሠራ አይመስልም፡ “ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኃጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል።” ጥቅሱ የተፈጥሮአዊው አካባቢያዊ ሁኔታ እንደ ሥረ መሰረቱ አለመቀጠሉንና በዓይነቱ ዛሬ ሣይንስ ከሚለው ፍጹም የተለየ መሆኑን ያሳያል። ሞት የማያውቀው ዓለም ዛሬ እያጠናነው ካለው ዓለም ፍጹም የተለየ እንደመሆኑ፤ ፈጽሞ ያልነበሩ ነገሮችን አቆራኝቶ መገመት ወደ ስህተት ይመራል።

የሣይንስ ሥረ መሰረት አረዳዱ የተሳሳተ የሆነው ሁለቱን ወሳኝ የፍጥረት ገጽታዎች ስለሚክድ ነው፡ ከበስተ ኋላ ያለውን ልዕለ ኃያል ማንነት እና የፍጥረት ሥረ መሰረት አሁን ካለው ጋር ፍጹም የተለያየ መሆኑን።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በውበት ጥያቄ ዙሪያ ተነጋገሩ። ለመሆኑ ውበት ምንድን ነው? እንዴት እንገልጸዋለን? አንድ ክርስቲያን ክርስቲያን ካልሆነ ሰው በተለየ ውበትን ሊገልጽና ሊያስተውል የሚችለው እንዴት ነው?

2.ክርስቶስ ፈር ቀዳጅ የምርምር ሥራው ካሳ የሚያስገኝለት የሣይንስ ሊቅ ሆኖ ወደ ምድር መምጣት ይችል ነበር። ወደር የማይገኝለት ዝና ያተረፈ የሙዚቃ ቀማሪ ሆኖ መገለጥም ይቻለው ነበር። እርሱ ግን ራሱን ትሁት አድርጎ በዕደ ጥበብ ሙያ ሠለጠነ። የፍጥረት ሥራ አካል ቢሆንም፤ እንደ ማንኛውም ተራ ሰው ሥልጠና ወስዶ በታዛዥነት ሥራውን አከናወነ። በየትኛውም የትምህርት ወይም የሙያ ጉዞ ልናልፍ ብንችልም--ይህ ምን ዓይነት ብርታት ይሰጠናል?

3.ምንም እንኳ እያንዳንዱ ክርስቲያን በየትምርት ቤቱ እንዲያስተምር ባይጠራም፤ ክርስቲያኖች አውቀውም ሆነ ፍጹም ሳያስቡት በቃልም ሆነ በተግባር ሁሌም መምህራን መሆን ይችላሉ። ከዚህ አኳያ እንደ ክርስቶስ ተማሪነታቸው እና የዓለም መምህርነታቸው ክርስቲያኖች ሊያዳብሩ የሚገባ ልምዶች ምንድን ናቸው?