
ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 3:16፣ 1ዮሐ. 5:13፣ 1ጢሞቴ. 1:16፣ 1ቆሮ. 13:12፣ ዘካ. 13:6።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“ ‘ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሔር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል’ ” (1ቆሮ. 2፡9)፡፡
ሰ
ው “ከመቃብር ባሻገር የሚጠብቀው ምን ዓይነት አዘቅት፣ ሞት፣ ኩነኔ እንደሆነ
ሳያውቅ እንዴት ይኖራል?” ሲል ሞትን አጥብቆ ይፈራ የነበረ አንድ ባለ ቅኔ
ጠይቆ ነበር። በግጥሙ አይ.ፒ.ኤች. ወይም የመጪው ዓለም መዘጋጃ ተቋም--ብሎ
የጠራውን ምህጻረ ቃል ፈጥሮ ነበር። ሆኖም ከመቃብር ባሻገር ያለው ሰው ሁናቴ
ሳይታወቅ እንዴት ለመጪው ዓለም መዘጋጀት ይቻላል?
እንደ ዕድል ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰማይ፣ ስለ አዲሲቱ ምድር፣ ለዘላለም
ስለምንማረው ትምህርት እና ስለምንኖረው ህይወት ታላቅ ግንዛቤ ያስጨብጠናል።
ባለፉት ዐሥራ ሁለት ሣምንታት እንደ ተማርነው አይ.ፒ.ኤች. ያለው አሁን፣ በዚህ
ህይወት እንደ መሆኑ--ሥርዓተ ትምህርቶቻችን ሁሉ--የትኛውም የጥናት መስክ
ቢሆን--“ለመጪው ዓለም” ሊያዘጋጀን ይገባል።
መቼም ማንኛውም ትምህርት ቤት ለተማሪዎች ብዛት ያላቸውን መልካም
መረጃዎች፣ ተግባራዊ እና ጠቃሚ ዕውቀቶች ያስተላልፋል ተብሎ ይታመናል። ነገር
ግን ተማሪዎች ጥሩ ዕውቀት ቀስመው ሲያበቁ፤ የዘላለማዊውን ህይወት ዕውቀት
የሚያጡ ከሆነ ከቶ ምን ይጠቀማሉ? በዚህ ሣምንት ለዘላለም ያለማቋረጥ ትምህርት
ስለሚሰጥበት እና እኛም ያለማሰለስ በዕውቀት ስለምንበለጽግበት--የወደፊቱ ድህረ
ምረቃ ትምህርት ቤት አምላካዊው ቃል የሚነግረንን እንመለከታለን። ዛሬ በዚህ
ምድር ፈጽሞ ልንገምት የማንችላቸውን ነገሮች በመጪው ዓለም ትምህርት ቤት
እንማራቸዋለን።
ባሊዝ ፓስካል በመባል የሚታወቅ በ1600ዎቹ የነበረ ፈረንሳዊ ጸሐፊ አብልጦ ስለ
ሰብዓዊው ፍጡር ይብሰለሰል ነበር። ለእርሱ አንድ ነገር ግልጽ ነበር፡ ሰው የቱንም
ያህል ዕድሜ ቢኖር (በዚያን ዘመን የሰው ዕድሜ ያዛሬውን ያህል አለመሆኑን ልብ
ይሏል) እና የቱንም ያህል የተደላደለና መልካም ህይወት ቢኖርም (አሁንም የዚያን
ዘመኑ ፈታኝና አስቸጋሪ ህይወት ከአሁኑ ጋር እንደማይነጻጸር ያስቡ) ገና በለጋነቱ
ወይም ጥቂት ዘግየት ብሎ ይሞታል።
በተጨማሪ ከሞት በኋላ የሚመጣው ነገር ምንም ይሁን ምን--በምድር በሞት
ከተደመደመው አጭር ህይወት ጋር ሊነጻጸር የማይችል የትዬለሌ ዘመን ይሆናል።
ስለዚህ ለጸሐፊው ፓስካል--የሞቱትን ሰዎች የሚጠብቃቸውን መገንዘብ፤ ሰው
ሊደርስበት የሚገባ እጅግ ምክንያታዊና ተገቢ አስተሳሰብ ነው። ሰዎች ከሞቱ በኋላ
ሊነሳ ለሚችለው ጥያቄ ምንም ደንታ ሳይሰጣቸው “ሥራ በማጣታቸው ወይም
ክብሬን የሚነካ ስድብ ተሰድቤ ይሆናል” ብለው ሲጨነቁና ሲቆዝሙ መመልከቱ
በእጀጉ እንደሚያስደንቀው ይናገራል።
ፓስካል የሚያመለክተው ነጥብ ነበረው። መጽሐፍ ቅዱስ ያን ያህል ጊዜ ወስዶ
በየሱስ ያሉ ስላገኙት የደኅንነት ኪዳን እና ወደፊት ስለሚጠብቃቸው የተስፋ ቃል
መናገሩ በዚህ የተነሳ ነው።
በመቀጠል የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ። በመልእክቶቹ ምን ዓይነት ተስፋ
ተሰጥቶአል? ዮሐ. 6:54፣ ዮሐ. 3:16፣ 1ዮሐ. 5:13፣ 1ጢሞቴ. 1:16፣ ዮሐ.
4:14፣ ዮሐ. 6:40፣ ይሁዳ 1፡21፣ ቲቶ. 3፡7።
ዘላለማዊ ህይወት በመስቀሉ ብርሃን ሲታይ ጥልቅ ትርጉም ይሰጣል። የመስቀሉ
ብርሃን አብልጦ ትርጉም የሚሰጠው በዘላለማዊው ህይወት ላይ ነው። “የምንኖረውና
የምንንቀሳቀሰው፣ ያለነውም” (ሐዋ. 17፡28) በእርሱ--ዩኒቨርስን እና “ዓለማት
በፈጠረ” (ዕብ. 1፡2) እንደመሆኑ፤ እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ በዚያ ሥጋ
የሞተው… ለምንድን ነው? መንገድ ላይ ተገጭቶ እንደሚበሰብስ ሙት ለመሆን?
አዲስ ኪዳን ብቸኛው የዘላለማዊ ህይወት ካሳ ዋስትና ከሆነው የዘላለማዊ ህይወት
ተስፋ ጋር ተሳስሮ የሚመጣው ለዚህ ነው። ክፉውን ለማካካስ ሚሊዮንም ሆነ
ቢሊዮን ዓመታት በቂ መልካም ጊዜያቶች ላይዙ ይችላሉ። ሁሉንም ነገሮች ሚዛናዊ
ማድረግ የሚችለው ዘላለማዊነት ብቻ ነው። ምክንያቱም ውሱን ያልሆነው ወሱን
ከሆነው ስለሚልቅ እና ሁሌም በዘላለማዊነት ውስጥ ስለሚኖር ነው።
ፓስካል ትክክል ነበር፡ ምክንያቱም እዚህ ያለው ጊዜአችን ከሚመጣው ጋር
ሲነጻረጸር በጣም የተገደበ ነው። ለሚጠብቀን ዘላለማዊነት አለመዘጋጀት
ምንኛ መጃጃል ነው!
ከሞት በኋላ ለሚሆነው ነገር ፍጹም ደንታ ስለማይሰጠው ሰው ምን
ይላሉ? ግለሰቡ የያዘውን ጤናማ ያልሆነ አቋም መመልከት ይችል
ዘንድ እንዴት ሊረዱት ይችላሉ?
“እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀደመው ሥርዓት ልፎአልና” (ራእ. 21፡4)። ሞት፣ ሐዘን እና ሥቃይ የተወገደበት አዲሱ ተፈጥሮአችን ከዚህ ዓለም ምን ያህል የተለየ ሊሆን እንደሚችል ይህ ምን ይነግረናል?
አንድ ክርስቲያን በየሱስ ክርስቶስ ስለሚገኘው የወንጌል ተስፋ ቃል ከባልጀራው ጋር እየተነጋገረ ነበረ። ግለሰቡ ግን አሉታዊ ምላሽ ሰጠው። “ዘላለማዊ ህይወት--ነው ያልከው?” አለው እየተንቀጠቀጠ። “እንዴት ያለ ዘግናኝ አስተሳሰብ ነው! የምድሩ 70 እና 80 ዓመት ክፋት ከበቂ በላይ ነው። ይህን ሁኔታ ወደ ዘላለማዊነት ለመለጠጥ ማን ሊፈልግ ይችላል? ወደ ፍጹም ገሐነምነት ይለወጣል” የዘላለም ሕይወት ተስፋ አሁን የሚስተዋለውን ምድራዊ ሕይወት እንዳለ ይዞ እንደሚቀጥል አድርጎ ግለሰቡ ከመሳቱ በቀር በእርግጥም የተናገረው ውሃ የሚቋጥር ነው። ደግሞስ ያን ማን ይፈልጋል? ይልቁንም ከላይ የቀረበው ጥቅስ እንደሚለው-የቀድሞው ሥርዓት አልፎአል፤ ሁሉም ነገር አዲስ ይሆናል! የምንጎናጸፈውን አዲስ ማንነት አስመልክቶ የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ይነግሩናል? 2ጴጥ. 3:10–13
ራእ. 21:1–6
በዚህ ሁሉ ውስጥ ለእኛ አስፈላጊ የሆነው ጥያቄ፡ የዚህ አዲስ ፍጥረት
ባለቤት ለመሆን ምን ይጠበቅብናል? እዚያ እንዴት እንደርሳለን? የዚያ
አካል ለመሆናችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? እግዚአብሔር
በየሱስ አማካይነት ቃል የገባልን ሕይወት ተካፋዮች እንዳንሆን መሰናክል
የሆኑብን ነገሮች ካሉ ምንድን ናቸው?
“ሰማይ ትምህርት ቤት--ዩኒቨርስ የጥናት መስክ ሲሆን መምህሩ ደግሞ ወሰን የሌለው
አምላክ ነው። የዚህ ትምህርት ቤት ቅርንጫፍ በኤደን ተቋቁሞ ነበር። የደኅንነት
እቅድ ግቡን እንደ መታ ሁሉ ሥነ ትምህርትም ዳግም በኤደን ገነት ይቀጥላል።”—
Ellen G. White, Education, p. 301.
እንደ ማንኛውም ሰው እርስዎም ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሮት ይችላል--ኃጢአት ለምን
ኖረ? ሥቃይ፣ ህመም፣ ሞት ለምን ተከተሰተ?--የሚል።
ስለ ተፈጥሮአዊው ዓለም እና በወስጡ ስለያዘው ምስጢርም እንዲሁ አያሌ ጥያቄዎች
አሉን። በሣይንሱ መስክ የታየው አስደናቂ ግስጋሴ ዓለምን ብሎም በአጠቃላይ
ዩኒቨርስን በጥልቅ ለመረዳት እንድንችል ቢረዳንም፤ አሁንም ከእኛ አስተሳሰብ በላይ
የሆኑ ብዙ፣ ብዙ ነገሮች አሉ።
በጣም ቀላል ከሆኑት የሕይወት ቅርጾች--ከአናታችን በላይ እስከተሰየመው ሰማይ፣
ከሰብ-አቶሚክ ቅንጣት በአጽናፈ ሰማያት እስከተዘረጉት ከዋክብት እያማተርን፤
እጅግ ከተወሳሰቡና ከአእምሮአችን በላይ ከሆኑ ጥልቅ እውነታዎች ጋር እየተጋፈጥን
ለማጥናት እንጥራለን--በዚህችው በምድር ላይ ባለችን እንደ ጥላ ውልብ ብላ
የምታልፍ ዕድሜ!
በሌላ በኩል፤ እንደ ልባችን ጥናት ለማድረግ የሚያስችለን በዓመታት ያልተገደበ
ዘላለማዊነት ባለቤት ስንሆን፤ መጠነ ሰፊ ምስጢሮችን ማስተዋላችን ጥርጥር
የለውም።
ይህ አሳዛኝ የኃጢአት ምዕራፍ ተደምድሞ ሥቃይና ሞት ካበቃ በኋላ
ስለምንማራቸው ነገሮች ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?
1ቆሮ. 13:12
1ቆሮ. 4:5
አሁን የተሰወሩብንን ነገሮች የምናስተውልበት ክህሎት እንደሚሰጠን የተስፋ
ቃል ተሰጥቶናል። ዛሬ በጣም አስቸጋሪ የሚመስሉንን በድግዝግዝ የምናያቸውን
ነገሮችን አንዴ አይተን ማስተዋል መቻላችን በእጅጉ አስደናቂ ተስፋ ነው። ለዚህ
በጎነቱ እግዚአብሔርን ከማመስገን ሌላ ምን እንላለን?! አሁን ለእኛ ቁልፉ ነገር-እምነታችንን አጥብቀን መያዝ፣ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል መታመን፣ ባገኘነው
የብርሃን መጠን መመላለስ እና እስከ መጨረሻው በጽናት መዝለቅ ነው፡ “ኃይልን
በሚሰጠኝ በእርሱ ሁሉን ማድረግ እችላለሁ” (ፊልጵ. 4፡13)።
በልብዎ ውስጥ የሚመላለሰው ጥያቄ የትኛው ነው? አሁን ለመረዳት
የሚከብዶት ነገሮች ምንድን ናቸው? በሚረዷቸው ነገሮች ላይ
በእግዚአብሔር መታመን መማርዎ--አሁን ለማያስተውሏቸው ነገሮች
እንዴት ሊረዱዎት ይችላሉ?
“ምክንያቱም ቀላልና ጊዜያዊ የሆነው መከራችን ወደር የማይገኝለት ዘላለማዊ ክብር ያስገኝልናል። ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኩረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው” (2ቆሮ. 4፡17-18)። ጥቅሶቹ ምን ተስፋ ይሰጡናል? በየሱስ ቃል ከተገቡልንና ከምንጠብቃቸው ከእነዚህ የማይታዩ ዘላለማዊ ነገሮች መካከል አንዳንዶቹ ምን ሊሆኑ ይችላሉ? ራእ. 21:1-2፣ ራእ. 2:7፣ ራእ. 7:14–17።
ምንም እንኳ በየሱስ የተሰጡን ተስፋዎች እውነትነት ባያጠያይቅም፤ እንድናምንባቸው
መንስኤ የሚሆኑን አያሌ ምክንያቶች አሉን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚጠብቀን ነገር
በጭላንጭል ፍንጭ ይሰጠናል። ህይወት ያለ ኃጢአት አሉታዊ ውጤትና ውድመት
ምን ሊመስል እንደሚችል ስናስብ፤ እጹብ ድንቅ ሊሆን እንደሚችል እርግጠኞች
ለመሆን እንችላለን።
በዚህ ምድር የምንታገለው ህመም፣ ሥቃይና መከራ በሙሉ የኃጢአት ውጤት
ነው። ይህን ለመቀልበስ የመጣው ክርስቶስ ምድርን ኃጢአት ከመግባቱ አስቀድሞ
ወደነበረችበት የቀደመ አምላካዊ እቅድ ይመልሳታል። በዚህ ሁሉ እጹብ ድንቅ ሁኔታ
መሃል ለመዳናችን የተከፈለውን የእጆቹን እና የእግሮቹን ጠባሳ ለዘላለም መንካት
የምንችል መሆናችን፤ መንግሥተ ሰማይን ይበልጥ የተሻለ ስፍራ ያደርገዋል።
“ዐይኖቻችንን ጋርዶ የነበረው ጥቁር መጋረጃ ሲገለጥ አሁን በድንግዝግዝ ለማየት
የምንታትረው የዓለም ውበት ወለል ብሎ ይገለጥልናል። በብዙ ርቀር ተስፈንጥረው
የሚገኙትን ዓለማት ዛሬ በቴሌስኮፕ ለማየት ደፋ ቀና ቢባልም፤ በዚያን ጊዜ ግን
ዐይኖቻችን የሰማያትን ክብር ያያሉ። የኃጢአት መቅሰፍት ተወግዶ መላይቱ ምድር
በጌታችንና አምላካችን ውበት ስታበራ--አዲስ የጥናት መስክ ይከፈትልናል! በዚያ
ስፍራ የሳይንስ ተማሪው የፍጥረትን መዛግብት ሲያገላብጥ የክፉው ሕግ አስተዋሾች
አለመኖራቸውን ይረዳል። የተፈጥሮን ሙዚቃዊ ድምጾች ሊሰማ ቢችልም፤ የዋይታ
ወይም የልቅሶ ሹክሹክታ ቃና ያለውን ድምጸት ግን አያገኝም። በግዙፉ ዩኒቨርስ
ሁሉም የፍጥረት ሥራዎች ላይ የእግዚአብሔር ስም በጉልህ ተጽፎ ይመለከታል።
በምድር፣ በባሕር ወይም በሰማይ አንድ እንኳ የክፉ ምልክት አይኖርም””—Ellen
G. White, Education, p. 303.
በዚህ ምድር ህይወትን አስቸጋሪ ያደረገው ሁሉ ነገር በሌለበት፤ ሙሉ
ለሙሉ አዲስ በሆነው ዓለም ለዘላለም መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል
በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ። ምን ዓይነት ይመስሎታል? በተለይ
በጉጉት የሚጠባበቋቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?
የክርስቶስ የዚህ ምድር አገልግሎት አንድ ማዕከላዊ ገጽታ መምህርነቱ እንደ ነበር
በዚህ ሩብ ዓመት ተመልክተናል። ከአገልግሎቱ ጅማሬ አንስቶ በተለያዩ ድርጊቶችና
መርኀ ግብሮች አማካይነት ስለ ራሱ፣ ስለ አብ፣ ስለ ደኅንነት እንዲሁም ስለሚጠብቀን
ተስፋ እውነቶች ሳያሰልስ ተከታዮቹን አስተምሮአል (ማቴ. 5:2፣ ማር. 4:2፣ ሉቃ.
19:47፣ ዮሐ. 6:59)።
ይህን ለማስተዋል ከወንጌል አንዱን መጽሐፍ ገረፍ ገረፍ አርጎ በማንበብ ብቻ
የየሱስን አስተምህሮዎች ማግኘት ይቻላል። አሁን ጌታ በቃሉ አማካይነት እኛን
ማስተማር ባያቆምም፤ ይህ ሁናቴ በአዲሲቱ ምድርም እንዲሁ ይቀጥላል። ሥነ
ትምህርት ምናባዊ ባልሆነ እና በኃጢአት ባልተገደበ ማንነት ምን ያህል የተለየ ሊሆን
እንደሚችል በዐይነ ህሊናዎ ለመመልከት ይሞክሩ።
“አንድ ሰው፣ ይህ በሰውነትህ ላይ ያለው ቁስል ምንድን ነው? ብሎ
ቢጠይቀው፣ በባልንጀሮቼ ቤት ሳለሁ የቆሰልሁት ነው ይላል” (ዘካ.
13፡6)። ይህ ጥቅስ ስለ ምን የሚናገር ይመስሎታል?
“ዘላለማዊዎቹ ዓመታት በተተረተሩ ቁጥር ስለ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ ይበልጥ
የከበረ ነገር ይገልጣሉ። ዕውቀት ደረጃ በደረጃ በተገለጠ ቁጥር ፍቅር፣ አክብሮት
እና ደስታም የዛኑ ያህል እየጨመረ ይሄዳል። ሰዎች ስለ እግዚአብሔር አብልጠው
በተማሩ መጠን ለባህሪው የሚኖራቸው አድናቆት የዛኑ ያህል እያደገ የሚሄድ
ይሆናል። ከሰይጣን ጋር በተደረገው ታላቁ ተጋድሎ የተገኘውን ደኅንነት ሙላት እና
አስደናቂ ድል የሱስ ወለል አድርጎ በፊታቸው ሲከፍት--የተዋጁት ልቦች አምልኮና
ስግደት ከቀድሞው በጋለ የደስታ ስሜት የተሞላ ይሆናል፤ በላቀ ደስታና ፍስሐ
በወርቅ በገናዎቻቸው ምስጋናና ዝማሬ ያቀርባሉ። አሥር ሺህ ጊዜ አሥር ሺህ
የመዘምራን ድምጾች በአንድነት በብርቱ ያስተጋባሉ…
“ታላቁ ተጋድሎ ተጠናቋል። የኃጢአትም ሆነ ኃጢአተኞች ህልውና አክትሟል።
አጽናፈ ሰማይ በንጽህና ተሞልቷል። መላው ፍጥረት ፍጹም በሆነ ስምምነትና ለዛ
ባለው የሐሴት ድባብ ተሞልቷል። ህይወት፣ ብርሃን እና ደስታ--ሁሉን ከፈጠረውና
ለግዛቱ ወሰን ከሌለው አምላክ ይፈሳል። ኢምንት ከሆነው አቶም እስከ ግዙፉ
ዓለም፣ ሕይወት ያለውም ሆነ የሌለው--ባልተጋረደ ውበት እና ፍጹም በሆነ ደስታ
እግዚአብሔር ፍቅር መሆኑን ያውጃሉ።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 678.
ለዘላለም ከምንማራቸው አስደናቂ እውነቶች መሃል ክርስቶስ ስለ
እኛ መሥዋዕት የመሆኑን ያህል የሚማርከን አንዳች ነገር አይኖርም።
ይህ ለዘላለም የሚኖረን ጥናት ምን ያህል የጠለቀ እና የከበረ ሊሆን
እንደሚችል ያስቡ። አሁንም ቢሆን፣ የሱስ በመስቀል ላይ ያደረገልንን
ነገር በተሻለ ለማድነቅ መማር የሚችሉት እንዴት ነው?
Read Ellen G. White, “The School of the Hereafter,” pp.
301–309 in Education; “The Controversy Ended,” pp. 662–678, in The
Great Controversy.
“በዚህ ምድር አብልጦ የሚያስፈራን አንበሳ ከበግ ጋር ይሰማራል። በአዲሲቱ ምድር
ያለው ማንኛውም ነገር በሰላምና ስምምነት የተሞላ ይሆናል። የአዲሲቱ ምድር ዛፎች
መጉበጥ የማያውቀው፣ ቀጥ ያለ ቅርጽ የተላበሱና ግዙፍ ናቸው።
“በምድራዊ ቤታችን ያለው ውብ ነገር ሁሉ--ታዋቂ አርቲስት በሥዕሉ ሊገልጽ
የማይችለውን ወይም ሟች አንደበት የማያብራራውን እንደ መስታወት የጠራ ወንዝ
እና አረንጓዴ መስኮች፣ የሚወዛወዙ ዛፎች እና ህያው ምንጮች፣ አንጸባራቂዋን
ከተማ እና ነጭ መጎናጸፊያ የለበሱ ዘማሪያን ያሉበትን--ሰማያዊ ቤታችንን
ያስታውሰን። ሰማይ ማንኛውም ብሩህ ህሊና ሊገምት ከሚችለው በላይ መሆኑን
ሳይዘነጉ፤ የዳኑትን መኖሪያ በምናብዎ ለመሳል ይሞክሩ።”—Ellen G. White,
Heaven, pp. 133, 134.
“ክርስቶስ በአባቱ ቤት መኖሪያ ሊያዘጋጅችላቸው እንደሚሄድ ለደቀ መዛሙርቱ
አረጋግጦላቸዋል። የክርስቶስን አስተምህሮ ቃል አምነው የተቀበሉ ሰማያዊውን
መኖሪያ አስመልክቶ ሙሉ ለሙሉ አላዋቂ አይሆኑም… ጻድቃን የሚያገኙትን ሽልማት
ሰብዓዊው ቋንቋ መግለጽ አይቻለውም። በዐይኖቻው ለሚያዩት ብቻ ወለል ብሎ
የሚታይና የተገለጠ ይሆናል። የአምላካዊውን ገነት ክብርና ሞገስ የትኛውም ውሱን
አእምሮ ሊያስተውል አይችልም።”—Ellen G. White, The Great Controversy,
pp. 674, 675.
1.በእሁድ ጥናታችን በፓስካል እሳቤ መሰረት ዘላለማዊው ነገር ይዞት
የሚመጣው ነገር ስለማያሳስባቸው ሰዎች ተወያዩ። ሰዎች እንዲህ
ዓይነት መሰረተ ቢስ አመለካከት የሚኖራቸው ለምንድን ነው?
2.የዘላለማዊ ህይወት ተስፋ ለእምነታችን እጅግ ወሳኝ በሆነበት
ምክንያት ዙሪያ ተወያዩ። ያለ ዘላለማዊ ህይወት ምንም የሌለን ከንቱ
የሆንነው ለምንድን ነው?
3.በተፈጥሮአዊው ዓለም ውስጥ ስለሚገኙት ሁሉም ዓይነት አስደናቂ
ምስጢሮች አሰብ ያድርጉ። በሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ)፣ ሥነ ምድር
(ጂኦሎጂ)፣ ስነ ፈለክ፣ የቁስ አካልና ኃይል ጥናት (ፊዚክስ)፣
ወይም ፍጥረትን ሁሉ ለመለየት የሚታወቅበት ብልሃት (ኬሚስትሪ)-በሁሉም መስኮች ሰዎች መጀመሪያ ካሰቡት ይልቅ ሁሉም ነገር
ይበልጥ ውስብስብ ይሆንባቸዋል። ለምሳሌ ሳይንቲስቶች ስለ “ቀላል
የህይወት አፈጣጠር” መናገር ትተዋል። ምክንያቱም ቀላል የተባለውን
ነገር ጫፍ ለመያዝ ሲሞከር እጅግ ውስብስ ባህሪ ተገልጦ ይወጣል።
እያንዳንዱ አዲስ ስኬት እና ግኝት መልስ ከመሆን ይልቅ አብልጦ
ጥያቄዎችን የሚያጭር ብቻ ይመስላል። ከዚህ በኋላ ባለው ትምህርት
ቤት ምን ያህል እንደምንማር መገንዘብ እንችል ዘንድ እነዚህ ሁሉ
እንዴት ሊረዱን ይችላሉ?
የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ
ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው
ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ
ማሳሰቢያ
የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን
አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡
እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ
ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም
ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን
ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና
ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት
ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም
ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ
ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ
ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡
በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ
የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ
ይበረታታሉ፡፡
ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ
ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ
ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡
በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ
በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡
ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም
ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ
እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡
ድርጅቱ