
ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 3:1–11፣ ሮሜ 5:11–19፣ ዘፍ. 28:10–17፣ ዮሐ. 1:1–14፣ ማቴ. 15:21–28፣ ማር. 10:46–52።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡“ኢየሱስም ‘ሂድ እምነትህ አድኖሃል’ አለው፤ ወዲያውም ዐይኑ በራለት፤ በመንገድም ኢየሱስን ተከትሎት ሄደ” (ማር. 10፡52)።
ከ
እኛ መሃል በራሱ ሐፍረት ተሰምቶት የማያውቅ ማን ነው? ትውስ ሲሉን
የሚዘገንኑን፣ ለማሰብ እንኳ የሚያስጨንቁንን ነገሮች ከእኛ መሃል ያላደረገና-ስለ ጉዳዩ ሌሎች ማወቃቸው ሲታሰብ ደግሞ ያልተሸበርን ስንቶቻችን ነን? ከሞላ
ጎደል ሁላችንም በዚህ ውስጥ አልፈናል ቢባል ማጋነን አይሆንም።
አዳምና ሔዋን ከተከለከለው ፍሬ ከበሉ በኋላ የነበራቸው ስሜት ምን ይመስል እንደ
ነበር በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ፤ ወይም ያዕቆብ አባቱን አታልሎ ለወንድሙ
ይገባ የነበረውን ምርቃት ከወሰደ በኋላ የኤሳውን ቁጣ ፈርቶ የኮበለለበትን ታሪክ
ያገናዝቡ። ለመሆኑ ያዕቆብ እንቅልፍ በዐይኑ ዞሮ ይሆን? ያቺ--እጅ ከፍንጅ
“ስታመነዝር ተያዘች” (ዮሐ. 8፡4) የተባለችውን ሴት ሁኔታም እንዲሁ አሰብ
ያድርጉ። ዳዊት በመዝ. 32 ያሰፈረው ግልጥ ኑዛዜ በእንዲህ ያለው አሳዛኝ ሁናቴ
ውስጥ ማለፍ ምን ሊመስል እንደሚችል ያሳየናል።
ወንጌል ዩኒቨርስ አቀፍ--የክርስቶስ ሞት ደግሞ ለመላው ሰብዓዊ ዘር የሆነበት
አንዱ ምክንያት ይኸው ነው። አንዳችን ከሌላው ጋር ያለን ልዩነት የቱንም ያህል
የሰፋ ወይም የጠበበ ሊሆን ቢችል እንኳ በእርግጠኝነት አንድ ነገር ያስተሳስረናል-ኃጢአተኝነታችን!
ስለዚህ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት ከንቱና ጸለምተኛ ከሆነው ሁናቴ
በተቃራኒ እኛን ወደ ብቸኛው መፍትሔ የሚያመላክት ሊሆን ይገባል።
በዚህ ሣምንት--ብቸኛ መፍትሔአችን በሆነው ታላቁ መምህራችን ዙሪያ
ምልከታ እናደርጋለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡1-11። እግዚአብሔር አዳምን ተጣርቶ “የት ነህ?” ብሎ ለምን ጠየቀው?
የተለመዱ የውድቀት ታሪኮች እነ አዳም የበሉትን ፍሬ አፕል ወይም ፖም ብለው
ያቀርባሉ። ሆኖም ጥቅሱ--በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሚገኝ ዛፍ (ዘፍ. 3፡
3) ከማለት ውጪ እንዲህም፣ እንዲያም አይልም። ቁም ነገሩ የፍሬው ዓይነት
ሳይሆን ዛፉ ከበሰተ ጀርባው የሚወክለው ነገር መኖሩን ተከትሎ ከፍሬው መብላት
መከልከሉን ልብ ይሏል። እግዚአብሔርን ገሸሽ ለማድረግ በመፈተን “ለህይወቴ
ይበጃል ያልኩትን ወሳኝ እርምጃ የምወስደው እኔው ራሴው ነኝ፤ እኔ ለራሴ--የራሴ
አምላክ ነኝ። በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሥልጣን አለኝ” የሚል አንደምታ አለው-ከበስተ ኋላው።
እርግጥ ነው--እባቡ አዳምና ሔዋንን ሲያገኛቸውና ከፍሬው አማልሎ እንዲበሉ
ሲያደርጋቸው ድንገት ህይወታቸው ከቀናው ጎዳና ሸርተት አለ። ከዚያም
እግዚአብሔር አምላክ በአትክልቱ ስፍራ አካባቢ እየተመላለሰ እንደሆነ ሲሰማቸው
“በዛፎቹ መካከል ተሸሸጉ” (ዘፍ. 3፡8)።
እግዚአብሔር--አዳም ያለበትን እያወቀ “የት ነህ?” ብሎ መጠየቁ በእርግጥም እንግዳ
ነገር ቢመስልም፤ ምናልባት ጌታ ይህን ጥያቄ የጠየቀበት ምክንያት፤ አዳምና ሔዋን
የሠሩት ሥራ ባስከተለው መዘዝ እያደረጉ የነበረውን ነገር ማለትም መደበቃቸውን
እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው አስቦ ሊሆን ይችላል። ማለትም ድርጊታቸው ያስከተለውን
አሳዛኝ ውጤት እንዲመለከቱ እየረዳቸው ነበር።
ጳውሎስ በሮሜ 5፡11-19 መልእክቱ አዳም በኤደን የአትክልት ስፍራ ያደረገውን
የሱስ በመስቀል ላይ ካደረገው ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ያቀርባል። የሱስ አዳም
ያደረገውን ነገር ለመሻር መምጣቱን አስመልክቶ ይህ ምን ይነግረናል?
የደኅንነት እቅድ እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን የሰጠው ምላሽ ነው--ብሎ አንድ
ሰው ሽንጡን ይዞ ሊሞግት ይችላል። ኃጢአታቸው ባስከተለው ሐፍረትና ጸጸት
ከእግዚአብሔር ቢሸሸጉም፤ እርሱ ግን ሊያድናቸው መጣ። በተመሳሳይ እኛም
በገዛ መንገዶቻችን በመባዘን ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸማችን እነሆ የሱስ ሊያድነን
መጣ። ስለሆነም “የት ነህ?” የሚለው ጥያቄ በትክክል ለእኛም መሥራት ይችላል።
ኃጢአተኛና በደለኛ መሆንዎን ተከትሎ የሱስ እርስዎን ከወደቁበት አዘቅት ሊያወጣ
መጥቶአል--የት ነዎት?
የምንገኝበት ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ከእግዚአብሔር እንድንሸሸግ በሚያደርግ ሳንካ
የተሞላ ቢሆንም፤ ክርስቲያናዊው ሥነ ትምህርት የቱንም ያህል እንዲያካትት
የሚጠይቀውን ሁሉ አካትቶና አጽንኦት ሰጥቶ--ክርስቶስን በመፍትሄነት ማመላከት
የሚኖርበት ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 28፡10-17። የታሪኩ ዐውደ ሀሳብ ምንድን ነው? በኃጢአታቸው በመኮብለል ላይ ለሚገኙ ስለ ቀረበው አምላካዊ ጸጋ ምን ያስተምረናል?
ያዕቆብ ከተቀረው የቤተሰቡ አባላት ጋር በነበረው ግንኙነት፤ በእናቱ እርዳታ አስከፊ
የማታለል ድርጊት በመፈጸሙ ያልተገባ ሥራው ያስከተለውን መዘዝ መክፈል
ግድ ሆነበት። ወንድሙ እሳት ለብሶ፣ እሳት ጎርሶ ያዘንባቸው የነበሩ ቁጣ የተሞሉ
ማስፈራሪያዎች ለሽሽት ስለ ዳረገው ካራን ወደሚገኘው አጎቱ የሚያደርሰውን
መንገድ ተያያዘው። በወቅቱ ሁሉም ነገር ያልተረጋጋና አስፈሪ ገጽታ የያዘ ነበር።
ረጅሙን መንገድ ሲያዘግም የዋለው ያዕቆብ አመሻሽ ላይ አንድ ስፍራ ደረሰ።
በወቅቱ የነበረው ብቸኛ አማራጭ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ የተዘረጋውን ሰማይ
ጣሪያው አድርጎ አዳሩን በዚያ ጭው ያለ ምድረ በዳ ማሳለፍ ነበር። አልፎ አልፎ
ጣል ጣል ካሉት ድንጋዮች አንዱን ብድግ አድርጎ ተንተራሰና ተኛ። ሆኖም ጭልጥ
ብሎ በወሰደው እንቅልፍ መሃል አንድ ነገር ጣልቃ ገባ--ሕልም። ከህልምም እስከ
ዛሬ ዝና ያተረፈ ሕልም! ጫፉ ሰማይ የሚደርስ መሰላል በምድር ላይ ቆሞ--በላዩ ላይ
የእግዚአብሔር መላእክት ሲወጡና ሲወርዱ ያዕቆብ በሕልሙ አየ።
ከዚያም “የአብርሃም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” የሚል ድምፅ ሰማ። በጉልህ
መሰማቱን የቀጠለው ይኸው ድምፅ ያስተጋባቸው የተስፋ ቃላት ያዕቆብ ከወጣበት
ቤተሰብ ወግና ልማድ አስተምህሮዎች ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። ዘርህ እንደ አሸዋ
ይበዛል። የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ። “እኔ
ከአንተ ጋር ነኝ።” እያለ ድምፁ በመቀጠል “በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ እጠብቅሃለሁ…
የሰጠሁህን ተሰፋ እስክፈጽም ድረስ አልተውህም” አለው (ዘፍ. 28፡15)።
“ሰማይና ምድርን ያገናኘው መሰላል--ፍፁም ያልሆነውን ፍጥረት ፍጹም ከሆነው
አምላክ ጋር ያስተሳሰረውን ክርስቶስን እንደሚወክል አስመልክቶ” ኋላ ላይ ጳውሎስ
አብልጦ መገንዘቡን ኤለን ኋይት ጽፋለች። “የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት አሁን
ረዳቱ፣ አማካሪውና ህይወቱን አሳልፎ እየሰጠው ያለው አምላክ ላይ ምን ያህል እንደ
ተማመኑ ሲያስብ እምነቱ ብርታት አገኘ።”—The Acts of the Apostles, p. 512.
ያዕቆብ ከእንቅልፉ ሲነቃ፡ “‘ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ አለ፤ እኔ ግን ይህን
አላወቅሁም ነበር ’ አለ” (ዘፍ. 28፡16)። እንዴት ያለ በክብር የተሞላ “አስፈሪ” ስፍራ
ነው! ይህን ስፍራ ፈጽሞ ሊረሳው እንደማይችል እርግጠኛ የነበረው ያዕቆብ ስም
አወጣለት። ከዚያም በህይወቱን ዘመን ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆን ኪዳን ገባ።
ኃጢአተኞች ብንሆንም እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ወደ እኛ
ለመድረስ እያሳየ ስላለው ብርቱ መሻት ከዚህ ታሪክ ምን እንማራለን?
ክርስቲያናዊው ሥርዓተ ትምህርት ይህን መርኅ የአስተምህሮው ግንባር
ቀደም ክፍል ማድረግ የሚኖርበት ለምንድን ነው?
በአዲስ ኪዳን ከሚጀምሩ ምዕራፎች ሁሉ ከዚህ ጥቅስ በላይ ዝና ያተረፈ የለም፡
“በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ”
(ዮሐ. 1፡1)። በዚህ ሳያበቃ፤ ዮሐ. ምዕ. 1 ወደ ሌላኛው አይረሴ ጥቅስ ይወስዶታል፡
“ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ፤ እኛም ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ
የመጣውን የአንድያ ልጅን ክብር አየን” (ዮሐ. 1፡14)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡1-14)። የሱስ ማን እንደነበርና ምን ያደርግ
እንደ ነበረ አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል? ከታላቅ መምህርነቱ
ምሳሌ አኳያስ?
አዳምና ሔዋንን በኤደን ገነት፣ ያዕቆብን ደግሞ ጭልጥ ባለ ምድረ በዳ ላይ ያናገረው ያው
አምላክ አሁን ደግሞ ሰብዓዊውን አካል ለብሶ ታየ። እግዚአብሔር እንደሚለው አዲስ
ኪዳን የሱስ በአካል የተገለጠበት መንገድ ነበር። በየሱስ አማካይነት ስለ እግዚአብሔር
ፈቃድና መንገድ መማር እንችላለን። ምክንያቱም የሱስ እግዚአብሔር ነበር።
በኢየሩሳሌም የነበሩ የኃይማኖት መሪዎች ሳይቀሩ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ የተለየ ጥርጣሬ
እንዳደረባቸውና ይህ አጥብቆ ሊደመጥ የሚገባው ሰባኪ በእርግጥም የተለየ ሊሆን
ይችላል ብለው ማሰባቸውን በማውሳት ምዕራፉ ይቀጥላል። ዮሐንስ ግን ከእርሱ
ለላቀው መንገድ እየጠረገ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ “የጫማውን ማሰሪያ ለመፍታት እንኳ
የማልበቃ” (ዮሐ. 1፡27) ብሎ የሚገልጸው አስደናቂና ልዩ የሆነው እርሱ የሚገለትበት
ጊዜ ተቃርቦ ነበር።
በቀጣዩ ቀን የሱስን ተመለከተውና “የእግዚአብሔር ልጅ” መሆኑን በይፋ ዐወጀ። ያን
ዕለት እንዲሁም በማግስቱ “የእግዚአብሔር በግ” ሲል የሱስን ጠራው።
ደግሞም ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት መካከል ሁለቱ የሱስን ለመከተል በራሳቸው
ወሰኑ። ምን ይፈልጉ እንደሆነ የሱስ ሲጠይቃቸው “ረቢ” (መምህር) ብለው ሲጠሩት
እንመለከታለን (ዮሐ. 1፡38)።
የሱስ በዚያን ወቅት ረቢ፣ መምህር የነበረ ሲሆን ነገር ግን እንደ እርሱ ያለ ሰብዓዊ
መምህር ታይቶም፣ ተሰምቶም አይታወቅም። ምክንያቱም እርሱ እግዚአብሔር በመሆኑ
ነው። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር ሰው ሆኖ፣ ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ ወረደና በዚህ
አካሉ እንደ ረቢ፣ መምህር አገልግሎት ሰጠ። ከዚህ አኳያ ኤለን ኋይት “ዓለም አይቶት
የማያውቀው ታላቅ መምህር”—Signs of the Times, June 10, 1886. ብላ ብትጠራው
ብዙ አይገርምም። ምክንያቱም እርሱ እግዚአብሔር ነውና!
የየሱስን ማንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት--መንፈሳዊ እውነቶችን ለማስተማር የተሻሉ
መንገዶችን ከእርሱ መማር ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ለማስተማር--የምንናገረው
ነገር ብቻ ሳይሆን የምናደርገውም አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ ከየሱስ ምን መማር
እንችላለን?
የሱስ ታላቅ መምህር ነው። የእግዚአብሔር እውነተኛ ባህርይ በትምህርቱ እና በምድራዊ
ህይወቱ ተንጸባርቆአል። በወንጌል ላይ ከምናገኛቸው ታሪኮች አንዱ የሱስን ከማናገር
እስካልተገታን ድረስ እንደሚመልስልን ያሳያል።
የሱስ የአይሁድ ትውልድ ካልነበራቸው ሰዎች ጋር ስለ ነበረው ግንኙነት ወይም
በጢሮስና ሲዶና አካባቢ ወደ እርሱ የመጣችውን ከነዓናዊቷን ሴት ታሪክ ያንብቡ (ማቴ.
15:21–28፣ ማር. 7:24–30)። በየሱስ ዙሪያ የነበሩ ሰዎች ምን ያህል እንድትለያቸው
እንደ ፈለጉና የሱስም ቢሆን አንድም ቃል ሳይመልስ ተለይቶአት ሊሄድ እንደ ነበር
ልብ ይሏል። ከሴትየዋ ድፍረት ምን ይገነዘባሉ? የሱስ ራሱ ለሌሎች ስላስተማረው
ትምህርት ይህ ታሪክ ምን ያስተምረናል?
የሱስ በጢሮስና ሲዶና አካባቢ ነበር። ያ ስፍራ ከአይሁድ ትውልድ ያልሆኑ እንግዶች
አብዝተው የሚገኙበት በመሆኑ ጎሳዊ ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶበት ነበር።
የግሪክ ቋንቋ ተናጋሪ ከተሜዎች በገጠራማ ስፍራ ይኖሩ የነበሩትን አይሁድ ገበሬዎች
ይንቁ የነበረ ሲሆን፤ በአጸፋው ባላገር አይሁዶች ግሪኮችን ይጠየፉ ነበር።
የየሱስ መኖሪያ የነበረችው የገሊላ አውራጃ አሻንጉሊት ገዢ የነበረው ሔሮድስ ብዙም
ሳይቆይ መጥምቁ ዮሐንስን አስገደለው። የሱስ የመጥምቁ ዮሐንስን ራእይ ከመጋራቱ
አኳያ ይህ በእርሱ ላይ የተፈጸመ ግድያ ሥጋት ያጫረ ቢመስልም--የሱስ ግን ተልእኮውን
አደጋ ላይ ሊጥል የሚችለውን ኃይል ፊት ለፊት መጋፈጥ ጀመረ።
ሁኔታው የውጥረት ስሜት የፈጠረበት የሱስ ወደ አንድ ቤት እንደ ገባና እዚያ መኖሩን
ማንም እንዲያውቅበት እንዳልፈለ ማርቆስ ይነግረናል (ማር. 7፡24)። ሆኖም የተባለችው
ሴት አገኘችው።
በዚያ ዘመንና ባህል መሰረት አንዲት ሴት ራሷን የመግለጥ መብት አልነበራትም። ከዚያ
በላይ--የቀራቸው ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም ይህች ሴት በአይሁድ ባህል እና ጎሳ ሥርዓት
ስር መተዳደሯ በራሱ ተጨማሪ ማነቆ ነበር።
ሆኖም ሴት ልጇ ታማባት ነበር። ይህች ሴት እርዳታ ትፈልግ ስለነበር መፍትሔ
እንደሚሆናት ያመነችበትን መወትወቷን ቀጠለች።
የሱስ ግን “ ‘የልጆችን እንጀራ ወስዶ ለውሾች መወርወር አይገባም’ ” (ማቴ. 15፡26) ሲል
ገሸሽ አደረጋት። ምናልባት ይህ አስተያየቱ ስሜቷን ጎድቶ ሊሆን ይችላል።
ከዚያ አንድ አስገራሚ ነገር ተከሰተ። ሴቲቱ ለየሱስ ምላሽ ሰጠችው። ውሻን በለማዳ
የቤት እንስሳነት በቤታቸው ከማያኖሩት አይሁዳውያን በተቃራኒ ለእንስሳቱ ባይተዋር
ያልነበረችው ይህች ሴት “ ‘አዎን ጌታ ሆይ፤ ውሾችም እኮ ከጌታቸው ማዕድ የወዳደቀውን
ፍርፋሪ ይበላሉ’ አለችው” (ማቴ. ማቴ. 15፡27)።
ይህ አስገዳጅ እና አሳማኝ አስተያየቷ ለውጥ አመጣ። የሱስ ልጇን ፈወሰላት።
“‘እንደ ፈለግሽው ይሁንልሽ’ ” (ማቴ. 15፡28)። እነዚህን ቃላት
እንዴት እናስተውላቸዋለን? ነገሮች እኛ በተመኘነው ጊዜና ሰዓት ክንውን
ባያገኙም እንኳ ምላሻችን ምን ይሆናል?
የሱስ እና ተከታዮቹ ወደ የሩሳሌም ተመልሰዋል። ቀደም ሲል የመጥምቁ ዮሐንስ ቀጥተኛ
መልእክት ሄሮድስን ያውከው እንደ ነበር ሁሉ፤ አሁን ደግሞ የየሱስ ሁናቴ እርሱንም ሆነ
ባለሟሎቹን አሳስቦአቸዋል። ለውጥ እንዲመጣ አጥብቀው ይሹ የነበሩ ድኾች እና ተጎጂ
የሕብረተሰብ ክፍሎች የተከታዮቹ አካል ነበሩ።
ከምንም በላይ የየሱስ ፍላጎት ለዓለም ተስፋ ማምጣት ነበር። ከፍተኛ ሥልጣንና ፈላጭ
ቆራጭ መብት የነበራቸው--ይህን ተልእኮ ድምጥማጡን ለማጥፋት የተቻላቸውን
ጥረት እንደሚያደርጉ እርግጠኛ ነበር። የእርሱ ጉዞ ስኬት ይቀዳጅ ዘንድ ፍላጎታቸው
አልነበረም።
የየሱስ የቅርብ ተማሪዎች የነበሩት ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ከእርሱ ጎን
ለመቆም ጉጉት ቢኖራቸውም፤ በተመሳሳይ ግራ የመጋባት ወይም የመታወር ሁናቴ
ይስተዋልባቸው ነበር። ለምሳሌ በማር. 8፡31-33 ታላቁ መምህር ተማሪዎቹ ይቀበሉት
ዘንድ ጠንካራ የሆነባቸውን ነገር መመልከት እንዲችሉ ሲሞግታቸው ይስተዋላል። ደቀ
መዛሙርቱ በብዙ አቅጣጫ ሲታዩ--እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ነጥቦች ዙሪያ ገና እንደታወሩ
እንደ ነበሩ ይህ በጉልህ ያሳያል (ማር. 8፡37)።
የየሱስን እና ፈውስ ያገኘውን የዐይነ ስውሩን በርጤሜዎስ ታሪክ ያንብቡ (ማር. 10፡
46-52)። የሱስ ያሳየውን ታላቅ ምኅረት ልብ ይበሉ። ሰውየው ለማየት የነበረው ጉጉት
የሱስ ወደ የሩሳሌም በሚያደርገው ጉዞ ተከትሎት ለመሄድ እንዲወስን እንዳደረገው
ልብ ይሏል። ምናልባት ማርቆስ በበርጤሜዎስ እና በሌሎቹ ደቀ መዛሙርት መካከል
ንጽጽር እያደረገ ይመስሎታል? ታሪኩ ከሚፈነጥቀው ብርሃን አኳያ ለታላቁ መምህር
ምላሽ ሰጪ መሆን ለእርስዎ ምን ማለት ነው?
በርጤሜዎስ የተጠቀለለውን ዞማ የህጻን ልጅ ፀጉር እንዲሁም የመከሩን ስንዴ ቀለማት
ለማየት ይፈልግ ነበር። ሆኖም ማየት ከአካላዊው ነገር የላቀውን ያካትታል። በሌላ
አነጋገር ይህ ታሪክ መንፈሳዊውን ነገር በማየት ዙሪያ ያጠነጥናል። ጉዳዩ ታላቁ መምህር
የሚለውን በትክክል ስለ ማግኘትና ስለ መጨበጥ ነው። አካላዊ የዐይን ብርሃን አንድ
ነገር ነው። አስፈላጊም ነው። ደግሞም ይህን የሱስ ያውቃል። ነገር ግን የእያንዳንዱ ሰው
ጥልቅ ምኞት አዲስ እና የተሻለ ህይወት መቀዳጀት መሆኑንም ያስተውላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 5፡12-14። ስለ እውነኛው ሥነ ትምህርት ምን ያስተምሩናል?
Read Ellen G. White, “The Test of Discipleship,” pp. 57–65,
in Steps to Christ.
ለታላቁ መምህር እውነተኛ ምላሽ ስንሰጥ “አምላካዊውን አምሳል ለመላበስ፣ መንፈሱን
እስትንፋሳችን ለማድረግ፣ ፈቃዱን ለማድረግና እርሱን ለማስደሰት እንናፍቃለን።”-(Steps to Christ, p. 58). ከየሱስ ክርስቶስ ጋር ስንሆን ፈቃዱን በማድረጋችን “ደስታ
እናገኛለን”--(Steps to Christ, p. 59)። ለበለጠ ግንዛቤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማቴ. ምዕ.
5-7 ይመልከቱ። ይህ ታላቁ መምህር ተማሪዎቹ እንዲያውቁ ከፈለጋቸው የማጠቃለያ
ሀሳቦች አንዱ የሆነውና ሊመሰርት የመጣው መንግሥት ዋና መንፈስ የሆነው የተራራው
ላይ ስብከቱ ነው።
1.እግዚአብሔር ለአዳም እና ሔዋን እንዲሁም ለያዕቆብ የነገረውን እነሆ የሱስ ደግሞ
ለእኛ ነገረን። ማንነታችንንና ወዴት እያመራን እንደሆነ ከግምት በማስገባት ጥልቅ
ከሆነው የልባችን መናፈቅ ጋር ግንኙነት እየፈጠረ ያስደምመናል (ለበርጤሜዎስ
እንዳደረገው)። ይህን ብርሃን ተጠቅመን ልጆቻችንንም ሆነ ሌሎችን እንዴት
መጽሐፍ ቅዱስ ማስተማር እንዳለብን አሰብ ያድርጉ። መሃከለኛውን መስመር
ከያዘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ እና በአስገዳጁ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን
ነው? በሰዎች ሕይወት ተጨባጭ ልዩነት ማምጣት የሚችለውስ የትኛው ነው?
2.በሕይወት ጉዞዎ አሁን በሚገኙበት ሁኔታ ዙሪያ የሚነሳ ጥያቄ ፍጹም ግላዊ
እንደሆነ ተጠብቆ እንዲኖር ይፈልጋሉ ወይስ ለሚያምኗቸው ማጋራት ጠቃሚ
እንደሆነ ያምናሉ? ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ናት (1ቆሮ. 12፡27) የሚለው
ጽንሰ ሀሳብ ከሌሎች ጋር በሚደረግ መነጋገር እርስዎ አንዳች ነገር እንዲያውቁ
ክርስቶስ የሚፈልግባቸው መንገዶች አንዱ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
3.በሐሙስ ጥናታችን እንደ ተማርነው በርጤሜዎስ ዐይኖቹ በርተውለት ማየት እንደ
ቻለና ከአካላዊ (እና መንፈሳዊ) ዕውርነቱ እንደ ተላቀቀ ወደ የሩሳሌም ይጓዝ የነበረውን
የሱስ ተከትሎት ሄደ። በዚህ ጎዳና ስለ ታላቁ መምህር ጥበብ በየቀኑ ይሰማ ነበር።
አሁን አምላካዊውን አምሳል ለመላበስ፣ መንፈሱን እስትንፋሱ ለማድረግና ፈቃዱን
ለመፈጸም እንደናፈቀ ለመገመት እንችላለን። በተራራው ስብከት እንደተጠቀሰውና
ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ መንገድ በሚለው መጽሐፍ እንደተወሳው አንድ ሰው
አምላካዊውን ፈቃድ በመፈጸም “ደስታ” የሚያገኘው እንዴት ነው?
4.በሐሙስ ጥናት መጨረሻ ክፍል በቀረበው ጥያቄ ዙሪያ ጥቂት ቆይታ ያድርጉ።
በመልካምና በክፉ መካከል ያለውን ልዩነት መለየት መማር የምንችለው እንዴት
ነው? መልካም የሆነውን እና ክፉ የሆነውን እንዴት ተንትነን ማቅረብ እንችላለን?
ምናልባት ይህ ዕውቀት ኖሮን የምናደርገው--ላይ ላዩን ካለው ዕውቀት ይልቅ ይበልጥ
አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?