
ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1:26-27፣ ኢሳ. 11:1–9፣ 2ጢሞቴ. 3:14–17፣ 1ነገሥ. 4:29–34፣ ዮሐ. 14:17፣ 1ቆሮ. 2:1–16።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት፣ በጽድቅ መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” (2ጢሞቴ. 3፡16)፡፡
መ
ጽሐፍ ቅዱስ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረውን የእግዚአብሔርን እና የሕዝቡን
ታሪክ ይነግረናል። በእርግጥ አንዳንዴ ዝብርቅርቁ የወጣ ዓይነት የፍቅር
ታሪክ ሊመስል ይችላል--ቢያንስ ለጊዜው። ወይም ውለው አድረው ልብ እንደ ገዙ
አመጸኛ ልጆች እና አባት ታሪክ ሊታይ ይችላል።
ሌላው ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የምናገኘው፣ ለዚህ ሣምንት ጥናታችን የሚውለው
መሪ ሀሳብ--አስተማሪውና ተማሪዎቹ ብለን ሰይመነዋል። ተማሪዎቹ በተደጋጋሚ
በፈተና ቢወድቁም፤ እርሱ ግን በመጨረሻ ቢያንስ አንዳንዶች እስኪገባቸው
በትዕግሥትና በተደጋጋሚ ትምህርቱን ከመግለጽና ከማብራራት ወደ ኋላ አላለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እኛ ጠንቅቀን ከምናውቃቸው ከገዛ ራሳችን ሰብዓዊ ታሪኮች
የተለየ አይደለም--ከአንድ ጉዳይ በቀር። የእግዚአብሔር እና የሕዝቦቹ ታሪክ
የታለመለትን ግብ የመምታቱና የፍጻሜው መልካምነት የተረጋገጠ ነው። ለሕዝቦቹ
የተቸረው መለኮታዊ ጸጋ የዚህን ውጤት የተረጋገጠ ያደርገዋል። በዚህ ግንኙነት
ዙሪያ ሰብዓዊው ፍጡር የሚኖረው ኃላፊነት አዘውትሮ በስህተት የተስተዋለ ሲሆን፤
እንደውም እንደ ሸክም ለሚያስቡት ስጋት ሆኖ ኖሮአል። ነገር ግን፤ የመጽሐፍ
ቅዱስ ታሪክ እግዚአብሔርን እና የእርሱን ፈቃድ እናውቅ ዘንድ የቀረበልን ግብዣ
ነው። እርግጥ ነው፤ እግዚአብሔርን ማወቅ መማር--ለጸጋው የምንሰጠው ተቀዳሚ
ምላሽ ነው። የእንዲህ ያለው ጸጋ ባለቤት የምንሆነው ጉዳዩን ስንማርና ስናውቅ
እንደመሆኑ፤ የክርስትና ሥርዓተ ትምህርት ይህን ጸጋ የትምህርቱ አስኳል አድርጎ
ካላስተማረን ታዲያ ምኑን ሥርዓተ ትምህርት ሆነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1፡26-27፣ ዘፍ፣ 5፡1፣3። እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን እንዴት እንደ ፈጠረና ከዚያም ከኃጢአት በኋላ ምን እንደ ተከሰተ አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?
“የእግዚአብሔር አምሳል” የተሰኘው ሀረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎችን ልብ
ለዘመናት ሲማርክ ኖሮአል። ለመሆኑ ይህ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች የተፈጠሩበት
አምሳል ምንድን ነው? ለምሳሌ የእርሱ አዲስ ፍጡር ራሱን ይመስል ዘንድ በመስታወት
እያየ ፈጠረው--ማለት ነው? ወይስ ሰው ከሌሎች ሕይወት ያላቸው ፍጡራን ይበልጥ
በተለየ እግዚአብሔርን ይመስላል የሚል ፍቺ አለው? ወይስ በፈጣሪና ፍጡሩ
በሆነው መካከል ያለውን መንፈሳዊና አእምሮአዊ ስምሙነት ለመጥቀስ ነው? ምንም
እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ ጠበብት ከአምላካዊው ቃል ተነስተው ይህ ሀረግ ሊኖረው
ይችላል ብለው የገመቷቸውን አያሌ ትርጓሜዎች ቢሰጡም--ጥቅሱ ግን እንዲህ
ነው ብሎ እቅጩን አይነግረንም። ሆኖም ከኃጢአት በኋላ ይህ አምሳል እየተለወጠ
እንደመጣ መመልከት ግን እንችላለን። ይህን አስመልክታ ኤለን ኋይት በጽሑፏ-የሥርዓተ ትምህርት ግብ የፈጣሪውን አምሳል በፍጡሩ ዳግም ማኖር እንደሆነ
አስፍራለች (Education, pp. 14–16)።
ለመሆኑ ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት እንዲህ ዓይነቱን አስደናቂ
ግብ ማሳካት የሚችለው እንዴት ነው?
በመጀመሪያ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሁሉ እግዚአብሔርም
ከእርሱ ጋር ግንኙነት እንመሰርት ዘንድ እንደሠራን ማስታወስ ይኖርብናል።
ወላጆች አምሳያቸውን ልጆች እንደሚወልዱ፤ እርሱም የቤተሰቡ አካል ልጆቹ
አድርጎ ይቀበለንና ያሳድገን ዘንድ እነሆ በአምሳሉ ሠራን (ዘፍ. 5፡1)። ከእኛ ጋር
ተግባቦት ለመፍጠርም ሆነ ዘላለማዊ ግንኙነት ለመመስረት ይቻለዋል። ስለዚህ
የእግዚአብሔር አምሳል በአብዛኛው “አእምሮአዊ አምሳል” ወደ መሆን ያደላል።
ይህ ደግሞ እነዚህ ሁለቱ ማለትም አንደኛው መለኮታዊ ሌላኛው ደግሞ ሰብዓዊ
ማንነቶች--አእምሮአዊ ግንኙነት እንዲመሰርቱ ያስችላቸዋል። ጉዳዩ በሥነ ትምህርቱ
ዘርፍ በትክክል የሚከሰት ሲሆን ይኸውም መጀመሪያ በቤት ውስጥ ማለትም
በወላጆችና በልጆች፤ ዘግየት ብሎ ደግሞ በትምህርት ቤት፤ መምህራን የማስተማሩን
ኃላፊነት በሚወስዱበት ጊዜ ይሆናል። በተጨባጭ እንደሚስተዋለው እግዚአብሔር
ይህን የሥነ ትምህርት ንድፍ ማውጣቱን በሚገባ መገንዘብ የምንችለው እኛን
ከሌሎች ህይወት ያላቸው ፍጡራን ለይቶ በገዛ አምሳሉ በመፍጠሩ ሲሆን፤ ይህንንም
ያደረገው አምሳሉ (አእምሮው) በእኛ ተንጸባርቆ እርሱ እኛን ማስተማር እንዲችል፣
እኛም ከእርሱ መማር እንችል ዘንድ ነው።
የመዋጀት ታሪክ ከፍጥረት እስከ ሥጋ መልበስ፤ ከሥጋ መልበስ ዳግም አዲስ ፍጥረት
እስከ መሆን ያለው የክርስቲያናዊው ሥነ ትምህርት ታሪክ ነው። እግዚአብሔር
መምህር ሰማይ ደግሞ ዘላለማዊ መማሪያ ክፍል ነው (see Ellen G. White, Education, p. 301)።
ክርስቲያናዊ ሥርዓተ ትምህርት በቤት፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በትምህርት ቤት፣
በዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በህይወት ውስጥ እንዲንሰራፋ ካለን ቁርጠኝነት አኳያ
የዚህ አስተሳሰብ አንደምታዎች ምንድን ናቸው?
መጽሐፍ ቅዱስ የሱስን በብዙ መንገድ ይገልጸዋል። በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል-የእግዚአብሔር ልጅ፣ መሲህ፣ የሰው ልጅ፣ አዳኝ፣ ቤዛ፣ ጌታ፣ የእግዚአብሔር በግ…።
ነገር ግን በይሁዳና በገሊላ ከሦስት ዓመት በላይ በሰጠው የዐደባባይ አገልግሎቱ
ለሚያውቁት መምህር ነበር። “መምህር” ወይም “ረቢ” ብለው ይጠሩት ነበር።
የሁለቱም ቃላት ፍቺ ተመሳሳይ ነው።
ስለዚህ የመምህርነት ሙያ እና የማስተማር ሥራ በተለይ የሱስ የዐደባባይ
አገልግሎቱን እንዲያካሂድ ምቹ ሁናቴ ሳይፈጥርለት እንዳልቀረ ይታመናል። የሆነው
ሆኖ ቤዛ የመሆን አገልግሎቱ ከማስተማር ሥራው ጋር ፍጹም ተዛማጅ ነበር። ከዚህ
በተጨማሪ ያለው ሁሉ አስቀድሞ በነቢያት ተተንብዮአል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 11፡1-9። ስለ የሱስ የማስተማር ሚና ምን
ይገልጣል?
በብሉይ ኪዳን ስለ መሲህ ከተነገሩ አስደናቂ ትንቢቶች አንዱ በኢሳ. 11 የቀረበው
ነው። ከቁ. 1-3 የቀረበው መልእክት ወደፊት የሚመጣውን መሲህ ትምህርት ነክ
ከሆኑ ጽንሰ ሀሳቦች ማለትም ከዕውቀት፣ ምክር፣ ጥበብና ማስተዋል ጋር አቆራኝቶ
ያቀርበዋል። መላው ምዕራፉ “ውሃ ባሕርን እንደሚሸፍን፣ ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን
በማወቅ ትሞላለችና” (ኢሳ. 11፡9) በሚል አስደናቂ ተስፋ ይደመደማል። ምናልባት
ኤለን ኋይት ሥነ ትምህርት በመባል በሚታወቀው መጽሐፏ (see Education, p.
30) የማስተማር ሥራ እና የመቤዠት ሥራ አንድ ናቸው ብላ እንድትጽፍ ያነሣሣት
ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሊሆን ይችላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 3፡1-3። ኒቆዲሞስ የሱስን ረቢ ብሎ ይጠራው ነበር። የሱስ
ያደረጋቸው ምልክቶች፣ ለህይወት ትርጉም ሰጭ ታምራቶቹ እና ወደ ውስጥ የማየት
ክህሎቱ በእርግጥም የእርሱ ልዩ የማስተማር ስጦታዎች ከእግዚአብሔር እንደ
መጡ አስተውሎአል። የሱስ የተሰጠውን የማዕረግ መጠሪያ ተከትሎ ኒቆዲሞስ
የእግዚአብሔርን መንግሥት ያይ ዘንድ (እንዲያስተውልና እንዲገባ) ዳግመኛ
መወለድ እንዳለበት በመንገር በዚያ የቀደመ ጥንታዊ መምህርነቱ ለኒቆዲሞስ ምላሽ
እንደሰጠው እንመለከታለን። ይህ ደግሞ ከየሱስ አኳያም እንኳ ቢሆን ሌሎችን
የማስተማር ሥልጣን ከእግዚአብሔር እንደሚመነጭ ያሳያል።
ማስተማር ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ስጦታ መሆኑ እሙን ነው። በእግዚአብሔር
የተሰጠ፣ በየሱስ ሥራ ላይ የዋለና ከመለኮት የተቸረ ሥልጣን በተሰጣቸው ዘንድ
የታወቀ ነው።
እስከ ምድር ዳርቻ ሁሉም ስለ ጌታ ዕውቀት እንደሚኖረው የተነገረውን
ትንቢት ፍጻሜ ከመመልከታችን አኳያ ምን ዓይነት ሚና ይኖረናል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 3፡14-17። በክርስቲያናዊ ሥነ ትምህርት ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለሚኖረው ሚና ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ክፍል የሆነው ቶራ አያሌ ሕግጋት ማቀፉን
ተከትሎ አንዳንዴ “ሕጉ” በሚል ፍቺ ይታወቃል። ነገር ግን እንደ እውነቱ ከሆነ
ቶራ “ማስተማር” ወይም “ማስታወቅ” የሚል ትርጓሜ ይዞአል። ይህ ማስተዋል
ከእግዚአብሔር መልካም ጸጋዎች አኳያ ለመመላለስ ሕጎችና ደንቦች ብለን
በመጥራት ልንከተላቸው ከሚገቡትና ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ የተቀመጠውን
“ሕግ” ከሚያስቡት በብዙ የተለየ ነው። ሕጉ በመጀመሪያ የተሰጠበት ዓላማ እንደ
ቀደመው ህይወትን በስኬትና በሰላም እንኖር ዘንድ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ኪዳን
ማስተማሪያ ሰነድ ሆኖ እንዲያገለግል ነው።
የሚቀጥሉት የዕብራውያኑ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ክፍሎች የእግዚአብሔር ሕዝቦች
ይህን የመማሪያ ሰነድ ምን ያህል በሚገባ መማር እንዳለባቸው፣ እንደ ተማሩትና
እንደኖሩበት አስመልክቶ የነቢያቱን ዘገባ ይዞአል። ቀሪው የብሉይ ኪዳን ክፍል
(በዕብራውያኑ “ጽሑፎች” ተብሎ የሚጠራው) በስኬታማ እና አነስተኛ ስኬታማ
መምህራንና ተማሪዎች ምሳሌ የተሞላ ነው--የትምህርት ተሞክሮአቸው እንዳለ
ሆኖ። በትምህርታቸው ስኬት ያገኙ ምሳሌዎች ሆነው በእነዚህ መጻሕፍት የቀረቡት፡
አስቴር፣ ሩት፣ ዳንኤል እና ኢዮብ ናቸው። አራቱ የኢዮብ ጓደኞች ደግሞ ውድቀት
ከጎበኛቸው መሃል ይመደባሉ። እርግጥ ነው--ምንም እንኳ መጽሐፈ መዝሙር
የመዝሙር መጽሐፍ ቢሆንም ቢያንስ ሦስት ትምህርታዊ መዝሙሮች አሉት፡ መዝ.
1፣ መዝ. 37 እና መዝ. 73።
በአዲስ ኪዳን የምናገኛቸው የወንጌል መልእክቶች ለትምህርታዊ ዓላማ በታሰቡ
ሰነዶች የታጨቁ ናቸው--በተለይ የየሱስ ምሳሌዎች። አብዛኞቹ የጳውሎስ
ደብዳቤዎች ወንጌልን በብርቱ በማወጅ ይጀምሩና መቋጫቸው ግን ስለ ክርስቲያኖች
የየዕለት ኑሮ ተግባራዊ ትምህርት የሚሰጥ መማሪያ ሰነድ ይሆናል። የራእይ መጽሐፍ
ትምህርት ነክ በሆኑ ሰነዶች የተሞላ ነው። ለአብነት ያህል የወደፊቷን የክርስቶስ ቤተ
ክርስቲያን ሁኔታ የያዘውን የታሸገ ጥቅል መክፈት የሚችለው የእግዚአብሔር በግ፣
ታላቁ መምህር የሱስ ብቻ እንደሆነ በመጽሐፉ ተገልጾአል (ራእ. 5፡1-5)።
አንዳንዶች በሙሴ ዘመን የነበሩት የማስተማሪያ ሰነዶች በሙሉ በእኛ
ዘመን ሊሠሩ አይችሉም ብለው ሲናገሩ ሊደመጡ ይችላሉ። ይህ ደግሞ
ትክክል ነው። ነገሥታትን አስመልክቶ በዘዳ. 17፡14-20 የተሰጠው መመሪያ
ለንጉሥነት የሚመረጥ ሰው ስለሚያልፍባቸው መስፈርቶች ግልጽ
መመሪያዎች አስቀምጧል። እርግጥ ነው ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ምንም
ዓይነት ንጉሥ አንሾምም። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን እነዚህን
ማስተማሪያዎች በሙሉ በተገቢው መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኝነት
የሚኖረን እንዴት ነው?
ዘመናችን--ትምህርት ቤት፣ ጥናት እና ትምህርት ለተሰኙት ቃላት ግልጽ አረዳድ ቢኖረውም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን የተለመዱ አይደሉም። ጠቢብ (ብልህ) የተሰኘ አንድ የተለመደ ቃል አለ። ለአብነት ያህል የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ስለ ጠቢብ ሴት እና ወንድ ይናገራል (2ሳሙ. 14፡2፣ ምሳ. 16፡23)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 4፡29-34። ስለ ጥበብ አስፈላጊነት ምን ያስተምረናል?
ንጉሥ ሰሎሞን ስለ እንስሳትና ዕፀዋት ህይወት ምሳሌዎችን በታላቅ ጥበብ መናገር
የቻለ ብቸኛ ማስተዋል የነበረው፤ የትምህርት ሰው ሆኖ ቀርቦአል (1ነገሥ. 4፡2934)። መጽሐፈ ምሳሌ እና መጽሐፈ መክብብ ለሰሎሞን እንዲሁም በጥንት ዘመን
ለነበሩ ጠቢብ መምህራን የተቸሩ አያሌ በጥበብ የተሞሉ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚዳስሱ
አስተምህሮዎች ይዘዋል (ምሳ. 1:1፣ ምሳ. 25:1፣ ምሳ. 30:1፣ ምሳ. 31:1)።
መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ጥበብ በዛሬው ዘመን ካለን የትምህርት ሁኔታ ጋር
በጣም ይመሳሰላል። አንድ ሰው በተለይ በወጣትነቱ ከወላጆቹ እና ከመምህራኖቹ
ትምህርት መቅሰሙ አንድ ነገር ቢሆንም (መክ. 12፡1)፤ በህይወት ዘመኑ ሁሉ
የሚያከማቸው ነገር ነው። በሁለተኛ ደረጃ ጥበብ በጥቅሉ በሥራ ላይ መዋል የሚችል
ጎን አለው። ለምሳሌ--ለክረምት ቀለብ የሚሆናቸውን ምግብ በበጋ ከሚሰበስቡ
ጉንዳኖች መማር (ምሳ. 6፡6-8)።
ይህም ሆኖ ጥበብ በተግባር ላይ የሚውል ብቻ አይደለም--ንድፈ ሀሳባዊ ጎንም
አለው። ለዚህ መንስኤው፤ በእግዚአብሔር ላይ በሚኖር እምነት ይጀምርና የተወሰኑ
መሰረታዊ መርኅዎችን ስለሚከተል ነው (ምሳ. 1፡7)። ጥበብ ኃላፊነት ተሰምቶን
መኖር እንድንችል እና ለሌሎች ጥቅም ግድ እንዲለን፣ እንዲሁም ከአበሳ እንድንጠበቅ
ይረዳናል። በመጨረሻ--ጥበብ ልክ እንደ ዛሬው ትምህርት ለጥያቄዎቻችን ሁሉ
ምላሽ አይኖረውም። ነገር ግን ገና ያላወቅነውን ለማወቅ ማሰሳችን እንዳለ ሆኖ፤
በምናውቀው ነገር ደስተኞች እንድንሆን ያስችለናል። ይህ ደግሞ እግዚአብሔርን
ለማወቅና በጸጋው ለመታመን ጥሩ ይዞታ ሊሆነን ይችላል። ኤር. 18፡18 ላይ
እንደምናነበው የጥበበኛ መምህር ሚና ከካህኑ እና ከነቢዩ እኩል ቀርቦአል።
እነዚህ ሦስቱም--በሕጉ ውስጥ ባለው ትምህርት፣ በትምህርታዊ ምክረ ሀሳብ
እና ከእግዚአብሔር በሚሰጡ ልዩ መልእክቶች ከእርሱ የሚመጣውን መልእክት
ለሕዝቦቹ ያስተላልፋሉ።
ጥበብን ተምረን ለተተኪዎቻችን ማስተላለፍ የምንችለው እንዴት ነው?
ይህ እንደ ሕዝብ ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ከምናገኛቸው የሥነ ትምህርት አስደናቂ መርኅዎች አንዱ ታላቁ
መምህር የሱስ ተማሪዎቹን ደቀ መዛሙርት ተለይቷአቸው ሊሄድ የተዘጋጀበት
ወቅት ነው። ለሦስት ዓመት ተኩል አብሮአቸው የቆየ ሲሆን፤ ይህ አብሮነቱ ዛሬ
የሁለተኛ ደረጃ ወይም የኮሌጅ ትምህርት ከሚወስደው ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ሊሆን
እንደሚችል መገመት ይቻላል። ከሁለቱ አንደኛውን ያጠናቀቀ፤ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ
ተማሪው ነገሮችን በራሱ ለመምራት ዝግጁ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ነገር ግን ለተከታዮቹ የተሻለውን ያውቅ የነበረው የሱስ በመንፈስ ቅዱስ የማስተማር
አደራ ቀጣይነት ያለውን ትምህርት አበረከተላቸው። ያ ለየሱስ ተከታዮች በቋሚነት
የተሰጠ ትምህርት ሰጭ (በግሪክኛው ጰራቅሊጦስ) አስተማሪ፣ በሌላ ስፍራ መምህር፣
የሚመራ ወይም አጽናኝ ተብሎ ተጠቅሶአል (ዮሐ. 14፡16-17)። የእውነት መንፈስ
በሚል ማንነት ተገልጾአል። መንፈስ ቅዱስ በአስተማሪነት ተለይቶ ባይቀመጥም ነገር
ግን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ በእርግጥም አስተማሪ ነው--በተለይ እውነትን በመፈለግ
እና በማግኘት ረገድ ወሳኝ ሚና አለው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 2፡1-16። ጳውሎስ ከሥነ ትምህርት ዐውድ
የሚናገረው በጣም አስፈላጊ ነገር ምንድን ነው?
በቆሮንቶስ ያለችውን ቤተ ክርስቲያን በማስታወስ የሚጀምረው ጳውሎስ
በቀዳሚነት ወደ እነርሱ በመጣ ጊዜ ከየሱስ ክርስቶስ እና ከተሰቀለው በቀር ሌላ
አንዳችም ነገር እንዳልነገራቸው በመጥቀስ ይጀምራል--ወንጌልን ከማወጅ ውጪ
ሌላ ጥበብ የሌለበት (1ቆሮ. 2፡2)። ነገር ግን ያ የነገሩ መጨረሻ አልነበረም (1ቆሮ.
2፡6) ምክንያቱም እነዚህ አዲስ ክርስቲያኖች አንዴ ከበሰሉ በኋላ ሐዋርያው ዓለም
ከመፈጠሩ አስቀድሞ በእግዚአብሔር ተሰውሮ የነበረውን አምላካዊ ጥበብ ምስጢር
(1ቆሮ. 2፡7) ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር (1ቆሮ. 2፡10) ሊያስተምራቸው ተመልሶ
ይመጣል። መንፈስ ቅዱስ ከሚማረው ልብ ጋር ጥምረት በሚፈጥርበት ጊዜ ሁሉም
በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ምሪት ያጠናሉ።
ጥናቱ ምን ያህል ጥልቀት ይኖረዋል? ትምህርቱ በመንፈስ ለተመሩት ሰዎች ምን
ያህል ግልጽ ይሆናል? ምዕራፉ ከነቢዩ ኢሳይያስ በተወሰደ ጥቅስ ይደመደማል፡
“የእግዚአብሔርን መንፈስ የተረዳ፣ አማካሪውስ ሆኖ ያስተማረው ማነው?” (ኢሳ.
40፡13)። ነቢዩ ለነበረበት ዘመን ተራ ሕዝብ ከተናገረው ድምፀት አኳያ--ያንን
ማንም ማድረግ አይችልም እንደሚል ይጠበቃል። ነገር ግን ጳውሎስ በመደምደሚያ
ላይ የክርስቶስ አእምሮ እንዳለን በመጥቀስ ባሰፈረው ሀሳብ ያንን ግንዛቤ አርሞታል።
ይህም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን አእምሮ እንኳ
ከማንበብ እንደማይገቱና ማንኛውም የመማርና የመረዳት መጠን (1ቆሮ. 2፡10-13)
የጽድቅን መንገድ ለማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ ያሳያል።
ታላቁ የወንጌል ተልዕኮ (ማቴ. 28፡18-20) መላውን ዓለም
በአስደናቂ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ያቀፈ ነበር። ጥቂት ሐዋርያት ወይም የወንጌል
ሠራተኞች (የሁለቱም ቃሎች ትርጉም ተመሳሳይ ነው) ወደ ሁሉም የምድር ክፍል
በማምራት ተማሪዎችን ሰበሰቡ፣ ደቀ መዛሙርቶቻቸው አደረጓቸው፣ በየሱስ ያምኑ
ዘንድ ጥሪ አቀረቡላቸው፣ አጠመቋቸው፣ ከዚያም የሱስ ያዘዛቸውን ነገሮች ሁሉ
ማስተማር ቀጠሉ። አያሌ ባህልና ትውፊት የሚወክሉ እና የተለያዩ ቋንቋዎችን
የሚናገሩ ክርስትናን የተቀበሉ የዓለም ሕዝቦች--ከውሃ ጥምቀት ከወጡ በኋላ ገና
ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርት ሊጀምሩ መሆኑን ልብ ይሏል። እነዚህ ወገኖች
ገና የሚማሩት ነገር ከመኖሩ አኳያ ይህ ብዙም አይደንቅም።
ክርስቲያኖች ዘወትር ተማሪዎች የመሆናቸው መንስኤ የማስተዋል ችግር ኖሮባቸው
ወይም ዕውቀት የማካበት አባዜ ተጸናውቶአቸው ሳይሆን፤ የክርስትና ሕይወት
እና እምነት የእያንዳንዱ የዕለት ከዕለት ኑሮ መሰረት በመሆኑ ነው። በጣም
ብዙ የምንማረው ነገር አለ። ከዚህ የተነሳ የአዲስ ኪዳን ደብዳቤዎች የሱስን
የሚያውጁ እና ክርስቲያኖች በሁሉም ዘርፎች ሊማሩአቸው የሚገቡ ትምህርቶችን
ይዘዋል። ለእወጃው ጥሩ ምሳሌ የሚሆነንን መልእክት በ1ቆሮ. 2፡2 የቀረበ ሲሆን፤
ክርስቲያናዊው ሥነ ትምህርት ደግሞ 1ቆሮ. 4 ላይ ይጀምርና በራ፣ ጠፋ እያለ እስከ
ምዕራፉ ማብቂያ ይዘልቃል። ለመሆኑ ክርስቲያኖች መማር ያለባቸው ነገር ምንድን
ነው?
ሥራ፣ ዕረፍት፣ ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች፣ ቤተ ክርስቲያን እና
አምልኮ፣ ምጣኔ ሐብት፣ በጎ አድራጎት፣ ከባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት መፍጠር፣
የምክር አገልግሎት፣ ቤተሰባዊ ሥርዓቶች፣ የጋብቻ ግንኙነቶች እና የልጆች
አስተዳደግ፣ ምግብ እና አዘገጃጀት፣ አለባበስ፣ እንዲሁም--እርጅና እና ለመጨረሻዎቹ
የእርጅና ዘመናት ዝግጅት ማድረግ ናቸው። ክርስቲያን መሆን ማለት እነዚህን ሁሉ
ጨምሮ ስለ ሌሎች ነገሮችም መማር ነው። እነዚህን ማስተዋል በተፈጥሮ የሚገኝ
አይደለም--በትምህርት እንጂ!
1.በትምህርት የበለጸገ ሥራ ለቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ ምን ያህል
አስፈላጊ ነው?
2.ኤለን ኋይት “ሰማይ ትምህርት ቤት ነው” (Education, p. 301)
ስትል ምን ማለቷ ነው?
3.ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 2፡1-16። እግዚአብሔር
በመንፈሱ አማካይነት እየገለጸልን ስላለው ነገር ጳውሎስ ምን እያለን
እንደሆነ ልብ ብለው ይመልከቱ። ስለዚህ ዓለም ገዢዎች እና ለብዙ
ዓመታት የካበተ ጥበባቸው መጨረሻው ከንቱ መሆኑን አስመልክቶ ስለ
ሰጠው ማረጋገጫ አሰብ ያድርጉ። እርሱ ለዚያን ዘመኑ ያንን ማለት
ከቻለ፤ ዛሬ በዘመናችን ስላለውስ ጥበብ?