የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ኢሳይያስ፡ “ሕዝቤን አጽናኑ”


1ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከየካቲት 6 – 12

8ኛ ትምህርት

Feb 13 - Feb 19




“ሕዝቤን አጽናኑ”



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 40:1-2፣ ኢሳ. 40:3–8፣ ኢሳ. 40:9–11፣ ኢሳ. 40:12–31።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “አንተ ለጽዮን የምሥራች የምትናገር፤ ከፍ ወዳለው ተራራ ውጣ፤ አንተ ለኢየሩሳሌም ብሥራት የምትናገር፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ጩኽ። ከፍ አድርገው፤ አትፍራ፤ ለይሁዳም ከተሞች፣ ‘እነሆ፤ አምላካችሁ!’ በል” (ኢሳ. 40፡9)።

የ ሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጎርጎሮሳውያኑ 1945 ሲያበቃ ጃፓናዊው ወታደር ሾይቺ ዮኪ በጉአም ደሴት ጥቅጥቅ ጫካ ውስጥ ተደብቆ ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ አውሮፕላኖች ሰላም መውረዱን የሚያበስሩ በራሪ ጽሁፎች በትነው ነበር። ዮኪ ግን ማታለያ እንደሆነ አሰበ። ታማኝ የንጉሥ አርበኛ የነበረው ይህ ወታደር ፈጽሞ እጁን ላለመስጠት ምሏል። ከሥልጣኔ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስላልነበረው በጫካው ውስጥ የሚያገኘውን እየለቀመ ከባድ የሚባል ዓይነት ህይወት ለመግፋት ተገደደ። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ከ27 ዓመታት በኋላ ማለትም በ1972፤ ዮኪ ዓሣ እያጠመደ አዳኞች ወደ እርሱ መጡ። ያ የሰላም መልእክት እውነት እንደ ነበር የተረዳው በዚህ ወቅት ነበር። የተቀሩት የእርሱ ወገኖች ላለፉት 27 ዓመታት ሰላምን ሲያጣጥሙ፤ ዮኪ ግን በምግብ እጦት፣ በድህነትና ለህይወት አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ነገሮችን በማጣትና በጭንቀት ኖረ።—Roy Gane, Altar Call (Berrien Springs, Mich.: Diadem, 1999), p. 304, adapted.

እግዚአብሔር የሕዝቡ ጭንቀትና ሥቃይ በእርግጠኝነት ማብቃቱን ከብዙ ምዕተ ዓመታት በፊት በኢሳይያስ አማካይነት አስታውቋል፡ “አጽናኑ፤ ሕዝቤን አጽናኑ፤ ይላል አምላካችሁ። ለኢየሩሳሌም አለዝባችሁ ንገሯት፤ ዐውጁላትም፤ በባርነት ያገለገለችበት ዘመን አብቅቶአል፤ የኃጢአቷም ዋጋ ተከፍሎአል፤ ስለ ኃጢአቷ ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ ሁለት ዕጥፍ ተቀብላለች።” (ኢሳ. 40፡1-2)። የዚህን ፍቺ እንመልከት።

የካቲት 7
Feb 14

ስለ ወደፊት መጽናናት (ኢሳ. 40፡1-2)


በኢሳ. 40፡1-2 እግዚአብሔር ሕዝቡን ያጽናናል። የቅጣት ዘመናቸው በመጨረሻ ፍጻሜ ያገኛል። ለመሆኑ ይህ ቅጣት ምንድን ነው?



ለዚህ ጥያቄ ብዙ መልሶች አሉ። የእግዚአብሔር ቁጣ በትር የሆነ (ኢሳ. 10) በአሦር የሚተዳደር ቅጣት ነበር። ከክርስቶስ ልደት በፊት በ701 እግዚአብሔር የሰናክሬምን ሰራዊት ደምስሶ (ኢሳ. 37) ይሁዳን ከዚህ ኃይል ታድጓል። ሕዝቅያስ ሀብቱን ለመሮዳክ ባልዳን መልእክተኞች በማሳየቱ ምክንያት ቁሳቁሱን እና ሰዉን ከይሁዳ የሚያግዝ በባቢሎን የሚተዳደር ቅጣት ነበር። እንዲሁም ከሌሎች መንግሥታት መሃል በአንዱ ይተዳደር የነበረ ቅጣት መኖሩን ኢሳይያስ በጻፈው መልእክት ቀርቦአል (ኢሳ. 14-23)።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምንም እንኳ “አሦር” እና “አሦራውያን” ከኢሳ. 7፡17-38፡ 6 ባሉት መልእክቶች 43 ጊዜ ቢጠቀሱም፤ በተቀረው የኢሳይያስ መጽሐፍ ይህ መንግሥት ግብፅ እና “አሦራውያን” ስለፈጸሙት የቀደመ ጭቆና በሚገልጸው ኢሳ. 52፡4 አንድ ጊዜ ብቻ ብቅ ይላል። በኢሳይያስ መጽሐፍ የመጨረሻ ክፍል ከባቢሎን ምርኮ ነጻ ስለመውጣት የተጠቀሰ ሲሆን (ኢሳ. 43:14፣ ኢሳ. 47:1፣ ኢሳ. 48:14፣ 20) በ539 ላይ ባቢሎንን ድል አድርጎ በግዞት የነበሩ ይሁዳውያንን ነጻ ያወጣው ፋርሳዊው ቂሮስ ነበር (ኢሳ. 44:28፣ ኢሳ. 45:1፣ ኢሳ. 45:13)።

ኢሳ. 1-39 ከክርስቶስ ልደት በፊት 701 ላይ ይሁዳ ከአሦራውያን ነጻ ስለሆነችባቸው ክስተቶች አጽንኦት ይሰጣል። ነገር ግን በምዕራፍ 40 መጀመሪያ አካባቢ መጽሐፉ አንድ ምዕተ ዓመት ተኩል ወደ ፊት ተስፈንጥሮ በ539 ፍጻሜ ወደ’ሚያገኘው የባቢሎን አገዛዝ እና ከዚያ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ገቢራዊ ወደ’ሚሆነው የአይሁዳውያን መመለስ ያመራል። ከባቢሎን የመመለስ መልእክት ጭብጥ ከቀደመው የኢሳይያስ ዘመን ጋር አንዳች ትስስር አለው? ካለ--ምንድን ነው?

ኢሳ. 39 ከሕዝቅኤል ዘር የሚወጡ ልጆቹ የመጨረሻ ሁኔታን ጨምሮ (ኢሳ. 39፡ 6-7) ስለ ባቢሎናውያን ግዞት በመተንበይ ለተከታዮቹ ምዕራፎች እንደ መሸጋገሪያ ያገለግላል። በተጨማሪ የኢሳ. ምዕ. 13፣ 14 እና 21 ትንቢቶች ስለ ባቢሎን ውድቀት እና ውድቀቱ ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ይዞ ስለሚመጣው ነጻነት ይናገራሉ፡ “እግዚአብሔር ለያዕቆብ ይራራለታል፤ እስራኤልን እንደ ገና ይመርጠዋል፤ በራሳቸውም አገር ያኖራቸዋል… እግዚአብሔር ከሥቃይህ፣ ከመከራህና ከጽኑ ባርነትህ ባሳረፈህ ቀን፣ በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሣለቃለህ” (ኢሳ. 14፡1-4)። እግዚአብሔር የህዝቡ ሥቃይ እንደሚያበቃ የተስፋ ቃል ከሰጠበት ኢሳ. 40: 1-2 ጋር ያለውን ትስስር ልብ ይበሉ።

አሁን ካለው ሥቃይ አኳያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥቃይ ማክተም የሚሰጣቸው የተስፋ ቃላት ለእርስዎ ምን ትርጉም አላቸው? እምነታችን ያለእነዚህ የተስፋ ቃሎች ምን ያህል መልካም መሆን ይችል ነበር? ምንም ይሁን ምን ከእነሱ ጋር መጣበቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

የካቲት 8
Feb 15

አምላካዊ ሕልዎት፣ ቃል እና መንገድ የማቅናት ሥራ (ኢሳ. 40:3–8)


የእግዚአብሔር ሕዝቦች መጽናናት የሚቀበሉት እንዴት ነው? ኢሳ. 40፡1-8



አንድ ስሙ ያልተገለጸ ዐዋጅ ነጋሪ እግዚአብሔር ክብሩን ለመግለጥ እንደሚመጣ ይናገራል (ኢሳ. 40፡3-5)። ሌላ ድምፅ ደግሞ ሰዎች እንደ ቅጠል የሚጠወልጉ ቢሆኑም “የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” ይላል (ኢሳ. 40፡8)። ከግዞት በኋላ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በሲና ተራራ ላይ ተቀብለውት የነበረውን መልሰው አገኙ። ከዚያ በኋላ በአምላካዊው ህልዎት እና ቃል--ቅጣት የተቀበሉበትን ክህደታቸውን እርግፍ አድርገው ተዉ።

እነዚህ እግዚአብሔር ከእስራኤላውያን ጋር የገባው ኪዳን መሰረታዊ አላባዎች፤ በሕዝቡ መሃል በታነጸው አምላካዊ መቅደስ ተጠበብቀው የኖሩ ናቸው (ዘፀ. 25፡8፣16)። ቃሉን በመተላለፋቸው ምክንያት እግዚአብሔር ቤተ መቅደሱን ተወ (ሕዝ. 9-11)። ሆኖም ግን ተመልሶ እየመጣ ነበር። እምነት የሚጣልበት የእርሱ ሕልዎት እና ዘላለማዊ ቃሉ መጽናናት፣ መዳን እና ተስፋ ያመጣል። ለጌታ መምጣት ምን ዓይነት ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል? ኢሳ. 40፡ 3-5።



አባጣ ጎርባጣ መንገድ ላይ እየተንገጫገጩ መሄዱ ለንጉሥ ተገቢ አይደለም። ስለዚህ ከእርሱ በፊት መንገድ የመደልደል ሥራ የሚሠሩ ባለሙያዎች ይቀድማሉ። ለነገሥታት ንጉሥ ግን ከዚህም የላቀ ይጠበቃል! በመቅደስነት ከሕዝቡ ጋር በግዞት ከኖረበት ከወደ ምሥራቅ መምጣቱ፤ (ሕዝ. 11፡16) ወጣ ገባውን መሬት የማስተካከል ከፍ ያለ ሥራ ይጠይቃል። ከየሩሳሌም በስተምሥራቅ የሚገኘው ኮረብታማና ወጣ ገባ የበዛበት አስቸጋሪ መልክአ ምድር ላይ መንገድ ቀዶ ማውጣት፤ በድማሚት እና ቡልዶዘር እንኳን ተስፋ አስቆራጭ ነው። ሆኖም ብቸኛው ሥራውን መሥራት የሚችል “ጎርባጣውን ስፍራ አስተካክላለሁ” (ኢሳ. 42፡16) ሲል የተናገረ እግዚአብሔር አምላክ ነው። በእርግጥ በኪሩብ ሠረገላ (ሕዝ. 1፡9-11) የሚበር እርሱ በምድር ላይ መራመድ አያስፈልገውም።

በመጥምቁ ዮሐንስ ስብከት ፍጻሜ ያገኘውንና ኢሳይያስ ስለ መንፈሳዊው መንገድ የማቅናት ሥራ የተናገረውን ትንቢት አዲስ ኪዳን ትክክል ይተገብራል (ማቴ. 3፡ 3)። የእርሱ መልእክት “ ‘መንግሥተ ሰማይ ቀርባለችና ንስሐ ግቡ’ ” (ማቴ. 3፡2) የሚል ሲሆን፤ ጥምቀቱ ደግሞ “ለኃጢአት ስርየት የንስሓ ጥምቀት” (ማር. 1፡4) ነበር። ስለዚህ መንገድ የማቅናቱ ሥራ የእግዚአብሔርን አጽናኝ ይቅርታ እና ሕልዎት ለመቀበል የሚያስችል ንስሐ እና ከኃጢአት የመመለስ ፈቃደኝነት ነበር።

ኤር. 31፡31-34 አምላካዊውን መንገድ የማቅናት ሥራ መንፈሳዊ ተፈጥሮ ለማስተዋል የሚያስችል ተመሳሳይ መንፈሳዊ መልእክት በግዞት ለነበረችው ይሁዳ ብዙ ጊዜ አውጇል። በዚህ ምንባብ ጌታ ለአዲስ ጅማሮ ፈቃደኞች ለሆኑ የ “አዲስ ኪዳን” የተስፋ ቃል የሰጠ ሲሆን፤ ይኸውም ሕጉን በልባቸው በማኖር አምላካቸው ለመሆን ቃል በመግባት ነው። ይቅር ስላላቸው፤ እርሱንም ሆነ ባህሪውን ያውቃሉ። ጥቅሶቹን በጥንቃቄ ያንብቡ፡ ኢሳ. 40፡6-8። ሰው እንደ ሣር ከመድረቁ አኳያ ከእነዚህ ጥቅሶች ምን ዓይነት ተስፋ ማግኘት ይችላሉ? እምነት ስለምንጥልበት ነገር ምን ሊያስጠነቅቁን ይገባል?

የካቲት 9
Feb 16

የወንጌል አገልግሎት መወለድ (ኢሳ. 40፡9-11)


በኢሳ. 40፡9-11 ምን ዓይነት ክስተት ተገልጾአል?



በኋለኛው የኢሳይያስ መልእክት ተባዕት የንጉሥ ምሥራች አብሳሪ በየሩሳሌም ብቅ ይላል (ኢሳ. 41፡27፣ ኢሳ. 52፡7)። ነገር ግን በዕብራውያን የተገለጠው እውነት እንደሚያሳየው በኢሳ. 40፡9 ከተራራ ላይ “እነሆ አምላካችሁ!” የሚል የምሥራች ብስራት ነጋሪዋ እንስት (1962 ትርጉም) ሆና እናገኛታለን። “እግዚአብሔር ብቸኞችን በቤተሰብ መካከል ያኖራል፤ እስረኞችን ነፃ አውጥቶ ያስፈነድቃል” (መዝ. 68፡6) በማለት ዳዊት እግዚአብሔርን ያወድሰዋል። ምንም እንኳን እዚህ ላይ እነዚህ ቃላት ከግብፅ ባርነት ስለ መውጣት የሚናገሩ ቢሆንም፤ ኢሳይያስ ተመሳሳይ ጽንሰ ሀሳቦችን ተጠቅሞ ሁለተኛውን በከፍተኛ ቁጥር ግልብጥ ብሎ መውጣት ለማወጅ፡ ከባቢሎን ምርኮ መመለስ የተሰኘውን ሀረግ በማመሳከሪያነት ይጠቀማል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ አዲስ ኪዳን--በኢሳ. 40፡3-5 የቀረበውን መልእክት፤ ዘላለማዊው ቃል ሥጋ ሆኖ በህዝቡ መካከል ላደረው (ዮሐ. 1፡14) ክርስቶስ--መንገድ ጠራጊ ለሆነው ለመጥምቁ ዮሐንስ ያውለዋል። ከዮሐንስ ቀደም ብሎም ቢሆን፤ ስለ መምጣቱ መልካም ዜና ሌሎችም ተናግረዋል። ከእነዚህ የመጀመሪያዎቹ መካከል በእርጅና ዘመናቸው፤ ህፃኑ የሱስ በቤተ መቅደስ ለእግዚአብሔር ተባርኮ በሚሰጥበት ሥነ ስርዓት ላይ የነበሩት ስምዖን እና ሐና ይጠቀሳሉ (ሉቃ. 2፡25-38)። ልክ እንደ ኢሳይያስ የንጉሥ ምሥራች ነጋሪዎች ተባዕት እና እንስት ነበሩ። ስምዖን የእስራኤልን መጽናናት (መሲህ) ለማየት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር (ሉቃ. 2፡25-26)።

የኢሳያስ ትንቢት ከሚፈነጥቀው ብርሃን አኳያ፤ ነቢይት ሐና ለመጀመሪያ ጊዜ የጌታን መምጣት ከፍ ካለው ቤተ መቅደስ ለየሩሳሌም ብሥራት ማወጇ በአጋጣሚ የሆነ አልነበረም፡ “በዚያኑ ጊዜ ቀርባ እግዚአብሔርን አመሰገነች፤ የኢየሩሳሌምንም መቤዠት ለሚጠባበቁ ሁሉ ስለ ሕፃኑ ተናገረች” (ሉቃ. 2፡38)። እንደምናውቀው ይህ፡ የሱስ ክርስቶስ ደኅንነት ለማምጣት የተገለጠበት፣ ለዓለም የሚታወጀው መልካም የምሥራች የሆነው የክርስትና ወንጌል ውልደት ነበር። ቆየት ብሎ፤ ምድራዊ የወንጌል ተልዕኮው ሙሉ ክንውን ማግኘቱን ያረጋገጠውን፣ የድል አድራጊ ትንሣኤ የመጀመሪያ ዜና እንድታበስር ክርስቶስ አደራ የሰጠውም እንዲሁ፤ ለሌላዋ እንስት መግደላዊት ማርያም ሆና እናገኛለን (ዮሐ. 20፡17-18)። ሥጋ እንደ ሳር ነው፤ ሥጋ የሆነው ዘላለማዊ ቃል ግን ዘላለማዊ ነው (ኢሳ. 40፡6-8)።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 40፡11። በዚህ ስፍራ የቀረበው መግለጫ ምን ይመስላል? በጌታ እረኛነት ስር በመዋል ዙሪያ በግል የተለማመዱትን በጽሑፍ ለማቅረብ ይሞክሩ። ጌታ ያደረገሎትን ምሪት ደጋግሞ መቁጠርና ማሰላሰል መልካም የሆነው ለምንድን ነው?

የካቲት 10
Feb 17

በምኅረት የተሞላው ፈጣሪ (ኢሳ. 40፡12-31)


ኢሳይያስ 40 የአምላካዊውን ምሕረት እና ኃይል መሪ ሃሳቦች የሚያዳብረው እንዴት ነው?



በዚህ ምዕራፍ የእግዚአብሔር ምኅረት እና ኃይል በአንድነት ተገምደዋል እንደውም ተደባልቀዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕዝቡን ያድን ዘንድ እነዚህ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው። እርሱ በምህረት የተሞላ አምላክ በመሆኑ ሊያድናቸው ይፈልጋል። ኃያል በመሆኑም ሊያድናቸው ይችላል። ምኅረት (ኢሳ. 40፡1-5)፡ መጽናናት፣ ጌታ ሊያድን መምጣቱ። ኃይል (ኢሳ. 40፡3-8)፡ ክብር፣ ዘላለማዊነት ከሰብዓዊ ደካማነት ሲነጻጸር። ምኅረት (ኢሳ. 40፡9-11)፡ የማዳኑ የምሥራች፣ የሕዝቡ እረኛ። ኃይል (ኢሳ. 40፡ 12-26)፡ ተወዳዳሪ የሌለው ፈጣሪ። ምኅረት (ኢሳ. 40፡27-31) ፈጣሪ እንደመሆኑ ለደከመው ኃይል ይሰጣል።

ኢሳይያስ የእግዚአብሔርን ኃይል ከክብሩ እና ከዘላለማዊነቱ ጋር ሲያስተዋውቅ (ኢሳ. 40፡3-8)፤ ለምድርና ምድራዊ የሆኑ ነገሮች ደካማ ገጽታ (ኢሳ. 40፡12-17) በመስጠት ኃይሉንና የላቀ ጥበቡን ይገልጻል። እዚህ ላይ ኢሳይያስ የተጠቀመው ምድርንና በወስጧ ያለውን ያጣቀሰ ተምሳሌታዊ አጠያየቅና ጉልህ የማመሳሰል ዘይቤ፤ እግዚአብሔር ለኢዮብ የሰጠውን መልስ ይጋራል (ኢዮ. 38፡41)። ለኢሳይያስ ተምሳሌታዊ ጥያቄ መልሱ ምድንድን ነው፡ “እንግዲህ እግዚአብሔርን ከማን ጋር ታወዳድሩታላችሁ” (ኢሳ. 40፡18)?



በኢዮብ ከቀረበው በተመሳሳይ በኢሳይያስም፡ ማንም የለም--የሚል መልስ ሳይሰጥ ይቀጥላል። እግዚአብሔር ተወዳዳሪ የለውም። ነገር ግን ኢሳይያስ የጠየቀውን ጥያቄ፤ አያሌ የጥንት ሕዝቦች እግዚአብሔርን በጣኦት ከመሰሉበት ሁኔታ አኳያ ያነሣዋል (ኢሳ. 40፡19፣20)። ለዚህ አስተሳሰብ ኢሳይያስ ምላሽ ይሰጣል። ጣኦትን በእግዚብሔር አምሳል ጥቅም ላይ ለማዋል መሞከር አስቀድሞም ቢሆን ሞኝነት መሆኑን በማውሳት፤ ነገር ግን ሕዝቡ ያነሣውን ነጥብ ለማግኘቱ እርግጠኛ ለመሆን ያህል፤ የእግዚአብሔርን ተወዳዳሪ የለሽ ማንነት ያስረዳና ቅዱስ ፈጣሪ ነው የሚለውን የማይካድ ሙግት ያስከትላል (ኢሳ. 40፡21-26)።

ኢሳ. 27--በኢሳይያስ መልእክት የቀረበውን የሕዝቡን አመለካከት የሚገልጸው እንዴት ነው? ተመሳሳይ አመለካከት በመያዝ እኛም ጥፋተኞች ልንሆን የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?



የእግዚአብሔር መልእክት ዓላማ መልእክቱን የሚሹ ወገኖችን ማጽናናት ነው! እንደ ኢዮብ፤ መከራቸው አምላካዊውን ባህሪ አስመልክቶ ግራ እንዲጋቡና ተስፋ እንዲቆርጡ አድርጓቸዋል። ጥቅሶቹን በጥልቀት ይመልከቱ። ጥቅሶቹ ስለ እግዚአብሔር ምኅረት እና ኃይል ብቻ ሳይሆን እርሱ ፈጣሪ የመሆኑን እውነታ ጭምር ይናገራሉ። ይህን እውነት መረዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሰንበት--በየሣምንቱ ይህን ወሳኝ ነጥብ ለማጠናከር እንዴት ይረዳል?

የካቲት 11
Feb 18

ከጣዖት አምልኮ ጋር የተያያዘው ችግር (ኢሳ. 40፡19-20)


ጣዖት አምልኮ እግዚአብሔርን በሌላ ነገር በመተካት ልዩ የሆነውን ወዳጃዊ ግንኙነት ያጠፋል (ዘፀ. 20፡4-5፣ ኢሳ. 42፡8)። ይህን ተከትሎ ነቢያት ጣዖት አምልኮን ከመንፈሳዊ “ዝሙት” ጋር ያጣምሩታል (ኤር. 3፡6-9)። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 41፡29። ኢሳይያስ የጣዖት አምልኮን የገለጠው እንዴት ነበር? በጥቅሱ ጣዖት አምልኮን የገለጸበትን መንገድ እንዴት ያስተውሉታል? ጣዖቱ ምንም ይሁን ምን--ነገር ግን ይህ የተገለጸበት መንገድ ትክክል የሆነው ለምንድን ነው?



የጥንት ጣዖት አምላኪያን በሥዕል ወይም ምሳሌ አማካይነት ኃያል የሆኑ አማልክትን እንደሚያመልኩ ያምኑ ነበር። ለሌላ አምላክ የሚወከል የጣዖት አምልኮ፡ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ” (ዘፀ. 20፡3) የሚለውን የመጀመሪያውን ትእዛዝ ያፈርሳል። ነገር ግን እንደ ወርቅ ጥጃው (ዘፀ. 32፡4-5) የጣዖት አምልኮው እውነተኛውን አምላክ በመወከል የሚደረግ ከሆነ፤ እግዚአብሔር በምን እንደሚመሰል ማንም ስለማያውቅ (ዘዳ. 4፡15-19) እና የእርሱን ክብርና ታላቅነት ምንም ሊመስለው ስለማይችል ጌታ ይህን ይቃወማል። ስለዚህ ራሱ ጣዖት እንደ ሌላ አማልክት ስለሚሠራ፤ ያን ማምለክ የመጀመሪያውንና ሁለተኛውን ትእዛዝ መጣስ ነው።

የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጣዖት አያስፈልጋቸውም፤ ምክንያቱም የራሱ መቅደስ በሆነው በራሳቸው ውስጥ የእርሱ እውነተኛ ሕልዎታዊ መገኘት አላቸው። ዛሬ እንደ ቤተ ክርስቲያን እየተጋፈጥናቸው ያሉ ጣዖቶች ምን ዓይነት ናቸው? ጣዖት አምልኮ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ስውር ባህሪያት ያሉት ቅርጾች ይዟል? ከሆነ፤ እንዴት?



“የክርስትናን ስም የሚሸከሙ ብዙዎች ከጌታ ሌላ አማልክት እያገለገሉ ይገኛሉ። ፈጣሪያችን የእኛን የላቀ ፍቅርና ቁርጠኝነት እንዲሁም የቀደመውን ታማኝነት ይጠይቃል። ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር የማዳከም ወይም ለእርሱ በምንሰጠው አገልግሎት ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ያለው ማንኛውም ነገር ጣዖት አምልኮ ይሆናል።”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 2, pp. 1011-1012. የጣዖት አምልኮ ከቁሳዊ ነገር ጋር ቁርኝት ያለው መሆኑን ተከትሎ አጓጊ ነገር እንደነበረው ከጥንት ጽሑፎች እንረዳለን። የሚመስላቸውን የአምልኮ ስልት የሚጠቀሙት ጦዖት አምላኪዎች፤ መራባት እና ብልጽግና ሊሰጡን ይችላሉ ብለው ያመኑባቸውን ኃይላት ያከብሩ ነበር።

ጌታ እንደገና ከመምጣቱ በፊት--የመጨረሻውን መንገድ የሚያቀናውን የኤልያስ የእርቅ መልእክት (ሚልክ. 4) ተከትሎ ምርጫው በኢሳይያስ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡ ሰማይና ምድር የፈጠረውን ማምለክ ወይም ለሌላ ነገር መስገድ (ራእ. 13-14) በስተመጨረሻ ሁሉም ከሁለቱ ለአንዱ አምልኮ ማቅረቡ አይቀሬ ይሆናል።

የካቲት 12
Feb 19


ተጨማሪ ጥናት


Read Ellen G. White, “Behold Your God!” in Prophets and Kings, pp. 311–321. “በኢሳይያስ ዘመን ሰዎች ስለ እግዚአብሔር አምላክ ማንነት ሳያስተውሉ በመቅረታቸው መንፈሳዊ አረዳዳቸው በጽልመት የተዋጠ ነበር። ሰዎች ፈጣሪያቸውን የኃጢአት፣ የመከራ እና የሞት ደራሲ አድርገው እንዲመለከቱ ለማድረግ ሰይጣን ከረጅም ጊዜ አንስቶ ይፈልግ ነበር። በዚህ መንገድ ያታለላቸው ሰዎች እግዚአብሔርን ምኅረት የለሽና ከዚህ ባህሪው ውልፊት የማይል አድርገው ያስቡታል። በደለኛውን ለመርዳት የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት እስከ ሌለ ድረስ፤ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ፣ ኃጢአተኛውን ለመውቀስና ለማውገዝ ተግቶ የሚጠባበቅ አድርገው ይስሉታል።

ሰማይ የሚተዳደርበት የፍቅር ሕግ የሰዎችን ደስታ የሚገድብ እና ከዚህ ቀንበር በማምለጥ እፎይታ እንደሚገኝ ተደርጎ በሐሰት አቀናባሪው ተዛብቶ ቀረበላቸው። ትእዛዞቹ ሊጠበቁ የማይችሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሕጉን በመተላለፍ የሚመጡ ቅጣቶች በዘፈቀደ የተጣሉ ናቸው ሲል ለፈፈ።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 311.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. በኢሳ. 40፡12-31 የቀረበውን መልእክት አጠር አድርገው በራስዎ ቃላት ያቅርቡ። የአምላካችንን አስደናቂ ኃይል ይበልጥ የሚያሳዩ ዘመናዊ የሳይንስ ግኝቶችን ያካተቱ የቅርብ ምርምሮችን ተጠቅመው ይፃፉ። መልስዎን ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ።

2. ኢሳይያስ የዘላለማዊውን አምላክ ቃል ከተሰባሪው ሰብዓዊ ህይወት ጋር (ኢሳ. 40፡6-8) በማነጻጸር ያቀረበው መግለጫ የሞት ፍርሃትዎን የሚናገረው እንዴት ነው? ከትሣኤ ተስፋዎ ጋር እንዴት ይዛመዳል? (ኢዮ. 19፡25-27፣ ዳን. 12:2፣ 1ቆሮ. 15:51–57፣ 1ተሰ. 4:13– 18)?

3.አንድ ሰው በኢሳ. 40፡12-31 የቀረበውን መልእክት በመውሰድ እንዴት ከትዕቢትና ዕብሪት መፈወስ ይችላል?

ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር መከራ ለደረሰባቸው ሰዎች በኢሳይያስ በኩል መጽናናት አመጣ። የችግራቸው ጊዜ ስላበቃ እግዚአብሔር ወደ እነሱ እየተመለሰ ነበር። ተስፋ ከመቁረጥና ግራ ከመጋባት ይልቅ፣ በእርሱ በመታመን አምላካዊውን የፈጣሪ ኃይል ለራሳቸው መጠቀም ይችላሉ።