የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 15 - ታህሳስ 15

መደበኛ እትም

Sept 25- Dec 24




አዘጋጆች ጄራልድ እና ቻንታል ክላይንቢል

ዘላለም አስረስ እንደተረጎመው



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ

የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ፡ ኦሪት ዘዳግም

ታሪኩ የሚከተለው ነው፡ ንጉሥ ኢዮስያስ በየሩሳሌም በነገሠበት ወቅት (ከክ.ል.በ. 640 – 609) ምናልባት በቤተ መቅዱስ ይሠራ የነበረ አንድ ሰው የመጽሐፉን ቅጂ አገኘ። መጽሐፉም በንጉሥ ኢዮስያስ ፊት ተነበበ። “ንጉሡም የሕጉን መጽሐፍ ቃል ሲሰማ ልብሱን ቀደደ” (2ነገሥ. 22፡11)። ለምን? ምክንያቱም እርሱና ሕዝቡ በመጽሐፉ ውስጥ የተጻፈውን እየታዘዙ እንዳልነበረ ተገነዘበ! ከዚያም “የቃል ኪዳኑ መጽሐፍ” (2ነገሥ. 23፡2) ተብሎ በተጠራው በዚህ መጽሐፍ መሠረት ኢዮስያስ ታላቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ ማካሄድ ጀመረ። ስለ ተሐድሶው በ2ነገሥ. 23 ማንበብ እንችላለን።

በንጉሡና በሕዝቡ ላይ እንዲህ ያለ ተጽዕኖ ያሳደረው መጽሐፍ ለመሆኑ የትኛው ነበር? አዎ--መጽሐፉ የዚህ ሩብ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ትኩረት የሚያደርግበት ኦሪት ዘዳግም እንደሆነ ይታመናል። ከአምስቱ የሙሴ መጻሕፍት መካከል አምስተኛውና የመጨረሻ የሆነው ዘዳግም፣ የእንግሊዝኛው ስያሜ የመጣው ከላቲን ቃል ማለትም-ዲውትሮኖሚየም ሲሆን “ሁለተኛው ሕግ” የሚል ፍቺ አለው። የዘዳግም መጽሐፍ እንደሚከተለው በአጭሩ ሊገለጽ ይችላል።

የእስራኤል ልጆች ከምድረ ግብጽ ወጥተው ከጌታ ጋር በሲና ቃል ኪዳን ከገቡ በኋላ በቀጥታ ወደ ከነዓን ከመጓዝ ይልቅ ለአርባ ዓመታት በምድረ በዳ ተቅበዘበዙ። አርባዎቹ ዓመታት ተጠናቅቀው በመጨረሻም ዕብራውያኑ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሊሻገሩ ሲቃረቡ፣ ሙሴ ተከታታይ ንግግሮች አድርጎላቸዋል። የእነዚህ ንግግሮች ፍሬ ነገር ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተቃርባችኋል የሚል ነበር። በመጨረሻም! ጌታ ያደረገላችሁን አትርሱ፣ አሁን ከእናንተ የሚጠይቀውን ይኸውም እርሱን በፍጹም ልባችሁ እና በፍጹም ነፍሳችሁ መውደድ እንደሆነና፣ ይህን መውደዳችሁን ደግሞ በኪዳኑ መሠረት ለፈቃዱ ሁሉ በመታዘዝ መግለጥ መሆኑን አትዘንጉ--ይላል።

ሙሴ የቃል ኪዳኑን አስፈላጊነት ለማጉላት ሲል ጌታ ከአባቶቻቸው ጋር የገባው የቃል ኪዳን ግዴታ ሕጋዊ መሠረት የሆኑትን ዐሥርቱን ትእዛዛት ለሕዝቡ በድጋሚ ያቀረበላቸው ሲሆን--ሆኖም በዚህ ወቅት ከነዓን ድንበር ላይ ነበሩ። ስለዚህ እንዲህ ብለን እንጠይቃለን፡ በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ የነበሩት የእስራኤል ልጆች የተጋፈጡት ነገር--እኛ ዛሬ በተስፋይቱ ምድር ድንበር ያለን እየተጋፈጥን ከምንገኘው ጋር ተመሳሳይነት አይኖረው ይሆን? በመሆኑም የዚህ ሩብ ዓመት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን “ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም” የሚል ርዕስ የያዘ ሲሆን፤ ከእግዚአብሔር ቃሎች ለቃል ኪዳኑ ሕዝቦች ልንወስድ በምንችላቸው የወቅታዊ እውነት መልእክቶች ላይ ምልከታ እናደርጋለን።

በዚህ የዘዳግም መጽሐፍ ጥናታችን እግዚአብሔርን መውደድ እና ባልንጀራን መውደድ ምን ማለት እንደሆነ በሚገልጸው ዘላለማዊ ኪዳን፣ ሕግ እና ጸጋ ዙሪያ ምልከታ የምናደርግ ከመሆኑ በተጨማሪ--ከሁሉም በላይ ግን በየሱስ የመስቀል ላይ ሞት እና ትንሣኤ በብርቱ ኃይል የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፍቅር--የዘዳግም መጽሐፍ እንዴት ፍንትው አድርጎ እንደሚያሳይ እንመለከታለን። እንደሚታወቀው ረጅም ዘመን እና ባህላዊ ክፍፍል የዛሬዋን ቤተ ክርስቲያን ከቀደመችው ለያይቷታል። ይሁን እንጂ ከእነሱ ጋር በጋራ የሚያመሳስለን ነገር ከሚለያየን ይልቅ የሚበልጥ ነው ተብሎ ይታመናል። ለምሳሌ የሚከተሉት ቃላት ዛሬ ለእኛም መነገር አይችሉ ይሆን?

“ ‘ገብታችሁ በምትወርሷት ምድር፣ እንድትፈጽሟቸው እግዚአብሔር አምላኬ ባዘዘኝ መሠረት ሥርዐትንና ሕግን አስተምሬአችኋለሁ። በጥንቃቄ ጠብቋቸው፤ ስለ እነዚህ ሥርዐቶች ሁሉ ለሚሰሙና፣ በእውነቱ ይህ ታላቅ ሕዝብ የቱን ያህል ጥበበኛና አስተዋይ ነው ለሚሉ ሕዝቦች ይህ ጥበባችሁንና ማስተዋላችሁን ይገልጣልና” ’ ” (ዘዳ. 4፡5-6)።

እዚህ ላይ በሌሎች ሕዝቦች ፊት “ጥበበኛና አስተዋይ” ያደረጋቸው ሕጎቹ በራሳቸው ሳይሆኑ የሕዝቡ ለሕጎቹ መታዘዝ መሆኑን ልብ ይሏል። በዚህ ዘዳግም መጽሐፍ ውስጥ በእርግጠኝነት ለእኛ ዘመን ገጣሚ የሆነ መልእክት አለ። ክሊፎርድ አር. ጎልድስቴይን የጎልማሶች መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መመሪያ አዘጋጅ እና--Baptizing the Devil: Evolution and the Seduction of Christianity--መጽሐፍ ደራሲ ናቸው።