የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ኢሳ. 14:12–14፣ ኤፌ. 5:5፣ ኢያሱ 7፣ ዮሐንስ 12:1–8፣ የሐዋ. ሥራ 5:1–11፣ 1ኛ ቆሮ. 10:13።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ አላቸው” (ሉቃስ 12:15)።
መ
ጎምጀት የራስ ያልሆነውን ሀብት ወይም ንብረት ለማግኘት የሚደረግ
ገደብ የለሽ ፍላጎት ነው። መጎምጀት እጅግ ትልቅና አሳሳቢ ጉዳይ
ከመሆኑ የተነሣ አትዋሽ፣ አትስረቅ ወይም አትግደል ከሚሉ
ትዕዛዛት ጋር አብሮ ተቀምጦአል፤ እጅግ ጎጂ ከመሆኑ የተነሣ እግዚአብሔር
በታላቁ የግብረገብ ሕግ ሊያስጠነቀቅን መረጠ። “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ፤
የባልንጀራህን ሚስት ሎሌውንም ገረዱንም በሬውንም አህያውንም ከባልንጀራህ
ገንዘብ ሁሉ ማናቸውንም አትመኝ” (ዘጸ. 20:17)።
መመኘት ብዙ ጊዜ አንድን ሰው ከእግዚአብሔር መንግስት ውጪ ከሚያደርጉ
አስከፊ ኃጢአቶች ጋር ተዘርዝሮ እናገኘዋለን። “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን
መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን
የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት
የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም
ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም” (1ኛ
ቆሮ. 6:9፣ 10)።
መመኘት ከመቀማት፣ ከሴሰኝነትና ከዝሙት ጋር ሊመደብ ይችላል? ጥቅሱ
እየነገረን ያለው ይህንን ሲሆን በዚህ ሳምንት መመኘት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ
የሚገልጹ ምሳሌዎችንና መመኘትን ለማሸነፍ ምን ማድረግ እንደምንችል
እንመለከታለን።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለየካቲት 25 ሰንበት ለመዘጋጀት ይጥኑ።
ኃጢአት በእግዚአብሔር ዩኒቨርስ ውስጥ እንዴት እንደተነሣ ብዙ ጊዜ ጥያቄ ይነሳል። ቢያንስ እንዴት እንደተነሣ እንረዳለን። የኃጢአት ዋናው መነሻ መመኘት (መጎምጀት) ነው። ስለዚህ መመኘት የመጀመሪያው ቀዳሚ ኃጢአት ነው ሊባል ይችላል። ኢሳይያስ 14:12–14ን ያንብቡ። በዚያ ቦታ ስለ ሉሲፌር ውድቀት የተሰጡ ፍንጮች ምንድር ናቸው? በዚያ ውድቀት ውስጥ መጎምጀት ወሳኝ ሚና የተጫወተው እንዴት ነበር?
“ከሰማያዊ ሰራዊት በላይ የተከበረ ቢሆንም፣ በተሰጠው ስልጣን ባለመርካት ለፈጣሪ ብቻ የተገባውን ስግደት በድፍረት ተመኘ። ፍጡራን ሁሉ ባላቸው የፍቅር ስሜትና ታማኝነት ውስጥ እግዚአብሔርን ከሁሉም በላይ ለማድረግ ከመሻት ይልቅ የእነርሱን አገልግሎትና ታማኝነት ለራሱ ለማድረግ ጥረት አደረገ። ይህ የመላእክት መስፍን፣ ዘላለማዊው አብ ለልጁ የሰጠውን ክብር በመመኘት የክርስቶስ ብቻ የሆነውን የተለየ መብት ወይም ስልጣን ለመቀማት ተነሳሳ።”— Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 35. ኤፌሶን 5:5 እና ቆላ. 3:5ን ያንብቡ። ጳውሎስ መጎምጀትን ከምን ጋር ነው እኩል አድርጎ የሚያየው? ለምን?
ጳውሎስ መጎምጀትን ከጣዖት አምልኮ ጋር ሁለት ጊዜ እኩል አድርጎ ማየቱ
ምንኛ የሚያስደንቅ ነው። ሰዎች ጣዖት አምልኮን የሚለማመዱት በአምልኮ ጊዜ
ነው። ይህ ማለት ከእግዚአብሔር ውጭ ለሆነ ነገር፣ ከፈጣሪ ይልቅ ለፍጡር
ሕይወታቸውን ቀድሰው መስጠት ማለት ነው (ሮሜ 1፡25)። ስለዚህ መመኘት
ማለት እኛ ሊኖረን የማይገባውን ነገር መፈለግና ከእግዚአብሔር ይልቅ ለዚያ ነገር
ያለን ፍላጎት የልባችን ዋና ትኩረት እስኪሆን ድረስ አጥብቀን መሻት ማለት ነው።
ሉሲፌር እነዚህ የተሳሳቱ ፍላጎቶች ወዴት እንደሚመሩት መጀመሪያ እንዳላወቀ
ምንም ጥርጥር የለውም። የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ሊሆን ይችላል። መጎምጀትን
የሚከለክለው ትዕዛዝ፣ ስለ ሀሳቦቻችን የሚጠቅሰው ብቸኛው ትዕዛዝ፣ ሌሎቹንም
ትዕዛዛት ወደ መጣስ የሚመሩንን ድርጊቶች ከመፈጸም ሊያስቆመን ይችላል።
(2ኛ ሳሙኤል l 11ን ይመልከቱ)።
1ኛ ጢሞ 6:6፣ 7ን ያንብቡ። ጳውሎስ በዚህ ቦታ በጻፈው ነገር ላይ
ትኩረት ማድረግ እኛን ከመጎምጀት ለመከላከል እንዴት ሊረዳን
ይችላል?
ጊዜው አከራካሪ በሆነ መልኩ በእሥራኤል ታሪክ እጅግ ታላቅ ከሚባሉ
ጊዜያቶች ውስጥ አንዱ ነበር። ለ40 ዓመታት በምድረ በዳ ከተቅበዘበዙ በኋላ
በመጨረሻ ወደ ተስፋይቱ ምድር እየገቡ ነበር። የእሥራኤል ልጆች ሞልቶ
የነበረው የዮርዳኖስ ወንዝ ትዕይንታዊ በሆነ ተዓምራት ተከፍሎ በደረቅ
ምድር ተሻግረዋል። ዮርዳኖስ ተከፍሎ በደረቅ ምድር መሻገራቸው እጅግ
አስደናቂ ከመሆኑ የተነሣ የአህዛብ ነገሥታት ልብ ቀልጦ ስለነበር የመዋጋት ወኔ
አልነበራቸውም ነበር (ኢያሱ 5፡1)።
የከነዓንን ህዝብ ድል በማድረግ ሂደት የመጀመሪያው ግድድሮሽ በግንብ አጥር
የተመሸገችው የኢያሪኮ ከተማ ነበረች። የኢያሪኮ ከተማ ኗሪዎችን ለማሸነፍ
ምን ማድረግ እንደሚቻል የሚያውቅ አንድም ሰው አልነበረም--ኢያሱም
ቢሆን አያውቅም ነበር። ኢያሱ ለጸለየው ጸሎት እግዚአብሔር መልስ ሲሰጠው
ከተማዋን እንዴት ማጥፋት እንደሚችሉ ዕቅዱን ሰጣቸው፣ እነርሱም ተከተሉት።
ነገር ግን ነገሮች ከተጠበቀው በተቃራኒ መጥፎ አቅጣጫ ያዙ።
ኢያሱ ምዕራፍ 7ን ያንብቡ። በኢያሪኮ ላይ ከተገኘው ኃይለኛ ድል በኋላ
ምን ሆነ? ከዚህ ታሪክ ለራሳችን መውሰድ ያለብን መልእክት ምንድር
ነው?
አካን ፊት ለፊት ሲያፋጥጡት እነዚያን ዕቃዎች ‹‹ተመኘሁ›› በማለት ያደረገውን
ነገር አመነ። መመኘት ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጡ ‹‹ችምድ›› የሚለው
ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንዳንደ ቦታዎች አዎንታዊ በሆነ መልኩ ጥቅም
ላይ ውሏል። ለምሳሌ በዳንኤል መጽሐፍ 9፡23 ላይ ገብርኤል ለዳንኤል አንተ
‹‹እጅግ የተወደድህ›› ሰው ነህ ብሎ ሲነግረው ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ተመሳሳይ
መነሻ ያለው ቃል ነበር።
በዚህ አጋጣሚ ግን ችምድ የሚለው ቃል መጥፎ ዜና ነበር። ከተማዎቹን
ሲይዙ ምንም ነገር ለራሳቸው መውሰድ እንደሌለባቸው ግልጽ የሆነ መመሪያ
ቢሰጣቸውም አካን አታድርጉ የተባለውን በማድረጉ በመላው ሕዝብ ላይ
ውርደትን አመጣ (ኢያሱ 6፡18፣ 19)። በዓይ ላይ ከገጠማቸው ሽንፈት በኋላ
“ከነዓናውያንም በምድሪቱ የሚኖሩ ሁሉ ሰምተው ይከብቡናል፥ ስማችንንም
ከምድር ያጠፋሉ፤ ለታላቁ ስምህም የምታደርገው ምንድር ነው??” (ኢያሱ 7:9)
በማለት ኢያሱ ፍርሃቱን ገለጸ። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር እነዚህን ታላላቅ
ድሎች በዚያ ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች ኃይሉንና በራሱ ሕዝብ መካከል እየሰራ ያለውን
ሥራ እንዲያውቁ ለመጠቀም ፈለገ። የሚያገኙአቸው ድሎች ዓላማ ያህዌ ኃያል
ለመሆኑ ምስክር እንዲሆኑ ነበር። በዓይ ላይ ከደረሰው ሽንፈት በኋላ የሰው
ሕይወት ከመጥፋቱ ባሻገር ምስክርነቱም ለድርድር ቀርቦ ነበር።
አካን ድርጊቶቹ ትክክል ለመሆናቸው እንዴ በቀላሉ ሰበብ ማቅረብ
ይችል እንደነበር ያስቡ፡- ከሌላው ምርኮ አንጻር የወሰድኩት እዚህ ግባ
የሚባል አይደለም። ማንም አያውቅም፣ ደግሞስ ምን ጉዳት ያስከትላል?
ገንዘቡ ደግሞ ለቤተሰቤ እጅግ ያስፈልጋል። እነዚህን የሚመስሉ አደገኛ
ምክንያቶች ከማቅረብ ራሳችንን ማቀብ የምንችለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉ እጅግ አሳዛኝ ታሪኮች መካከል አንዱ
የይሁዳ ያስቆሮቱ ታሪክ ነው። ይህ ሰው በዓለም ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ አሥራ አንድ
ሰዎች ብቻ ያገኙት ዕድል ነበረው። ያውም ከኢየሱስ ጋር ሁልጊዜ አብሮ የመሆንና
ዘላለማዊ እውነቶችን በቀጥታ ከራሱ ከጌታ የመማር ዕድል ነበር። ይሁዳ የነበረው
ዓይነት ዕድል ያልነበራቸው ብዙ ሰዎች ሲድኑ ይሁዳ ለዘላለም ጥፋት ራሱን
አሳልፎ መስጠቱ እንዴት የሚያሳዝን ነገር ነው!
ምንድር ነው የሆነው? መልሱ ‹‹መመኘት›› በሚል በአንድ ቃል ውስጥ ይገኛል።
ለመጥፋቱ ምክንያቱ የልቡ ምኞት ነው።
ኢያሱ 12:1–8ን ያንብቡ። ማርያም በግብዣው ላይ ያደረገችው እጅግ
ትኩረት የሳባ ነገር ምን ነበር? ለዚህ ድርጊት የይሁዳ ምላሽ ምን ነበር?
ለምን? የኢየሱስ ምላሽስ ምን ነበር?
ኢየሱስ የይሁዳን የመመኘት አስተያየት በጨዋነት መዝለፉ የግብዣውን
አዳራሽ ትቶ እንዲወጣና የኢየሱስ ጠላቶች ተሰብስበው ወደነበሩበት ወደ ሊቀ
ካህኑ ቤተ መንግስት እንዲሄድ አደረገው። ከማርያም ስጦታ እጅግ ለሚያንስ
ገንዘብ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ተስማማ። (ማቴ. 26፡14-16ን ይመልከቱ)።
ይሁዳ ምንድር ነው የሆነው? እጅግ አስደናቂ የሆኑና በቀላሉ የማይገኙ ዕድሎች
እያሉት እንደዚህ ዓይነቱን ክፋት ለምን ይፈጽማል? ኤለን ጂ ኋይት ስለ ይሁዳ
እንዲህ በማለት ትገልጻለች፡- ይሁዳ ‹‹ታላቁን መምህር ይወደው ስለነበር ከእርሱ
ጋር መሆንን ፈለገ። የባህርይና የሕይወት ለውጥ እንደሚያስፈልገው ተሰማው።
ይህን ለውጥ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለማግኘት ተስፋ አደረገ። አዳኙ
ይሁዳን አልገፋውም (አብሮት እንዳይሆን አልከለከለውም)። በአስራ ሁለቱ
መካከል ቦታ ሰጠው። የወንጌላዊን ሥራ እንዲሰራ ሀላፊነት ሰጠው። በሽተኞችን
እንዲፈውስና አጋንንትን እንዲያስወጣ ኃይል ሰጠው። ነገር ግን ይሁዳ ሙሉ
በሙሉ ራሱን ለኢየሱስ አሳልፎ ወደ መስጠት ደረጃ አልመጣም ነበር።”—The
Desire of Ages, p. 716.
በመጨረሻ፣ ሁላችንም ራሳችንን አሳልፈን ከሰጠን፣ በእኛ ውስጥ
በሚሰራው በእግዚአብሔር ኃይል ልናሸንፋቸው የምንችላቸው የባህርይ
ጉድለቶች አሉብን። ነገር ግን ይሁዳ ራሱን ሙሉ በሙሉ ለክርስቶስ አሳልፎ
ስላልሰጠ በክርስቶስ ኃይል ሊያሸንፍ ይችል የነበረው የመጎምጀት ኃጢአት
አሸነፈውና አሳዛኝ ውጤቶችን አስከተለ።
በመካከላችን በአንድም ሆነ በሌላ ነገር ከመጎምጀት ጋር የማይታገል ማን አለ?
እርሱ የተመኘው ገንዘብ ሲሆን የልብ ችግር የሆነው ያ ምኞት ወደ ስርቆት መራው
(ኢያሱ 12፡6)። ይህ ድርጊቱ በመጨረሻ ኢየሱስን አሳልፎ ወደመስጠት መራው።
መጎምጀት በሁላችንም ላይ ሊያመጣ ስለሚችለው አደጋ እንዴት ያለ አስፈሪ
ትምህርት ነው። ትንሽ የሚመስል ነገር፣ ቀላል የሆነ የልብ ፍላጎት፣ ወደ አደጋና
የዘላለም ክስረት ሊያመራ ይችላል።
የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን የሰዎች ስሜት መነሳሳት የታየበት ጊዜ
ነበር። በጴንጤቆስጤ ቀን የወረደውን ታላቁን የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ተከትሎ
ሐዋርያት ወንጌልን በኃይል ይሰብኩ ስለነበር በሺሆች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤተ
ክርስቲያንን እየተቀላቀሉ ነበር።
“ከጸለዩም በኋላ ተሰብስበው የነበሩበት ስፍራ ተናወጠ፥ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ
ሞላባቸው፥ የእግዚአብሔርንም ቃል በግልጥ ተናገሩ። ያመኑትም ሕዝብ አንድ
ልብ አንዲትም ነፍስ ነበሩአቸው፥ ገንዘባቸውም ሁሉ በአንድነት ነበረ እንጂ ካለው
አንድ ነገር ስንኳ የራሱ እንደ ሆነ ማንም አልተናገረም” (የሐዋ. ሥራ 4:31፣ 32)።
ለአናኒያና ሰጲራ የቀደምት ቤተ ክርስቲያን አባል በመሆን የቤተ ክርስቲያኗን
እድገትና አስደናቂ በሆነ ሁኔታ የመንፈስ ቅዱስን መገለጥ ለማየት መታደላቸው
መልካም ዕድል ነበር። “በመካከላቸው አንድ ስንኳ ችግረኛ አልነበረምና፤ መሬት
ወይም ቤት ያላቸው ሁሉ እየሸጡ የተሸጠውን ዋጋ ያመጡ ነበርና፥ በሐዋርያትም
እግር አጠገብ ያኖሩ ነበር፤ ማናቸውም እንደሚፈልግ መጠን ለእያንዳንዱ
ያካፍሉት ነበር” (የሐዋ. ሥራ 4:34፣ 35)።
አናኒያና ሰጲራ እየሆነ ባለው ነገር በመሳባቸውና የዚህ እንቅስቃሴ አካል ለመሆን
በመፈለጋቸው ንብረታቸውን ለመሸጥና ለቤተ ክርስቲያን ለመስጠት የወሰኑት
በዚህ ሁኔታ ነበር። እስከዚህ ድረስ የነበረው ነገር መልካም ነበር።
የሐዋ. ሥራ 5:1–11ን ያንብቡ። ከመሬቱ ሽያጭ ገንዘብ የተወሰነውን
ቀንሶ ከማስቀረትና ከመዋሸት እጅግ አስከፊ የሆነው የትኛው
ይመስላችኋል? እንደዚህ ዓይነት የጭካኔ ቅጣት ለምን ያስፈልጋል?
በመጀመሪያ ለሥራው ለመስጠት በመፈለጋቸው ከልባቸው ፍላጎት ያላቸው
ይመስል ነበር። ነገር ግን “በኋላ አናኒያና ሳጲራ ለመጎምጀት ስሜት በመሸነፋቸው
መንፈስ ቅዱስን አሳዘኑ። ለጌታ ለመስጠት ቃል በመግባቸው ተጸጸቱና
ለእግዚአብሔር ታላቅ ሥራ እንዲሰሩ ልባቸውን ያሞቀውን የበረከቱን ጣፋጭ
ተጽእኖ ወዲያውኑ አጡ።”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles,
p. 72. በሌላ አነጋገር በመልካም አነሳሽ ሀሳብ የጀመሩ ቢሆንም ስስታቸው
ያልሆኑትን እንደሆኑ አድርገው እንዲያስመስሉ አደረጋቸው።
“በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ”
(የሐዋ. ሥራ 5:11)። ከዚህ ክስተት በኋላ በእርግጠኝነት በአስራት
አመላለሳቸው የበለጠ ጥንቁቅ መሆን አለባቸው። ነገር ግን ይህ አሳዛኝ
ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተካተተው በአሥራት አመላለሳቸው
ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ለማስጠንቀቅ አይደለም። ይልቁንም
መጎምጀት ወዴት እንደሚመራን ምን ያስተምረናል?
መጎምጀት የልብ ጉዳይ ሲሆን እንደ ኩራትና ራስ ወዳድነት ሁሉ ሰዎች
ሳይገነዘቡት ሥር ሊሰድ ይችላል። ገዳይና አሳሳች የሚሆንበት ምክንያትም ከዚህ
የተነሣ ነው። እንደ መዋሸት፣ ዝሙት፣ መስረቅና ሰንበትን መሻር የመሳሰሉ ግልጽ
ኃጢአቶችን ማሸነፍ ከባድ ነው። ነገር ግን እነዚህ ተግባራት ከመፈጸማችን በፊት
ማሰብ ያለብን ውጫዊ ተግባራት ናቸው። ነገር ግን የስህተት ሀሳቦችን ማሸነፍ
ምን ያህል ከባድ ነው? እነዚህን ሀሳቦች ማሸነፍ የበለጠውን ከባድ ነው።
1ኛ ቆሮ. 10:13ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ የተሰጠው ተስፋ ምንድር ነው?
ከመጎምጀት አውድ ለመረዳት ይህ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር
ነው?
ታዲያ ከዚህ አደገኛ ከሆነው አታላይ ኃጢአት በእግዚአብሔር ኃይል
ልንጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
1. እግዚአብሔርን ለማገልገልና በእርሱ ለመደገፍ፣ በተጨማሪም የእርሱ
ቤተሰብ አባል ለመሆን ወስኑ። “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን
እግዚአብሔርን እናመልካለን” (ኢያሱ 24:15)።
2. በየዕለቱ ጸልዩና በማቴዎስ 6፡13 ላይ “ከክፉም አድነን እንጂ ወደ
ፈተና አታግባን፤ መንግሥት ያንተ ናትና ኃይልም ክብርም ለዘለዓለሙ፤ አሜን”
የሚለውን አካትቱ። መመኘት እንደሌለባችሁ የምታውቁትን ነገር የመመኘት
ስሜት እየተሰማችሁ ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በ1ኛ ቆሮ. 10፡13 ላይ ያሉትን
ተስፋዎች እንዲሰጣችሁ በመጠየቅ ጸልዩ።
3. መጽሐፍ ቅዱሳችሁን በቋሚነት አጥኑ። “አንተን እንዳልበድል፥
ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” (መዝ. 119:11)።
ኢየሱስ ሰብአዊውን የኃጢአት ችግር ተጋፍጧል። እኛ በምንፈተንበት
በእያንዳንዱ ነጥብ ተፈትኗል። እነዚህን ፈተናዎች ለመቋቋም በጸሎት ከአባቱ
ጋር እየተገናኘ ሙሉ ሌሊቶችን አሳልፏል። ኢየሱስ በሕይወት ምሳሌነቱ መንገድ
እስከሚያበጅና እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቶስን የመሰለ ባህርይ እንዲያጎለብት
ኃይል ለመስጠት ተስፋ እስኪሰጥ ድረስ ከዚህ ምድር ለቆ አልሄደም ነበር።
“እግዚአብሔር በሚገኝበት ጊዜ ፈልጉት፥ ቀርቦም ሳለ ጥሩት፤ ክፉ ሰው መንገዱን
በደለኛም አሳቡን ይተው፤ ወደ እግዚአብሔርም ይመለስ እርሱም ይምረዋል፥
ይቅርታውም ብዙ ነውና ወደ አምላካችን ይመለስ” (ኢሳ. 55:6፣ 7)።
በሕይወትዎ መጎምጀት ያስከተላቸው መዘዞች ካሉ ምን ዓይነት
መዘዞችን አስከተለብዎ? ከዚህ ምን ትምህርቶችን አገኙ? አሁንም
ከእነዚህ መዘዞች መማር ያለብዎ ምን አለ?
:- ኢያሪኮን ባሸነፉ ጊዜ ወደ እሥራኤል ካምፕ ብርና ወርቅ
ተሸክሞ የመጣው አካን ብቻ አልነበረም። ኢያሱ ብርን፣ ወርቅንና የነሃስና የብረት
ዕቃዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ግምጃ ቤት እንዲያመጡ ለወንዶቹ ትዕዛዝ
ሰጥቶ ነበር
(ኢያሱ 6:19፣ 24)። ሌላ ነገር በሙሉ መቃጠል ነበረበት። ነገር ግን አካን
ለራሱ የሆነ ነገር ያስቀረ ብቸኛ ሰው ነበር። “በዚያ የተቀደሰ የድልና የፍርድ
ሰዓት ከእሥራኤል ሚሊዮኖች መካከል የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ለመተላለፍ
የደፈረ አንድ ሰው ነበር። የአካን መጎምጀት የተቀሰቀሰው ዋጋው እጅግ ውድ
የሆነ የሰናዖር ካባ ከመመልከቱ የተነሣ ነበር፤ ከሞት ጋር እንዲጋፈጥ ባደረገው
ጊዜ እንኳን ‹መልካም የሆነ የባቢሎናውያን ልብስ›› ብሎ ነበር የተናገረው።
አንዱ ኃጢአት ወደ ሌላኛው ኃጢአት ስለመራው ወደ እግዚአብሔር ግምጃ ቤት
እንዲገባ የተሰጠውን ወርቅና ብር ለራሱ ወሰደ። የከነዓንን ምድር የመጀመሪያ
ፍሬዎች ከእግዚአብሔር ቀማ። ”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 496.
ጳውሎስ የመጨረሻዎቹ ቀናት ምልክቶች እንደሆኑ ከዘረዘራቸው ነገሮች መካከል
የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ለገንዘብና ለንብረት ያለንን አመለካከት የሚያካትቱ ናቸው።
“ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች
ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፥ ገንዘብን የሚወዱ፥ ትምክህተኞች፥ ትዕቢተኞች፥
ተሳዳቢዎች፥ ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ፥ የማያመሰግኑ” (2ኛ ጢሞ. 3:1፣ 2)።
በመጨረሻ ዘመን፣ አሁን እኛ ያለንበት ዘመን፣ ራስ ወዳድነትና የገንዘብ ፍቅር
ወሳኝ የሆኑ የሰብአዊነት መገለጫዎች ናቸው።
:1.
1ኛ ጢሞ 6:6–10ን ያንብቡ:- “ኑሮዬ ይበቃኛል
ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤
ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ
አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ
ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን
በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና
በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ
ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው
በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” ለገንዘብ ካላቸው ፍቅር የተነሣ
‹‹በብዙ ሀዘን ራሳቸውንና ሌሎችን የወጉትን›› ሰዎች ምሳሌ
በክፍል ውስጥ ተወያዩ። ብዙ ምሳሌዎች አሉ፣ አይደለም?
ገንዘብ እንደሚያስፈልገን ስለምናውቅ ጳውሎስ እዚህ ላይ
በሚያስጠነቅቀን ወጥመድ ውስጥ ሳንወድቅ ትክክለኛውን ሚዛን
ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
2.
ከገንዘብ ሌላ ልንመኝ የምንችላቸው ነገሮች ምንድር
ናቸው?
3.
አንድን ነገር ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለማግኘት በመፈለግና
በመጎምጀት መካከል ያለው ልዩነት ምንድር ነው? ለአንድ ነገር
ያለው ሕጋዊ ፍላጎት ወደ መጎምጀት ሊቀየር የሚችለው መቼ
ነው?