የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ጌታ እስኪመጣ ድረስ የእርሱን ንብረት ማስተዳደር


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2023

የካቲት 11-17

8ኛ ትምህርት

Feb 18 - 24




ለስኬት ማቀድ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- መክብብ 12:1፤ ዘፍ. 2:15፤ 1ኛ ጢሞ. 5:8፤ ቆላ. 3:23፣ 24፤ ዘፍ. 39:2–5፤ ምሳሌ 3:5–8።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፥ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፥ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና” (ቆላ. 3:23, 24)።

አ ብዛኞቹ ሰዎች ‹‹ስኬታማ›› እና ደስተኛ ሕይወት መኖር ይፈልጋሉ። በሰዎች ላይ ያልተጠበቁ አሳዛኝ ነገሮችና አደጋዎች በድንገት በሚደርሱበት በዚህ የወደቀ ዓለም ላይ ስንኖር ሁልጊዜ ከዚህ ግብ ላይ በቀላሉ ላይደረስ ይችላል። ስለዚህ ‹‹ስኬትን›› እንዴት ነው መተርጎም የምንችለው? የሚል ጥያቄ ይነሳል። ዮሴፍ በግብጽ ያጋጠመው ጉዳይ አለ፤ ስኬታማ ሕይወት አለ ከተባለ ያ ሕይወት በእርግጠኝነት የእርሱ ሕይወት ነው፣ አይደለም እንዴ? ከእስር ቤት ወደ ቤተ መንግስት መሄድን የመሰለ ነገር። በሌላ በኩል ስለ መጥምቁ ዮሐንስስ ምን ይላሉ? እርሱ ከእስር ቤት ወደ መቃብር ሄደ። የእርሱ ሕይወት ምን ያህል ስኬታማ ነበር? በድጋሚ የእርሱ ሁኔታም የሚደገፈው ‹‹ስኬታማ›› የሚለውን ቃል በምትተረጉሙበት መንገድ ላይ ነው።

በዚህ ሳምንት ‹‹የስኬትን›› ሀሳብ ከመሰረታዊ መጋቢነትና የገንዘብ መርሆዎች አውድ እንመለከታለን። ማንም ብንሆን ወይም የትም ብንኖር ፣ ብንወድም ባንወድም፣ ገንዘብና ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ነገሮች የሕይወታችን አካል ሆነው መቀጠላቸው እሙን ነው። ታዲያ ለስኬት ዋስትና ባይሰጡንም በገንዘብ ነክ ጉዳዮች ስኬትን ከባድ ከሚያደርጉ የተለመዱ ወጥመዶችና ስህተቶች ማምለጥ እንድንችል እግረ መንገዳችንን መውሰድ የምንችላቸው አንዳንድ ተግባራዊ እርምጃዎች ምንድር ናቸው? *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለየካቲት 18 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

የካቲት 12
Feb 19

መቅደም ያለባቸውን ነገሮች ማስቀደም


መክብብ 12:1ን ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለእኛ ያለው መልእክት ምንድር ነው?



ወጣቶች እየበሰሉ ወደ ጉልምስና ዕድሜ ሲደርሱ ለሰው ልጅ የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን--ምግብ፣ ልብስና መጠለያ--የማቅረብ ሀሳቦች ይነሳሉ። ኢየሱስ “ነገር ግን አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ. 6:33) በማለት ለሚያስፈልጉን ነገሮች እንዴት ቅድሚያ መስጠት እንዳለብን ነግሮናል። በእድሜ ለገፉና በወጣትነት ዘመናቸው ኢየሱስን ላልመረጡ ሰዎች መጋቢነትን በተመለከተ አሁንም ትክክለኛ ምርጫ ለመምረጥ ጊዜ አለላቸው።

በዘፍጥረት ምዕራፍ 28:20–22 ላይ እንደተመለከትነው ያዕቆብ አንዳንድ ወሳኝ የሆኑ የሕይወት ምርጫዎችን አደረገ፤ እነዚህ ምርጫዎች መንፈሳዊውንም ገንዘብን የሚመለከተውንም ጉዳይ ያካተቱ ነበር። በራዕይ እግዚአብሔር “የአባትህ የአብርሃም አምላክ የይስሐቅም አምላክ እኔ እግዚአብሔር ነኝ” (ዘፍ. 28:13) በማለት ራሱን ለያዕቆብ አስተዋወቀ። ከዚያ በኋላ ያዕቆብ የመሃላው አካል በማድረግ “እግዚአብሔር አምላኬ ይሆንልኛል” (ዘፍ. 28:21) አለ። ዘፍጥረት 29:9–20ን ያንብቡ። በያዕቆብ ሕይወት የዚህን ክስተት ጊዜ መጠበቅን በተመለከተ አስፈላጊው ነገር ምንድር ነው?



ያዕቆብ መንፈሳዊና ገንዘብን የተመለከተ ቃል ኪዳን ከእግዚአብሔር ጋር ከፈጸመ በኋላ እግዚአብሔር በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ ወደ ራሄል መራው (ዘፍጥረት 29፡ 9-20 ይመልከቱ)። ወደ ትዳር ቃል ኪዳን ከመግባታችሁ በፊት መንፈሳዊ ውሳኔ ማድረግና ለሕይወታችሁ ስለምትሰሩት ሥራ መወሰን ተገቢ ነው። የወደፊት የትዳር አጋርህ ወዴት እየገባች እንደሆነ ማወቅ አለባት። ይህ ግለሰብ ራሱን የሰጠ ክርስቲያን ነውን? ምን ዓይነት ሥራ ላይ ነው መሳተፍ የሚችለው? ይህ ግለሰብ መሆን የሚችለው መምህር ነው ወይስ ነርስ? ጠበቃ ወይስ የቀን ሰራተኛ ወይስ ሌላ? ምን ዓይነት ሕይወት ለመምራት ነው ራሴን እየሰጠሁ ያለሁት? ከጋብቻ ቃል ኪዳን በፊት መነሳት ያለባቸው ሌሎች ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡የትምህርት ደረጃው/ደረጃዋ ምንድር ነው? ወደ ጋብቻ ተይዞ እየተመጣ ያለው ዕዳ ምን ያክል ነው? ይህን ሁኔታ እንደ ሀላፊነቴ አካል አድርጌ ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ?

2ኛ ቆሮ. 6:14፣ 15ን ያንብቡ። የሕይወት አጋር ሲፈለግ ይህ መርህ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው? ምንም እንኳን ይህ መርህ ለጥሩ ጋብቻ ዋስትና ባይሰጥም ጥሩ ትዳር የመፈጸም ዕድሎች የተሻሉ እንዲሆኑ የሚረዳው ለምንድር ነው?

የካቲት 13
Feb 20

የሥራ በረከት (እንዲሆን በሚፈለግ መልኩ)


የማንም ጥገኛ ያልሆንክ ሀብታም ካልሆንክ ወይም በሕይወትህ አንድም ቀን እንዳትሰራ አባትህ ወይም እናትህ ወይም ሁለቱም ያስቀመጡልህ ገንዘብ ተጠቃሚ ካልሆንክ በስተቀር ይፍጠንም ይዘግይም ለኑሮህ መስራት የግድ ያስፈልግሃል። ስለ እነዚህ ሳይሰሩ ከወላጆቻቸው ሀብት ስላገኙ ልጆች በርካታ ታሪኮችን ስታነቡ በረከት እንዲሆን የተሰጠው ገንዘብ ብዙ ጊዜ አሳዛኝ ውጤት ሲያስከትል ትመለከታላችሁ። በእርግጥ ሆኖ ማየት የምትፈልጉት ነገር ቢኖር ጥሩ ገቢ የሚያስገኝላችሁንና ለማግኘት የምትጓጉለትን የሆነ ነገር ማግኘት፣ በዚያ ላይ ስልጠና መውሰድ፣ በሰለጠናችሁበት መስክ ሥራ ማግኘትና በቀሪው ዘመናችሁ ያንን ሥራ እየሰራችሁ መኖር ነው። ሆኖ ማየት የምትፈልጉት ይህ ቢሆንም ሁልጊዜ እናንተ እንደምትፈልጉት አይሆንም።

ዘፍጥረት 2:15ን ያንብቡ። (መክብብ 9:10 እና 2 ተሰ. 3:8– 10ንም ይመልከቱ). ኃጢአት ከመግባቱ በፊት ለአዳም (ለሄዋንም ጭምር) ሥራ የመሰጠቱ አስፈላጊነት ምንድር ነው? ከላይ እንደተገለጸው ሰርተው የማያውቁ ሰዎች ሁኔታቸው እርግማን እንደሚሆንባቸው ይህ እንዴት ሊያብራራ ይችላል?



ሥራ ቅጣት አልነበረም። ሥራ የታቀደው ለእነርሱ ጥቅም ነበር። ኃጢአት፣ ሞትና ሥቃይ ባልነበረበት ዓለም፣ በኤደን ገነት እንኳን፣ ሰብአዊ ፍጡራን መስራት እንዳለባቸው እግዚአብሔር አወቀ። “አዳም የአትክልት ቦታውን የመንከባከብ ሥራ ተሰጠው። አዳም ያለ ሥራ ደስተኛ እንደማይሆን ፈጣሪ አወቀ። የአትክልት ቦታው ውበት አስደሰተው፣ ነገር ግን ይህ በቂ አልነበረም። ድንቅ የሆኑ የአካል ክፍሎቹን ለማሰራት ሥራ ሊኖረው ይገባ ነበር። ምንም ባለመሥራት ደስታ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ሰው በቅዱስ የዋህነት ይኖር በነበረበት ጊዜ ሥራ ሳይሰጠው መተው ይቻል ነበር። ነገር ግን ሰውን የፈጠረው ፈጣሪ ሰውን ምን ሊያስደስተው አንደሚችል አወቀ፤ ወዲያውኑ እንደፈጠረው የተመደበለትን ሥራ ሰጠው።

የወደ ፊት ክብር ተስፋና ሰው የእለት እንጀራውን ለማግኘት መልፋት እንዳለበት የሚገልጸው አዋጅ የመጣው ከዚያ ከአንዱ ዙፋን ነው።”—Ellen G. White, Our High Calling, p. 223. ሆኖም ከውድቀት በኋላ እንኳን፣ ልክ እንደ ሌላው ነገር ሁሉ ሥራም በኃጢአት ቢበከልም፣ እግዚአብሔር ለአዳም እንዲህ አለው፡- “ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ” (ዘፍ. 3:17)። እግዚአብሔር ምድርን በአዳም ምክንያት ‹‹ከአንተ የተነሳ›› በማለት እንደረገመ ልብ ይበሉ፤ ይህን ሲል እግዚአብሔር የነበረው ሀሳብ አዳም፣ በተለየ ሁኔታ ወደ ኃጢአት እንደወደቀ ፍጡር፣ ሥራ ያስፈልገዋል የሚል ነው። ስናስበው ሥራ ለእኛ በረከት እንዲሆን የሚያደርገው ነገር ምንድር ነው?

የካቲት 14
Feb 21

ሰርተን ገቢ የምናገኝባቸው ዓመታት


ሰዎች በአንድ ወይም በሌላ የሥራ ዘርፍ ሥራን እንዲሰሩ እግዚአብሔር ማቀዱን አይተናል። የሕይወታችን ይህኛው ክፍል (የሥራ ዓመታት) ወደ 40 ዓመታት ይሆናል። ይህ ጊዜ ብዙ ሰዎች ልጆችን የሚያሳድጉበትና የሚያስተምሩበት፣ እንዲሁም ቤትና ሌሎች ዋና የሆኑ ነገሮች የሚገዙበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ገንዘብን በተመለከተ ከፍተኛ መጨናነቅ የሚኖርበት ጊዜ ነው። ይህ ጊዜ ቤተሰብ አብሮ መስራትን እየተማሩ ያሉበትና የቤተሰብ አባላትም የዕድሜ ልክ ግንኙነት እየፈጠሩ ያሉበት ጊዜ ስለሆነ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጊዜ ነው። በዚህ ነጥብ ላይ የገንዘብ ጫና ትዳርን ማፍረስ የሚችልበት ጊዜ ነው፣ ብዙ ጊዜ ያፈርሳልም። ሁለቱም የትዳር አጋሮች ለክርስቲያናዊ ቃል ኪዳናቸው የተሰጡ ሲሆኑና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆዎችን ለመከተል ፈቃደኛ ከሆኑ ትዳራቸው እጅግ የተረጋጋ ነው።

1ኛ ጢሞ. 5:8፣ ምሳሌ 14:23፤ እና ቆላ. 3:23፣ 24ን ያንብቡ። ከእነዚህ ጥቅሶች በቤት ውስጥ ስላለው የገንዘብ አያያዝ ምን አስፈላጊ ነጥቦችን መውሰድ እንችላለን?



ምንም እንኳን ሁለቱም የትዳር አጋሮች ሰራተኞች ቢሆኑም አብዛኛውን ጊዜ የቤተሰቡ አባወራ ባል ነው። በርግጥ ይህን ምቹ ሁኔታ ከባድ የሚያደርጉ እንደ በሽታ፣ የኢኮኖሚ ማሽቆልቆል፣ የመሳሰሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ። ስለዚህ ሰዎች እንደ ሁኔታው ራሳቸውን ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል። በዚህ የሕይወት ክፍል ላይ ወደዚህ ዓለም እንዲመጡ የተደረጉ ልጆች ‹‹የእግዚአብሔር ስጦታ ናቸው›› ተብለዋል (መዝ. 127፡3)። ልጆች ሲመጡ ከእነርሱ ጋር ከባድ ኃላፊነቶችን ይዘው እንደሚመጡ ማስታወስ አለብን። የክርስቲያን ወላጆች ኃላፊነት ልጆቻቸው በዚህ ዓለም ላይ የማንም ጥገኛ ያልሆኑ ጎልማሶች እንዲሆኑና ለሚመጣውም ሕይወት ገጣሚ እንዲሆኑ ማሰልጠን ነው። ወላጆችን የሚረዱ ሶስት ነጥቦች ከዚህ በታች ይገኛሉ፡-81-

1. ክርስቲያናዊ መኖሪያ አከባቢን ማዘጋጀት። ይህ ቋሚ የሆነና ደስ የሚል የቤተሰብ አምልኮን፣ በቋሚነት ሰንበት ትምህርትንና ቤተ ክርስቲያንን መከታተልን እና በአሥራትና በስጦታዎች ታማኝ መሆንን ያካትታል። እነዚህ ነገሮች በልጅነት ዕድሜ መፈጠር ያለባቸው ታላላቅ ልማዶች ናቸው።

2. ሥራ ለመስራት ፈቃደኛ እንዲሆኑና ሥራን እንዲያደንቁ አስተምሩአቸው። በሥራ ላይ የሚያሳዩት ትጋትና ታማኝነት ሁልጊዜ እንደሚታይ፣ እንደሚደነቅና ሽልማት እንደሚያስገኝ ልጆች ያውቃሉ። ለሌሎች ሰዎች ጠቃሚ የሆኑ ተግባራትን በማከናወን ለእነርሱ ጊዜ ከመስጠታቸው የተነሳ ገንዘብ እንደሚገኝ ይማራሉ።

3. በጥሩ ትምህርት እርዱአቸው። ዛሬ ትምህርት፣ በተለይም በግል ትምህርት ቤቶች የሚሰጥ የክርስቲያን ትምህርት ውድ ነው። ነገር ግን ለልጆቻቸው ለዚህ ሕይወት ብቻ ሳይሆን ለሚመጣውም ሕይወት ዕቅድ ላላቸው ወላጆች ያንን ማውጣት የተገባ ነው። በርግጥ ወላጆች ምንም ቢያደርጉም ልጆቻቸው ስለሚሄዱበት አቅጣጫ ማንም ዋስትና የለውም። ያደጉ ልጆቻቸው ስለሚመርጡት ምርጫ ወላጆች ራሳቸውን ጥፋተኛ አለማድረጋቸው የሚጠቅመው ለምንድር ነው?

የካቲት 15
Feb 22

በታማኝነት መስራት


‹‹የስኬታማ›› ሕይወት ሌላኛውና የመጨረሻው ክፍል እጅግ አስደሳች የመሆን አቅም አለው። ይህ ሊሆን የሚችለው የቀደምት ዓመታት ውሳኔዎች በጥበብ የተፈጸሙ ከሆኑና ባልተጠበቁ ክስተቶች ካልተበላሹ ነው። ወላጆች ላሰቡት ነገር በሚስማማ ሁኔታ ልጆቻቸው ራሳቸውን የቻሉ ጎልማሶች እንዲሆኑ አሰልጥነዋል፣ ለቤት የሚከፈለው ወጪ ተከፍሏል፣ የትራንስፖርት ፍላጎቶችም ተመልሰዋል፣ የሚንከባለሉ ዕዳዎች የሉም፣ አንጋፋ የቤተሰብ አባላት ፍላጎቶችን ለማሟላትም በቂ የገቢ ምንጭ አለ።

እግዚአብሔር በሥራና በሕይወት ልጆቹ ከፍ ወዳለ መስፈርት እንዲደርሱ ይጠራቸዋል። መስፈርቱ በልባችን የተጻፈውና በባህርያችን የተንጸባረቀው የእግዚአብሔር ሕግ (ኤርምያስ 31፡33ን ይመልከቱ) ነው። ማህበረሰቡ እየተሸረሸረ ሲሄድና የክርስትና ትምህርት እየቀጠነና እያነሰ ሲሄድ ለግለሰብ ክርስቲያን ከነቀፌታ በላይ በሆነ ደረጃ መኖርና መስራት የበለጠ አስፈላጊ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፡- “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፥ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” (ምሳሌ 22:1)።

እግዚአብሔርን የሚፈራ ተቀጣሪ ስላላቸው መባረካቸውን የተገነዘቡ ቀጣሪዎች መኖራቸውን መጽሐፍ ቅዱስ መዝግቧል። ያዕቆብ ከአማቱ ላባ ተለይቶ ከቤተሰቡ ጋር ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ በፈለገ ጊዜ ላባ እንዲህ በማለት እንዳይሄድ ተማጸነው፡- “በዓይንህ ፊት ሞገስን የማገኝ ብሆንስ ከዚሁ ተቀመጥ፤ እግዚአብሔር በአንተ ምክንያት እንደ ባረከኝ ተመልክቼአለሁና አለው” (ዘፍ. 30:27)። ዮሴፍ በግብፅ ምድር ለባርነት በተሸጠ ጊዜ ጌታው ጶጥፋር ስለ ዮሴፍ ስራ ተመሳሳይ መረዳት የነበረው ሲሆን በዚህ ላይ ተመስርቶ ሽልማት አግኝቷል። ዘፍጥረት 39:2–5ን ያንብቡ። ጥቅሶቹ በትክክል ነቅሰው ባይነግሩንም ዮሴፍ በጌታው ዘንድ በመልካም እንዲታይ ያደረገ ምን ነገር ያደርግ እንደነበር ምን ያስባሉ?



“እንግዲህ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ኛ ቆሮ. 10:31)። ስለዚህ በሥራችንና በገንዘብ አያያዛችን ወይም ምንም ነገር ብናደርግ ሁሉንም ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ አለብን። በሕይወታችን ስኬት እንድናገኝ እውቀትና ብርታት የሚሰጠን እርሱ ነው።

“አቤቱ፥ በሰማይና በምድር ያለው ሁሉ የአንተ ነውና ታላቅነትና ኃይል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ነው፥ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። ባለጠግነትና ክብር ከአንተ ዘንድ ነው፥ አንተም ሁሉን ትገዛለህ ኃይልና ብርታት በእጅህ ነው ታላቅ ለማድረግ፥ ለሁሉም ኃይልን ለመስጠት በእጅህ ነው” (1 ዜና 29:11፣ 12)። በሥራዎ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በሕይወትዎ እየተከተሉአቸው ያሉት መርሆዎች ምንድር ናቸው? ምን ዓይነት ለውጦች ማድረግ የሚያስፈል ይመስሎታል?

የካቲት 16
Feb 23

እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎችን ምክር መሻት


በገንዘብ አያያዛቸው አንቱ የተባሉ (ልዩ እውቀት ያላቸው) በርካታ ዓለማዊ ሰዎች አሉ፣ ነገር ግን ከአምላክ ለተሰጡን ሀብቶች አያያዝ እነርሱን እንዳናማክር እግዚአብሔር አስጠንቅቆናል። “ምስጉን ነው በክፉዎች ምክር ያልሄደ፥ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፥ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል፥ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያስባል። እርሱም በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደ ተተከለች፥ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፥ ቅጠልዋም እንደማይረግፍ ዛፍ ይሆናል፤ የሚሠራውም ሁሉ ይከናወንለታል” (መዝሙር 1:1–3)።

ስለዚህ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው ሰው (በዚህ ቦታ ሕግ በስፋት የሚስተዋለው እንደ እግዚአብሔር ቃል ነው) ይባረካል። ይህ ምን ያህል ቀላል ነው? ይከናወንለታል--ስኬታማ ይሆናል። ምሳሌ 3:5–8ን ያንብቡ። ይህን መርህ መሰረታዊ በሆኑ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ላይ እንዴት እንተገብራለን?



በገንዘብ አያያዝ ላይ እንደ ማጠቃለያ የተሰጠው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ልንከተላቸው የሚገቡ እጅግ ጠቃሚ ነጥቦችን ይሰጠናል። ከእነዚህ መካከል ሰባቱን እንመልከታቸው። 1. ራሳችሁን በጥሩ ሁኔታ አደራጁ። የገንዘብ አወጣጥ እቅድ አዘጋጁ (ምሳሌ 27፡ 23፣24)። ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ከደሞዝ እስከ ደሞዝ ነው። ስለ ገቢ፣ ስለ ወጪና ስለ ቁጠባ ቀላል እቅድ ከሌለ ሕይወት እጅግ አስጨናቂ ነው።

2. ወጪአችሁ ከገቢያችሁ በታች ይሁን። በገቢያችሁ ልክ ለመኖር ወስኑ (ምሳሌ 15፡16)። በምዕራብ አገሮች የሚኖሩ ብዙ ቤተሰቦች ወጪ የሚያደርጉት ከገቢያቸው በላይ ነው። ይህ ሊሆን የቻለው የክሬዲት ካርድ ከመኖሩ የተነሣ ብቻ ነው። በዕዳ ውስጥ ያሉትን ብዙ ችግሮች ያጠቁአቸዋል።

3. ከደሞዛችሁ ሁልጊዜ የተወሰነውን ቆጥቡ (ምሳሌ 6:6–8)። የምንቆጥበው ወደ ፊት ታላላቅ ነገሮችን ለመሸመትና እንደ አደጋና ሕመም ያሉ ያልተጠበቁ ወጪዎችን ለመሸፈን ነው። አንዳንድ ቁጠባዎች የሚቆጠቡት ከዕድሜ የተነሣ ተቀጥረን መስራት ለማንችልበት ጊዜ (ለጡረታ ጊዜ) ነው።

4. ዕዳን እንደ ኮቪድ - 19 ሽሹት። (ምሳሌ 22፡7)። ፍላጎት ያለ እርሱ መኖር የምትችሉት ሌላ ወጪ ነው። በዕዳ ወይም ገንዘብን በመበደር የሚኖር ግለሰብ ወይም ቤተሰብ ዛሬን ወደ ፊት ለማግኘት በሚጠብቁት ገንዘብ እየኖሩ ነው። ምንም ዓይነት የሕይወት ለውጥ ቢያጋጥም አሳሳቢ የገንዘብ ዕጦት ሀፍረት ይገጥማቸዋል።

5. ትጉህ ሰራተኛ ሁኑ። “የታካች ሰው ነፍስ ትመኛለች፤ አንዳችም አታገኝም፤ የትጉ ነፍስ ግን ትጠግባለች” (ምሳሌ 13:4)። 6. ገንዘብን በተመለከተ ለእግዚአብሔር ታማኝ ሁኑ (ዘዳግም 28፡ 1-14)። ያለ እግዚአብሔር በረከት አንድም ቤተሰብ መኖር አይችልም።

7. ይህቺ ምድር እውተኛ መኖሪያችን እንዳልሆነች አስታውሱ። አያያዛችን የመጨረሻዎቹ ቅድሚያ የምንሰጣቸው ነገሮች ስላሉበት ቦታ ብዙ ይነግረናል (ማቴ 25፡ 14-21ን ይመልከቱ)።

የካቲት 17
Feb 24


ተጨማሪ ሀሳብ


:-“ስለ ወደፊቱ ዘላለማዊ ሕይወት ሳያስብ በአሁኑ አጭር ሕይወት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ማንኛውም የንግድ ንድፍ ወይም የሕይወት ዕቅድ ጤናማ ወይም የተሟላ ሊሆን አይችልም።…በምድር ላይ ያልበለጸገና ያልከበረ ሕይወት ያለው ሰው በሰማይ ሀብት ማስቀመጥ አይችልም። ”—Ellen G. White, Education, p. 145. “በንግድ ታማኝነትና የእውነተኛ ስኬት መሰረት ላይ ያለው ነገር የእግዚአብሔርን ባለቤትነት መገንዘብ (እውቅና መስጠት) ነው። የሁሉም ነገር ፈጣሪ የሆነው እርሱ የመጀመሪያው ባለቤት ነው። እኛ የእርሱ መጋቢዎች ነን። ያለን ነገር ሁሉ እርሱ በሚሰጠን መመሪያ መሰረት እንድንጠቀምበት ከእርሱ በአደራ የተሰጠን ነው።”—Education, 137.

የቤተሶቻችንን ፍላጎቶች ለማሟላት ካለብን ጫና የተነሣ ብዙ ጊዜ ሥራ የምንሰራው ገቢ ለማግኘት ብቻ እንደሆነ እናስባለን። ነገር ግን እንደ ክርስቲያንነታችን ኢየሱስ ለተከታዮቹ ሁሉ በሰጠው ታላቁ ተልዕኮ ላይ የራሳችንን ድርሻ መወጣትም ይጠበቅብናል። ኤለን ጂ ኋይት በማርቆስ 16፡15 ላይ ያለውን ጥቅስ ከጠቀሰች በኋላ እንዲህ ብላለች፡- ‹‹ሁሉም አገልጋዮች ወይም ሚስዮናውያን እንዲሆኑ አልተጠሩም፤ ነገር ግን ሁሉም ለመሰሎቻቸው ‹መልካሙን ዜና› በመስጠት ከእርሱ ጋር አብረው ሰራተኞች መሆን ይችላሉ። ትዕዛዙ የተሰጠው ታላቅ ወይም ታናሽ፣ ምሁር ወይም ማሃይም፣ ወጣት ወይም ሽማግሌ ሳይል ለሁሉም ነው።”—Education, p. 264.

“እግዚአብሔር ለሕይወታችን ያለውን ዕቅድ በጥንቃቄ መከተል አለብን። በአጠገባችን ያለውን ሥራ ከሁሉ በተሻለ ሁኔታ መስራት፣ መንገዳችንን ለእግዚአብሔር አደራ መስጠትና የእርሱን ምሪት መጠበቅ በሥራ ምርጫችን ትክክለኛ ምሪት እንደምናገኝ የሚያረጋግጡ ነገሮች ናቸው።”—Education, p. 267.


የውይይት ጥያቄዎች



1.እኛ እንደ ክርስቲያን ‹‹ስኬታማ›› ሕይወትን እንዴት ነው የምንተረጉመው? ዓለም ስኬት ነው ብሎ በሚተረጉመውና እኛ መተርጎም ባለብን መካከል የሚኖረው ልዩነት ምን ይሆን? ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስን ውሰዱ። በክፉ ሴት ፍላጎት መሰረት ተዋርዶ ወህኒ የተጣለውን የእርሱን ሕይወት እንዴት ትተረጉማላችሁ? የእርሱ ሕይወት ስኬት ነው ትላላችሁ? ለመልሳችሁ የምትሰጡአቸው ምክንያቶች ምንድር ናቸው?

2. ስለ ሀብት አያያዝም ሆነ በአጠቃላይ ስለ ሕይወት ከመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎች መካከል አንዱንም የማይከተሉ ብዙ ‹‹ስኬታማ›› ሰዎች የመኖራቸውን እውነታ እንዴት ታብራሩታላችሁ? ወይም እነርሱን ለመከተል እየሞከሩ ስኬት ማግኘት ስለማይችሉትስ ምን ትላላችሁ? ምናልባትም ሊታመሙ ወይም አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል። እነዚህን ሁኔታዎች እንዴት ነው ማስተዋል ያለብን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL