የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 14:10፣ 24፤ ዘፍ 3:7-9፤ ዮሐ. 16:27፣ 28፤ ዮሐ. 16:7-11፤ ዮሐ. 17፡1-26።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም
የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (ዮሐ. 14፡26)።
የዮሐንስ ወንጌል በተለያየ ሁኔታ የተቀመጡ ጭብጦች የተሰባሰቡበት (ሞዛይክ)
ነው። ዮሐንስ ኢየሱስ በነቢያት የተነገረለት መሲሕ ስለመሆኑ የሚያስረዱ ምልክቶችን
(ተአምራቶችን) ይዘግባል። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ መሆኑን ለማወጅም ዮሐንስ ብዙ
ምስክሮችን ያመጣል። ወደ መለኮታዊነቱ ለመጠቆም “እኔ ነኝ” የሚለውንም መግለጫ
ይጠቀማል።
ሦስቱም የመለኮት አካላት በዮሐንስ 1 (ዮሐ. 1፡1-4፣ 14፣ 18፣ 32-34)
ተጠቅሰዋል። ለብዙ መቶ ዘመናት ሰዎች የመለኮትን ምንነት ሙሉ በሙሉ ለመረዳት
ሞክረዋል፣ ነገር ግን ስላልተቻለ ብዙዎች ሃሳቡን ተቃውመዋል። ነገር ግን አንድን ነገር ሙሉ
በሙሉ ልንረዳው ስላልቻልን ወይም በሰዎች የማሰብ ችሎታ ጠባብ ገደብ ውስጥ ስለማይገባ
ብቻ አለመቀበል ምንኛ ሞኝነት ነው።
ዮሐንስ እግዚአብሔርን ለመረዳት ከፈለግህ ኢየሱስንና በቃሉ ውስጥ የተገለጠውን
መመልከት አለብህ ይላል። ይህ አካሄድ ለእኛ በሦስቱ የመለኮት አካላት መካከል፣ በመለኮት
አካላት እና በሰብዓዊ ፍጡራን መካከል፣ ብሎም በሰዎችም ዘንድ አዲስ የግንኙነት ዓለም ከፍቶ
ያሳየናል። የዚህ ሳምንት ትምህርት፣ የዮሐንስ ወንጌል ከክርስቶስ የስንብት ንግግር አውድ አንፃር
(ዮሐ. 13-17) አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን እንዴት እንደሚገልጽ እንመለከታለን።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለታኅሣሥ 5 ሰንበት ይዘጋጁ።
የዮሐንስ ወንጌል ከአጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትረካ አንጻር፣ ከእኛ መነሻ በመጀመር
የተጻፈ ነው። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፡1)። ወይም
በመጀመሪያ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሰማይንና ምድርን ፈጠሩ። እነርሱ ላሉት ነገሮች ሁሉ
ምንጭ ናቸው። እነርሱ አጽናፈ ሰማይን (ዩኒቨርስን)፣ በውስጡ የሚኖሩትን ፍጥረታትን ጨምሮ
ፈጥረዋል። በምድራችን ላይ ልዩ የሕይወት ፍጥረት አለ፣ እና ከፍጥረት ሁሉ ልዩ የሆነው የሰው
ልጅ ነው። እናም እግዚአብሔር የሰውን ልጅ የፈጠረበት ዓላማ ከእርሱ ጋር እና እርስ በእርሳችን
በፍቅር ተስማምተን እንድንኖር ነው።
እንደ አለመታደል ሆኖ ሉሲፈር ኃጢአትን ወደዚህ ዓለም አመጣ። ኃጢአት ከሌሎች
ነገሮች በተጨማሪ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሸ ነው። አምላክ ማን እንደሆነም
በተሳሳተ መንገድ የሚያሳይ ነው። ስለዚህም፣ የእግዚአብሔርን እውቀት ወደነበረበት
ለመመለስ እና ለሰው ልጆች ድነትን ለማምጣት ኢየሱስ የእኛን ሰብዓዊ ተፈጥሮ በራሱ ላይ
አደረገ።
በዚህ ምድር እያለ፣ ኢየሱስ ሕይወቱን ለአብ በማስገዛት በእርሱ መመሪያ መሠረት
ኖረ። እናም እርሱ “እኔና አብ አንድ ነን” (ዮሐ. 10፡30) አለ። “አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ
እንደ ሆንሁ’’ (ዮሐ. 10፡38)። “እኔ የአባቴን ሥራ ባላደርግ አትመኑኝ” (ዮሐንስ 10፡37)።
በሚቀጥሉት ጥቅሶች እንደተገለጸው የአብ አንዳንድ ሚናዎች ምን ነበሩ?
ዮሐ. 3:16, 17፤ ዮሐ. 6:57
ዮሐ. 5:22፣ 30
ዮሐ. 6:32፤ ዮሐ. 14:10፣ 24
ዮሐ. 6:45
ዮሐ. 15:16፣ ዮሐ. 16:23
እነዚህ ጥቅሶች አብ ከልጁ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለውን ቅርርብ ያሳያሉ። አብ
ከዓለማችን ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና ለደህንነታችን ደግሞ ጥልቅ የሆነውን
መዋለ ነዋይ ያፈሰሰ ነው። ይህ እግዚአብሔር ለእኛ ስላለው ፍቅር እውነት ምን
ያስተምረናል?
እኛ በመለኮት የተፈጠርነው ከእርሱ ጋር ግላዊ የሆነ ግንኙነት እንድናደርግ ነው (ዘፍ. 1፡26፣ 27)። ሆኖም፣ በኃጢአት ምክንያት፣ ያ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ ተበላሽቷል። በኤደን ገነት ታሪክ ውስጥ ይህ መስተጓጎል በፍጥነት ያስከተለውን ውጤት ማየት እንችላለን። ዘፍጥረት 3:7-9ን ያንብቡ። ይህ ኃጢአት ያስከተለውን ከፍተት የሚገልጸው እንዴት ነው? እነርሱ ሳይሆኑ በተገላቢጦሹ አምላክ ሲፈልጋቸው ነበር ማለት ምን ማለት ነው?
የሰው ዘር ሁሉ እርሱ ያቀረበውን ባይቀበልም፣ የመለኮት አሳብ ግን በኃጢአት
ምክንያት ለተፈጠረው ጥሰት ለሰው ልጆች ሁሉ ፈውስ መስጠት ነበር።
ይህንን ግንኙነት ወደነበረበት ቦታ ለመመለስ፣ አንዱ የመለኮት አባል ሰው ሆነ።
ስለዚህም ቃል ሥጋ ሆነ የእግዚአብሔርንም ክብር እየገለጠ በእኛ መካከል አደረ (ዮሐ. 1፡
14-18)። በዚህም ምክንያት ሰብዓዊ ፍጡር ሙላቱንና ጸጋውን ተቀበለ። ኢየሱስ ሊያካፍል
የመጣው ለዚሁ ነው፤ በኃጢአት ምክንያት የፈረሰውን ግንኙነት ለማደስ፣ ቢያንስ በክርስቶስ
ኢየሱስ የቀረበላቸውን በእምነት ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑት ሁሉ የእግዚአብሔርን ክብር
ለመግለጥ ማለት ነው።
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ዓይነት አስደናቂ ተስፋ ይታየናል?
ዮሐ. 1:1፣ 2፤ ዮሐ. 5:16-18፤ ዮሐ. 6:69፤ ዮሐ.10:10፣ 30፤ ዮሐ. 20:28።
“የክርስቶስ ሕይወት ከጥንት ከመሠረቱ ከራሱ የመነጨ እንጂ በብድር ወይም በውሰት
ከሌላ የተገኘ አይደለም” (ኤለን ጂ. ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 549)። ሆኖም በሥጋ
የተገለጠው ልጅ “ራሱን ባዶ አደረገ” (ፊል. 2፡7) የሥልጣኑን ተግባር በተመለከተ፣ ክርስቶስ፣
በሰው መካከል ሰው ሆኖ በምድር ላይ ስለመኖሩ ሲናገር፣ የእርሱን ሕይወት እንደ እግዚአብሔር
ስጦታ ሊያመላክት ይችላል። “የክርስቶስ መለኮታዊነት የአማኙ የዘላለም ሕይወት ማረጋገጫ
ነው” (የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 549)።
እግዚአብሔር በሰብዓዊ ፍጡር ዕውቅና አልተቸረውም (ዮሐ. 17፡25)። ስለዚህም
እርሱ አብ ይታወቅ ዘንድ አንድያ ልጁን ላከ (ዮሐ. 9፡4፣ ዮሐ. 16፡5)።
በሕዋ (ኮስሞስ) አውድ ውስጥ አምላክ የለም የሚል አንድ ሰው እንዲህ ሲል
ጽፏል:- “በእኛ ግርዶሽ፣ በዚህ ሁሉ ሰፊ በሆነው ውስጥ፣ እኛን ከራሳችን ለማዳን
እርዳታ ከሌላ ቦታ እንደሚመጣ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለም።” መጽሐፍ ቅዱስ
ይህ ሰው ምን ያህል ስህተት እንደሆነ በማሳየት የሚያስተምረው ምንድን ነው?
በ
ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሐዋርያው ወልድ የሆነው ኢየሱስ፣ አብን የሚያመለክቱ
ተግባራትን እንዴት እንደሚያከናውን ገልጿል። ኢየሱስ አብ ማን እንደሆነ በመግለጽ፣
እርሱ ከዓለማችን ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሆነ አሳይቷል። ይህ ሁሉ ከዮሐንስ 1፡18 ጋር
የሚስማማ ነው፣ ይህም ጥቅስ አብን ያሳውቃል (የግሪኩ “ኤክስጂኦማይ” “exēgeomai”
የሚለው ማብራራት፣ መተርጎም፣ መግለፅ የሚለውን ትርጉም ይይዛል)። ኢየሱስ ደጋግሞ
ይህን ያደርጋል። አብ (“ፓተር” “patēr”) የሚለው ቃል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ 136
ጊዜ፣ ከምዕራፍ 1-3 ድረስ ብቻ ደግሞ 18 ጊዜ ተጠቅሷል፤ ይህም በአዲስ ኪዳን ውስጥ
ከተጠቀሰው ከጠቅላላው ከአንድ ሦስተኛው እጅ በላይ ነው ማለት ነው። የመሰናበቻው ንግግር
ደግሞ ኢየሱስ በወንጌል ውስጥ አብን ካሳወቀበት ቦታዎች ዋናው ነው።
ኢየሱስ በምድር ላይ የአብ ወኪል ነበር፣ እናም በሰብዓዊ ሥጋ ውስጥ ሆኖ የአብን
ፈቃድ ለመኖር መጣ። በእርግጥ ኢየሱስ በሁሉም ነገር የአብን ፈቃድ ለማድረግ እንደሚፈልግ
ተናግሯል (ዮሐ. 5፡30)። ይህ በመጀመሪያ አስገራሚ ንግግር ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን
ኢየሱስ እንደ ሰው ለአብ ምን ያህል እራሱን እንደሰጠ ያሳያል። ኢየሱስ አብ የእርሱን ሥራ
እንዲጨርስ እንደላከው ያም ሥራ ደግሞ የሰብዓዊ ፍጡር ድነት እንደሆነና አብ ራሱ ስለ እርሱ
ሥራ እንደመሰከረለት ተናግሯል (ዮሐ. 5፡36–38)።
አብ እርሱን የላከው ሰብዓዊ ፍጡር በእርሱ በኩል ወደ አብ የሚመጣበት ብቸኛው
መንገድ ሆኖ እንዲያገለግል እንደሆነ ኢየሱስ ተናግሯል (ዮሐ. 6፡40፣ 44)። በትንሣኤ
እንደሚያስነሣቸው ቃል የገባው አብ፣ ሰዎች በኢየሱስ የሚገኘውን የዘላለም ሕይወት
እንዲያገኙ ይፈልጋል።
የሚከተሉት ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ እና ስለ አብ ግንኙነት ምን ያስተምሩናል? ዮሐ. 7:16፤
ዮሐ. 8:38፤ ዮሐ. 14:10፣ 23፤ ዮሐ. 15:1፣ 9፣ 10፤ ዮሐ. 16:27፣ 28፤ ዮሐ. 17፡3።
ኢየሱስ ከአብ ጋር ስላለው ግንኙነት የተናገራቸው ነገሮች አስገራሚ ናቸው። ሁሉም
የእርሱ ትምህርቶች የአብ ትምህርቶች መሆናቸውን፤ ይህም እርሱ የሚናገረው ነገር ሁሉ በግል
ከአብ እንደ ሰማው የሚናገረው መሆኑን፤ በእርሱ ማመን ማለት በአብ ከማመን ጋር አንድ
እንደሆነ፣ ቃላቱም ሥራውም ሁሉ ከአብ ዘንደ የመጣ እንደሆነና እርሱ እና አብ ለሰው ልጆች
መዳን በፍቅር እና በሥራ አንድ እንደሆኑ አስረግጦ ተናግሯል። ይህ ኢየሱስ በሰማይ ካለው
አባቱ ጋር ስላለው ቅርበት እንዴት ያለ ጠንካራ ምስክርነት ነው!
ሐሳባችሁና ተግባራችሁ ሙሉ በሙሉ እግዚአብሔር ለሕይወታችሁ ያለውን ፈቃድ
የሚገልጽ ቢሆን ኖሮ ሕይወታችሁ እንዴት ይለወጥ ነበር? ማለትም፣ ለሕይወታችን
ከኢየሱስ ዘንድ የምናውቀውን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዴት በተሻለ መንገድ
መኖር እንችላለን?
መንፈስ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ እንደ አብና ወልድ ጎልቶ አይታይም።
ሆኖም፣ ለኢየሱስ ተልዕኮ ስኬት የእርሱ ሚና ወሳኝ ነው።
ዮሐንስ 1:10-13ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ መንፈስ ቅዱስ ለመለወጥ አስፈላጊ
ስለመሆኑ ምን ያስተምረናል?
በዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያው ምዕራፍ እንኳን፣ የመንፈስ ቅዱስ ሚና ምን ያህል ማዕከላዊ እንደሆነ እንመለከታለን። ዮሐንስ ቃሉን የተቀበሉት፣ ማለትም በእርሱ ያመኑ ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ልጆች እንደ ሆኑ ይነግረናል፣ “እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ. 1:13)። ይህ የሚሆነው ከመንፈስ ቅዱስ ሥራ ብቻ ነው። የሚከተሉት ምንባቦች ስለ መንፈስ ቅዱስ ተግባራት ምን ይናገራሉ? ዮሐ. 3፡5-8፣ ዮሐ. 6፡63፣ ዮሐ. 14፡26፣ ዮሐ. 15፡26፣ ዮሐ. 16፡7-11።
“ክርስቶስ የመንፈስ ቅዱስን ተግባር በመግለጽ የእርሱን ልብ ባረካው ደስታና ተስፋ
ደቀ መዛሙርቱን ለማነቃቃት ፈለገ። ክርስቶስን ያስደሰተው ለቤተ ክርስቲያኑ የሚሆን እርዳታ
በገፍ መዘጋጀቱ ነው። ክርስቶስ ወገኖቹን ለማስከበር አባቱን ለምኖ ለማግኘት የሚችለው እጅግ
በጣም ከፍተኛ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ ነው። መንፈስ ቅዱስ የተሰጠው ምዕመናንን ለማደስና
ለማነቃቃት ሲሆን ያለ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስ የከፈለው መስዋዕት ውጤት አይኖረውም።
የሰይጣን ኃይል ለብዙ ዘመናት እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን ሰዎች ለዚህ ሰይጣናዊ ኃይል
ያሳዩት የተገዥነት መንፈስ አስገራሚ ነው። ኃጢአትን መከላከልና ማሸነፍ የሚቻለው ከሶስቱ
መለኮታዊ አካላት አንዱ በሆናውና ሙሉ መለኮታዊ ኃይል ባለው በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት
ብቻ ነው (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 708)።
እንግዲህ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆኑን የሚያረጋግጠውን መንፈስ ቅዱስን
መቀበል እንዴት ያለ በረከት ነው (ዮሐ. 3፡33)። ስለ ኃጢአት፣ ስለ ጽድቅ እና ስለ ፍርድ
የሚወቅሰው መንፈስ ነው (ዮሐ. 16፡8-11)። ስለዚህ፣ ትክክል የሆነውን፣ እውነት የሆነውን፣
ጥሩ የሆነውን እንድናውቅ ዋናው ቁልፍ፣ በሚወቅሰውና አሳማኝ በሆነው በመንፈስ ቅዱስ
ኃይል አማካኝነት የእኛን ምክንያትና የሕይወት ልምዳችንን ለእግዚአብሔር ቃል ማስገዛታችን
ነው።
የዮሐንስ ወንጌል 17 አንዳንድ ጊዜ የኢየሱስ የክነት ጸሎት ይባላል። ይህ የእርሱን
የስንብት ንግግር የሚያጠናቅቅ ነው። ኢየሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው የሰው ልጅ በመጨረሻ
ከእግዚአብሔር ጋር ወደነበረው ግላዊ ግንኙነት እንዲታደስ ነው። እግዚአብሔር እንዲሠራ
የሰጠውን ምልክት በታማኝነት ፈፀመ። በቃልም በተግባርም እግዚአብሔርን ለሰዎች
አስተዋውቋል።
ኢየሱስ በቅርቡ ከዚህ ምድር ወጥቶ ሊሄድ ነው። ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ፍቅር አንድ
ጊዜ ደግሞ ማካፈል ፈልጎ ነበር። በራሱ፣ በአብ እና በመንፈስ ቅዱስ መካከል ያለውን የጠበቀ
ግንኙነት እንዲገነዘቡ ፈልጓል። እናም ከእግዚአብሔር አብ እና እርሱ ራሱ ወደ ነበረው መንፈስ፣
ወደዚህ አንድ ዓይነት ግንኙነት ሊያመጣቸው ፈለገ።
ዮሐንስ 17:1-26ን ያንብቡ። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የኢየሱስን ፍላጎት፣ ማለትም
በእርሱ፣ በአብ እና በደቀ መዛሙርቱ መካከል ያለውን የፍቅር ግንኙነት በተመለከተ
የሚገልጹት የትኞቹ ቃላት ወይም ሀረጎች ናቸው?
ዮሐንስ 17ን ያነበቡ ብዙዎች፣ ብቸኛው የሚያስፈልገው ነገር አንድነት እና ፍቅር ነው
ብለው ይተረጉማሉ። አዎን ምንም አያጠያይቅም፣ የእግዚአብሔር አላማ ከእርሱ እና ከሁሉም
ሰዎች ጋር ቀድሞ ወደነበረው ግላዊ ግንኙነት እንድንመለስ ነው። ነገር ግን የበለጠ ጥንቃቄ
የተሞላበት ንባብ በፍቅር እና በእውነት መካከል በጣም አስፈላጊ የሆነ ግንኙነት እንዳለ
ይጠቁማል።
“እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ
ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” (ዮሐ. 17፡3)። ይህ ማለት እንግዲህ እኛ እግዚአብሔር
ነው ብለን እንደመሰለን አይደለም ማለት ነው። “…ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው።
… ቃልህንም ጠብቀዋል …” (ዮሐ. 17:6፣ 8)። “በእውነትህ ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው”
(ዮሐ. 17፡17)።
ክርስቶስ አብን ሊገልጥ መጣ። ይህ መገለጥ አስፈላጊ ነበር ምክንያቱም ስለ
እግዚአብሔር ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች ስላሉ። የዮሐንስ ወንጌል ኢየሱስ ይህን ተልእኮ ምን
ያህል በቁም ነገር እንደወሰደው ያሳያል። እርሱ የአምላክን ቃልና ድርጊት የወከለው በትክክል
ነበር። እውነት ለውጥ የማያመጣ ቢሆን ኖሮ ለምን የዚህን ያህል ርቀት መሄድ አስፈለገ?
ኢየሱስ ከባድ ችግር ያለበትን ሕይወት በመኖር፣ በመጨረሻም በኃይማኖት ባለ
ሥልጣናት ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ ተደረገ። ከሕዝቡና አልፎ ተርፎም ከራሱ ደቀ መዛሙርት
በተንጸባረቀው ግድየለሽነት ሲሰቃይ ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሰጠው፣ ሌላው
ሦስት ጊዜ ካደው። በማያቋርጥ ፈተና አልፎ ሊያድናቸው በመጡ ሰዎች እጅ በመስቀል ላይ
ተስቅሎ ሞተ።
በኢየሱስ እና በአብ መካከል ያለውን ዓይነት የእግዚአብሔር ፍቅር በራሳችሁ
ሕይወት ውስጥ እንዴት በተሻለ መንገድ ማንጸባረቅ ትችላላችሁ?
ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ከሚለው መፅሐፍ “ልባችሁ
አይጨነቅ” ገጽ 662-680፤ “Additional Note on [John] Chapter 1,” The
SDA Bible Commentary, vol. 5, pp. 911–919 ያንብቡ።
ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስ ማን እንደሆነ በሰዎች መመዘኛዎች ከገመገሙ በኋላ “ሥጋዊ
ፍርድ” ነበር የሰጡት (ዮሐ. 8፡15)። ይህ ምናልባት “በመልክ” ከመፍረድ የከፋ ነው (ዮሐ. 7፡
24)። እዚህ በወደቀው ዓለም ውስጥ፣ ያለ መንፈስ ቁጥጥር ሥር ሳይሆኑ የወደቀውን የሰው
ልጅ የሥጋን መመዘኛ ተጠቀሙ (ዮሐ. 3፡3-7ን ተመልከቱ)። “ሥጋ” የሆነውን አይተውታል፣
ነገር ግን ቃል ሥጋ ሊሆን እንደሚችል አላሰቡም ነበር (ዮሐ. 1፡14)። ክርስቶስን በጣም ውስን
በሆነ መስፈርት መመልከት እርሱን ከዓለማዊ እይታ አንጻር መመዘን ማለት ነው (2ቆሮ. 5፡
16)።
“አጽናኙ መንፈስ የእውነት መንፈስ ይባላል። የእርሱ ሥራ የእውነትን ምንነት
መግለጽና እውነትን መንከባከብ ነው። የእውነት መንፈስ ወደ ልብ ይገባና አጽናኝ ይሆናል።
ሰላምና መጽናናት የሚገኘው ከእውነት እንጂ ከሐሰት አይደለም። ሰይጣን በሰው አእምሮ ላይ
ስልጣን የሚኖረው በሐሰት ጽንሰ ሐሳቦችና ባሕላዊ ወጎች አማካይነት ነው። ሰዎችን በሐሰት
ሚዛን ራሳቸውን እንዲለኩ በማድረግ ባሕርይን ያዛባል። መንፈስ ቅዱስ ግን በቅዱሳን
መጻሕፍት አማካይነት መልእክት ወደ ሕሊናችን እንዲደርስ በማድረግ እውነትን በልባችን
ያትመዋል። በዚህ አካኋን ስህተትን እያጋለጠ ከሕሊና እንዲወጣ ያደርገዋል። ክርስቶስ
የመረጣቸውን ወገኖቹን ለእርሱ እንዲገዙ የሚያደርጋቸው በእግዚአብሔር ቃል ማካይነት
በሚሠራው በእውነት መንፈስ ነው” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 707)።
1. የዘላለም ሕይወት እግዚአብሔርን ማወቅ ነው (ዮሐ. 17፡3)። ስለ እግዚአብሔር
የተወሰኑ እውነታዎችን ማለትም እርሱ ኃያል ወይም አፍቃሪ ወይም የፍትህ
አምላክ ነው ብሎ ብቻ ከማወቅ በዘለለ እግዚአብሔርን ማወቅ ምን ማለት
ነው? አንድ ሰው “እግዚአብሔርን ታውቃለህ?” ብሎ ቢጠይቅህ ምን ትላለህ?
ኢየሱስ በመልስህ ውስጥ የሚካተተው እንዴት ባለ መልኩ ነው?
2. በተግባራዊ፣ በዕለት ተዕለት አነጋገር፣ ኢየሱስ “ቃልህ እውነት ነው” ማለቱ
ምንን ያመላክታል? (ዮሐ.17:17)።
3. ኢየሱስ ሲጸልይ፡- “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው
አልለምንም” አለ (ዮሐ. 17፡15)። ይህ ጸሎት በሕይወታችን ውስጥ ጥሩ ሆኖ
እንዲመለስ ከማድረግ አኳያ የራሳችን ምርጫዎች እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራሉ?