የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ.18:33-19:5፤ ዮሐ.
19:17-22፤ ዮሐ. 19:25-27፤ ሉቃስ 2:34፣ 35፤ ዮሐ. 20:1-18፤ 1ኛ. ቆሮ. 15፡12-20።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ጲላጦስም:- እንግዲያ ንጉሥ ነህን? አለው።
ኢየሱስም መልሶ፡- እኔ ንጉሥ እንደ ሆንሁ አንተ ትላለህ። እኔ ለእውነት
ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ፤ ከእውነት የሆነ ሁሉ ድምፄን ይሰማል አለው” (ዮሐ. 18፡37)።
የ
ኢየሱስ መስቀል እና ትንሳኤ የዮሐንስ ወንጌል ትልቁ መዳረሻ ነው። የመጀመሪያዎቹ
አሥር ምዕራፎች እስከ ሦስት ዓመት ተኩል የሚሆነውን ጊዜ የሚሸፍኑ ናቸው። ከምዕራፍ
11-20 በተቃራኒው ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንታትን ይሸፍናሉ።
አራቱ ወንጌሎች የኢየሱስን ሞት በተለያየ መንገድ ይገልጻሉ። ዘገባዎቻቸው እርስ
በርሳቸው የሚጣጣሙ ቢሆኑም፣ እያንዳንዱ ጸሐፊ በተለይ ከወንጌል መልዕክታቸው ጭብጥ
ጋር የሚስማሙ ቁልፍ ነጥቦችን አጉልተው ያሳያሉ። ማቴዎስ የቅዱሳት መጻሕፍትን ፍጻሜ
አጽንዖት ሲሰጥ፣ ማርቆስ በኢየሱስ ጥምቀት እና በመስቀል መካከል ባለው ትይዩ ሐሳብ ላይ
ያተኩራል፤ ሉቃስ መስቀሉን እንደ ፈውስ እና መዳን አድርጎ (በመስቀል ላይ ያለውን የሌባ ታሪክ
አያይዞ) ያቀርባል።
ነገር ግን ዮሐንስ መስቀሉን፣ በተለይም በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጊዜ እንደተጠቀሰው
በሰዓቱ ከሆነው ሃሳብ ጋር በማያያዝ እንደ ኢየሱስ ዙፋን አድርጎ ያቀርባል (ዮሐ. 7፡30፣ ዮሐ. 8፡
20፣ ዮሐ. 12፡27)። ሮማውያን ስቅለትን እጅግ የውርደት እና አሳፋሪ የሞት መንገድ አድርገው
የሚጠቀሙበት ስለነበር ይህ የዙፋን ፅንሰ ሃሳብ እንግዳ የሆነ ምስል ነው። ይህ ንጽጽር
የሚያመላክተው ዮሐንስ ያቀረበውን ጥልቅ እንግዳ መግለጫ ሲሆን፡- ኢየሱስ የኀፍረት ሞት
እየሞተ፣ ነገር ግን በተመሳሳይ ሰዓት እንደ አዳኝ በክብር ዙፋን ላይ መቀመጡን ያመላክታል።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለታኅሣሥ 12 ሰንበት ይዘጋጁ።
በዮሐንስ 18፡28-32፣ የኢየሱስ የፍርድ ሂደት በዝርዝር አልተገለጸም። ትኩረቱ የነበረው በጴንጤናዊው ጲላጦስ ፊት በቀረበው ኢየሱስ ላይ ነው። ዮሐንስ 18:33-38ን ያንብቡ። ጲላጦስ እና ኢየሱስ ስለ ምን ነበር የተነጋገሩት?
ገዥው ኢየሱስ የአይሁድ ንጉሥ እንደሆነ ጠየቀው (ዮሐ. 18፡33)። ይህ ማዕረጉ
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰበት ሥፍራ ሲሆን ነገር ግን የመጨረሻው አልነበረም። ኢየሱስ
ጲላጦስን ይህን ጥያቄ የጠየቀው ከራሱ ወይም ሌሎች እርሱ እንደሆነ ስላሉ ነው በማለት
ጠየቀው። ጥያቄው ጠረጴዛውን ወደ ገዥው በማዞር እርሱ ከማን ጋር እየተናገረ እንደነበረ
ተረድቶ እንደሆነ የሚያሳስብ ነበር። ይህንን የሚያነብ ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን ያውቃል። ገዥው
ግን ያውቅ ይሆን?
ጲላጦስም በጥያቄ ሲመልስ “እኔ አይሁዳዊ ነኝን? ወገኖችህና የካህናት አለቆች ለእኔ
አሳልፈው ሰጡህ፤ ምን አድርገሃል? አለው” (ዮሐ. 18:35)። ይህ ኢየሱስ ተግባራዊ አድርጎ
የጠየቀውን ጥያቄ ለማስወገድ በብስጭት የተጠየቀ ጥያቄ ነበር። ጭፍን ጥላቻ አመለካከቱን
እንዲገድበው በማድረግ ከእውነት የራቀ የገዢው የመጀመሪያ እርምጃ ነበር።
ኢየሱስ መንግሥቴ ከዚህ ዓለም አይደለችም ብሎ መለሰ (ዮሐ. 18፡36)።
ጲላጦስም ኢየሱስ ከንግግሩ ንጉሥ ነኝ እያለ እንደሆነ ወደ ድምዳሜ ደረሰ (ዮሐ. 18፡37)።
ይህም ኢየሱስን ለእውነት ለመመስከር መወለዱን እና “ከእውነት” የሆነ ሰው ሁሉ ድምፁን
እንደሚሰማ ወደ ገለጸው ጠቃሚ ማብራሪያ መራው (ዮሐ. 18፡37)።
ከዚያም ጲላጦስ፣ “እውነት ምንድን ነው?” ሲል ጠየቀ (ዮሐ. 18፡38)። ነገር ግን
መልሱን አልጠበቀም ነበር። ይልቁንም ኢየሱስን ከሕዝቡ ለማዳን ወደ ውጭ ወጣ።
እውነት የዮሐንስ ወንጌል ዋናው ሐሳብ (ጭብጥ) ነው። እንደ ዘላለማዊ ቃል (ሎጎስ፣
ዮሐ. 1፡1-5)፣ ኢየሱስ ብርሃን እና እውነት ነው። ይህ ሁሉ ከጨለማ እና ከስህተት ጋር ተቃራኒ
የሆነ ነው። እርሱ በጸጋና በእውነት የተሞላ ነው (ዮሐ. 1፡14)። ጸጋና እውነት በእርሱ በኩል
መጣ (ዮሐ. 1፡17)። መጥምቁ ዮሐንስ ስለ እውነት መስክሯል (ዮሐ. 5፡33)። ኢየሱስ
አባቱ “እውነት” መሆኑን አረጋግጧል (ዮሐ. 7፡28)። ኢየሱስ ራሱ እውነትን ከአባቱ ሰምቷል
(ዮሐ. 8፡40)። ኢየሱስ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” ነው (ዮሐ. 14፡6)። የእግዚአብሔር
ቃል “እውነት” ነው (ዮሐ. 17፡17)። ጲላጦስ በተሳሳተ አመላካከቱ፣ ቀደም ሲል ባደረጋቸው
ውሳኔዎችና ከደረሰበት ጫና የተነሳ እውነቱን የማወቅ አጋጣሚን አጣ።
ኢየሱስ እውነት ነው የሚለውን ሃሳብ እንዴት ትረዱታላችሁ?
ዮሐንስ 18:38-19:5ን ያንብቡ። ጲላጦስ ሕዝቡ ኢየሱስ እንዲፈታ እንዲጠይቅ ለማሳመን የሞከረው እንዴት ነበር?
ጲላጦስ እውነትን በተመለከተ ከኢየሱስ መልስ አልጠበቀም ነበር። ይልቁንም
ሕዝቡን ለማሳመን ወደ ውጭ ወጣ። ጲላጦስ ኢየሱስን በነፃ እንዲለቀቅ ከመፍቀድ ይልቅ
ከሕዝቡ ጋር በመነጋገር ራሱን ለችግር ዳርጓል። የኃይማኖት መሪዎቹ ገዥውን በሕዝቡ
አማካኝነት ለሚፈልጉት ዓላማ ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ አውቀው ነበር።
ጲላጦስ በፋሲካ ወቅት አንድ እስረኛን ነፃ የመልቀቅ ልማድን በመጥቀስ ሕዝቡ
“የአይሁድን ንጉሥ” እንዲፈታላቸው ይፈልጉ እንደሆነ ጠየቀ። በሚያስደንቅ እናም እንግዳ
በሆነ ሁኔታ ህዝቡ ንፁህ የሆነውን ኢየሱስን ሳይሆን በርባን የተባለውን ወንበዴ እንዲፈታ
ጠየቀ።
አሁን የኢየሱስ ፌዝ እና ውርደት የሚጀምርበት ጊዜ ደረሰ። የሮማውያን ወታደሮች
የእሾህ አክሊል ጐንጕነው፣ ቀይ ልብስ አለበሱትና ወደ እርሱ እየመጡ የአይሁድ ንጉሥ እያሉ
ማሾፍ ተያያዙ። የዚህ ዓይነት ሰላምታ ወታደሮቹ ለንጉሠ ነገሥቱ ከሚሰጡት የሰላምታ መንገድ
ጋር ይመሳሰላል፤ ነገር ግን ይህ አሁን በፌዝ ነበር የተከናወነው።
ጲላጦስ የሕዝቡን ርኅራኄ በመጠቀም ኢየሱስን የሚፈታበትን መንገድ እየፈለገ
ያለ ይመስላል። ኢየሱስ የእሾህ አክሊል ተጎንጉኖ እንዲጫንበትና ሐምራዊውን ልብስ ለብሶ
እንዲወጣ አደረገው። ትዕይንቱ፣ በዮሐንስ አስተያየት ባይሰጥበትም፣ ነገር ግን ኢየሱስ ፌዘኛ
የሆነውን የንጉሥ ልብስ ለብሶ፣ ገዥውም ሕዝቡን “እነሆ ሰውዬው!” (ዮሐ. 19፡5) ብሎ ሲጣራ
ያሳያል። ይህ በዮሐንስ 1፡29 ያለውን የመጥምቁ ዮሐንስን ቃል አንባቢው እንዲያስታውስ
ያደርጋል፣ “እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ!” አንድ የአሕዛብ ገዥ፣
መሲሑን በዚህ ንጉሣዊ ዓይነት አለባበስ በእስራኤል ፊት ማቅረቡ እጅግ እንግዳ የሆነ ድርጊት
ነበር።
ነገር ግን ሕዝቡ ዮሐንስ 19፡6-16 እንደሚያሳየው፣ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ
ነኝ ብሏል በሚለው መሠረት እንዲሰቀል ጠየቀ። ይህም የኢየሱስን መፈታት ይበልጥ
የሚፈልገውን ጲላጦስን አስፈራው። ነገር ግን መሪዎቹ ኢየሱስን መልቀቅ ቄሳርን መቃወም
ነው በማለት የኢየሱስን እጣ ፈንታ ያተሙ መሰለ። ጲላጦስ ለቄሳር ያለው ታማኝነት፣ ተመሳሳይ
ሚናን እጫወታለሁ የሚለውን ሰው ሊፈታ እንዳይችል እንደሚያደርገው ያውቃሉ። መሪዎቹ
ከቄሳር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም አሉ። ስለዚህ ሕዝቡ ለኢየሱስ ያላቸው ጥልቅ ጥላቻ
ከብሔራዊ ኩራታቸው የሚበልጥ ነበር። ይህንን ኢየሱስን ለማስወገድ፣ አገራዊ የሆነውን ራስን
በራስ የማስተዳደር መብትን እንኳን ለመሰዋት ፈቃደኞች ነበሩ።
ኢየሱስን ሊያውቁት የሚገባቸው የአገሩ መንፈሳውያን መሪዎች እንዲሰቀል
እየፈለጉ ሳለ በምትኩ አንድ አረማዊ ገዥ እሱን ሊፈታው መፈለጉን ማየት እንዴት
አስፈሪ ነገር ነው! ከዚህ ለራሳችን ምን ዓይነት ትምህርት እናገኛለን?
ዮሐንስ 19፡17-22 እንደሚያሳየው፣ ጲላጦስ በላቲን፣ በግሪክ እና በዕብራይስጥ
ቋንቋ “የአይሁድ ንጉሥ የናዝሬቱ ኢየሱስ” የሚል ጽሑፍ ጻፈ (ዮሐ. 19፡19)። የኃይማኖት
መሪዎቹ ይህ እንዲለወጥ ይፈልጉ ነበር። ጲላጦስ ግን አልፈቀደም ነበር፤ እናም ስለ ኢየሱስ
እውነት እና ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ በመስቀል ላይ እንደነገሠ ከሚጠቁሙት ምልክቶች አንዱ፣
ዝምተኛው ምሥክር የሆነው ጽሑፉ ከእርሱ ጋር አብሮ ተሰቀለ። እነሆ ኢየሱስ፣ በእውነት
ንጉሣቸው፣ አዎ የአይሁድ ንጉሥ፣ እንደ ተራ ወንጀለኛ በመስቀል ላይ ተንጠልጥሎ ይታያል።
“ያ ማስታወቂያ እንደዚያ ተጽፎ እንዲሰቀል ያደረገ ከአይሁዶችና ከጲላጦስ በላይ
የሆነ አንድ ኃይል ነበር። በእግዚአብሔር ጸጋ ይህ ማስታወቂያ ሰዎች ቅዱሳት መጻሕፍትን
እንዲመረምሩ ለማድረግ አሳባቸውን የሚቀሰቅስ ነበር” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣
ገጽ 791)።
ዮሐንስ 19:25-27ን ያንብቡ። የኢየሱስን እናት በተመለከተ በመስቀል ላይ ምን
ልብ የሚነካ ሁኔታ ተከሰተ?
በዚያን እለት በመስቀል ስር ከቆሙት መካከል የተወደደው ደቀ መዝሙር ዮሐንስ፣ የኢየሱስ እናት ማርያም እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከብዙ አመታት በፊት፣ ዮሴፍ እና ማርያም ኢየሱስን ሊያስባርኩት ወደ ቤተ መቅደስ ባመጡት ጊዜ ስምዖን ይህንኑ ተንብዮ ነበር (ከሉቃስ 2፡34፣ 35 ጋር አነጻጽሩ)። አሁን ኢየሱስ በሚሞትበት ጊዜ፣ እናቱን “አንቺ ሴት፣ እነሆ ልጅሽ አላት” እና ዮሐንስን ደግሞ፣ “እናትህ እነኋት አለው” (ዮሐ. 19፡26፣ 27)። ዮሐንስ 19:28-30ን ያንብቡ። ኢየሱስ እየሞተ ሳለ የተናገረው “ተፈጸመ” የሚለው ቃል ምን ትርጉም አለው?
በቁጥር 28 ላይ የግሪክ “ቴሎ” (teleō) የሚለው ግስ (መጨረስ፣ ማጠናቀቅ፣
ማከናወን) “ሁሉ እንደተፈጸመ” ተብሎ የተቀመጠ ሲሆን በቁጥር 30 ላይ “ተፈፀመ” ተብሎ
ጥቅም ላይ ከዋለው ግስ ጋር ተመሳሳይ ነው። በተጨማሪም፣ ተዛማጅ የሆነው “ቴሊዮ” (te-
leio) የሚለው ግስ (መጨረስ፣ ፍጹም ማድረግ) በቁጥር 28 ላይ የቅዱሳት መጻሕፍትን
ፍጻሜ በማመልከት “የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም” ተብሎ ተቀምጧል። ምንም እንኳን ትዕይንቱ
አሰቃቂ ቢሆንም፣ ሁሉም ነገር እየተፈጸመ፣ እየተሳካ፣ እየተጠናቀቀም ነበር።
ኢየሱስ፣ “ተፈጸመ!” ሲል፣ አብ እንዲሠራው የሰጠውን ሥራ በመፈጸም፣ በማጠናቀቅ
ላይ ነበር። ኢየሱስ “ተፈጸመ” ያለው ለእያንዳንዳችን ምን ትርጉም አለው?
የተጠናቀቀው ነገር ምንድን ነበር? ይህስ በሕይወታችን ላይ እንዴት ተግባራዊ ይሆናል?
ዮሐንስ 20:1-7ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የተገለጸው ነገር ለእኛ ያለው ጠቀሜታ ምንድን ነው?
ኢየሱስ የሞተው አርብ ከሰአት ረፋዱ ላይ ሲሆን፣ እሁድ እጅግ በማለዳ ላይ ደግሞ
ተነስቷል። የተቀበረበት ጊዜ ሰንበት ሊጀምር የተቃረበበት ስለሆነ (ዮሐ. 19፡42)፣ ግብዓተ
መሬቱ በፍጥነት ተፈጽሟል፤ ነገር ግን ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም ነበር። ኢየሱስን የቱንም
ያህል የሚወዱት ቢሆንም ተከታዮቹ የሰንበትን ቀን በማክበር ወደ መቃብር አልሄዱም ነበር
(ከማር. 16፡1፣ ሉቃስ 23፡56 ጋር አነጻጽሩ)። ሰንበት ካለፈ በኋላ፣ ሴቶች እሁድ በጥዋት ወደ
መቃብሩ ለማምጣት ሽቶ (ቅመማ ቅመሞችን) ገዙ። ሲመጡም በጣም ባስደነገጣቸው ሁኔታ
ድንጋዩ ተንከባሎ፣ መቃብሩ ባዶ ነበር።
መግደላዊት ማርያም በማለዳ ወደ መቃብሩ ከመጡት አንዷ ነበረች። ያየችውን
ለመንገር ወደ ጴጥሮስና ወደ ዮሐንስ ሮጠች። እነርሱም ሁለቱ ወደዚያ ሮጡ። ዮሐንስ ከጴጥሮስ
ቀድሞ በመጀመሪያ ደረሰ። ጎንበስ ብሎ ወደ ውስጥ ተመለከተና ኢየሱስ ተጠቅልሎበት
የነበረውን የተልባ እግር ልብስ በዚያ ተቀምጦ አየ። ነገር ግን እርሱ ወደ ውስጥ አልገባም ነበር።
ጴጥሮስ ግን ወደ ውስጥ ገባና ተቀምጦ የነበረውን የተልባ እግር ልብስ አየ። በኢየሱስ
ራስ ላይ የነበረውን የፊት መጎናጸፊያም ተመለከተ፣ ነገር ግን ከቀሩት ጨርቆች ጋር በአንድ ላይ
አልነበረም፤ ይልቅ ተጣጥፎ ለብቻው ተቀምጦ ነበር።
ዮሐንስ 20:8-10ን ያንብቡ። ተጣጥፎ የነበረው የፊት ጨርቅ ትርጉሙ ምን ነበር?
ጴጥሮስ ወደ መቃብሩ ከገባ በኋላ ዮሐንስ ደግሞ ገባ። ዮሐንስ 20፡8 ላይ ቃሉ ዮሐንስ
ወደ ውስጥ ገብቶ እንዳየና እንዳመነ ይናገራል። የመቃብር ልብሶች እዚያው ተጋድመው እና
የፊት መጎናጸፊያውም ተለይቶ ለብቻው ተጣጥፎ መቀመጡ ዮሐንስ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን
እንዲያምን ያደረገው ለምንድነው?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በመጀመሪያ መቃብሩ ለምን ባዶ ሆነ ብሎ ማሰብ
አስፈላጊ ነው። በጣም የተለመደው መልስ የመቃብር ዘራፊዎች ዘርፈውት ይሆናል የሚለው
ነው። ነገር ግን ይህ ማብራሪያ ከሦስት ምክንያቶች የተነሳ ውድቅ ይሆናል። በመጀመሪያ፣ ማቴዎስ
መቃብሩ እየተጠበቀ እንደነበረ ይነግረናል (ማቴ. 27፡62-66)፣ ይህም የመቃብር ዝርፊያን
የማይመስል ያደርገዋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ የመቃብር ዘራፊዎች በተለምዶ የሚሰርቁት ውድ የሆኑ
ዕቃዎችን እንጂ እየበሰበሰ ያለን አስክሬን አይደለም። ሦስተኛ፣ የመቃብር ዘራፊዎች ተግባራቸውን
በጥድፊያ የሚያከናውኑ ስለሆነ የመቃብር ልብስን አያጣጥፉም። ለዚህ ነው ዮሐንስ የፊት
መጎናጸፊያውን ታጥፎ ባየ ጊዜ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ ማመኑ ምንም የማያስደንቀው።
ዮሐንስ 20:11-13ን ያንብቡ። ከዚህ ላይ መግደላዊት ማርያም ስለ ባዶው መቃብር ትርጉም እንዳልተረዳች የሚያሳያው ነገር ምን ነበር?
ከዚህ ጥቅስ በፊት ከማርያም ጋር ተያይዞ የተጠቀሰው ቃል፣ ማርያም ለጴጥሮስና
ለዮሐንስ ስለ ባዶ መቃብሩ የነገረቻቸውን አካቷል (ዮሐ. 20፡2)። እነርሱም ወደ መቃብሩ ሮጡ፣
እሷም ትንሽ ቆይታ ከዚያ ተመለሰች። ጴጥሮስና ዮሐንስ መቃብሩን ከመረመሩ በኋላ ትተውት
ሄዱ። ማርያም ግን እንደገና ተመልሳ እያለቀሰች እዚያ ቆየች። ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ብዙ
እንዳለቀሰች ምንም ጥርጥር የለውም። እና አሁንም ይህ ቀጥሏል? ጎንበስ ብላ ወደ መቃብሩ
ውስጥ ተመለከተች።
እርሷን በሚያስገርም ሁኔታ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክት በመቃብሩ ውስጥ፣
የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረበት ቦታ ተቀምጠው ነበር። “አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ?”
ብለው ጠየቁአት (ዮሐ. 20፡13)። የእርሷ ሕመም ያለበት ምላሽ ጌታዋን እንደወሰዱትና ወዴት
እንዳኖሩት አላውቅም የሚል ነበር።
ዮሐንስ 20:14-18ን ያንብቡ። ለማርያም ሁሉንም ነገር የለወጠው ምንድን ነበር?
ማርያም እንባ በተሞሉ አይኖቿ ዘወር ብላ አንድ ሰው ከኋላዋ ቆሞ አየች።
ከመላእክቱ ቃላት ጋር በሚመሳሰል መልኩ እንግዳው “አንቺ ሴት፣ ለምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ
ትፈልጊያለሽ?” (ዮሐ. 20:15) ብሎ ጠየቃት። እርሷ ግን አትክልተኛውን እያነጋገረች መስሏት
የኢየሱስን አስከሬን ለማግኘት ይረዳ እንደሆነ ጠየቀችው።
እንግዳው “ማርያም” በማለት አንድ ቃል ተናገረ። ዓለምን የለወጠው የአንድ ቃል
መገለጥ ነበር። ወዲያውኑም፣ የተገረመችው ማርያም ከሞት የተነሳው ኢየሱስ እያነጋገራት
እንደነበር ተገነዘበችና ጠራችው። ኢየሱስ የግድ ወደ አባቱ መውጣት ስላለበት እርሱን
እንዳትነካው ተናገራት። ነገር ግን የእርሷ የሥራ ድርሻ የነበረው ሄዳ ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ
አባቴና ወደ አባታችሁ፣ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ’” (ዮሐ. 20፡17) ባለው መሠረት ወደ
ሰማይ እንደሚያርግ መንገር ነው። ማርያም ተልዕኮዋን ተወጣች። እርሷም ጌታን እንዳየችው
ለደቀ መዛሙርቱ ነገረቻቸው እናም የቀረውንም ከእርስዋ ጋር የተነጋገረውን ዝርዝር ነገሮች
አካፈለቻቸው (ዮሐ. 20፡18)።
1ኛ ቆሮንቶስ 15:12-20ን ያንብቡ። ጳውሎስ እንደተናገረው ክርስቶስ ከሙታን
ካልተነሣ የክርስትና እምነታችን ጥቅሙ ምን ላይ ነው?
ከኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ከሚለው መፅሐፍ “ተፈፀመ”
ገጽ 758-764፤ “ለምን ታለቅሻለሽ?” ገጽ 788-794 ያንብቡ፤ እንዲሁም Clifford
Goldstein, Risen: Finding Hope in the Empty Tomb (Nampa, ID:
Pacific Press, 2020) ተመልከቱ።
“ጲላጦስ የሱስን ለማዳን ጉጉት ነበረው፣ ነገር ግን የሱስን ከሞት ማዳን ማለት
ማዕረጉንና ክብሩን ማጣት ማለት መሆኑን አወቀ። ዓለማዊ ሥልጣኑን ከማጣት ንጹሁን
ነፍስ አሳልፎ መስጠትን መረጠ። ክስረት ወይም ስቃይ እንዳይደርስባቸው በማለት ጲላጦስ
እንዳደረገው ሁሉ መርሕን የሚጥሱ ስንት ናቸው? ሕሊናና ግዴታ ወደ አንድ አቅጣጫ ሲያመለክቱ
ራስ ወዳድነት ግን ወደ ተቃራኒ አቅጣጫ ያመለክታል። ማዕበሉ የሚገፋው ወደተሳሳተ አቅጣጫ
ስለሆነ ከኃጢአት ጋር የሚደራደር ሁሉ ተጠርጎ ወደ ኃጢአት ጨለማ ይገባል” (ኤለን ጂ ዋይት፣
የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 782)።
“ክርስቶስ የመጣበትን ተልእኮ ሳያከናውን ሕይወቱ አላለፈችም፤ ስለሆነም
የመጨረሻ እስትንፋሱን በተነፈሰ ጊዜ “ተፈፀመ” ሲል ጮኸ። ዮሐ. 19፡30። ጦርነቱ በድል
ተፈፀመ። የሱስ ድልን የተጎናጸፈው በራሱ ኃይል ነው። ድል በማድረጉም ሰንደቅ ዓላማውን
ከሁሉ በላይ ከፍ አድርጎ ሰቀለ። መላእክትስ በዚህ ድል አልተደሰቱምን? በየሱስ አሸናፊነት
ሰማየ ሰማያት የድል ተሳታፊ ሆኑ። ሰይጣን ድል ተመታ፣ መንግሥቱንም እንዳጣ አወቀ።
“ለመላእክትና በኃጢአት ላልተበከሉት ዓለማት ተፈፀመ የሚለው አነጋገር ጥልቅ
ትርጉም ያለው ነው። ታላቅ የማዳን ሥራ መጠናቀቁ እንደ እኛ ለእነርሱም ጠቀሜታ አለው።
ምክንያቱም የክርስቶስ ድል አድራጊነት የሚያስገኘውን ውጤት ከእኛ ጋር ይሳተፋሉና” (ኤለን
ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 804)።
1. ጲላጦስ የሠራውን ዓይነት ስህተት እንዳትሠሩ ሊረዷችሁ የሚችሉ የውሳኔ
አሰጣጥ ሂደቶች ምንድን ናቸው?
2. ኢየሱስ በእኛ ቦታ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው? ለምንስ ምትካችን
መሆን አስፈለገው? እኛ መዳን ካለብን የእርሱ ሞት ለምን አስፈለገ?
መልሳችሁንስ የሚደግፉት የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ናቸው?
3. በኢየሱስ ትንሣኤ ማመንን በተመለከተ በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎችና
በታሪክ ማስረጃዎች መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው? የኢየሱስን
ትንሣኤ በብርቱ የሚያረጋግጡት ታሪካዊ ማስረጃዎችስ ምንድን ናቸው?
4. ስለ 1ኛ ቆሮንቶስ 15፡12-20 አስቡ። “በክርስቶስ ያንቀላፉት” ወዲያውኑ ወደ
ሰማይ የሚሄዱ ከሆነ፣ ያለ ክርስቶስ ትንሣኤ “ በክርስቶስ ያንቀላፉት ደግሞ
ጠፍተዋላ” (1ኛ ቆሮ. 15:18) የሚለውን ቃል፣ አንድ ሰው ትርጉም የሚሰጥ
ሊያደርግ የሚችለው እንዴት ነው? እዚህ ላይ የጳውሎስ ቃላት፣ ሙታን
በክርስቶስ ዳግም ምፅአት ጊዜ እስከሚሆነው ትንሣኤ ድረስ በእንቅልፍ ላይ
ናቸው የሚለውን እውነት የሚያረጋግጡት እንዴት ነው?