የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡1–5፣ ዘፍ. 1፡1፣
ዮሐ.1፡9–13፣ ዮሐ. 3፡16–21፣ ዮሐ. 9፡35–41፣ ማቴ. 7፡21–23፣ ዮሐ. 17፡1-5።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም
በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ”
(ዮሐ 1፡1)
የመጀመሪያው ሳምንት ስለ ዮሐንስ ወንጌል የመጨረሻ ክፍል የሚናገር ሲሆን፣ ይህም
ወንጌሉን ለምን እንደጻፈ ያስረዳል። የዚህ ሳምንት ትምህርት ዮሐንስ በመንፈስ ቅዱስ
አነሳሽነት አንባባቢዎቹን ሊወስድ ያሰበበትን አቅጣጫ ወደሚያመላክትበት የወንጌሉ
መጀመሪያ ይመለሳል። የሐዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ብዙውን ጊዜ በጽሑፋቸው የመጀመሪያ
ቃላትና አንቀጾች ውስጥ ለመሸፈን ያሰቡትን ጭብጥ ያቀርባሉ። ዮሐንስም እንዲሁ፣ ከፍጥረት
በፊትም ያሉትን ጨምሮ ወደ ኋላ በመመለስ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠቃሚ እውነቶችን
ስለሚያሳዩ ትልልቅ ሀሳቦች ይናገራል።
በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ያለው ይህ አቀራረብ፣ ኢየሱስ መሲሑ መሆኑን ካወቀ
በኋላ የጻፈው ስለሆነ፣ በመጽሐፉ በራሱ ውስጥ ያሉት ገጸ ባህሪያት እንኳ ሊያገኙት ዕድሉ
ያልነበራቸውን ጥቅም ለአንባቢዎች ይሰጣል። ወንጌላዊው የየሱስን ታሪክ ሲናገር ወደኋላ
ተመልሶ የሚመለከታቸውን ታላላቅ ጭብጦች አንባቢው በግልፅ ማየት ይችላል። እነዚህ
ታላላቅ ጭብጦች የተቀመጡት በኢየሱስ ምድራዊ ሕይወት ታሪካዊ ጊዜ ውስጥ ነው።
የዚህ ሳምንት ትምህርት ከመቅድሙ በመጀመር (ዮሐ. 1፡1-18) ዋና መሪ ሃሳቦችን
ጠቅለል አድርጎ ይመለከታል። እነዚህን ጭብጦች በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሌሎች
ቦታዎችም እንመለከታቸዋለን።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 9 ሰንበት ተዘጋጁ።
ዮሐንስ 1:1-5ን ያንብቡ። እነዚህ ቃላት “ቃል” ስለሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምን ያሳያሉ?
የዮሐንስ ወንጌል የሚጀምረው በዚህ አስደናቂ ሐሳብ ነው፦ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ
ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” (ዮሐ. 1፡1)። ይህ ውብ ዓረፍተ
ነገር በቀላሉ ልንረዳው የማንችለውን ጥልቅ ሐሳብ ይዟል።
ልክ ሲጀምር፣ ወንጌላዊው “በመጀመሪያ” የሚለውን የፍጥረት ታሪክን፣ ከዘፍጥረት
1፡1 ላይ ጠቅሷል። ቃሉ (ኢየሱስ) ሰማይና ምድር ከመኖራቸው በፊት አስቀድሞ ነበር። በዚህም
ዮሐንስ የኢየሱስን ዘላለማዊ ህያውነት ያረጋግጣል።
በመቀጠል በዮሐንስ 1፡18 “ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” ሲል ዮሐንስ “በአብ
እቅፍ ውስጥ እንዳለ” አመልክቷል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል
ብንሞክር አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን፦ ኢየሱስና አብ በጣም ቅርብ ናቸው።
ከዚያም፣ “ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ይላል። ግን ቃሉ እንዴት ከእግዚአብሔር ጋርም
እግዚአብሔርም ሊሆን ይችላል? መልሱ የሚገኘው ከግሪኩ ነው። የግሪኩ ቋንቋ የተወሰነ
አመልካች ቅጽል (definite article “the”) ሲኖረው፣ ነገር ግን ያልተወሰነ አመልካች ቅጽል
(indefinite article “a/an”) የለውም። ለእኛ አስፈላጊ የሆነው፣ የግሪኩ የተወሰነ አመልካች
ቅጽል (definite article “the”) የሆነው አንድን የተወሰነ ነገር ወይም ግለሰብን የሚያመለክት
መሆኑ ነው።
“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ” በሚለው ሐረግ ውስጥ “እግዚአብሔር”
የሚለው አገላለጽ አመልካች ቅጽሉ ስላለው አንድን ግለሰብ ማለትም አብን ያመለክታል።
“ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” በሚለው ሐረግ ውስጥ ግን፣
«እግዚአብሔር» የሚለው ቃል አመልካቹ ቅጽል የለውም፤ ስለሆነም በዚህ አገላለጽ ውስጥ
ይህ የመለኮትን ባህሪያት ያመለክታል። ኢየሱስ አምላክ ነው እንጂ አብ አይደለም፤ ነገር ግን
አሁንም መለኮታዊው የእግዚአብሔር ልጅ፣ የመለኮት ሁለተኛ አካል ነው።
ዮሐንስ 1:3፣ 4 ኢየሱስ የፍጥረት ሁሉ ፈጣሪ እንደሆነ ስለሚናገር ሐዋርያው ይህን
መረዳት ያረጋግጣል። በአንድ ወቅት ያልነበረ. ነገር ግን ወደ ሕልውና የመጣው ነገር ሁሉ
የሆነው በፈጣሪ አምላክ በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው።
“ከዘለዓለም ጀምሮ ጌታ የሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር ነበረ። እርሱም የእግዚአብሔር
አምሳያ ነበር። የታላቅነቱና የግርማው አምሳያና የክብሩ አንጸባራቂ ነበረ” (ኤለን ጂ ዋይት፣
የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 9)።
ለምንድን ነው የክርስቶስ ሙሉ መለኮታዊነት የትምህርታችን አስፈላጊ አካል የሆነው?
በማንኛውም መንገድ ኢየሱስ ፍጡር ቢሆን ኖሮ ምን እናጣለን? መልሶቻችሁን በሰንበት ቀን
ወደ ሰንበት ትምህርት ክፍል አምጡና የክርስቶስ ዘላለማዊ አምላክነት ለእምነታችን ለምን
አስፈላጊ እንደሆነ ለመወያየት ተዘጋጁ።
ዮሐንስ 1:1-3፣ 14ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር ራሱ ምን እንዳደረገ ይነግሩናል — ይህ እውነት እስካሁን ካወቅነው ሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ዮሐንስ ወንጌሉን የጀመረው “ኢየሱስ” በሚለው ስም ወይም እርሱ እንደ መሲሕ/
ክርስቶስ ባለው ሚና ሳይሆን፣ ቃል (ሎጎስ) በሚለው ነው። ዮሐንስ በጻፈበት ዘመን የተለያዩ
ፍልስፍናዎች ሎጎስ የሚለውን ቃል የአጽናፈ ዓለሙን (ሕዋን) ምክንያታዊ መዋቅር ወይም
የአመክንዮ እና የማመዛዘን ሃሳብን ለማመልከት ተጠቅመውበታል።
እንዲሁም፣ ተደማጭነት ያለው የጥንት ፈላስፋ ፕላቶ ያስተማረው ትምህርት
የገሀዱን እውነት በሁለት ጎራዎች ከፍሎ ነበር። አንደኛው ምሉዕ ፍፁምነት ያለበት፣ ሰማያዊ
እና የማይለወጥ ግዛት ነው። ሌላው እዚህ ምድር ያለው ግዛት ነው፡— የሚበላሽ፣ የሚለወጥ፣
በጣም ፍጹም ያልሆነው፣ አለ ተብሎ በሚታሰብበት በየትኛውም ሥፍራ ሁሉ ፍጹም የሆነውና
ከላይ ያለው ግዛት ውክልና ያለው። (ከላይ ያለው የት እንዳለ ግን ፕላቶ ጥያቄውን በጭራሽ
አልመለሰም)። አንዳንድ ፍልስፍናዎች “ቃል/ሎጎስ”ን በዘላለማዊ እና በሚበላሹ ምድራዊ
አካላት መካከል ረቂቅ የሆነ መካከለኛ ነገር ነው ብለው አስቀምጠዋል።
ዮሐንስ ቃሉን የተጠቀመው ፍጹም በተለየ መንገድ ነው። እውነት የሆነው ቃል (ሎጎስ)፣
በሰማይና በምድር መካከል የሚንሳፈፍ የማይጨበጥ እና ረቂቅ ፅንሰ-ሀሳብ አለመሆኑን
ያስረግጣል። ቃል (ሎጎስ) ማንነት ያለው አካል ነው፦ የሱስ ክርስቶስ ሥጋ ሆኖ በእኛ አደረ (ዮሐ.
1፡14)።
ለዮሐንስ ሎጎስ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ አምላክ ግንኙነት
አደረገ፤ ማለትም ራሱን ለሰው ልጆች እጅግ በጣም ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ገለጠ፣
እግዚአብሔር ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ። በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ ሎጎስ የሚወክለው፣ ወደ ጊዜና
ቦታ የሚገባውን፣ የሚናገረውን፣ የሚሠራውንና ከሰዎች ጋር በግለሰብ ደረጃ የሚዛመደውን
ዘላለማዊውን አምላክ ነው። ዘላለማዊው አምላክ ከእኛ እንደ አንዱ ሰው ሆነ ነው።
በዮሐንስ 1፡14 ላይ ሐዋርያው ቃል (ሎጎስ) “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም
ተመልቶ በእኛ አደረ” ሲል አመልክቷል። አደረ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ድንኳን
መትከል የሚለውን ትርጉም ይይዛል። ዮሐንስ በዘጸአት 25:8 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን
በመካከላቸው ያድር ዘንድ መቅደስን (የማደሪያ ድንኳን) እንዲሠሩ የነገራቸውን እየጠቀሰ
ነው። በተመሳሳይ መልኩ፣ በተዋሕዶ (በመለኮት ሥጋ መልበስ)፣ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው
ኢየሱስ፣ ሰዎች ከእርሱ ጋር እንዲገናኙ ክብሩን ሸፍኖ ወደ ሰው ሥጋ ገባ።
ዮሐንስ እዚህ ጋ የጻፈው አንድምታ ላይ እንቆይ። ፈጣሪ እግዚአብሔር ራሱ ከእኛ እንደ
አንዱ ሰው ሆኖ እዚህ በመካከላችን ኖረ። (ለእኛ ሲል ለእኛ ሞተ ወደሚለው እንኳን ገና
አልደረስንም!) ይህ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስላለው ፍቅር እውነታ ምን ይነግረናል?
ከዚህ አስደናቂ እውነት ይህን ያህል መጽናናትን ማግኘት ያለብን ለምንድን ነው?
ዮሐንስ 1:9-13ን ያንብቡ። ዮሐንስ እዚህ ላይ ሰዎች ለኢየሱስ እንዴት ምላሽ እንደሚሰጡ በምን ዓይነት ጠንካራ ሐቅ እየገለጸ ነው?
በዮሐንስ 1፡1-18 ያለው መቅድም ቃል (ሎጎስ) የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ማን እንደሆነ
ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ከእርሱ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዳላቸውም
ጭምር ይገልጻል። በዮሐንስ 1፡9 ላይ ወደ ዓለም ለሚመጣው ሰው ሁሉ የሚያበራ እውነተኛው
ብርሃን ተብሏል። ያ ብርሃን ዓለምን ያበራል፣ ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርገዋል። ሲ ኤስ ሉዊስ
እንዲህ ሲል ያስቀምጣል፦ “ፀሐይ ወጥታለች ብዬ የማምነውን ያህል በክርስትና አምናለሁ፣
በማየቴ ብቻ ሳይሆን በሱ ሁሉንም ነገር በማየቴ ነው።” “ነገረ መለኮት ቅኔ ነውን?” (n. p.:
Samizdat University Press, 2014), p. 15, originally presented 1944)።
እንዲሁም፣ ዮሐንስ 1፡9 የሚናገረውን አንድምታ እንመልከት። ብርሃን ወደ ሁሉም
ይመጣል፣ ነገር ግን ብርሃኑን የሚቀበለው ሁሉም ሰው አይደለም። በነገው ጥናት ላይ
እንደምንመለከተው፣ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ዋናው ጭብጥ ሰዎች ኢየሱስን እንዴት
እንደሚቀበሉ ወይም እንደማይቀበሉት ነው። ያ ጭብጥ የሚጀምረው ከዚህ ነው። በጣም
የሚያሳዝነው መሲሑ ወደ ህዝቡ ማለትም ወደ እስራኤላውያን መጣ፣ ነገር ግን ብዙዎች እንደ
መሲህ አልተቀበሉትም ነበር።
በሮሜ 9-11፣ ጳውሎስ ብዙ አይሁዶች ኢየሱስን ስላለመቀበላቸው ተመሳሳይ
አሳዛኝ ጭብጥ ተናግሯል። ነገር ግን ጳውሎስ አሉታዊ ነገርን በመናገር ብቻ አላበቃም፤ ብዙ
አይሁዶች ደግሞ ከአሕዛብ ጋር ኢየሱስን መሲሕ አድርገው እንደሚቀበሉ በመናገርም እንጂ።
በእርግጥም አሕዛብ በአይሁድ ላይ እንዳይመኩ ያስጠነቅቃል። “አንተ በፍጥረቱ የበረሀ
ከነበረ ወይራ ተቆርጠህ እንደ ፍጥረትህ ሳትሆን በመልካም ወይራ ከገባህ፥ ይልቁንስ እነዚያ
በፍጥረታቸው ያሉት ቅርንጫፎች በራሳቸው ወይራ እንዴት አይገቡም?” (ሮሜ 11:24)።
በተመሳሳይ መልኩ፣ ኢየሱስን እንደ አዳኛቸው የሚቀበሉ ሁሉ የእግዚአብሔር
ልጆች እንደሚሆኑ ዮሐንስ ተናግሯል። ይህ የሚሆነው በስሙ በማመን ነው። (ዮሐ. 1:12ና
13ን እንመልከት።) በወንጌሉ መቅድም እና መደምደሚያ መካከል ያለው ትስስር ይህ ነው።
በዮሐንስ 20፡31 ሐዋርያው [ወንጌሉን] ለምን እንደ ጻፈ አቅርቧል፡— “ነገር ግን የሱስ እርሱ
ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ ታምኑ ዘንድ፥ አምናችሁም በስሙ ሕይወት ይሆንላችሁ
ዘንድ ይህ ተጽፎአል።” ስለዚህ መግቢያው እና መደምደሚያው በመካከላቸው ያለውን ሁሉ
የሚያጠቃልሉ ሆነው ተዛማጅ ጽንሰ-ሐሳቦች በመያዝ አንድነትን ይፈጥራሉ። ይህ ትስስር
ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ አዳኛቸው በማመን እንዲድኑ የሚለውን የዮሐንስ ወንጌል ዋና
ግብ ያመለክታል።
የእግዚአብሔር ልጅ በመሆንህ ወይም በመሆንሽ ሕይወትህ/ህይወትሽ እንዴት
ተለውጧል?
ዮሐንስ 3፡16-21፣ ዮሐንስ 9፡35-41፣ እና ዮሐንስ 12፡36-46ን ያንብቡ። እነዚህ ጽሑፎች በመቅድሙ ውስጥ የሚገኘውን የማመንን/አለማመንን ጭብጥ እንዴት ይደግማሉ?
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ የሰው ልጅ በሁለት ዋና ዋና ቡድኖች የተከፈለ ይመስላል፦
በኢየሱስ አምነው እንደመሲህ የተቀበሉት እና የማመን እድል አግኝተው፣ ነገር ግን ላለማመን
የመረጡት።
ደቀ መዛሙርቱ ከመጀመሪያው ጎራ ውስጥ ናቸው፤ ልክ እንደ ኒቆዲሞስ (ቀስ በቀስ
ወደ እምነት የመጣው)፣ በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ የነበረችው ሴት፣ እና ዐይነ ሥውር ሆኖ
የተወለደው ሰው። በሁለተኛው ቡድን ውስጥ ፈሪሳውያን እና ሊቃነ ካህናት፣ አምስት ሺህ
ሰዎችን ሲመግብ ተአምር የተመለከቱ ሰዎች እና ሌላው ቀርቶ ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ የሆነው
ይሁዳ ይገኙበታል።
የሚገርመው፣ “እምነት” ወይም በግሪክ “ፒስቲስ” (pistis) የሚለው ሥማዊ አገባብ
ያለው ቃል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ፈጽሞ አለመታየቱ ነው። ይሁን እንጂ “ማመን” “ፒሲቲኦ”
(pisteu) የሚለው ግስ 98 ጊዜ ተጠቅሷል። በአጠቃላይ በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ከ241
ጊዜ በላይ! ይህ ግስ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በጣም ትልቅ ጭብጥ ነው። ከሥም ይልቅ
የዚህ የግስ አጠቃቀም ክርስቲያን የመሆንን በጣም ንቁ ስሜት ሊያመለክት ይችላል። በኢየሱስ
ማመን እኛ የምንተገብረው ነገር ነው፣ እናም እንዴት እንደምንኖር ይገለጻል እንጂ እንዲሁ
በኃይማኖቶች ውስጥ መሆንን አይደለም። እንደምናውቀው፣ ዲያብሎስም እንዲሁ በየሱስ
ያምናል (ያዕቆብ 2፡19 ይመልከቱ)።
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ዋነኛው ልዩነት ከኢየሱስ
ጋር ያላቸው ግንኙነት ነው። አማኞች፣ ወይም ያመኑት፣ ሲቃወማቸው ወይም ሲገስጻቸውም፣
ለእርሱ ግልጽነት አላቸው። ወደ ኢየሱስ ይመጣሉ እንጂ ሸሽተው አይሄዱም። እርሱ
የሚያበራላቸው ብርሃን ነው። እናም በእምነትና በማመን የእግዚአብሔር ልጆች ይሆናሉ።
የማያምኑት ግን በተለምዶ እርሱን ለመቃወም ወደ ኢየሱስ ይመጣሉ። ከብርሃን
ይልቅ ጨለማን የሚወዱ ሰዎች በመሆን ተለይተው ይታወቃሉ። ንግግሩን መቀበል
ይከብዳቸዋል ወይም ያረጁ ወጎቻቸውን ሲጥስ እና የጠበቁትን ሳይፈጽም ያዩታል። የእርሱ
ብርሃን እንዲዳኛቸውና እንዲመዝናቸው ከመፍቀድ ይልቅ በእርሱ ላይ ለመፍረድ ይቆማሉ።
ነገር ግን እንደ ሕዝቡ መንፈሳዊ መሪዎች ኢየሱስን ለመቀበል የመጀመሪያዎቹ ሊሆኑ ሲገባ፣
ይህ አመለካከት በኃይማኖት መሪዎች ዘንድ በተደጋጋሚ ታይቷል።
የሱስ መሲሕ መሆኑን በአእምሮ ከማወቅ ባለፈ፣ እምነታችሁን እንዴት ነው
በሕይወታችሁና በኑሯችሁ የምትገልጡት? ልዩነቱን ማወቅ ለምን አስፈለገ?(ማቴ.
7:21–23 ተመልከቱ)።
ዮሐንስ 17:1-5ን ያንብቡ። ኢየሱስ፣ “አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።” ሲል ምን ማለቱ ነበር?
የትናንቱ ጥናት በኢየሱስ ማንነት እና በሚሠራው ሥራ ላይ በማጠንጠን፣ የዮሐንስ ወንጌልን ምድራዊ፣ የሰው ታሪክ፣ በሰዎች መካከል ያለውን ግጭትና መስተጋብር አንስቶ
ተመልክቷል። የዛሬው ጥናት የሚያተኩረው አሁንም በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በሚገኘው
መለኮታዊ፣ ሰማያዊ ታሪክ ላይ ነው።
መቅድሙ የሚጀምረው በዚያ የሰማይ ታሪክ ነው። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ፣
የአጽናፈ ሰማይ ፈጣሪ ሆኖ ቀርቧል። አሁንም ከዚያ በፊት ያልነበረ ነገር ግን ወደ ሕልውና
የመጣው ነገር ሁሉ የሆነው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው። “ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነውም አንዳች
ስንኳ ያለ እርሱ አልሆነም” (ዮሐ. 1:3)። ነገር ግን በሥጋ መልበስ (በተዋሕዶ) ሰው የመሆኑን
ክብር እያስታወሰ ይቀጥላል (ዮሐ. 1፡14)። ዮሐንስ እነዚህ ትርጉሞች ያሏቸውን “ክብር” (“dox-
sa” ብርሃን፣ ግርማ፣ ዝና፣ ክብር)፤ ማክበር (“doxsazo” ማሞገስ፣ ማክበር፣ ከፍ ማድረግ፣)
የሚሉት ቃላትን ይጠቀማል። ከሰዎች ክብርን ስለማግኘት እና ከእግዚአብሔር ክብርን ወይም
ግርማን ስለማግኘት ሁለቱንም ይናገራል።
በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ ኢየሱስን የማክበር ሐሳብ ከእርሱ ሰዓት፣ ማለትም፣
ከመሞቱ ጊዜ ጽንሰ-ሐሳብ ጋር የተያያዘ ነው። (ከዮሐ. 2፡4፣ ዮሐ. 7፡30፣ ዮሐ. 8፡20፣ ዮሐ. 12፡
23–27፣ ዮሐ. 13፡1፣ ዮሐ. 16፡32፣ ዮሐ. 17፡1 ጋር አነጻጽሩ) መስቀል የእርሱ የክብር ሰዓት ነው።
ይህ ሐሳብ እርስ በርሱ የሚቃረን ነው፤ ምክንያቱም ስቅለት በጥንት የሮማውያን ዓለም
እጅግ አሳፋሪ እና አዋራጅ የሞት ቅጣት መንገድ ነበር። ይህ የማይታመን ልዩነት፣ የአምላክ
በመስቀል መሞት፣ የሰው ሴራ ታሪክ ከመለኮት ጋር መጠላለፉን ያሳያል።
በሰው ደረጃ፣ ኢየሱስ፣ የተናቀው ወንጀለኛ በድካም “አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን
ተውከኝ?” ብሎ በሥቃይ በመጮህ ሞተ። ይህ ሰዋዊ የሆነ የመስቀሉ ጨለማ አንዱ ጎን በተለይ
በማቴዎስ እና በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ቀርቧል (ማቴ. 27፡46 ማር. 15:34)።
ነገር ግን የመስቀሉ የክብር ሌላው ጎን በተለይ በሉቃስ እና በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ
ቀርቧል (ሉቃስ 23፡32–47፣ ዮሐ. 19፡25–30)። ይህም የመዳን፣ የምሕረት እና የእግዚአብሔር
ልጅ ራሱን ለአባቱ የሚሰጥበት ቦታ ነው። እንዴት ያለ ተቃርኖ ነው! የእግዚአብሔር ታላቅ ክብር
የሚገለጠው የዓለምን ኃጢአት በራሱ ተሸክሞ እጅግ በመዋረዱ ውስጥ ነው።
እኛን ከኃጢአት ሊያድነን አምላክ ራሱ በመስቀል ላይ እንዲህ ያለ ከባድ ነገር
ወሰደ ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስቡ። ይህ ኃጢአት እንዴት መጥፎ እንደሆነ
ምን ሊነግረን ይገባል?
ኤለን ጂ ዋይት፣ «እግዚአብሔር ከእኛ ጋር» በዘመናት ምኞት፣ ገጽ
19-26።
“ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መለኮት የሆነው የእግዚአብሔር ልጅ፣ ከዘላለም ጀምሮ
የነበረ፣ ግላዊ፣ ነገር ግን ከአባቱ ጋር የሆነ ነው። እርሱ የሰማይ ታላቅ ክብር ነበር። እርሱ
ሰማያዊያን የሆኑ ጠቢባን አዛዥ ነበር፤ የመላእክትንም ስግደት እንደ መብቱ ተቀብሎታል። ይህ
ከእግዚአብሔር የተቀማ አልነበረም (ምሳ. 8፡22-27 ተጠቅሷል።]
“ዓለም ሳይፈጠር ክርስቶስ ከአብ ጋር አንድ የመሆኑ እውነት ውስጥ ብርሃንና ክብር
አሉ። ይህ በመለኮታዊ የመጀመሪያ ክብር፣ በጨለማ ቦታ ውስጥ የሚያበራውን ብርሃን ያማረ
ያደርገዋል። ይህ እውነት፣ በራሱ የማይደረስበት ምሥጢር ያለው ሆኖ ሳለ፣ ሌሎችን ሚስጥራዊ
እና በሌላ መንገድ ሊገለጹ የማይችሉ እውነቶችን ያብራራል፣ እሱ ግን ማንም ሊቀርበው
በማይችል እና ለመረዳት በማይቻል ብርሃን ውስጥ ተቀምጧል” (Ellen G. White Com-
ments, The Seventh-day Adventist Bible Commentary, vol. 5, p. 1126)።
“ኢየሱስም አለ፦ እኔ ከምድር ከፍ ከፍ ያልሁ እንደ ሆነ ሁሉን ወደ እኔ እስባለሁ” (ዮሐ. 12፡32)። ክርስቶስ ለኃጢአተኛው ሰው ስለ ዓለም ኃጢአት የሚሞት አዳኝ ሆኖ መገለጥ አለበት፤
እናም የእግዚአብሔርን በግ በቀራንዮ መስቀል ላይ ስናይ፣ የቤዛነት ምስጢር በአእምሯችን
መገለጥ ይጀምራል፤ የእግዚአብሔርም ቸርነት ወደ ንስሃ ይመራናል። ለኃጢአተኞች ሲሞት
ክርስቶስ ለመረዳት የማይቻል ፍቅር አሳይቷል፤ ኃጢአተኞች ይህን ፍቅር ሲያዩ፣ ልባቸው
ይለዝባል፣ አእምሯቸውም ይደነቃል፣ እና በነፍሳቸው ውስጥ መጸጸት ይቀሰቀሳል። … (ሰዎች)
ጽድቅን ለማድረግ በእውነተኛ መሻት ተነሳስተው ለመለወጥ ጥረት ባደረጉ ጊዜ ሁሉ፣
የክርስቶስ ኃይል ነው የሚስባቸው። እነርሱ ሳያውቁት ተጽእኖ በነፍስ ላይ ይሠራል፣ እናም ሕሊና
ሕያው ይሆናል፣ ውጫዊው ህይወትም ይሻሻላል። ደግሞም ክርስቶስ መስቀሉን እንዲመለከቱ፣
ኃጢአታቸው የወጋውን እርሱን እንዲያዩ ሲስባቸው፣ ትእዛዙ ወደ ሕሊናቸው ይመጣል” (ኤለን
ጂ ዋይት፣ ወደ ክርስቶስ የመሚመራ መንገድ፣ ገጽ 26፣ 27)።
1. ዮሐንስ ኢየሱስን በፈጣሪነት ሚናው ገልጾ በመናገር የጀመረው ለምንድን
ነው? ይህ በሁሉም ሥነ-መለኮት ውስጥ ስለ ፍጥረት አስፈላጊነት ምን
ይነግረናል? ታዲያ ለምንድን ነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጠው
ስለ ፍጥረት ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን የሚያስፈልገው?
2. በእሁድ ጥናት መጨረሻ ላይ በተጠየቀው ጥያቄ ላይ የበለጠ ጊዜ ወስዳችሁ
ተወያዩ። በመስቀል ላይ የሞተው በዘለአለማዊው አምላክ ፋንታ ፍጡር
ቢሆን ኖሮ ምን ይሆን ነበር? ኢየሱስ የዘላለም አምላክ ባይሆን ኖሮ
የምናጣው ምን ነበር?