የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


ጥቅምት 9 - 15

4ኛ ትምህርት

Oct 19 - 25




ክርስቶስ መሲሕ የመሆኑ ምሥክሮች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ.1:19–23፤ ኢሳ. 40:1–5፤ ዮሐ.1:29–37፤ ሮሜ. 5:6፤ ዮሐ.1:35–39፤ ዮሐ. 1:43–51፤ ዮሐ. 3፡1-21።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ኢየሱስም መለሰ እንዲህም አለው፦ እውነት እውነት እልሃለሁ፥ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም” (ዮሐ. 3፡3)።



እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው” የሚለውን ጨምሮ ኢየሱስ ስለራሱ የተናገራቸውን ነገሮች ለማጽናት ኃይል ያለውን የእግዚአብሔርን ቃል ከቅዱሳን መጻሕፍት ለሰዎች በማስረጃነት ያቀርብ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለውም (ዮሐ. 6:47)። ግን ደግሞ ሌላም አለ፦ ውሃን ወደ ወይን መለወጥ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በጥቂት እንጀራ መመገብ፤ የመኮንኑን ልጅ መፈወስ፤ በቤተሳይዳ መጠመቂያ አጠገብ የነበረውን ሰው መፈወስ፤ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ዓይኖች እንዲያዩ ማድረግ፣ አልዓዛርን ከሙታን ማስነሣት። ወንጌላዊው የተለያዩ ክንውኖችን እና ሰዎችን—ከአይሁዳውያን፣ ከአሕዛብ፣ ከባለ ጠጎች፣ ከድሆች፣ ከወንድ፣ ከሴት፣ ከገዥዎች፣ ከተራ ሰዎች፣ ከተማሩ እና ካልተማሩ ሰዎች ጎራ፣ ስለ ኢየሱስ ማንነት እንዲመሰክሩ ጥሪ አቅርቧል።

እግዚአብሔር አብና መጽሐፍ ቅዱስም እንኳ ሁሉም ማንነቱን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ዮሐንስ አመልክቷል። ይህ ሳምንት የሚጀምረው በመጥምቁ ዮሐንስ ኃያል ምስክርነት ነው። ሌሎች ምስክሮችም ወደ መድረኩ ይመጣሉ፦ እንድርያስና ስምዖን ጴጥሮስ፣ ፊልጶስ እና ናትናኤል፣ እንዲሁም ማንም ያልጠበቀው ምስክር፣ ፈሪሳዊው ኒቆዲሞስ። ነገር ግን በጥላ ውስጥ የተደበቀ ሌላ ምሥክር ነበር፤ ከእንድርያስ ጋር ያለው ሌላ ደቀ መዝሙር ዮሐንስ ራሱ (ዮሐ. 1:35፣ 40)። የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 16 ሰንበት ተዘጋጁ።

ጥቅምት 10
Oct 20

የመጥምቁ ዮሐንስ ምስክርነት


ባለፈው ሳምንት ትምህርት እንደተገለጸው፣ የዮሐንስ ወንጌል የሚጀምረው ከፍጥረት በፊት ጀምሮ ህያው በነበረውና የእግዚአብሔር ቃል በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ነገር ግን በዚያው መቅድም ላይ፣ መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስ ምስክር ሆኖ ቀርቧል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ አይሁዶች፣ አንዱ ካህን ሌላኛው ደግሞ ንጉሣዊ የሆኑ ሁለት መሲሖችን ይጠባበቁ ነበር። የዮሐንስ ወንጌል መጥምቁ ዮሐንስ ከእነዚህ መሲሖች አንዱ መሆኑን እንዳልተናገረና ይልቁንም የአንዱ የእውነተኛው መሲሕ ምሥክር እንደነበር በግልጽ ያስተምራል። ዮሐንስ 1:19–23ን ያንብቡ። መጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎቱንና ተልእኮውን እንዴት ነበር የገለጸው?



የኃይማኖት መሪዎቹ ዮሐንስን እንዲጠይቁት ካህናትንና ሌዋውያንን ላኩ። አይሁድ መሲሑን በከፍተኛ ጉጉት ይጠብቁ ስለነበር፣ መጥምቁ ዮሐንስ ከዚህ አንጻር ያለውን ዝምድና መግለጹ አስፈላጊ ነበር። እርሱ ብርሃን አልነበረም፣ ነገር ግን ስለ ብርሃን ሊመሰክር እና ለመሲሑ መምጣት መንገድን እንዲጠርግ፣ ከእግዚአብሔር ተልኮ ነበር (ዮሐ. 1፡6-8)። ለዚህም ነው የቻለውን ያህል ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲል የመለሰላቸው፦ “እኔ ክርስቶስ አይደለሁም” (ዮሐ. 1:20)።

ደግሞም፣ ዮሐንስ በውኃ አጠመቀ፣ ክርስቶስ ግን በመንፈስ ያጠምቅ ነበር (ዮሐ. 1፡26፣ 33)። ዮሐንስ የኢየሱስን የጫማ ማሰሪያ ሊፈታ የተገባው አልነበረም (ዮሐ. 1፡27)።

ክርስቶስ ከዮሐንስ ይልቅ ይመረጣል፣ ምክንያቱም እርሱ ከዮሐንስ በፊት ነበር (ዮሐ. 1፡ 30)። ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ እናም ዮሐንስ ወደ ክርስቶስ ብቻ አመለከተ (ዮሐ. 1፡34)። ኢሳይያስ 40:1-5 እና ዮሐንስ 1:23ን ያንብቡ። ዮሐንስ እነዚህን ጥቅሶች የተጠቀመባቸው እንዴት ነው?



የተበላሹና በድንጋይ የተሞሉ መንገዶች በነበሩበት ጊዜ የንጉሡን መንገድ ለማስተካከል አንዳንድ ጊዜ አገልጋዮች ከንጉሡ ፊት ይላኩ ነበር። ስለዚህ፣ በትንቢቱ ፍጻሜ፣ ዮሐንስ የመጣው የሰዎችን ልብ ለኢየሱስ ለማዘጋጀት ነበር። እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች፣ የመጥምቁን ዮሐንስ ዓይነት አገልግሎት የምንሠራው በምን መንገድ ነው? ከዚህ ጋር ተነጻጻሪ የሆኑ ነገሮች ምንድን ናቸው?

ጥቅምት 11
Oct 21

የእግዚአብሔር በግ


የእሥራኤል ሕዝብ ከሮም ነጻ የሚያወጣቸውን መሲሕ ይፈልጉ ነበር። የዮሐንስ ወንጌል ዓላማ ስለ መሲሑ ያላቸውን ግንዛቤ በመቀየር ስለሚመጣው ንጉሥ የሚነገሩትን ትንቢቶች በኢየሱስ አማካይነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ነበር። መሲሑ ምድራዊ ገዥ አይሆንም።

እርሱ የመጣው ስለ ራሱ የገባውን የብሉይ ኪዳን ተስፋዎች ሁሉ ሊፈጽም ነው፤ ይህም ስለ ዓለም ራሱን መስዋዕት ማድረግን እንዲሁም በእግዚአብሔር እና በሕዝቡ መካከል ያለውን ግንኙነት ማደስን ይጨምራል። ዮሐንስ 1:29-37ን ያንብቡ። መጥምቁ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ምን ዐዋጅ ይናገራል? እርሱን ለመግለጽስ ምን ዓይነት ምስል ይጠቀማል? ደግሞስ ይህ የኢየሱስን ማንነትና የተልዕኮውን ምንነት ከማስረዳት አንጻር ያለው ጉልህ ፋይዳ ምንድን ነው?



መጥምቁ ኢየሱስን የእግዚአብሔር በግ መሆኑን አስመልክቶ የሰጠው መግለጫ የዮሐንስ ወንጌል ዓላማን ይደግፋል፣ እርሱም ስለመሲሑ ሥራ እና ማንነት አዲስ ግንዛቤ ለማምጣት ነው። ኢየሱስ በእርግጥም በዘፍጥረት 3፡15 ወደነበረው ወደ ቤዛነቱ ተስፋ መጀመሪያ በመመለስ፣ የመሥዋዕቱ ሥርዓት የተስፋ ቃል ፍጻሜ ይሆናል።

“የሱስ በተጠመቀ ጊዜ ዮሐንስ የሱስ የእግዚአብሔር በግ እንደሆነ ሲናገር ስለ መሲሑ ሥራ አዲስ ብርሃን መከሰቱ ነበር። የነቢዩ አእምሮ “እንደ በግ ለመታረድ ቀረበ” ወደሚለው የኢሳይያስ ቃል ነበር (ኢሳ. 53:7)” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 121)። ማርቆስ 10:45፣ ሮሜ 5:6፣ እና 1ኛ ጴጥሮስ 2:24ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የኢየሱስን ሚና “እንደ እግዚአብሔር በግ” እንደ እንድንገነዘብ የሚረዱን እንዴት ነው?





መጥምቁ ዮሐንስ ምንም እንኳ ስለኢየሱስ አገልግሎት ይበልጥ ለማወቅ ቢፈልግም፣ ነገር ግን ኢየሱስ ቃል የተገባውና የትንቢት ፍጻሜ ሆኖ የመጣው መሲሕ እርሱ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነበር። ኢየሱስ “የእግዚአብሔር በግ” ተብሎ የተጠራበትን ይህን የማዕረግ ስም በጥልቀት እንመልከት። ወደ አእምሯችን ያመጣቸው ምስሎች ምንድን ናቸው? ከብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ሥርዓት ጋር ያለው ትስስር የመዳናችንን ታላቅ ዋጋ እንድናደንቅ የሚረዳን እንዴት ነው?

ጥቅምት 12
Oct 22

ሁለቱ የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት


ኢየሱስ በዚያ ሲያልፍ ሁለት የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አብረውት ቆመው ነበር። ዮሐንስ (በዮሐ. 1፡36) “እነሆ የእግዚአብሔር በግ!” ሲል አውጆ ነበር። ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የዮሐንስን መልእክት ሰምተው ነበር; እርሱም ስለሚመጣው መሲሕ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ይፈጽማል። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ከመጥምቁ ዮሐንስ እንደሚበልጥ እና እርሱ የዮሐንስ መልእክት ፍጻሜ መሆኑን አውቀው ዮሐንስን ትተው ኢየሱስን ተከተሉት። ዮሐንስ 1:35-39ን ያንብቡ። እነዚህ ሁለት ደቀ መዛሙርት ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ የሰጠውን ምስክርነት ከሰሙ በኋላ ምን አደረጉ?



ከኢየሱስ ጋር ለመሆን በመሻት ቀኑን ሙሉ ከእርሱ ጋር አብረው አሳልፈዋል። ያን ጊዜ የተማሩትን እና ያጋጠሟቸውን አስደናቂ ነገሮች ማን ያውቃል?

በጣም ድንቅ ነገሮች መሆን አለባቸው፣ ምክንያቱም ብዙም ሳይቆዩ ፍላጎታቸው ልምዳቸውን ለሌሎች ማካፈል ነበር። ከሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው እንድርያስ እርሱ አስቀድሞ የራሱን ወንድም ስምዖንን አገኘውና፦ “መሢሕን አግኝተናል አለው፤ ትርጓሜውም ክርስቶስ ማለት ነው” (ዮሐ. 1፡41)። እንድርያስ ወንድሙን ወደ ኢየሱስ ባመጣው ጊዜ፣ ወዲያው ኢየሱስ እንደሚያውቀው እንዲህ ሲል ነገረው፦ “አንተ የዮና ልጅ ስምዖን ነህ።

አንተ ኬፋ ትባላለህ” (ዮሐ. 1:42)። ኢየሱስ ጴጥሮስን አውቆ ተረድቶታል። ኢየሱስ ሰውን እንደሚያውቅ ማሳየት የዮሐንስ ወንጌል የተደጋገመ ጭብጥ ነው (ለምሳሌ ዮሐንስን 2:24፣ 25ን እንመልከት)።

“ዮሐንስና እንድርያስ እንደ ካህናቱና መኳንንቱ ያለማመን መንፈስ ቢኖርባቸው ኖሮ በየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጠው የመማር ዕድል አይኖራቸውም ነበር። በቃሉ ላይ ለመተቸት ስህተት ፍለጋ ወደ እርሱ ይመጡ ነበር። … እነዚህ የመጀመሪያ ደቀ መዛሙርት ግን ይህን አላደረጉም። በዮሐንስ መጥምቁ ስብከት አማካይነት የመንፈስ ቅዱስን ጥሪ ተቀበሉ። አሁን የሰማያዊውን መምህር ድምፅ ለማወቅ ቻሉ። … በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሚገኙት ትምህርቶች ላይ መለኮታዊ ብርሃን ፈነጠቀባቸው። ብዙ ርዕስ ያለው እውነት በአዲስ ብርሃን ጎልቶ ወጣ” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት ገጽ 124)።

የዮሐንስ ወንጌል በጠቅላላው አጽንዖት የሰጠው ይህ የምሥራች ለዓለም ይነገር ዘንድ የኢየሱስን ማንነት ወደ ብርሃን ማምጣትን ነው። ክርስቶስ እና በክርስቶስ ያለን እምነት ህይወታችንን በምን መንገድ ለውጦታል? አሁንም ምን ሌሎች ለውጦች እንዲከሰቱ እንፈልጋለን?

ጥቅምት 13
Oct 23

ፊልጶስ እና ናትናኤል


ዮሐንስ 1:43-46ን ያንብቡ። የፊልጶስ መልእክት በኢየሱስ ላይ ስላለው እምነት ምን አሳይቷል?



ልክ እንደ እንድርያስና እንደ ጴጥሮስ ሁሉ፣ ፊሊጶስም የቤተሳይዳ ሰው ነበር። ወዳጁ ናትናኤልን አግኝቶ ስለ ኢየሱስ ነገረው። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር በግ” ብሎ ጠርቶታል። እንድርያስ ለጴጥሮስ “መሲሑን” እንዳገኘ ነግሮት ነበር። ፊልጶስ ግን ሙሴና ነቢያት የጻፉለትን ኢየሱስን “የናዝሬቱ ኢየሱስ” ሲል ጨምሮ ጠርቷል። ናዝሬት የሚለውን ሥም መጥቀሱ ከጓደኛው የሰላ ምላሽን አስከትሏል።

ናትናኤል ለትንሿ ናዝሬት ከተማ ጭፍን ጥላቻ የነበረው ይመስላል። በእርግጥ ንጉሥ ከእንዲህ ዓይነቱ መንገድ ዳር ላይ ከለ ሥፍራ እንደማይመጣ የታወቀ ነው። ጭፍን ጥላቻ በእውነት ዋጋ ያለውን ነገር እንዳያዩ ሰዎችን በቀላሉ አይናቸውን ያሳውራል። ፊልጶስ ቀደም ሲል ከናትናኤል ጋር ካደረገው ውይይት ምናልባትም ጭፍን ጥላቻን ለመቋቋም ትክክለኛው መንገድ ከፍ ያለ ፍልስፍናዊ ወይም ሥነ-መለኮታዊ ክርክር ሳይሆን ግለሰቡ እውነቱን ለራሱ እንዲያውቅ መጋበዝ እንደሆነ የተገነዘበ ይመስላል። ዝም ብሎ “መጥተህ እይ” አለው።

ያደረገውም ይህንኑ ነው። ሄዶ አየ። ዮሐንስ 1:47-51ን ያንብቡ። ኢየሱስ ናትናኤልን ማንነቱን ያሳመነው እንዴት ነበር? የናትናኤልስ ምላሽ ምን ነበር?



በቁጥር 46 እና 47 መካከል የሌለው ነገር ናትናኤል ለፊልጶስ ግብዣ የሰጠው ምላሽ ወሳኝ ዝርዝር ጉዳይ ነው። ምንም ቢሆን ግን ተነሥቶ ለማየት ሄደ። ከፊልጶስ ጋር የነበረው ወዳጅነት ከጭፍን ጥላቻ ይልቅ የበረታ ነበር፤ እናም ሕይወቱ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተለወጠ።

ኢየሱስ ስለ ናትናኤል ጥሩ ቃላት ተናግሯል፣ “ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው” ብሎ ጠራው (ዮሐ. 1:47); ይህ ናትናኤል (በዮሐ. 1:46) ስለ ኢየሱስ ከተናገረው በጣም የተለየ ነው። ናትናኤል ኢየሱስን ከዚህ በፊት አግኝቶት ስለማያውቅ በመገረም መለሰ።

ከዚያም ኢየሱስ ከበለስ ዛፍ ሥር እንዳየው የተናገረ ሲሆን፣ ይህ ጥቂት ንግግር ናትናኤልን አሳምኖታል። ናትናኤል እውነትን በመሻት በዚያ ዛፍ ሥር ሲጸልይ ኢየሱስ በመለኮታዊ መገለጥ ተመልክቶታል። ናትናኤልም መልሶ፦ “መምህር ሆይ፥ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ፤ አንተ የእስራኤል ንጉሥ ነህ” ሲል ከፍ ያለ ኑዛዜን ተናገረ። ትንሽ የሚመስለው መገለጥ ወደ ትልቁ የእምነት ኑዛዜ እንዴት እንደሚመራ አስተውሉ።

ጥቅምት 14
Oct 24

የኒቆዲሞስ ምስክር


ዮሐንስ 3:1-21ን ያንብቡ። የኒቆዲሞስ ምስክርነት የዮሐንስን ወንጌል ጭብጥ የሚደግፈው እንዴት ነው?



ኒቆዲሞስ በእስራኤል ውስጥ የተከበረ መምህር፣ ባለጸጋ እና የአይሁድ ሸንጎ አባል ነበር። የእርሱ ምስክርነት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወተው በብዙ ምክንያቶች ነው። ኢየሱስን “መምህር” ሲል ጠርቶታል እንዲሁም ኢየሱስ ያደረጋቸውን ምልክቶች የመለኮታዊ ተልእኮው ማስረጃ እንደሆኑ ጠቁሟል። በመሆኑም ኒቆዲሞስ የሚያደርገውን ነገር ከመገንዘቡ በፊት እንኳ፣ የኢየሱስን መሲሕነት የሚደግፍ ማስረጃ እየሰጠ ነበር።

ኒቆዲሞስ ምልክቶቹን ራሳቸውን የኢየሱስ መለኮታዊ ጥሪ ማስረጃዎች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር፤ ነገር ግን በብሉይ ኪዳን ስለ መሲሑ የተነገሩት ትንቢቶች ፍጻሜ በመሆን ወደ ኢየሱስ እንደሚያመለክቱ አላያቸውም ነበር። ስለዚህ፣ ኒቆዲሞስ ጥቂት መጠራጠርን ይዞ መጣ፤ በዚህ ጊዜ ኢየሱስን እንደ ክርስቶስ አላወቀውም ነበር። ዮሐንስ 3:3-21ን ያንብቡ። በኒቆዲሞስ ውስጥ የተደበቀውን ነገር ሁሉ እንደሚያውቅ ለማሳየት ኢየሱስ ምን አለው?



ኢየሱስ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ያውቃል። ለኒቆዲሞስ የሰጠው ምላሽ ድንገተኛ ሊመስል ይችላል ነገር ግን በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ነበር የሄደው። ምንም እንኳን አይሁዶች አሕዛብ መለወጥ እንዳለባቸው ቢያምኑም፣ ነገር ግን ብዙዎቹ የተመረጡት ሕዝብ ወገን የሆኑት እንኳ መለወጥ እንደሚያስፈልጋቸው አልተረዱም ነበር። ዜግነቱ ወይም ያደገበት ቤተ ክርስቲያን ምንም ይሁን ምን፣ በዚያ ስለተወለደ ብቻ አይድንም።

እስከ አብርሃም ድረስ ወደኋላ ብንሄድ የአይሁዶች አስደናቂ ታሪካዊ አመጣጥ ብዙ ልዩ ልዩ ጥቅሞችን ሰጥቷቸው እንደነበር ምንም አያጠያይቅም (ሮሜ 3፡1፣ 2ን እንመልከት)።

ነገር ግን ያ በራሱ በቂ አልነበረም። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ ለማሰብ እንኳ የማይቻልን ነገር ነገረው፦ በእሥራኤል ውስጥ መምህርና ገዢ ቢሆንም ቅሉ፣ ከላይ ከሰማይ እንደገና መወለድ እዳለበት!

ከዚያም ኢየሱስ ኒቆዲሞስን ስለ መንፈሳዊ አላዋቂነቱ እንዲህ ሲል ተጋፍጦት ነበር፦ “አንተ የእስራኤል መምህር ስትሆን ይህን አታውቅምን?” (ዮሐ. 3:10)። “የተከበርህ መምህር ሆነህ ሳለ፣ እንዴት ይህንን ላታውቅ ትችላለህ?” ይህ ተግሣጽ በጣም ሳያስደነግጠው አልቀረም።

ኒቆዲሞስ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ስለ ኢየሱስ ምንም ዓይነት ጥያቄዎች ቢኖሩትም፣ ቆይቶ ግን ከየሱስ ተከታዮች ጎን ቆመ (ዮሐ. 19፡39 ተመልከቱ)። “ዳግመኛ መወለድ” ሲባል ምን ማለት ነው፤ ለምንስ ነው የሱስ ስለዚህ አጽንዖት የሰጠው?

ጥቅምት 15
Oct 25


ተጨማሪ ሀሳብ


የዘመናት ምኞት ከሚለው የኤለን ጂ ዋይት መጽሐፍ፣ በገጽ 167 - 177 «ኒቆዲሞስ» የሚለውን ያንብቡ።

“ኒቆዲሞስ ስለ ንድፈ ሀሳብ መከራከር ሳይሆን ሕይወትን ለማግኝት ሲል ቅዱሳት መጻሕፍትን በአዲስ መንገድ መረመረ። እራሱን ለመንፈስ ቅዱስ መሪነት እንዳስረከበ መጠን የሰማይን መንግሥት ማየት ጀመረ።

“በእምነት የእግዚአብሔርን ጸጋ እንቀበላለን፤ እምነት ግን አዳኛችን አይደለም።

እምነት የሚያስገኘው ነገር የለም። እምነት ክርስቶስን የምንጨብጥበትና የኃጢአት መድኃኒት የሆነውን የእርሱን ብቃት የምናገኝበት እጃችን ነው። … ለኃጢአት ይቅርታ የሚገኘው ከክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ ንስሐ መግባት በእርሱ አማካይነት ነው።

“ታዲያ እንዴት ነው የምንድነው? “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ” እንዲሁም የሰው ልጅ ተሰቀለ። የተታለሉና በእባብ የተነደፉ ሁሉ እርሱን በመመልት መኖር ይችላሉ። “እነሆ የዓለምን ኃጢ

አት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ. 1፡29)። ከመስቀሉ ላይ የሚወጣው ብርሃን የእግዚአብሔርን ፍቅር ይገልጻል። ፍቅሩ ወደ እርሱ ይስበናል። ይህን ስበት ካልተቋቋምን አዳኛችን እንዲሰቀል ካደረገው ኃጢአት ንስሐ በመግባት ወደ መስቀሉ እንመራለን። ያን ጊዜ በእምነት አማካይነት የእግዚአብሔር መንፈስ ለነፍሳችን አዲስ ሕይወት ይሰጣል። ሀሳብና ምኞት ሁሉ ለክርስቶስ ፈቃድ ተገዥ ይሆናል። ልብና አእምሮም በውስጣችን ሁሉንም ነገር ለእርሱ ተገዥ በሚያደርገው አምላክ አምሳያ ይቀረጻል። ይህ ሲሆን የእግዚአብሔር ሕግ በልባችንና በአእምሯችን ላይ ይጻፋል፤ ያን ጊዜ እኛም እንደ ክርስቶስ “አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” እንላለን (መዝ. 40:8)” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 163-164)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. መጥምቁ ዮሐንስ የኢየሱስን መንገድ ሊያዘጋጅ መጣ። አገልግሎቱ ቢያንስ በሰው እይታ ምን ያህል የተሳካ ነበር ትላላችሁ? በተጨማሪም፣ ስለ መልሳችሁ እያሰባችሁ ይህንንም ጠቃሚ ጥያቄ ጠይቁ፦ በመንፈሳዊ ነገሮች ያለንን “ስኬት” የምንገልጸው እንዴት ነው?

2. ቆይቶ መጥምቁ ዮሐንስ ከልብ የሆኑ ጥቂት ጥርጣሬዎችን ገለጸ (ማቴ. 11:2፣ 3፤ ሉቃ. 7:19)። የጥያቄዎቹ መንስኤ ምንድን ነው? በእምነታችን እንዴት እንደምንጸና ከነዚህ የምንማረውስ ምንድን ነው?

3. በጥናት ቡድናችሁ ውስጥ፣ እንደ ኒቆዲሞስ ሁሉ ዛሬም እውነተኛይቱ ቤተክርስትያን ውስጥ መሪ የሆነና ብዙ እውቀት ያለው ሰው በእርግጥም እንዴት አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች መንፈሳዊ አላዋቂነት ሊኖረው እንደሚችል ተወያዩ። ከእንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ ምን ትምህርቶችን ልንማር እንችላለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL