የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


ጥቅምት 16 - 22

5ኛ ትምህርት

Oct 26 - Nov 1




የሳምራውያን ምሥክርነት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 4:1-42፤ ዮሐ.3:26–30፤ ኤር. 2:13፤ ዘካ. 14:8፤ ሕዝ. 36፡25-27።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ሴቲቱንም፦ አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” (ዮሐ. 4፡42)።



ምራውያን እነማን ነበሩ? ሰሜናዊው የእስራኤላውያን መንግስት በ722 ዓመተ ዓለም በአሦራውያን ተማርኮ ነበር። የፖለቲካ መረጋጋት ለመፍጠር አሦራውያን ምርኮኞቻቸውን በመላው ግዛቶቻቸው በትነው ነበር። በተመሳሳይም ከሌሎች ሀገራት ህዝቦች የተወሰዱ ምርኮኞች በሰሜናዊው የእሥራኤል መንግሥት ምድር እንዲሠፍሩ ተደረገ፤ እነዚህም የራሳቸውን ዓይነት የአይሁድ እምነት የሚከተሉ ሳምራውያን ሆኑ።

ነገር ግን በእነርሱ እና በአይሁዶች መካከል የነበረው ግንኙነት ጥሩ አልነበረም።

ለምሳሌ አይሁዳውያን ከባቢሎን ሲመለሱ ቤተ መቅደሱን እንደገና እንዳይገነቡ ሳምራውያን ተቃውመዋል። ሳምራውያን በገሪዛን ተራራ ላይ የራሳቸውን ቤተ መቅደስ ሠርተው ነበር። ነገር ግን ይህ ቤተ መቅደስ በአይሁድ ገዥ በዮሐንስ ሂርካነስ በ128 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት (ከ.ክ.ል.በ) ፈረሰ።

በክርስቶስ ጊዜም ይህ ጥላቻ ቀጥሎ ነበር። አይሁዶች በተቻለ መጠን ከሰማርያ ራቁ። ንግድ የቀጠለ ቢሆንም፣ ሌላ መስተጋብር ግን የተከለከለ ነበር። አይሁዶች ከሳምራውያን አይበደሩም ወይም ከእነርሱ ውለታን እንኳን አይቀበሉም ነበር። በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ ውስጥ፣ ዮሐንስ በውኃ ጉድጓዱ አጠገብ በኢየሱስና በሴቲቱ እንዲሁም በሕዝቡ ዘንድ፣ በሳምራውያን ከተማ በሲካር የሆነውን ክስተት ይተርካል። የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለጥቅምት 24 ሰንበት ተዘጋጁ።

ጥቅምት 17
Oct 27

የክስተቱ መቼት


ዮሐንስ 4:1-4ን ያንብቡ። ኢየሱስን በሰማርያ እንዲያልፍ ያደረገው ከጀርባ ያለው ታሪክ ምን ነበር?



ፈሪሳውያን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይልቅ ብዙ ሰዎችን እያጠመቁ እንደሆነ አወቁ። ይህ ሁኔታ በዮሐንስና በኢየሱስ ተከታዮች መካከል አለመግባባት ሊፈጥር ይችላል። የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት፣ በተፈጥሯቸው፣ ለጌታቸው ዝና እና ደረጃ ቅናት ነበራቸው (ከዮሐ. 3:26-30 ጋር አነጻጽሩ)። ነገር ግን የዮሐንስ አስደናቂ መልስ እንዲህ የሚል ነበር፦ “እርሱ ሊልቅ እኔ ግን ላንስ ያስፈልጋል”(ዮሐ. 3፡30)። ምናልባት ጠብ እንዳይፈጠር ኢየሱስ ወደ ገሊላ ሊሄድ ይሁዳን ተወ። በእነዚህ ሁለት ቦታዎች መካከል ለመጓዝ ቀጥተኛው መንገድ በሰማርያ ማለፍ ነበር፣ ነገር ግን ይህ ማለፍ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ አልነበረም። ወግ አጥባቂ አይሁዶች በፔርያ በኩል ወደ ምሥራቅ ዞረው በማለፍ ረጅም መንገድ ይጓዙ ነበር። ኢየሱስ ግን በሰማርያ ተልእኮ ነበረው። ዮሐንስ 4:5-9ን ያንብቡ። በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካለች ሴት ጋር ውይይት ለመጀመር ኢየሱስ ይህን አጋጣሚ የተጠቀመበት እንዴት ነው?



የያዕቆብ ጒድጓድ በሴኬም አቅራቢያ ይገኝ የነበረ ሲሆን፣ ሴቲቱ የምትኖርበት ከተማ ሲካር አንድ ማይል (1.5 ኪሎ ሜትር ገደማ) ይርቅ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ምግብ ሊገዙ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ኢየሱስ ከጉድጓዱ አጠገብ ተቀመጠ። የጉድጓዱን ቀዝቃዛ ውኃ ለማግኝት የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረውም። ሴቲቱም ውኃ ልትቀዳ ስትመጣ እንድታጠጣው ጠየቃት።

በዮሐንስ 3 ላይ፣ የአይሁድ ገዥ እና መምህር የሆነው ኒቆዲሞስ ወደ ኢየሱስ ለመምጣት ራሱን ዝቅ ማድረጉ የሚያስገርም ነበር። ሰዎች እንዳያዩት ሲል በሌሊት መጣ።

ነገር ግን በዮሐንስ 4 ላይ፣ ሴቲቱ በጠራራ ፀሀይ ትደበቃለች፣ ምናልባትም በቀኑ መጀመሪያ ወይም መገባደጃ ላይ ፀሐዩ በረድ ሲል ከመጡ ሴቶች ጋር እንዳትገናኝ ይህ አመቺ ጊዜ ነው። ለመሆኑ ውኃ ለመቅዳት በእኩለ ቀን ሊጥል በሚችል ፀሐይ፣ ረጅም መንገድ ለምን ሄደች? እዚያ የምትገኝበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከኢየሱስ ጋር መገናኘቷ ሕይወቷን ለውጦታል።

ቀጥሎ ምን ትዕይንት ይታያል? አንድ አይሁዳዊ አስተማሪ ከአንዲት መጥፎ ስም ከነበራት ሳምራዊት ሴት ጋር ተነጻጽሯል። እንዴት ያለ ተቃርኖ ነው! ነገር ግን፣ በዚህ ትክክለኛ አውድ ውስጥ፣ አንድ አስደናቂ ገጠመኝ ይከሰታል። ለሌሎች ያለንን ምስክርነት ሊያደናቅፉ የሚችሉ ባህላችን ውስጥ እንደነውር ተቆጥረው የተከለከሉ አንዳንድ ነገሮቻችን ምንድን ናቸው? እነዚህን ነገሮች መሻገርን እንዴት እንማራለን? መልሶቻችሁን በሰንበት ወደ ጥናት ቡድናችሁ አምጡ።

ጥቅምት 18
Oct 28

በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ያለች ሴት


ዮሐንስ 4:7-15ን ያንብቡ። ኢየሱስ ለዚህች ሴት መመሥከርን ለመጀመር ይህን አጋጣሚ የተጠቀመበት እንዴት ነው?



“በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል የነበረው ጥላቻ ሴቲቱ የሱስን ከመርዳት አገዳት። አዳኛችን ግን የልብዋን በር ለመክፈት በማሰብ ከመለኮታዊ ፍቅር በመነጨ ዘዴ ቸሮታ ጠየቀ እንጂ አላበረከተም። ችሮታ ሊያደርግላት ቢሞክር ኖሮ ምናልባት አትቀበልም ይሆናል፤ ነገር ግን እምነት እምነትን ይወልዳል” (ኤለን ጂ. ኋይት የዘመናት ምኞት ገጽ 173)።

ልክ ከኒቆዲሞስ ጋር እንደተገናኘበት ሁኔታ ሁሉ፣ ኢየሱስ በሌሎች ልብ ውስጥ ያለውን ያውቃል። አንድ አይሁዳዊ እንዲህ ያለውን ውለታ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት መጠየቁ ለፈጠረባት መደነቅ ምላሽ ለመስጠት በቀጥታ ወደ ጉዳዩ ነበር የሄደው። ኢየሱስ መልሶ፦ “የእግዚአብሔርን ስጦታና፣ ውኃ አጠጪኝ የሚልሽ ማን መሆኑንስ ብታውቂ፥ አንቺ ትለምኚው ነበርሽ የሕይወትም ውኃ ይሰጥሽ ነበር” አላት (ዮሐ. 4፡10)።

የሴቲቱ ምላሽ እንደ ኒቆዲሞስ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚል ነበር (ዮሐ. 3:9)። እርሷም እንዲህ ብላ ጠየቀች፦ “ጌታ ሆይ፥ መቅጃ የለህም ጕድጓዱም ጥልቅ ነው፤ እንግዲህ የሕይወት ውኃ ከወዴት ታገኛለህ?” (ዮሐ. 4:11)። በሁለቱም ሁኔታዎች ኢየሱስ እነርሱን (ዝነኛውን የአይሁድ አስተማሪና በሥውር መልካም ያልሆነ ስብእና ያላትን ሳምራዊት ሴት) እያሳየ የነበረው እያንዳንዱ ሰው ሊሰማውና ሊረዳው የሚገባውን እጅግ የላቀ መንፈሳዊ እውነትን ነበር። በእያንዳንዱ ሁኔታ፣ ኢየሱስ በመሠረቱ ለሁለቱም ተመሳሳይ ነገር እየነገራቸው ነበር፦ ይህም መለወጥ እንደሚያስፈልጋቸው ነው። ኢየሱስ ስለ ሕይወት ውኃ ለተናገረው ሀሳብ የብሉይ ኪዳን ዳራው ምንድን ነው? (ኤር. 2፡13፣ ዘካ. 14፡8)



ውኃ ለሕይወት አስፈላጊ ነው፤ ሰዎች ከውሃ ውጭ ሊኖሩ አይችሉም፣ እናም ውኃም እንዲሁ ለዘላለም ሕይወት ኃያል እና ተገቢ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ለዘላለም አይጠማም። እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል” (ዮሐ. 4:14)። ዮሐንስ 7:37፣ 38ን ያንብቡ። ኢየሱስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን እያለን ነው፣ እሱ የሰጠውንስ ተስፋ እንዴት እንለማመዳለን?

ጥቅምት 19
Oct 29

“ጌታ ሆይ ይህን ውኃ ስጠኝ”


“ጥሩ ውኃንም እረጭባችኋለሁ እናንተም ትጠራላችሁ፥ ከርኵሰታችሁም ሁሉ ከጣዖቶቻችሁም ሁሉ አጠራችኋለሁ። አዲስም ልብ እሰጣችኋለሁ አዲስም መንፈስ በውስጣችሁ አኖራለሁ፤ የድንጋዩንም ልብ ከሥጋችሁ አወጣለሁ የሥጋንም ልብ እሰጣችኋለሁ።

መንፈሴንም በውስጣችሁ አኖራለሁ በትእዛዜም አስሄዳችኋለሁ፥ ፍርዴንም ትጠብቃላችሁ ታደርጉትማላችሁ” (ሕዝ. 36:25-27)። ሕዝቅኤል 36፡25-27 ኢየሱስ ለኒቆዲሞስና በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ለነበረችው ሴት ሊሰጣቸው የፈለገውን እውነት የሚያንጸባርቀው እንዴት ነው?



በሁለቱም ሁኔታዎች፣ ኢየሱስ ይህን ለማድረግ ከተፈጥሮው ዓለም ምሳሌዎችን ቢጠቀምም፣ ለእነዚህ ሰዎች መንፈሳዊ እውነቶችን ለማድረስ ይሻ ነበር።

ሁለቱም በእርግጠኝነት ኢየሱስ ምን ማለቱ እንደነበር አልተረዱም ነበር። ኒቆዲሞስ፦ “ሰው እንዴት ዳግመኛ ሊወለድ ይችላል?” ሲል ጠየቀ። ማለትም፣ ወደ እናቱ ማኅፀን እንዴት ይመለሳል? ምንም እንኳን ኢየሱስ ወደ መንፈሳዊ እውነት እየጠቆመው ቢሆንም፣ ኒቆዲሞስ ግን በዘልማዳዊና ምድራዊ መንገድ እያሰበ ነበር። ይህች ሴትም ኢየሱስ ስለ ውኃ የተናገረውን ቃል በቃል የወሰደችው ኢየሱስ በግልጽ ስለ መንፈሳዊ ነገር ሲናገር ሳለ ነበር።

ሴትዮዋ ለኢየሱስ የሕይወት ውኃ ስጦታ የሰጠችው ምላሽ፣ “ጌታ ሆይ፥ እንዳልጠማ ውኃም ልቀዳ ወደዚህ እንዳልመጣ ይህን ውኃ ስጠኝ” የሚል ነበር (ዮሐ. 4፡15)። ኢየሱስ ያቀረበው ውኃ፣ ወደ ጕድጓዱ የሚደረገውን ጉዞ እንደሚያስቀርና ከሌሎች ጋር የመገናኘት ዕድልን እንደሚቀንስ አሰበች። ንግግራቸው ከኢየሱስ የሚጠጣ ውኃ ጥያቄ ወደ ሴቲቱ የሚጠጣ ውኃ ጥያቄ በፍጥነት መቀየሩ አስገራሚ ነው። ዮሐንስ 4:16ን ያንብቡ። ኢየሱስ ለሴቲቱ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?



ኢየሱስ በድንገት የውይይቱን ርዕስ ለወጠው፤ ሴቲቱ ሄዳ ባሏን ጠርታ እንድትመለስ ነገራት። ድንገተኛ የርዕስ ለውጥ ለምን አስፈለገ? የሴቲቱ ተግባር ጉዳዩን ወደጎን ለማድረግ መፈለግን ያመለክት ነበር። ኢየሱስ የልቧን ማንበብ ይችል ነበር። ፈውስ ለማግኘት ሁኔታውን መጋፈጥ አለባት። “ይህቺ ሴት የሱስ ሊሰጣት የፈለገውን ስጦታ ከመቀበልዋ በፊት ኃጢአትዋንና አዳኝዋን ማወቅ ነበረባት” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 175)።

ጥቅምት 20
Oct 30

የኢየሱስ መገለጥ


ዮሐንስ 4:16-24ን ያንብቡ። ኢየሱስ ይህችን ሴት ጥልቅ ሚስጥሯን እንደሚያውቅ ለማሳየት ምን አደረገ? እሷስ ምን ምላሽ ሰጠች?



ብርሃኑ ዓይንን የሚያሳውር ከመሆኑ የተነሳ በቀጥታ ለማየት አይቻልም ነበር።

ሴቲቱ ኢየሱስ ነብይ መሆኑን ብትረዳም፣ አሁንም ለመደበቅ ትሞክራለች። በአይሁዶችና በሳምራውያን መካከል ስላለው ኃይማኖታዊ አለመግባባት ማለትም፣ ስለ ትክክለኛው የአምልኮ ቦታ ጥያቄ አነሳች።

ኢየሱስ የሰጠው ምላሽ ሳምራውያን የሚያመልኩትን እንደማያውቁ ነበር። የእነርሱ አምልኮ የአይሁድ እምነት እና የጣዖት አምልኮ ውህደት ነበር። አይሁዶች ራሱን የሚገልጥ አምላክን ያመልኩ እንደነበር መናገር ለአንዲት ሳምራዊት አንድ ጠቃሚ እውነታን መቀበል ነበር።

የእውነተኛው አምላክ አምልኮ ከአንድ ቦታ ጋር የተቆራኘ አይደለም። ስለዚህ ስለ አንድ የአምልኮ ቦታ የተደረገው ውይይት ከነበረው ንንግግር ጋር ምንም ግንኙነት የለውም።

እግዚአብሔር መንፈስ ነውና የሚሰግዱለትም በመንፈስና በእውነት ሊያደርጉት ይገባቸዋል። ሴትዮዋ ኢየሱስ የተናገረውን ግልጽ እውነት የተቀበለች ከመሆኑም ሌላ፣ ለበለጠ ነገር ዝግጁ ነበረች። ዮሐንስ 4:25፣ 26ን ያንብቡ። ኢየሱስ ማንነቱን የገለጸላት እንዴት ነበር?



በአራቱም ወንጌላት ውስጥ፣ ኢየሱስ ከመከራው በፊት መሲሕ መሆኑን ለአንድ ሰው በግልፅ የተናገረበት ብቸኛው ክፍል ይህ ነው። ይህንንም ያደረገው ለብዙ ሕዝብ ወይም ትልቅ ቦታ ላለው ሰው አይደለም፣ ነገር ግን በያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ላለች ስሟ ላልተጠቀሰ ሳምራዊት ሴት እንጂ። እርሱ መገለልና እና ብቸኝነት ስለሚሰማው ስለ ማንኛውም ብቸኛ ነፍስ ግድ ይለዋል።

ስለዚህም እንግዳ ከሆነ ባህል የመጣች ብቻ ሳትሆን መልካም ስብእናም ለሌላት ለእንደዚህች ዓይነት ሴት ኢየሱስ ማንነቱን ፊትለፊት ገልጧል። ደግሞም፣ በጨለማ ስለተሸሸገው ምስጢሯ ያለውን ዕውቀት ከገለጠላት በኋላ፣ ለዚህች ሴት እንዲሁ በእርሱ እንድታምን ትልቅ ምክንያት ሰጣት። ይህ ታሪክ እኛ ሰዎች እርስ በእርሳችን ላይ የምንፈጥረውን አጥር ወንጌል ለምን ማፍረስ እንዳለበት ምን ሊነግረን ይገባል?

ጥቅምት 21
Oct 31

የሳምራውያን ምስክርነት


ዮሐንስ 4:27-29ን ያንብቡ። ሴትዮዋ ምን አስገራሚ እርምጃ ወሰደች?



ኢየሱስ ከሴቲቱ ጋር ያደረገው ውይይት የተቋረጠው ደቀ መዛሙርቱ በመጡ ጊዜ ነው።

ከሴት ጋር መነጋገሩ ቢገርምም አልጠየቁትም ነበር። ይልቁንም እንዲበላ ገፋፉት።

ሴቲቱ በበኩሏ የውሃ ማሰሮዋን ትታ ከኢየሱስ ጋር ያጋጠማትን ነገር ለሌሎች ለማካፈል ወደ ከተማዋ በፍጥነት ሮጠች። ዮሐንስ 4:30-42ን ያንብቡ። ከዚህ ገጠመኝ በኋላ ምን ሆነ? ወንጌል እንዴት ሊስፋፋ እንደሚችልስ ምን ያስተምራል?



ኢየሱስ ስለ መኸር የተናገረው ትረካ በከተማው ውስጥ የብዙዎችን የንግግር ታሪክ ማቋረጡ እንግዳ የሚመስል ነገር ነው። ዮሐንስ ግን ኢየሱስ እየሆነ ያለውን ነገር እንዴት እንደተረዳ እንድንመለከት ይፈልጋል። የመዳንን እቅድ ለሳምራዊቷ ሴት ማጋራት ለእርሱ ከመብል እጅግ የላቀ ነበር። ነፍሳትን ወደ ድነት መምራት አላማው ነበር፣ እናም እንደ እነርሱ ላልሆኑትም ጭምር ወንጌልን የማካፈልን አጣዳፊነት ለደቀ መዛሙርቱ ለማስተማር ይህንን አጋጣሚ ተጠቀመበት።

በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ብዙ ከፍ ያሉ ነጥቦች አሉ። በእርግጥም ዮሐንስ 4፡39-42 ከእነዚህ መካከል ነው። “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ስትል በመሰከረችው ሴት ምክንያት ብዙ ሳምራውያን አመኑ (ዮሐ. 4፡39)።

ሳምራውያን ኢየሱስን ከእነርሱ ጋር እንዲቆይ ጠየቁት። በውጤቱም ብዙዎች በየሱስ ቃል ምክንያት አመኑ። “ሴቲቱንም። አሁን የምናምን ስለ ቃልሽ አይደለም፥ እኛ ራሳችን ሰምተነዋልና፤ እርሱም በእውነት ክርስቶስ የዓለም መድኃኒት እንደ ሆነ እናውቃለን ይሉአት ነበር” (ዮሐ. 4፡42)። የአንድ ሰው ምስክርነት ምን ያህል ኃይል እንዳለው ይህ ታሪክ ምን ሊነግረን ይገባል? ኢየሱስ በሕይወታችን ስላደረገው ነገር ምን ያህል ጠንካራ ምስክሮች ነን?

ጥቅምት 22
Nov 1


ተጨማሪ ሀሳብ


የኤለን ጂ ዋይትን «በያዕቆብ ጉድጓድ» ገጽ 183–195፣ ከዘመናት ምኞት ውስጥ ያንብቡ።

“ሳምራዊቷ ሴት አዳኛችንን እንዳገኘችው ወዲያውኑ ሌሎችን ወደ እርሱ አመጣች።

ከደቀ መዛሙርቱ የተሻለች ወንጌላዊት መሆንዋን አስመሰከረች። ደቀ መዛሙርቱ በሰማርያ ለወንጌል ሥራ የሚያደፋፍር ሁኔታ አልታያቸውም ነበር። ትኩረታቸው ወደ ፊት በሚከናወን ትልቅ ሥራ ላይ ነበር። በዙሪያቸው ለመሰብሰብ የደረሰ አዝመራ መኖሩ አልታያቸውም። ነገር ግን በናቅዋት ሴት አማካይነት የአንድ ከተማ ሕዝብ በሙሉ አዳኛችንን ለመስማት መጣ።

ለወገኖችዋ ብርሃንን በአንድ ጊዜ አዳረሰች።

“ይህች ሴት የተግባራዊ እምነት አሠራር ምሳሌ ናት። እያንዳንዱ እውነተኛ ደቀ መዝሙር ለእግዚአብሔር መንግሥት ወንጌላዊ ለመሆን ተወልዷል። ከሕይወት ውኃ የጠጣ ሁሉ እራሱ ምንጭ ይሆናል። ተቀባዩ ሰጪ ይሆናል ማለት ነው። በነፍስ ውስጥ የክርስቶስ ጸጋ ሁሉን ለማርካት እንደሚፈልቅና ለመጥፋት የተቃረቡትን ሁሉ ከሕይወት ውሃ ለመጠጣት ጉጉት እንዲያድርባቸው እንደሚያደርግ የምድረ በዳ ምንጭ ነው” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 184)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በጥናት ቡድናችሁ ውስጥ፣ ለእሁዱ የመጨረሻ ጥያቄ የሰጣችኋቸውን መልሶች ተመልከቱ። በጉዳዩ ላይ ፍጹም ሀቀኛ ሁኑ። እናንተ ራሳችሁ ለሌሎች እንዳትመሰክሩ የሚያግዷችሁ፣ በባህላችሁ ውስጥ ያሉ እንደ ነውር የሚታዩ ነገሮች ምንድን ናቸው?

2. ኢየሱስ ከራሱ ሰዎች በተቃራኒ በሳምራውያን መካከል እንዲህ ያለ የሞቀ አቀባበል የተደረገለት ለምን ይመስላችኋል?

3. ራሳችንን በዚያች ሳምራዊት ሴት ቦታ እናስቀምጥ። አንድ እንግዳ ሰው መጥቶ ጥልቅ ምስጢሯን እንደሚያውቅ ያሳውቃታል። ማንኛውም ሰው፣ ያውም ደግሞ እንግዳ፣ እነዚህን ነገሮች እንዴት ሊያውቅ ቻለ? በኢየሱስ መገረሟ ምንም አያስደንቅም። ጌታ ጥልቅ እና በጨለማ ውስጥ የደበቅናቸውን ምሥጢሮች እንኳ ሳይቀር ስለ እኛ ሁሉንም ነገር እንዴት እንደሚያውቅ ይህ ታሪክ ምን ሊነግረን ይገባል? ግን ደግሞ፣ ምስጢራችንን እያወቀ እንኳ እርሱ እኛን እንዴት ሊንከባከበን እንደሚፈልግ እሷን ያስተናገደበት መንገድ ምን ይለናል? ከዚህ እውነት ምን ማጽናኛ ማግኘት እንችላለን?

4. ኢየሱስ በውኃ ጉድጓድ አጠገብ ለነበረችው ሳምራዊት ሴት ባከናወነው አገልግሎት ውስጥ እስካሁን የተማርናቸው በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የሚገኙት የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL