የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ግንቦት 22 - 28

10ኛ ትምህርት

May 30 - Jun 5




ንስሐ እና ይቅርታ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 61:10፤ ሆሴዕ 6፤ የሐዋርያት ሥራ 3:18-19፤ ዘጸ. 34:1-10፤ ሮሜ. 6:23፤ ማቴ. 22:1-14።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ኃጢአታችንን ብንናዘዝ፣ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው” (1ኛ ዮሐንስ 1:9)።

የተስፋዪቱ ምድር በሜዳው ላይ ባለው የደመና አምድ ስር ለሰፈሩት እስራኤላውያን በጣም የራቀች ትመስል ነበር። ሙሴ ከብዙ ቀናት በፊት የተራራውን ጫፍ ሸፍኖ ወደነበረው ጨለማ ወጥቶ ነበር። ወይ በረሃብ ካልሆነም በጫፉ ላይ ካለው የሚቃጠል እሳት የተነሳ መሪያችን አሁን ሞቷል ብለው አሰቡ። በመካከላቸው የተደባለቀው ሕዝብ እረፍትና ትዕግስት አጥቶ፣ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ለመሄድ ተዘጋጅቶ ነበር። ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ከጥቂት ቀናት በፊት እርሱን ለመታዘዝ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ቢገቡም፣ ሊያዩት የሚችሉትን ምስል ፈልገው ነበር። ስለዚህ፣ በአሮን ድንኳን ዙሪያ ተሰብስበው ጣዖት እንዲሰራላቸው ጠየቁት። አሮን ለራሱ ደህንነት በመፍራት በሀሳባቸው ተስማማ። በዘጸአት 32-34፣ ይህ አሳዛኝ ታሪክ እንዴት እንደቀጠለ እናነባለን። ይህ ዘገባ የዚህ ሳምንት የትምህርት ዋና ጭብጥ ስለሆነው ስለ ንስሐና ይቅር ባይነት የሚያስተምር ከቅዱሳት መጻሕፍት የተወሰደ አንድ ታሪክ ብቻ ነው። የእያንዳንዱን ቀን ትምህርት ሲያጠኑ የዚህን ሳምንት መሪ ጥቅስ ጭብጥ በአእምሮዎ ይያዙ። አዎ፣ ኃጢአት እንሠራለን፣ ነገር ግን ለመስቀሉ እና ለመዳን እቅድ ምስጋና ይግባውና ለሚናዘዝና ለሚጸጸት ኃጢአተኛ ይቅርታ አለ። *ለግንቦት 29 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ግንቦት 23
May 31

የሕይወት ሩጫ


በጣም የተጨናነቀ ሳምንት ነበር። ከሰንበት በፊት ብዙ የሚሠራ ነገር እንዳለ ብታውቅም፣ አጣዳፊው ነገር አስፈላጊ የሆነውን ነገር የሚውጥ ይመስል ነበር፣ እና ሳታውቀው ፀሐይ ጠልቃ ነበር። ቤተሰቡ አንድ ላይ ልዩ የአርብ ምሽት ምግብና አምልኮ ተካፈሉ። ነገር ግን የሰንበት ጠዋት ሲመጣና በማለዳ ስትነቃ፣ መታጠቢያ ቤቱ ቆሽሾ ስላገኘችው ጠራረገችው። ከዚያም ትንሹ ልጇ አልጋውን በሽንቱ እንዳራሰ አየች፣ ስለዚህ አንሶላዎቹን ከሌሎች ልብሶች ጋር ወደ ማጠቢያ ማሽን ጣለችው። ለቤተሰቧ ቁርስ ስታዘጋጅ፣ ለምሳ የሚሆን ጣፋጭ ምግብ እንደሌለ ተገነዘበች እና በፍጥነት የሙዝ ዳቦ ጋገረች። ባለቤቷ ለቤተ ክርስቲያን የሚተኮስ ሸሚዝ እንደሚያስፈልገው አየች፣ ስለዚህ ተኮሰችለት፣ ከዚያም ልብሶችን አጣጠፈችና ቆሻሻዎቹን አወጣች። ከዚያም ነገሩ ነካት። ሰንበት ነው - ከሌሎቹ ሁሉ በላይ የምወደው ቀን ነው! ሆኖም ግን፣ እነዚህን ሁሉ የቤት ውስጥ ሥራዎች እየሠራሁ እነዚህ ነገሮች ከሰንበት ጣዕም(በረከት) ማለትም ወደ እግዚአብሔር ከመቅረብ እንዲያዘናጉኝ ፈቅጃለሁ። ለአፍታ፣ አእምሮዋ ድርጊቶቿ ትክክለኛ እንደነበሩ ራሷን ለማሳመን ጀመረ - እነዚህ ሁሉ መደረግ ያለባቸው ነገሮች ነበሩ። በእርግጥ ግን ነበሩ?



እንደ ማርታ “በብዙ አገልግሎት በመጨነቅ” (ሉቃስ 10:40) እንደምትሠራ ተገነዘበች፣ ነገር ግን የኢየሱስ ቃላት በአእምሮዋ ውስጥ “በብዙ ነገር ትጨነቂአለሽ ትታወኪማለሽ፥ የሚያስፈልገው ግን ጥቂት ወይም አንድ ነገር ነው፤ ማርያምም መልካም ዕድልን መርጣለች ከእርስዋም አይወሰድባትም።” (ሉቃስ 10፥41-42) ሲል አስተጋባ። ለኢየሱስ ካላት ጥልቅ ፍቅር የተነሳ በሰንበት ብቻ ሳይሆን በየቀኑ በኢየሱስ እግር ስር ትቀመጥ ነበር። ዛሬ ጠዋት ግን ያንን አልመረጠችም። እግዚአብሔርን ትወድ ነበር፣ ሆኖም ግን ግንኙነታቸውን ለማጠናከር ሰንበትን በጊዜ ውስጥ እንደ ስጦታ እንደሰጣት መርሳት ቀላል ነበር። በጸጥታ በወጥ ቤት ውስጥ ቆማ ሳለች ከዓይኖቿ እንባ ፈሰሰ። የዚህ ምሳሌ ዓላማ በሰንበት ቀን ምን ማድረግ እንዳለብን ወይም ምን ማድረግ እንደሌለብን ላይ ማተኮር አይደለም፤ ይልቁንም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያዳክሙ ወይም የሚያበላሹ ነገሮችን ማስተዋል ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ማስታወስ ነው። በልባችን ውስጥ የኃጢአትና የመለያየት ሥቃይ ሲሰማን ወደ እርሱ ስንጣራ ኢየሱስ በጣም ቅርብ ነው (መዝ. 53:2)። በደም በተሸፈኑ እጆቹ ነጭ ልብስ ይይዛል። የንስሐ እንባችንን አይቶ የቆሸሹ ልብሶቻችንን ያስወግዳል። ከዚያም ንፁህ የጽድቅ ልብሱን በዙሪያችን ሁሉ ላይ ያደርጋል። ንጽሕናው ኃጢአታችንን - ሙሉ በሙሉ እና ፍጹም በሆነ መልኩ ይሸፍናል። ልብሳችንን በደሙ ማጠብ እንችላለን (ራዕይ 7:14)። ኢሳይያስ 64:6፣ ዘካርያስ 3:4 እና ኢሳይያስ 61:10 ስለ ክርስቶስ ጽድቅ ይህን አስፈላጊ እውነት ለእኛ የሚገልጹት እንዴት ነው? እዚህ ላይ የተሰጠንን የተስፋ ቃል ሁልጊዜ አጥብቀን መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

ግንቦት 24
Jun 1

የመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ


በእርሱና በሚስቱ መካከል ስላለው ርቀት ሲያስብ፣ ስህተት እንደሠራ ገብቶታል።

ደግነት የጎደለው እና ጨካኝ ሆኖ ነበር፣ የሚጸጸትባቸውን አንዳንድ ነገሮች ተናግሯል። ሆኖም ቀጣዩ ሀሳቡ ትንሽም ቢሆን ይህ የሚገባት አይደለችም ወይ? የሚለው ነበር። ይህ የአስተሳሰብ ሂደት ለእርስዎ የተለመደ ይሆን? ከጸጸት ስሜት ወደ ሀሳባችን እና ድርጊታችን ትክክል ለመሆኑ ምክንያትን ማግኘት ቀላል ነው። ስህተት ስንሠራ “ይቅርታ…” ማለት ሁልጊዜ ቀላል አይደለም፣ ነገር ግን ይህ ማንኛውንም ግንኙነት እንደገና ለመገንባት ወይም ለማጠናከር በጣም አስፈላጊ ነው። በእኛ እና በእግዚአብሔር መካከል ባለው ግንኙነትም ተመሳሳይ ነው። መንፈስ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ የፈፀምናቸውን ኃጢአቶች ያስታውሰናል። ልባችን በእነዚህ ወቀሳዎች ምክንያት ይንቀሳቀሳል፣ ነገር ግን በተወሰነ መንገድ ለምን እንደሠራን ምክንያት ለመስጠት በመሞከር ያንን ጸጥ ያለ፣ ትንሽ ድምጽ መግፋት ሊቀለን ይችላል። የመንፈስ ቅዱስ ሚናዎች አንዱ “ስለ ኃጢአት ዓለምን መውቀስ” (ዮሐንስ 16፡7-8) ነው። ይህ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው አስደናቂ ስጦታ (ሉቃስ 11:13) ነው፣ ከእርሱ ጋር ስንጓዝ የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት እንዲህ ያሉ ወቀሳዎች እንዴት እንደሚያስፈልጉን! ሆሴዕ 6ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለንስሐ በሚያቀርበው ልመና ውስጥ ራሱን እንዴት እንደገለጸ እዚህ ላይ ምን ያስተውላሉ?



መንፈስ ቅዱስ እኛን ወደ ወይኑ ግንድ መልሶ በማያያዝ ሂደት ውስጥ ያለውን ሚና አስቡበት (ዮሐንስ 15:4)። “አብዛኛውን ጊዜ የምናዝነው ክፉ ሥራችን መልሶ እኛኑ የሚጎዳ ነገር ስለሚያመጣብን ነው፤ ነገር ግን ይህ ንስሐ መግባት አይደለም። ስለ ኃጢአት የሚደረግ እውነተኛ ሀዘን የመንፈስ ቅዱስ ሥራ ውጤት ነው። መንፈስ ቅዱስ ልባችን ክርስቶስን በማሳዘንና ችላ በማለት የሚያሳየውን ምስጋናቢስነት በመግለፅ በትህትና ወደ መስቀሉ እንድንቀርብ ያደርገናል። እያንዳንዱ ኃጢአት ክርስቶስን ያቆስለዋል፤ . . . በእርሱ ላይ ጉዳት ስላደረሰው ኃጢአት እናዝናለን። የዚህ ዓይነቱ ሀዘን ኃጢአትን እንድንተው ያደርገናል።”— ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 299. እውነቱ ግን፣ በምርጫ የሚደረግና የተወደደ ኃጢአት በእኛና በእርሱ መካከል ቆሞ እያለ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ማደግ አንችልም። ፍጹም መሆን አንችልም፣ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ወደ አእምሯችን ሲያመጣው ከኃጢአታችን ንስሐ መግባት እንችላለን፣ ይገባናልም (ኤፌ. 4:30)። ለመጨረሻ ጊዜ የንስሐ ተግሣጽ ወይም የንስሐ ጥሪ የሰሙት መቼ ነበር? ምን አይነት ምላሽ ሰጡ? በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር ልብዎን እንዲያለሰልስና በቃሉ ውስጥ ያለውን ድምፅ እንዲሰሙ ጆሮዎን እንዲከፍትልዎ አሁን በጸሎት ጊዜ ያሳልፉ።

ግንቦት 25
Jun 2

እውነተኛ ንስሐ


እግዚአብሔር ለአገልጋይነት እና ለየዋህነት(ማቴ. 5:5) ካቀረበው ጥሪ በተቃራኒ ዓለም የነፃነት፣ የተመኘነውን የማድረግ እና ራስን የማስተዋወቅ መልዕክቶች ሰጥታናለች።

የሚገርመው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በመጥምቁ ዮሐንስ፣ እና በኢየሱስ የተነገሩት የመጀመሪያ ቃላት ተመሳሳይ ነበሩ። ዮሐንስ “ ‘መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ!’” ብሏል (ማቴ. 3:1, 2)። ኢየሱስ “ጊዜው ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች። ንስሐ ግቡ፥ በወንጌልም እመኑ” ብሏል። (ማርቆስ 1:14-15፣ ሉቃስ 24:46-47ን ይመልከቱ)።

ኢየሱስም ሆነ ዮሐንስ የንስሐን ጥሪ የሚሰሙትን የጠሩት መንግሥተ ሰማያት ስለቀረበ ነው። ይህ መልእክት ዛሬም ለእኛም የሚጠቅም መልእክት ሊሆን ይችላል? የሐዋርያት ሥራ 3:18-19ን ያንብቡ። በመንፈሳዊ እድገት ሂደት ውስጥ ንስሐ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? “የመታደስ ወራት” ምንድን ነው?



የእግዚአብሔር ቸርነት እና መልካምነት ወደ ንስሐ ይመራናል (ሮሜ. 2:4)። ንስሐ መግባት ሁለት ደረጃዎችን ያካትታል፤ (1) ለኃጢአታችን እውነተኛ ህመም፤ እና (2) ኃጢአትን ለመተው እውነተኛ ውሳኔ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ንስሐ መግባት ሁልጊዜ ማለት ይቻላል ከይቅርታ ጋር የተያያዘ ነው። በእውነት ስንጸጸት፤ እግዚአብሔር ይቅር ይለናል። ይህን ያህል ቀላል ነው (1ኛ ዮሐንስ 1:9፣ ራዕይ 3:19)። “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።” 2ኛ ጴጥሮስ 3፥9)። ነፍሳችንን በግላችን ለዳግም ምጽአቱ ስናዘጋጅ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነገሮችን እንድናስተካክል ጊዜ እየሰጠን ነው። ኢየሱስ መከራ ተቀብሎ ሞተ፣ እናም ተነሣ፣ ስለዚህ ንስሐ ስንገባ፣ ጸጋው በሕይወታችን ውስጥ ተአምር ሊሠራ ይችላል። አሁን ባለንበት ደህና መሆናችንን ከሚነግረን ዓለም በተቃራኒ፣ እግዚአብሔር በንስሐ እና በእምነት ወደ እርሱ እንድንመለስ ይጠይቀናል (የሐዋርያት ሥራ 20:21)፣ ራሳችንን ሙሉ በሙሉ በእጁ ውስጥ በማስቀመጥ፣ ገፀ ባህሪያችንን ወደ እርሱ መልክ ሊቀርጽና ስለ እርሱ መመስከር እንድንችል ይጠይቀናል (ዮሐንስ 15:2፣ 8)። ከዚያም ከንስሐ ጋር በሚስማማ መንገድ እናድጋለን፣ ፍሬም እናፈራለን (ማቴ. 3:8)። “መታደስን የማያስከትል ንስሐ እውነተኛ ንስሐ አይደለም። የክርስቶስ ጽድቅ ባሕሪን የሚለውጥና ፀባይን የሚቆጣጠር የሕይወት መርህ እንጂ የድብቅ ኃጢአት መሸፈኛ ካባ አይደለም።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 571። ንስሐ ወደ ሕይወት ይመራል (የሐዋርያት ሥራ 11:18) እና ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ለማደግ ወሳኝ ነው። በመገዛት፣ በንስሐ፣ በመጸጸት እና እግዚአብሔር እንዲገርዘን በመፍቀድ ሂደት ውስጥ፣ ለእርስዎ በጣም ፈታኝ የሆነው እርምጃ የትኛው ነው?

ግንቦት 26
Jun 3

የሚበቃ ፀጋ


የኃጢአታችን ክብደት ሲሰማንና መንፈስ ቅዱስ ወደ መስቀሉ እግር እንዲመራን ስንፈቅድ፣ “እግዚአብሔር መሓሪና ይቅር ባይ ነው፥ ከቍጣ የራቀ ምሕረቱም የበዛ ነው” (መዝ. 103:8) የሚለውን ቃል በማመን እግዚአብሔር ይቅር እንዲለን ልንጠይቅ ይገባናል። ይህ ተመሳሳይ ጥቅስ የተመረጠው ሕዝቡ ካሳዘነው በኋላ በእግዚአብሔር በራሱ (ዘጸ. 34:6) ተነግሮ ነበር። ዘጸአት 34:1-10ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ምን ወሳኝ እውነት ይገኛል?



ጌታ መሐሪና ቸር፣ ለቁጣ የዘገየና ምሕረቱ የበዛ መሆኑ ኢየሱስ በመስቀል ላይ የሞተበት ዋነኛው ምክንያት ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነትም እንደገና እንዲስተካከል ነው።

ይህም ተግባራዊ የሚሆነው ኃጢአታችንን ለመቀበልና ለመናዘዝ ፈቃደኛ ስንሆን ነው፤ ጌታ ሆይ፣ እንደገና እዚህ ነኝ ስንል . . እና “እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ!” (ሉቃስ 18:13) ስንል ነው፣ ከመፀለያችን በፊት እንኳን በእኛና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት ለእኛ ሲሠራ የነበረው ኢየሱስ -- ክብደቱን አይቶ ከእኛ ይወስደዋል። ሸክማችን የተነሳልን በቀራንዮ ላይ ነው፤ እናም ኢየሱስ ወደ እርሱ ስንመጣ በእርግጥ በጣም ቅርብ ነው፣ እና ከዚያ በፊትም ቢሆን እንደ መልካም እረኛ ሊፈልገን በበሩ ቆሞ ያንኳኳል (ራዕይ 3:20)። እግዚአብሔርን ከሩቅ እያየን ከመስቀሉ አንራቅ። ወደ ኢየሱስ እንሩጥ እና ኃጢአታችንንና ሸክማችንን በጽድቅ እንለውጥ (ዘካ. 3:4)። ቀጣዮቹን ጥቅሶች ቀስ ብለው ያንብቡ። ስለ እግዚአብሔር ጸጋ የሚነግሩዎትን በራስዎ ቃል መልሰው ይፃፉ፡- “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ. 6:23)። “ “በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።”(ሮሜ 5:20-21)። “ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል።” (ሮሜ 5:8)

ግንቦት 27
Jun 4

እጅግ ውድ የሆነው ልብስ


በዓለማዊ መመዘኛዎች ጥሩ ልብስ ብዙውን ጊዜ ባለጠጎችን የሚገልፅ ነው። አንዳንድ ሰዎች “እኔ ማን እንደሆንኩ ለመግለጽ በዚህ መንገድ እለብሳለሁ” ይላሉ። ነገር ግን በሰማይ፣ ከግንኙነቶቻችን ውጪ ያለው ነገር ሁሉ ይጠፋል (ማቴ. 6:19-21)። የግል ማንነታችን በኢየሱስ እና ፍጹም በሆነው የጽድቅ ልብሱ መጠቅለል አለበት። ይህንን ለማስረዳት ኢየሱስ በማቴዎስ 22:1-14 ላይ የጻፈውን ምሳሌ ያንብቡ። በዚህ ምሳሌ ውስጥ ምን መልእክቶችን ማግኘት እንችላለን?..



ኢየሱስ የሠርግ ልብስ ያልለበሰውን ሰው “ወዳጄ” ብሎ ጠርቶታል፤ ምንም እንኳን ምላሽ ባይሰጥም፣ ግንኙነት ግን ነበራቸው። ሰውየው ስለ ልብሱ ቢያውቅም ላለመልበስ መርጦ ነበር። የኢየሱስ ባሕርይ ፍጹምና እድፍ የለሽ ነው፤ ይህንንም “ “ያጌጠና የተጣራ ቀጭን የተልባ እግር ልብስ እንድትጐናጸፍ ለሙሽራው ሰጥቶአታል” (ራዕ. 19:8) በማለት ለእኛ ሰጥቶናል፣ “እድፍ ወይም መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር” (ኤፌ. 5:27) አይኖርባትም። ነጭ የተልባ እግር “የክርስቶስ ጽድቅ፣ የራሱ የሆነ እንከን የለሽ ባሕርይ ነው፣ ይህም በእምነት አማካይነት እርሱን እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ለሚቀበሉት ሁሉ የሚሰጥ ነው።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 310።

አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከመሥራታቸው በፊት ለስላሳ የብርሃን ነጭ ልብስ ለብሰው ነበር፤ ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ግን ራቁታቸውን መሆናቸውን ተገነዘቡ (ዘፍ. 3:7)። ከዚያም እግዚአብሔር በአዳምና በሔዋን የተሠሩትን የበለስ ቅጠሎች ልብስ በእንስሳት ቆዳ ልብስ ለወጠው። ልብሳቸው እንዲሠራ መስዋዕት ያስፈልግ ነበር። በተመሳሳይ መንገድ የኢየሱስን መስዋዕትነት የምንቀበለው የጽድቁን ልብስ በመቀበል ነው። “በራቁትነትና በሀፍረት ሆነው ሰማያዊውን ልብስ ከበለስ ቅጠል በተሰፋ ግልድም ለመተካት ሞከሩ። … የሰው ልጅ ያጣውን የንፅህና መጎናፀፊያ የሚተካ ምንም ነገር ራሱ መሥራት አይችልም። የበለስ ቅጠል ግልድም ያደረጉ ወይም የተንቆጠቆጠ ዓለማዊ ልብስ የለበሱ ማናቸውም ከክርስቶስና ከመላእክቱ ጋር በበጉ የሰርግ እራት ላይ መቀመጥ አይችሉም። ነገር ግን ክርስቶስ ራሱ የሰጠን መጎናፀፊያ ብቻ ነው በእግዚአብሔር ፊት መቆም እንድንችል የሚያደርገን። ክርስቶስ በንስሐ በሚጸጸትና በሚያምን ነፍስ ሁሉ ላይ የራሱ የጽድቅ ልብስ የሆነውን ይህን ልብስ ያለብሰዋል።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 174 (በአማርኛው)። ያስቡበት፡- በየቀኑ የኢየሱስን የጽድቅ ልብስ መልበስ አለብን። ይህ በእርግጥ ምን ማለት ነው፣ እና ይህንንስ እንዴት እናደርጋለን?

ግንቦት 28
Jun 5


ተጨማሪ ሀሳብ


መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ የእኛን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመግለጽ የግብርና ዘይቤዎችን ይጠቀማል። ሆሴዕ 10፡12 በዚህ ሳምንት የተወያየንበትን የሚይዝ አንድ ምሳሌ ነው፡- “እግዚአብሔር መጥቶ ጽድቅን እስኪያዘንብላችሁ ድረስ እርሱን የምትሹበት ዘመን ነውና ለእናንተ በጽድቅ ዝሩ፥ እንደ ምሕረቱም መጠን እጨዱ፥ ጥጋታችሁንም እረሱ።” (ሆሴዕ 10፥12) እኛ እንዘራለን፥ እናጭዳለን፥ ጠንካራውንም አፈር እናለሰልሳለን፥ እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንዲቀርብም እንፈልጋለን። የልባችን አፈር ለዝናብ (መንፈስ ቅዱስ) ዝግጁ መሆን አለበት። እግዚአብሔር አፈሩን ለማዘጋጀት ፍላጎት ሊሰጠን ይችላል፥ ነገር ግን በዋናነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት አጋርነት ነው (ፊልጵ. 2፡12፣ 13ን ይመልከቱ)። ፊታችንን ወደ እርሱ ማዞር፥ ወደ እርሱ መዘርጋት እና ከእርሱ ጋር መጣበቅ አለብን። ከዚያም የቀረውን ለማድረግ በእኛ ውስጥ ይሠራል። ከእግዚአብሔር ጋር መጣበቅ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ጥሩ ምሳሌ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ይገኛል፡- “ “ብዔልፌጎርን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በብዔልፌጎር ያደረገውን ዓይኖቻችሁ አይተዋል። “እናንተ ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የተከተላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ ሁላችሁ በሕይወት ትኖራላችሁ።”— ዘዳግም 4፥3-4


የመወያያ ጥያቄዎች




1. “ወደ ፈተና አታግባን፥ ከክፉም አድነን እንጂ” (ማቴ. 6:13)። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በዚህ መንገድ እንዲጸልዩ በተለይ አስተምሯቸዋል፣ ነገር ግን ይህንን ኃሳብ በዕለት ተዕለት ጸሎታችን ውስጥ እንይዘዋለን? ከፈተናና ከኃጢአት እንዲጠብቀን ምን ያህል አዘውትረን እንጸልያለን?

2. የክርስቶስን የጽድቅ ልብስ ውድ ስጦታ ክርስቲያን ላልሆነ ወይም አዲስ አማኝ የምትገልፁለት እንዴት ነው?

3. የክርስቶስ የጽድቅ ልብስ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛን ይቅር ስለ ማለትና ስለ ማንፃት ከሚያተኩረው ከቤተመቅደሱ መልእክት ጋር የሚገናኘው እንዴት ነው? እርስዎ የዚህን መልእክት ውበትና ጥልቀት ምን ያህል ተረድተውታል? ማጠቃለያ፡- ለመንፈስ ቅዱስ ወቀሳ ምላሽ በመስጠት ኃጢአታችንን መለየት እና ራሳችንን በንስሐ ማስገዛት ከእግዚአብሔር ጋር የበለጸገ ግንኙነት ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃዎች ናቸው። ሙሉ በሙሉ ይቅር እንደተባልን እና በኢየሱስ የጽድቅ ካባ እንደተሸፈንን ማወቅ ለሰው ልጅ እጅግ በጣም ለውጥ የሚያመጣው ልምምድ ነው። የኃጢአት ሸክም መነሳቱ እንዲሰማን ብቻ ሳይሆን፣ ወደ እርሱ ስንቀርብ የእግዚአብሔር ፍቅር በዙሪያችን እንዳለ ይሰማናል። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር ያስተሳስረናል፣ በመንፈሳዊ ረገድ ያጠነክረናል፣ እና በሁለንተናችን እንድንወደው ግድ ይለናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL