የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ግንቦት 15 - 21

9ኛ ትምህርት

May 23 - 29




ኃጢአት፣ ወንጌል፣ እና ህጉ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መሳፍንት 14፣ ማርቆስ 9:42-48፣ ሮሜ 3:20፣ ማቴ. 5:17-18፣ ሮሜ 3:28፣ ማቴ. 7:24-29።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በእርሱ ሕያው አድርገኸኛልና ፍርድህን ለዘላለም አልረሳም። እኔ የአንተ ነኝ፤ ፍርድህን ፈልጌአልሁና አድነኝ።” (መዝሙር 119:93-94)።

ከእግዚአብሔር ከሚለዩን ነገሮች ዋናው ኃጢአት መሆኑ አያጠራጥርም። ኃጢአት ከእግዚአብሔር መለየት ብቻ ሳይሆን (ኢሳ. 59:2)፣ ያታልለናል፣ ይጎዳናል፣ ያበላሸናል፣ በመጨረሻም ያጠፋናል። ከኃጢአትና ከራሳችን ጋር የምናደርገው ውጊያ እጅግ በጣም አስደናቂ፣ ዘላለማዊ አንድምታ ያለው ትልቁ ጦርነት ነው። አንዳንዶች ኃጢአትን የሕይወት መደበኛ ክፍል አድርገው ይመለከቱታል። ደግሞም በደስታ መጥለም የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው። ታድያ ኅብረተሰቡ ከኃጢአት ጋር በጣም ስለተመቻቸ ኃጢአትን ማቃለል ይኖርብናል? አንድን ሰው ስለ ኃጢአቱ ብንነግረው እናስቀይመዋለን ብለን በመፍራት ስለ ኃጢአት ጉዳይ ላንናገር እንችላለን፣ ነገር ግን በመጨረሻ፣ በምቾት ለመኖር በመረጥን ቁጥር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ጤናማ ግንኙነት እንንሸራተታለን። አዎ፣ እያንዳንዱ ሰው ኃጢአትን ይሠራል፣ እናም ሀሳባችን፣ መነሳሳታችን፣ ድርጊታችን እና ቃላታችን ሌሎችን፣ ራሳችንን እና እግዚአብሔርን ይጎዳሉ። በዋናነት፣ ኃጢአት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ያበላሻል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያለው ኃጢአት ላይ ብርሃን የሚያበራውን ሕጉን በማሳወቅ ራሱን ገልጦልናል። በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር ሕጉን ለእኛ የሰጠበትን ምክንያት እንመርምራለን፣ እና አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ሕግ ሲጥስ እና በዚህም ምክንያት ኃጢአት ሲሠራ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኙነት ለማደስ ምን ወይም ማን ሊረዳው እንደሚችል እንመርምር። *ለግንቦት 22 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ግንቦት 16
May 24

ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮች እና ፈተናዎች


በመሳፍንት 14 እና በመሳፍንት 16:1፣ 4፣ 16፣17 ላይ ስለ ሳምሶን ፈተናዎች ያንብቡ።

ምንም እንኳን እግዚአብሔር ለአንድ የተወሰነ ዓላማ ቢጠራውም፣ ሳምሶን እግዚአብሔርን በማገልገል ውስጥ ለፈተና እጅ ሰጠ። የሕይወቱ ውጤት ምን ያስተምረናል?



ታላቁ ተጋድሎ እውን ነው፣ እናም ሁላችንም በዚህ ውስጥ እየተሳተፍን ነው። በሰማይ የተጀመረው ዓለም-ዓቀፍ ውጊያ አሁን በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ እየተካሄደ ነው። ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳይኖረን ለማድረግ ኢየሱስ ከመምጣቱ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ ያለውን ሁሉ መጠቀም እንዳለበት ያውቃል።

ምናልባት በራሱ ስህተት ላይሆን ቢችልም በጣም ብዙ ጊዜና ጉልበት ስለሚወስድ ለእግዚአብሔር ምንም ቦታ በማያስቀር ነገር ትኩረትዎ ተከፋፍሎ ይሆናል። ምናልባት ሥራ፣ ማህበራዊ ሚዲያ፣ እቃ መግዛት፣ ስፖርት ወይም ምግብ ሊሆን ይችላል።

ራሳችንን በደንብ ስንመለከት፣ ከመጠን በላይ እነዚህ ላይ ትኩረት ማድረግ እና ሚዛናዊ አለመሆን ለእግዚአብሔርና ለሌሎች ሰዎች የሚሆን ጊዜ ያሳጣናል። ጠላት እያንዳንዱን ድክመታችንንና ከእግዚአብሔር ጋር ጊዜ ከማሳለፍ የሚያዘናጉንን ነገሮች ያውቃል። ወደ ቀናችን ከመቸኮልና ወደ እኛ የሚመጣውን ሁሉ ከመጀመራችን በፊት እግዚአብሔርን መፈለግ እንዳለብን ማስታወስ አለብን (ማቴ. 6:33)። ኢየሱስ ያለንበትን ሁኔታ ይረዳል፣ ነገር ግን ግድየለሽነታችንን ይገሥጻል (ራዕ. 3:14-22)። እርሱ እግዚአብሔር ቢሆንም፣ እንደኛ ድካም የሚሰማው ሰውም ነበር (ዮሐንስ 4:6)። እንደ እኛ የሕይወትን ጫናዎች ያውቅ ነበር፣ ነገር ግን ብቻውን ከአባቱ ጋር በመነጋገር ማሸነፍ ቻለ (ሉቃስ 5:16፣ ሉቃስ 6:12፣ ማርቆስ 1:35፣ ማቴ. 14:23)። ከአባቱ ጋር የነበረው ጊዜ ፈተናዎችን ለመዋጋትና ጥንካሬን መልሶ ለማግኘት ማድረግ የሚችለው ከሁሉ የተሻለው ነገር እንደሆነ ያውቅ ነበር።

ለእኛም ከሁሉ የተሻለውና አስተማማኙ መንገድ እሱ ነው። ሳምሶን የወደቀው በራሱ ጠንካራ እንደሆነ ስላሰበ ነው። ፈተናዎችን ለማሸነፍ በራሱ ጥንካሬ ላይ ይተማመን ነበር። የነፍሳት ጠላት ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማዳከምና ለማጥፋት በሚሞክርበት ሁኔታ፣ እያንዳንዳችን በየዕለቱ ከኃጢአት ጋር ውጊያ እንገጥማለን።

ድክመቶቻችንን ስለሚያውቅ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለማዳከም እና የጥፋተኝነት ስሜት ለማምጣት፣ ከእግዚአብሔርም ሊያርቀን በድካሞቻችን ይጠቀምባቸዋል። ዲያብሎስ በሕይወታችን በሆነ ክፍል ውስጥ ምሽግ ለማግኘት አስተሳሰባችንን፣ ዓላማችንን እና ድርጊታችንን ለመቀየር ይሰራል። ነገር ግን ያስታውሱ፡- እምነታችን እንድንቆም ይረዳናል፣ እምነትም የሚመጣው የእግዚአብሔርን ቃል በመስማት ነው። አሁን እርስዎ እየታገሉ ያሉት በምን ጉዳይ ነው? በዚህ ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር ቃል ሊረዳዎት የሚችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 17
May 25

ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት


ውስጥ ያሉ ጠንካራ ጎኖች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስላለን ግንኙነት እና በክርስቶስ እንዳናድግ ስለሚከለክሉን እንቅፋቶች የሚናገሩ ብዙ መልእክቶች አሉ። እነዚህን የጳውሎስ እና የኢየሱስ ቃላት እናስብባቸው፡- “ስለዚህ እንደቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” (1ኛ ቆሮ. 10፡12)። እንደ ሳምሶን አይነት በራስ መተማመን ያዋርደናል። “እንግዲህ. .. ግብዞች በሰው ዘንድ ሊከበሩ በምኩራብ በመንገድም እንደሚያደርጉ በፊትህ መለከት አታስነፋ፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።” (ማቴዎስ 6፥2)

እርስዎ ምን ያህል መልካም እንደሆኑ ለሁሉም መናገርዎን ያቁሙ! ኢየሱስ ትሑት እንደሆነ ትሑት ሁኑ። ‘እኔ ግን እላችኋለሁ፥ ወደ ሴት ያየ ሁሉ የተመኛትም ያን ጊዜ በልቡ ከእርስዋ ጋር አመንዝሮአል።“ቀኝ ዓይንህም ብታሰናክልህ አውጥተህ ከአንተ ጣላት።”(ማቴዎስ 5፥28-29)። በልብዎ ውስጥ ያለውን ክፉ ምኞት ለማስወገድ ማንኛውንም ነገር ያድርጉ፣ ምክንያቱም ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ላለዎት ግንኙነት እንቅፋት ነው። “እንዳይፈረድባችሁ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱበት ፍርድ ይፈረድባችኋልና።” ማቴዎስ 7፥1-2 (ማቴ. 7:1-2)። ሌሎችን በጣም መንቀፍና በሌሎች ላይ መፍረድ ያቁሙ።

እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና (1ኛ ቆሮ. 4:5)። “እኔ ግን እላችኋለሁ፣ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፣ የሚረግሙአችሁን መርቁ፣ ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፣ ለሚበድሉአችሁና ለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ’” (ማቴ. 5:44)። ጠላቶቻችሁን መጥላት አቁሙ። ክፉ ለሚያደርጉባችሁ ሰዎች አሉታዊ ስሜት ሲሰማችሁ፣ ወዲያውኑ ከእግዚአብሔር ጋር ባለችሁ ግንኙነት ላይ እንቅፋት ይሆናል።

በምትኩ፣ ለጠላቶቻችሁ መጸለይ ጀምሩና ይህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎትን አረማመድ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጋር ያለዎትን ግንኙነትም እንዴት እንደሚለውጥ ይመልከቱ። “እኔ ግን እላችኋለሁ፥ በወንድሙ ላይ የሚቆጣ ሁሉ ፍርድ ይገባዋል” (ማቴ. 5:22)።

ምናልባት በአቅራቢያችሁ ባሉት ላይ ጮክ ብላችሁ በቁጣ ለምን እንደምትናገሩ ምክንያታዊ ለመሆን እየሞከራችሁ ሊሆን ይችላል። ቁጣችሁ ከእግዚአብሔር ጋር ባለችሁ ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል፣ በተናደዳችሁባቸው ላይስ? እነዚህ እንድንሰናከል የሚያደርጉን ጥቂት ቦታዎች ብቻ ናቸው። ኢየሱስ እጆቻችን፣ እግሮቻችንና ዓይኖቻችን ኃጢአት እንድንሠራ ሲያደርጉን ምን ማድረግ እንዳለብን አስጠንቅቋል። ኢየሱስ ስለ ምን እያስጠነቀቀን ነው? ማርቆስ 9:42-48ን ያንብቡ። ኃጢአት እንድንሠራ ስለሚያደርገን እጃችንን ወይም እግራችንን መቁረጥ፣ ወይም ዓይናችንንም ማውጣት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ኢየሱስ ኃጢአትን እና በሕይወታችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ የሚመለከተው በዚህ መንገድ ነው። እርስዎስ ምን ያህል ትኩረት እየሰጡት ነው?

ግንቦት 18
May 26

ሕጉ


ኃጢአትን ክርስቲያን ላልሆነ ሰው እንዴት ትተረጉሙለታላችሁ? መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአትን የሚገልፀው እንዴት ነው? ሮሜ 3:20 እና 1 ዮሐንስ 3:4ን ያንብቡ።



ኃጢአት የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍ ነው (1 ዮሐንስ 3:4)፣ ኃጢአትም በተፈጥሯችን ውስጥ የተጠቀለለ ነው (መዝ. 51:5፣ ኤር. 17:9)። ስለዚህ፣ ኃጢአት በእርግጥ ምን እንደሆነ የሚያበራው ሕጉ ነው። ሕጉ በዙሪያችን ያለውን ነገር በግልጽ ማየት እንድንችል መነጽር እንደ ማድረግ ወይም በትክክል ምን እንደምንመስል ለማየት መስታወት እንደ መጠቀም ነው። ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ እና ለእሱ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እየነገረን በተመሳሳዩ ጊዜ ለሕይወታችን እና ለገጸ ባህሪያችን ግልጽነትን እና እምነትን ያመጣል። አስርቱ ትእዛዛት (ዘጸ. 20:3-17) የተጻፉት በእግዚአብሔር ጣት ነው። ኢየሱስ አስፈላጊነታቸውን አስተጋብቷል፡- “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ የምትል ናት። ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት።

ሁለተኛይቱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የምትል እርስዋን የምትመስል ይህች ናት። ከእነዚህ የምትበልጥ ሌላ ትእዛዝ የለችም።” (ማርቆስ 12:30-31)። አክሎም “በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል።” (ማቴ. 22:40)። እግዚአብሔር በሲና ተራራ ለእስራኤላውያን እና ዛሬ ለእኛ (ዕብ. 1:1-2) የተናገራቸው ቃላት ሕጉ ስለ ግንኙነቶች ብቻ እንደሆነ ይነግሩናል። እግዚአብሔር ሕጉን የሰጠው ከእርሱና ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለመጠበቅ እንደ መከላከያ አድርጎ ነው። ሆኖም፣ ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕግ ውበት በማዛባት አንዳንዶች እንደ ሸክም አድርገው እንዲመለከቱት አድርጓል። መጽሐፍ ቅዱስ “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና፤ ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም።(1ኛ ዮሐንስ 5:3)” ቢለንም እንኳ ከፍቅርና ከነፃነት ይልቅ ሕግን በመጠበቅ ለመዳን መፈለግ ብዙውን ጊዜ ከሕጉ ጋር የተያያዘ ነው።
1. ከ1 እስከ 5 ባለ መለኪያ፣ ሕያው የሆነው ቃል (ሕጉን ጨምሮ) ለእኔ ምን ያህል ውድ ነው?
2. ስለ እግዚአብሔር ሕግ ሳስብ፣ ይገድበኛል ወይስ ያጠነክረኛል? የመጀመሪያው ለእኔ ስለ እግዚአብሔር ሕግ ሳስብ፣ ይገድበኛል ወይስ ያጠነክረኛል? የመጀመሪያው ለእኔ እውነት ከሆነ ሕጉን እንዴት በተሻለ ሁኔታ መረዳት እችላለሁ?
3. እግዚአብሔር ለእርሱና ለሌሎች ያለው የፍቅር ሕግ በሕይወቴ፣ በቤተሰቤና በቤተ እግዚአብሔር ለእርሱና ለሌሎች ያለው የፍቅር ሕግ በሕይወቴ፣ በቤተሰቤና በቤተ ክርስቲያኔ ማዕከል ቢሆን ምን ሊፈጠር ይችላል? በሕይወቴና በግንኙነቶቼ ውስጥ ምን ሊለወጥ ይችላል?

ግንቦት 19
May 27

ሕጉና ወንጌል


ኢየሱስ ራሱ ከሕጉ ጋር ያለው ግንኙነት ምን እንደሆነ በኃይልና በአጭሩ አብራርቷል።

በማቴዎስ 5:17-18፣ ኢየሱስ ስለ ሕጉ ምን አለ?



ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስቀምጡት ገደብ እነርሱ ዋጋ ስለሚሰጡት ነገር እንደሚናገር ሁሉ፣ የእግዚአብሔር ሕግ ስለ ባህሪው እና ለእርሱ አስፈላጊ የሆነውን ነገር ይነግረናል።

እግዚአብሔር ሕጉን የሰጠን ከእርሱ ጋርና እርስ በእርሳችን ያለንን ግንኙነት ለመጠበቅ ነው፡ በእርሱ ውስጥ ስናድግ ሕጉ የሕይወታችንን እያንዳንዱን ገጽታ እንደሚመራ ያውቃል። ደግሞስ፣ ኃጢአት፣ የሕግ ጥሰት፣ በእያንዳንዳችን ላይ ያስከተለውን አስከፊ መዘዝ ያልቀመሰ ማን አለ? ኢየሱስን ማፍቀር የሕጉ ማዕከል ነው። ኢየሱስ “ ‘ብትወዱኝ ትእዛዜን ትጠብቃላችሁ’” ብሏል (ዮሐንስ 14:15)። ኢየሱስን በእውነት ስንወደው፣ በተፈጥሮ ሕጉን እንድንጠብቅ እንገደዳለን። ሕጉን በግልጽ ስናይ፣ ኢየሱስን የበለጠ እንድንወደው እንገደዳለን። ከዚህም በላይ ደግሞ የመስቀሉንና የክርስቶስን የምትክነት ሞት ሁልጊዜ በዓይናችን ፊት ማየት ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለማሳደግ ምርጡ መንገድ ነው። ወንጌል ከሕጉ ጋር የሚሄደው ለዚህ ነው ። ያም ማለት፣ በሕጉ እና ሕጉን በመጠበቅ አስፈላጊነት ምንም ያህል ብናምን ሕጉ በእግዚአብሔር ፊት ባለን ህጋዊ አቋም ረገድ፣ ሕጉ የሚኮንን ብቻ መሆኑን ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን። ሕጉ ፈጽሞ ይቅር አይልም፣ ፈጽሞ አያጸድቅም፣ በፍጹም አያስተሰርይም። በተቃራኒው፣ ለምን ይቅር መባል እንደሚያስፈልገን፣ ለምን መጽደቅ እንደሚያስፈልገን እና ለምን መቤዠት እንደሚያስፈልገን ያሳያል። ሕግን ለመረዳት መሠረት በሆነው ወንጌል፣ የክርስቶስ ለእኛ መሞት፣ ሕግን በመጠበቅ ሳይሆን በእምነት መዳናችን ከሕጉ ጋር አብሮ የተነገረን ለዚህ ነው። የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡28፣ ሮሜ 4፡13–16፣ ገላትያ 2፡16፣ ገላትያ 3፡ 13፣ ፊልጵስዩስ 3፡9። እነዚህ ጥቅሶች ሕግን በመጠበቅ ረገድ ለመዳን ሳይሆን የምናምን ሰዎች ስለዳንን ሕጉን እንድንታዘዝ የሚረዱን እንዴት ነው?

ግንቦት 20
May 28

ማወቅና ማድረግ


በተራራው ስብከት፣ ኢየሱስ ከእርሱ ጋር እና እርስ በርስ ስለሚኖር ግንኙነት ብዙ ይናገራል ። በመልዕክቱ መጨረሻ ላይ በጣም የሚያም ነገር ተናግሯል፡- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” (ማቴ. 7፡21)። ኢየሱስ አንዳንዶች ስሙን እንደሚጠሩና እርሱን በግል ሳያውቁት ስለ እርሱ ብቻ እንደሚያውቁ ተናግሯል። እርግጥ ነው፣ እውቀትን መፈለግ ጠቃሚ ነው፣ እናም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የእግዚአብሔርን እውቀት በማጣታቸው እና ስለ እርሱ ያላቸውን እውቀት በመካዳቸው ሊጠፉ እንደሚችሉ ይነግረናል (ሆሴ. 4፡1፣ 6፣ 10)። ጊዜ የማይሽረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አስፈላጊነት በፍፁም ዝቅ አድርገን መመልከት የለብንም። ነገር ግን እንዲህ ዓይነቱ እውቀት እኛን የማይለውጥ እና ቁርጠኝነታችንን እና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ጉዞ የማያጠናክር ከሆነ ምንም ፋይዳ የለውም። “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:3)። ኢየሱስ ወደ ሰማይ የመግባት ቅድመ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማድረግ እና በመጨረሻም እግዚአብሔርን ማወቅ እንደሆነ ተናግሯል፤ ምክንያቱም እርሱን ሳናውቅ ፈቃዱን ማድረግ ስለማንችል ነው። ይህ ወሳኝ ነገር እና በጣም ምክንያታዊ ነው። ልጅዎ እንደሚወድዎት ከነገረዎት እና ብዙውን ጊዜ እርስዎ ያዘዙትን ካደረገ፣ ተግባሩ ለእርስዎ ያለውን ፍቅር እና አክብሮት ጥልቀት ያሳያል። በተመሳሳይ መንገድ፣ እግዚአብሔርን ስንወድ፣ ፈቃዱን ማድረግ እንፈልጋለን፣ ምክንያቱም ከዚህ የተሻለ ማድረግ ያለብን ነገር እንደሌለ እናውቃለን! ለእርሱ የምንሰጠው ምላሽ እና በዋናነትም፣ እንደ ፍቅራችን ብዛት ለእርሱ ያለን ታዛዥነት፣ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት እውነተኛ ተፈጥሮ ያሳያል። ኢየሱስ የተራራውን ስብከት ለአድማጮቹ ከባድ የመጨረሻ ተግዳሮት በመስጠት ያጠናቅቃል።

ግድድሮሹ ምን ነበር? ማቴዎስ 7:24-29ን ያንብቡ።



የኢየሱስን መልእክቶች በትክክል ስንሰማ፣ ተግዳሮትን ከመጋፈጥ እና ከመለወጥ መቆጠብ አንችልም። ስለዚህም ከእግዚአብሔር ጋር በቅርበት ግንኙነት የመኖር ንድፍ በነፍሳችን ላይ በእያንዳንዱ እስትንፋስ እንዲቀረጽ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጆሯችን መከፈትና ልባችን ተቀባይ መሆን አለበት፣። ሕይወታችን በዓለቱና በእግዚአብሔር ፍጹም ዕቅድ ላይ ሊገነባ ይችላል። ይህ የቅርብ ግንኙነት ንድፍ ምስጢር አይደለም። በእግዚአብሔር አነሳሽነት በተጻፈው ቃል ገጾች ላይ ተገልጧል፣ እናም ለእያንዳንዱ ሰው ይህን ያቀርባል። በእምነት ለመቀበል፣ የክርስቶስን ፍጹም ጽድቅ የራስ ማድረግ እና ከዚያም ያንን ጽድቅ መኖር የእያንዳንዱ ሰው የግል ምርጫ ነው።

ግንቦት 21
May 29


ተጨማሪ ሀሳብ


ሰይጣን በእግዚአብሔር ላይ ያቀረበው ዋናው ተግዳሮት ስለ ሕጉ በመሆኑ የሕጉ ርዕስ እንዲህ የተጣመመ እና በስህተት የሚስተዋል መሆኑ ሊያስደንቀን አይገባም። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ሕጉን ለማስወገድ እንደመጣ ያስቡ ነበር፣ ነገር ግን ያ ከእውነት የራቀ ነበረ። ኢየሱስ እግዚአብሔር ምን እንደሚመስል ሊያሳየንና ሕጉንና የእግዚአብሔርን ውብ ባሕርይ ብርሃን አብርቶ ሊፈጽም መጣ (ማቴ. 5:17-18) ። “ሰዎች መለኮታዊውን ዓላማ ለማሳካት ተስፋ ማድረግ የሚችሉት በልባቸው ውስጥ ለእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል አክብሮት ሲኖር ብቻ ነው። በዳዊት ዘመን እና በሰሎሞን የግዛት ዘመን ቀደምት ዓመታት እስራኤል የረታችውና የበለፀገችው ሕጉን ስለጠበቀች ነበር። በኤልያስና በኢዮስያስ ዘመን ተሐድሶ ሊመጣ የቻለው በሕያው የእግዚአብሔር ቃል ላይ እምነት ስለነበረ ነው። ኤርምያስም ወደ ተሐድሶ ባደረገው ጥሪ የጠየቀው ወደ እነዚህ የእውነት ቅዱሳት መጻሕፍት እንዲመለሱ ነበር።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ ነቢያትና ነገስታት፣ ገጽ 314(በአማርኛው)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ዛሬ ብዙዎች የሚከተሉት ባህል ኃጢአትን የሚመለከተው እንዴት ነው?

ቤተክርስቲያናችን እንዴት ምላሽ መስጠት አለባት?

2. ኃጢአት ከእግዚአብሔር እና ከሌሎች ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደሚያበላሽ በገዛ ዓይንዎ የተመለከቱት መቼ ነበር?

3. ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዝ በሕይወትዎ ውስጥ ቀላል ነው ወይስ ከባድ? ለዚህ

አስተዋጽኦ ያደረጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

4. ስማችን ሕጉን ምን ያህል በትኩረት እንደምንመለከተው የሚያሳየው እኛ አድቬንቲስቶች፣

በሕግ ለመዳን ከመሞከር ወጥመድ ማምለጥ የምንችለው እንዴት ነው? (የምናብ ሙከራ ያድርጉ፡ በፍርድ ቀን፣ ኃጢአትዎ ሁሉ በቅዱሱና ፍጹም በሆነው እግዚአብሔር ፊት ሲቀርብ መተማመኛዎት ምንድነው? ሕግን መጠበቅዎ? ወይስ በእርስዎ ምትክ የሚታየው የኢየሱስ ፍጹም ጽድቅ?)

5. እውቀት (ወይም የእውቀት ማነስ) አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው ግንኙነት ላይ

ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 24:3፣ 13፣14ን ያንብቡ።) ማጠቃለያ፡ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር በሚለየን ኃጢአት የተበከለ ነው። ሆኖም፣ እግዚአብሔር በአእምሯችን፣ በልባችን፣ በነፍሳችንና በኃይላችን እንድናውቀውና እንድንወደው ይጋብዘናል። ይህንን ስናደርግ፣ ለሌሎች የበለጠ ፍቅር ይኖረናል።

ለእግዚአብሔርና ለሌሎች እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በእግዚአብሔር ሕግ ውስጥ ተካቷል፣ ሕጉም ከእርሱና በዙሪያችን ካሉ ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት ለመጠበቅ የተሰጠ ነው።

የእግዚአብሔር ሕግ የእርሱ ባሕርይ ውብ ነጸብራቅ ነው፣ እናም ሕጉን ስንረዳ፣ ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት እየጠነከረ ይሄዳል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL