የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማሳደግ



2ኛ ሩብ ዓመት 2026


ሰኔ 6 - 12

12ኛ ትምህርት

Jun 13 - 19




ኢየሱስን አካፍሉት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 28:18-20፣ 2 ጴጥ. 3:18፣ 1ኛ ጴጥ. 3:8-15፣ ሆሴዕ 7፣ ዘካርያስ 10።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ልዑል እግዚአብሔር የተባ አንደበት ሰጥቶኛል፤ ስለዚህ ደካሞችን ብርቱ ለማድረግ ምን ማለት እንዳለብኝ ዐውቃለሁ፤ በየማለዳው ያነቃኛል፤ በመማር ላይ እንዳለ ተማሪ ለመስማት ጆሮዬን ያነቃዋል።”(ኢሳይያስ 50:4)።

ለፓስተር ጂ የተጨናነቀ የሰንበት ጠዋት ነበር። በሰንበት ትምህርት ክፍል ለማወያየትም ሆነ ለስብከቱ ዝግጅት ለማድረግ በማለዳ ተነስቶ ነበር፤ ከሰዓት በኋላም የወንጌል ጥረት ተከታታይ ትምህርትን ያስተምር ነበር። ቁልፎቹን ይዞ ከበሩ ወጥቶ በፍጥነት ሄደ። ብዙ ሰዎች በቅዳሜ ጠዋት መኪናቸውን ይዘው በመውጣታቸው ለቤተ ክርስቲያን እንዳያስረፍዱት በማሰብ ተበሳጭቶ በከተማው ጭንቅንቅ ውስጥ ነዳ። ሌሎቹ ሁሉ ወዴት እየሄዱ ነበር? ከዚያም ድንገት አንድ መኪና ከፊቱ መጥቶ ቆመ። ፍሬኑን ይዞ በብስጭትና በቁጣ ጡጫውን አነሳ፣ ሹፌሩም ላይ ጮኸ። በመጨረሻም፣ ፓስተር ጂ ወደ ቤተክርስቲያኑ ደረሰ። ትምህርቱን ለማስተማር ሲቆም፣ ዓይኖቹ ክፍሉን ቃኙና በሚያውቀው ፊት ላይ አረፉ፡ ከ20 ደቂቃ በፊት የተናደደበት የመኪና ሹፌር። በኋላ፣ አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ሹፌሩን አድቬንቲስት ያልሆነና ዘመዶቹን ሊጎበኝ እንደመጣ ሲያስተዋውቀው፣ ፓስተር ጂ፣ ከሚያውቋቸውም ሆነ ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር ያለው እያንዳንዱ ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋር ካለው ዘላቂ ግንኙነት በሚፈስ ፍቅር እንዴት መታጠብ እንዳለበት በድጋሚ አስተዋለ። ድርጊቶችዎ፣ በተለይም እንደ አማኝ፣ ሌሎች ላይ እንዴት ተፅዕኖ ሊያሳድሩ እንደሚችሉ በጭራሽ አያውቁም። ለሰኔ 13 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑደ

ሰኔ 7
Jun 14

ሞልቶ ሲፈስ


በማቴዎስ 28:18-20 ታላቁን ተልእኮ ያንብቡ። “ሁሉ” ወይም “ሁልጊዜ” (በግሪክኛ ተመሳሳይ ቃል “ፓስ” ነው) ብሎ ኢየሱስ የተናገረባቸው ጥቅሶች ውስጥ ያሉ የተለያዩ መልእክቶችን ይጻፉ።



ኢየሱስ መልእክቱን ለዓለም እንድናካፍል ኃላፊነት ሰጥቶናል፡- “ስለዚህ ሂዱና ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ሌሎችን ደቀ መዛሙርት ማድረግ የሚችሉ ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ነው። በዚህ መንገድ ሁላችንም ዘላለማዊውን ወንጌል እና የሦስቱን መላእክት መልእክት (ራዕ. 14፡6-12) እያወጅን ዓለማችንን በቅርብ ለሚሆነው የኢየሱስ ዳግም መመለስ እያዘጋጀን ነው። በክርስቶስ አዲስ ሕይወት የተቀበለ ማንኛውም ሰው ለመመስከር ተጠርቷል። ሆኖም፣ ብዙ ጊዜ ሰዎች መመስከርን የማይችሉት ወይም ማድረግ የማይፈልጉት ነገር አድርገው ያስባሉ። በመንገድ ጥግ ላይ እየሰበኩ ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እየሰጡ እራስዎን በዓይነ ሕሊናዎ ሊመለከቱ ይችላሉ፣ ስለዚህ ጭንቅላትዎን ነቅንቀው “እኔ አይደለሁም! በፍፁም! እኔ አይን አፋር ሰው ነኝ፤ ምስክርነት የምቾት ቀጠናዬ አይደለም።” ይሁን እንጂ፣ እውነተኛ ምስክርነት የሚገኘው እግዚአብሔር በሕይወትዎ ውስጥ ስለሚያደርገው ነገር የዓይን ምስክር በመሆን፣ በእርሱ ውስጥ እያደጉ ሲሄዱ የሚያስተምርዎትን በማየት እና ከዚያም ተሞክሮዎን ለሌሎች በማካፈል ብቻ ነው።

እግዚአብሔር በጣም ቸር ነው፣ ለእኛ ያደረገውም ይህ ዓለም ሊሰማው የሚገባው ምርጡ ዜና ነው። ዝም ማለት አንችልም እና ዝም ማለት የለብንም! እርሱ ዋጅቶናል፤ በስም ጠርቶናል - እኛ የእርሱ ነን።

በየትኛውም ቦታ ለማንም ከዚህ የተሻለ ዜና ሊኖር ይችላል? ምንም እንኳን በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን የነበሩት ደቀ መዛሙርት የተማሩ ወይም አንደበተ ርቱዕ ባይሆኑም፣ አሁንም ከእነርሱ መማር እንችላለን። የሐዋርያት ሥራ 1:8 እና የሐዋርያት ሥራ 4:13ን ያንብቡ። ለቀደምትዋ ቤተ ክርስቲያን ምስክርነት ምን ይመስል ነበር? ጴጥሮስና ዮሐንስ ሲመሰክሩ በሰሙት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳደሩ?



ጴጥሮስና ዮሐንስ “ያየነውንና የሰማነውን ከመናገር ዝም ማለት አንችልም” ብለው አወጁ (የሐዋርያት ሥራ 4:20)። “ከኢየሱስ ጋር ነበሩ” (የሐዋርያት ሥራ 4:13)። እናም ከእርሱ ጋር መሆናቸው ለማካፈል ግድ ብሏቸው ነበር። መንፈስ ቅዱስ በቃላቸው ውስጥ ድፍረትን እና አሳማኝ ኃይልን ሰጣቸው። አሁን በጸሎት ጊዜ ያሳልፉ። እግዚአብሔር በድፍረት ልትመሰክሩላቸው ወደምትችሏቸው ሰዎች ሲመራችሁ፣ መቼ መናገር እንዳለባችሁ እና ምን እንደምትናገሩ ለማወቅ ጥበብን እንዲሰጣችሁ ጠይቁ። 1ኛ ዮሐንስ 4:7-11ን አንብቡ እና ለዚህ አይነት ፍቅር ጸልዩ።

ሰኔ 8
Jun 15

ያለ ግዳጅ ግን በኃይል


ያለ ግዳጅ ግን በኃይል ኢየሱስ በየቀኑ ብዙ ሰዎችን የመቅረብ፣ የመፈወስ፣ የማጽናናት፣ የመስበክ እና የማስተማር ተነሳሽነትን እንዴት ጠብቆ እንዳቆየው አስበው ያውቃሉ? “ሕዝቡም እረኛ እንደሌለው በግ ተጨንቀውና ተመልካች የለሽ ሆነው ባየ ጊዜ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) ተብሎ ተፅፏል። ኢየሱስ እንዲተጋ ያስቻለው ለሰው ልጆች ያለው ፍቅር እና ርኅራኄ ነበር።

በተመሳሳይ መልኩ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ነፍሳትን ወደ እርሱ እና ወደ እውነት የመምራት ሸክም እንዲሰማን ሊገፋፋን ይገባል (2ኛ ቆሮ. 5:14)። በሕዝቡ መካከል እንግዶችን ሲመለከቱ ኢየሱስን ያውቁ ይሆን ብለው ወደ ዘላለም አስበው ያውቃሉ? የእግዚአብሔር ፍቅር በእርስዎ ውስጥ ለእንግዶች ሲሰራ ተሰምቶዎት ያውቃል? የእግዚአብሔር ፍቅር ነፍሳትን ወደ እርሱ የመምራት ሸክም እንዲሰማን ያስገድደናል። ኤርምያስ “ “ነገር ግን፣ “ከእንግዲህ የእርሱን ስም አላነሣም፤ በስሙም አልናገርም” ብል፣ ቃሉ በልቤ እንደ እሳት፣ በዐጥንቴም ውስጥ እንደ ረመጥ ሆነብኝ፤ አፍኜ መያዝ አቃተኝ፤ ጨርሶ መቋቋም አልቻልሁም።” ሲል ይህንን ገልጿል (ኤር. 20:9)። ሆኖም፣ ስለ እግዚአብሔር ለሌሎች ስናካፍል፣ አንድን ሰው እግዚአብሔርን ወይም መጽሐፍ ቅዱሱን እንዲቀበል ለማስገደድ ፈጽሞ መሞከር የለብንም። ለእግዚአብሔር አምልኮ መተላለፊያ እንድንሆን ራሳችንን መፍቀድ አለብን። ማስገደድ ከእግዚአብሔር ባህሪ ጋር ይቃረናል። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉ ከምታስታውቀዋ ዛፍ እንዲርቁ አላስገደዳቸውም (ዘፍ. 2:16-17)። ሰዎች ከጥፋት ውሃ እንዲድኑ ወደ መርከቡ እንዲገቡ አላስገደዳቸውም (ዘፍ. 7:1)። እስራኤላውያን ከእርሱ ጋር በገቡት ቃል ኪዳን እንዲጸኑ አላስገደዳቸውም (ዘዳግም 4:29-31)። በምትኩ ፍላጎቶቻቸውን አሟላላቸውና (ማቴ. 4:23-25) እንዲከተሉት ጠራቸው። ኢየሱስ ማንንም ሰው እርሱን ወይም እውነቱን እንዲከተል አላስገደደም፣ ነገር ግን በእኛ ተስፋ አይቆርጥም (ማቴ. 23:37)። እንደምናየው፣ አካሄዳችን ሁልጊዜ የኢየሱስን አቀራረብ ማንጸባረቅ አለበት። ኤለን ጂ. ኋይት እንዲህ ትላለች፣ “ሰዎች እሱን እንዲቀበሉት ማስገደድ የክርስቶስ ተልእኮ አካል አይደለም። ሕሊናን ለማስገደድ የሚጥሩት ሰይጣን እና በመንፈሱ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው… ሥራችንን የማያደንቁትን ወይም ከሐሳባችን ጋር የሚቃረኑትን ከጎዳን እና ካጠፋን የሰይጣንን መንፈስ ስለ መያዛችን አሳማኝ ማስረጃ እየሰጠን ነው።”—የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 487

ሰኔ 9
Jun 16

ኢየሱስን ለማካፈል ጠቃሚ ምክሮች


ኢየሱስን ለማካፈል ጠቃሚ ምክሮች ለእያንዳንዳችን የሚጠየቀው ጥያቄ፡- ኢየሱስን ለማን ነው የምታካፍሉት - ለፖስታ ሰራተኛው፣ ለመጋዘኑ ጸሐፊ፣ በየቀኑ ለእግር ጉዞ ስትወጡ ለምታዩት ሰው? እግዚአብሔር እያንዳንዱን አማኝ በዚህ ሥራ እንዲረዳው ይጠራል፣ እርሱም “ለደከመው ሰው በጊዜው ቃልን እንዴት መናገር እንደምትችሉ ታውቁ ዘንድ የተማሩትን ምላስ” እንደሚሰጣችሁ ቃል ገብቷል (ኢሳ. 50:4)። እንዲሁም የክርስቲያን ግዴታ ሁልጊዜም “ለእምነቱና በውስጣችን ስላለው ተስፋ ለሚጠይቁን ሁሉ መልስ ለመስጠት ዝግጁ መሆን ነው (1ኛ ጴጥ. 3:15)። 1ኛ ጴጥሮስ 3:8-15ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር ቃል በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚነግረን ምንድነው?



ለሌሎች ኢየሱስን ለማካፈል እንዴት መሆን እንደሚቻል የበለጠ ሲያስቡ ማስታወስ ያለብዎት አንዳንድ ቀላል ምክሮች እነሆ፡-



ሰኔ 10
Jun 17

ተንከራታቹ ልጅ


ልጆች፣ ምንም እንኳን ጠንካራና መንፈሳዊ በሆነ ቤተሰብ ውስጥ ቢያድጉም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ከነበራቸው ግንኙነት ለመለየት ሲመጥጡ ብዙዎች ልጅ ማፍራት የሚያስከትለውን ጭንቀት እና የልብ ህመም ያውቃሉ። ኤፍሬም፣ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ፣ ከጌታ ራቀ። ሆሴዕ 4:17 እና ሆሴዕ 7 ስለ ኤፍሬም ኃጢአቶች ምን ይነግሩናል?



በተጨማሪም፣ የኤፍሬም አያት ራሔል፣ ኤፍሬም ከእግዚአብሔር ጋር ከነበረው ግንኙነት ስለራቀ ምሳሌያዊ በሆነ ሁኔታ እንዳለቀሰች እናነባለን (ኤር. 31:15)። ጌታ በኤርምያስ 31:16-17 ላይ በተዘረዘሩት ቃላት ለእሷ ታላቅ ሀዘን ምላሽ ሰጥቷታል፡- “ድምፅሽን ከልቅሶ ዓይንሽንም ከእንባ ከልክዪ፤ ለሥራሽ ዋጋ ይሆናልና፥ ከጠላትም ምድር ይመለሳሉ።

ለፍጻሜሽም ተስፋ አለ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ ልጆችሽም ወደ ዳርቻቸው ይመለሳሉ።” ራሔል ስለ ዓመፀኛ ልጇ ከማለቅስ ይልቅ ተስፋ እንዳላት ተነግሯታል። ይህ ምዕራፍ ሌላ ምን ይነግረናል? ኤርምያስ 31:18-19ን ያንብቡ።



በእነዚህ ታሪኮች አማካኝነት፣ እግዚአብሔር ተስፋ ስለማይቆርጥ (ለኤፍሬምና ለጎሜር እንደሆነው ሁሉ) ሁልጊዜም ተስፋ እንዳለ እንማራለን። እግዚአብሔር ግን ደጋግሞ የሚገሥጽ ቢሆንም፣ ርኅራኄው ፈጽሞ አያልቅም፣ እናም በዚህ ምዕራፍ ውስጥም የእርሱ መልእክት ይቀጥላል (ኤር. 31:20ን ይመልከቱ)። ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት የተዉትን የቅርብ ዘመዶቻችንን እንኳን አሉታዊ በሆነ መንገድ ልንናገራቸው፣ ስለ እነርሱ ስናስብም ከፍተኛ ህመም፣ ብስጭት እና ተስፋ መቁረጥም ሊሰማን ይችላል። ሆኖም እግዚአብሔር እዚህ ላይ “ወደኋላ የቀረውን ልጅ” እንዳልረሳው ያስታውሰናል - በፍጹም! የእግዚአብሔር ለእንደዚህ አይነት ሰው ያለው ሀሳብ ጊዜያዊ ሳይሆን ከልብ የመነጨ እና ቅን ነው። እንዲያውም እግዚአብሔር እንደዚህ አይነት ግለሰቦችን እንደሚናፍቅ ይናገራል። ወደ እርሱ እንዲመለሱ ይናፍቃል፣ ምህረቱም ታላቅ ነው። በኤፍሬም ዓመፀኝነት ለደረሰባት ስቃይ ለራሔል ይህ የእግዚአብሔር ምላሽ መሆኑን ማወቅዎ ከጌታ ስለ ራቁና ስለምታውቋቸው ሰዎች ምን እንዲሰማዎ ያደርጋል? ይህ ግድድሮሽ የሚያበረታታዎት እንዴት ነው?

ሰኔ 11
Jun 18

መልሷቸው


መልሷቸው ሁላችንም ከእግዚአብሔር ጋር በምናደርገው ጉዞ ደካማ ወይም የሚዋዥቁ ጊዜያት ነበሩን - ልባችን ታማኝ ያልሆነበት ወይም ለረጅም ጊዜ ለብ ያልንባቸው ሁኔታዎች ነበሩ።

ከእርሱ ጋር ወደ ዘላቂ ግንኙነት የመለሰዎት ምንድን ነው? ዘካርያስ 10 ውስጥ እግዚአብሔር ሕዝቡን ወደ እርሱ ስለ መመለሱ አንዳንድ ውብ መልዕክቶችን እናገኛለን። ይህንን ምዕራፍ ቀስ ብለው ያንብቡ እና ዋና ዋና መልዕክቶቹን ፃፏቸው።



በተግባራዊ መልኩ፣ ከጌታ ጋር ካለው ግንኙነት የራቀ ወዳጅዎን እንዴት መቅረብና መያዝ እንደሚቻል ማወቅ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ለተለየ ውጤት እንዴት ማድረግ እንደሚችሉ ያስቡ ይሆናል፤ የተለየ የዓለም እይታ ስለያዙ አሁን ከእነርሱ ጋር እንዴት መገናኘት እንደሚሉ ግራ ይገባዎ ይሆናል። እና አሁንም ስለሚወስኗቸው ደካማ ውሳኔዎች ተስፋ መቁረጥ እና አቅም ማጣት ሊሰማዎት ይችላል። እነዚህ ሀሳቦች ሁልጊዜ የሚወዱት ሰው አያያዝዎ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፤ስለዚህ ከአዳኝዎ ጋር ካለዎት የግል ጊዜዎ እንዳገኙት በረከት መኖር እና መናገር በጣም አስፈላጊ ነው። ከእግዚአብሔር ለራቀው የትዳር ጓደኛዎ ወይም ልጅዎ የሚፀልዩት ጸሎት፣ የሚሰጡት የህይወት ምስክርነት፣ ድርጊትዎ እና አነጋገርዎ ሕይወታቸውንና ወደፊታቸውን በእጅጉ ሊለውጠው ይችላል። (በሉቃስ 22:31- 32 እና ዮሐንስ 21:15-17 ላይ ኢየሱስ ለጴጥሮስ የጸለየው ጸሎት የወደፊት ሕይወቱን እንዴት እንደለወጠው ያንብቡ።) ስለ እነርሱ ሊሰማዎት የሚችለውን ማንኛውንም ሀዘን፣ ፍርድ ወይም ኩነኔ ለየሱስ አስረክቡ፤ በምትኩ እነዚህን ስሜቶች እግዚአብሔር እርሱ ብቻ ሊሰጥ በሚችለው ፍቅር እንዲተካላችሁ ጠይቁት። ፍቅርንና ራስ ወዳድ ያልሆነን አመለካከት ማግኘት እንድትችሉ እግዚአብሔር በባህሪው እንዲሸፍናችሁ ጠይቁት። “ራስ ወዳድነት እንደጎደለው ሕይወት በሰው ነፍስ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር የሚችል ሌላ ኃይል እንደሌለ አስታውሱ። አፍቃሪ እና ተወዳጅ ክርስቲያን ለሰዎች ወንጌልን በመናገር ውስጥ በጣም ጠንካራው ማሳመኛ ነው።” ኤለን ጂ. ኋይት፣የፈውስ አገልግሎት፣ ገጽ 470። ሌሎችን ወደ ክርስቶስ የሚያመላክት ወጥ የሆነ ሕይወት፣ ክርስቶስን የካዱ ሰዎች ከእግዚአብሔር ብቻ ሊመጣ የሚችለውን በእኛ ውስጥ እንዲያዩ ያደርጋል። ማስተዋልን የሚያልፍ ሰላም፣ ፈጽሞ የማይለቅ ፍቅር እና ምንም ቢመጣ የሚያምን ተስፋን ያያሉ።

እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ፈጽሞ አይናወጥም። ይህንን በየቀኑ የምንቀበለውን ፍቅር፣ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች ልንሰጥ እንችላለን። ኤፌሶን 3:17-19 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል?

ሰኔ 12
Jun 19


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሙያው ምንም ይሁን ምን፣ ማንም ሰው ለወንድሙ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ከሌለው በስተቀር ለእግዚአብሔር ንፁህ ፍቅር የለውም። ነገር ግን ሌሎችን ለመውደድ በመሞከር ይህንን መንፈስ ማግኘት አንችልም። የሚያስፈልገው ከልብ ክርስቶስን ማፍቀር ነው። እኔነት በክርስቶስ ውስጥ ሲዋጥ ፍቅር ከውስጥ ይፈልቃል።”— ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 384 “ነፍሳትን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ለመሳብ በእውነተኛ ፍላጎት ስራቸውን በንቃት የሚሰሩ፣ በመንፈሳዊነት እና ለጌታ በመሰጠት ያደጉ ናቸው።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የወንጌል ሥራ፣ ገጽ 356 “ክፉን የመቃወም ጥንካሬ የሚገኘው ወደ ፊት በሚገፋና በሚናጠቅ አገልግሎት ነው።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 105. “ወደ እርሱ ደስታ ማለትም በመሥዋዕቱ የተዋጁ ነፍሳትን ወደ ማየት ደስታ ለመግባት እነርሱን ለመቤዠት በሠራው ሥራ መሳተፍ አለብን።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 142። “በአገልግሎት ከክርስቶስ ጋር መተባበር የማይፈልጉ፣ ከእርሱ ጋር በክብሩ አብሮ ለመሆን የሚያስችል ብቃት የሚሰጠውን ብቸኛውን ስልጠና እየገፉ ነው።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ ስነ ትምህርት፣ ገጽ 264።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ለየትኛውም አይነት ውጤታማ ምስክርነት ፍቅር መሰረታዊ እና አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?

2. ነፍሳትን ለጌታ መማረክ በግላችን ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ጉዞ ጋር የተያያዘ ነው። ይህ እውነት ሆኖ ያገኙት መቼ ነው?

3. እግዚአብሔርን ለሌሎች ለማካፈል የሚያስፈልግ መሰረታዊ ግንዛቤ አለ? ካለስ ምንድነው?

4. ለማያምን ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መስጠትን በተመለከተ፣ ከየት ይጀምራሉ?

የመጀመሪያ ትኩረትዎ ምንድን ነው፡ የተወሰኑ ትምህርቶቻችን ትክክል እንደሆኑ ማሳመን ወይስ ኢየሱስን እንዲያውቅ መጋበዝ?

5. ከውዳሴ መዝሙር መጽሐፍ “ዳንኩኝ!” (የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት መዝሙር፣

ቁጥር 24) የተወሰዱትን ቃላት ይዘምሩ ወይም ያዳምጡ። እናም እንዴት በህይወትዎ ይህን እያወጁ እንደሆነ ይግለፁ። ማጠቃለያ፡ የእግዚአብሔር ፍቅር እና ሕያው ቃሉ የዕለት ተዕለት ሕይወታችንን ሲሞሉ፣ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች እሱን ለመውደድ እና ለማካፈል ግድ ይለናል። ከአፉ የሚወጣው ቃል ወደ እርሱ በከንቱ እንደማይመለስ ነገር ግን የላከውን እንደሚፈጽም (ኢሳ. 55:11) በማመን፣ በጸሎት፣ በርህራሄ እና ትኩረት ሰጥተን መመስከር ይኖርብናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL