የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝሙር 80፣ 1ኛ ተሰ. 4:17፣ ራዕይ 21:9–27፣ ኢሳ. 25:8፣ ራዕይ 7:17፣ ራዕይ 21:4፣ ዮሐንስ 6:44።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ወዳጆች ሆይ፤ እኛ አሁን የእግዚአብሔር ልጆች
ነን፤ ወደ ፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እርሱ በሚገለጥበት ጊዜ
እናየዋለንና፣ እርሱን እንደምንመስል እናውቃለን።” (1ኛ ዮሐንስ 3:2)።
መጪው ጊዜ ምን ይዞላችሁ እየመጣ ይሆን? ወደፊት ምን ይጠብቃችኋል?
በአንድ ጊዜ አስፈሪ፣ አስደሳች፣ አስደንጋጭ እና አስደናቂ ሊሆን ይችላል።
ኢየሱስ ታማኝ እንደሆነ እና ቃላቱ እውነት እንደሆኑ እወቁ (ራዕ. 3:14)።
ወደፊት አስቸጋሪ ጊዜያት ይኖራሉ (ማቴ. 24:21፣ 22)፣ ነገር ግን ፈጽሞ እንደማይተወንና
እንደማይጥለን ቃል ገብቷል (ዕብ. 13:5)። እሱ የተናገረውን በትክክል ያደርጋል - አድርጓልም
ያደርጋልም (ዕብ. 10:23)። እና “እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል” (ማቴ. 24:13)።
በምድር ላይ የቀሩን ቀናት ምንም ያህል ቢሆኑም፣ ዓይኖቻችንን በኢየሱስ ላይ እናተኩር፣
እርሱን አጥብቀን እንመልከተው። ሁልጊዜ የእኛን ትኩረት ፈልጎ በሚሻማ ዓለም ውስጥ
ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም እንደ ዳዊት “ “ዐይኖቼ ሁል ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ናቸው፤
እግሮቼን ከወጥመድ የሚያላቅቃቸው እርሱ ነውና።” እንበል (መዝ. 25:15)።
በዚህ ሳምንት፣ ስለ ሰማይ (ማቴ. 5:12፣ ራዕ. 22:12)፣ ሰማይ ምን እንደሚመስል፣
በዋናነትም፣ ከፈጠረን፣ እስከ ሞት ድረስ ከወደደን፣ ከኃጢአታችን ከተቤዠን፣ እና በቅርቡ
ከሚመጣው ጋር መሆን ምን ያህል አስደናቂ እንደሚሆን እንማራለን። እስከዚያው ድረስ
በእምነታችን መቆየት አለብን።
*ለሰኔ 20 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
ዙሪያችንን ስንመለከት፣ ዓለም እየተንቀጠቀጠና እየቃተተ፣ ኢየሱስ የነገረን ምልክቶችም በዓይናችን ፊት እየተከሰቱ እያየን ነው። ጦርና የጦርነት ወሬዎች፣ ሀገራት በሌሎች ሀገራት ላይ ሲነሱ፣ ረሃብ፣ ቸነፈር፣ የመሬት መንቀጥቀጥ እና ስደት (ማቴ. 24:6–11) በዙሪያችን እየተከሰቱ ነው፣ እና ጊዜ እየገፋ ሲሄድ እየጨመሩ የሚሄዱ ይመስላሉ። አዎ፣ በከባድ ጊዜያት ውስጥ እንኖራለን - ከእግዚአብሔር ጋር የተጣበቀ ግንኙነት የሚያስፈልገን ጊዜ ላይ እንገኛለን። “የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቦአል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ።” (1ኛ ጴጥ. 4:7) ተብለናል። ይህ ከሆነ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የግል ግንኙነት ለማጠናከር ጊዜው አሁን ነው። ምንም ያህል ረጅም ጊዜ ቢቆይም፣ የራሳችን ሕይወት ሁሌም አጭር ናት። “እናንተ “ዛሬ ወይም ነገ ወደዚህች ወይም ወደዚያች ከተማ እንሄዳለን፤ በእርሷም አንድ ዓመት እንቈያለን፤ እንነግዳለን፤ እናተርፋለንም” የምትሉ እንግዲህ ስሙ። ሕይወታችሁስ ምንድን ነው? ለጥቂት ጊዜ የሚታይና ከዚያም የሚጠፋ ጭጋግ ነው” (ያዕቆብ 4:13፣ 14)። ይህ ማስጠንቀቂያ ምን ያህል እውነት እንደሆነ እናውቃለን። እነዚህን ቃላት አሁን የምናነብ ዛሬ ቀኑ ከማለቁ በፊት በሕይወት ላንኖር እንችላለን። ይህ በወደቀ ዓለም ውስጥ የመኖር አሳዛኝ እውነታ አካል ነው። እንግዲህ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ማረጋገጥ እና ሁልጊዜም ስለ እርሱ እና ስለ አዳኝ ጸጋው በመረዳት መኖር ምን ያህል አስፈላጊ ነው? መዝሙር 80 ላይ ለእግዚአብሔር ውብ የሆነ ልመና ያቀርባል። ምዕራፉን ያንብቡ እና በተለይም ከቁጥር 1-3፣ 14-17፣ 18፣ 19 ላይ ያሰላስሉ። እና “እኔ” የሚለውን ቃል “እኛ” በሚለው ቦታ ይተኩ። ይህ መዝሙር የተዘመረበት ጊዜ፣ ቦታ እና አውድ ምንም ያህል የተለየ ቢሆንም፣ በምን መንገዶች ከእርሱ ጋር መዛመድ እንችላለን?
ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ መነቃቃት ያስፈልገናል። እግዚአብሔር ያደረገልንን እና
እያደረገልን ያለውን ነገር ችላ ማለት ወይም መርሳት በጣም ቀላል ነው። በትግል ውስጥ
እያለፈ ቢሆንም እንኳን፡- “ፊትህንም አብራ፤ እኛም እንድናለን!” (መዝ. 80፡19) ብሎ
የማይፀልይ የትኛው አማኝ ነው?
ኢየሱስ ያደረገላችሁን ስትቀበሉ፣ ኃጢአታችሁ ይቅር እንደተባለላችሁ እና በእምነት
በተቆጠረላችሁ ፍጹም ጽድቅ እንደተሸፈናችሁ ስታውቁ፣ በእርሱ እንደዳናችሁ ማወቅ
ትችላላችሁ።
በተለይም የእርሱ ጽድቅ ብቻ እንደሚያድንዎት በማወቅ እግዚአብሔር “ፊቱን በእናንተ ላይ
ያበራል” የሚለውን እንዴት ተረዱት?
በመጨረሻ፣ ፊት ለፊት የተፈጠርነው ከእግዚአብሔር ጋር እንድንቀራረብ ነው (ዘፍ. 2:7)። የሰውን ልጅ ከፈጠረ ጀምሮ፣ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ያለንን የተበላሸ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ የቻለውን አድርጓል(ዮሐንስ 3:16)። ዘላለማዊነትን በልባችን ውስጥ አስቀምጧል፣ ነገር ግን የሰው ልጆች እግዚአብሔር ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያደረገውን ሊረዱ አይችሉም (መክብብ 3:11)። በዙሪያችን በእኛ ውስጥም እየተቀጣጠለ ያለው ታላቅ ተጋድሎ አካል ብንሆንም፣ ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንዲኖረን ወደፈለገው ግንኙነት እንድንመለስ የተከፈለልንን ከፍተኛ ዋጋ ለማሰብ በቂ ጊዜ አንወስድም። ብዙ ጊዜ፣ በምድራዊ ውጊያዎቻችንና በፈተናዎቻችን ውስጥ ተጠምደን እናገኛለን፣ “ “እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን፤እርሱም ሁሉን ለራሱ ባስገዛበት ኀይል፣ ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል።” (ፊልጵ. 3:20-21)። ዓለም ወደ ፍጻሜው እየቀረበ ሲመጣ፣ አንድ ቀን በምሥራቅ ሰማይ ላይ ትንሽ ነጭ ደመና እንደሚታይ እናውቃለን። እየቀረበ ሲመጣ፣ በዚያ ደመና ላይ “የሰው ልጅ የሚመስል በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ያለው” (ራዕ. 14:14) ተቀምጦ እናየዋለን። ኢየሱስ በሺዎች በሚቆጠሩ መላእክት (ማቴ. 25:31) ይታጀባል፣ እና ሁሉም ዓይኖች ያዩታል (ራዕ. 1:7)። ሲወርድ የእግዚአብሔርን የመለከት ድምፅ ሲሰሙ “በክርስቶስ የሞቱት ሰዎች መቃብሮች ይከፈታሉ (1ኛ ተሰ. 4:16)። የሚጠራቸውንም ድምፅ ያውቃሉ (ዮሐንስ 5:28)። ቀጥሎ ምን ይሆናል? 1ኛ ተሰሎንቄ 4:17ን ያንብቡ። በዋናነት ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 2:10-11 ላይ የጻፈው ነገር በመላው አጽናፈ ዓለም ያስተጋባል።
እንዴት ያለ እጅግ አስደናቂ፣ ድንቅ ሀሳብ ነው! አንድ ቀን ኢየሱስን እናየዋለን -
በእውነት እናየዋለን። ድምፁን እንሰማለን፣ እርሱም ጌታ እንደሆነ እንናገራለን። ስለ እርሱ
ያነበብንለት፣ ወደ እርሱ የጸለይንለት፣ ከሌሎች ጋር የተነጋገርንለት፤ ልባችን የናፈቀውን...
ፊት ለፊት እናየዋለን። እግዚአብሔር ታማኝ ስለሆነና ቃል ኪዳኖቹም እውነት ስለሆኑ በዚህ
ላይ እርግጠኞች መሆን እንችላለን (ራዕ. 22:6)።
በዚያ ቅጽበት፣ መለከቶቹ ሲነፉና የሰው ዓይን ሁሉ ኢየሱስን ሲያይ፣ መጠበቃችን ዋጋ
እንዳለው እናውቃለን። እያንዳንዱ የጽናት ጸሎት፣ ከእርሱ ጋር ለምናሳልፈው ጊዜ ቅድሚያ
የሰጠንበት እያንዳንዱ ቅጽበት፣ ስለ እሱ በድፍረት የተናገርንበት ጊዜ ሁሉ፣ እያንዳንዱም
ፈተና - ፊቱን በማየት ይጠናቀቃል (ራዕ. 22:4)።
በጳጥሞስ ደሴት እስረኛ የነበረው ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስ ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር ስንገናኝ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ራእይ ተሰጥቶታል። ራዕይ 21:9-11ን ያንብቡ። ምን ንፅፅር ተቀምጧል፣ እና ለምን ጥቅም ላይ እንደዋለ ያስባሉ?
ሙሽራይቱ ውብ ናት፣ እና በሠርጓ ቀን፣ሁሉም ሰው ሊያያት ይፈልጋል። የሠርግ ቀን
ለሙሽራውና ለሙሽሪት አብሮ መኖር የሚጀመርበት አዲስ ምዕራፍ ነው፤ እናም ይህ ደግሞ
ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ላይም እውነት ይሆናል። ኢየሱስ ለእኛ ቦታ ሲያዘጋጅልን
ቆይቷል (ዮሐንስ 14:1-3)፣ ለመግለጽ በጣም አስደናቂ የሆነ ውብ ቦታ ነው። እንዲያውም፣
“የሰው ልጅ ቋንቋ የጻድቃንን ሽልማት ለመግለጽ በቂ አይደለም። የሚገባቸው የሚያዩት
ብቻ ናቸው። ውሱን የሆነው አእምሮ የእግዚአብሔርን ገነት ክብር ሊረዳ አይችልም።”—
ኤለን ጂ. ኋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 675።
ምንም እንኳን አዲሱ ሰማይና አዲሲቱ ምድር ምን እንደሚመስሉ በትክክል መረዳት
ባንችልም፣ እግዚአብሔር ለዮሐንስ የዚህን ቦታ ራእይ ስላሳየው በቅርቡ የሚሆነውን
“ሠርግ” በጉጉት እንጠባበቃለን። በእርግጥም፣ “አሳባችሁ በላይ ባለው ላይ እንጂ በምድራዊ
ነገር ላይ አይሁን።” (ቆላ. 3:2) ተብለናል።
እግዚአብሔር ለዚህ ሰርግ በጥንቃቄ እየተዘጋጀ ነው፣ እናም ይህ “ሠርግ” በድንገት
እንዲይዘን አልፈለገም (ማቴ. 22:1-14፣ ማቴ. 25:1-13ን ይመልከቱ)። አጽናፈ ዓለም ይህንን
ክስተት የሚያይ ጉባኤ ነው፣ እናም በዚህ ታሪክ ውስጥ ካሉት ማዕከላዊ ሰዎች መካከል
ጥቂቶቹ ነን። ኢየሱስ ዳግም ሲመጣ ይወስደንና “ሙሽራ” ከሆነችው ከዚህች ከተማ
ጋር እንቀላቀላለን። የሚገርመው፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ (ቅዱሳን) ሙሽራ ተብለውም
ይጠራሉ (ራዕ. 19:7ን ይመልከቱ)፣ ምናልባትም “በቅድስት ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም፣
ከእግዚአብሔር ከሰማይ ወርደው፣ ለባሏ እንደ ተሸለመች ሙሽራ ተዘጋጅተው” ስለሚገኙ
ሊሆን ይችላል (ራዕ. 21:2)።
ይህ የቅድስት ከተማ ውብ መግለጫ በእግዚአብሔር ሕዝብ እና በከተማው መካከል
የጠበቀ ግንኙነት እንዳለ ያሳያል፣ ምክንያቱም ሁለቱም “ሙሽራ” ተብለው ተጠርተዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት መዲና እና ወኪል የሆነችውን ቅድስቷን
ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌምን” “የበጉ ሚስት፣ ሙሽራ” የሚል ዝርዝር መግለጫ ይሰጣል።
—ኤለን ጂ. ኋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 426።
ራእይ 21:9-27ን ያንብቡ። በምናባችን ለመሳል ያን ያክል የሚከብደን ለምንድነው?
አእምሯችንን በዚህ ቦታ ቃል በተገባልን ተስፋ ላይ ማድረግ መጀመር የምንችለው እንዴት ነው?
በሠማይ ምን ለማየት እንደምትጓጉ ተጠይቃችሁ ታውቃላችሁ? ልጆችን ብትጠይቁ፣“ነብር መጋለብ”፣ “ከቀጭኔ አንገት ላይ ተንሸራትቶ መውረድ” ወይም “ወደተለያዩ ፕላኔቶች መብረር” ሊሉ ይችላሉ። ታዳጊዎችን ብትጠይቁት፣ “ከቤት ሥራና ትምህርት ነክ ነገሮች መገላገላችን” ወይም “ያለ ምንም ጉዳት ከጓደኞቼ ጋር መንግሥተ ሰማያት ውስጥ ሳላቋርጥ መዞር” ሊሉ ይችላሉ። የአዋቂዎችን ቡድን ብትጠይቁ፣ “ከዚህ በላይ ህመም፣ ስቃይ ወይም ሞት በሌለበት ቦታ መሆን” ወይም “ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር እንደገና መገናኘት” ሊሉ ይችላሉ። እነዚህ ሁሉ ምላሾች ጥሩ እና እውነት ናቸው፣ እና በአዲሱ ሰማይ እና በአዲሱ ምድር የምንጠብቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ዘላለማዊነት በልባችን ውስጥ ይቀጣጠላል፣ እና በውስጣችን፣ ከዚህ እና አሁን ካለው የበለጠ ነገር መኖር እንዳለበት እናውቃለን። ከዘላለም ሕይወት ምን ሌሎች በረከቶችን ልንጠብቅ እንችላለን? ኢሳይያስ 25:8፣ ራዕይ 7:17 እና ራዕይ 21:4ን ያንብቡ።
በእርግጥ የሰማይ ታላቅ በረከት በመጨረሻ ኢየሱስን ማየት እና በዚህች በወደቀች
ምድር ላይ ላደረገልን ነገር በአካል ማመስገን ነው።
ከዘላለም ሞት በመስቀል ላይ ስለዳንን ለእሱ ያለንን ፍቅር እና አምልኮ ማጣጣም
እንፈልጋለን። “የታረደው በግ ኀይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣
ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል!” (ራእይ 5:12)።
መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስን “የእግዚአብሔር በግ” ሲል አስተዋወቀው (ዮሐንስ 1:35-
37)። ደቀ መዛሙርቱም በቅርበት ተከትለውት ነበር፣እና ዮሐንስ ራዕይ 14:4 እኛም እንዲሁ
እናደርጋለን ይላል። “ በጉ ወደሚሄድበት የሚከተሉት እነዚህ ናቸው” (ራእይ 14:4)። ሆኖም
ግን፣ በሰማይ እርሱን ለመከተል እንድንፈልግ፣ በመጀመሪያ እዚህ ምድር ላይ እርሱን መከተል
አለብን። በጉ የሆነው ኢየሱስ እረኛችን ነው፣ እና ከማንም በላይ መንገዳችንን ይመራናል።
ይህ እራሳችንን በምናገኝባቸው አስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ ስንታገል በጣም የሚያጽናና ነው፣
ነገር ግን ኢየሱስ በሰማይም ቢሆን መምራቱን አያቆምም።
ራዕይ 7:17 እንዲህ ይላል፣ “በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ እረኛቸው ይሆናልና፥
ወደ ሕይወትም ውኃ ምንጭ ይመራቸዋል።” ለዘላለም በእርሱ መገኘት ውስጥ መሆን
ስለምንፈልግ እንደ ሕዝቡ፣ በጎቹ፣ ኢየሱስን በሰማይ እንከተላለን። የእግዚአብሔር ሕዝብ
አንድ ገላጭ ባህሪ “ስሙ በግምባራቸው ላይ ይሆናል” (ራዕይ 22:4) የሚለው ነው።
ማለትም፣ ሁልጊዜ እርሱን እናስባለን።
https://www.youtube.com/watch?v=Nejb7N6mm_w በሚለው ሊንክ በመጠቀም
“በጉን ተከተሉ” የሚለውን መዝሙር ያዳምጡ እና ስንኞቹን የግል ጸሎትዎ አካል ያድርጉት።
ዛሬ በድጋሚ “ኑ” የሚለው ግብዣ ቀርቧል፤ የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡና ወደ እርሱ እንድንመጣ የተሰጠውን ግብዣ ያስተውሉ፡ ማቴ. 11:28-30፣ ኢሳ. 55:1-3፣ ዮሐንስ 6:44
መንፈስ ቅዱስ ዛሬ ወደ ኢየሱስ ሊስበን ይፈልጋል። ኢየሱስ እስኪመጣ ድረስ ወደ
እርሱ እንድንቀርብ፣ ዛሬም ሆነ በየቀኑ በእርሱ እንድንኖር ይጋብዛል። ምላሽ ስንሰጥና ወደ
እርሱ ስንቀርብ፣ ልባችን ለስላሳ ሲሆን አእምሮአችንንም ለርሱ ስናስረክብ፣ በዚህች ምድር
የመጨረሻ ቀን ምንም ያህል ብቁ ባንሆን እንደሚያስነሳን ስለምናውቅ ሰላም ይሰማናል።
ኢየሱስ “ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” (ዮሐንስ 6:37) ብሏል ።
ሌሎች ከኢየሱስ ጋር ወደ መዳን ግንኙነት እንዲመጡ ከቅዱስ መንፈስ ጋር የመሥራት
አጣዳፊነት ሊሰማን ይገባል። “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ። የሚሰማም፦ ና ይበል።
የተጠማም ይምጣ፥ የወደደም የሕይወትን ውኃ እንዲያው ይውሰድ።”(ራዕ. 22:17)።
ግብዣው እንደ ጸጋ ስጦታ በነፃ የሚቀርብ ነው። ወደ ሕይወታችን ስናስገባው እና
በልባችን፣ በአእምሯችን፣ በነፍሳችን እና በኃይላችን ሁሉ ስንወደው (ዘዳግም 6:5)፣ ዛሬም
ይሁን ለዘላለምም ሕይወታችን ይለወጣል።
ኢየሱስ ወደ እርሱ እንድንመጣ እንደሚጋብዘን ሁሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉት
የመጨረሻዎቹ ቃላት ይህንን ተስፋ ይሰጡናል፡- “አዎን፥ በቶሎ እመጣለሁ ይላል። አሜን፥
ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ና።” (ራዕ. 22:20)።
የሚመጣው እንዴት ባለ ፍጥነት ነው? ከኛ እይታ አንጻር፣ ዓይኖቻችንን በሞት
እንደተዘጉ፣ ቀጥሎ የምናውቀው ነገር የክርስቶስ መመለስ ይሆናል። ሕይወታችን ምን ያህል
በፍጥነት እንደሚያልፍ ስንመለከት፣ ኢየሱስ ለእኛ በፍጥነት የሚመለስ እንደዚያ ነው።
ምናልባት በትንሣኤው የመጀመሪያ ሀሳባችን “ዋው፣ ጌታ ሆይ፣ መምጣትህ በእርግጥም
ቅርብ ነበር!” የሚል ሊሆን ይችላል። በእርግጥ፣ አሁን ግን በመስታወት ውስጥ እንዳለን
በድንግዝግዝ እናያለን። ግን በዚያን ጊዜ ፊት ለፊት እናየዋለን። በመጠበቅ መታከታችን
ያቆማል። ይህንን ፍላጎት በእምነት፣ በእግዚአብሔር ፍቅር እና በቸርነቱ በመታመን ሁልጊዜ
በፊትዎ ሕያው አድርገው ይጠብቁት። ጌታ ኢየሱስ፣ እባክህ ና!
እምነታችን እንዲጸና፣ እምነታችን ላዳነን እና ለእኛም በቶሎ ለሚመጣው ለእርሱ ሙሉ
በሙሉ ራሳችንን እንድናስረክብ እንዲያስችለን እንፀልይ።
“የእግዚአብሔርን ቃል በመመገብ የክርስቶስን ኃይማኖት
ካልተቀበልን፣ ወደ እግዚአብሔር ከተማ የመግባት መብት አይኖረንም። ምድራዊ ምግብን
በመመገብና ዓለማዊ ነገሮችን የመውደድ ጣዕማችንን እየተለማመድን ከኖርን ለሰማይ
አደባባዮች ብቁ አንሆንም፤ በሰማይ የሚዘዋወረውን ንፁህ፣ ሰማያዊ ጅረት ማድነቅ
አንችልም። የመላእክት ድምፅና የበገናዎቹ ዜማ አያረካንም። የሰማይ ሳይንስ ለአእምሯችን
እንቆቅልሽ ይሆናል። የክርስቶስን ጽድቅ መራብና መጠማት አለብን፤ ለሰማያዊ መላእክት
ማኅበር እንድንበቃ በጸጋው ህይወት የመቀየር ተጽዕኖ መቀረጽ አለብን። . . .
“ከዚያም ሕዝቦች ከሰማይ ሕግ ውጪ ሌላ ሕግ አይኖራቸውም። ሁሉም ደስተኛ፣
የተባበረ ቤተሰብ ይሆናሉ፣ የምስጋና ልብስ ለብሰዋል።. . .በትዕይንቱ ላይ የንጋት ከዋክብት
አብረው ይዘምራሉ፣ የእግዚአብሔርም ልጆች በደስታ ይዘምራሉ፣ እግዚአብሔር አብ
እና ክርስቶስም ‘ከእንግዲህ ኃጢአት አይኖርም፣ ሞትም አይኖርም’ ብለው በአንድነት
ያውጃሉ። “ስለ ሰማይ፣ ውብ ስለሆነው ስለ ሰማይ፣ የመናገር ልማድ ማዳበር እንፈልጋለን።
እግዚአብሔር ሕያው እስከሆነ ድረስ የሚቀጥል ሕይወት እንነጋገራለን፣ ከዚያም ትንንሽ
ፈተናዎቻችንንና ችግሮቻችንን እንረሳለን። አእምሮአችንም ወደ እግዚአብሔር ይሳብ።”—
Ellen G. White, The Faith I Live By, p. 363።
1. ቀደምት ጽሁፎች ከሚለው መጽሐፍ፣ ገጽ 14-20 ላይ የሚገኘውን ኤለን ጂ. ዋይት
ስለ ሰማይ ያየችውን ራዕይ ያንብቡ። በዚህ መግለጫ ውስጥ በጣም የሚያስደንቅዎት
ምንድን ነው?
2. ኢየሱስን ፊት ለፊት እስኪያዩት ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎትን ግንኙነት
ኢየሱስን ፊት ለፊት እስኪያዩት ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር ያለዎትን ግንኙነት
ለማጠንከር ከዚህ የሩብ ዓመት ትምህርት የትኛውን የበለጠ ማስታወስ ያለብዎት
ይመስሎታል?
3. በሕይወትዎ ውስጥ ስለ ሰማይ ተስፋ መስማት ያለበት ማን ነው? በተቻለ ፍጥነት
በሕይወትዎ ውስጥ ስለ ሰማይ ተስፋ መስማት ያለበት ማን ነው? በተቻለ ፍጥነት
ለእነርሱ ለማካፈል ቁርጥ ውሳኔ ያድርጉ። ያስታውሱ፡ እርስዎ ራስዎ የሌለዎትን ተስፋ
ለእነርሱ ማጋራት አይችሉም።
ማጠቃለያ፡- በግቡ ላይ ስናተኩር፣ በእኛ “መልካም ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ
ክርስቶስ ቀን ድረስ እንደሚፈጽመው እርግጠኞች” እንሁን (ፊልጵ. 1:6)። ከእርሱ ጋር
ያለንን ግንኙነት የጀመረው ራሱ እግዚአብሔር ነው፣ እርሱም ይፈፅመዋል። በእምነት ለእኛ
በተቆጠረልን በክርስቶስ ጽድቅ ብቻ እያረፍን በፍቅርና በእምነት እንደግ።
ማሳሰቢያ
ድርጅቱ