መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከመጋቢት 8 – 14

አስራሁለተኛ ትምህርት

March 17–March 23

የመጋቢው ልማዶች

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 5:15–17፣ ቆለ. 3:23፣ ሉቃስ 12:35–48፣ ያዕ. 4:14፣ ሐዋ. 3:21፣ 1ቆሮ. 9:24–27፡፡

 

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ “ጎልማሳ መንገዱን እንዴት ያነጻል? በቃልህ መሠረት በመኖር ነው፡፡ በሙሉ ልቤ ፈለግሁህ፤ ከትእዛዛትህ ፈቀቅ እንዳልል አድርገኝ፡፡ አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ፡፡” (መዝ. 119፡9-11)፡፡

ል ማዶችዎ የህይወትዎን ዓላማና አቅጣጫ ገልጠው ያሳያሉ፡፡ መልካም የሆኑትን ልማዶች የሚያጎለብቱ መጋቢዎች--በጣም ታማኝ መጋቢዎች ናቸው፡፡ ዳንኤል በየቀኑ የመጸለይ ልማድ ነበረው (ዳን. 6፡10)፡፡ ወደ ምኩራብ መግባት ለጳውሎስ ልማዱ ነበር (ሐዋ. 17፡1-2)፡፡ በተጨማሪ ጳውሎስ “‘አትሳሳቱ መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን ጠባይ ያበላሻል’ ” (1ቆሮ. 15፡33) ሲል ጽፏል፡፡ መጥፎውን ባህሪ በመልካም ለመተካት መልካሙን ባህሪ መኮትኮትና ማዳበር ይጠበቅብናል፡፡

“ልማዶቻችን ግላዊ ማንነታችንን ለአሁንና ለዘላለም ቀርጸው ያኖራሉ፡፡ ትክክለኛውን ልማድ የሚተገብር ህይወት ባለቤት የሆኑና በማንኛውም የሥራ አፈጻጸም የታመኑ ሰዎች በሌሎች መንገድ ላይ የሚያበሩ የብርሃን ፈርጦች ይሆናሉ፡፡”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 4, p. 452.

በጎ ልማድ የሚፈጥረው ጎዳና አንድ ሰው የተመኘውን ሽልማት ለማግኘት የሚረዳው ፈጣን መንገድ ነው፡፡ ልማድ ስር የሰደደ ውሳኔ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር አንድ ነገር ለማድረግ--ከማድረግ ውጪ ማሰብም አያስፈልግም--እንደማለት፡፡ ያ ልማድ የግለሰቡን ድርጊት ተከትሎ በጣም ጥሩ ወይም በጣም መጥፎ ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ሣምንት መጋቢው የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን ኀይለኛ ልምዶች እንመለከታለን፡፡


 

መጋቢት 9
March 18
 

እግዚአብሔርን መሻት የማስቀደም ልማድ

 

ሁላችንም ብንሆን ልማዶች አሉን፡፡ ጥያቄው--ምን ዓይነት ናቸው? ጥሩ ወይስ መጥፎ? የሚል ሲሆን፤ ከሁሉም መልካም ልምዶች በላይ አንድ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በየቀኑ የማስቀደም መሻት በውስጡ ሊኖር ይገባል፡፡

“በየማለዳው ራስዎን፣ ነፍስዎን፣ አካልዎንና መንፈስዎን ለእግዚአብሔር ቀድሰው ይስጡ፡፡ በአዳኝዎ ላይ የአምልኮና የመታመን ልማዶችን አብልጠው ይመስርቱ፡፡” —Ellen G. White, Mind, Character, and Personality, vol. 1, p. 15. እንዲህ ዓይነት ልምድ ካለን ወደ ዘላለማዊ ህይወት በሚወስደው በጠባብ በር እንገባለን (ማቴ. 7፡14)፡፡

“ ‘ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ’ ” (ዘፀ. 20፡3) በማለት እግዚአብሔር ተናግሯል፡፡ የሱስ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቻችን ዐውድ ሲናገር “ ‘ከሁሉ አስቀድማችሁ ግን የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን እሹ’ ” (ማቴ. 6፡33) ይላል፡፡ በተጨማሪ እንዲህ ተብለናል “‘እናንተ ትፈልጉኛላችሁ፤ በፍጹም ልባችሁ ከፈለጋችሁኝ ታገኙኛላችሁ’ ” (ኤር. 29፡13)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 22፡37-38፣ ሐዋ. 17፡28፣ ኤፌ. 5፡15-17፣ ቆለ. 3፡23፡፡ እግዚአብሔርን በሕይወታችን እንዴት ማስቀደም እንዳለብን የሚረዱን እነዚህ ጥቅሶች ምን ይላሉ?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ጌታን ከሁሉ ማስቀደም እንዳለብን ከተሰጡን ምሳሌዎች ሁሉ የየሱስን ዓርአያነት የሚያህል የለም፡፡ የሱስ ከሁሉም ነገር በላይ አባቱን አስቀደመ፡፡ ይህን የማስቀደም ተግባር መመልከት የጀመረው ገና ብላቴና ሆኖ በፋሲካ በዓል ወቅት ከወላጆቹ ጋር ወደ የሩሳሌም በመጣ ጊዜ ነበር፡፡ ማርያም ከአጠገቧ ያጣችውን የሱስ “በቤተ መቅደስ” አግኝታው ይህ እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ስትጠይቀው “በአባቴ ቤት መገኘት” ይገባኛል (ሉቃስ 2፡46-49) ሲል ነበር የመለሰው፡፡

ከጸሎት ልማድ ህይወቱ እንደታየው፤ የሱስ ህይወቱን ሙሉ ከአባቱ ጋር መሆን ምኞቱ ነበር፡፡ ይህን ልማዱን ደቀ መዛሙርቱ ሙሉ ለሙሉ አልተረዱም ነበር፡፡ የሱስ ከአብ ጋር ሙሉ ለሙሉ ጥምረት መፍጠር ልማዱ ማድረጉን ተከትሎ፤ ሁሉም የጨለማ ኃይላት ከአባቱ ሊነጥሉት አልተቻላቸውም፡፡

እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን፣ ሀሳባችንና ነፍሳችን ለመውደድ በመወሰን የየሱስን ምሳሌ መከተል እንችላለን (ማቴ. 22፡37፡፡ ዘወትር በመጸለይ፣ የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና የየሱስን ጸባይ ለመከተል በመመኘት፤ በምናደርገው ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን በሕይወታችን ማስቀደም ልማዳችን ማድረግ እንችላለን፡፡ ደግሞስ ለክርስቲያኖች ከዚህ የተሻለ ምን ሊኖር ይችላል?

እስቲ እግዚአብሔርን ምን ያህል በህይወቴ አስቀድሜአለሁ? ብለው ራስዎን ይጠይቁ፡፡

መጋቢት 10
March 19
 

የየሱስን ዳግም ምጽአት የመጠባበቅ ልማድ

 


 

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃስ 12፡35-48፡፡ ምሳሌያዊው ታሪክ ራሳችንን ከየሱስ ዳግም ምጽአት ጋር እንዴት ማገናኘት እንዳለብን ምን ያስተምረናል? ሁላችንም ዘወትር የምናደርጋቸው ነገሮች ከተጨባጩ ዳግም ምጽአት ዐውድ አኳያ ሊሆኑ የሚገባው ለምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጋቢነት በየሱስ ዳግም ምጽአት ብርሃን በተግባር ገልጠን የምናሳየው ልማድ መሆን አለበት፡፡ ታማኝ ሳይሆኑ--ታማኝ እንደሆኑ የሚያስመስሉ መጋቢዎች ባህሪ ውሎ አድሮ በድርጊታቸው ይገለጣል፡፡ እውነተኛና ታማኝ መጋቢዎች ግን ጌታቸው አጠገባቸው ያለ ያህል ተግተው እየተጠባበቁና እየሠሩ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ ለወደፊት እየኖሩ በየቀኑ በታማኝነት ይሠራሉ፡፡ “እኛ ግን አገራችን በሰማይ ነው፤ ከዚያ የሚመጣውንም አዳኝ፣ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በናፍቆት እንጠባበቃለን” (ፊልጵ. 3፡20)፡፡

አብርሃም ዘላለማዊቷን ከተማ የተጠባበቀ ሲሆን (ዕብ. 11፡10) ጳውሎስ ደግሞ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ተጠባብቆአል (ዕብ. 10፡25)፡፡ እነርሱ ስለ ወደፊቱ በጥልቅ የሚያስቡ፣ ተስፋ የሚያደርጉ፣ ዕቅድ የሚያወጡና በማንኛውም ቅጽበት የሱስን ለመገናኘት ዝግጁ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡ እኛም የወንጌል መልእክት መደምደሚያ ወደ ሆነው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ተስፋ አትኩረን የመመልከታችንን ልማድ ከማዳበር ወደ ኋላ አንበል (ቲቶ. 2፡13)፡፡ አልፎ አልፎ ወይም በድንገት ወደ ትንቢት ከማጮለቅ ይልቅ ክርስቶስ ሲመለስ ለሚጠብቀን ዘላለማዊነት ሁሌም ግንዛቤ ሊኖረንና ያለማቋረጥ እየተመለከትን፣ እየተጠባበቅንና እየሠራን ልንገኝ ይገባል፡፡ ይህን እያደረግን በምድር የመጨረሻ ጊዜያቶች ክስተት ዙሪያ የሚሰነዘሩ ወፍ ዘራሽና ምናባዊ መላ ምቶችን ከእኛ ማራቅ ይኖርብናል፡፡ የዳግም ምጽአቱ ተስፋ ለሕይወታችን አቅጣጫ በመስጠትና ስለ ዛሬው ትክክለኛ ግንዛቤ በማስጨበጥ በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆነውን ነገር እንድናስታውስ ይረዳናል፡፡ ወደ የሱስ ዳግም ምጽአት የመመልከት ልምድ ለመጋቢው ትርጉምና ዓላማ ይሰጠዋል፡፡

መስቀሉ ከአዳኙ ጋር ላለን ቀጠሮ መንገዱን ጠርጎልናል፡፡ ክርስቶስ በአባቱ ግርማ ከቅዱሳን መላእክት ጋር የሚመጣበትን ሁናቴ የሚያመላክቱንን በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጡ ምልክቶች እንጠባበቃለን (ማር. 8፡38)፡፡ “ስለዚህ ዐይናችን የሚያተኩረው በሚታየው ነገር ላይ ሳይሆን በማይታየው ላይ ነው፤ የሚታየው ጊዜያዊ ነውና፤ የማይታየው ግን ዘላለማዊ ነው” (2ቆሮ. 4፡18)፡፡

አዎን፤ ሁሌም በተጨባጭ በዙሪያችን ያለው የሞት ሁኔታ በዚህ ምድር ያለን ቆይታ ምን ያህል ውሱንና ጊዜያዊ መሆኑን እንድንገነዘብ ሊረዳን ይገባል፡፡ ደግሞም የዳግም ምጽአቱ ተስፋ ሞት ራሱ ጊዜያዊና ኃላፊ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እንግዲያው እያንዳንዱ መጋቢ ክርስቲያን እንዴት መኖር እንዳለበት ተጽእኖ ሊያደርግ በሚገባ ተስፋ ይኸውም በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ብርሃን የመመላለሱ ተገቢነት እምብዛም አይገርምም፡፡ የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ተስፋ እየተጠባበቁ መኖር ለአሁንም ሆነ ለሁል ጊዜ ልማዳችን እናድርገው፡፡ መጠሪያ ስማችን በራሱ ተጠባባቂ የመሆናችንን እውነታ ይገልጣል፡፡

መጋቢት 11
March 20 

ጊዜን በብልሃት የመጠቀም--ልማድ

 

“ ‘እኛ ትላንት ስለተወለድን አንዳች አናውቅምና፤ ዘመናችንም በምድር ሁሉ እንደ ጥላ ነውና’ ” (ኢዮ. 8:9)፡፡

እየሠራ ያለውን ሠዓት ማቆም ይቻል እንደሆን እንጂ እየከነፈ ያለውን ጊዜ ማቆም ግን ፈጽሞ አይታሰብም፡፡

ካልተጠቀሙበት ተሸቀዳድመው ቶሎ፤

ጊዜ ታክሲ አይደለም አይጠብቅም ቆሞ፡፡

እንደተባለው ምንም ሳንሠራ እጆቻችንን አጣጥፈን ብንቀመጥ፤ ጊዜ ይሄዳል፣ ይነጉዳል እንጂ ቆሞ አይጠብቀንም፡፡

የሚከተሉት ጥቅሶች በዚህ በህይወት፣ በምድር ስላለን ጊዜ ምን ያስተምሩናል? ያዕ. 4:14፣ መዝ. 90:10-12፣ መዝ. 39:4-5፣ መክ. 3:6–8፡፡ በዚህ ምድር ያለን ጊዜ ምን ያህል የከበረ እንደሆነ አስመልክቶ ከጥቅሶቹ ልንወስድ የሚገባን መሰረታዊ መልእክት ምንድን ነው?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

ውሱን በሆነውና ዳግም መታደስ በማይችለው በጊዜ ውስጥ የምንመላለስ ክርስቲያኖች መልካም መጋቢዎች መሆናችን በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህ ህይወትና ለቀጣዩ፤ አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ ትኩረት እያደረግን፤ ጊዜን በጥበብ ጥቅም ላይ የማዋልን ልማድ ማጎልበት ይኖርብናል፡፡ ጊዜ ወርቅ ነው፤ ግን አላፊ ነው እንዲሉ የእግዚአብሔር ቃል ጊዜን አስፈላጊ አድርጎ በሚገልጽልን መሰረት በከንቱ እንዳያልፍ በአግባቡ ልንዳኘው የግድ ነው፡፡ ምክንያቱም ጊዜ አንዴ ከሄደ መልሰን ልንጠቀመው አንችልም፡፡ ገንዘብ ቢጠፋብን ቆየት ብለን፤ ምናልባትም እጥፉን መልሰን እናገኘዋለን፡፡ ጊዜ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ አንዷ ሰከንድ አለፈች ማለት--ለዘላለም ነጎደች ነው፡፡ ምናልባት ያቺን ያለፈች ሰከንድ ወደ ኋላ ከመመለስ ይልቅ የፈሰሰን ውሃ ማፈስ ይቀል ይሆናል፡፡ በዚህ የተነሳ በእግዚአብሔር ከተበረከቱልን እጅግ የከበሩ ነገሮች መሃል አንዱ ጊዜ ነው፡፡ የተሰጠንን ጊዜ በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል ልማድ ማጎልበታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

“ዘመናችን የእግዚአብሔር ነው፡፡ እያንዳንዱ ደቂቃ የእርሱ እንደመሆኑ መልሰን ለእርሱ የማዋል እጅግ የከበረ የውዴታ ግዴታ አለብን፡፡ ማንንም ያለ አንዳች መክሊት እንዲሁ ያልተወው አምላክ ጊዜያችንን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንድናውል በጥብቅ ይጠይቀናል፡፡

“የጊዜ ዋጋ ከስሌት በላይ ነው፡፡ ክርስቶስ እያንዳንዱን ጊዜ እንደ ከበረ ነገር ይመለከተው እንደ ነበር ሁሉ፤ እኛም የእርሱን ምሳሌ ልንከተል ይገባል፡፡ ህይወት እጅግ አጭር እንደመሆኗ ከንቱ በሆነው ቧልትና ፌዝ አናባክናት፡፡ ለዘላማዊው ህይወት ዝግጅት የምናደርግባቸው ጥቂት የሙከራ ጊዜያቶች ብቻ አሉን፡፡ ስለዚህ የምናባክነው፣ ለራስ ወዳዱ የግል ፍላጎት ወይም ለኃጢአት እርካታ የምናውለው ጊዜ የለንም፡፡” —Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 342.

“እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ” (ኤፌ. 5፡15-16)፡፡ ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ምን ይነግረናል? ምክረ ሃሳቦቹን አሁን የምንገኝበት ሁናቴ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 12
March21
 

አዕምሮን፣ አካልንና ነፍስን ጤናማ አድርጎ የመጠበቅ--ልማድ

 

እኛ መጀመሪያ በአእምሮ፣ በአካልና በመንፈስ ፍጹም ሆነን በእግዚአብሔር ተፈጠርን፡፡ ነገር ግን ኃጢአት እጹብ ድንቅ በነበረው ማንኛውም የፍጥረት ሥራ ላይ ውድመትና ጥፋት አደረሰ፡፡ እግዚአብሔር እኛ መጀመሪያ ወደ ነበረን ፍጹም ማንነት የመመለስ ሂደት ላይ መሆኑ መልካም የምስራች (ወንጌል) ነው፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 3፡21፣ ራእ. 21፡1-5፡፡ በጥቅሶቹ ምን ዓይነት ተስፋ እናገኛለን? የመጨረሻውን ዳግም መታደስ እየተጠባበቅን ዛሬን እንዴት ልንኖር ይገባል?

ክርስቶስ በዚህ ምድር ይመላለስ በነበረ ጊዜ ሰብዓዊውን ፍጡር ለመጨረሻው ተሃድሶ ለማዘጋጀት--በመንፈስ፣ በአእምሮና በአካል የማነቃቃት ሥራውን ግንባር ቀደም ሆኖ ያለመታከት ሠራ፡፡ የየሱስ የፈውስ አገልግሎት እስከ መጨረሻው በተቻለ ጤናሞች ሆነን እንድንመላለስ የእግዚአብሔር ፍላጎት የመሆኑ ምስክር ነው፡፡ ሰለዚህ መጋቢዎች ጤናማውን የአኗኗር ዘይቤ እየተከተሉ አእምሮአቸውን፣ አካላቸውንና ነፍሳቸውን የማበልጸግ ልማድ ይከተላሉ፡፡

በመጀመሪያ፡ አእምሮ አብልጦ ጥቅም ላይ እንዲውል በተደረገ ቁጥር ይበልጥ እየበለጸገ፣ እየጎለበተ ይሄዳል፡፡ “በመጨረሻም ወንድሞች ሆይ፤ እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ” (ፊልጵ. 4፡8)፡፡ እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ሰላም ያመጣል (ኢሳ. 26፡3) ደግሞም “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” (ምሳ. 14፡30)፡፡ ጤናማው አእምሮአዊ ልማድ ሰብዓዊው የኃይል ማዘዣ ጣቢያ ምርጥ አገልግሎት እንዲሰጥ ያስችለዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ፡ እንደ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና ተገቢውን ምግብ የመመገብ መልካም የጤና አጠባበቅ ልማድ መኖሩ፤ ለራሳችን ጥንቃቄ እያደረግን መሆኑን ያሳያል፡፡ ለአብነት ያህል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የጭንቀት ስሜት እንዲሁም የደም ግፊት እንዲቀንስ ያደርጋል፣ ተለዋዋጩን ስሜት (ሙድ) ያሻሽላል፣ እንዲሁም በማንኛውም መድኃኒት ቤት መደርደሪያ ሊገኝ ከሚችል ጸረ-እርጅና መድኃኒት ይልቅ ፍቱኑ እርሱ ነው፡፡

በሦስተኛ ደረጃ፡ መጋቢው ነፍሱን ለማበረታታት የሚያስችለውን መልካም ልማድ ያዳብራል፡፡ ነፍሳችንን ወደ እግዚአብሔር አንስተን (መዝ. 86፡4-5) እርሱን እንጠባበቅ (መዝ. 62፡5)፡፡ “ለእውነት ታማኝ ሆነን ስንመላለስ” (3ዮሐ. 3) ነፍሳችን ትበለጽጋለች “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ ያለነቀፋ” ትጠበቃለች (1ተሰ. 5፡23)፡፡

ስለ ልማዶችዎ አሰብ ያርጉና--በመንፈስዎ፣ በአካልዎ፣ በአእምሮዎና በጤናዎ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ እያሳደሩ እንደሆነ ይመልከቱ፡፡ መሻሻል ያመጡ ዘንድ በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ለውጥ እንዲያደርጉ የሚጠየቁባቸው ክፍሎች ይኖሩ ይሆን? የመጨረሻውን ተሃድሶ በሚጠባበቁበት በአሁኑ ወቅት የሕይወትዎ የጥራት ደረጃ እንዲሻሻል የትኛውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ የኔ ብለው ይይዛሉ? ምን ዓይነት ምርጫዎች ማድረግስ ይችላሉ?

መጋቢት 13
March 22

ራስን የመግዛት፡ ልማድ

  

ራስን መግዛት ወይም በሥነ ምግባር መምራትና ማስተዳደር መጋቢው ሊኖሩት ከሚችሉ እጅግ አስፈላጊ ባህሪያት መካከል አንዱ ነው፡፡ “እግዚአብሔር የኀይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንምና” (2ጢሞቴ. 1፡7)፡፡ ራስን በሥነ ምግባር ማነጽ ለሚለው ሃረግ የግሪክ አቻው ቃል ሶፍሮኒስሞስ ሲሆን በአዲስ ኪዳን ጥቅም ላይ የዋለው በዚህ ስፍራ ብቻ ነው፡፡ ቃሉ ሚዛን ጠብቆ መጓዝንና ከአምላካዊው መርኅዎች ያለማፈንገጥ ክህሎቶችን በውስጡ ይዞአል፡፡ ራስን በሥነ ምግባር መምራት “መልካሙን ከክፉ ለመለየት” (ዕብ. 5፡14) ይረዳናል፡፡ በዙሪያችን ያለውን ሁናቴ ለማስተዋል ያስችለናል፤ እንዲሁም ግፊቶችና ውድመት ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮች፤ የቱንም ዓይነት ውጤት ሊኖራቸው ቢችል እንኳ፤ በእርጋታና በትህትና ተቋቁመን ለማለፍ ያስችለናል፡፡ ከሳምሶን በተቃራኒ የነበረው ዳንኤል በአናብስት ጉድጓድ ቢጣል እንኳ ከትክክለኛው ሥነ ምግባር ፍንክች አላለም፡፡ ባንጻሩ ከጥብቅ ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ሕይወት ይመራ የነበረው ሳምሶን፤ ራሱን ለማረቅ ወይም ሚዛናዊውን አካሄድ ለመከተል ያሳየው ተነሳሽነት በእጅጉ አነስተኛ ነበር፡፡ በፈርዖን ቤት የነበረው ዮሴፍ ሥነ ምግባራዊውን መርኅ ሲከተል፤ ሰለሞን ግን በባዕድ አምልኮ ተዘፈቀ (1ነገሥ. 11፡4-5)፡፡

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 9፡24-27፡፡ ጳውሎስ ራስን ስለ መግዛት ምን ይላል?

--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

 “ዓለም ለሥጋ ፍላጎት ማርኪያ ውሎአል፡፡ ስህተትና ተረት ሰፍኖአል፡፡ ነፍሳትን ለማጥፋት የሰይጣን መሰናክሎች በዝተዋል፡፡ እግዚአብሔርን በመፍራት ራሳቸውን በፍጹም ቅድስና ለመጠበቅ የሚሹ ሁሉ ራስን የመግዛትና የመቆጣጠር ትምህርት መማር አለባቸው፡፡ የምግብ ፍላጎትና ስሜታዊ ግፊት ሁሉ ለአእምሮ ኃይል ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ ይህ ራስን የመቆጣጠር ችሎታ ከእግዚአብሔር ቃል የሚገኘውን የተቀደሰ እውነት ለማስተዋልና በተግባር ለመተርጎም የሚያስችለንን መንፈሳዊ የአእምሮ ጥንካሬ ለማግኘት አስፈላጊ ነው፡፡” የዘመናት ምኞት ገጽ 82- 83 (አማርኛው ትርጉም)፡፡

ራስን መግዛት በዕለት ከዕለት ልማድ መዳበርና መሻሻል ይችላል፡፡ እግዚአብሔር--ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራሳችሁን አሠልጥናችሁ (1ጢሞቴ. 4፡7) “በኑሮአችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ” (1ጴጥ. 1፡15) ሲል ጥሪ ያቀርብልናል፡፡ መጋቢዎች ልዩ ችሎታና ብቃት እንዳላቸው አትሌቶችና ሙዚቀኞች፤ ራሳቸውን ለመግዛት የሚያስችላቸውን ልምምድና ሥልጠና ማድረግ አለባቸው፡፡ በእግዚብሔር ኃይልና ትጋት በተሞላው የገዛ ጥረታችን ግድ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ ራሳችንን በሥነ ምግባር መምራትና ማስተዳደራችን የግድ ይሆናል፡፡

በዚህ በኃጢአት በወደቀና በተበላሸ ዓለም ታማኝ መጋቢዎች ሆነን ለመኖር የሚያስችለንን፤ ራስን በሥነ ምግባር የመምራት ኃይል በብቸኝነት ለሚሰጠን፤ ለእግዚአብሔር መገዛት መማር የምንችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 14
March 23 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 

ጥቂቶች ብቻ ታማኝ ሆነው በቀሩባቸው ፍቅረ-ቁስ እና አመጸኝነት አብልጦ በተትረፈረፈበት በጥንቱ ዓለም፤ ሄኖክ እና ኖኅ ግን አረማመዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ ልማዳቸው አደረጉ (ዘፍ. 5፡24፣ 6፡9)፡፡ እነዚያን የመልካም መጋቢነት ዐደራዎች ሲወስዱ፤ የእግዚአብሔርን ጸጋ ተገንዝበው ተቀብለው ነበር፡፡

ከጥንት አንስቶ ለዘመናት ብዙዎች እንደ ሄኖክ እና ኖኅ አረማመዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አድርገዋል፡፡ ለምሳሌ ዳንኤልና ጓደኞቹ “በአረማውያን የሐሰት ኃይማኖቶች መሃል የእውነተኛው ኃይማኖት ተወካዮች ሆኖው ለመቆም የአእምሮ ንጽህናና ፍጹም የሆነ ክርስቲያናዊ ባህሪ ሊኖራቸው የግድ መሆኑን ተገንዝበው ነበር፡፡ ደግሞም እግዚአብሔር ራሱ መምህራቸው ነበር፡፡ ተግተው መጸለያቸው፣ በጥንቃቄ ማጥናታቸውና ከማይታየው ጋር የጠበቀ ቁርኝት መፍጠራቸው እንደ ሄኖክ እነርሱም አረማመዳቸውን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲያደርጉ አስቻላቸው፡፡” —Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 486.

“አረማመድን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረግ” የመጋቢውን ድርጊት በመግለጽ በምድር ህይወቱ ነጋ ጠባ ከእግዚአብሔር ጋር መኖሩን ያሳያል፡፡ ብልሁ መጋቢ በተበላሸው ዓለም ውስጥ እየኖረ አረማመዱን ግን ከእግዚአብሔር ጋር ያደርጋል፡፡ በተመሳሳይ እኛም ከእግዚአብሔር ጋር እንዲህ ዓይነቱን ግንኙነት በመፍጠር ብቻ በክፉው ከመዘረር ወደ ማሸነፍ መሸጋገር እንችላለን፡፡

ታማኝ መጋቢ መሆን ሁሉንም የህይወታችንን ክፍል ባካተተ መልኩ ከእግዚብሔር ጋር በስምምነት መጓዝ መጀመር ይጠይቃል (አሞጽ 3፡3)፡፡ በክርስቶስ መራመድ (ቆለ. 2፡6)፣ በአዲስ ሕይወት (ሮሜ 6፡4)፣ በፍቅር (ኤፌ. 5፡2)፣ በጥበብ (ቆለ. 4፡5)፣ በእውነት (መዝ. 86፡11)፣ በብርሃን (1ዮሐ. 1፡7)፣ ያለ ነውር (ምሳ. 19፡1)፣ በአምላካዊው ሕግ (ዘፀ. 16፡4)፣ በመልካም ሥራ (ኤፌ. 2፡10)፣ በቀጥተኛው መንገድ (ምሳ. 4፡26) እንድንጓዝ ተጠርተናል፡፡

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. ትህትና ምንድን ነው? በመጋቢው ህይወት የሚኖረው ሚናስ ምን ይመስላል? (ማቴ. 11:29፣ ኤፌ. 4:2፣ ፊልጵ. 2:3፣ ያዕ. 4:10)፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር በሚኖረን አረማመድ ትህትና አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ሚክ. 6፡8)

  2. ራስን በሚጎዳ መጥፎ ልማድ ውስጥ የታሰሩን ሰዎች ልንረዳ በምንችልባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያዩ፡፡ እርስዎ እንደ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባልነትዎ እነዚህን ወገኖች ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

  3. ክርስቲያን መጋቢዎች ሊኖሯቸው የሚገቡ ሌሎች መልካም ልማዶች ምንድን ናቸው? ቲቶ 2:7፣ መዝ. 119:172፣ ማቴ. 5:8

  4. ስለ ጊዜና በጊዜ ምስጢራዊነት ዙሪያ ተነጋገሩ፡፡ ለመሆኑ ጊዜን እንዲህ የሚያከንፈው ነገር ምንድን ነው? ጊዜ ምን እንደሆነ እንኳ ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? በዚህ ምድር ካለን አጭር ቆይታ አኳያ መልካም መጋቢዎች መሆናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?