መጋቢነት፡ ልብ አነሳሹ ሞተር
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2018

ከመጋቢት 15 – 21

አስራሶስተኛ ትምህርት

March 24–March 30

የመጋቢነት ውጤቶች

 

ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 3:1–9፣ ሕዝ. 14:14፣ ፊልጵ. 4:4–13፣ ምሳ. 3:5፣ 1ጴጥ. 2:11-12፣ ማቴ. 7:23፣ 25:21፡፡

የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ “ምንም እንኳ ክፉ እንደምትሠሩ አድርገው ቢያሟችሁም ለፍርድ በሚመጣበት ጊዜ መልካሙን ሥራችሁን ዐይተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ፣ በአሕዛብ መካከል በመልካም ሕይወት ኑሩ” (1ጴጥ. 2፡12)፡፡

እ ኛ እንደ መጋቢነታችን የምናመልከው አምላክ ምስክሮች ሆነን መመላለስ ይጠበቅብናል፡፡ ይኸውም መልካም በሆነው ነገር ሁሉ በዙሪያችን ላሉ ብርቱ ተጽእኖ አሳዳሪ መሆን ነው፡፡


ከገሃዱ ዓለም ተነጥሎ መኖር የታሪካችን አካል አይደለም፡፡ ይልቁንም የተሰጡንን ነገሮች ለማያውቁ የተሻለውን የአኗኗር ዘይቤ የማንጸባረቅ ልዩ መብትና ጥቅም ተችሮናል፡፡ መጋቢነት እግዚአብሔርን እየመሰልን እንድንኖር ለቀረበልን ጥሪ ምላሽ እየሰጡ እያበቡና እየዳበሩ መሄድ ነው፡፡ እግዚአብሔር በምድር ከሚስተዋለው ማንኛውም ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ በተለየ የምንኖርበትን ችሎታ ሰጥቶናል (2ቆሮ. 6፡17)፡፡ ሌሎች ይህን ተገንዝበው ምስጢሩን እስከ መጠየቅ ይደርሳሉ፡፡ “ክርስቶስን ጌታ አድርጋችሁ በልባችሁ ቀድሱት፡፡ እናንተ ስላላችሁ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋችሁ ሁሉ መልስ ለመስጠት ሁል ጊዜ የተዘጋጃችሁ ሁኑ፤ ነገር ግን ይህን ሁሉ በትሕትናና በአክብሮት አድርጉት” (1ጴጥ. 3፡15)፡፡


በዚህ የሩቡ ዓመት የመጨረሻ ክፍል ትምህርታችን መጋቢው በህይወቱ ሐሴት የሚያደርግባቸው ቁልፍ የሆኑ ግላዊ ጥቅሞች፣ መንፈሳዊ ውጤቶች፣ ስኬታማ ተግባሮችና ተጽእኖዎች ዙሪያ ምልክታ የምናደርግ ሲሆን ይኸውም “የክብር ተስፋ የሆነው በእናንተ ውስጥ ያለው ክርስቶስ” (ቆለ. 1፡27) መሆኑን እናውቅ ዘንድ ነው፡፡


 

መጋቢት 16
March 25
 

መጋቢነትና እውነተኛ መንፈሳዊነት

 



እውነተኛ መንፈሳዊነት ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ነው፡፡ እውነተኛ መንፈሳዊነት ያላቸው ሕዝቦች ለአምልኮ ያዘነበሉና እርሱን ደስ የሚያሰኘውን በተግባር እየገለጡ፣ (መዝ. 4፡3፣ ቲቶ 2፡12) ክርስቶስን እየመሰሉ የተቀደሰ ኑሮ ይኖራሉ (ቲቶ 1፡1)፡፡ እውነተኛ መንፈሳዊነት የእውነተኛ ኃይማኖት ማሳያና የዘላለማዊ ሕይወት ተስፋ ቃል ነው፡፡ የትኛውም ምድራዊ ፍልስፍና፣ ሀብት፣ ዝና፣ ሥልጣን ወይም ከታላቅ መወለድ የዚህ ተስፋ ባለቤት አያደርግም፡፡


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 3፡1-9፡፡ ጳውሎስ ከታማኙ መጋቢ ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላለው ጉዳይ የሚሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጽሐፈ ኢዮብ ስለ ኢዮብ ጸባይና ድርጊቶች ገለጻ ያደርግልናል፡፡ በሥቃይና መከራ ውስጥም ሆኖ--እውነተኛ መንፈሳዊነት የተላበሰውን ገጽታ ያሳየናል፡፡ በተጨማሪ ሰይጣን እንደዚያ ያለውን አኗኗር ምን ያህል እንደሚጠላ ያሳየናል፡፡ የኢዮብን ምርጥ እምነትና አኗኗር ባለቤትነት ማንም ሊስተካከለው እንደማይችል እግዚአብሔር ራሱ ማረጋገጫ የሰጠበት ጉዳይ ነው (ኢዮ. 2፡3)፡፡


“ዖፅ በሚባል አገር የሚኖር ኢዮብ የተባለ ሰው ነበረ፤ ይህ ሰው ነቀፋ የሌለበት፣ ቅን፣ እግዚአብሔርን የሚፈራና ከክፋት የራቀ ነበር” (ኢዮ. 1፡1)፡፡ የኢዮብ እምነት ከቃላት ያልዘለለ ወይም ኃይማኖታዊ ሥርዓት ብቻ ያቀፈ ሳይሆን የህይወቱ ክፍል እንደነበር ከጥቅሱ እንመለከታለን (ኢዮ. 1፡5)፡፡ እግዚአብሔርን መፍራቱ በአስከፊ የመከራ ወቅቶቹ እንኳ ሳይቀር በእውነተኛ መንፈሳዊነት በኖረው አጠቃላይ የሕይወት ዘመኑ በይፋ መታየት የቻለ ነበር፡፡ በእውነተኛ መንፈሳዊነት መኖራችን ፍጹምነትን በዙሪያችን እንድናንጸባርቅ ያስችለናል እንጂ ፍጹማን ነን ለማለት አያስደፍርም፡፡


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሕዝ. 14፡14፡፡ ጥቅሱ ስለ ተወሱት ሰዎች ጸባይ ምን ዓይነት ምስክርነት ይሰጣል? በእኛ በሁላችንም ውስጥ መታየት ስላለበት ነገር በጋራ የያዘው ነጥብ ምንድን ነው?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጋቢነት በእርግጥም በእውነተኛ መንፈሳዊነት የምንኖረው ህይወት መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ መጋቢዎች በእውነተኛ መንፈሳዊነት የሚመላለሱ ሲሆን፤ ይህ ማንነት በአኗኗራቸውና በተቀበሉት ዐደራ አያያዝ ይገለጣል፡፡ እምነታቸው በሚያደርጉት ነገር ብቻ ሳይሆን በማያደርጉትም ጭምር ይታያል፡፡
 

መጋቢት 17
March 26
 

እርካታ

 



“ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና” (ፊልጵ. 4፡11 /1962 ትርጉም/)፡፡ በምንገኝበት የትኛውም ሁኔታ መርካት ከቻልን የእርካታችን ምንጩ ምን ሊሆን ይገባል?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


ይገልጻል (1ጢሞቴ. 6፡5)፡፡ ዛሬ በአገልግሎት ስም በየቴሌቪዥን ጣቢያው የሚነግዱትን ከዚህ የተሻለ ምን ሊገልጻቸው ይችላል? የጣቢያ ታዳሚዎቻቸው በገንዘባቸው ታማኝ ከሆኑ (ታማኝነታቸው የእነርሱን አገልግሎት በገንዘባቸው መደገፍን ያካትታል) እነርሱም ሀብታም ይሆናሉ… ማለት ነው? ሀብትን ከታማኝነት ጋር ማመጣጠን በክርስትና ጭምብል ሥር የሚገኝ ሌላው የቁሳዊነት መገለጫ ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ እውነተኛ መንፈሳዊነትን ከሀብት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ እንዲያማ ቢሆን አንዳንድ የምድራችን አጸያፊዎች በሀብታቸው ብዛት ከመንፈሳዊዎች ተርታ በተመደቡ ነበር፡፡ በዚህ ፋንታ ጳውሎስ “እውነተኛ መንፈሳዊነት ባለን ነገር ከመርካት ጋር ትልቅ ትርፍ ነው” (1ጢሞቴ. 6፡6) ይለናል፡፡ የእግዚአብሔር ጸጋ በገንዘብ ከሚገኝ ማንኛውም ትርፍ ባሻገር የከበረ ዋጋ ያለው እንደ መሆኑ፤ በማናቸውም ሁናቴ በደስታ የተሞላ መንፈሳዊነት ከሁሉ የላቀ ባለጸግነት ነው፡፡ ስለዚህ “ምግብና ልብስ ካለን” (1ጢሞቴ. 6፡8) ደስተኞች ልንሆን ይገባል፡፡ በመጨረሻ የቱንም ያህል ኖሮን ነገር ግን ዝንባሌአችን የበለጠ ለማግኘት ከሆነ ባለን ነገር ልንረካ አንችልም፡፡
“ባለን ነገር መርካትና ደስ መሰኘት መንፈሳዊ ምስጢርን የያዘ ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ ይህ በጥልቅ ሊጠናና ሊማሩት የሚገባ ሽሽግ ነገር ነው. . . ጣፋጭ፣ ውስጣዊ፣ የተረጋጋና በደርባባ መንፈስ የታቀፈው ክርስቲያናዊው እርካታ፤ በማናቸውም ሁናቴ ራሱን በነፃ የሚያስገዛና በአምላካዊው ጥበብና አባትነት ሐሴት የሚያደርግ ነው፡፡. . . በአስቸጋሪ ጊዜያቶችና ሁናቴዎች ወቅት የተናወጡ ልቦችን በእጅጉ የሚያጽናና ጠቃሚ የከበረ ቅባት የያዘ ሣጥን ነው፡፡”—Jeremiah Burroughs, The Rare Jewel of Christian Contentment, pp. 1, 3.


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 8:28፣ ዕብ. 13:5፣ ፊልጵ. 4:4–13፡፡ በእርካታ የተሞላን ሰዎች ሆነን እንድንኖር ሊረዱን የሚችሉ ምን ዓይነት ነጥቦች እናገኛለን?


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

 

መጋቢት 18
March 27
 

መታመን

 



ጥቅሱን ያንብቡ፡ ምሳ. 3፡5፡፡ ምን ዓይነት ወሳኝ መልእክት ተላልፎልናል? በተለይ በመጨረሻው ክፍል በራሳችን ማስተዋል መደገፍ እንደሌለብን የሚያነሳው ነጥብስ? (ኢሳ. 55፡9፣ 1ቆሮ. 4፡5፣ 13፡12፡፡)


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------


የእግዚአብሔር መጋቢዎች መርኅና ዓላማ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ” (ምሳ. 3፡5) የሚል ነው፡፡ እርግጥ ነው ይህን መናገሩ እንጂ ማድረጉ ብዙውን ጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር ለእኛ ባለው ፍቅሩና ጥንቃቄው እናምናለን እያልን አስቸጋሪ ነገር በገጠመን ቁጥር በተደጋጋሚ ራሳችንን ጭንቀት ውስጥ የማንከት ስንቶቻችን ነን? አንዳንዴ በገዛ ራሳችን ምናብ የወደፊቱን አስፈሪ አድርገን እንስላለን፡፡


ታዲያ እኛ እንደ መጋቢ በእግዚአብሔር መታመን የምንማረው እንዴት ነው? ይህን የምናደርገው በእምነት ወጥተን በምናደርገው ነገር ሁሉ ጌታን በመታዘዝ ነው፡፡ መተማመን ወይም እምነት መጣል የአእምሮ ውጤት እንደ መሆኑ፤ አእምሮ ሁሉንም አሟጦ ጥቅም ላይ አያውልም፡፡ በተቃራኒው አብልጠን በጌታ በታመን ቁጥር በእርሱ ላይ ያለንም እምነት የዛኑ ያህል እያደገ ይሄዳል፡፡ እንደ ታማኝ መጋቢዎች መመላለሳችን ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት የምንገልጽበት መንገድ ነው፡፡ ይህ መታመን የመጋቢው መሰረትና አነሳሽ ኃይሉ እንደመሆኑ በሚሠራቸው ነገሮች ውስጥ በገሃድ ይታያል፡፡


“ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ ውደድ” (ማቴ. 22፡37) በሚለው ጥቅስ “ልብህ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ሁል ጊዜ በምሳሌያዊ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል እንመለከታለን፡፡ ይህም ውሳኔያችን የሚመጣው ማንነታችንን ከሚመሰክረው ውስጣዊው የግብረገብ እኛነታችን ነው የሚል አንደምታ አለው፡፡ ይህ ደግሞ ጸባያችንን፣ ተነሳሽነታችንንና አሳቢነታችንን ያካትታል፡፡


ከቁጥጥራችን ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ በእግዚአብሔር ላይ እምነት መጣል ወይም በእርሱ መታመን ቀላል ነው፡፡ ምክንያቱም በእርሱ ላይ እምነት ከመጣል ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ይልቁንም ሙሉ ለሙሉ “ከልብ” መታመን የሚመጣው በቁጥጥራችን ስር ባለ ነበር ላይ ምርጫ ሲኖረንና በእግዚአብሔር ላይ ያለን መታመን በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እንድንመርጥ መንስኤ ሲሆነን ነው፡፡


ሐዋርያት በሙሉ ልባቸው በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያሉ፡፡ “ዛሬ በሥራው ከተሰማሩ ወገኖች በተመሳሳይ ደካማና ረዳተ-ቢስ ተፈጥሮ የነበራቸው ቢሆንም፤ እነርሱ ግን ሙሉ መታመናቸውን በጌታ ላይ አደረጉ፡፡ እግዚአብሔርን በማንኛውም ነገር ምርጥ ጀማሪና ፈጻሚ አድርገው የሚመላለሱ ሁሉ የዚህ ባለቤት ይሆናሉ፡፡” —Ellen G. White, Gospel Workers, p. 25.


እንደ እውነቱ ከሆነ አንድ ሰው ከቁጥጥሩ ውጪ ለሆነው ነገር በእግዚአብሔር መታመን ይቀለው እንደሆን እንጂ አይከብደውም፡፡ ጉዳዩ በተገላቢጦሽ በእርስዎ ቁጥጥር ስር ቢሆንስ? በእግዚአብሔር ላይ ያለዎት መታመን በምርጫዎ ላይ ተጽእኖ እንዲኖረው ይፈቅዳሉ?
 

መጋቢት 19
March 28
 

ተጽእኖአችን

 



“ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ” (ኤፌ. 5፡8)፡፡ ጳውሎስ የልብን መለወጥ እንደ አደባባይ ትዕይንት ይገልጸዋል፡ “በብርሃን ብንመላለስ” (1ዮሐ. 1፡7፣ ኢሳ. 30፡21) በዕቅድ የሚመራውና ነጋ ጠባ በሌሎች የሚስተዋለው መጋቢነታችን በጨለማው ዓለም ላይ ተጽእኖ የሚያደርግ ብርሃን ይሆናል፡፡


የሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ሲል ተናግሯል (ዮሐ. 8፡12)፡፡ በየቀኑ ከሰዎች ጋር ባለን መስተጋብር በማይናወጥ ባህሪ የእግዚአብሔርን ብርሃን እናንጸባርቃለን፡፡


ለእግዚአብሔር ክብር የሚያመጣው መጋቢነታችን በሌሎች ያለው ዕይታ ምን ይመስላል? የድርጊቶቻችን ተጽእኖስ? ማቴ. 5:16፣ ቲቶ 2:7፣ 1ጴጥ. 2:11-12፡፡


--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------

መጋቢነት የእግዚአብሔርን ንብረት ማስተዳደር ቢሆንም፤ ዐደራና ኃላፊነቱ ግን ከዚያም ባሻገር ነው፡፡ መጋቢነታችን በቤተሰባችን፣ በማኅበረሰባችን፣ በዓለማችን ብሎም በዩኒቨርስ ፊት የተገለጠ ነው (1ቆሮ. 4፡9)፡፡ በተግባር የሚታየው መጋቢነታችን፤ የሰማያዊው መንግሥት መርኅ በህይወታችን ላይ ያለውን ኃይል ገልጦ ያሳያል፡፡ በዚህም በሌሎች ላይ ተነሳሽነት መፍጠርና አርአያ መሆን እንችላለን፡፡ የአዳኙን ይሁንታ በያዘው ደግነትና መልካም ስብዕና ክርስቶስን ገልጠን እናሳያለን፡፡


እንዲሁም የሥራ ሥነ ምግባራችን ከመጋቢነት እሴቶቻችን ጋር ስምሙ ሊሆኑ የግድ ነው፡፡ ኃላፊነታችን የጻድቅ ሰው መጋቢነት የሚታይበት አንድ ደረጃ ነው፡፡ “ጽድቅህ እንደ ብርሃን፣ የአንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል” (መዝ. 27፡6)፡፡ መጋቢው በሥራ ቦታም ይሁን በሌላ ተጽእኖውን “በስውር ቦታ ወይም ከእንቅብ በታች” (ሉቃስ 11፡33) አይሸሽገውም፡፡ ይልቁንም በተራራ ላይ እንዳለች ከተማ በሰዎች ፊት ያበራዋል (ማቴ. 5፡14)፡፡ እንዲህ ያለውን ዓላማ መር ሕይወት ስንኖር በዙሪያችን ባሉ ወገኖች አእምሮና ልብ ተጽእኖአችንን እናሳድራለን፡፡


“እያንዳንዱ የተፈጥሮ አካል የተመደበበት ሥራ አለው፡፡ ኃላፊነቱንም ያለማጉረምረም ያከናውናል፡፡ ከመንፈሳዊ ነገሮች አኳያ እያንዳንዱ ወንድ ወይም እያንዳንዷ ሴት ግላዊ የሥራ ፍላጎት መስክና ኃላፊነት አለው/አላት፡፡ እግዚአብሔር የሚጠይቀው ፍላጎት በክርስቶስ ከተሰጠው ስጦታ ልኬት ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡… የከበረ ዋጋ ያለውን--የባህሪ ጽናት የተላበሰ ስብዕና የሚያሳዩበት የእርስዎ ጊዜና ልዩ መብት እነሆ አሁን ነው፡፡” —Ellen G. White, This Day With God, p. 243.


የሥራ ሥነ-ምግባርዎ አብረዋቸው በሚሠሩ ወይም በሚኖሩ ፊት ምን ዓይነት ተጽእኖ አለው? ስለ እምነትዎ የሚያስተላልፉላቸው መልእክት ምን ዓይነት ነው?


 

መጋቢት 20
March 29

ልንሰማ የምንፈልጋቸው (እና የማንፈልጋቸው) ቃላቶች

 



እኛ ፍጹም፣ ውብና ሰላማዊ የሆነው ሰማይ የመጨረሻ ግባችን የሆነ፣ የምድር መጻተኞችና ተጓዥ መንገደኞች ነን (ዕብ. 11፡13-14)፡፡ ሆኖም እስከ ጊዜው ድረስ ህልውናችን በዚህ ምድር ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከእግዚብሔር ወይም ከሰይጣን ጎራ ከመሰለፍ ውጪ መሃል ሰፋሪ የሚባል ነገር እንደሌለ--በተለይ የታላቁ ተጋድሎ የክርስትና ዓለም አቀፋዊ ገጽታ ይፋ ያደርግልናል፡፡ “‘ከእኔ ጋር ያልሆነ ሁሉ ይቃወመኛል፤ ከእኔም ጋር የማይሰበስብ ይበትናል’ ” (ማቴ. 12፡30)፡፡

ክርስቶስ ዳግም ከተገለጠ በኋላ እርሱን ተከትለናል የሚሉ ወገኖች ከነዚያ ሁለት ሐረጎች አንዱን ይሰማሉ፡፡ እነዚህ ሐረጎች ምንድን ናቸው? የእያንዳንዳቸውስ ፍቺ ምንድን ነው?


ማቴ. 25:21_____________________________________________________________________________
ማቴ. 7:23_____________________________________________________________________________


“‘ደግ አድርገሃል’” በሚል በክርስቶስ የሚነገሩት ቃላት መጋቢው ለመስማት የሚመኛቸው አስደሳችና አርኪ አባባሎች ናቸው፡፡ ብቃት በጎደለው ሰብዓዊ ማንነታችን--እንደ ችሎታችን መጠን መለኮታዊውን ሀብትና ንብረት የምናስተዳድርበት አምላካዊ ፈቃድ በማግኘታችን በቃላት ሊገለጽ የማይችል ደስታ ያጎናጽፈናል፡፡ የደኅንነታችን ሥረ መሰረት እኛ ለክርስቶስ የምንሠራው ሳይሆን እርሱ ለእኛ የሠራልን የመሆኑን እውነታ ጠንቅቀን እንገነዘባለን (ሮሜ 3፡21፣ 4፡6)፡፡

የታማኝ መጋቢ ህይወት የግለሰቡ ተጨባጭ እምነት ነጸብራቅ ነው፡፡ አንዳንዶች ራሳቸውን በእግዚብሔር ፊት ጻድቅ አድረገው ለማቅረብ የተመኙበት--የጽድቅ በሥራ አካሄድ ግለሰቦቹ በተናገሯቸው ቃላት መታየት ችሎ ነበር (ማቴ. 7፡21-22)፡፡ ማቴ. 7፡23--ራስን ስለማመጻደቅ ከንቱነት በትክክል ያሳየናል፡፡
“የክርስቶስ ተከታዮች የጌታ የሆነውን መልሰው ለእርሱ ሲሰጡ ‘ደግ አድርገሃል አንተ መልካም ታማኝ አገልጋይ፤…ወደ ጌታ ደስታ ግባ’ የተሰኙትን ቃላት በመስማት የሚሰጣቸውን ገጸ በረከት ከወዲሁ ያከማቻሉ፡፡’ ” —Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 523.


በመጨረሻም፤ መጋቢነት የሰበበ ድርጊትና የትጉ ሥራ መንፈስ ኃይል የሆኑትን--እግዚአብሔርን ውደድ እና ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ--ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት በህይወት መኖር ነው፡፡


የገዛ ሕይወትዎ እና በመጋቢነት የተገለጠው ሕይወትዎ እነዚህን ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት ምን ያህል በሚገባ አንጸባርቀዋል?

 

መጋቢት 21
March 30
 

ተጨማሪ ሀሳብ፡-

 


 “ክርስቶስ ወደዚህ ምድር የመጣው የእግዚአብሔርን ፍቅር ለመግለጽ ነው፡፡ ተከታዮቹ እርሱ የጀመረውን ሥራ መቀጠል አለባቸው፡፡ አንዱ ሌላውን በመደገፍና በማበረታታት ጥረት እናድርግ፡፡ ለሌሎች መልካም መሻት እውነተኛ ደስታ የምናገኝበት መንገድ ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርንና ባልንጀራውን የሚወድ ከሆነ ወደ ገዛ ጥቅሙ አያዘነብልም፡፡ መንፈሱ ከራስ ወዳድነት በራቀ ቁጥር ይበልጥ ደስተኛ ይሆናል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ እግዚአብሔር ለእርሱ ያለው ዓላማ ጠልቆ ስለሚሰማው ነው፡፡”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship, pp. 24, 25.


“በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሕይወት ባለ ቁጥር--መብዛትና ማደግ አለ፡፡ የራሱ የጌታ የሆነውን የመቀበልና የመስጠት፣ የመቀበልና የመመለስ ቋሚ መለዋወጥ አለ፡፡ እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ አማኝ ብርሃንና በረከት ይሰጣል፡፡ አማኙ ደግሞ ለጌታ በሚሠራው ሥራ ለሌሎች በልግስና የመመለስ ተግባር ይፈጽማል፡፡ ከሚቀበለው ላይ ሲሰጥ የመቀበል አቅሙ ይጎለብታል፡፡ ለትኩሱ ጸጋ እና እውነት አቅርቦት ስፍራ ይዘጋጃል፡፡ ግልጽነት የተላበሰ ብርሃንና መጠኑ የጨመረ ዕውቀት የእርሱ--የግለሰቡ ይሆናሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ዕድገት በዚህ መስጠትና መቀበል ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የሚቀበል ግን የማይሰጥ--ውሎ አድሮ መቀበል ያቆማል፡፡ እውነት ከእርሱ ወደ ሌሎች መፍሰስ ካልቻለ የመቀበል አቅሙን ያጣል፡፡ ትኩስና ለምለም የሆነውን በረከት የምንቀበል ከሆነ፤ ይህን ሰማያዊ ገጸ በረከት ማካፈላችን የግድ የሆናል፡፡”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 36.

 

የመወያያ ጥያቄዎች:-፡

 

  1. በጌታ መታመን ወደ እርካታ የሚመራን እንዴት ነው? በሙሉ ልብዎና ዕውቀትዎ በእግዚአብሔር ወደ መታመን የሚመራዎ እንዴት ነው? 2ቆሮ. 10፡5፡፡ “ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ” (ሮሜ 8፡28) ለማለት የሚቀለው--ለማመን ግን የሚከብደው ለምንድን ነው? ማለትም በእግዚአብሔር እንታመናለን የሚለው የዕውቀት ደረጃ ስለ ወደፊቱ ሲያስብ በፍርሃት የሚዋጠው ለምንድን ነው?
  2. የሚከተሉትን ጥያቄዎች የሰንበት ትምህርት ጥናት አባላትን ይጠይቁና መልሶቹን ያስተያዩ፡፡ “መጋቢነትን በ25 ቃላት ወይም ባነሰ ያብራሩ፡፡” “መጋቢነት የክርስትና ህይወት አስፈላጊ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው?”
  3. ጥቅሱን ደግመው ያንብቡ፡ ማቴ. 7፡21-23፡፡ ምን እየሆነ ነው ያለው? እነዚህ ሰዎች ስላደረጓቸው ነገሮች የሚያወሩት ለምንድን ነው? ንግግራቸው ስለ ራሳቸው ምን ይጠቁማል? መልካም መጋቢዎች ለመሆን ባለን ብርቱ ፍላጎት፣ የእምነትና የመታዘዝ ሕይወት ለመኖር በምናደርገው ጥረት፣ በእግዚአብሔር ስም መልካም ነገሮችን ለማድረግ በምናደርገው ያላሰለሰ ሙከራ ተመሳሳይ ራስ ማታለል ውስጥ ላለመውደቃችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
  4. ስለ ክርስትና ተጽእኖ ስናስብ ቀድሞ ወደ አእምሮአችን የሚመጣው ግላዊው ምሳሌነት ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ ደረጃ መደረግ የሚችለው ተጽእኖስ? በአጠቃላይ ቤተ ክርስቲያንዎ በማኅበረሰብዎ ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ አላት?