ሰንበት ከሰዓት
ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡-- ሕዝ. 28:1-2፣ 11 –17፣ ዘፍ. 3:1–7፣ ራእ. 12:1–17፣ ሮሜ 8:31–39፣ ራእ. 14:12፡፡
የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቆጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው፡፡”
ዓለም ከመጽሐፍ ቅዱስ ምልከታ ስትቃኝ በታላቅና ጽኑ ውዝግብ መሃል
ትገኛለች፡፡ ኃጢአት፣ ሥቃይ፣ ሞት፣ የመንግሥታት መነሳትና
መውደቅ፣ የወንጌል መሰራጨት፣ የመጨረሻው ዘመን ክስተቶች--
እነዚህ ሁሉ ከዩኒቨርስ አቀፍ ተቃርኖ ዐውድ ገቢራዊ በመሆን ላይ ይገኛሉ፡፡
ነገር ከሥሩ፤ ውሃ ከጥሩ--እንደሚባለው ተቃርኖው የጀመረባቸውን ወሳኝ
ስፍራዎች በዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን እንመለከታለን፡፡ እነሆ ዐመጻ
ፍጹም ሆኖ በተፈጠረው ሉሲፈር ልብ በስውር ተጠነሰሰ፡፡ እርሱም ይህንኑ ዐመጻ
ወደ ምድር ይዞ በመውረድ ፍጹም ወደ ነበሩት አዳምና ሔዋን አስተላለፈ፡፡
በእነዚህ ሁለት አበይት መነሾዎች፤ ማለትም በሉሲፈር እና በመጀመሪያዎቹ
ወላጆቻችን ውድቀት መንስኤ ታላቁ ውዝግብ ስር መስደድ ጀመረና ይኸው እስከ
ዛሬ ቁጣና መአት መሃል እንገኛለን፡፡ እኛ እያንዳንዳችን የዚያ ዩኒቨርስ አቀፍ
ተውኔት አካል ነን፡፡
አንድ ቀን ይህ ምድራዊ ሰቆቃ ማክተም ብቻ ሳይሆን ሰይጣን ሙሉ ለሙሉ
በክርስቶስ ድል ተመትቶ ውዝግቡ በድል መጠናቀቁ መልካም የምስራች ሲሆን፤
የሱስ በመስቀል ላይ የሠራውን ፍጹምና የተሟላ የጽድቅ ሥራ ተከትሎ ሁላችንም
የድሉ ተጋሪዎች መሆናችን ደግሞ ከሁሉ የላቀው የምስራች ነው፡፡ በየሱስ
የተሰጠንን ተስፋ በልባችን ሰንቀን ምጽአቱ የተረጋገጠውን ጌታ እየተጠባበቅን፤
እንደ አንድ የድሉ አካል በእርሱ ላይ እምነት እንዲኖረንና እንድንታዘዘው
እግዚአብሔር ጥሪ ያደርግልናል፡፡
አጽናፈ ሰማይን (ዩኒቨርስን) ያማከለው ውዝግብ የመጽሐፍ ቅዱስን
ዓለማቀፋዊ ገጽታ ታሪካዊ ዳራ ቅርጽ የሚሰጠን ከሆነ--ጉዳዩ ወደ ብዙ ጥያቄዎች
ይመራናል፡፡ ከእነዚህም አንዱና ዋንኛው ይህ ሁሉ እንዴት ተጀመረ? የሚለው
ይሆናል፡፡ መጀመሪያ አፍቃሪው አምላክ የፈጠረው ፍጹም የሆነውን አጽናፈ ሰማይ
እንደመሆኑ ክፋት፣ አመጻ፣ ግፍ እና ቅራኔ የፍጥረት ሥራው አካል አልነበሩም፡፡
ስለዚህ ውዝግቡ የተከሰተው ከቀደመው የፍጥረት ሥራው ተነጥሎ፣ ኋላ ላይ
እንደመሆኑ የእጆቹ ሥራ ውጤት ተደርጎ መቆጠር አይችልም፡፡ የሆነው ሆኖ በዚህ
ምድር እየተስተዋለ ያለው ውዝግብ ተጨባጭና ሁላችንንም ያካተተ ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ሕዝ. 28:1-2፣ 11–17፣ ኢሳ. 14:12–14፡፡ ስለ ሉሲፈር
ውድቀትና ስለ ክፋት መነሳት ምን ያስተምሩናል?
ሉሲፈር በሰማይ የሚኖር ፍጹም ፍጡር ነበር፡፡ በተለይ በእንደዚያ ዓይነት ፍጹም
ስፍራ እየተመላለሰ ክፋት እንዴት ከእርሱ ተነሳ? በእርግጥ ስለዚህ ጉዳይ
የምናውቀው ነገር የለም፡፡ እንደውም፣ ምናልባት መጽሐፍ ቅዱስ “የዐመፅ
ምስጢር” (2ተሰ. 2፡7) ብሎ የሚጠራው ለዚህ ይሆን?
እግዚአብሔር የማሰብ ችሎታ ላላቸው ሁሉም ፍጥረቶቹ ከሰጠው ተጨባጭ
የመምረጥ ነጻነት ውጪ ለሉሲፈር ውድቀት እንደ መንስኤ የሚቆጠር አንድም
ምክንያት የለም፡፡ “ኃጢአት እንዴት እንደተጠነሰሰ ለመግለጽ ለአብሮነቱ ምክንያት
የመስጠትን ያህል አዳጋች ነው… ኃጢአት ሰርጎ ገብ እንደመሆኑ ለአብሮነቱ አንዳች
ምክንያት መስጠት አይቻልም፡፡ ኃጢአት ምስጢራዊና ከተጠያቂነት አፈንጋጭ
ባህሪ ያለው እንደመሆኑ ለእርሱ ሰበብ መስጠት--ለራሱ ለኃጢአት ዘብ እንደመቆም
ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ለኃጢአት ሰበብ ሲቀርብ ወይም ለመከሰቱ ምክንያት ሲቀመጥ
--ኃጢአት እንደ ኃጢአትነት መታየቱ ይቀራል፡፡”—The Great Controversy,
pp. 492, 493.
ኃጢአት የተሰኘውን ቃል ክፉ በሚለው ብንተካው ከላይ የተመለከትነው
የሀሳብ ፍቺ አይፋለስም፡፡ ክፋት እንዴት እንደተጠነሰሰ ለመግለጽ ለአብሮነቱ
ምክንያት የመስጠትን ያህል አዳጋች ነው… ክፉው ሰርጎ ገብ እንደመሆኑ ለአብሮነቱ
አንዳች ምክንያት መስጠት አይቻልም፡፡ ክፉው ምስጢራዊና ከተጠያቂነት
አፈንጋጭ ባህሪ ያለው እንደመሆኑ ለእርሱ ሰበብ መስጠት--ለራሱ ክፉው ዘብ
እንደመቆም ይቆጠራል፡፡ ስለዚህ ለክፉው ሰበብ ሲቀርብ ወይም ለመከሰቱ
ምክንያት ሲቀመጥ--ክፉው እንደ ክፉነቱ መታየቱ ይቀራል፡፡
የግል ተሞክሮዎን ከተጨባጩ የመምረጥ ነጻነትዎ አኳያ አሰብ ያድርጉ፡፡
የተሰጠንን ነፃ የመምረጥ ችሎታ በጸሎትና በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ማዋል ያለብን
ለምንድን ነው?
ምንም እንኳ ክፉው ለምን እንደተከሰተ ማብራራት ባንችልም (ለህልዎቱ ተገቢ
ምክንያት እስከሌለ ድረስ) ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በሰማይ በሉሲፈር ልብ ውስጥ
መጠንሰሱን ይፋ ያደርግልናል፡፡ ከኤለን ጂ. ኋይት ሥራዎች ከምናገኛቸው
አስገራሚ ተጨማሪ ብርሃኖች (ለምሳሌ በ “ታላቁ ተጋድሎ” መጽሐፍ “የክፉው
አጀማመር” በሚል የቀረበው ምዕራፍ) ውጪ መጽሐፍ ቅዱስ ኃጢአት በሰማይ
እንዴት እንደተጠነሰሰ እምብዛም ሲነግረን አይስተዋልም፡፡ ሆኖም የምድር አነሳሱን
አስመልክቶ ግን የእግዚአብሔር ቃል ይበልጥ ግልጽ መልእክት ይሰጠናል፡፡
ጥቅሱን ያንብቡ፡--ዘፍ. 3፡1-7፡፡ ወደ ብርሃን ሲመጣ፤ አዳምና ሔዋንን ተወቃሽ
አድርጎ ያሳየ ምን ነገር ተከሰተ?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ሔዋን እግዚአብሔር የነገራቸውን በሚገባ የምታወቅ መሆኗ ጉዳዩን በእጅጉ
አሳዛኝ ያደርገዋል፡፡ እንደውም የተነገሯቸውን እነዚያኑ ቃላት ደግማ እንደ ተናገረች
እንመለከታለን “ነገር ግን እግዚአብሔር ‘በአትክልቱ ስፍራ መካከል ከሚገኘው ዛፍ
ፍሬ እንዳትበሉ፤ እንዳትነኩትም፤ አለበለዚያ ትሞታላችሁ’ ብሎአል” (ዘፍ. 3፡3)፡፡
ከጥቅሱ እንደምንመለከተው ከፍሬው መብላት ሞት ሊያስከትል እንደሚችል
በሚገባ ታውቅ ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ሰይጣን እግዚአብሔር የተናገራቸውን ቃላት በግልጽ እና በጉልህ
ተቃረነ “እባቡም ሴቲቱን እንዲህ አላት ‘መሞት እንኳ አትሞቱም’” (ዘፍ. 3፡4)፡፡
ምን ያህል የተራራቀ ንጽጽር ነው? ሰይጣን ጮሌ የሆነውን አቀራረብ
የተጠቀመው መጀመሪያ ላይ ነበር፡፡ ሆኖም አንዴ ትኩረቷን ካገኘ በኋላ ግን
እንደማትቋቋመው በመመልከቱ የጌታን ትእዛዝ በግልጽ ጥሶ ለማቅረብ ደፈረ፡፡
ሔዋን ዕውቀት እያላት ይህ መከሰቱ ጉዳዩን ልብ የሚሰብር ያደርገዋል፡፡ እንግዲህ
“አላወቅኩም ነበር” አትል ነገር--በሚገባ ታውቅ ነበር፡፡
ሔዋን ይህ ዕውቀት እየነበራት የሆነው ሆነና እርሷ ግን ተሳሳተች፡፡ ፍጹም
ድባብ ሰፍኖበት በነበረው ኤደን ዕውቀት በራሱ ሔዋን (እውነትን ያውቅ የነበረውን
አዳም ጨምሮ) ኃጢአት እንዳትሠራ ለመጠበቅ በቂ አልነበረም፡፡ እኛም ብንሆን
እውነትን ማወቃችን ወይም በእውነት ላይ ያለን ዕውቀት ብቻውን ዛሬ እኛን
ለማዳን በቂ ነው ብለን በማሰብ ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡ በእርግጥ
የእግዚአብሔር ቃል የሚነግረንን ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ነገር ግን ቃሉን ከማወቃችን
በተጨማሪ የሚነግረንን ለመታዘዝ ራሳችንን ለእርሱ ማስገዛት ይጠበቅብናል፡፡
እግዚአብሔር አንድ ነገር ሲናገር ሰይጣን ደግሞ ሌላ ነገር ተናገረ፡፡ አዳምና
ሔዋን የአምላካዊው ቃል ዕውቀት የነበራቸው ቢሆንም ነገር ግን ምርጫቸው
ሰይጣንን ማድመጥ ሆነ፡፡ ባለፉት ሺህ ዓመታት ምን ያህል አነስተኛ ለውጦች
እንደተስተዋሉ ያስቡ፡፡ እኛም ተመሳሳይ ስህተት ላለመሥራት ምን ማድረግ
እንችላለን?
በመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ላይ የደረሰው ውድቀት ይህችን ዓለም በኃጢአት፣
በክፉው እና በሞት ጥላ ስር እንድትወድቅ አደረጋት፡፡ ምናልባት ውድቀትን
ተከትሎ በተከሰተው ሁኔታ ወይም የማን ስህተት በመሆኑ ዙሪያ አንዳንዶች
ላይስማሙ ቢችሉም ነገር ግን ዙሪያችንን እያወከ ያለውን አመጻ፣ ብጥብጥና
ውዝግብ ማን ሊክድ ይችላል?
በአጽናፈ ሰማይ ስለተነሳው ተቃርኖ መነጋገራችን መልካም ነው፤ እውነትም
ነው፡፡ ነገር ግን የግጭቱ መንስኤ ምንም ይሁን ምን በዚህም ምድር እየተካሄደ
ነው፡፡ በእርግጥ ከዔድን ውድቀት አንስቶ እስከ መጨረሻዎቹ ክስተቶች ብሎም
የየሱስ የዳግም ምጽአት ያለው አብዛኛው ግዙፉ የተቃርኖ ታሪክ የመጽሐፍ ቅዱስ
አካል ነው፡፡ እኛም የምንኖረው በዚህ ተቃርኖ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ
እንቅስቃሴ ጀርባ ስላለው ነገር የእግዚአብሔር ቃል ማብራሪያ ይሰጠናል፡፡ ከሁሉ
በላይ ደግሞ እንዴት ወደ ፍጻሜ እንደሚመጣ ይፋ ያደርግልናል፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ራእ. 12፡ 1-17፡፡ ምዕራፉ በሰማይና በምድር ስለ ተከሰቱት ምን
ዓይነት ጦርነቶች እየነገረን ነው?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
በሰማይ የተካሄደውን ጦርነት እና ምድራዊዎቹን ጦርነቶች በጥቅሱ
እንመለከታለን፡፡ የመጀመሪያው ጦርነት የተደረገው በዘንዶው (ሰይጣን፣ ራእ. 12፡7
-9) እና በሚካኤል (የዕብራይስጥ ትርጉሙ፡ “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማን ነው?”)
መካከል ነበር፡፡ ሰይጣን (ጠላት፣ ባለጋራ) በሚል ስያሜ መታወቅ የጀመረው
አመጸኛው ሉሲፈር--ዘላለማዊ ፈጣሪ የሆነውን የሱስ የሚዋጋ ፍጡር ሆነ (ዕብ. 1፡1
-2፣ ዮሐ. 1፡1-4)፡፡
ሉሲፈር በፈጣሪው ላይ እያመጸ ነበር፡፡ ታላቁ ተቃርኖ በአማልክት መካከል
የተፈጠረ የከረረ ጸብ ሳይሆን በፈጣሪው ላይ ያመጸው ፍጡር ዐመጹን ፍጥረታትን
በማጥቃት ጭምር እያሳየ ያለበት ትዕይንት ነው፡፡
ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ባደረገው ግጥሚያ ሽንፈት የቀመሰው ሰይጣን፤ የሱስ
ሰብዓዊውን ሥጋ ለብሶ ወደዚህ ምድር ሲመጣ ሊያጠቃው ተመኝቶ ነበር (ራእ.
12፡4)፡፡ አሁንም በክርስቶስ ውልደት ወቅት የውጊያ እቅዱ የከሸፈበት ሰይጣን፤
የሱስ በጾም በደከመበት በምድረበዳ፣ ኋላም በቀራኒዮ መስቀል ላይ ጽኑና
የማይቀለበስ የሽንፈት ጽዋ ለመጎንጨት ተገደደ፡፡ ሰይጣን ከዚህ በኋላ በክርስቶስ
ሕዝቦች ላይ ብርቱ ጦርነት ከፈተ፡፡ ይህ አብዛኛውን የክርስትና ታሪክ የሚሸፍነው
ቁጣና መአት (ራእ. 12፡6፣ 14-16) እስከ ምድር ፍጻሜ የሚቀጥል ሲሆን (ራእ.
12፡17) ይኸውም በየሱስ ዳግም ምጽአት ሌላ ሽንፈት እስኪቀምስ ነው፡፡
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡--ራእ. 12፡10-12፡፡ በሌሎቹ ጥቅሶች ከተመለከትናቸው
ውዝግቦችና ተቃርኖዎች አኳያ በእነዚህ ጥቅሶች የምናገኘው ተስፋ ምን ይመስላል?
የራእይ መጽሐፍ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በዘመናት የሚደርስባቸውን ስደት
በየአብያተ ክርስቲያናቱ ታሪክ ጥሩ አድርጎ በመከፋፈል በትንቢት አስቀምጧል፡፡
በራእ. 12፡6 የምናገኘው 1260 ትንቢታዊ ቀናት (በተጨማሪ ራእ. 12፡14
ይመልከቱ) በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን 1260 ዓመታት የፈጀ የስደት ዘመን
ያመለክታል፡፡
“እነዚህ ሐዋርያው ጳውሎስ ሰማዕት በሆነባቸው፣ በንጉሠ ነገሥት ኔሮ የግዛት
ዘመን የጀመሩት የስደትና የመዐት ዘመናት አንዴ እየጋሙ ሌላ ጊዜ ደግሞ
እየቀዘቀዙ ለአያሌ መቶ ዓመታት ቀጥለው ነበር፡፡ ክርስቲያኖች እጅግ አስከፊ
ጥፋት የፈጸሙ ይመስል በሐሰት ተወነጀሉ፡፡ በምድር ላይ ለሚደርስ መቅሰፍት፣
ረሃብ፣ ቸነፈርና መሬት መንቀጥቀጥ እንደ ምክንያት ተቆጠሩ፡፡ ሁሉም በጥላቻና
በጥርጣሬ ዐይን የሚመለከታቸው መሆናቸውን ተከትሎ ወሬ አቀባዮች
ለጥቅማቸው ሲሉ ንጹሃኑን ለመካድ ዝግጁ ነበሩ፡፡ እንደ ሥርዓቱ አማጺ
ተቆጥረው ተኮነኑ፣ በኃይማኖት ጠላትነት ተፈረጁ፣ በማኅበረሰቡ ላይ መዐት
እንደሚያወርዱ ተምቾች ታዩ፡፡ እንደ ዛሬው ስታዲየም ክብ ሆነው በተገነቡ
ትዕይነት ማሳያዎች ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ክርስቲያኖች ለተራቡ አውሬዎች
ተወረወሩ፣ በቁማቸውም ተቃጠሉ፡፡”—The Great Controversy, p. 40.
በዚሁ ጊዜ ሴቲቱ (ቤተ ክርስቲያን) ወደ ምድረ በዳ ሸሸች (ራእ. 12፡6)፡፡
ሴቲቱ ሁለት ክንፎች እንዳሉት ንስር ሆና ተጠቅሳለች፡፡ ይህ ደግሞ እርዳታ ልታገኝ
ወደምትችልበት ስፍራ በርራ መሄድ የመቻሏ ተምሳሌት ነው፡፡ ሴቲቱ በምድረ በዳ
እንክብካቤ እየተደረገላት ስለነበር እባቡ ወይም ሰይጣን ሊደርስባት አልቻለም
(ራእ. 12፡14)፡፡ ብርቱ ስደት በተከሰተ ጊዜ እግዚአብሔር ሁሌም ትሩፋኑን
ታድጓል፡፡ ደግሞም እስከ መጨረሻው ይህን ያደርጋል፡፡
ክርስቶስ በመጨረሻዎቹ ዘመናት ገቢራዊ በሚሆኑት በአደጋ የተሞሉ ሁናቴዎች
ዐውድ ለሕዝቡ እንዲህ ብሎአል “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ
ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡20)፡፡ ከፍተኛ ቁጥር የነበራቸው ተከታዮቹ ሰማዕት
ከሆኑበት ክስተት አኳያ ይህን ግሩም ተስፋ የምናስተውለው እንዴት ነው? (ሮሜ.
8:31–39፣ ማቴ. 10:28.)፡፡
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
ስደት፣ ረሃብ ወይም ሞት እንኳ ቢሆን ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም፡፡
ክርስቶስ አብሮን በመሆኑ አሁንም ሆነ በመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ህመም፣ ሥቃይ፣
መከራ አልፎ ተርፎም ሞት አይደርስብንም ማለት አይደለም፡፡ በዚህኛው ሕይወት
ከእነዚህ ነገሮች ነፃ ናችሁ የሚል ተስፋ አልተሰጠንም፡፡ ይኸውም በየሱስ እና እርሱ
ለእኛ ባደረገልን ነገር እየተማመን፤ በመከራ ወቅት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንዳለ
የተሰጠንን የተስፋ ቃል እያስታወስን በአዲስ ሰማይና ምድር ተስፋ መኖር
እንችላለን ማለት ነው፡፡ በዚህ ምድር በየትኛውም አስቸጋሪ ሁናቴ ውስጥ ብናልፍ
እርሱን ተስፋ በማድረግ እየተመላለስን እንደ ጳውሎስ እንዲህ ማለት እንችላለን፡
“ወደ ፊት የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል፤ ይህንም ጻድቅ ፈራጅ የሆነው ጌታ
በዚያ ቀን ለእኔ ይሰጠኛል፤ ደግሞም ለእኔ ብቻ ሳይሆን፣ የእርሱን መገለጥ ለናፈቁ
ሁሉ ነው” (2ጢሞቴ. 4፡8)፡፡ እኛ መገለጡን የምንናፍቅ ሁሉ ይህን ተስፋ የግላችን
ማድረግ እንችላለን፡፡
እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ስማችን አብልጦ የምናምንበትን ነገር
መሰረት ይዞአል፡፡ ሰባተኛ ቀን የሚለው የመጠሪያ ስማችን አካል፤ አንዱን ትእዛዝ
ይኸውም ሰባተኛውን ቀን ብቻ ሳይሆን አሥሩንም ትእዛዛት የመጠበቃችንን
አንደምታ ያሳያል፡፡ አድቬንቲስት የሚለው የስማችን ክፍል በየሱስ ዳግም ምጽአት
ላይ ያለንን እምነት ያመላክታል፡፡ የዚህ እውነት ብቸኛ ህልውና ክርስቶስ
በመጀመሪያው ምጽአቱ ለኃጢአት ሥርየት የከፈለው ዋጋ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ
ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት የተሰኘው ስያሜያችን ሁለት መሰረታዊና የማይለያዩ
ወቅታዊ እውነታዎችን ይዞአል፡ ሕግ እና ወንጌል፡፡
ሕግ እና ወንጌል ምን ያህል በቅርብ የተሳሰሩ መሆናቸውን እነዚህ ጥቅሶች እንዴት
ያሳዩናል?
ኤር. 44:23 ________________________________________________
ሮሜ 3:20–26___________________________________________
ሮሜ. 7:7_________________________________________________
ወንጌል የምስራች ነው፡፡ ምንም እንኳ ኃጢአተኞችና የእግዚአብሔርን ሕግ
የተላለፍን በደለኞች ብንሆንም፤ ክርስቶስ እዳችንን በመስቀል ላይ መክፈሉን
በእምነት መቀበላችንና ይቅርታ ማግኘታችን መልካም የምስራች ነው፡፡ ከዚህ
በተጨማሪ አምላካዊውን ሕግ ሙሉ ለሙሉ የምንታዘዝበትም ኃይል እንዲሁ
ተሰጥቶናል፡፡
የምድር ታሪክ በሚቋጭባቸው የመጨረሻዎቹ ጊዚያቶች በብርሃንና ጨለማ
መሃል ያለው ታላቁ ተቃርኖ በብርቱ ቁጣና መዐት በሚጦዝበት በዚያን ወቅት
የእግዚአብሔር ሕዝቦች በተለየ ዐውድ መቅረባቸው ብዙም ላይገርም ይችላል፡፡
በራእ. 14፡12 የምናገኘው ጥቅስ በሕግና በወንጌል መካከል ያለውን ግንኙነት
እንዴት ያሳየናል?
--------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------------
የእግዚአብሔርን ሕግ መታዘዝ እንዳለባቸውና ይህን እንደሚያምኑ ሰባተኛ ቀን
አድቬንቲስትነታችን--ሕጉን መታዘዝ ሕጋዊነት ሳይሆን እግዚአብሔርን
በመውደድና በእርሱ በመዳን የሚገኝ ተፈጥሮአዊ ውጤት መሆኑን ለሌሎች
ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እንደ ዘዳ. 11፡1 እና 1ዮሐ. 5፡3 ያሉት ጥቅሶች
ይህን ነጥብ በምን መልኩ ይደግፉታል?
ራእ. 12፡ 9-12፣ የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ከተሰኘው መጽሐፍ “ኃጢአት ለምን ተፈቀደ?” ከገጽ 22-34 ያንብቡ፡፡ “ሁሉም ፍጡራን የፍቅርን ታማኝነት እስከተረዱ ድረስ በእግዚአብሔር ዩኒቨርስ ላይ የተስተካከለ መጣጣም ነበር፡፡ የፈጣሪያቸውን ዓላማ ማሳካት የሰማይ መላዕክት ደስታ ነበር፡፡ ክብሩን በማንጸባረቅና ምስጋናውን በመስጠትም ሐሴት ያደርጉ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ፍቅር ከሁሉም በላይ ሲሆን የእርስ በእርስ ፍቅርም ጠንካራና በስስት ያልተሞላ ነበር፡፡ ሰማያዊውን ፍቅር የሚያጎድፍ ያለመግባባትም አልነበረም፡፡ ሆኖም በዚህ ደስታን በተመላ መንግሥት ውስጥ ለውጥ ተከሰተ፡፡ እግዚአብሔር ለፍጡራኑ የሰጠውን ነጻነት በተሳሳተ አቅጣጫ የተረጎመ አንድ ፍጡር ብቅ አለ፡፡ ከክርስቶስ ቀጥሎ እጅግ በተከበረውና በሰማይ ነዋሪዎች ዘንድ ከፍ ያለ ኃይልና ግርማ በተሰጠው ሉሲፈር ኃጢአት ተጠነሰሰ፡፡” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት ገጽ 24፡፡) ኤለን ኋይት “የፍቅርን ታማኝነት” በሚል የጠቀሰቻቸውን ቃላት ልብ ይበሉ፡፡ ይህ ጠንካራ ፍቺ የያዘ ብርቱ ሃረግ ፍቅር ወደ ታማኝነት የመምራቱን ሐቅ ያመላክታል፡፡ የትዳር ጓደኛውን የሚወድ ወይም የምትወድ ተጓዳኝ ፍቅሯን የምትገልጸው ታማኝ በመሆን ነው፡፡ ይህ በሰማይ ፍጡራን እንደሆነ እኛም በምድር ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ተመሳሳይ መርኅ የተከተለ ሊሆን ይገባል፡፡ የመወያያ ጥያቄዎች፡ 1.ሰይጣን በታላቁ ተቃርኖ ውስጥ ስላለው ሚና በተጨባጭ የሚያመላክት ምን ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ድጋፍ አለን? ክፉውን ነገር በሰይጣን ከመመሰል ባሻገር ሰይጣን በተጨባጭ መኖሩን ሰዎች ማስተዋል እንዲችሉ ልንረዳ የምንችለው እንዴት ነው? 2.እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አኳያ በከፍተኛ ዕውቀት ተባርከናል፡፡ ምንም እንኳ ይህ ዕውቀት እጅግ አስደናቂ ቢሆንም እኛን ለማዳን በቂ ያልሆነው ለምንድን ነው? ከአእምሮ ዕውቀት በላቀ ምን ያስፈልገናል? 3.ዛሬ የሱስ በሕይወትዎ መኖሩን የተለማመዱባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ማንኛውም ዓይነት አስቸጋሪ ሁናቴ ሲገጥምዎ እነዚህ ተሞክሮዎች እንዴት ሊረዱዎት ይችላሉ? 4.በሰንበት ትምህርት ጥናት ክፍለ ጊዜ “የፍቅርን ታማኝነት” በሚለው ሃረግ ላይ በደንብ ተነጋገሩ፡፡ ይህ ጽንሰ ሃሳብ በሕግ እና በጸጋ እንዲሁም በእምነትና በመታዘዝ መሃል ያለውን ግንኙነት በተሻለ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው? በአጠቃላዩ የፍቅር ጽንሰ ሃሳብ ተፈጥሮ ውስጥ ስላለው ነጻነት ምን ያስተምረናል? አሁንም እንኳ “የፍቅርን ታማኝነት” ልንገልጽ የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?